የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es20 ገጽ 118-128
  • ታኅሣሥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታኅሣሥ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 1
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 3
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 5
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 6
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 11
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 12
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 13
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 16
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 17
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 18
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 19
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 20
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 21
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 25
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 27
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
es20 ገጽ 118-128

ታኅሣሥ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 1

በጣም አዘነላቸው።—ማር. 6:34

ኢየሱስን እንድንወደው ከሚያደርጉን ባሕርያት መካከል አንዱ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚረዳ መሆኑ ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ‘ደስ ከሚላቸው ጋር ይደሰት’ እንዲሁም ‘ከሚያለቅሱ ጋር ያለቅስ ነበር።’ (ሮም 12:15) ለምሳሌ ያህል፣ 70ዎቹ ደቀ መዛሙርት የተሰጣቸውን የስብከት ተልእኮ በተሳካ ሁኔታ ከተወጡ በኋላ የተሰማቸውን ደስታ ሲገልጹለት ኢየሱስ “በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት [አድርጓል]።” (ሉቃስ 10:17-21) በሌላ በኩል ደግሞ የአልዓዛር ሞት በሚወዱት ሰዎች ላይ ያስከተለውን ሐዘን ሲመለከት ‘እጅግ አዝኖና ተረብሾ’ ነበር። (ዮሐ. 11:33) ይህ ፍጹም ሰው ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ይህን ያህል ምሕረትና ርኅራኄ ሊያሳይ የቻለው እንዴት ነው? በዋነኝነት ሰዎችን ስለሚወድ ነው። ኢየሱስ ‘በተለይ በሰው ልጆች እጅግ ይደሰት ነበር።’ (ምሳሌ 8:31) ለሰው ልጆች የነበረው እንዲህ ያለ ፍቅር እነሱ የሚያስቡበትን መንገድ ጠንቅቆ እንዲያውቅ አስችሎታል። ሐዋርያው ዮሐንስ ኢየሱስን አስመልክቶ ሲናገር “በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ [ነበር]” ብሏል።—ዮሐ. 2:25፤ w19.03 20 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2

እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።—ኢዮብ 1:11

ሰይጣን በኢዮብ ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን ሰንዝሮበታል። በንብረቱ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሀብቱንና አገልጋዮቹን አሳጥቶታል፤ እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ የነበረውን መልካም ስም እንዲያጣ አድርጓል። በቤተሰቡ ላይ ጥቃት በመሰንዘር የሚወዳቸውን አሥር ልጆቹን ገድሎበታል። ከዚያም በአካሉ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ ክፉኛ በሚያሠቃይ እባጭ መቶታል። የኢዮብ ሚስት በጭንቀትና በሐዘን ከመዋጧ የተነሳ አምላክን ሰድቦ እንዲሞት በመገፋፋት ኢዮብን ተስፋ ልታስቆርጠው ሞከረች። ኢዮብ ራሱም ቢሆን ሞቱን ተመኝቶ ነበር። ያም ሆኖ ንጹሕ አቋሙን አላጎደፈም። በመሆኑም ሰይጣን ጥቃት የሚሰነዝርበት ሌላ ዘዴ ቀየሰ። በዚህ ጊዜ የተጠቀመው የኢዮብ ወዳጆች የሆኑ ሦስት ሰዎችን ነበር። እነዚህ ሰዎች ከኢዮብ ጋር ለቀናት ቢቆዩም አንድም የሚያጽናና ቃል አልተናገሩም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብን ጭካኔ በተሞላ መንገድ ነቅፈውታል። እየደረሰበት ካለው መከራ በስተጀርባ ያለው አምላክ እንደሆነና እሱ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ ወይም አለመጠበቁ ለአምላክ ግድ እንደማይሰጠው ገለጹ። ይባስ ብለው ደግሞ ኢዮብ ክፉ ሰው እንደሆነና ለፈጸማቸው መጥፎ ነገሮች የእጁን እያገኘ እንዳለ የሚጠቁም ነገር ተናገሩ!—ኢዮብ 1:13-22፤ 2:7-11፤ 15:4, 5፤ 22:3-6፤ 25:4-6፤ w19.02 4 አን. 7-8

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 3

ይሖዋን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው።—መዝ. 111:10

ፍርሃት፣ ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋን እንዳናሳዝን መፍራታችን ተገቢ ነው። አዳምና ሔዋን እንዲህ ያለውን ፍርሃት አዳብረው ቢሆን ኖሮ በይሖዋ ላይ አያምፁም ነበር። ካመፁ በኋላ ዓይኖቻቸው ተከፈቱ፤ በሌላ አባባል ኃጢአተኛ መሆናቸውን ሙሉ በሙሉ ተገነዘቡ። ለልጆቻቸው ኃጢአትንና ሞትን ከማውረስ ውጭ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። ያሉበትን ሁኔታ ማየት ወይም መረዳት ስለቻሉ ራቁታቸውን መሆናቸው አሳፈራቸው፤ በመሆኑም ሰውነታቸውን የሚሸፍኑበት ነገር ሠሩ። (ዘፍ. 3:7, 21) ለይሖዋ ተገቢ የሆነ ፍርሃት ልናዳብር እንደሚገባ የታወቀ ነው፤ ለሞት ግን ከልክ ያለፈ ፍርሃት ሊኖረን አይገባም። ይሖዋ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት መንገድ አዘጋጅቶልናል። ኃጢአት ብንሠራም ከልብ ንስሐ የምንገባ ከሆነ ይሖዋ ይቅርታ ያደርግልናል። በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ካለን በደላችንን ይቅር ይለናል። እምነት እንዳለን የምናሳይበት ዋነኛው መንገድ ደግሞ ራሳችንን ለአምላክ መወሰንና መጠመቅ ነው።—1 ጴጥ. 3:21፤ w19.03 5-6 አን. 12-13

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4

ከየፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በስተቀር አንድም የተረፈ ሰው አልነበረም።—ዘኁ. 26:65

