ጥር
ረቡዕ፣ ጥር 1
ሙሴ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ ነበር።—ዘኁ. 12:3
ሙሴ የግብፅ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ሳለ የዋህ አልነበረም። እንዲያውም በአንድ ወቅት በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ ኢፍትሐዊ ድርጊት እንደፈጸመ የተሰማውን ሰው ገድሎታል። ሙሴ፣ ይሖዋ ይህን ድርጊቱን እንደሚደግፍለት እርግጠኛ ሆኖ ነበር። ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ለመምራት ድፍረት ብቻ ሳይሆን የዋህነትም እንደሚያስፈልግ ለማስተማር ሙሴን ለ40 ዓመታት ያህል አሠልጥኖታል። የዋህ ለመሆን ደግሞ ሙሴ ትሑት፣ ታዛዥና ገር መሆንም ያስፈልገዋል። ሙሴ ከይሖዋ ያገኘውን ሥልጠና በሚገባ ስለተቀበለ ጥሩ መሪ ሊሆን ችሏል። (ዘፀ. 2:11, 12፤ ሥራ 7:21-30, 36) እናንት የቤተሰብ ራሶችና የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ የሙሴን ምሳሌ ተከተሉ። ሌሎች ለእናንተ አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነገር ሲያደርጉባችሁ በቀላሉ አትበሳጩ። ያሉባችሁን ድክመቶች በትሕትና አምናችሁ ተቀበሉ። (መክ. 7:9, 20) ችግሮችን ለመፍታት ይሖዋ የሰጣቸውን መመሪያዎች በታዛዥነት ተከተሉ። በተጨማሪም ምንጊዜም ገርነት በሚንጸባረቅበት ወይም በለዘበ መንገድ መልስ ስጡ። (ምሳሌ 15:1) እንዲህ የሚያደርጉ የቤተሰብ ራሶችና የበላይ ተመልካቾች ይሖዋን ደስ ያሰኛሉ፣ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋሉ እንዲሁም የዋህነት በማሳየት ረገድ ለሌሎች ግሩም ምሳሌ ይተዋሉ። w19.02 8 አን. 1፤ 10 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ጥር 2
በጣም አዘነላቸው።—ማር. 6:34
ኢየሱስ ለሕዝቡ ያዘነላቸው ወይም የራራላቸው ለምንድን ነው? ሕዝቡ ‘እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንደነበሩ’ አስተውሎ ነበር። ምናልባትም ኢየሱስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ድሆች እንደሆኑና ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ሲሉ አድካሚ ሥራ እንደሚሠሩ አስተውሎ ይሆናል። አንዳንዶቹ ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት አጥተው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መረዳት አይከብደውም። ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ በእሱም ላይ ሳይደርሱበት አይቀሩም። ኢየሱስ ለሌሎች ያስብ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እነሱን የሚያጽናና መልእክት መናገር ይፈልግ ነበር። (ኢሳ. 61:1, 2) ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? በኢየሱስ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በዘመናችንም በርካታ ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” ሆነዋል። ከተለያዩ ችግሮች ጋር ይታገላሉ። እኛ ደግሞ እነዚህ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማለትም የመንግሥቱን መልእክት ይዘናል። (ራእይ 14:6) በመሆኑም ‘ለችግረኛውና ለድሃው የሚያዝነውን’ የጌታችንን ምሳሌ በመከተል ምሥራቹን እንሰብክላቸዋለን። (መዝ. 72:13) ለሰዎች ስለምንራራ እነሱን ለመርዳት ስንል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። w19.03 21-22 አን. 6-7
ዓርብ፣ ጥር 3
ሸክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን . . . ይሖዋ ይወደስ።—መዝ. 68:19
ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉ። በየዕለቱ የምናገኛቸውን መልካም ነገሮች የሚሰጠን እሱ ከመሆኑም ሌላ ስለ ራሱና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን አስተምሮናል። (ዮሐ. 8:31, 32) መመሪያና ድጋፍ የምናገኝበትን የክርስቲያን ጉባኤ አዘጋጅቶልናል። በዛሬው ጊዜ ሸክማችንን የሚሸከምልን ሲሆን ወደፊት ደግሞ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቶናል። (ራእይ 21:3, 4) ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማሳየት ሲል እስካሁን ድረስ ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ስናሰላስል እሱን ለመውደድ እንገፋፋለን። እሱን ስንወደው ደግሞ ለእሱ ተገቢ የሆነ ፍርሃት እናዳብራለን። በጥልቅ የምንወደውን አካል እንዳናሳዝን እንፈራለን። የይሖዋን አመራር መከተልህ ምን ያህል እንደሚጠቅምህ እየተገነዘብክ ስትሄድ ለይሖዋም ሆነ እሱ ላወጣቸው መሥፈርቶች ያለህ ፍቅር ያድጋል። ይህም ሰይጣን በሚያቀርበው ማንኛውም ዓይነት ማታለያ እንዳትሸነፍና ይሖዋን ማገልገልህን እንዳታቆም ይረዳሃል። እስቲ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ሕይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ወደኋላ መለስ ብለህ ስታስብ በሕይወትህ ውስጥ ካደረግካቸው ውሳኔዎች ሁሉ የላቀው፣ ለመጠመቅ ያደረግከው ውሳኔ እንደሆነ መረዳትህ አይቀርም! w19.03 6 አን. 14፤ 7 አን. 19
ቅዳሜ፣ ጥር 4
ባለሙያ ሚስትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከዛጎል እጅግ ይበልጣል።—ምሳሌ 31:10
እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አድናቆቱን የሚገልጽ ከሆነ መላው ቤተሰብ ይጠቀማል። ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው አድናቆታቸውን የሚገልጹ ከሆነ ዝምድናቸው ይበልጥ ይጠናከራል። በተጨማሪም እርስ በርስ ይቅር መባባል ቀላል ይሆንላቸዋል። ለሚስቱ አድናቆት ያለው ባል፣ ሚስቱ የምትናገራቸውንና የምታደርጋቸውን መልካም ነገሮች አስተውሎ ዝም ከማለት ይልቅ “ተነስቶ ያወድሳታል።” (ምሳሌ 31:28) ጥበበኛ የሆነች ሚስት ደግሞ የምታደንቅለትን ነገሮች ለይታ በመጥቀስ ባሏን ታመሰግነዋለች። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ አድናቆታቸውን እንዲገልጹ ማሠልጠን የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆቻችሁ የምትናገሩትንና የምታደርጉትን ነገር እንደሚኮርጁ አትርሱ። በመሆኑም ልጆቻችሁ አንድ ነገር ሲያደርጉላችሁ በማመስገን ጥሩ ምሳሌ ተዉላቸው። በተጨማሪም ሰዎች የሆነ ነገር ሲያደርጉላቸው ‘አመሰግናለሁ’ እንዲሉ አስተምሯቸው። የሚያቀርቡት ምስጋና ከልብ የመነጨ መሆን እንዳለበትና የሚናገሯቸው የምስጋና ቃላት በሌሎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። w19.02 17 አን. 14-15
እሁድ፣ ጥር 5
እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!—ኢዮብ 27:5
እነዚህ ቃላት ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። ኢዮብ፣ ሰይጣን ላደረሰበት መከራ ፈጽሞ እጅ ላለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር፤ እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን። ሰይጣን በእያንዳንዳችን ላይ ተመሳሳይ ክስ ሰንዝሯል። ይህ ክስ አንተን በግለሰብ ደረጃ የሚነካህ እንዴት ነው? በተዘዋዋሪ መንገድ ሰይጣን ይሖዋ አምላክን ከልብ እንደማትወደው፣ ራስህን ለማዳን ስትል እሱን ማገልገልህን እንደምታቆምና በፈተናዎች ሥር ንጹሕ አቋምህን እንደማትጠብቅ ተናግሯል! (ኢዮብ 2:4, 5፤ ራእይ 12:10) ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ያሳድርብሃል? ስሜትህ በጣም እንደሚጎዳ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም እስቲ የሚከተለውን ለማሰብ ሞክር፦ ይሖዋ፣ ንጹሕ አቋምህን እንዲፈትነው ለሰይጣን ፈቅዶለታል። ይህን ግሩም አጋጣሚ የሰጠህ በአንተ ላይ ሙሉ እምነት ስላለው ነው። ይሖዋ፣ ንጹሕ አቋምህን እንደምትጠብቅና ሰይጣን ውሸታም መሆኑ እንዲረጋገጥ እንደምታደርግ ይተማመንብሃል። ደግሞም በዚህ ረገድ እንደሚረዳህ ቃል ገብቷል። (ዕብ. 13:6) የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ የሚተማመንብህ መሆኑ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ታዲያ ንጹሕ አቋምህን መጠበቅህ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘብክ? ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችን የሰይጣንን ውሸት ውድቅ ለማድረግ፣ ለአባታችን መልካም ስም ጥብቅና ለመቆም እንዲሁም የእሱን አገዛዝ ለመደገፍ ያስችለናል። w19.02 5 አን. 9-10
ሰኞ፣ ጥር 6
እናንተን የሚገድል ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል።—ዮሐ. 16:2
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ከፊታቸው ስለሚጠብቃቸው መከራ ነግሯቸዋል። ከዚያም ራሱን ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ “አይዟችሁ!” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 16:1-4ሀ, 33) በርካታ ዓመታት ካለፉ በኋላም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግና ድፍረት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተላቸውን ቀጥለው ነበር። በራሳቸው ላይ ከባድ ጉዳት ቢያስከትልባቸውም እንኳ በተለያዩ መከራዎች ሥር እርስ በርስ ይደጋገፉ ነበር። (ዕብ. 10:33, 34) እኛም በተመሳሳይ ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንከተላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በእምነታቸው ምክንያት ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞቻችንን ለመርዳት ድፍረት ማሳየት ያስፈልገናል። አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቻችን ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለእስር ይዳረጉ ይሆናል። በዚህ ወቅት እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፤ ይህም ለእነሱ ጥብቅና መቆምን ይጨምራል። (ፊልጵ. 1:14፤ ዕብ. 13:19) ከዚህም ሌላ “በድፍረት” መስበካችንን በመቀጠል የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ሥራ 14:3) ሰዎች ቢቃወሙን ወይም ስደት ቢያደርሱብንም እንኳ ልክ እንደ ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት ለማወጅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። w19.01 22-23 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ጥር 7
እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ።—ዕብ. 10:24, 25
በስብሰባዎች ላይ የሚያበረታቱ ሐሳቦችን ለመስጠት የሚረዱን የትኞቹ ጠቃሚ ምክሮች ናቸው? ለእያንዳንዱ ስብሰባ ጥሩ ዝግጅት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። አስቀድመን ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን ሐሳብ መስጠት ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። (ምሳሌ 21:5) ለስብሰባዎች ጥሩ ዝግጅት ማድረግ የትኞቹን ነገሮች ያካትታል? ምንጊዜም መዘጋጀት ከመጀመርህ በፊት ይሖዋ መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጥህ መጸለይ ይኖርብሃል። (ሉቃስ 11:13፤ 1 ዮሐ. 5:14) ከዚያም የተወሰኑ ደቂቃዎችን ወስደህ የጥናቱን አጠቃላይ ይዘት ለመቃኘት ሞክር። ይህም ዋናውን ርዕስ፣ ንዑስ ርዕሶቹን፣ ሥዕሎቹንና ሣጥኖቹን አንድ በአንድ መመልከትን ይጨምራል። ከዚያም እያንዳንዱን አንቀጽ ስትዘጋጅ፣ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱ ጥቅሶችን ለማንበብ የቻልከውን ያህል ጥረት አድርግ። ልትመልሳቸው ባሰብካቸው ነጥቦች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ በትምህርቱ ላይ አሰላስል። ጥሩ ዝግጅት ባደረግክ መጠን ከስብሰባዎች የምታገኘው ጥቅምም የዚያኑ ያህል ይጨምራል፤ ከዚህም በላይ ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።—2 ቆሮ. 9:6፤ w19.01 9 አን. 6፤ 11-12 አን. 13-15
ረቡዕ፣ ጥር 8
ራእዩን ጻፈው።—ዕን. 2:2
ይሖዋ፣ ዕንባቆም ያስጨነቀውን ነገር እንዲጽፍ በመንፈሱ በመምራት አንድ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቶናል፦ ስላስጨነቀን ነገር ወይም በውስጣችን ስላደረው ጥርጣሬ ለእሱ መናገር ሊያስፈራን አይገባም። እንዲያውም በጸሎት አማካኝነት ልባችንን በፊቱ እንድናፈስ በደግነት ጋብዞናል። (መዝ. 50:15፤ 62:8) ዕንባቆም የቅርብ ወዳጁና አባቱ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችለውን እርምጃ ወስዷል። ያለበትን ሁኔታ እያሰበ ከመብሰልሰል አሊያም በራሱ ማስተዋል ከመመካት ተቆጥቧል። ከዚህ ይልቅ የተሰማውን ስሜትና ያስጨነቀውን ነገር በጸሎት ለይሖዋ ተናግሯል። በዚህ መንገድ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ጸሎት ሰሚ የሆነው ይሖዋም ቢሆን ያስጨነቁንን ነገሮች ለእሱ በመናገር እንደምንታመንበት እንድናሳይ ግብዣ አቅርቦልናል። (መዝ. 65:2) እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ የሚሰጠንን ምላሽ መመልከት እንችላለን፤ ይሖዋ ደግነት የሚንጸባረቅበት አመራር ስለሚሰጠን በእጆቹ እቅፍ እንዳደረገን ሆኖ ይሰማናል። (መዝ. 73:23, 24) ያጋጠመን ተፈታታኝ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አስተሳሰብ እንድናውቅ ይረዳናል። ለአምላክ የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በእሱ እንደምንታመን ከምናሳይባቸው ዋነኛ መንገዶች መካከል አንዱ ነው። w18.11 13 አን. 2፤ 14 አን. 5-6
ሐሙስ፣ ጥር 9
በምድር ላይ ያሉት ቅዱሳን፣ ክብር የተላበሱት አገልጋዮች እጅግ ደስ ያሰኙኛል።—መዝ. 16:3
መዝሙራዊው ዳዊት ጓደኝነት የመሠረተው ከእኩዮቹ ጋር ብቻ አልነበረም። ‘ክብር ከተላበሱት አገልጋዮች’ መካከል የዳዊት የቅርብ ወዳጅ የነበረው ማን እንደሆነ ታስታውሳላችሁ? ዮናታን ነው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት በጣም ጠንካራ የሆኑ ወዳጅነቶች መካከል አንዱ በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረው ወዳጅነት ነው። ይሁንና ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ገደማ ይበልጠው እንደነበር ታውቃላችሁ? ታዲያ ለጓደኝነታቸው መሠረት የሆነው ነገር ምንድን ነው? በአምላክ ላይ ያላቸው እምነት፣ እርስ በርስ የነበራቸው አክብሮትና የአምላክን ጠላቶች በተፋለሙበት ወቅት አንዳቸው የሌላውን ድፍረት መመልከታቸው ነው። (1 ሳሙ. 13:3፤ 14:13፤ 17:48-50፤ 18:1) እናንተም ልክ እንደ ዳዊትና ዮናታን ይሖዋን ከሚወዱና በእሱ ላይ ያላቸውን እምነት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት በመመሥረት ‘እጅግ ደስ መሰኘት’ ትችላላችሁ። ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ያገለገለችው ኪራ እንዲህ ብላለች፦ “ከእኔ የተለየ አስተዳደግና ባሕል ካላቸው በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መመሥረት ችያለሁ።” እናንተም በዚህ መልኩ ፍቅራችሁን የምታሰፉ ከሆነ የአምላክ ቃልና ቅዱስ መንፈሱ በአምላክ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲሰፍን የማድረግ ኃይል እንዳላቸው በግልጽ መመልከት ትችላላችሁ። w18.12 26 አን. 11-13
ዓርብ፣ ጥር 10
በፆታ ብልግና ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።—ማቴ. 19:9
‘የፆታ ብልግና’ ከጋብቻ ውጭ የሚፈጸሙ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ኃጢአቶችን ያመለክታል፤ ይህም ምንዝርን፣ ዝሙት አዳሪነትን፣ ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን፣ ግብረ ሰዶማዊነትንና ከእንስሳ ጋር የሚፈጸም የፆታ ግንኙነትን ያካትታል። አንድ ሰው የፆታ ብልግና ከፈጸመ ሚስቱ እሱን ለመፍታት ወይም ላለመፍታት ልትወስን ትችላለች። ኢየሱስ አንድ ሰው የፆታ ብልግና (ፖርኒያ) ከፈጸመ የግድ ከሚስቱ ጋር መፋታት አለበት እንዳላለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ሚስት ባለቤቷ የሥነ ምግባር ብልግና ቢፈጽምም ትዳራቸውን ላለማፍረስ ትወስን ይሆናል። ይህን ውሳኔ የምታደርገው ባሏን ስለምትወደው እንዲሁም ይቅርታ ለማድረግና በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ፈቃደኛ ስለሆነች ሊሆን ይችላል። ደግሞም ባሏን ከፈታችው በኋላ ሳታገባ ብትኖር ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟት ግልጽ ነው። ለምሳሌ ቁሳዊና ፆታዊ ፍላጎቷን ማሟላት የምትችለው እንዴት ነው? ብቸኝነት ቢሰማትስ? ልጆች ካሏቸው ደግሞ ውሳኔዋ በእነሱ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? (1 ቆሮ. 7:14) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በደል የተፈጸመበት ወገን ለመፋታት መወሰኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ሊያስከትልበት ይችላል። w18.12 12 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ ጥር 11
እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ።—መዝ. 97:10
ይሖዋ ክፋትን ይጠላል። (ኢሳ. 61:8) ይሖዋ በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት ውስጣችን ወደ መጥፎ ነገር ያዘነበለ እንደሆነ ቢያውቅም ለክፋት የእሱ ዓይነት ጥላቻ እንድናዳብር መክሮናል። ይሖዋ ክፋትን የሚጠላው ለምን እንደሆነ ማሰላሰላችን የእሱ ዓይነት አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል፤ ይህም ከመጥፎ ድርጊቶች ለመራቅ የሚያስችል ተጨማሪ ጥንካሬ ይሰጠናል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለክፋት ያለውን አመለካከት ማዳበራችን፣ አንዳንድ ድርጊቶች በአምላክ ቃል ውስጥ በቀጥታ ባይወገዙም እንኳ ስህተት መሆናቸውን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ላፕ ዳንሲንግ የሚባለው የዳንስ ዓይነት በዓለም ዙሪያ በብዙዎች ዘንድ እየተለመደ መጥቷል። ይህ የዳንስ ዓይነት ልቅ የሆነ ምግባር የሚንጸባረቅበት ቢሆንም አንዳንዶች ድርጊቱ የፆታ ግንኙነት እንደመፈጸም ስለማይቆጠር ምንም ችግር እንደሌለው ይሰማቸዋል። ይሁንና ማንኛውንም ዓይነት ክፋት የሚጸየፈው አምላክ ለዚህ ድርጊት ያለው አመለካከት ፈጽሞ የተለየ ነው። እንግዲያው ራስን የመግዛት ባሕርይን በማዳበርና ይሖዋ የሚጸየፋቸውን ነገሮች በመጸየፍ ከክፋት ድርጊት እንራቅ።—ሮም 12:9፤ w18.11 25 አን. 11-12
እሁድ፣ ጥር 12
ጻድቅ . . . በታማኝነቱ በሕይወት ይኖራል።—ዕን. 2:4
እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ይሖዋ የገባው ቃል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከመሆኑ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ ሦስት ጊዜ ጠቅሶታል! (ሮም 1:17፤ ገላ. 3:11፤ ዕብ. 10:38) ጻድቅ ሰው ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስበት እምነት እስካለው ድረስ የአምላክ ዓላማ ሲፈጸም ያያል። ይሖዋ አሁን ካለው ጊዜ ባሻገር ያለውን ነገር እንድናይ ይፈልጋል። የዕንባቆም መጽሐፍ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ትልቅ ትምህርት ይዟል። ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት ላላቸው ጻድቃን በሙሉ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። እንግዲያው በማንኛውም ዓይነት መከራ ወይም ችግር ውስጥ ብንሆን ምንጊዜም በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ይኑረን። ይሖዋ፣ እንደሚደግፈንና እንደሚያድነን የሚገልጽ ማረጋገጫ በዕንባቆም አማካኝነት ሰጥቶናል። በተጨማሪም በእሱ እንድንተማመንና የወሰነውን ጊዜ በትዕግሥት እንድንጠብቅ በደግነት ጠይቆናል፤ በዚያን ጊዜ የአምላክ መንግሥት፣ መላዋ ምድር ደስተኛና ገር በሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች እንድትሞላ ያደርጋል።—ማቴ. 5:5፤ ዕብ. 10:36-39፤ w18.11 16-17 አን. 15-17
ሰኞ፣ ጥር 13
በእውነት ውስጥ [ተመላለሱ]።—3 ዮሐ. 4
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ለኢየሱስ ትምህርቶች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር፤ በኋላ ላይ ግን በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን አልቀጠሉም። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስ እጅግ ብዙ ሰዎችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከመገበ በኋላ ሰዎቹ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተከትለውት ሄዱ። ከዚያም ኢየሱስ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁና ደሙን ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” በማለት የሚያስደነግጥ ነገር ተናገረ። ሰዎቹ ኢየሱስ ጉዳዩን እንዲያብራራላቸው ከመጠየቅ ይልቅ በተናገረው ነገር ተሰናከሉ፤ እንዲያውም “ይህ የሚሰቀጥጥ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” በማለት ተናገሩ። በውጤቱም “ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ትተውት ወደነበረው ነገር ተመለሱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም እሱን መከተላቸውን አቆሙ።” (ዮሐ. 6:53-66) የሚያሳዝነው በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችም እውነትን አጥብቀው ሳይዙ ቀርተዋል። አንዳንዶቹ ኃላፊነት ያለው አንድ ወንድም በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ምክንያት ተሰናክለዋል። ሌሎቹ ደግሞ እውነትን የተዉት በተሰጣቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ቅር ስለተሰኙ ወይም በእነሱና በእምነት አጋራቸው መካከል አለመግባባት ስለተፈጠረ ነው። w18.11 9 አን. 3-5
ማክሰኞ፣ ጥር 14
መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ [ነው]።—ማቴ. 23:10
ድርጅቱ አንዳንድ ለውጦች ያደረገበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ መረዳት በሚከብደን ጊዜ ክርስቶስ ጥንት የነበሩ የአምላክ ሕዝቦችን የመራበትን መንገድ ማሰባችን ጠቃሚ ነው። በኢያሱ ጊዜም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቶስ ለአምላክ ሕዝቦች በቡድን ደረጃ ጥበቃ ለማድረግ፣ እምነታቸውን ለማጠናከርና አንድነታቸውን እንዲጠብቁ ለመርዳት ሲል ምንጊዜም ጥበብ የተንጸባረቀበት መመሪያ ይሰጥ ነበር። (ዕብ. 13:8) “ታማኝና ልባም ባሪያ” በተገቢው ጊዜ የሚሰጠን መመሪያ ኢየሱስ እንደሚወደንና ለመንፈሳዊ ደህንነታችን እንደሚያስብ ያሳያል። (ማቴ. 24:45) ክርስቶስ እየሰጠን ያለውን አመራር ስናስተውል፣ መሪያችን መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ሊረዳን እንደሚፈልግ እንገነዘባለን። ክርስቶስ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ከማሟላት በተጨማሪ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ካሉት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ሥራ ላይ እንድናተኩር ይረዳናል፤ ይህም የስብከቱ ሥራ ነው።—ማርቆስ 13:10፤ w18.10 25 አን. 13-16
ረቡዕ፣ ጥር 15
ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ . . . በፍጹም ትሕትና . . . ኑሩ።—ኤፌ. 4:1, 2
ሌሎች፣ ተገቢ ያልሆነ ነገር በሚያደርጉብን ጊዜ ራሳችንን በመግዛት ረገድ በ2 ሳሙኤል 16:5-13 ላይ የሚገኘው ዘገባ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። የንጉሥ ሳኦል ዘመድ የሆነው ሺምአይ በዳዊትና በአገልጋዮቹ ላይ ስድብና አካላዊ ጥቃት ሰንዝሮባቸው ነበር። ዳዊት ይህን ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ማስቆም ቢችልም ሁኔታውን በትዕግሥት አለፈው። ዳዊት እንዲህ ያለ ራስን የመግዛት ባሕርይ ለማሳየት የረዳው ምንድን ነው? በመዝሙር 3 አናት ላይ ያለው መግለጫ እንደሚጠቁመው ዳዊት ይህን መዝሙር ያቀናበረው “ከልጁ ከአቢሴሎም በሸሸ ጊዜ” ነው። በቁጥር 1 እና 2 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በሁለተኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 16 ላይ ስለተገለጹት ክንውኖች የሚያወሳ ነው። መዝሙር 3:4 ደግሞ ዳዊት በይሖዋ ምን ያህል እንደሚታመን ያሳያል፤ ጥቅሱ “ድምፄን ከፍ አድርጌ ይሖዋን እጣራለሁ፤ እሱም . . . ይመልስልኛል” ይላል። እኛም ጥቃት በሚሰነዘርብን ጊዜ መጸለይ እንችላለን። ይሖዋ ለመጽናት የሚረዳንን ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ጸሎታችንን ይመልስልናል። አንተስ ትዕግሥትህን የሚፈታተን ሁኔታ ሲያጋጥምህ ራስህን በመግዛት አሊያም ሌሎች ያለምክንያት ሲጠሉህ በነፃ ይቅር በማለት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ መከራህን ተመልክቶ እንደሚባርክህስ ትተማመናለህ? w18.09 6-7 አን. 16-17
ሐሙስ፣ ጥር 16
እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።—1 ቆሮ. 3:9
አገልግሎት ላይ ስንሆን ምንጊዜም ለሰዎች አሳቢነትና አክብሮት ማሳየት አለብን፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ በክልላችን ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሁኔታ በደንብ ማወቅ ይኖርብናል። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ሰዎቹ ቤት የምንሄደው ተጋብዘን እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ለመወያየት ይበልጥ በሚያመቻቸው ጊዜ መሄዳችን በጣም አስፈላጊ ነው! (ማቴ. 7:12) ለምሳሌ፣ በክልላችሁ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቅዳሜና እሁድ አረፋፍደው የመነሳት ልማድ አላቸው? ከሆነ ቀኑ ረፈድ እስኪል ድረስ በአደባባይ ምሥክርነት ልትካፈሉ ወይም መንገድ ላይ ልታገለግሉ አሊያም ደግሞ በጠዋት እንደሚነሱ ለምታውቋቸው ሰዎች ተመላልሶ መጠየቅ ልታደርጉ ትችሉ ይሆናል። ብዙ ሰዎች ፕሮግራማቸው የተጣበበ ነው፤ በመሆኑም ቢያንስ መጀመሪያ አካባቢ ውይይታችንን አጠር ማድረጉ ተገቢ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮ. 9:20-23) ሰዎች ሁኔታቸውን እንደተረዳን ወይም ሥራ የሚበዛባቸው መሆኑን እንዳስተዋልን ሲመለከቱ በሌላ ጊዜም ውይይቱን ለመቀጠል ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። በአገልግሎታችን ላይ የአምላክን መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ማንጸባረቅ ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ “ከአምላክ ጋር አብረን [መሥራት]” እንችላለን፤ ይሖዋም አንድን ሰው ወደ እውነት ለመሳብ በእኛ ሊጠቀም ይችላል።—1 ቆሮ. 3:6, 7፤ w18.09 32 አን. 15-17
ዓርብ፣ ጥር 17
ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና።—ማቴ. 5:5
ገር መሆን ለደስታ አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው? ሰዎች የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ሲቀስሙ የባሕርይ ለውጥ ያደርጋሉ። እነዚህ ሰዎች በአንድ ወቅት ጨካኝ፣ ጠበኛና ቁጡ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን ግን “አዲሱን ስብዕና” ስለለበሱ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን” ያሳያሉ። (ቆላ. 3:9-12) በዚህም ምክንያት ሕይወታቸው ሰላም፣ ፍቅርና ደስታ የሰፈነበት ሆኗል። ከዚህም ሌላ የአምላክ ቃል እንደሚናገረው እንዲህ ያሉ ገር ሰዎች “ምድርን ይወርሳሉ።” (መዝ. 37:8-10, 29) ‘ገሮች ምድርን የሚወርሱት’ በምን መንገድ ነው? በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘ምድርን ይወርሳሉ’ የሚባለው ነገሥታትና ካህናት ሆነው ምድርን ስለሚያስተዳድሩ ነው። (ራእይ 20:6) ወደ ሰማይ የመሄድ ተስፋ የሌላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ቢሆኑ ፍጹም ሆነው በምድር ላይ በሰላምና በደስታ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ስለሚያገኙ ምድርን ይወርሳሉ ሊባል ይችላል። w18.09 19 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ ጥር 18
ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ . . . መሆን አለበት።—ያዕ. 1:19
በዚህ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ይሖዋ ነው። (ዘፍ. 18:32፤ ኢያሱ 10:14) በዘፀአት 32:11-14 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ዘገባ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምረን እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ከሙሴ ጋር መመካከር ባያስፈልገውም ሙሴ ሐሳቡን እንዲገልጽ አጋጣሚ ሰጥቶታል። አንተ ብትሆን ሲሳሳት ያየኸውን ሰው ሐሳብ በትዕግሥት አዳምጠህ የእሱን ሐሳብ ተግባራዊ ታደርጋለህ? ይሖዋ ግን በእምነት ወደ እሱ የሚጸልዩ ሰዎችን ሁሉ በትዕግሥት ያዳምጣል። ሁላችንም ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ይሖዋ ራሱን ዝቅ በማድረግ አብርሃምን፣ ራሔልን፣ ሙሴን፣ ኢያሱን፣ ማኑሄን፣ ኤልያስን እና ሕዝቅያስን በትዕግሥት ካዳመጠ እኔስ ከወንድሞቼ ጋር በተያያዘ እንዲህ ማድረግ የለብኝም? ወንድሞቼ ሐሳብ ሲሰጡ በማዳመጥ ብሎም የሰጡኝን ጥሩ ሐሳብ በተግባር በማዋል አክብሮት ላሳያቸውስ አይገባም? በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ወንድሞች አሊያም ከቤተሰቤ አባላት መካከል በአሁኑ ወቅት የእኔ ትኩረት የሚያስፈልገው ሰው አለ? ግለሰቡን ለመርዳት ምን ማድረግ እችላለሁ?’—ዘፍ. 30:6፤ መሳ. 13:9፤ 1 ነገ. 17:22፤ 2 ዜና 30:20፤ w18.09 6 አን. 14-15
እሁድ፣ ጥር 19
ለጋስ ሰው ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም እሱ ራሱ ይረካል።—ምሳሌ 11:25
የምንኖረው የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ማስቀደም በሚፈልጉ ሰዎች መካከል ስለሆነ ምንጊዜም የልግስናን መንፈስ ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ኢየሱስ ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችን፣ በሙሉ አእምሯችንና በሙሉ ኃይላችን መውደድ እንዲሁም ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ እንደሆኑ ተናግሯል። (ማር. 12:28-31) ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች እሱን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ለሌሎች በልግስና መስጠት ያስደስታቸዋል። እኛም ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ያበረታቱናል፤ ምክንያቱም ይህ እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኝልን ያውቃሉ። ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት የልግስናን መንፈስ ለማንጸባረቅ የምንጥር ከሆነ ይሖዋን እናስከብራለን፤ እንዲሁም ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን። ሌሎችን በተለይ ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት አሁንም ቢሆን ጥረት እያደረግን እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። (ገላ. 6:10) እንዲህ ማድረጋችንን ከቀጠልን ሌሎች እንደሚወዱንና ጥረታችንን እንደሚያደንቁ መተማመን እንችላለን፤ ይህ ደግሞ ደስታ ያስገኝልናል። w18.08 22 አን. 19-20
ሰኞ፣ ጥር 20
የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ።—ዮሐ. 7:24
የዘር፣ የብሔር፣ የጎሳ፣ የአገር ወይም የቋንቋ ልዩነት በይሖዋ ፊት ምንም ቦታ የለውም። አምላክን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ማንኛውም ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው። (ገላ. 3:26-28፤ ራእይ 7:9, 10) ይህ እውነት መሆኑን አንተም እንደምትስማማ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ያደግከው ጭፍን ጥላቻ በተስፋፋበት አካባቢ ወይም ቤተሰብ ውስጥ ቢሆንስ? አንተ በግልህ አድልዎ የማታደርግ ሰው እንደሆንክ ታስብ ይሆናል፤ ሆኖም በውስጥህ የቀረ የጭፍን ጥላቻ ርዝራዥ ሊኖር ይችላል። ይሖዋ የማያዳላ አምላክ መሆኑን ለሌሎች የማሳወቅ መብት አግኝቶ የነበረው ጴጥሮስም እንኳ ጭፍን ጥላቻ እንዳለው የሚያሳይ ነገር ከጊዜ በኋላ አድርጓል። (ገላ. 2:11-14) ታዲያ የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት ከመፍረድ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? በውስጣችን የቀረ ጭፍን ጥላቻ ይኖር እንደሆነ ለማወቅ የአምላክን ቃል በመጠቀም ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር ይኖርብናል። (መዝ. 119:105) በተጨማሪም የቅርብ ጓደኛችን ጭፍን ጥላቻ እንዳለን ካስተዋለ እንዲነግረን ልንጠይቀው እንችላለን፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳለን ለራሳችን ላይታወቀን ይችላል። (ገላ. 2:11, 14) መሠረተ ቢስ ጥላቻ በውስጣችን ለረጅም ጊዜ ከመቆየቱ የተነሳ እንዲህ ያለ አመለካከት እንዳለን እንኳ በቀላሉ አናስተውል ይሆናል። w18.08 9 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ጥር 21
ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።—ማቴ. 5:16
ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘በሙሉ ልቤ ለይሖዋ ታማኝ እንደሆንኩ ለሌሎች በግልጽ ይታያል? የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ለሌሎች ማሳወቅ የምችልባቸውን አጋጣሚዎች እፈልጋለሁ?’ የይሖዋ ንብረት እንደሆንን ለሌሎች መናገር የሚያሳፍረን ከሆነ ሕዝቡ አድርጎ የመረጠን ይሖዋ በዚህ በጣም እንደሚያዝን ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 119:46፤ ማር. 8:38) የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖች “የዓለምን መንፈስ” ስለሚያንጸባርቁ አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ እንዳይታይ አድርገዋል። (1 ቆሮ. 2:12) “የዓለም መንፈስ” ሰዎች ‘በሥጋቸው ፍላጎት’ ላይ እንዲያተኩሩ ያበረታታል። (ኤፌ. 2:3) ለምሳሌ ያህል፣ አለባበስንና አጋጌጥን በተመለከተ በተደጋጋሚ ምክር ቢሰጥም አንዳንዶች አሁንም አለባበሳቸውና አጋጌጣቸው ልከኝነት የጎደለው ነው። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሳይቀር በጣም የተጣበቁና ሰውነትን የሚያጋልጡ ልብሶችን ይለብሳሉ። አሊያም ወጣ ያለ የፀጉር አቆራረጥ ወይም አሠራር ስታይል ይከተላሉ። (1 ጢሞ. 2:9, 10) በዚህም የተነሳ ከሌሎች ሰዎች ጋር አብረው ሲሆኑ ማን የይሖዋ ንብረት፣ ማን ደግሞ “የዓለም ወዳጅ” እንደሆነ መለየት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።—ያዕ. 4:4፤ w18.07 24-25 አን. 11-12
ረቡዕ፣ ጥር 22
ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ።—ማቴ. 23:8
“ወንድማማቾች” እንድንባል የሚያደርገን አንዱ ምክንያት ሁላችንም የአዳም ልጆች መሆናችን ነው። (ሥራ 17:26) ምክንያቱ ግን ይህ ብቻ አይደለም። የኢየሱስ ተከታዮች፣ ይሖዋን እንደ ሰማያዊ አባታቸው አድርገው ስለሚቀበሉ ሁሉም ወንድማማችና እህትማማች እንደሆኑ ኢየሱስ ገልጿል። (ማቴ. 12:50) በተጨማሪም የክርስቶስ ተከታዮች በፍቅርና በእምነት የተሳሰረ የአንድ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባላት ናቸው። ሐዋርያት በጻፏቸው ደብዳቤዎች ላይ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ‘ወንድሞች’ እና ‘እህቶች’ ብለው የጠሯቸው ለዚህ ነው። (ሮም 1:13፤ 1 ጴጥ. 2:17፤ 1 ዮሐ. 3:13) ኢየሱስ፣ እንደ ወንድማማችና እንደ እህትማማች ልንተያይ እንደሚገባ ከተናገረ በኋላ የትሕትናን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ማቴ. 23:11, 12) በሐዋርያቱ መካከል አንድነት እንዳይኖር ያደረገው ተገቢ ያልሆነ ኩራት ነው። በተጨማሪም በኢየሱስ ዘመን ሰዎች በዘራቸው በጣም ይኮሩ ነበር። ይሁንና አይሁዳውያን የአብርሃም ዘሮች መሆናቸው እንዲኮሩ ሊያደርጋቸው ይገባል? በርካታ አይሁዳውያን እንዲህ ይሰማቸው ነበር። ሆኖም መጥምቁ ዮሐንስ “አምላክ ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆች ማስነሳት [አይሳነውም]” ብሏቸዋል።—ሉቃስ 3:8፤ w18.06 9-10 አን. 8-9
ሐሙስ፣ ጥር 23
አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው።—ምሳሌ 17:27
ትዕግሥታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ወይም በባሕርይ አለመጣጣም ምክንያት ከአንድ ሰው ጋር በተደጋጋሚ ስንጋጭ አንደበታችንን ወይም ቁጣችንን ለመቆጣጠር እንሞክራለን? (ምሳሌ 10:19፤ ማቴ. 5:22) ሌሎች የሚያበሳጭ ነገር ሲፈጽሙብን “ለቁጣው” ማለትም ለይሖዋ ቁጣ “ዕድል [መስጠት]” ይኖርብናል። (ሮም 12:17-21) ምንጊዜም ወደ ይሖዋ የምንመለከት ከሆነ እሱ ተገቢ ነው ብሎ ባሰበው ሰዓት እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት በመጠበቅ ለቁጣው ዕድል እንሰጣለን፤ በዚህ መንገድ ለይሖዋ ተገቢውን አክብሮት እናሳያለን። ከዚህ በተቃራኒ ራሳችን በሆነ መንገድ ለመበቀል መሞከራችን ለይሖዋ አክብሮት እንደማጣት ይቆጠራል። ይሖዋ የሚሰጠንን አዳዲስ መመሪያዎች በታማኝነት እንፈጽማለን? ከሆነ ነገሮችን ሁልጊዜ በለመድነው መንገድ ለመሥራት አንሞክርም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን ማንኛውንም አዲስ መመሪያ ለመከተል ፈጣኖች እንሆናለን። (ዕብ. 13:17) በተጨማሪም ‘ከተጻፈው ላለማለፍ’ እንጠነቀቃለን። (1 ቆሮ. 4:6) በዚህ መንገድ ዓይናችን ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዲመለከት እናደርጋለን። w18.07 15-16 አን. 17-18
ዓርብ፣ ጥር 24
ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር።—ዕብ. 6:1
በመንፈሳዊ እየጎለመስን ስንሄድ፣ ለመሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ ትኩረት መስጠት እንጀምራለን። ምክንያቱም ሕጎች የሚሠሩት ለተወሰኑ ሁኔታዎች ብቻ ነው፤ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ግን ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ልናደርጋቸው እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ትንሽ ልጅ መጥፎ ጓደኝነት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ላይገነዘብ ይችላል፤ በመሆኑም አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጃቸውን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲሉ ሕግ ያወጡለታል። (1 ቆሮ. 15:33) ልጁ እየበሰለ ሲሄድ ግን የማሰብ ችሎታው ስለሚዳብር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞ ማመዛዘን ይጀምራል። በመሆኑም ጥሩ ጓደኞች የመምረጥ ችሎታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ይሄዳል። (1 ቆሮ. 13:11፤ 14:20) በይሖዋ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ጊዜ ወስደን የምናሰላስል ከሆነ የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ ስለምናዳብር ሕሊናችን ይበልጥ አስተማማኝ መሪ ይሆንልናል። ይሖዋን የሚያስደስቱ ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዱን ነገሮች በሙሉ ተሟልተውልናል። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ [ሆነን እንድንገኝ]” ይረዱናል።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ w18.06 19 አን. 14፤ 20 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ጥር 25
ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?—ሉቃስ 10:29
አይሁዳውያን፣ እውነተኛ ባልንጀራ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ከሳምራዊ መማር እንደሚችሉ ኢየሱስ የተናገረው ታሪክ በግልጽ ያሳያል። (ሉቃስ 10:25-37) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ “በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንዲሰብኩ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። (ሥራ 1:8) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ተልእኮ ለመወጣት፣ ኩራትንና ጭፍን ጥላቻን ማስወገድ ነበረባቸው። ኢየሱስ፣ የሌላ አገር ሰዎች ያሏቸውን መልካም ባሕርያት ጎላ አድርጎ በመናገር ተከታዮቹ ለሁሉም ብሔራት ለመስበክ አእምሯቸውን እንዲያዘጋጁ ቀደም ብሎ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ፣ የሌላ አገር ተወላጅ የሆነ አንድ የጦር መኮንን ያሳየውን ታላቅ እምነት አድንቋል። (ማቴ. 8:5-10) ባደገባት በናዝሬት ደግሞ፣ ይሖዋ ለባዕድ አገር ሰዎች ሞገስ እንዳሳያቸው የተናገረ ሲሆን በሰራፕታ ትኖር የነበረችውን ፊንቄያዊት መበለት እንዲሁም የሥጋ ደዌ ይዞት የነበረውን ሶርያዊውን ንዕማንን እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። (ሉቃስ 4:25-27) ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሴት ሰብኳል፤ እንዲሁም አንዳንድ ሳምራውያን መልእክቱን ለመስማት ፍላጎት ስላሳዩ በሳምራውያን ከተማ ሁለት ቀን አሳልፏል።—ዮሐ. 4:21-24, 40፤ w18.06 10 አን. 10-11
እሁድ፣ ጥር 26
የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች መቋቋም እንድትችሉ ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ ልበሱ።—ኤፌ. 6:11
ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያኖችን ሕይወት በጨበጣ ውጊያ ላይ ካሉ ወታደሮች ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። እርግጥ ነው፣ ይህ ሲባል ቃል በቃል እንዋጋለን ማለት አይደለም፤ ውጊያው መንፈሳዊ ነው። ያም ቢሆን ጠላቶቻችን በእውን ያሉ አካላት ናቸው። ሰይጣንና አጋንንቱ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያካበቱ ተዋጊዎች ናቸው። በመሆኑም በውጊያው ለማሸነፍ ጨርሶ ተስፋ የሌለን ይመስል ይሆናል። በተለይ ደግሞ ወጣት ክርስቲያኖች በቀላሉ የሚሸነፉ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ታዲያ ወጣቶች፣ ከሰው በላይ አቅም ካላቸው ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውጊያ አሸናፊ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ወጣቶች በውጊያው ማሸነፍ ይችላሉ፤ ደግሞም እያሸነፉ ነው! እንዲያሸንፉ የረዳቸው ምንድን ነው? ‘ከጌታ ኃይል’ ማግኘታቸው ነው። ከዚህም ሌላ ለጦርነት ታጥቀዋል። ጥሩ ሥልጠና እንዳገኙ ወታደሮች ሁሉ እነዚህ ወጣቶችም “ሙሉ የጦር ትጥቅ [ለብሰዋል]።” (ኤፌ. 6:10-12) ጳውሎስ ይህን ምሳሌ የተናገረው የሮም ወታደሮች የሚለብሱትን የጦር ትጥቅ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል።—ሥራ 28:16፤ w18.05 27 አን. 1-2
ሰኞ፣ ጥር 27
በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።—ማቴ. 6:9
በስብከቱ ሥራችን የምንካፈልበት ዋነኛ ምክንያት ይሖዋን ለማስከበርና ሰዎች ሁሉ ስሙን እንዲቀድሱ ለማድረግ ነው። (ዮሐ. 15:1, 8) እርግጥ የአምላክ ስም ይበልጥ ቅዱስ እንዲሆን ማድረግ አንችልም። ምክንያቱም የአምላክ ስም፣ ፍጹም በሆነ መልኩ ቅዱስ ነው። ሆኖም ነቢዩ ኢሳይያስ “ቅዱስ አድርጋችሁ ልትመለከቱ የሚገባው የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ነው” ብሎ እንደተናገረ ልብ እንበል። (ኢሳ. 8:13) የአምላክ ስም እንዲቀደስ ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል፣ ስሙን ከሌሎች ስሞች ሁሉ የተለየ አድርገን መመልከትን እንዲሁም ሌሎች ቅዱስ አድርገው እንዲመለከቱት መርዳትን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ አስደናቂ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት እንዲሁም የሰው ልጆች በገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ለማድረግ ስላለው ዓላማ እውነቱን ስናውጅ፣ ሰይጣን በአምላክ ስም ላይ የሰነዘረው ነቀፋ ውሸት መሆኑን እናጋልጣለን። (ዘፍ. 3:1-5) ከዚህም ሌላ ይሖዋ “ግርማ፣ ክብርና ኃይል” ሊቀበል እንደሚገባው በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ስናሳውቅ የአምላክ ስም እንዲቀደስ እናደርጋለን።—ራእይ 4:11፤ w18.05 18 አን. 3-4
ማክሰኞ፣ ጥር 28
ለይሖዋ ምስጋና ማቅረብ ጥሩ ነው፤ . . . ይሖዋ ሆይ፣ ባከናወንካቸው ነገሮች እንድደሰት አድርገኸኛልና፤ ከእጅህ ሥራዎች የተነሳ እልል እላለሁ።—መዝ. 92:1, 4
