የካቲት
ቅዳሜ፣ የካቲት 1
አገልግሎትህን በተሟላ ሁኔታ ፈጽም።—2 ጢሞ. 4:5
ኢየሱስ ለሰዎች ከልቡ ይራራ ነበር። የመንግሥቱን መልእክት የሰበከላቸው ሰዎች ኢየሱስ እንደሚወዳቸው ስለተገነዘቡ ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል። እኛም ለሰዎች ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት ባደረግን መጠን በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ እንሆናለን። የምንሰብክላቸውን ሰዎች ስሜት መረዳት የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን በአገልግሎት ላይ በምናገኛቸው ሰዎች ቦታ ማስቀመጥ እንዲሁም ሌሎች እኛን እንዲይዙን በምንፈልገው መንገድ እነሱን መያዝ ይኖርብናል። (ማቴ. 7:12) እያንዳንዱ ግለሰብ ምን እንደሚያስፈልገው ለማሰብ ሞክሩ። በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ ተመሳሳይ መግቢያ አንጠቀምም። ከዚህ ይልቅ የእያንዳንዱን ግለሰብ ሁኔታና አመለካከት ግምት ውስጥ እናስገባለን። ጥያቄዎችን በዘዴ በመጠቀም ግለሰቡ የውስጡን አውጥቶ እንዲናገር አድርጉ። (ምሳሌ 20:5) ሰዎች ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ስናደርግ በተዘዋዋሪ መንገድ ምሥራቹ የሚያስፈልጋቸው ለምን እንደሆነ እንዲነግሩን እያደረግን ነው። ይህን ካወቅን ልክ እንደ ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ምን እንደሚያስፈልጋቸው መገንዘብና በዚያ ላይ ተመሥርተን እርዳታ መስጠት እንችላለን።—ከ1 ቆሮ. 9:19-23 ጋር አወዳድር፤ w19.03 20 አን. 2፤ 22 አን. 8-9
እሁድ፣ የካቲት 2
የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።—ምሳሌ 16:3
አዳምና ሔዋን፣ ይሖዋ ላደረገላቸው ነገሮች ሁሉ ምንም ዓይነት አድናቆት እንደሌላቸው አሳይተዋል። ሁላችንም እነሱ ያደረጉትን ውሳኔ ምን ያህል እንደምንቃወም የምናሳይበት አጋጣሚ ተከፍቶልናል። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ለእኛ መሥፈርት የማውጣት ሥልጣን ያለው ይሖዋ ነው፤ ራሳችንን ወስነን ስንጠመቅ ይህን አምነን እንደተቀበልን ለይሖዋ እናሳያለን። አባታችንን እንደምንወደውና እንደምንተማመንበት እናረጋግጣለን። ከተጠመቅን በኋላ በየዕለቱ በራሳችን ሳይሆን በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት አለብን፤ ይህ ደግሞ ተፈታታኝ እንደሆነ አይካድም። ሆኖም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ እያደረጉ ነው። አንተም የአምላክን ቃል በጥልቀት የምታጠና፣ ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር አዘውትረህ የምትሰበሰብ እንዲሁም አፍቃሪ ስለሆነው አባትህ የተማርከውን ነገር ለሌሎች በቅንዓት የምትሰብክ ከሆነ ልክ እንደ እነሱ በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ትችላለህ። (ዕብ. 10:24, 25) ውሳኔዎችን ስታደርግ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠውን ምክር ስማ። (ኢሳ. 30:21) እንዲህ ካደረግክ የምታከናውነው ነገር ሁሉ ይሳካልሃል።—ምሳሌ 16:20፤ w19.03 7 አን. 17-18
ሰኞ፣ የካቲት 3
መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው፤ ይህ የሚወርደው ከሰማይ ብርሃናት አባት [ነው]።—ያዕ. 1:17
ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦልናል። ለምሳሌ በጉባኤ ስብሰባዎቻችን፣ በመጽሔቶቻችንና በድረ ገጾቻችን አማካኝነት ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። አንድን ንግግር አዳምጠህ፣ ጽሑፍ ላይ የወጣ ርዕስ አንብበህ ወይም ብሮድካስቲንግ ላይ አንድ ቪዲዮ ተመልክተህ ‘የሚያስፈልገኝ ይህ ነበር’ ያልክበት ጊዜ የለም? ታዲያ ይሖዋ ላደረገልን ነገር አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? (ቆላ. 3:15) አንዱ መንገድ በጸሎታችን ላይ ይሖዋን ለእነዚህ መልካም ስጦታዎች አዘውትረን ማመስገን ነው። ለይሖዋ ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ የአምልኮ ቦታዎቻችንን ንጹሕና ሥርዓታማ አድርገን መያዝ ነው። የስብሰባ አዳራሾቻችንን በማጽዳቱና በመጠገኑ ሥራ አዘውትረን መካፈል ይኖርብናል። በተጨማሪም የጉባኤው ንብረት በሆኑ የድምፅና የቪዲዮ መሣሪያዎች ላይ እንዲያገለግሉ የተመደቡ ወንድሞች እነዚህን መሣሪያዎች በጥንቃቄ መያዝ ይኖርባቸዋል። የስብሰባ አዳራሻችንን ጥሩ አድርገን የምንይዝ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግለን ከመሆኑም በላይ ያን ያህል ከባድ ጥገና አያስፈልገውም። ይህም በዓለም ዙሪያ ተጨማሪ የስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባትና ለማደስ የሚያገለግል ተጨማሪ ገንዘብ እንዲገኝ ያስችላል። w19.02 18 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ የካቲት 4
እነዚህ የመንገዱ ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እሱ የሰማነው የሹክሹክታ ያህል ብቻ ነው!—ኢዮብ 26:14