እስራኤላውያን አድናቆት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች ነበሯቸው። ይሖዋ በግብፅ ላይ አሥር መቅሰፍቶችን በማምጣት ከባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። ከዚያም መላውን የግብፅ ሠራዊት ቀይ ባሕር ውስጥ በማስጠም ከጥፋት ታድጓቸዋል። እስራኤላውያን ለተደረገላቸው ነገር በጣም አመስጋኝ ከመሆናቸው የተነሳ የድል መዝሙር በመዘመር ይሖዋን አወድሰዋል። ታዲያ እንዲህ ያለውን የአድናቆት ስሜት ይዘው ቀጥለው ይሆን? እስራኤላውያን ከዚህ በፊት አጋጥመዋቸው የማያውቁ ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው፣ ይሖዋ ያደረገላቸውን መልካም ነገር በሙሉ ወዲያውኑ ረሱ። በመሆኑም አድናቆት እንደጎደላቸው የሚያሳይ ነገር አደረጉ። (መዝ. 106:7) እንዴት? “መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ . . . በሙሴና በአሮን ላይ ማጉረምረም ጀመረ።” እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ሰዎች ያጉረመረሙት በይሖዋ ላይ ነበር። (ዘፀ. 16:2, 8) ይሖዋም ሕዝቡ ምስጋና ቢስ በመሆኑ በጣም አዘነ። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ፣ ከኢያሱና ከካሌብ በቀር ያ የእስራኤላውያን ትውልድ በሙሉ በምድረ በዳ እንደሚያልቅ ተናገረ።—ዘኁ. 14:22-24፤ w19.02 17 አን. 12-13

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 5

እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ።—ማቴ. 11:29

ኢየሱስ የሞቱ መታሰቢያ ለየት ባለ መንገድ እንዲከበር በማድረግ ወደ ራሱ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት አልሳበም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ በዓመት አንድ ጊዜ ቀለል ባለ ዝግጅት አማካኝነት የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 13:15፤ 1 ቆሮ. 11:23-25) ቀለል ያለ ሆኖም ለሥነ ሥርዓቱ ተስማሚ የሆነው ይህ ዝግጅት ኢየሱስ ኩሩ እንዳልነበር ይጠቁማል። በሰማይ ያለው ንጉሣችን ካሉት ግሩም ባሕርያት መካከል አንዱ ትሕትና በመሆኑ ደስተኞች ነን። (ፊልጵ. 2:5-8) ትሕትና በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ከራሳችን ይልቅ የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት በማስቀደም ነው። (ፊልጵ. 2:3, 4) ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን የመጨረሻ ምሽት ለማሰብ ሞክሩ። ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሰቃቂ በሆነ መንገድ እንደሚገደል ያውቃል፤ ያም ሆኖ ከሁሉ በላይ ያሳሰበው በእሱ ሞት ምክንያት ከባድ ሐዘን ላይ የሚወድቁት ታማኝ ሐዋርያቱ ሁኔታ ነበር። በመሆኑም የመጨረሻውን ምሽት ያሳለፈው እነሱን በማስተማር፣ በማበረታታትና በማጽናናት ነው። (ዮሐ. 14:25-31) ኢየሱስ ትሑት ስለሆነ ከራሱ ይልቅ የሌሎች ሰዎች ደህንነት ያሳስበው ነበር። በእርግጥም በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! w19.01 21 አን. 5-6

እሁድ፣ ታኅሣሥ 6

ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ በፈቃደኝነት የማቀርበውን የውዳሴ መባ በደስታ ተቀበል።—መዝ. 119:108

እጃችሁን አውጥታችሁ ሐሳብ ለመስጠት ባሰባችሁ ቁጥር ጭንቅ ይላችኋል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማችሁ እናንተ ብቻ አይደላችሁም። እውነቱን ለመናገር አብዛኞቻችን ሐሳብ ስንሰጥ በተወሰነ መጠን እንፈራለን። እርግጥ እንዲህ ያለው ስሜት ስለ እናንተ አዎንታዊ ነገር የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ትሑት እንደሆናችሁና ሌሎችን ከራሳችሁ አስበልጣችሁ እንደምትመለከቱ ያሳያል። እንዲህ ያለው ባሕርይ ይሖዋን ያስደስተዋል። (መዝ. 138:6፤ ፊልጵ. 2:3) ሆኖም ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ እሱን እንድታወድሱት እንዲሁም ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን እንድታበረታቱ ይፈልጋል። (1 ተሰ. 5:11) ደግሞም ስለሚወዳችሁ የሚያስፈልጋችሁን ድፍረት ይሰጣችኋል። በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ከምንናገረው ነገርም ሆነ ከምንናገርበት መንገድ ጋር በተያያዘ ሁላችንም ልንሳሳት እንደምንችል ይገልጻል። (ያዕ. 3:2) ይሖዋ ፍጹም እንድንሆን አይጠብቅብንም፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ቢሆኑ ከእኛ ፍጽምና አይጠብቁም። (መዝ. 103:12-14) መንፈሳዊ ቤተሰባችን ስለሆኑ ይወዱናል። (ማር. 10:29, 30፤ ዮሐ. 13:35) አንዳንድ ጊዜ የምንናገረው፣ ለመናገር ያሰብነውን ነገር እንዳልሆነ ይረዱልናል። w19.01 8 አን. 3፤ 10-11 አን. 10-11

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7

በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ።—መክ. 12:1

በዛሬው ጊዜ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ተፈታታኝ ነው። ፈጽሞ የማይቻል ነገር ግን አይደለም። ይሖዋ እውነተኛ ስኬትና እርካታ እንድታገኙ ይፈልጋል። በአምላክ እርዳታ ወጣት እያላችሁ ብቻ ሳይሆን ሕይወታችሁን በሙሉ ስኬታማ መሆን ትችላላችሁ። የዚህን እውነተኝነት ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር መቆጣጠር የቻሉት እንዴት እንደሆነ እንመርምር። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲቃረቡ አምላክ የውጊያ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ወይም ለጦርነት እንዲሠለጥኑ አላዘዛቸውም። (ዘዳ. 28:1, 2) ከዚህ ይልቅ ትእዛዛቱን መጠበቅና በእሱ መታመን እንደሚያስፈልጋቸው ነግሯቸዋል። (ኢያሱ 1:7-9) ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ይህ ሞኝነት ይመስል ነበር። ሆኖም ምክሩ ከሁሉ የተሻለ ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋ ሕዝቦቹ በከነአናውያን ላይ ተከታታይ ድል እንዲጎናጸፉ ረድቷቸዋል። (ኢያሱ 24:11-13) አዎ፣ አምላክን መታዘዝ እምነት የሚጠይቅ ነገር ቢሆንም እንዲህ ያለው እምነት ምንጊዜም ለስኬት ያበቃል። ይህ እውነታ መቼም ቢሆን አይለወጥም። በጥንት ጊዜ ይሠራ እንደነበር ሁሉ ዛሬም ይሠራል። w18.12 25 አን. 3-4