መንፈሳዊ ግቦች እንድናወጣ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት፣ ይሖዋ ላሳየን ፍቅርና ላደረገልን ነገሮች አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ያለን ፍላጎት ነው። ይሖዋ ያደረገልህን ነገሮች ሁሉ እስቲ መለስ ብለህ አስብ። ሕይወትህ፣ ይሖዋን ማወቅና ስለ እሱ እውነቱን መማር መቻልህ፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጉባኤው እንዲሁም በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋህ ከእነዚህ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠትህ ከአምላክ ላገኘሃቸው ለእነዚህ በረከቶች አመስጋኝነትህን ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጥሃል፤ ይህ ደግሞ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ይረዳሃል። መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግህ መልካም ሥራ በማከናወን ረገድ በይሖዋ ዘንድ ጥሩ ስም እያስመዘገብክ ለመሄድ ያስችልሃል። ይህም ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳሃል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም” በማለት ቃል ገብቷል። (ዕብ. 6:10) መንፈሳዊ ግቦችን ለማውጣት ዕድሜያችሁ እንዳልደረሰ አድርጋችሁ ፈጽሞ አታስቡ። ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ግቦችን ለማውጣትና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ለምን ጥረት አታደርግም?—ፊልጵ. 1:10, 11፤ w18.04 26 አን. 5-6
ረቡዕ፣ ጥር 29
የይሖዋ መንፈስ ባለበት . . . ነፃነት አለ።—2 ቆሮ. 3:17
በሮም ግዛት የነበሩ ሰዎች፣ ባሏቸው ሕጎች እንዲሁም ፍትሕንና ነፃነትን በማስከበራቸው ይኩራሩ ነበር። ይሁን እንጂ ኃያል የሆነው የሮም ግዛት የተገነባው በባሪያዎች ጉልበት ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት በሮም ግዛት ውስጥ ከነበሩት ነዋሪዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ባሪያዎች ነበሩ። ከዚህ አንጻር የባርነትና የነፃነት ጉዳይ በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ጨምሮ በብዙኃኑ አእምሮ ውስጥ የሚጉላላ ርዕስ እንደነበረ አያጠራጥርም። ሐዋርያው ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ ላይ ስለ ነፃነት በተደጋጋሚ ተናግሯል። ሆኖም የአገልግሎቱ ዓላማ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች እንደሚመኙት ከማኅበራዊ ወይም ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለውጥ ማምጣት አልነበረም። ጳውሎስና የእምነት ባልንጀሮቹ የትኛውም ሰብዓዊ ገዢ ወይም ድርጅት ነፃነት እንዲያስገኝላቸው አልጠበቁም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራችና የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስላለው ውድ ዋጋ ሰዎችን ለማስተማር በትጋት ሠርተዋል። ጳውሎስ፣ እውነተኛ ነፃነት የሚገኘው ከየት እንደሆነ ለእምነት ባልንጀሮቹ ነግሯቸዋል። w18.04 8 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ጥር 30
ስምዖን፣ ስምዖን፣ ሰይጣን ሁላችሁንም እንደ ስንዴ ያበጥራችሁ ዘንድ ጥያቄ አቅርቧል። እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ፤ አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።—ሉቃስ 22:31, 32
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ከላይ የሚገኘውን ሐሳብ ነግሮት ነበር። ጴጥሮስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ እንደ ዓምድ መሆኑን አስመሥክሯል። (ገላ. 2:9) በጴንጤቆስጤ ዕለትና ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት ባከናወናቸው ድፍረት የሚጠይቁ ነገሮች አማካኝነት ወንድሞቹን አበረታቷል። ለበርካታ ዓመታት በዘለቀው አገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢ ለእምነት ባልንጀሮቹ ደብዳቤ ጽፎላቸው ነበር። የደብዳቤዎቹን ዓላማ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የጻፍኩላችሁ . . . እናንተን ለማበረታታትና ይህ የአምላክ እውነተኛ ጸጋ እንደሆነ አጥብቄ ለመመሥከር ነው። ይህን ጸጋ አጥብቃችሁ ያዙ።” (1 ጴጥ. 5:12) ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ደብዳቤዎች በጥንት ዘመን ለኖሩም ሆነ ዛሬ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የብርታት ምንጭ ሆነዋል፤ ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች የሚፈጸሙበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ባለንበት በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለውን ማበረታቻ ማግኘታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—2 ጴጥ. 3:13፤ w18.04 17 አን. 12-13
ዓርብ፣ ጥር 31
ነፃ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ በትኩረት የሚመለከትና በዚያ የሚጸና ሰው [በሚያደርገው] ነገር ደስተኛ ይሆናል።—ያዕ. 1:25
የፈለጉትን የማድረግ ወይም በፈለጉት መንገድ ሕይወታቸውን የመምራት ነፃነት በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ጉዳይ ይመስላል። ይህን ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሞክሩት ግን በምን መንገድ ነው? ከማኅበራዊና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ብዙዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲሉ ተቃውሞ ያሰማሉ፤ ሰልፍ ይወጣሉ፤ ዓመፅ ያነሳሳሉ ብሎም አብዮት ያካሂዳሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው አካሄድ የታለመለትን ግብ ማሳካት ችሏል? በፍጹም፤ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ለብዙ መከራና ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ይሆናል። ይህም ንጉሥ ሰለሞን በመንፈስ መሪነት የጻፈውን “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው። (መክ. 8:9) በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያዕቆብ እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት የሚያስችለውን ቁልፍ ተናግሯል። የዚህ ፍጹም ሕግ ምንጭ የሆነው ይሖዋ፣ የሰው ልጆች እውነተኛ ደስታና እርካታ ለማግኘት ምን እንደሚያስፈልጋቸው ከማንም በተሻለ ያውቃል። ደግሞም ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ ሰጥቷቸዋል፤ ከእነዚህም መካከል እውነተኛ ነፃነት ይገኝበታል። w18.04 3 አን. 1-3