ኢዮብ ድንቅ በሆኑት የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ ጊዜ ወስዶ ያሰላስል ነበር። (ኢዮብ 26:7, 8) ምድርን፣ ሰማይን፣ ደመናትንና ነጎድጓድን ሲያስብ ጥልቅ በሆነ የአድናቆት ስሜት ተውጦ ነበር፤ ያም ሆኖ ይሖዋ ስለፈጠራቸው ነገሮች ያለው እውቀት በጣም ውስን እንደሆነ አምኖ ተቀብሏል። በተጨማሪም ኢዮብ፣ ይሖዋ ለተናገራቸው ነገሮች አድናቆት ነበረው። “የተናገረውን ቃል . . . ከፍ አድርጌ ተመልክቻለሁ” በማለት ለአምላክ ቃል ያለውን አድናቆት ገልጿል። (ኢዮብ 23:12) ኢዮብ ለአምላክ ከፍተኛ አድናቆትና ጥልቅ አክብሮት ነበረው። ይህም ይሖዋን እንዲወደውና እሱን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርበት አነሳስቶታል። ይህ ደግሞ ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ያደረገውን ውሳኔ ይበልጥ ለማጠናከር አስችሎታል። እኛም ልክ እንደ ኢዮብ ማድረግ ይኖርብናል። ድንቅ ስለሆኑት የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች ያለን እውቀት በኢዮብ ዘመን ከነበሩት ሰዎች እጅግ የላቀ ነው። በተጨማሪም በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ስላለን የይሖዋን ማንነት በሚገባ ማወቅ እንችላለን። ስለ ይሖዋ የምንማራቸው ነገሮች ሁሉ ልባችን በአድናቆት እንዲሞላ ያደርጋሉ። ለይሖዋ ያለን አድናቆትና አክብሮት ደግሞ እሱን እንድንወደውና እንድንታዘዘው እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን የመጠበቅ ልባዊ ፍላጎት እንድናዳብር ይረዳናል።—ኢዮብ 28:28፤ w19.02 5 አን. 12
ረቡዕ፣ የካቲት 5
አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?—መዝ. 118:6
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰብዓዊ ገዢዎች በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ስደት አድርሰዋል። እነዚህ ሰዎች በተለያዩ የሐሰት ክሶች ቢወነጅሉንም በእኛ ላይ ስደት የሚያደርሱበት እውነተኛው ምክንያት ግን “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን [ለመታዘዝ]” መምረጣችን ነው። (ሥራ 5:29) በዚህ አቋማችን ምክንያት ሊሾፍብን፣ ለእስር ልንዳረግ አልፎ ተርፎም አካላዊ ጥቃት ሊሰነዘርብን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ስለሚረዳን፣ ስደት ሲደርስብን አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ ገርነት ማሳየታችንን እንቀጥላለን። በግዞት ወደ ባቢሎን የተወሰዱት ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ የተባሉ ሦስት ዕብራውያን የተዉትን ምሳሌ እንመልከት። ንጉሡ ለሠራው ምስል አምልኮ የማያቀርቡበትን ምክንያት ለንጉሡ በገርነት ነገሩት። ይሖዋ የፈቀደውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። (ዳን. 3:1, 8-28) ለአምላክ ያለንን ታማኝነት የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥመን የእነዚህን ሦስት ዕብራውያን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ትሑት በመሆን ይሖዋ እንደሚረዳን እንተማመናለን። (መዝ. 118:7) የሐሰት ክስ ለሚሰነዝሩብን ሰዎች ገርነትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ መልስ እንሰጣለን። (1 ጴጥ. 3:15) በተጨማሪም ከአፍቃሪው አባታችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ፈጽሞ ለድርድር አናቀርብም። w19.02 10-11 አን. 11-13
ሐሙስ፣ የካቲት 6
አይዟችሁ!—ዮሐ. 16:33
የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስላስገኘልን ተስፋ ማሰባችን ይበልጥ ደፋሮች እንድንሆን ይረዳናል። (ዮሐ. 3:16፤ ኤፌ. 1:7) ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት፣ ለቤዛው ያለንን አድናቆት የምናሳድግበት ልዩ አጋጣሚ እናገኛለን። በዚህ ወቅት ለመታሰቢያው በዓል የተዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማንበባችንና ከኢየሱስ ሞት ጋር በተያያዙ ክንውኖች ላይ ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን የጌታ ራት በዓልን ለማክበር በምንሰበሰብበት ወቅት ስለ ቂጣውና ስለ ወይን ጠጁ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች ስለሚወክሉት ወደር የለሽ መሥዋዕት ይበልጥ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳናል። ይሖዋና ኢየሱስ ስላደረጉልን ነገሮች ስናውቅ እንዲሁም እነሱ ያደረጉት ነገር እኛንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ስንገነዘብ ተስፋችን የሚጠናከር ከመሆኑም ሌላ እስከ መጨረሻው በድፍረት ለመጽናት እንገፋፋለን። (ዕብ. 12:3) ኢየሱስ በዛሬው ጊዜም በሰማይ ሊቀ ካህናት ሆኖ ለእኛ ሲማልድ እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ዕብ. 7:24, 25) በመሆኑም ለዚህ ያለንን ልባዊ አድናቆት ለማሳየት ኢየሱስ ባዘዘን መሠረት የሞቱን መታሰቢያ በዓል በታማኝነት ማክበር ይኖርብናል።—ሉቃስ 22:19, 20፤ w19.01 22 አን. 8፤ 23-24 አን. 10-11
ዓርብ፣ የካቲት 7
ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ በፈቃደኝነት የማቀርበውን የውዳሴ መባ በደስታ ተቀበል።—መዝ. 119:108
ይሖዋ ለሁላችንም እሱን የማወደስ መብት ሰጥቶናል። በስብሰባዎች ላይ የምንሰጠው ሐሳብ ለይሖዋ የምናቀርበው “የውዳሴ መሥዋዕት” አንዱ ክፍል ሲሆን ማንም ሰው በእኛ ፋንታ ይህን መሥዋዕት ሊያቀርብልን አይችልም። (ዕብ. 13:15) ሆኖም አምላክ በስብሰባዎች ላይ ከምንሰጠው ሐሳብ ጋር በተያያዘ ሁላችንም ተመሳሳይ መሥዋዕት እንድናቀርብ ይጠብቅብናል? በፍጹም! የጉባኤ ስብሰባን ከጓደኞችህ ጋር አብረህ እንደተገኘህበት ግብዣ አድርገህ ልትመለከተው ትችላለህ። በጉባኤህ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ግብዣ አዘጋጅተው ቢጠሩህና በግብዣው ላይ ቀለል ያለ ምግብ ይዘህ እንድትመጣ ቢጠይቁህ ምን ታደርጋለህ? ይህ በተወሰነ መጠን ሊያስጨንቅህ ቢችልም በግብዣው ላይ የተገኙት ሁሉ የሚወዱትን ነገር ይዘህ ለመሄድ አቅምህ የፈቀደውን ያህል እንደምታደርግ የታወቀ ነው። ጋባዣችን ይሖዋ፣ በስብሰባዎቻችን ላይ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦልናል። (መዝ. 23:5፤ ማቴ. 24:45) ሆኖም እያንዳንዳችን በስብሰባው ላይ የሆነች ነገር ይዘን ለመሄድ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ይደሰታል። እንግዲያው ጥሩ ዝግጅት ለማድረግና የቻልከውን ያህል ብዙ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ ካዘጋጀው ማዕድ መመገብ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን የሚጠቅም ስጦታ ይዘህ መሄድም ትችላለህ። w19.01 8 አን. 3፤ 13 አን. 20
