የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es21 ገጽ 67-77
  • ሐምሌ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐምሌ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 1
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 2
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 3
  • እሁድ፣ ሐምሌ 4
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 5
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 6
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 7
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 8
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 9
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 10
  • እሁድ፣ ሐምሌ 11
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 12
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 13
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 14
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 15
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 16
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 17
  • እሁድ፣ ሐምሌ 18
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 19
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 20
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 21
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 22
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 23
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 24
  • እሁድ፣ ሐምሌ 25
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 26
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 27
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 28
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 29
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 30
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2021
es21 ገጽ 67-77

ሐምሌ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 1

ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።—ፊልጵ. 4:6

ሌሎች፣ ስሜት የሚጎዳ ነገር ሲናገሩን አሊያም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጉብን ጉዳዩ ይረብሸን ይሆናል። በተለይ ደግሞ ይህን ያደረገው የቅርብ ወዳጃችን ወይም የቤተሰባችን አባል ከሆነ ሁኔታው በጣም ይጎዳናል። የሚያስጨንቅ ነገር በሚያጋጥመን ጊዜ፣ ጣውንቷ እጅግ ትሳለቅባት የነበረችውን የሐናን ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በማንበብ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (1 ሳሙ. 1:12) ልክ እንደ ሐና ጭንቀታችንንና ስጋታችንን ግልጽልጽ አድርገን ለይሖዋ በመንገር ረዘም ያለ ጸሎት ማቅረብ እንችላለን። ስንጸልይ ባማረና በደንብ በተቀናበረ መንገድ ሐሳባችንን መግለጽ እንዳለብን ሊሰማን አይገባም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ እንባ እየተናነቀን ምሬት የተሞላበት ነገር እንናገር ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ እኛን መስማት መቼም ቢሆን አይታክተውም። ስለ ችግሮቻችን ከመጸለይ በተጨማሪ በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘውን ምክር ማስታወሳችን አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የምስጋና ጸሎት ማቅረብ እንዳለብን በግልጽ ተናግሯል። ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ስለሰጠን ሕይወት፣ ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ፣ ስለ ታማኝ ፍቅሩ እንዲሁም ስለሰጠን አስደናቂ ተስፋ ልናመሰግነው እንችላለን። w20.02 21-22 አን. 3, 6

ዓርብ፣ ሐምሌ 2

[ለመናገር] ጊዜ አለው።—መክ. 3:7

የመናገር ችሎታ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ነው። (ዘፀ. 4:10, 11፤ ራእይ 4:11) ይሖዋ ይህን ስጦታ በአግባቡ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ በቃሉ አማካኝነት ያስተምረናል። ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ ለመናገር ምንጊዜም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። (ማቴ. 24:14፤ ሮም 10:14) እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣበት አንዱ ምክንያት ስለ አባቱ የሚገልጸውን እውነት ለሰዎች ለማስተማር ነው። (ዮሐ. 18:37) ይሁንና የምንናገርበት መንገድም ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ማስታወስ አለብን። ስለ ይሖዋ የምንናገረው “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ሊሆን ይገባል፤ እንዲሁም ለግለሰቡ ስሜትና እምነት አክብሮት ማሳየት ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 3:15) እንዲህ ካደረግን ንግግራችን ወሬ ከመሆን ባለፈ ለግለሰቡ ትምህርት የሚሰጥና ልቡን የሚነካ ይሆናል። ሽማግሌዎች አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ምክር እንደሚያስፈልጋቸው ካስተዋሉ ከመናገር ወደኋላ ሊሉ አይገባም። እርግጥ ነው ግለሰቡ እንዳይሸማቀቅ የሚናገሩበትን ጊዜ በጥበብ መምረጥ ይኖርባቸዋል። w20.03 18-19 አን. 2-4

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 3

ሳታሰልሱ . . . ጸልዩ።—ማቴ. 26:41

ስለ ምን ነገር መጸለይ እንችላለን? “እምነት ጨምርልን” በማለት ወደ ይሖዋ ልንጸልይ እንችላለን። (ሉቃስ 17:5፤ ዮሐ. 14:1) ሰይጣን የኢየሱስን ተከታዮች በሙሉ ስለሚፈትን እምነት ያስፈልገናል። (ሉቃስ 22:31) ይሁንና እምነት የሚረዳን እንዴት ነው? እምነት፣ አንድን ፈታኝ ሁኔታ ለመወጣት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን በኋላ የቀረውን ለይሖዋ እንድንተው ያነሳሳናል። ይሖዋ ጉዳዩን ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ሊይዘው እንደሚችል ስለምንተማመን ውስጣዊ ሰላም እናገኛለን። (1 ጴጥ. 5:6, 7) ጸሎት ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል። በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙትን ሮበርት የተባሉ አንድ ታማኝ የጉባኤ ሽማግሌ ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብለዋል፦ “በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘው ምክር በሕይወቴ ውስጥ ያጋጠሙኝን ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድወጣ ረድቶኛል። የኢኮኖሚ ችግር ያጋጠመኝ ወቅት ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደግሞ በሽምግልና የማገልገል መብቴን አጥቼ ነበር።” ታዲያ ወንድም ሮበርት ውስጣዊ ሰላማቸውን ጠብቀው መኖር የቻሉት እንዴት ነው? “ጭንቀት ሲሰማኝ ወዲያውኑ እጸልያለሁ። በተደጋጋሚ አጥብቄ በጸለይኩ ቁጥር ይበልጥ ውስጣዊ ሰላም አገኛለሁ” በማለት ተናግረዋል። w19.04 9-10 አን. 5-7

እሁድ፣ ሐምሌ 4

አንተን፣ አዎ ከማንም በላይ አንተን በደልኩ።—መዝ. 51:4

ሕፃናትን ማስነወር በአምላክ ላይ የሚፈጸም ኃጢአት ነው። አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ ኃጢአት ሲሠራ በይሖዋም ላይ ኃጢአት እንደሠራ ይቆጠራል። አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠው አንድ ሕግ ይህን ሐቅ ያስገነዝበናል። ሕጉ ባልንጀራውን የሚያታልል ሰው “በይሖዋ ላይ ታማኝነት የማጉደል ተግባር [እንደሚፈጽም]” ይናገራል። (ዘሌ. 6:2-4) በመሆኑም ሕፃናትን የሚያስነውር አንድ የጉባኤው አባል፣ ጥቃት የተፈጸመበትን ልጅ ስለሚያታልል በይሖዋ ላይ ታማኝነት የማጉደል ተግባር ይፈጽማል። ልጁ እምነት በሚጥልበት ሰው እንዲህ ያለ በደል ስለተፈጸመበት ከዚያ በኋላ የመረጋጋት ስሜት አይሰማውም። በተጨማሪም በልጆች ላይ ፆታዊ ጥቃት የሚፈጽም ክርስቲያን በይሖዋ ስም ላይ ከፍተኛ ነቀፋ ያስከትላል። በእርግጥም ሕፃናትን ማስነወር፣ በአምላክ ላይ የሚፈጸም ከባድ ኃጢአት ስለሆነ ሊወገዝ ይገባል። ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ከደረሰባቸው ስሜታዊ ቁስል ማገገም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ፣ ሌሎች እነሱን መርዳትና ማበረታታት የሚችሉት እንዴት እንደሆነና ወላጆች ልጆቻቸውን ከዚህ ