ኅዳር
እሁድ፣ ኅዳር 1
ይህን ምግብ የሚበላ ሁሉ . . . ለዘላለም ይኖራል።—ዮሐ. 6:58
ይሖዋን ማገልገላችን የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር በሙሉ መልሰን የምናገኝበት አጋጣሚ ይከፍትልናል። አዳምና ሔዋን ይሖዋን ለማገልገል ያልመረጡት ለእሱ ጥልቅ ፍቅር ስላላዳበሩ ነው። ያም ሆኖ ይሖዋ ረዘም ያለ ዕድሜ ኖረው ልጆች እንዲወልዱና እነዚህን ልጆች ራሳቸው ባወጡት መሥፈርት መሠረት እንዲያሳድጉ ፈቅዶላቸዋል። አዳምና ሔዋን ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት ያደረጉት ውሳኔ ምን ያህል ሞኝነት የተንጸባረቀበት እንደሆነ ብዙም ሳይቆይ ታይቷል። የመጀመሪያ ልጃቸው ምንም ጥፋት የሌለበትን ወንድሙን ገድሏል፤ እንዲሁም በጊዜ ሂደት የሰው ዘር ሕይወት በዓመፅና በራስ ወዳድነት የተሞላ ሆኗል። (ዘፍ. 4:8፤ 6:11-13) ይሁንና ይሖዋ ከአዳምና ከሔዋን ልጆች መካከል እሱን ለማገልገል የመረጡትን ሁሉ የሚያድንበት መንገድ አዘጋጅቷል። (ዮሐ. 6:38-40, 57) ይሖዋ ምን ያህል ታጋሽና አፍቃሪ እንደሆነ እየተማርክ ስትሄድ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይበልጥ ማደጉ አይቀርም። አዳምና ሔዋን ከተከተሉት ጎዳና በመራቅ ራስህን ለይሖዋ መወሰን እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። w19.03 2 አን. 3፤ 4 አን. 9
ሰኞ፣ ኅዳር 2
የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ።—1 ጴጥ. 3:8
የሌላውን ስሜት የምትረዱ ለመሆን የቤተሰባችሁ አባላት ወይም የእምነት ባልንጀሮቻችሁ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመረዳት ጥረት አድርጉ። በጉባኤያችሁ ውስጥ ላሉ ወጣቶች እንዲሁም የታመሙ፣ በዕድሜ የገፉና የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ ወንድሞች አሳቢነት አሳዩ። ስላሉበት ሁኔታ ጠይቋቸው። ሐሳባቸውን ሲገልጹ በትኩረት አዳምጧቸው። ያለባቸውን ችግር በደንብ እንደምትረዱላቸው እንዲሰማቸው አድርጉ። አቅማችሁ በፈቀደ መጠን እነሱን ለመርዳት ዝግጁ እንደሆናችሁ ግለጹላቸው። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር እንዳላችሁ በተግባር ታሳያላችሁ። (1 ዮሐ. 3:18) ሌሎችን ለመርዳት ስንሞክር አቀራረባችንን እንደ ሰዎቹ ሁኔታ መቀያየር አለብን። ለምን? ምክንያቱም ሰዎች ላጋጠማቸው ችግር ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ የተለያየ ነው። አንዳንዶች ማውራት ይፈልጋሉ፤ ሌሎች ደግሞ ስለ ችግራቸው ማውራት አይፈልጉም። በመሆኑም እርዳታ መስጠት ብንፈልግም የግል ጉዳያቸውን የሚያውጣጡ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ መቆጠብ ይኖርብናል። (1 ተሰ. 4:11) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች የሚሰማቸውን አውጥተው ቢናገሩም፣ እነሱ በተናገሩት ሐሳብ የማንስማማበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ሆኖም ይህ የእነሱ ስሜት እንደሆነ ልናስታውስ ይገባል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር፣ ለመስማት የፈጠንንና ለመናገር የዘገየን መሆን እንፈልጋለን።—ማቴ. 7:1፤ ያዕ. 1:19፤ w19.03 19 አን. 18-19
ማክሰኞ፣ ኅዳር 3
በዚህ ጊዜ በጣም ፈራሁ።—ነህ. 2:2
ስለ እውነት በሰዎች ፊት መናገር ያስፈራችኋል? እስቲ ነህምያን አስታውሱ። ነህምያ በአንድ ኃያል ንጉሥ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር። በአንድ ወቅት፣ የኢየሩሳሌም ቅጥሮችና በሮች መፈራረሳቸውን በመስማቱ በጣም አዝኖ ነበር። (ነህ. 1:1-4) ነህምያ ፊቱ በሐዘን የጠቆረበትን ምክንያት እንዲናገር ንጉሡ ሲጠይቀው ምን ያህል ፈርቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን! ነህምያ ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ ከጸለየ በኋላ ለንጉሡ ምላሽ ሰጠው። ንጉሡም ነህምያ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የአምላክን ሕዝቦች ለመርዳት ብዙ ነገሮችን አድርጓል። (ነህ. 2:1-8) ሌላው ምሳሌያችን ደግሞ ዮናስ ነው። ይሖዋ ለነነዌ ነዋሪዎች መልእክት እንዲናገር ባዘዘው ጊዜ ዮናስ በጣም ከመፍራቱ የተነሳ ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ሸሽቶ ነበር። (ዮናስ 1:1-3) ሆኖም በይሖዋ እርዳታ፣ የተሰጠውን ኃላፊነት ሊወጣ ችሏል። ደግሞም ያወጀው መልእክት የነነዌ ሰዎችን በጣም ጠቅሟቸዋል። (ዮናስ 3:5-10) የነህምያ ታሪክ፣ መልስ ከመስጠታችን በፊት መጸለያችን ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ያስገነዝበናል። የዮናስ ታሪክ ደግሞ ይሖዋ፣ የሚሰማንን ከፍተኛ ፍርሃት አሸንፈን እሱን ማገልገል እንድንችል እንደሚረዳን ያስተምረናል። w19.01 11 አን. 12
ረቡዕ፣ ኅዳር 4
ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም [ቤተሰብን] የተወ ሁሉ፣ አሁን . . . 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።—ማር. 10:29, 30
ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር መወሰናችን ከወዳጆቻችንና ከዘመዶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ለምን? ኢየሱስ ተከታዮቹን አስመልክቶ “በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው” በማለት ጸልዮአል። (ዮሐ. 17:17 ግርጌ) “ቀድሳቸው” የሚለው ቃል “ለያቸው” የሚል ትርጉም ሊያስተላልፍም ይችላል። እውነትን ስንቀበል ከዓለም እንለያለን፤ ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ዓለም በፈለገው መንገድ ሊቀርጸን አይችልም። ዓለም ከሚመራበት የተለየ መሥፈርት መከተል ስለምንጀምር ሰዎች ለእኛ ያላቸው አመለካከት ይቀየራል። ሕይወታችንን የምንመራው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባለው እውነት ይሆናል። ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን መቀጠል ብንፈልግም አንዳንድ ወዳጆቻችንና የቤተሰባችን አባላት ራሳቸውን ከእኛ ሊያርቁ አልፎ ተርፎም የምናምንበትን ነገር ሊቃወሙ ይችላሉ። ይህ ሊያስደንቀን አይገባም። ምክንያቱም ኢየሱስ “በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 10:36) በተጨማሪም እውነትን በመግዛታችን የምናገኘው በረከት እውነትን ለመግዛት ስንል ከምንከፍለው ከማንኛውም መሥዋዕት በእጅጉ እንደሚበልጥ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። w18.11 6 አን. 11
ሐሙስ፣ ኅዳር 5
በአሕዛብ መካከል የሚገኙ ጉባኤዎችም ሁሉ ያመሰግኗቸዋል።—ሮም 16:4
ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ አድናቆት ነበረው፤ ይህን አድናቆቱን ደግሞ ስለ እነሱ በሚናገራቸው ነገሮች አሳይቷል። በግሉ ጸሎት ሲያቀርብ ሁልጊዜ እነሱን አስመልክቶ አምላክን ያመሰግን ነበር። በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይም ለእነሱ ያለውን አድናቆት ገልጿል። በሮም ምዕራፍ 16 ላይ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 15 ቁጥሮች ላይ ብቻ 27 የሚያህሉ ክርስቲያኖችን ስም ዘርዝሯል። ለምሳሌ ጵርስቅላና አቂላ ለእሱ ሲሉ “ሕይወታቸውን ለአደጋ [እንዳጋለጡ]” ለይቶ ጠቅሷል፤ በተጨማሪም ፌበን እሱን ጨምሮ “ለብዙ ወንድሞች ድጋፍ” እንደሆነች ተናግሯል። ጳውሎስ እነዚህን ተወዳጅና ትጉ ክርስቲያኖች አመስግኗቸዋል። (ሮም 16:1-15) ጳውሎስ ወንድሞቹና እህቶቹ ፍጽምና የጎደላቸው እንደሆኑ ያውቃል፤ ሆኖም በእነሱ ጥሩ ባሕርያት ላይ ለማተኮር መርጧል። ደብዳቤው በጉባኤ መካከል ጮክ ተብሎ ሲነበብ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ምን ያህል ተበረታተው ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ! ይህም በእነሱና በጳውሎስ መካከል ያለውን ወዳጅነት እንዳጠናከረው ምንም ጥርጥር የለውም። አንተስ የጉባኤህ አባላት ለሚናገሯቸውና ለሚያደርጓቸው ጥሩ ነገሮች ያለህን አድናቆት የመግለጽ ልማድ አለህ? w19.02 16 አን. 8-9
ዓርብ፣ ኅዳር 6
ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!—ኢዮብ 27:5
ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ፍጹም መሆን አለብን ማለት ነው? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንም እንከን እንዳለብን አልፎ ተርፎም ብዙ ስህተት እንደምንሠራ ይሰማናል። ሆኖም ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ አንችልም የሚል ስጋት ሊያድርብን አይገባም፤ ምክንያቱም ይሖዋ በጉድለቶቻችን ላይ አያተኩርም። ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ማን ሊቆም ይችል ነበር?” (መዝ. 130:3) አምላክ ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደለን እንደሆንን ስለሚያውቅ ምንጊዜም እኛን ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። (መዝ. 86:5) በተጨማሪም ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብ ስለሚረዳ ከምንችለው በላይ እንድናደርግ አይጠብቅብንም። (መዝ. 103:12-14) የይሖዋ አገልጋዮች ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ዋነኛው ነገር ፍቅር ነው። በሰማይ ላለው አባታችን ያለን ፍቅርና ታማኝነት ምንጊዜም ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን አለበት። ፈተናዎች በሚደርሱብን ጊዜም እንኳ ፍቅራችን ሙሉ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀናል ሊባል ይችላል። (1 ዜና 28:9፤ ማቴ. 22:37) ይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች እንዳሉት እንገነዘባለን፤ እንዲሁም በሰማይ ያለው አባታችንን በማስደሰት ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ለአምላክ ያለን ፍቅር ውሳኔ በምናደርግበት ወቅት ለእሱ ፈቃድ ቅድሚያ እንድንሰጥ ያነሳሳናል። በዚህ መንገድ ንጹሕ አቋም እንዳለን እናስመሠክራለን። w19.02 3 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ኅዳር 7
ልብህን ጠብቅ።—ምሳሌ 4:23
ትክክል የሆነውን ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከትን ቁጥር እምነታችን እየጠነከረ ይሄዳል። (ያዕ. 1:2, 3) ይሖዋ እኛን ልጆቼ ብሎ መጥራት እንደሚያኮራው ስለምናውቅ ልባችን በደስታ ይሞላል፤ እንዲሁም እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ይጨምራል። (ምሳሌ 27:11) የሚያጋጥመን እያንዳንዱ ፈተና፣ አሳቢ የሆነውን አባታችንን የምናገለግለው በግማሽ ልብ እንዳልሆነ የምናሳይበት አጋጣሚ ይሰጠናል። (መዝ. 119:113) ፈተናዎችን በጽናት በመወጣት ይሖዋን በሙሉ ልባችን እንደምንወደው ማለትም የእሱን ትእዛዛት ለመጠበቅና ፈቃዱን ለመፈጸም ከልባችን እንደቆረጥን እናሳያለን። (1 ነገ. 8:61) እርግጥ ነው፣ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ስለሆንን ስህተት እንደምንሠራ የታወቀ ነው። በዚህ ጊዜ የንጉሥ ሕዝቅያስን ታሪክ እናስታውስ። ሕዝቅያስ ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ንስሐ በመግባት “በሙሉ ልብ” ይሖዋን ማገልገሉን ቀጥሏል። (ኢሳ. 38:3-6፤ 2 ዜና 29:1, 2፤ 32:25, 26) እንግዲያው ሰይጣን ልባችንን በእሱ አስተሳሰብ ለመበከል የሚያደርገውን ጥረት እንቋቋም። ይሖዋ “ታዛዥ ልብ” እንዲሰጠንና ለእሱ ታማኝ ሆነን ለመኖር እንዲረዳን እንጸልይ።—1 ነገ. 3:9፤ መዝ. 139:23, 24፤ w19.01 18-19 አን. 17-18
እሁድ፣ ኅዳር 8
የውዳሴ መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ፤ ይህም ስሙን በይፋ የምናውጅበት የከንፈራችን ፍሬ ነው።—ዕብ. 13:15
በስብሰባ ላይ ሐሳብ መስጠታችን ራሳችንን ይጠቅመናል። (ኢሳ. 48:17) እንዴት? አንደኛ፣ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ለመስጠት ግብ ካወጣን ጥሩ ዝግጅት አድርገን ለመሄድ እንነሳሳለን። ጥሩ ዝግጅት ማድረጋችን የአምላክን ቃል በጥልቀት እንድንረዳ ያስችለናል። የአምላክን ቃል በጥልቀት መረዳታችን ደግሞ የተማርነውን ነገር በተሻለ መንገድ ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዳናል። ሁለተኛ፣ በውይይቱ ላይ ተሳትፎ ስለምናደርግ ስብሰባው ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል። ሦስተኛ፣ ሐሳብ መስጠት ጥረት ማድረግ የሚጠይቅ ነገር ስለሆነ የሰጠነውን መልስ በአብዛኛው ለረጅም ጊዜ እናስታውሰዋለን። በተጨማሪም እምነታችንን ስንገልጽ ይሖዋ ይደሰታል። ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ስንሰጥ እንደሚያዳምጠንና በዚህ ረገድ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሚል. 3:16) እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ብርቱ ጥረት በመባረክ አድናቆቱን ያሳየናል። (ሚል. 3:10) በግልጽ ማየት እንደምንችለው በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ እንድንሰጥ የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። w19.01 8 አን. 3፤ 9-10 አን. 7-9
ሰኞ፣ ኅዳር 9
ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።—ሮም 12:9
ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚይዛቸው ጥበብ በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕጎች ከመስጠት ይልቅ በፍቅር ሕግ እንድንመራ በትዕግሥት ያስተምረናል። እሱ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንድንከተልና ክፉ የሆነውን እንድንጠላ ይፈልጋል። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ የሰጠው ትምህርት ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፤ የተራራው ስብከት ያተኮረው መጥፎ ድርጊቶችን እንድንፈጽም በሚያነሳሳን ውስጣዊ ግፊት ላይ ነው። (ማቴ. 5:27, 28) የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ክርስቶስ፣ ከጽድቅና ከዓመፅ ጋር በተያያዘ የእሱን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ማንጸባረቅ እንድንችል በአዲሱ ዓለም ውስጥም እኛን ማስተማሩን ይቀጥላል። (ዕብ. 1:9) በተጨማሪም አካላዊና አእምሯዊ ፍጽምና ላይ እንድንደርስ ይረዳናል። እስቲ አስቡት! በዚያን ጊዜ ወደ ኃጢአት እንድናዘነብል ከሚያደርገን ግፊትም ሆነ ኃጢአት ካስከተለብን አስከፊ መዘዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንወጣለን። በመጨረሻም ይሖዋ ቃል የገባልንን “ክብራማ ነፃነት” ማጣጣም እንችላለን። (ሮም 8:21) እርግጥ ነው፣ ነፃነታችን ምንጊዜም ቢሆን ገደብ ይኖረዋል። ነፃነታችንን ሙሉ በሙሉ ተጠቅመንበታል ሊባል የሚችለው በአምላካዊ ፍቅር የምንመራ ከሆነ ብቻ ነው።—1 ዮሐ. 4:7, 8፤ w18.12 23 አን. 19-20
ማክሰኞ፣ ኅዳር 10
የፍቺ የምሥክር ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ ያሰናብታት።—ዘዳ. 24:1
አንድ እስራኤላዊ በሚስቱ ላይ “ነውር የሆነ ነገር [ካገኘባት]” ሊፈታት ይችላል። ሕጉ “ነውር” ተብሎ የሚቆጠረው ነገር ምን እንደሆነ አይገልጽም። ሆኖም ጉዳዩ ተራ ነገር ሳይሆን አሳፋሪ ወይም ከባድ ጉዳይ እንደሚሆን ግልጽ ነው። (ዘዳ. 23:14) የሚያሳዝነው ግን በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን “በማንኛውም ምክንያት” ፍቺ ይፈጽሙ ነበር። (ማቴ. 19:3) እኛ እንዲህ ያለ አመለካከት ማዳበር እንደማንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ነቢዩ ሚልክያስ አምላክ ለፍቺ ምን አመለካከት እንዳለው ግልጽ አድርጓል። በወቅቱ የነበሩ በርካታ ወንዶች ይሖዋን የማያመልኩ ወጣት ሴቶችን ለማግባት ሲሉ ክህደት በመፈጸም ‘የወጣትነት ሚስታቸውን’ ይፈቱ ነበር። አምላክ “እኔ ፍቺን እጠላለሁ” በማለት ስለዚህ ጉዳይ ያለውን አመለካከት በግልጽ ተናግሯል። (ሚል. 2:14-16) ይህም የአምላክ ቃል የመጀመሪያውን ጋብቻ አስመልክቶ ‘ሰው ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ በማለት ከሚናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ዘፍ. 2:24) ኢየሱስም “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” በማለት የአባቱን አመለካከት እንደሚጋራ አሳይቷል።—ማቴ. 19:6፤ w18.12 11 አን. 7-8
ረቡዕ፣ ኅዳር 11
አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው።—ማቴ. 9:37
አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ሄደው ለማገልገል ሁኔታቸው ፈቅዶላቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የነቢዩ ኢሳይያስ ዓይነት አመለካከት አላቸው። ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት ላቀረበው ጥያቄ ኢሳይያስ “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። (ኢሳ. 6:8) አንተስ የይሖዋን ድርጅት ለማገዝ ፈቃደኛ ነህ? ሁኔታህ እንዲህ ለማድረግ ይፈቅድልሃል? ኢየሱስ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ማቴ. 9:38) ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል ምናልባትም በዚያ ክልል አቅኚ ሆነህ መሥራት ትችል ይሆን? አሊያም ደግሞ እንዲህ እንዲያደርግ ልትረዳው የምትችለው ሰው ይኖር ይሆን? በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ ለአምላክና ለባልንጀሮቻቸው ፍቅር ማሳየት የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ የመከሩ ሠራተኞች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ወይም ክልል ውስጥ በአቅኚነት ማገልገል እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። አንተስ አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖሩ ይሆን? ይህን ማድረግ ታላቅ ደስታ ያስገኛል። w18.08 27 አን. 14-15
ሐሙስ፣ ኅዳር 12
አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ።—ዕብ. 13:5
የወንጌል ዘገባዎች ይሖዋ ለቁሳዊ ነገሮች ምን አመለካከት እንዳለው ያሳዩናል። አምላክ ልጁን እንዲያሳድጉ የመረጠው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ባልና ሚስት ነበር። (ዘሌ. 12:8፤ ሉቃስ 2:24) ማርያም ኢየሱስን ስትወልድ በእንግዶች ማረፊያ ቤት ውስጥ ቦታ ስላልተገኘ ‘ልጁን በግርግም ውስጥ ለማስተኛት’ ተገዳ ነበር። (ሉቃስ 2:7) ይሖዋ ቢፈልግ ኖሮ ልጁ በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ እንዲወለድ ማድረግ የሚችልባቸው ብዙ መንገዶች ነበሩ። ሆኖም የይሖዋ ዋነኛ ፍላጎት ልጁ መንፈሳዊ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ እንክብካቤ አግኝቶ እንዲያድግ ነበር። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ ለቁሳዊ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንድንገነዘብ ይረዳናል። አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው በቁሳዊ ነገሮች ረገድ የተሻለ ሕይወት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያምናሉ፤ ለዚህ ሲባል የልጆቻቸው መንፈሳዊ ጤንነት አደጋ ላይ ቢወድቅ እንኳ ግድ አይሰጣቸውም። ይሖዋ ግን ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ነገሮች እንደሆነ በግልጽ መረዳት እንችላለን። ታዲያ ስለዚህ ጉዳይ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አላችሁ? ድርጊታችሁ ምን ያሳያል? w18.11 24 አን. 7-8
ዓርብ፣ ኅዳር 13
አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!—መዝ. 144:15
አምላክ የደስታ ምንጭ በመሆኑ እኛም ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል፤ ደግሞም ለደስታ ምክንያት የሚሆኑ ብዙ ነገሮችን ሰጥቶናል። (ዘዳ. 12:7፤ መክ. 3:12, 13) ይሁንና በዛሬው ጊዜ ደስተኛ መሆን አስቸጋሪ ነው። ለምን? አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ለምሳሌ የምንወደው ሰው ሲሞት ወይም ከጉባኤ ሲወገድ፣ ትዳራችን ሲፈርስ አሊያም ከሥራ ስንፈናቀል ደስታችንን ልናጣ እንችላለን። ከዚህም ሌላ በቤታችን ውስጥ ጠብና ጭቅጭቅ ካለ አሊያም የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች የሚያሾፉብን ከሆነ ደስታችን እንደሚቀንስ የታወቀ ነው። በእምነታችን ምክንያት ስደት ቢደርስብን ወይም ብንታሰር አሊያም ደግሞ ሥር የሰደደ የጤና እክል ወይም የመንፈስ ጭንቀት ቢኖርብን ደስተኞች መሆን ቀላል እንደማይሆንልን ጥያቄ የለውም። ሆኖም “ደስተኛውና ብቸኛው ኃያል ገዢ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ማጽናናትና ደስታ እንዲያገኙ መርዳት እንደሚያስደስተው እናስታውስ። (1 ጢሞ. 6:15፤ ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ፣ የሰይጣን ዓለም የሚያመጣቸው ችግሮችና ፈተናዎች ቢኖሩም እንኳ ደስተኞች ለመሆን የሚረዱንን ባሕርያት በተራራ ስብከቱ ላይ ጠቅሷል። w18.09 17-18 አን. 1-3
ቅዳሜ፣ ኅዳር 14
ለሞተ ሰው ብላችሁ ሰውነታችሁን አትተልትሉ፤ ቅንድባችሁንም አትላጩ።—ዘዳ. 14:1
አንድ ሰው ለእውነት ሲል ከሚከፍላቸው በጣም ከባድ የሆኑ መሥዋዕቶች መካከል አንዱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ባሕሎችንና ልማዶችን መተው ነው። (ምሳሌ 23:23) አንዳንዶች እንዲህ ያሉትን ልማዶች እንዲተዉ የሚያነሳሷቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች መቀበል አይከብዳቸው ይሆናል፤ ሌሎች ግን ከቤተሰባቸው አባላት፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከቅርብ ጓደኞቻቸው በሚደርስባቸው ተጽዕኖ ምክንያት እነዚህን ልማዶች መተው ከባድ ይሆንባቸዋል። በተለይም የሞቱ ዘመዶችን ለማክበር ተብለው የሚደረጉ ሥርዓቶች ከስሜት ጋር የተያያዙ ስለሆኑ እነዚህን ልማዶች መተው ቀላል አይደለም። ሌሎች በዚህ ረገድ የተዉትን የድፍረት ምሳሌ መመልከታችን አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ይረዳናል። ቀደም ሲል የአስማት ድርጊት ይፈጽሙ የነበሩ በቅርቡ ወደ ክርስትና የተለወጡ የኤፌሶን ነዋሪዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለማስወገድና እውነትን ለመግዛት ሲሉ ምን እርምጃ ወሰዱ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ። የመጽሐፎቹንም ዋጋ ሲያሰሉ 50,000 የብር ሳንቲሞች ሆኖ አገኙት።” (ሥራ 19:19, 20) እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ውድ ዋጋ የከፈሉ ሲሆን በውጤቱም በዋጋ ሊተመን የማይችል በረከት አግኝተዋል። w18.11 7 አን. 15-16
እሁድ፣ ኅዳር 15
እነሱም መላውን ብሔር ገርዘው ሲጨርሱ የተገረዙት ከቁስላቸው እስኪያገግሙ ድረስ እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ቆዩ።—ኢያሱ 5:8
እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ ብዙም ሳይቆይ ኢያሱ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ አንድ ሰው ፊት ለፊቱ ቆሞ አየ። ይህ ሰው ለአምላክ ሕዝቦች ጥበቃ የሚያደርገው “የይሖዋ ሠራዊት አለቃ” ነው። (ኢያሱ 5:13-15) መሪ ሆኖ የተሾመው መልአክ የኢያሪኮ ከተማን ድል ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ለኢያሱ ግልጽ መመሪያዎች ሰጠው። መልአኩ ከሰጠው መመሪያዎች መካከል አንዳንዶቹ መጀመሪያ ላይ ውጤታማ አይመስሉም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሁሉም ወንዶች እንዲገረዙ ትእዛዝ የሰጠ ሲሆን ይህም ወንዶቹ ለተወሰኑ ቀናት መንቀሳቀስ እንዳይችሉ የሚያደርግ ነበር። (ዘፍ. 34:24, 25፤ ኢያሱ 5:2) ራሳቸውን መከላከል የማይችሉት እነዚህ የእስራኤል ወታደሮች ጠላት በሰፈራቸው ላይ ጥቃት ቢሰነዝር ቤተሰባቸውን ማዳን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ሳያሳስባቸው አይቀርም። ሆኖም አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ! ኢያሪኮ “በእስራኤላውያን የተነሳ ጥርቅም ተደርጋ [እንደተዘጋች]” የሚገልጽ ወሬ ተሰማ። (ኢያሱ 6:1) ይህ ያልተጠበቀ ሁኔታ እስራኤላውያን በአምላክ አመራር ላይ ያላቸውን እምነት ምንኛ አጠናክሮት ይሆን! w18.10 23 አን. 5-7
ሰኞ፣ ኅዳር 16
እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን።—ሥራ 14:15
ትሕትና በማሳየት ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በአንደኛ ደረጃ፣ በይሖዋ ኃይል ላከናወንነው ነገር ሌሎች ለየት ያለ አድናቆት እንዲሰጡን መጠበቅ የለብንም፤ እንዲህ ያለ አድናቆት ቢሰጠንም ልንቀበል አይገባም። ሁላችንም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ለምሰብክላቸው ሰዎች ምን አመለካከት አለኝ? አንዳንድ የማኅበረሰቡ ክፍሎችን በተመለከተ በአካባቢዬ ያሉ ብዙ ሰዎች ያላቸው ዓይነት የተዛባ አመለካከት ሳይታወቀኝ አዳብሬ ይሆን?’ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በክልላቸው ውስጥ ምሥራቹን የሚቀበሉ ተጨማሪ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው። እንዲያውም አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ማኅበረሰቡ ዝቅ አድርጎ የሚመለከታቸውን ሰዎች ቋንቋና ባሕል ተምረዋል። ይሁንና እንዲህ የሚያደርጉ ክርስቲያኖች፣ ከሚሰብኩላቸው ሰዎች እንደሚበልጡ አድርገው ራሳቸውን በፍጹም ሊመለከቱ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ለእያንዳንዱ ሰው ትኩረት በመስጠት ምሥራቹን የግለሰቡን ልብ በሚነካ መንገድ ለማቅረብ መጣር ይኖርባቸዋል። w18.09 5 አን. 9, 11
ማክሰኞ፣ ኅዳር 17
የገሊላው ይሁዳ ተነስቶ ተከታዮች አፍርቶ ነበር።—ሥራ 5:37
ሮማውያን ይሁዳን በሞት ቀጥተውታል። እንደ ይሁዳ ካሉ ከሮም አገዛዝ ነፃ መውጣት የሚፈልጉ አክራሪዎች በተጨማሪ አብዛኞቹ አይሁዳውያንም ፖለቲካዊ ለውጥ የሚያስገኝ መሲሕ ይመጣል ብለው በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። መሲሑ ሲመጣ፣ አገራቸውን ክብር እንደሚያጎናጽፋትና ከሮም ባርነት ነፃ እንደሚያወጣቸው ተስፋ ያደርጉ ነበር። (ሉቃስ 2:38፤ 3:15) ብዙዎች፣ መሲሑ በእስራኤል ውስጥ መንግሥት እንደሚያቋቁም ብሎም በተለያዩ አገሮች ተበታትነው የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ያምኑ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ በአንድ ወቅት ኢየሱስን “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል እንደጠየቀው እናስታውስ ይሆናል። (ማቴ. 11:2, 3) ዮሐንስ ይህን ያለው፣ አይሁዳውያን ተስፋ የሚያደርጓቸውን ነገሮች በሙሉ የሚፈጽም ሌላ ሰው ይመጣ እንደሆነ ለማወቅ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ፣ ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ላይ ያነጋገራቸው ሁለት ደቀ መዛሙርትም ከመሲሑ ጋር በተያያዘ ይፈጸማሉ ብለው የጠበቋቸው አንዳንድ ነገሮች እንዳልተፈጸሙ ገልጸዋል። (ሉቃስ 24:21) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የኢየሱስ ሐዋርያት “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” ብለው ጠይቀውታል።—ሥራ 1:6፤ w18.06 4 አን. 3-4
ረቡዕ፣ ኅዳር 18
ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል።—ምሳሌ 14:15
በተለይ ደግሞ የይሖዋን ሕዝብ ከሚመለከቱ ዘገባዎች ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ሰይጣን የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከሳሽ መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ። (ራእይ 12:10) ኢየሱስም ቢሆን፣ ተቃዋሚዎች “ክፉውን ሁሉ በውሸት [እንደሚያስወሩብን]” ነግሮናል። (ማቴ. 5:11) በመሆኑም የይሖዋን ሕዝብ በተመለከተ አስደንጋጭ የሆኑ ወሬዎችን ብንሰማ አንደናገጥም። ለጓደኞችህና ለምታውቃቸው ሰዎች ኢ-ሜይሎችን እና የጽሑፍ መልእክቶችን መላክ ያስደስትሃል? አዲስ የወጣ ዜና ስታይ ወይም ለየት ያለ ተሞክሮ ስትሰማ ወሬውን ማንም ሳይቀድምህ ለመናገር ትጓጓለህ? ከሆነ እንዲህ ያለውን ወሬ ለሌሎች ከመላክህ በፊት ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምልከው መረጃ እውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ? ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃስ አለኝ?’ እርግጠኛ ያልሆንክበትን መረጃ የምትልክ ከሆነ ሳይታወቅህ ለወንድሞችህ የተሳሳተ መረጃ ልታሰራጭ ትችላለህ። መረጃው ትክክል መሆኑን ከተጠራጠርክ አትላከው፤ እንዲያውም አጥፋው! w18.08 3 አን. 3፤ 4 አን. 6-7
ሐሙስ፣ ኅዳር 19
ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል።—ሉቃስ 6:38
ኢየሱስ ለጋሶች በመሆን ደስታ እንድናገኝ ይፈልጋል። ብዙዎች፣ ሌሎች ልግስና ሲያሳዩአቸው መልካም ምላሽ ይሰጣሉ። እርግጥ ነው፣ አመስጋኝ የሚሆኑት ሁሉም ሰዎች አይደሉም፤ ሆኖም ለተደረገላቸው ነገር አድናቆት የሚያሳዩ ሰዎች ልክ እንደ እኛ ለሌሎች በልግስና ለመስጠት ሊነሳሱ ይችላሉ። ስለዚህ ሰዎች አድናቆት አሳዩም አላሳዩ በልግስና ከመስጠት ወደኋላ አትበሉ። የምታከናውኑት አንድ የልግስና ተግባር እንኳ በሰዎች ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል አታውቁም። እውነተኛ ልግስና የሚያሳይ ሰው በምላሹ የሆነ ነገር ለማግኘት አይጠብቅም። ኢየሱስ ይህን ሐሳብ በአእምሮው በመያዝ የሚከተለውን ትምህርት ሰጥቷል፦ “ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፣ ሽባዎችን፣ አንካሶችንና ዓይነ ስውራንን ጥራ፤ ብድር ሊመልሱልህ ስለማይችሉ ደስተኛ ትሆናለህ።” (ሉቃስ 14:13, 14) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ለጋስ ሰው ይባረካል” ብሏል። ሌላኛው ደግሞ “ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 22:9፤ መዝ. 41:1) በእርግጥም ሌሎችን መርዳት ደስታ ስለሚያስገኝ በልግስና መስጠት ይኖርብናል። w18.08 21-22 አን. 15-16
ዓርብ፣ ኅዳር 20
በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።—ምሳሌ 3:5, 6
በዛሬው ጊዜ፣ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ማግኘትና መረጃን ገምግሞ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ መድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው። ለምን? ምክንያቱም የምናገኘው አብዛኛው መረጃ ያልተረጋገጠ ወይም ያልተሟላ ነው፤ በዚያ ላይ ደግሞ የራሳችን አለፍጽምና አለ። ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ይረዳናል? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው። አንዱ መሠረታዊ ሥርዓት፣ አንድ ሰው እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ ቢሰጥ ሞኝነት እንደሚሆንበትና ውርደት እንደሚከናነብ ይገልጻል። (ምሳሌ 18:13) ሌላው መሠረታዊ ሥርዓት ደግሞ ሳናጣራ ቃልን ሁሉ ማመን እንደሌለብን ያሳስበናል። (ምሳሌ 14:15) በተጨማሪም በእውነት ቤት ውስጥ የቱንም ያህል ተሞክሮ ቢኖረን በገዛ ራሳችን ማስተዋል ላለመመካት መጠንቀቅ ይኖርብናል። በእርግጥም አስተማማኝ የሆኑ መረጃዎችን በመጠቀም ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ለመድረስና ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ለማድረግ ከጣርን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥበቃ ይሆኑልናል። w18.08 7 አን. 19
ቅዳሜ፣ ኅዳር 21
የመንፈሳዊ ሕይወታችን አባት ለሆነው [ልንገዛ] አይገባም?—ዕብ. 12:9
በውኃ ስንጠመቅ የይሖዋ ንብረት መሆናችንን አምነን እንደተቀበልንና ራሳችንን ለእሱ ለማስገዛት ፈቃደኞች እንደሆንን በሕዝብ ፊት እናሳያለን። ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል፤ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል” ብሎ ለይሖዋ የተናገረ ያህል ነበር። (መዝ. 40:7, 8 ግርጌ) ኢየሱስ በመጠመቁ ይሖዋ ምን ተሰማው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ፤ እነሆ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤ የአምላክም መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ አየ። ደግሞም ‘በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማያት ተሰማ።” (ማቴ. 3:16, 17) ምንም እንኳ ኢየሱስ ቀድሞውንም ቢሆን በሰማይ ያለው አባቱ ንብረት የነበረ ቢሆንም ይሖዋ፣ ልጁ የእሱን ፈቃድ ብቻ ለማድረግ ራሱን በፈቃደኝነት በማቅረቡ ተደስቷል። ይሖዋ እኛም ራሳችንን ስንወስን የሚደሰት ከመሆኑም ሌላ በረከቱን ያፈስልናል።—መዝ. 149:4፤ w18.07 23 አን. 4-5
እሁድ፣ ኅዳር 22
ከዚህ ዓለት ለእናንተ ውኃ ማፍለቅ አለብን?—ዘኁ. 20:10
ሙሴ “አለብን” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ራሱንና አሮንን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም። ሙሴ የተጠቀመበት አገላለጽ የተአምሩ እውነተኛ ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ አክብሮት እንደጎደለው የሚያሳይ ነው። በመዝሙር 106:32, 33 ላይ ያለው ሐሳብም ይህን የሚደግፍ ይመስላል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በመሪባ ውኃ አጠገብ አምላክን አስቆጡት፤ በእነሱም የተነሳ ሙሴ ችግር ላይ ወደቀ። መንፈሱን አስመረሩት፤ እሱም በከንፈሮቹ በችኮላ ተናገረ።” (ዘኁ. 27:14) ሙሴ ያደረገው ነገር ይሖዋ የሚገባውን ክብር እንዳያገኝ አድርጓል። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ‘ሁለታችሁም በሰጠሁት ትእዛዝ ላይ ዓምፃችኋል’ ብሏቸዋል። (ዘኁ. 20:24) ይህ በእርግጥም በጣም ከባድ ኃጢአት ነው! ቀደም ሲል ይሖዋ እስራኤላውያን በእሱ ላይ ስላመፁ አንድ ትውልድ በሙሉ ወደ ከነአን ምድር እንዳይገባ ከልክሎ ነበር። (ዘኁ. 14:26-30, 34) በመሆኑም ይሖዋ፣ ሙሴ ለፈጸመው የዓመፅ ድርጊትም ተመሳሳይ ፍርድ መስጠቱ ተገቢና ፍትሐዊ ነው። ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከልክሏል። w18.07 14 አን. 9, 12፤ 15 አን. 13
ሰኞ፣ ኅዳር 23
ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት፣ የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው።—ሮም 14:21
ከአንተ የተለየ ሕሊና ያለውን ወንድም ላለማሰናከል ስትል መብትህ የሆኑ ነገሮችን ለመተው ፈቃደኛ ነህ? እንደምትሆን የታወቀ ነው። አንዳንድ ወንድሞቻችን ወደ እውነት ከመምጣታቸው በፊት አልኮል ከመጠን በላይ ይጠጡ ነበር፤ አሁን ግን ፈጽሞ አልኮል ላለመጠጣት ወስነዋል። ማናችንም ብንሆን ወንድማችን ቀደም ሲል የነበረው ጎጂ ልማድ እንዲያገረሽበት አስተዋጽኦ ማድረግ አንፈልግም። (1 ቆሮ. 6:9, 10) እንግዲያው አንድ ወንድም መጠጥ እንዲጠጣ ያቀረብንለትን ግብዣ ባይቀበል ልንጫነው አይገባም። ጢሞቴዎስ፣ ምሥራቹን የሚሰብክላቸውን አይሁዳውያን ላለማሰናከል ሲል በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ ተገርዟል፤ ይህን ማድረጉ ሥቃይ እንዳስከተለበት ጥያቄ የለውም። ጢሞቴዎስ እንዲህ ያለ እርምጃ መውሰዱ የሐዋርያው ጳውሎስ ዓይነት አመለካከት እንደነበረው የሚያሳይ ነው። (ሥራ 16:3፤ 1 ቆሮ. 9:19-23) አንተስ ሌሎችን ለመጥቀም ስትል እንደ ጢሞቴዎስ የግል ምርጫህን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ? w18.06 18-19 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ ኅዳር 24
ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።—ሶፎ. 3:9
ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች በደግነት ወደ እውነተኛው አምልኮ በመሳብ የመንፈሳዊ ቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። (ዮሐ. 6:44) የይሖዋ ምሥክር ያልሆነን አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ስታገኙት ስለዚያ ሰው ምን የምታውቁት ነገር ይኖራል? ከስሙና ከውጫዊ ገጽታው ባለፈ ያን ያህል መረጃ ላይኖራችሁ ይችላል። ይሖዋን የሚያውቅንና የሚወድን ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ስታገኙ ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። ግለሰቡ ከእናንተ የተለየ አስተዳደግ፣ ባሕል ወይም ጎሳ ቢኖረው አሊያም ከሌላ አገር የመጣ ቢሆን እንኳ ስለ እሱ ብዙ መረጃ ይኖራችኋል! እሱም ቢሆን ስለ እናንተ ብዙ ነገር ያውቃል። ለምሳሌ ያህል፣ ቋንቋችሁ የተለያየ ቢሆንም ሁለታችሁም የእውነትን “ንጹሕ ቋንቋ” ትናገራላችሁ። በመሆኑም ስለ አምላክ፣ ስለምትመሩባቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜና ስለ ሌሎች ጉዳዮች ያላችሁ እምነት ተመሳሳይ ነው። ደግሞም እነዚህ መረጃዎች በአንድ ግለሰብ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉን በጣም አስፈላጊ መረጃዎች ናቸው። በተጨማሪም ከሰዎች ጋር ጤናማና ዘላቂ ወዳጅነት ለመፍጠር የሚያስችሉ መሠረት ናቸው። w18.12 21 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ኅዳር 25
ካልተገረዛችሁ በቀር ልትድኑ አትችሉም።—ሥራ 15:1
በክርስቶስ አመራር ሥር ያለው የበላይ አካል አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች መገረዝ እንደማያስፈልጋቸው ግልጽ አደረገ። (ሥራ 15:19, 20) ሆኖም ይህ ውሳኔ ከተላለፈ በርካታ ዓመታት ቢያልፉም ልጆቻቸውን የሚገርዙ ብዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነበሩ። ይሁንና ‘ኢየሱስ በሞቱ አማካኝነት የሙሴን ሕግ የሻረ ቢሆንም ጉዳዩ መፍትሔ ሳያገኝ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ እንዲቆይ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። (ቆላ. 2:13, 14) አንዳንዶች አዳዲስ ማስተካከያዎችን ለመቀበል ጊዜ ይወስድባቸዋል። አይሁዳውያን ክርስቲያኖችም አመለካከታቸውን ለማስተካከል በቂ ጊዜ ያስፈልጋቸው ነበር። (ዮሐ. 16:12) አንዳንድ አይሁዳውያን አማኞች ግርዘት ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና እንዳላቸው የሚያሳይ ምልክት መሆኑ እንዳበቃ መቀበል ከብዷቸው ነበር። (ዘፍ. 17:9-12) ሌሎች ደግሞ በአይሁድ ማኅበረሰብ መካከል ለየት ብለው መታየታቸው ለስደት እንዳይዳርጋቸው ፈርተው ነበር። (ገላ. 6:12) ከጊዜ በኋላ ግን ክርስቶስ፣ ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው ደብዳቤዎች አማካኝነት ተጨማሪ መመሪያዎችን ሰጥቷል።—ሮም 2:28, 29፤ ገላ. 3:23-25፤ w18.10 24-25 አን. 10-12
ሐሙስ፣ ኅዳር 26
ቀያፋ . . . አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ቢሞት ለእነሱ የተሻለ እንደሚሆን ለአይሁዳውያን ምክር [ሰጠ]።—ዮሐ. 18:14
ቀያፋ፣ ኢየሱስን እንዲያስሩት ወታደሮች የላከው ጨለማን ተገን አድርጎ ነበር። ኢየሱስ ይህ እንደሚሆን ስላወቀ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ሰይፍ እንዲይዙ ነገራቸው። ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሊያስተምራቸው ያሰበውን ጠቃሚ ትምህርት ለማስተላለፍ ሁለት ሰይፎች በቂ ነበሩ። (ሉቃስ 22:36-38) በዚያው ምሽት ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን ሊያስሩ ከመጡት ሰዎች የአንዱን ጆሮ በሰይፍ ቆረጠው። ጴጥሮስ ይህን ያደረገው፣ ሰዎቹ ኢየሱስን በሌሊት በማሰር እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊ ድርጊት መፈጸማቸው አበሳጭቶት ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 18:10) ይሁንና ኢየሱስ “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” አለው። (ማቴ. 26:52, 53) ኢየሱስ የሰጠው ይህ ጠቃሚ ትምህርት፣ ተከታዮቹ የዓለም ክፍል መሆን እንደሌለባቸው በመግለጽ በዚያው ምሽት አቅርቦት ከነበረው ጸሎት ጋር የሚስማማ ነው። (ዮሐ. 17:16) ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ እርምጃ የመውሰድ መብት ያለው አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ እንዲህ ባለው የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ በሕዝቡ መካከል ያለውን አንድነት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!—ሶፎ. 3:17፤ w18.06 7 አን. 13-14, 16
ዓርብ፣ ኅዳር 27
ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ እጅግ ተቆጥቶ . . . ከዘሯ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።—ራእይ 12:17
ሰይጣን አጓጊ ማታለያዎችን ከማቅረብ በተጨማሪ ቀጥተኛ ጥቃት በመሰንዘር ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት እንድናጓድል ለማድረግ ይሞክራል። ለምሳሌ ያህል፣ መንግሥታት በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ እንዲጥሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል። አሊያም ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመመራት ባለን ፍላጎት ምክንያት የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች እንዲያፌዙብን ሊያደርግ ይችላል። (1 ጴጥ. 4:4) አሳቢ የሆኑ የቤተሰባችን አባላት ከጉባኤ ስብሰባዎች እንድንቀር እንዲገፋፉንም ያደርግ ይሆናል። (ማቴ. 10:36) ታዲያ እነዚህን ፈተናዎች መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰይጣን እንዲህ ያለ ቀጥተኛ ጥቃት ሊሰነዝርብን እንደሚችል መጠበቅ አለብን፤ ምክንያቱም በእኛ ላይ ጦርነት አውጇል። (ራእይ 2:10) ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ካሉት ፈተናዎች በስተ ጀርባ ያለውን ዋነኛ ጉዳይ ማስታወስ ይኖርብናል፦ ሰይጣን፣ ይሖዋን የምናገለግለው ሁኔታዎች ሲመቻቹልን ብቻ እንደሆነ በመናገር ከሶናል። ችግሮች ሲደራረቡብን አምላክን እንደምንክድ ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) በመጨረሻም፣ የደረሱብንን ፈተናዎች ለመቋቋም ብርታት እንዲሰጠን ይሖዋን መጠየቅ አለብን። ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይጥለን አንዘንጋ።—ዕብ. 13:5፤ w18.05 26 አን. 14
ቅዳሜ፣ ኅዳር 28
የትኛው እንደሚያድግ . . . አታውቅምና።—መክ. 11:6
የምንሰብከው መልእክት ወደ ሰዎች ልብ ጠልቆ እንዳልገባ ቢሰማንም እንኳ ዘር የመዝራቱ ሥራችን የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልለን መመልከት የለብንም። እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች የምንናገረውን መልእክት አያዳምጡም፤ ያም ሆኖ ሁኔታችንን ማየታቸው አይቀርም። ንጹሕና ሥርዓታማ አለባበሳችንን፣ ትሕትናችንን እንዲሁም ሞቅ ያለ ፈገግታችንን ያስተውላሉ። ምግባራችን፣ አንዳንዶች ስለ እኛ ያላቸው አሉታዊ አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን ውሎ አድሮ እንዲገነዘቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። በአቅኚነት የሚያገለግሉት ሰርዦ እና ኦሊንዳ እንዲህ ብለዋል፦ “በሕመም ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ወደዚያ አደባባይ አልሄድንም ነበር። በኋላ ላይ ተመልሰን ስንሄድ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች ‘ምነው ጠፋችሁ? ናፍቃችሁን ነበር’ አሉን።” በእርግጥም የመንግሥቱን ዘር ከመዝራት ‘እጃችን ሥራ እስካልፈታ’ ድረስ ‘ለብሔራት ሁሉ ምሥክርነት’ በመስጠቱ ሥራ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከት እንችላለን። (ማቴ. 24:14) ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ሞገስ እንደምናገኝ ማወቃችን ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል፤ ምክንያቱም ይሖዋ “በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ” ሰዎችን ሁሉ ይወዳል።—ሉቃስ 8:15፤ w18.05 16 አን. 16-18
እሁድ፣ ኅዳር 29
አምላክ . . . በሚደርስብን መከራ ሁሉ ያበረታታናል።—2 ቆሮ. 1:3, 4 ግርጌ
የሰው ዘር በኃጢአት ከወደቀበትና ፍጽምናውን ካጣበት ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ማበረታቻ በመስጠት ረገድ ግሩም ምሳሌ መሆኑን አሳይቷል። በኤደን ዓመፅ በተነሳበት ወቅት ይሖዋ ገና ወደፊት ለሚወለዱት የአዳም ዘሮች ወዲያውኑ አበረታች የሆነ ተስፋ ሰጥቷል። በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ትርጉሙን ለተረዱት የሰው ዘሮች ሁሉ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነበር፤ ይህ ትንቢት “የጥንቱ እባብ” ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስ ከጊዜ በኋላ ከነክፉ ሥራዎቹ እንደሚጠፋ ይገልጻል። (ራእይ 12:9፤ 1 ዮሐ. 3:8) የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ኖኅ የኖረው ፈሪሃ አምላክ በሌለው ዓለም ውስጥ ሲሆን በዚያ ወቅት ከነበሩት ሰዎች መካከል ይሖዋን የሚያመልከው የእሱ ቤተሰብ ብቻ ነበር። በወቅቱ ዓመፅና ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነት በጣም ከመስፋፋቱ የተነሳ ኖኅ ተስፋ ሊቆርጥ ይችል ነበር። (ዘፍ. 6:4, 5, 9, 11፤ ይሁዳ 6) ይሁንና ይሖዋ ያን ክፉ ዓለም እንደሚያጠፋው ለኖኅ የነገረው ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቡን ለማዳን ምን ማድረግ እንዳለበት ገልጾለታል። (ዘፍ. 6:13-18) በእርግጥም ይሖዋ ለኖኅ የብርታት ምንጭ ሆኖለታል። w18.04 15 አን. 1-2
ሰኞ፣ ኅዳር 30
አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።—1 ተሰ. 5:11
በባሕርያችን ከሰዎች ጋር መግባባት ስለሚከብደን ብቻ ሌሎችን ማበረታታት እንደማንችል የሚሰማን ከሆነ ተሳስተናል። ለሌሎች የብርታት ምንጭ መሆን ያን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፤ አንድን ሰው ሰላም ስንለው ሞቅ ያለ ፈገግታ ማሳየታችን ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ መልሶ ፈገግ ካላለ ይህ አንድ ችግር እንዳለ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ግለሰቡ ሲናገር ማዳመጣችን ብቻ ያጽናናው ይሆናል። (ያዕ. 1:19) ሁላችንም ማጽናኛ ለሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች የብርታት ምንጭ መሆን እንችላለን። ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል ምንኛ መልካም ነው! ብሩህ ዓይን [ወይም “በፈገግታ የተሞላ ፊት”] ልብን ደስ ያሰኛል፤ መልካም ዜናም አጥንትን ያበረታል።” (ምሳሌ 15:23, 30) ጳውሎስ የመንግሥቱን መዝሙሮች በአንድነት መዘመር እንኳ የብርታት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። (ሥራ 16:25፤ ቆላ. 3:16) የይሖዋ ቀን ይበልጥ ‘እየቀረበ ሲመጣ’ እርስ በርስ መበረታታት ይበልጥ አስፈላጊ እየሆነ ይሄዳል። ዕብ. 10:25፤ w18.04 23 አን. 16፤ 24 አን. 18-19