ቅዳሜ፣ የካቲት 8
ሌሎች አማልክትን የሚከተሉ ሐዘናቸውን ያበዛሉ።—መዝ. 16:4
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሐሰት አምልኮ አብዛኛውን ጊዜ ልቅ የሆነ የፆታ ብልግናን ያካተተ ነበር። (ሆሴዕ 4:13, 14) በርካታ ሰዎች ኃጢአተኛ ለሆነው ሥጋቸው ማራኪ በሆነው እንዲህ ባለው አምልኮ መካፈል ያስደስታቸው ነበር። ሆኖም ይህ ዘላቂ ደስታ አላስገኘላቸውም። እንዲያውም ውጤቱ ፍጹም ተቃራኒ ነበር! ዳዊት “ሌሎች አማልክትን የሚከተሉ ሐዘናቸውን ያበዛሉ” በማለት ተናግሯል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ልጆችም በእነሱ ምክንያት ለአሰቃቂ መከራ ተዳርገዋል። (ኢሳ. 57:5) ይሖዋ እንዲህ ያለውን የጭካኔ ድርጊት ይጸየፋል! (ኤር. 7:31) በዘመናችንም ቢሆን አብዛኞቹ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች የፆታ ብልግናን አልፎ ተርፎም ግብረ ሰዶማዊነትን በቸልታ ያልፋሉ። ሆኖም ሰዎች ሥነ ምግባራዊ ነፃነት ብለው የሚያስቡት አካሄድ ያስከተለው ውጤት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው። (1 ቆሮ. 6:18, 19) እንዲህ ያለ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች ‘ሐዘናቸውን እያበዙ’ እንዳሉ እናንተም ሳታስተውሉ አትቀሩም። እንግዲያው ወጣቶች፣ በሰማይ ያለው አባታችሁ የሚላችሁን ስሙ። እሱን መታዘዛችሁ ራሳችሁን የሚጠቅማችሁ እንዴት እንደሆነ በሚገባ አስቡ። መጥፎ ድርጊት መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ ለማጤን ሞክሩ፤ ደግሞም መጥፎ ድርጊት መፈጸም የሚያስገኘው ጊዜያዊ ደስታ ድርጊቱ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም።—ገላ. 6:8፤ w18.12 27-28 አን. 16-18
እሁድ፣ የካቲት 9
እኔም ከአንቺ ጋር ግንኙነት አልፈጽምም።—ሆሴዕ 3:3
የአንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛ የፆታ ብልግና ከፈጸመ በደል የተፈጸመበት ክርስቲያን ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ያጋጥመዋል። ኢየሱስ ታማኝ የሆነው ወገን ፍቺ ለመፈጸምና ድጋሚ ለማግባት የሚያስችል መሠረት እንዳለው ተናግሯል። (ማቴ. 19:9) በሌላ በኩል ግን በደል የተፈጸመበት ወገን ይቅርታ ለማድረግ ሊወስን ይችላል። ይህ ውሳኔ ስህተት አይደለም። ሆሴዕ ጎሜርን መልሶ አምጥቷታል። ተመልሳ ከመጣች በኋላ ግን ከሌላ ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም አትችልም ነበር። ሆሴዕ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከጎሜር ጋር ‘ግንኙነት አልፈጸመም።’ (ሆሴዕ 3:1-3 ግርጌ) ከጊዜ በኋላ ሆሴዕ ከጎሜር ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ጀምሮ መሆን አለበት፤ ይህም አምላክ ሕዝቦቹን መልሶ ለመቀበልና ከእነሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለመቀጠል ያለውን ፈቃደኝነት ያንጸባርቃል። (ሆሴዕ 1:11፤ 3:4, 5) ይህ ታሪክ በዛሬው ጊዜ ላሉ ባለትዳሮች ምን ትምህርት ይዟል? አንድ ክርስቲያን በደል ከፈጸመበት የትዳር ጓደኛው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸሙን መቀጠሉ ለትዳር ጓደኛው ይቅርታ እንዳደረገለት ያሳያል። (1 ቆሮ. 7:3, 5) ሁለቱ ሰዎች ግንኙነት መፈጸማቸው ለፍቺ መሠረት የሆነው ነገር እንዲወገድ ያደርጋል። በመሆኑም ከዚያ በኋላ እርስ በርስ በመደጋገፍ አምላክ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። w18.12 13 አን. 13
ሰኞ፣ የካቲት 10
ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል።—ምሳሌ 22:3
በምናጠናበት ወቅት፣ የይሖዋ አስተሳሰብ ወደፊት በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አስቀድመን ማሰባችን ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጋችን በአፋጣኝ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ግራ እንዳንጋባ ይረዳናል። ዮሴፍ የጶጢፋር ሚስት ያቀረበቻቸውን ማባበያዎች ወዲያውኑ ውድቅ አድርጓል፤ ይህም ይሖዋ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ስለመሆን ያለውን አመለካከት አስቀድሞ እንዳሰበበት የሚያሳይ ነው። (ዘፍ. 39:8, 9) በተጨማሪም ለጶጢፋር ሚስት “እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” የሚል ምላሽ መስጠቱ የአምላክ ዓይነት አመለካከት እንዳዳበረ የሚጠቁም ነው። እናንተስ በዚህ ረገድ እንዴት ናችሁ? ለምሳሌ የሥራ ባልደረባችሁ ሊያሽኮረምማችሁ ቢሞክር አሊያም አንድ ሰው የብልግና ጽሑፍ ወይም ምስል ወደ ሞባይል ስልካችሁ ቢልክ ምን ታደርጋላችሁ? ይሖዋ እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ለማወቅ አስቀድመን ጥረት ካደረግንና ምን እርምጃ እንደምንወስድ ከወሰንን ሁኔታው ሲከሰት ቆራጥ አቋም መያዝ ቀላል ይሆንልናል። w18.11 25 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ የካቲት 11
በይሖዋ ሐሴት አደርጋለሁ።—ዕን. 3:18