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8

ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ።—ዮሐ. 6:68

አንዳንዶች አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በምንረዳበት መንገድ ላይ በተደረገው ማስተካከያ ምክንያት ተሰናክለዋል። ከከሃዲዎች ወይም የምናምንባቸውን ነገሮች ከሚያጣምሙ ተቃዋሚዎች ጎን በመቆማቸው ምክንያት ከእውነት መንገድ የወጡ ክርስቲያኖችም አሉ። በዚህ መንገድ ሆን ብለው ከይሖዋና ከጉባኤው ‘ርቀዋል።’ (ዕብ. 3:12-14) እነዚህ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት ጠብቀው ቢቀጥሉ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! ሌሎች ደግሞ ከእውነት ጎዳና የሚወጡት ቀስ በቀስ ምናልባትም ሳይታወቃቸው ነው። የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ ቀስ በቀስ ከወደቡ እየራቀ ከሚሄድ ጀልባ ጋር ይመሳሰላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ሂደት ‘ቀስ በቀስ መወሰድ’ በማለት ይገልጸዋል። (ዕብ. 2:1) ቀስ በቀስ ከእውነት የሚወሰድ ሰው ከእውነት ከሚርቅ ሰው በተለየ መልኩ ይህን የሚያደርገው ሆን ብሎ አይደለም። ይሁንና እንዲህ ያለው ሰው ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና እንዲዳከም ውሎ አድሮም እንዲጠፋ ሊፈቅድ ይችላል። w18.11 9 አን. 5-6

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 9

ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።—መዝ. 110:3

ቅዱስ አገልግሎት ለማከናወን የበለጠ ብቁ እንድትሆን የሚረዳ ተጨማሪ ሥልጠና ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መሠልጠን ትችል ይሆናል። ይህ ትምህርት ቤት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በመስኩ ላይ ይበልጥ መሥራት እንዲችሉ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና ይሰጣል። በዚህ ትምህርት ቤት ለመሠልጠን የሚያመለክቱ ሁሉ፣ ከተመረቁ በኋላ በተመደቡበት በማንኛውም ቦታ ለማገልገል ፈቃደኞች መሆን አለባቸው። አንተስ በዚህ መንገድ ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ፈቃደኛ ነህ? (1 ቆሮ. 9:23) የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን የጥሩነት፣ የደግነትና የፍቅር መገለጫ የሆነውን ልግስናን እናሳያለን፤ እንዲሁም በየዕለቱ ለሌሎች አሳቢነት ለማሳየት እንጥራለን። ይህን ስናደርግ ደስታና ሰላም እናገኛለን። (ገላ. 5:22, 23) በእርግጥም ሁኔታህ ምንም ይሁን ምን እንደ ይሖዋ ለጋስ በመሆን እንዲሁም ከእሱ ጋር አብረህ በመሥራት ደስታ ማግኘት ትችላለህ!—ምሳሌ 3:9, 10፤ w18.08 27 አን. 16-18

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10

አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።—ማቴ. 19:6

‘አንድ ክርስቲያን ፍቺ መፈጸምና ድጋሚ ማግባት የሚችልበት መሠረት ይኖረው ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ኢየሱስ ለፍቺ ያለውን አመለካከት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በማመንዘር ሚስቱን ይበድላል፤ አንዲት ሴትም ብትሆን ባሏን ፈታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች።” (ማር. 10:11, 12፤ ሉቃስ 16:18) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት የነበረው ሲሆን ሌሎችም የእሱ ዓይነት አመለካከት እንዲያዳብሩ ይፈልጋል። አንድ ወንድ የሆነ ሰበብ ፈልጎ ታማኝ የሆነች ሚስቱን ከፈታ በኋላ ሌላ ቢያገባ ምንዝር እንደፈጸመ ይቆጠራል። (ታማኝ የሆነ ባሏን ከምትፈታ ሴት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።) ይህ መሆኑ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም አንድ ሰው የትዳር ጓደኛውን ስለፈታ ብቻ የጋብቻ ጥምረቱ አይፈርስም። አሁንም ቢሆን ሁለቱ ሰዎች በአምላክ ዓይን “አንድ ሥጋ” ናቸው። በተጨማሪም ኢየሱስ አንድ ሰው ታማኝ የሆነች ሚስቱን መፍታቱ ሚስቱን ምንዝር ለመፈጸም እንደሚያጋልጣት ተናግሯል። እንዴት? በዚያ ዘመን የነበረች ከባሏ የተፋታች አንዲት ሴት ቁሳዊ ድጋፍ ለማግኘት ስትል ድጋሚ ለማግባት ትገደድ ይሆናል። እንዲህ ያለው ጋብቻ ደግሞ ምንዝር እንደመፈጸም ይቆጠራል። w18.12 11 አን. 8-9

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 11

በጥበቃ ቦታዬ ላይ እሰየማለሁ።—ዕን. 2:1

ዕንባቆም ከይሖዋ ጋር ያደረገው ውይይት ውስጣዊ ሰላም እንዲያገኝ ረድቶታል። በመሆኑም በይሖዋ በመታመን አምላክ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ዕንባቆም ይህን ውሳኔ ያደረገው ስሜታዊ ሆኖ አይደለም፤ ምክንያቱም ከጊዜ በኋላም “የጭንቀትን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ” በማለት በድጋሚ ተናግሯል። (ዕን. 3:16) ዕንባቆም ካደረገው ቁርጥ ውሳኔ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንደኛ፣ ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስብን ወደ ይሖዋ መጸለያችንን ማቆም የለብንም። ሁለተኛ፣ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ በኩል የሚነግረንን መስማት ያስፈልገናል። ሦስተኛ፣ ይሖዋ ችግራችንን ራሱ በወሰነው ጊዜ እንደሚፈታልን ሙሉ በሙሉ በመተማመን እሱን በትዕግሥት መጠባበቅ አለብን። ልክ እንደ ዕንባቆም የልባችንን አውጥተን ለይሖዋ የምንነግረውና በትዕግሥት በመጠባበቅ እሱ የሚለንን የምንሰማ ከሆነ እኛም ውስጣዊ ሰላም ይኖረናል፤ ይህም እንድንጸና ያደርገናል። ይሖዋ የሰጠን ተስፋ ይበልጥ ታጋሾች እንድንሆን ይረዳናል፤ ትዕግሥት ደግሞ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ደስተኞች እንድንሆን ያስችለናል። በተጨማሪም ተስፋ፣ በሰማይ ያለው አባታችን እርምጃ መውሰዱ እንደማይቀር እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ሮም 12:12፤ w18.11 15-16 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 12

ሴቶች . . . በልከኝነትና በማስተዋል፣ ተገቢ በሆነ ልብስ ራሳቸውን ያስውቡ።—1 ጢሞ. 2:9

ሌሎችን ከማሰናከል ጋር በተያያዘ አምላክ ምን አመለካከት አለው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል።” (ማር. 9:42) እነዚህ ቃላት ጠንካራ መልእክት ያስተላልፋሉ! ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ ስለዚህ ይሖዋም ግድ የለሽ በሆነ ድርጊታቸው ምክንያት የኢየሱስን ተከታዮች የሚያሰናክሉ ሰዎችን አጥብቆ እንደሚቃወም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ዮሐ. 14:9) እኛስ በዚህ ረገድ የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት አለን? ድርጊታችን ምን ያሳያል? ለምሳሌ ያህል፣ እኛ የወደድነው አለባበስ ወይም አጋጌጥ በጉባኤያችን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ቅር የሚያሰኝ ወይም የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ያለን ፍቅራዊ አሳቢነት የግል ምርጫችንን እንድንተው ያነሳሳናል? w18.11 25 አን. 9-10

እሁድ፣ ታኅሣሥ 13

ሰይጣንም ለይሖዋ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ኢዮብ አምላክን የሚፈራው እንዲያው በከንቱ ነው? . . . እስቲ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ አጥፋ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”—ኢዮብ 1:9, 11

ንጹሕ አቋም ሁላችንም ሊኖረን የሚገባ አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው? ሰይጣን በይሖዋም ሆነ በእያንዳንዳችን ላይ ግድድር ስላነሳ ነው። ይህ ዓመፀኛ መልአክ አምላክን መጥፎ፣ ራስ ወዳድና አታላይ ገዢ አስመስሎ በማቅረብ የይሖዋን መልካም ስም አጉድፏል። የሚያሳዝነው፣ አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጎን በመቆም በይሖዋ ላይ ዓመፁ። (ዘፍ. 3:1-6) በኤደን ገነት ውስጥ የነበራቸው ሕይወት፣ ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅር የሚያጠናክሩበት ሰፊ አጋጣሚ ይሰጣቸው ነበር። ሆኖም ሰይጣን ግድድሩን ባስነሳበት ወቅት ፍቅራቸው እንከን የለሽ ወይም ሙሉ አልነበረም። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ‘ለይሖዋ አምላክ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ታማኝነቱን የሚጠብቅ ሰው ሊኖር ይችላል?’ የሚል ጥያቄ ተነሳ። በሌላ አባባል ጥያቄው ‘የሰው ልጆች ንጹሕ አቋማቸውን ሊጠብቁ ይችላሉ?’ የሚል ነው። ይህ ጥያቄ የተነሳው ከኢዮብ ጋር በተያያዘ ነበር። (ኢዮብ 1:8-11) ኢዮብ ልክ እንደ እኛ ፍጽምና የጎደለው ሰው ስለሆነ ስህተት ሠርቷል። ሆኖም ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ይሖዋ ይወደው ነበር። w19.02 3-4 አን. 6-7

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 14

ያለውን ሁሉ ወዲያውኑ በመሸጥ ዕንቁውን ገዛው።—ማቴ. 13:46

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው እውነት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ለማሳየት ጥሩ ዕንቁ ሲፈልግ ቆይቶ መጨረሻ ላይ ያገኘን አንድ ተጓዥ ነጋዴ ምሳሌ ሰጥቷል። ነጋዴው ያገኘው ዕንቁ በጣም ከፍተኛ ዋጋ ያለው ከመሆኑ የተነሳ ንብረቱን ሁሉ “ወዲያውኑ በመሸጥ” ዕንቁውን ገዝቶታል። (ማቴ. 13:45, 46) በተመሳሳይም ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን እውነት ጨምሮ ከአምላክ ቃል ላይ የተማርናቸው ውድ እውነቶች በሙሉ ለእኛ በጣም ከፍተኛ ዋጋ አላቸው፤ በመሆኑም እነዚህን እውነቶች ለማግኘት ስንል ወዲያውኑ አስፈላጊውን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነናል። እውነትን ከፍ አድርገን መመልከታችንን እስከቀጠልን ድረስ ፈጽሞ ‘አንሸጠውም።’ (ምሳሌ 23:23) የሚያሳዝነው ግን ከአምላክ ሕዝቦች መካከል አንዳንዶቹ እውነት ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳለው የዘነጉ ከመሆኑም በላይ እውነትን ሸጠውታል። እኛ ግን እንዲህ ያለ ነገር ማድረግ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው! እውነትን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተውና ፈጽሞ ልንሸጠው እንደማንፈልግ ለማሳየት ‘በእውነት ውስጥ ተመላለሱ’ የሚለውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (3 ዮሐ. 2-4) በእውነት መመላለስ ማለት በሕይወታችን ውስጥ ለእውነት ቅድሚያ መስጠትና ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ማለት ነው። w18.11 9 አን. 3

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15

እስራኤላውያን የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ በእምነት ወደቀ።—ዕብ. 11:30

እስራኤላውያን በኢያሪኮ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ከዚህ ይልቅ ለስድስት ቀን ከተማዋን በቀን አንድ ጊዜ፣ በሰባተኛው ቀን ላይ ደግሞ ሰባት ጊዜ እንዲዞሯት ትእዛዝ ተሰጣቸው። አንዳንድ ወታደሮች ‘ለምን ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ዝም ብለን እናባክናለን?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። በዓይን የማይታየው የእስራኤል መሪ ማለትም ይሖዋ ግን የሚያደርገውን ነገር ያውቅ ነበር። የእሱን መመሪያ መከተላቸው የእስራኤላውያንን እምነት ያጠናከረላቸው ከመሆኑም ሌላ ከኢያሪኮ ኃያል ተዋጊዎች ጋር ፊት ለፊት ከመጋፈጥ አድኗቸዋል። (ኢያሱ 6:2-5) ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ጊዜ ድርጅቱ አዳዲስ መመሪያዎችን የሰጠበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ መረዳት ሊከብደን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ለስብሰባዎች፣ ለግል ጥናትና ለአገልግሎት እንድንጠቀም የተሰጠን መመሪያ መጀመሪያ ላይ ጥቅሙ አልታየን ይሆናል። አሁን ግን ሁኔታችን እስከፈቀደ ድረስ እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀማችን ያለውን ጥቅም ተገንዝበን መሆን አለበት። ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬ ሊያድርብን ቢችልም እንዲህ ያሉ ለውጦች ያስገኙትን ጥሩ ውጤት መመልከታችን እምነታችን እንዲጨምርና አንድነታችን እንዲጠናከር ያደርጋል። w18.10 23 አን. 8-9

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 16

ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?—ሥራ 1:6

የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ጨምሮ በርካታ አይሁዳውያን መሲሑ ችግሮቻቸውን እንደሚፈታላቸው ይጠብቁ ነበር። የገሊላ ሰዎች ኢየሱስን ለማንገሥ የሞከሩት ለዚህ መሆን አለበት። ኢየሱስ የላቀ ችሎታ ያለው መሪ እንደሚሆንላቸው አስበው ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም አስደናቂ የንግግር ችሎታ አለው እንዲሁም የታመሙትን መፈወስ አልፎ ተርፎም የተራቡትን መመገብ ይችላል። ኢየሱስ 5,000 ወንዶችን ከመገበ በኋላ “ሰዎቹ መጥተው ሊይዙትና ሊያነግሡት እንዳሰቡ ስላወቀ ብቻውን ዳግመኛ ወደ ተራራ ገለል አለ።” (ዮሐ. 6:10-15) ሕዝቡ በማግስቱ ከገሊላ ባሕር ማዶ ሲያገኙት ግን ስሜታቸው ተረጋግቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የሥራውን ዓላማ አብራራላቸው። ወደ ምድር የመጣው በመንፈሳዊ ሊረዳቸው እንጂ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት አይደለም። “ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን . . . ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ” ብሏቸዋል።—ዮሐ. 6:25-27፤ w18.06 4 አን. 4-5

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 17

የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም።—ኢሳ. 42:3

ኢየሱስ እንደተቀጠቀጠ ሸምበቆ ወይም ሊጠፋ እንደተቃረበ የጧፍ ክር የሆኑትን ሰዎች ስሜት ይረዳ ነበር። በመሆኑም አሳቢነት፣ ደግነትና ትዕግሥት አሳይቷቸዋል። (ማር. 10:14) እኛ የኢየሱስ ዓይነት ማስተዋልና የማስተማር ችሎታ እንደሌለን የታወቀ ነው። ያም ሆኖ በክልላችን ውስጥ ላሉት ሰዎች አሳቢነት ማሳየት እንችላለን፤ ደግሞም ይህን ልናደርግ ይገባል። ይህም ‘ሰዎችን የምናነጋግረው እንዴት ነው? የምናነጋግራቸው መቼ ነው? እንዲሁም ለምን ያህል ደቂቃዎች ነው?’ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰብን ይጨምራል። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ምግባረ ብልሹና ጨካኝ በሆኑት የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የንግዱን ሥርዓት በሚቆጣጠሩት ሰዎች በደል ይደርስባቸዋል፤ እነዚህ ሰዎች ‘እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈዋል እንዲሁም ተጥለዋል።’ (ማቴ. 9:36) በዚህም ምክንያት ብዙዎች ተጠራጣሪ ከመሆናቸውም ሌላ ተስፋ ቆርጠዋል። እንግዲያው የምንናገረው ነገርም ሆነ የድምፃችን ቃና ደግነትና አሳቢነት የሚንጸባረቅበት መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው! ደግሞም ብዙ ሰዎች መልእክታችንን ለመቀበል የሚያነሳሳቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችን ወይም የማስረዳት ችሎታችን ብቻ ሳይሆን ለእነሱ ልባዊ አሳቢነትና አክብሮት ማሳየታችንም ጭምር ነው። w18.09 31-32 አን. 13-14

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 18

መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።—ማቴ. 5:3

ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥማት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው? መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ፣ ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ በመስጠት እንዲሁም ደስተኛ ለሆነው አምላክ የምናቀርበውን አምልኮ ከምንም ነገር በላይ በማስቀደም ነው። እንዲህ ካደረግን ደስታችን እየጨመረ ይሄዳል። አምላክ የሰጠን ተስፋ እንደሚፈጸም ያለን እምነትም ይጠናከራል። (ቲቶ 2:13) ዘላቂ ደስታ ለማግኘት ቁልፉ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁልጊዜ [በይሖዋ] ደስ ይበላችሁ። ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ!” ሲል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (ፊልጵ. 4:4) ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና ለመመሥረት ግን መለኮታዊ ጥበብ ያስፈልገናል። (ምሳሌ 3:13, 18) ዘላቂ የሆነ ደስታ ለማግኘት የአምላክን ቃል ማንበብ ብቻ ሳይሆን ያነበብነውን በተግባር ማዋልም ይኖርብናል። ኢየሱስ የተማርነውን ነገር በተግባር የማዋልን አስፈላጊነት ሲያጎላ “እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ” ብሏል። (ዮሐ. 13:17፤ ያዕ. 1:25) መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካትም ሆነ ዘላቂ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው። w18.09 18 አን. 4-6

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 19

[ኤጳፍራ] ዘወትር በጸሎቱ ስለ እናንተ እየተጋደለ ነው።—ቆላ. 4:12

ኤጳፍራ ወንድሞቹን በሚገባ ያውቃቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከልቡ ያስብላቸው ነበር። እሱም እንደ ጳውሎስ “እስረኛ” የነበረ ቢሆንም ይህ የሌሎችን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳያስተውል አላደረገውም። (ፊልሞና 23) ደግሞም እነሱን ለመርዳት ስለፈለገ እነሱን በተመለከተ ጸልዮአል። በእርግጥም ኤጳፍራ ለሌሎች ከልቡ ያስብ ነበር። እኛም አብረውን ይሖዋን የሚያገለግሉ ክርስቲያኖችን በተመለከተ የምናቀርበው ጸሎት ታላቅ ኃይል አለው፤ በተለይ ደግሞ ስማቸውን ጠቅሰን መጸለያችን በጣም ጠቃሚ ነው። (2 ቆሮ. 1:11፤ ያዕ. 5:16) አንተም ኤጳፍራ እንዳደረገው ስማቸውን ጠቅሰህ ልትጸልይላቸው ስለምትችል ሰዎች ለማሰብ ሞክር። በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጉባኤያቸው ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ኤጳፍራ ጸሎት ያቀርባሉ፤ ለምሳሌ፣ ብዙ ኃላፊነት ያለባቸው ወይም ከባድ ውሳኔ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው አሊያም ፈተና የሚያጋጥማቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በተመለከተ ይጸልያሉ። ከዚህም በተጨማሪ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ፣ በአደጋ ወይም በጦርነት የተነሳ ችግር ያጋጠማቸው እንዲሁም ከኢኮኖሚ ችግር ጋር የሚታገሉ ወንድሞቻችንን በጸሎት ማሰባችን አስፈላጊ ነው። በእርግጥም ጸሎታችን የሚያስፈልጋቸው በርካታ ወንድሞችና እህቶች አሉ። w18.09 5-6 አን. 12-13

እሁድ፣ ታኅሣሥ 20

ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35

ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ስለ ቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ለሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ማበረታቻ፣ መመሪያና ሌላ ዓይነት ድጋፍ ስለመስጠት ጭምር ነው። (ሥራ 20:31-35) ይህ ሐዋርያ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ትኩረትን እና ፍቅርን በልግስና በመስጠት ረገድ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ ምሳሌ ትቶልናል። ስለ ሰዎች ባሕርይ የሚያጠኑ ተመራማሪዎችም መስጠት ሰዎችን ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ተገንዝበዋል። “አንዳንድ ሰዎች፣ ለሌሎች መልካም ካደረጉ በኋላ ደስታቸው በጣም እንደጨመረ ተናግረዋል” በማለት አንድ ጽሑፍ ገልጿል። ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ሰዎች ሌሎችን መርዳታቸው ሕይወታቸው “ይበልጥ ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን በማድረግ” ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፤ “ምክንያቱም መሠረታዊ የሆነው የሰው ልጆች ፍላጎት እንዲሟላ ያደርጋል።” በመሆኑም አንዳንድ ባለሙያዎች ሰዎች ጤንነታቸው እንዲሻሻልና ደስታቸው እንዲጨምር ከፈለጉ ማኅበረሰቡን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ በፈቃደኝነት እንዲሳተፉ ያበረታታሉ። እርግጥ ይህ ሐሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ያስጻፈው መጽሐፍ እንደሆነ አምነው ለሚቀበሉ ሰዎች የሚያስደንቅ አይደለም።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ w18.08 22 አን. 17-18

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 21

የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ።—ዮሐ. 7:24

ኢሳይያስ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት ልባችንን የሚያረጋጋና ተስፋ የሚሰጥ ነው። ኢሳይያስ እንደተናገረው፣ ኢየሱስ “ዓይኑ እንዳየ አይፈርድም ወይም ጆሮው በሰማው ነገር ላይ ብቻ ተመሥርቶ አይወቅስም።” ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “ለችግረኞች በትክክል ይፈርዳል።” (ኢሳ. 11:3, 4) ይህን ማወቃችን የሚያበረታታን ለምንድን ነው? የምንኖረው አድልዎና ጭፍን ጥላቻ በተንሰራፋበት ዓለም ውስጥ ስለሆነ ነው። በውጫዊ ገጽታ ላይ ተመሥርቶ የማይፈርደው ፍጹም ዳኛ የሚያስተዳድርበትን ጊዜ ሁላችንም በጉጉት እንጠባበቃለን! ሁላችንም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከምናገኛቸው የተለያዩ ሰዎች ጋር በተያያዘ የራሳችን ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። ያም ቢሆን እንደ ኢየሱስ ፍጹማን ስላልሆንን ስለ ሌሎች ያለን አመለካከት የተዛባ ሊሆን ይችላል። የሰዎች ውጫዊ ገጽታ ስለ እነሱ በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት “የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት” እንዳንፈርድ ከዚህ ይልቅ “በጽድቅ” እንድንፈርድ አዞናል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ኢየሱስ የእሱን ምሳሌ በመከተል በሰዎች ውጫዊ ገጽታ ላይ ተመሥርተን ከመፍረድ እንድንቆጠብ ይፈልጋል። w18.08 8 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 22

ጆሮህ ከኋላህ “መንገዱ ይህ ነው። በእሱ ሂድ” የሚል ድምፅ ይሰማል።—ኢሳ. 30:21

እርግጥ ይሖዋ ከሰማይ ሲናገር አንሰማውም። ሆኖም ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈልን ሲሆን በቃሉ በኩል መመሪያ ይሰጠናል። በተጨማሪም የይሖዋ መንፈስ ‘ታማኙ መጋቢ’ ለአምላክ አገልጋዮች ምግብ ማቅረቡን እንዲቀጥል ያደርጋል። (ሉቃስ 12:42) በታተሙም ሆነ ኢንተርኔት ላይ በሚገኙ ጽሑፎች፣ ቪዲዮዎችና ኦዲዮዎች አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት አምላክ ራሱ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት፣ ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚቆጣጠር እንዲሁም ሰይጣንና እሱ የሚገዛው ክፉ ዓለም ያስከተሉትን ማንኛውንም ጉዳት እንደሚቀለብስ እርግጠኞች እንድንሆን ያደርጉናል። እንግዲያው የይሖዋን ድምፅ በጥሞና ለመስማት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ችግሮች በሙሉ በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋል” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል።—ዕብ. 10:36፤ w19.03 13 አን. 17-18

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23

ይሖዋ . . . ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “አገልጋዬ ሙሴ ሞቷል። እንግዲህ አንተም ሆንክ ይህ ሕዝብ ተነስታችሁ ዮርዳኖስን [ተሻገሩ]።”—ኢያሱ 1:1, 2

ለረጅም ጊዜ እስራኤልን ሲመራ የቆየው ሙሴ ስለነበር ኢያሱ ‘የአምላክ ሕዝቦች እኔን እንደ መሪያቸው አድርገው ይቀበሉኝ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦት ሊሆን ይችላል። (ዘዳ. 34:8, 10-12) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ጽሑፍ ኢያሱ 1:1, 2⁠ን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ ለአንድ አገር ደህንነት እጅግ አስጊ ከሆኑት ወቅቶች መካከል አንዱ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት ጊዜ ነው።” ኢያሱ እንዲፈራ የሚያደርገው በቂ ምክንያት የነበረው ቢሆንም በጥቂት ቀናት ውስጥ ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። (ኢያሱ 1:9-11) ኢያሱ በአምላክ የታመነ ሲሆን አምላክም አላሳፈረውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ እንደሚያሳየው ይሖዋ ኢያሱንና ሕዝቡ የሆኑትን እስራኤላውያንን ወኪሉ በሆነ መልአክ አማካኝነት መርቷቸዋል። ይህ መልአክ “ቃል” ተብሎ የተጠራው የአምላክ የበኩር ልጅ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። (ዘፀ. 23:20-23፤ ዮሐ. 1:1) እስራኤላውያን ከሙሴ አመራር ወደ ኢያሱ አመራር በተሸጋገሩበት ወቅት የነበረውን ለውጥ በይሖዋ እርዳታ በተሳካ ሁኔታ ማለፍ ችለዋል። w18.10 22-23 አን. 1-4

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24

ይሖዋንም ለሚፈሩ . . . በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።—ሚል. 3:16

ይሖዋ በፈቃደኝነት ለሚያገለግሉት ሰዎች እውቅና የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ ስማቸው ‘በመታሰቢያ መጽሐፍ’ ላይ እንዲጻፍ ያደርጋል። ይሖዋ ባዘጋጀው “የመታሰቢያ መጽሐፍ” ላይ ስማችን መጻፉ የሚያስከትለው ኃላፊነት አለ። ሚልክያስ ‘ይሖዋን መፍራትና በስሙ ላይ ማሰላሰል’ እንዳለብን ገልጿል። ከይሖዋ ውጭ ለማንኛውም አካል ወይም ለማንኛውም ነገር አምልኮታዊ ክብር ማሳየታችን ስማችን ይሖዋ ካዘጋጀው የሕይወት መጽሐፍ ላይ እንዲደመሰስ ያደርጋል። (ዘፀ. 32:33፤ መዝ. 69:28) በመሆኑም ራስን ለይሖዋ መወሰን፣ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ ቃል ከመግባትና በውኃ ከመጠመቅ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። እነዚህ አንድ ጊዜ ተደርገው የሚያልፉ ነገሮች ናቸው። የይሖዋ ሕዝቦች በመሆን ከእሱ ጎን ለመቆም ያደረግነው ውሳኔ ግን አሁንም ሆነ ወደፊት በሕይወት እስካለን ድረስ ለእሱ ታዛዥ መሆናችንን ምንጊዜም ማሳየትን ይጠይቃል።—1 ጴጥ. 4:1, 2፤ w18.07 23-24 አን. 7-9

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 25

ስለ ክርስቶስ ከተማርነው መሠረታዊ ትምህርት አልፈን ስለሄድን ወደ ጉልምስና ለመድረስ እንጣጣር።—ዕብ. 6:1

ጉልምስና ያለምንም ጥረት የሚደረስበት ነገር አይደለም፤ ጳውሎስ እንዳለው ‘መጣጣር’ ማለትም ተግተን መሥራት ያስፈልገናል። እድገት አድርገን ጉልምስና ላይ ለመድረስ፣ እውቀታችንና የማስተዋል ችሎታችን እየጨመረ መሄድ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እንድናነብ የምንበረታታው ለዚህ ነው። (መዝ. 1:1-3) ይህን የማድረግ ግብ አውጥተሃል? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብህ፣ የይሖዋን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ ማስተዋል እንድትችልና የአምላክን ቃል በጥልቀት እንድታውቅ ይረዳሃል። ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባው ከሁሉ የሚበልጠው ሕግ የፍቅር ሕግ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 13:35) የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ፍቅርን “ንጉሣዊ ሕግ” ሲል ጠርቶታል። (ያዕ. 2:8) ጳውሎስ ደግሞ “ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው” ብሏል። (ሮም 13:10) ፍቅር የዚህን ያህል ጎላ ተደርጎ መገለጹ አያስገርምም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል።—1 ዮሐ. 4:8፤ w18.06 19 አን. 14-15

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26

መንፈሱን አስመረሩት፤ እሱም በከንፈሮቹ በችኮላ ተናገረ።—መዝ. 106:33

እስራኤላውያን ያስቆጡት ይሖዋን ቢሆንም የተመረረው ግን ሙሴ ነበር። ራሱን መግዛት አለመቻሉ፣ ውጤቱን ሳያመዛዝን እንዲናገር አድርጎታል። ሙሴ የሌሎች ድርጊት እንቅፋት እንዲሆንበት መፍቀዱ ዓይኑ ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዳይመለከት አድርጎታል። ሙሴ መጀመሪያ ላይ ያጋጠመውን ችግር ተገቢ በሆነ መንገድ ፈቶት ነበር። (ዘፀ. 7:6) ሆኖም ዓመፀኛ ከሆኑት እስራኤላውያን ጋር ለአሥርተ ዓመታት አብሮ ማሳለፉ እንዲዝልና ትዕግሥቱ እንዲሟጠጥ አድርጎት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ሙሴ ይሖዋን እንዴት ማክበር እንደሚችል ከማሰብ ይልቅ በራሱ ስሜት ላይ ብቻ አተኩሮ ይሆን? እንደ ሙሴ ያለ ታማኝ ነቢይ ትኩረቱ ሊከፋፈልና ሊደናቀፍ ከቻለ እኛም ተመሳሳይ ስህተት ልንሠራ የምንችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። ልክ እንደ ሙሴ እኛም በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደ ተስፋይቱ ምድር ማለትም ይሖዋ ቃል ወደገባልን አዲስ ዓለም ልንገባ ተቃርበናል። (2 ጴጥ. 3:13) ማናችንም ብንሆን ይህ ልዩ መብት እንዲያመልጠን አንፈልግም። ሆኖም ይህን ግባችንን ማሳካት የምንችለው ዓይናችን ምንጊዜም ወደ ይሖዋ እንዲመለከት የምናደርግ ማለትም ዘወትር የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የምንጣጣር ከሆነ ነው።—1 ዮሐ. 2:17፤ w18.07 15 አን. 14-16

እሁድ፣ ታኅሣሥ 27

ክፉውን [አሸንፋችሁታል]።—1 ዮሐ. 2:14

ሰይጣን፣ ሰዎች የማይፈልጉትን ነገር እንዲያደርጉ ማስገደድ አይችልም። (ያዕ. 1:14) እርግጥ ብዙዎች ሳያውቁት ከሰይጣን ጎራ ተሰልፈዋል። እውነትን ካወቁ በኋላ ግን ማንን እንደሚያገለግሉ በግለሰብ ደረጃ መምረጥ አለባቸው። (ሥራ 3:17፤ 17:30) የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም እስከቆረጥን ድረስ ሰይጣን ንጹሕ አቋማችንን በምንም መንገድ ማጉደፍ አይችልም። (ኢዮብ 2:3፤ 27:5) ሰይጣንና አጋንንቱ ማድረግ የማይችሏቸው ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የሰዎችን ልብ ወይም አእምሮ ማንበብ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ አናገኝም። ይህ ችሎታ እንዳላቸው የተገለጹት ይሖዋ እና ኢየሱስ ብቻ ናቸው። (1 ሳሙ. 16:7፤ ማር. 2:8) ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እንዲሆን ከልባችን ጥረት ካደረግን፣ ዲያብሎስ ዘላቂ ጉዳት እንዲያደርስብን ይሖዋ እንደማይፈቅድለት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝ. 34:7) ጠላታችንን ማወቅ ይኖርብናል፤ ይህ ሲባል ግን በፍርሃት ልንርድ ይገባል ማለት አይደለም። ፍጹም ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ በይሖዋ እርዳታ ሰይጣንን ማሸነፍ ይችላሉ። ዲያብሎስን ከተቃወምነው ከእኛ ይሸሻል።—ያዕ. 4:7፤ 1 ጴጥ. 5:9፤ w18.05 26 አን. 15-17

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28

የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።—ምሳሌ 16:3

ትልቅ ቦታ በሚሰጠው አንድ ዝግጅት ላይ ለመገኘት ስትል ራቅ ወዳለ ከተማ ለመጓዝ አስበሃል እንበል። ያሰብክበት ለመድረስ ለረጅም ሰዓት በአውቶቡስ መጓዝ ያስፈልግሃል። ወደ አውቶቡስ መናኸሪያው ስትደርስ ቦታው በአውቶቡሶች ተጨናንቋል። አንተ ወደምትሄድበት አቅጣጫ የሚሄደው አውቶቡስ ላይ መሳፈር ይኖርብሃል። ወዴት እንደሚሄድ ያላወቅከው አውቶብስ ውስጥ ዘለህ መግባት የፈለግክበት ቦታ ለመድረስ አያስችልህም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶችም ረጅም የሕይወት ጉዞ ይጠብቃቸዋል። በፊታቸው የተደቀኑት ውሳኔዎችና የሚቀርቡላቸው አጋጣሚዎች አንዳንድ ጊዜ ግራ ሊያጋቧቸው ይችላሉ። እናንት ወጣቶች፣ በሕይወታችሁ ምን ማድረግ እንደምትፈልጉ ግብ ካወጣችሁ ትክክለኛውን ምርጫ ማድረግ ቀላል ይሆንላችኋል። ይሖዋን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት ትመራላችሁ? እንዲህ ዓይነት ሕይወት መምራት የምትችሉት በሁሉም የሕይወታችሁ ዘርፎች ይሖዋ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ነው፤ ይህም ከትምህርት፣ ከሥራ፣ ትዳር ከመመሥረትና ልጆች ከመውለድ ጋር በተያያዘ የምታደርጉትን ውሳኔ ይጨምራል። ከዚህም ሌላ ይሖዋን በማስደሰት ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት ሲባል መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግን ያካትታል። አምላክን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመሩ ወጣቶች በሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ይሖዋ እንደሚረዳቸው መተማመን ይችላሉ። w18.04 25 አን. 1-3

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 29

ወዮ፣ ልጄ! ልቤን ሰበርሽው፤ እንግዲህ ከቤት የማስወጣው አንቺን ነው።—መሳ. 11:35

ዮፍታሔ ድንግል የሆነች ልጁ ሕይወቷን ሙሉ ሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን ውስጥ እንድታገለግል በመስጠት ስእለቱን ፈጽሟል። (መሳ. 11:30-35) ይህ ሁኔታ ለዮፍታሔ ከባድ እንደነበር አይካድም፤ የአባቷን ውሳኔ በፈቃደኝነት ለተቀበለችው ለዮፍታሔ ሴት ልጅ ደግሞ ሁኔታው ይበልጥ ከባድ ነበር። (መሳ. 11:36, 37) ትዳር የመመሥረት፣ ልጆች የመውለድ እንዲሁም የቤተሰቡን ስም የማስጠራትና ርስት የማቆየት መብቷን ለመተው ፈቃደኛ ሆናለች። በእርግጥም የዮፍታሔ ሴት ልጅ ከማንም በላይ ማጽናኛና ማበረታቻ ያስፈልጋት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ይህም በእስራኤል ውስጥ ልማድ ሆነ፦ የእስራኤል ወጣት ሴቶች የጊልያዳዊውን የዮፍታሔን ሴት ልጅ ለማመስገን በየዓመቱ ለአራት ቀን ያህል ይሄዱ ነበር።” (መሳ. 11:39, 40) በዛሬው ጊዜ ያሉ ‘ለጌታ ነገር’ ይበልጥ ትኩረት ለመስጠት ሲሉ ሳያገቡ የሚኖሩ ክርስቲያኖችስ አድናቆት ሊቸራቸውና ማበረታቻ ሊሰጣቸው አይገባም?—1 ቆሮ. 7:32-35፤ w18.04 17 አን. 10-11

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30

መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትና ተገቢ የሆነውን የመኖሪያ ስፍራቸውን የተዉትን መላእክት . . . በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አቆይቷቸዋል።—ይሁዳ 6

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መላእክት ከሰይጣን ጋር በመተባበር በይሖዋ ላይ ዓምፀዋል። ከጥፋት ውኃው በፊት ከእነዚህ መካከል ቢያንስ የተወሰኑትን ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር የፆታ ብልግና እንዲፈጽሙ ሰይጣን ገፋፍቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ በምሳሌያዊ መንገድ ሲገልጽ፣ ዘንዶው ከሰማይ ከዋክብት መካከል አንድ ሦስተኛውን ጎትቶ ወደ ምድር እንደወረወረ ይናገራል። (ዘፍ. 6:1-4፤ ራእይ 12:3, 4) እነዚህ መላእክት የአምላክን ቤተሰብ ጥለው በመውጣት ከሰይጣን ጎን ተሰልፈዋል። ይሁንና እነዚህን ዓመፀኛ መላእክት እንደ ተራ ረብሸኞች አድርገን ልናስባቸው አይገባም። አምላክ መንግሥት እንዳለው ሁሉ ሰይጣንም የራሱን የማይታይ መስተዳድር በማቋቋም ራሱን ንጉሥ አድርጓል። ሰይጣን፣ አጋንንትን መንግሥታት አድርጎ አደራጅቷቸዋል፤ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል እንዲሁም የዓለም ገዢዎች አድርጓቸዋል። (ኤፌ. 6:12) ሰይጣን በማይታየው ድርጅቱ አማካኝነት ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት ይቆጣጠራል። w18.05 23 አን. 5-6

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 31

ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ። በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ ያርመኛል።—መዝ. 16:7

አንዳንድ ጊዜ አምላክ ለእኛ ያለውን አባታዊ ፍቅር የሚያሳየው በሚሰጠን እርማት በኩል ነው። ዳዊት እንዲህ ያለውን ደግነት የተንጸባረቀበት ምክር በፈቃደኝነት ተቀብሏል። ዳዊት በአምላክ ማሳሰቢያዎች ላይ ያሰላስል ነበር፤ በተጨማሪም የአምላክን አስተሳሰብ ለማዳበርና በእሱ አስተሳሰብ ለመቀረጽ ጥረት ያደርግ ነበር። እናንተም እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ለአምላክ ያላችሁ ፍቅርና እሱን ለመታዘዝ ያላችሁ ፍላጎት ይጨምራል። ከዚህም በላይ መንፈሳዊ ጉልምስናና ብስለት ይኖራችኋል። ክሪስቲን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ምርምር ሳደርግና ባነበብኩት ነገር ላይ ሳሰላስል ይሖዋ ያን ሐሳብ ያጻፈው ለእኔ ብሎ እንደሆነ ይሰማኛል!” መንፈሳዊ አመለካከት መያዛችሁ የምንኖርበትን ዓለምና ወደፊት የሚጠብቁትን ነገሮች በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት እይታ እንዲኖራችሁ ያስችላችኋል፤ ይህም የላቀ እውቀትና ማስተዋል ያላችሁ ሰዎች እንድትሆኑ ይረዳችኋል። አምላክ እንዲህ ያለ እውቀትና ማስተዋል የሚሰጣችሁ ለምንድን ነው? በሕይወታችሁ ውስጥ ተገቢ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ እንድትሰጡ፣ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች እንድታደርጉና የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድትጠባበቁ ስለሚፈልግ ነው።—ኢሳ. 26:3፤ w18.12 26 አን. 9-10

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