አንዳንድ ምሁራን በዚህ ጥቅስ ላይ ያለው አገላለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “በጌታ በሐሴት እዘላለሁ፤ በአምላክ በደስታ እጨፍራለሁ” የሚል ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ። በእርግጥም በዕንባቆም ምዕራፍ 3 ከቁጥር 16 እስከ 19 ላይ ያለው ሐሳብ ለሁላችንም ትልቅ ማረጋገጫ ይሰጠናል! ይሖዋ አስደናቂ ተስፋዎችን ከመስጠት ባለፈ ታላቁን ዓላማውን ለመፈጸም ፈጣን እርምጃ እየወሰደ እንዳለ አረጋግጦልናል። የዕንባቆም መጽሐፍ የሚያስተላልፈው ዋነኛ መልእክት ‘በይሖዋ ታመኑ’ የሚል እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። (ዕን. 2:4) እንዲህ ያለውን እምነት ማዳበርና ይዘን መቀጠል የምንችለው የሚከተሉትን ነገሮች በማድረግ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ካጠናከርን ነው፦ (1) ያስጨነቀንንና ያሳሰበንን ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምንጊዜም በጸሎት መንገር፣ (2) ይሖዋ በቃሉ በኩል የሚያስተምረንን ትምህርትና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን ማንኛውንም መመሪያ በትኩረት መስማት፣ (3) ይሖዋን በእምነትና በትዕግሥት መጠበቅ። ዕንባቆምም ያደረገው ይህንኑ ነው። መጽሐፉን የጀመረው በእሮሮ ቢሆንም የደመደመው በደስታና በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት በመግለጽ ነው። እኛም ይሖዋ ልክ እንደ አባት እቅፍ እንዳደረገን እንዲሰማን ከፈለግን ዕንባቆም የተወልንን ግሩም ምሳሌ እንከተል! በጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ከዚህ የበለጠ መጽናኛ ከየት ይገኛል? w18.11 17 አን. 18-19
ረቡዕ፣ የካቲት 12
በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ [ክርስቶስ] ለሁሉም ሞቷል።—2 ቆሮ. 5:15
እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ እንደሚወዳቸው እርግጠኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው አንዱ ምክንያት የሚከተለው ነው፦ መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል” ይላል። (ዮሐ. 3:16) ኢየሱስም ቢሆን ሕይወቱን ለእኛ በመስጠት ታላቅ ፍቅር አሳይቶናል! ኢየሱስ ያሳየን ፍቅር ኃይል ይሰጠናል። የአምላክ ቃል ‘መከራም ሆነ ጭንቀት ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን እንደማይችል’ ይናገራል። (ሮም 8:35, 38, 39) አካላችንን የሚያዝሉ፣ ስሜታችንን የሚደቁሱ ወይም መንፈሳዊነታችንን የሚያዳክሙ ችግሮች ሲያጋጥሙን የክርስቶስ ፍቅር ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 5:14) ድንገተኛ አደጋ፣ ስደት አሊያም ተስፋ የሚያስቆርጥ ወይም የሚያስጨንቅ ሁኔታ ሲያጋጥመንም እንኳ የክርስቶስ ፍቅር ያበረታናል፤ እንዲሁም በሕይወት ለመቀጠል የሚያነሳሳ ጥንካሬ ይሰጠናል። w18.09 14 አን. 8-9
ሐሙስ፣ የካቲት 13
በእውነትህ እሄዳለሁ።—መዝ. 86:11
በእውነት ጎዳና ለመሄድ ይሖዋ የተናገራቸውን ነገሮች በሙሉ መቀበልና መታዘዝ አለብን። በሕይወታችን ውስጥ ለእውነት ቅድሚያውን መስጠትና አኗኗራችንን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ማስማማት ይኖርብናል። ዳዊት እንዳደረገው እኛም በአምላክ እውነት መሄዳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። አለዚያ ለእውነት ስንል በከፈልነው ዋጋ መቆጨት ልንጀምር አልፎ ተርፎም ከከፈልነው ነገር ላይ የተወሰነውን መልሰን ለመውሰድ ልንፈተን እንችላለን። በመሆኑም መላውን የእውነት ቃል አጥብቀን መያዛችን አስፈላጊ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መካከል የፈለግነውን ተቀብለን ያልፈለግነውን መተው እንደማንችል እንገነዘባለን። ምክንያቱም ይሖዋ ‘በእውነት ሁሉ’ እንድንሄድ ይጠብቅብናል። (ዮሐ. 16:13) ቀስ በቀስ ከእውነት እንዳንወሰድ ጊዜያችንን በጥበብ መጠቀም አለብን። ጠንቃቆች ካልሆንን በመዝናናት፣ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ እንቅስቃሴ በመካፈል፣ ኢንተርኔት በመቃኘት ወይም ቴሌቪዥን በመመልከት ከልክ ያለፈ ጊዜ ማሳለፍ ልንጀምር እንችላለን። እነዚህ ነገሮች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም ቀደም ሲል ለግል ጥናትና ለሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እናውል የነበረውን ጊዜ ሊሻሙብን ይችላሉ። w18.11 10 አን. 7-8
ዓርብ፣ የካቲት 14
ነፍሴን አረጋጋኋት፤ ደግሞም ጸጥ አሰኘኋት።—መዝ. 131:2
በሕይወታችን ውስጥ ያልተጠበቀ ለውጥ ሲያጋጥመን ስጋት ሊያድርብንና ልንጨነቅ እንችላለን። (ምሳሌ 12:25) አልፎ ተርፎም ለውጡን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ነፍሳችንን ‘ማረጋጋትና ጸጥ ማሰኘት’ የምንችለው እንዴት ነው? (መዝ. 131:1-3) አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን፣ አእምሯችንን የሚጠብቀው “የአምላክ ሰላም” ያለውን የማረጋጋት ኃይል በገዛ ሕይወታችን መመልከት እንችላለን። (ፊልጵ. 4:6, 7) በመሆኑም በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት የምንጥር ከሆነ የአምላክ ሰላም መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ያለንን ቁርጠኝነት እንድናጠናክርና ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። የአምላክ መንፈስ ልባችንን ከማረጋጋት ባለፈ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ በሚያበረታቱን ጥቅሶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንድንችል ይረዳናል።—ዮሐ. 14:26, 27፤ w18.10 27 አን. 2፤ 28 አን. 5, 8
ቅዳሜ፣ የካቲት 15
እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ።—ዘካ. 8:16
በሰው ልጆች ሕይወት ላይ እጅግ አስከፊ መዘዝ ያስከተለ ፈጠራ ምንድን ነው? ውሸት ነው! ውሸት ማለት አንድን ሰው ለማታለል ሲባል ሆን ተብሎ የሚነገር እውነት ያልሆነ ነገር ማለት ነው። ታዲያ የመጀመሪያውን ውሸት የፈለሰፈው ወይም የተናገረው ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ “የውሸት አባት” ዲያብሎስ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 8:44) ዲያብሎስ የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረው መቼ ነው? ዲያብሎስ የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት ውስጥ ነው። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋን ፈጣሪያቸው ባዘጋጀላቸው ገነት ውስጥ ተደስተው ይኖሩ ነበር። አምላክ እነዚህን ባልና ሚስት “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” እንዳይበሉ፣ ከበሉ ግን እንደሚሞቱ ነግሯቸው ነበር። ሰይጣን ይህን ትእዛዝ የሚያውቅ ቢሆንም በእባብ አማካኝነት ሔዋንን “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም” አላት፤ ይህ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የተነገረው የመጀመሪያው ውሸት ነው። አክሎም “አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው” በማለት ነገራት።—ዘፍ. 2:15-17፤ 3:1-5፤ w18.10 6 አን. 1-2
እሁድ፣ የካቲት 16
ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው፤ አምላክን ያያሉና።—ማቴ. 5:8
ልባችን ንጹሕ እንዲሆን አስተሳሰባችንም ሆነ ምኞታችን ንጹሕና ከርኩሰት የጸዳ መሆን አለበት። ይሖዋ አምልኳችንን እንዲቀበለው ከፈለግን እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮ. 4:2፤ 1 ጢሞ. 1:5) ይሁንና ‘ማንም ሰው አምላክን አይቶ በሕይወት መኖር እንደማይችል’ የታወቀ ነው፤ ታዲያ ልባቸው ንጹሕ የሆነ ሰዎች “አምላክን ያያሉ” ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ዘፀ. 33:20) “ያያሉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በዓይነ ሕሊና ማየት፣ መረዳት፣ ማወቅ” ተብሎም ሊፈታ ይችላል። በመሆኑም አምላክን ‘በልባቸው ዓይኖች’ የሚያዩት የእሱን ማንነትና ባሕርያት በሚገባ የሚያውቁ ሰዎች ናቸው። (ኤፌ. 1:18) የይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች፣ የአምላክን ባሕርያት ከማወቅ በተጨማሪ እሱ በግለሰብ ደረጃ የሚያደርግላቸውን እርዳታ ስለሚመለከቱ ‘አምላክን ያዩታል።’ (ኢዮብ 42:5) ልባቸው ንጹሕ የሆነ ሰዎች ‘አምላክን የሚያዩበት’ ሌላም መንገድ አለ፤ ይህም አምላክ ንጹሕ ሆነው ለመኖርና እሱን በታማኝነት ለማገልገል ለሚጥሩ ሰዎች ባዘጋጃቸው አስደናቂ በረከቶች ላይ ‘የልባቸው ዓይኖች’ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነው። w18.09 20 አን. 13, 15-16
ሰኞ፣ የካቲት 17
ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኝ።—ምሳሌ 4:7
ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር ማድረግ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። ጥበብ የሚመሠረተው በእውቀት ላይ ነው፤ ያም ቢሆን አንድን እውነታ ከመረዳት ያለፈ ነገርን ይጨምራል፤ ጥበብ የሚገለጸው በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ነው። ጉንዳኖች እንኳ ጥበብ እንዳላቸው ያሳያሉ። ጉንዳኖች ምግባቸውን በበጋ ወቅት ማዘጋጀታቸው በደመ ነፍስ ጥበበኞች እንደሆኑ ይጠቁማል። (ምሳሌ 30:24, 25) “የአምላክ ጥበብ” የተባለው ክርስቶስም ምንጊዜም የሚያደርገው አባቱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ነው። (1 ቆሮ. 1:24፤ ዮሐ. 8:29) አምላክ ትክክለኛውን ውሳኔ በማድረግና ውሳኔያችንን በተግባር በማዋል መካከል ልዩነት እንዳለ ያውቃል። እንዲሁም ምንጊዜም ትሕትና የሚያሳዩና ትክክል እንደሆነ የሚያውቁትን ነገር በተግባር የሚያውሉ ሰዎችን ይባርካል። (ማቴ. 7:21-23) እንግዲያው ትሕትና ለማሳየት ጥረት እናድርግ፤ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ሌሎች የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ይሖዋን በትሕትና እንዲያገለግሉ እናበረታታለን። ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር ማድረግ ጊዜና ትዕግሥት ይጠይቃል፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጋችን ትሕትና እንዳለን ያሳያል። ትሕትና ደግሞ አሁንም ሆነ ለዘላለም ደስተኞች እንድንሆን ያደርገናል። w18.09 7 አን. 18
ማክሰኞ፣ የካቲት 18
እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ [እንዲሁም] ራሱን ከሌላ ሰው ጋር [አያወዳድር]።—ገላ. 6:4
የፈጣሪ ዓላማ፣ ፍጹም የሆኑ ሰዎች የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም አብረውት እንዲሠሩ ነበር። በእርግጥ በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች ፍጹማን አይደሉም፤ ያም ቢሆን ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከይሖዋ ጋር በየዕለቱ መሥራት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በመካፈል “ከአምላክ ጋር አብረን [መሥራት]” እንችላለን። (1 ቆሮ. 3:5-9) የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከፍ አድርጎ በሚመለከተው በዚህ ሥራ፣ ከእሱ ጋር አብረን ለመሥራት ብቁ ሆነን መቆጠራችን ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ እስቲ አስበው! እርግጥ ነው፣ ከይሖዋ ጋር መሥራት የምንችለው ምሥራቹን በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረግ ብቻ አይደለም። ይህን ማድረግ የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ፤ እነዚህም ቤተሰቦቻችንንና የእምነት አጋሮቻችንን መርዳት፣ እንግዳ ተቀባይ መሆን፣ በቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ላይ ለመካፈል ራስን ማቅረብ እንዲሁም አገልግሎታችንን ማስፋት ናቸው። (ቆላ. 3:23) ይሁን እንጂ በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምንችለውን ነገር ሌሎች ከሚያከናውኑት ጋር ማወዳደር የለብንም። የእያንዳንዱ ሰው ዕድሜ፣ ጤንነት፣ ያለበት ሁኔታ እንዲሁም አቅም እንደሚለያይ እናስታውስ። w18.08 23 አን. 1-2
ረቡዕ፣ የካቲት 19
በተስፋ ጠብቀው! ያላንዳች ጥርጥር ይፈጸማልና።—ዕን. 2:3
ይሖዋ ዕንባቆምን ለጥያቄዎቹ መልስ እንደሚሰጠው አረጋግጦለታል። ዕንባቆምን ያስጨነቁት ነገሮች በሙሉ በቅርቡ መፍትሔ ያገኛሉ። አምላክ ነቢዩን “በትዕግሥት ጠብቅ፤ በእኔ ታመን። የሚዘገይ ቢመስልህም ለጥያቄህ መልስ እሰጣለሁ!” ያለው ያህል ነበር። ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች የሚፈጽምበትን ጊዜ እንደወሰነ ለዕንባቆም አስታውሶታል። በተጨማሪም ይህን ጊዜ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ መክሮታል። ዕንባቆም እንዲህ በማድረጉ ፈጽሞ አይቆጭም። ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቃችንና እሱ የሚነግረንን ነገር በትኩረት ማዳመጣችን በእሱ ላይ ያለንን እምነት የሚጨምርልን ከመሆኑም ሌላ መከራና ችግር ቢያጋጥመንም ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረን ይረዳናል። ኢየሱስ፣ “ጊዜያትንና ወቅቶችን” በተመለከተ አምላክ ለእኛ ያላሳወቀን ነገር እንዳለ ተናግሯል፤ በመሆኑም በዚያ ላይ ከማተኮር ይልቅ የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ወደር በማይገኝለት በይሖዋ ላይ እምነት እንድንጥል መክሮናል። (ሥራ 1:7) እንግዲያው ተስፋ አንቁረጥ፤ ከዚህ ይልቅ ትሕትና፣ እምነትና ትዕግሥት እያሳየን ይሖዋን እንጠባበቅ። እስከዚያው ድረስ ግን ጊዜያችንን አቅማችን የፈቀደውን ያህል ይሖዋን ለማገልገል እንጠቀምበት።—ማር. 13:35-37፤ ገላ. 6:9፤ w18.11 16 አን. 13-14
ሐሙስ፣ የካቲት 20
አምላክ ማንንም ሰው ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ማለት እንደማይገባኝ ገልጦልኛል።—ሥራ 10:28
በዘመኑ እንደነበሩት ሌሎች አይሁዳውያን ሁሉ ጴጥሮስም አሕዛብ ርኩስ እንደነበሩ ከልጅነቱ አንስቶ ያምን ነበር። ይሁን እንጂ ይህን አመለካከቱን እንዲያስተካክል የሚያደርጉ ነገሮች አጋጠሙት። ለምሳሌ ያህል ጴጥሮስ አንድ ራእይ ተመልክቶ ነበር። (ሥራ 10:9-16) እንደ ጴጥሮስ ሁሉ እኛም በውስጣችን ጭፍን ጥላቻ መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ራሳችንን በሚገባ መመርመር እንዲሁም ሌሎች የሚሰጡንን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን አለብን። ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን? ልባችንን ወለል አድርገን ከከፈትን ልባችን በጭፍን ጥላቻ ፋንታ በፍቅር ይሞላል። (2 ቆሮ. 6:11-13) የአንተ ዓይነት ዘር፣ ብሔር፣ አገር፣ ጎሳ ወይም ቋንቋ ካላቸው ሰዎች ጋር ብቻ መቀራረብ ይቀናሃል? ከሆነ ልብህን ወለል አድርገህ መክፈት ይኖርብሃል። ከአንተ የተለየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸውን ወንድሞች አብረውህ እንዲያገለግሉ ለምን አትጠይቃቸውም? ቤትህ ልትጋብዛቸውስ ትችል ይሆን? (ሥራ 16:14, 15) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ልብህ በፍቅር ስለሚሞላ ለጭፍን ጥላቻ ቦታ አይኖረውም። w18.08 9 አን. 3, 6፤ 10 አን. 7
ዓርብ፣ የካቲት 21
እንቅፋት አትሁኑ።—1 ቆሮ. 10:32
አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም የሚያንጸባርቀውን ምግባር አጥብቀው እንደማይቃወሙ የሚታይባቸው መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በግብዣዎች ላይ ሲገኙ ከክርስቲያኖች የማይጠበቅ ጭፈራ የሚጨፍሩ ከመሆኑም ሌላ ተገቢ ያልሆነ ምግባር ያሳያሉ። በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚያወጧቸው ፎቶዎችና የሚጽፏቸው አስተያየቶች ከአንድ መንፈሳዊ ሰው የማይጠበቁ ናቸው። በዚህ የተነሳ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል መልካም ምግባር ለማሳየት ጥረት በሚያደርጉ እኩዮቻቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። (1 ጴጥ. 2:11, 12) በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ ‘የሥጋ ምኞትን፣ የዓይን አምሮትንና ኑሮዬ ይታይልኝ ማለትን’ ለማበረታታት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። (1 ዮሐ. 2:16) እኛ ግን የይሖዋ ንብረት ስለሆንን “ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል ትተን አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ፣ በጽድቅና ለአምላክ በማደር እንድንኖር” ማበረታቻ ተሰጥቶናል። (ቲቶ 2:12) አነጋገራችን፣ ከምግብና ከመጠጥ ጋር በተያያዘ ያለን ልማድ፣ አለባበሳችንና አጋጌጣችን፣ የሥራ ሥነ ምግባራችን እንዲሁም የምናደርገው ሌላ ማንኛውም ነገር ይሖዋን ብቻ የምናመልክ ሰዎች መሆናችንን በግልጽ የሚያሳይ መሆን አለበት። w18.07 25 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ የካቲት 22
የእኛም ዓይኖች ሞገስ እስኪያሳየን ድረስ ወደ አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለከታሉ።—መዝ. 123:2
ምሳሌያዊ ዓይናችን ምንጊዜም በይሖዋ ላይ እንዲያተኩር የምናደርግ ከሆነ የሌሎች ድርጊት እንዲያስመርረን ወይም ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና እንዲያበላሽብን አንፈቅድም። በተለይ ደግሞ እንደ ሙሴ በአምላክ ድርጅት ውስጥ የተወሰነ ኃላፊነት ካለን እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ሁላችንም ‘በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችንን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተን መሥራት’ ያለብን ቢሆንም ይሖዋ በእያንዳንዳችን ላይ የሚፈርደው ድርቅ ባለ አንድ መሥፈርት ላይ ተመሥርቶ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። (ፊልጵ. 2:12) የበለጠ ኃላፊነት በተሰጠን መጠን ተጠያቂነታችንም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። (ሉቃስ 12:48) ይሖዋን ከልባችን የምንወድ ከሆነ ግን ምንም ነገር ሊያደናቅፈን ወይም ከእሱ ፍቅር ሊለየን አይችልም። (መዝ. 119:165፤ ሮም 8:37-39) በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ዓይናችንን ምንጊዜም ‘በሰማያት ዙፋን ላይ ወደተቀመጠው’ በማንሳት የእሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት እናድርግ። የሌሎች ድርጊት ከይሖዋ ጋር በመሠረትነው ዝምድና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ፈጽሞ አንፍቀድ። w18.07 16 አን. 19-20
እሁድ፣ የካቲት 23
ሰዎች . . . አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።—ማቴ. 5:16
የይሖዋ ሕዝቦች እያደረጉ ያሉትን እድገት መመልከት ምንኛ አስደሳች ነው! በ2017 በየወሩ ከ10,000,000 የሚበልጡ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንተናል። ይህም የአምላክ አገልጋዮች ብርሃናቸውን እያበሩ እንዳሉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው! በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ለእውነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም ለማሰብ እንሞክር። እነዚህ ሰዎች፣ አምላክ ቤዛውን በማዘጋጀት ስላሳየው ፍቅር ተምረዋል። (1 ዮሐ. 4:9) በዓለም ዙሪያ የምንኖር የይሖዋ ምሥክሮች የምንናገረው ቋንቋ የተለያየ ነው። ይህ መሆኑ ግን አባታችንን ይሖዋን በአንድነት ከማወደስ አያግደንም። (ራእይ 7:9) የአፍ መፍቻ ቋንቋችንና የምንኖርበት ቦታ ቢለያይም ሁላችንም “በዚህ ዓለም ውስጥ እንደ ብርሃን አብሪዎች” ማብራት እንችላለን። (ፊልጵ. 2:15) በየጊዜው እያደረግን ያለነው እድገት፣ በመካከላችን ያለው አንድነት እንዲሁም ምንጊዜም ነቅተን ለመኖር የምናደርገው ጥረት ለይሖዋ ክብር ያመጣል። w18.06 21 አን. 1-3
ሰኞ፣ የካቲት 24
ረቢ፣ ብላ እንጂ።—ዮሐ. 4:31
ኢየሱስ በሚያደርገው መንፈሳዊ ውይይት ተጠምዶ ስለነበር ረሃቡን ማስታገስ በኋላ ሊደርስ የሚችል ጉዳይ እንደሆነ ተሰምቶታል። ኢየሱስ፣ ለአንዲት ሳምራዊትም ቢሆን ምሥራቹ መሰበኩ የአባቱ ፈቃድ መሆኑን ያውቅ ነበር፤ ይህ ሥራ ለእሱ እንደ ምግብ ነበር። (ዮሐ. 4:32-34) ያዕቆብና ዮሐንስ ግን ኢየሱስ የሰጠው ትምህርት በደንብ አልገባቸውም። ከኢየሱስ ጋር ሆነው በሰማርያ እያለፉ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ማደሪያ ለማግኘት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ። ሆኖም ሳምራውያኑ ሊቀበሏቸው ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ያዕቆብና ዮሐንስ በዚህ እጅግ በመበሳጨታቸው እሳት ከሰማይ አውርደው መንደሯን ለማጥፋት ሐሳብ አቀረቡ። ኢየሱስ ግን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጣቸው። (ሉቃስ 9:51-56) በእንግድነት ሊቀበሏቸው ፈቃደኛ ያልሆኑት፣ የትውልድ አካባቢያቸው በሆነው በገሊላ የሚኖሩ ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ ያዕቆብና ዮሐንስ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አያቀርቡ ይሆናል። ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ያለ የጥላቻ ስሜት እንዲያሳዩ ያደረጋቸው ለሰማርያ ሰዎች የነበራቸው ጭፍን አመለካከት ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ የሰበከላቸው በርካታ ሳምራውያን ምሥራቹን እንደተቀበሉ ሲያይ ከዚያ ቀደም በቁጣ የተናገረው ነገር አሳፍሮት መሆን አለበት።—ሥራ 8:14, 25፤ w18.06 10-11 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ የካቲት 25
ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁ . . . ጸንታችሁ ቁሙ።—ኤፌ. 6:14
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደ ቀበቶ በሚገባ ከታጠቅን፣ ከዚህ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ እውነት ለመናገር እንነሳሳለን። ለመሆኑ መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን ከሚጠቀምባቸው በጣም ውጤታማ መሣሪያዎች አንዱ ውሸት ነው። ውሸት፣ ለተናጋሪውም ሆነ የተነገረውን ለሚያምነው ሰው ጎጂ ነው። (ዮሐ. 8:44) ስለዚህ ፍጽምና የሚጎድለን ሰዎች ብንሆንም እንኳ በተቻለን መጠን ውሸት ላለመናገር እንጠነቀቃለን። (ኤፌ. 4:25) በእርግጥ ይህን ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። የአሥራ ስምንት ዓመቷ አቢጋኤል እንዲህ ብላለች፦ “እውነት መናገር ሁልጊዜ ጠቃሚ ላይመስል ይችላል፤ በተለይ ደግሞ መዋሸት ከአንድ ችግር ለማምለጥ የሚያስችል በሚሆንበት ጊዜ እውነቱን መናገር ከባድ ይሆናል።” ታዲያ ምንጊዜም ቢሆን እውነቱን ለመናገር የሚያነሳሳን ምንድን ነው? የ23 ዓመት ወጣት የሆነችው ቪክቶሪያ እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ስንናገርና ለምናምንባቸው ነገሮች ጥብቅና ስንቆም ሌሎች ሊያስቸግሩን ይችላሉ። ሆኖም የምናገኘው ጥቅም ምንጊዜም የላቀ ነው፦ በራስ የመተማመን ስሜታችን ይጨምራል፤ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንቀርባለን እንዲሁም የሚወዱንን ሰዎች አክብሮት እናተርፋለን።” በእርግጥም ምንጊዜም ‘ወገባችንን በእውነት ቀበቶ መታጠቃችን’ የሚክስ ነው። w18.05 28 አን. 3, 5
ረቡዕ፣ የካቲት 26
ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።—ማቴ. 24:42
ይህ አስቸጋሪ ዘመን እየተባባሰ በሄደ መጠን ሁላችንም ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል። ይሖዋ በትክክለኛው ጊዜ እርምጃ እንደሚወስድ ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለውም። (ማቴ. 24:42-44) እስከዚያው ድረስ ግን ምንጊዜም ንቁ ሆነን በትዕግሥት እንጠባበቅ። የአምላክን ቃል በየዕለቱ እናንብብ፤ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች እንሁን። (1 ጴጥ. 4:7) ምንጊዜም ነቅተው በመጠበቅና ብርሃናቸውን በማብራት ደስታ ያገኙ ወንድሞችና እህቶች ከተዉት ግሩም አርዓያ ትምህርት እንውሰድ። በይሖዋ አገልግሎት ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ። ለሌሎች ደግነት አሳዩ፤ እንዲሁም ከእምነት አጋሮቻችሁ ጋር ጊዜ አሳልፉ። ይህን ማድረጋችሁ ታላቅ ደስታ ያስገኝላችኋል፤ ጊዜውም ሳታስቡት ያልፋል። (ኤፌ. 5:16) ፍጽምና የሌለን ሰዎች መሆናችን ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዳናገለግል እንደማያግደን ማወቅ የሚያበረታታ ነው። ደግሞም ይሖዋ እኛን ለመርዳት ሲል “ሰዎችን” ይኸውም የጉባኤ ሽማግሌዎችን ‘ስጦታ አድርጎ ሰጥቶናል።’ (ኤፌ. 4:8, 11, 12) እንግዲያው የጉባኤ ሽማግሌዎች እረኝነት ሲያደርጉላችሁ፣ ከሚሰጧችሁ ጥበብ ያዘለ ምክር ጥቅም ለማግኘት ጥረት አድርጉ። w18.06 24-25 አን. 15-18
ሐሙስ፣ የካቲት 27
ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ።—ዮሐ. 15:10
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “በፍቅሬ ኑሩ” ብሏቸዋል። እንዲህ ያላቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለዓመታት የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ሆኖ መኖር ጽናት ይጠይቃል። ኢየሱስ ከዮሐንስ 15:4-10 ባሉት ጥቂት ቁጥሮች ላይ ‘መኖር’ የሚለውን ቃል በተለያየ አገባቡ ደጋግሞ በመጠቀም የጽናትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። በክርስቶስ ፍቅር መኖርና እሱን ማስደሰት እንደምንፈልግ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ትእዛዛቱን በመጠበቅ ነው። በቀላል አነጋገር ኢየሱስ ‘ታዘዙኝ’ እያለን ነው። ደግሞም ኢየሱስ እንድናደርግ የጠየቀን እሱ ራሱ ያደረገውን ነገር ነው፤ “እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ [እኖራለሁ]” ብሏል። (ዮሐ. 15:10) ኢየሱስ ግሩም አርዓያ ትቶልናል። (ዮሐ. 13:15) ኢየሱስ ሄደን እንድንሰብክ የሰጠንን ተልእኮ ስንፈጽም ለአምላክም ፍቅር እንዳለን እናሳያለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ የሰጣቸው ትእዛዛት ምንጭ ይሖዋ ነው። (ማቴ. 17:5፤ ዮሐ. 8:28) ለይሖዋና ለኢየሱስ ፍቅር ስናሳይ ደግሞ እነሱም በምላሹ በፍቅራቸው እንድንኖር ያደርጉናል። w18.05 18 አን. 5-7
ዓርብ፣ የካቲት 28
የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።—ምሳሌ 21:5
ወጣቶች ከትምህርት፣ ከሥራና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውሳኔዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ግልጽ የሆኑ ግቦች ካሉህ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። በልጅነትህ ጥሩ ግቦችን ማውጣትህ በሕይወትህ ይበልጥ ስኬታማ እንድትሆን ይረዳሃል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከልባችን እናደንቃቸዋለን። እነዚህ ወጣቶች የሚያደርጉትን ሁሉ ለይሖዋ አደራ በመስጠት በቲኦክራሲያዊ ግቦች ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመራሉ። ትዳርንና ልጆች መውለድን ጨምሮ በሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ሁሉ የይሖዋን መመሪያዎች ይከተላሉ፤ በሕይወታቸውም ደስተኞች ናቸው። ሰለሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በይሖዋ ዓይን ውድ ናቸው፤ ይሖዋ በጣም የሚወዳቸው ከመሆኑም ሌላ ጥበቃው፣ አመራሩና በረከቱ አይለያቸውም። w18.04 26 አን. 7፤ 27 አን. 9
ቅዳሜ፣ የካቲት 29
እርስ በርሳችሁ [ተዋደዱ]፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።—ዮሐ. 13:34
ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ እንደ ዓምድ ነበር። ስለ ኢየሱስ አገልግሎት የሚናገረው ትኩረት የሚስብ የወንጌል ዘገባው በጥንት ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖች የብርታት ምንጭ ሆኗል። እንዲያውም የእውነተኛዎቹ ደቀ መዛሙርት መለያ ፍቅር እንደሆነ የሚገልጸው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ የሚገኘው በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው። (ዮሐ. 13:35) ዮሐንስ የጻፋቸው ሦስት ደብዳቤዎችም ሌሎች ውድ እውነቶችን ይዘዋል። በፈጸምነው ኃጢአት ምክንያት በበደለኝነት ስሜት በምንሠቃይበት ጊዜ “የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ [እንደሚያነጻን]” የሚገልጸውን ሐሳብ ስናነብ እፎይታ አናገኝም? (1 ዮሐ. 1:7) ልባችን ሁልጊዜ የሚኮንነን ከሆነ ደግሞ “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ” እንደሆነ ስናነብ በአመስጋኝነት ስሜት ከመሞላታችን የተነሳ እንባ አይተናነቀንም? (1 ዮሐ. 3:20) በተጨማሪም “አምላክ ፍቅር ነው” ብሎ የጻፈው ዮሐንስ ብቻ ነው። (1 ዮሐ. 4:8, 16) በሁለተኛና በሦስተኛ ደብዳቤዎቹ ላይ ደግሞ “በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ” ላሉ ክርስቲያኖች ያለውን አድናቆት ገልጿል።—2 ዮሐ. 4፤ 3 ዮሐ. 3, 4፤ w18.04 18 አን. 14-15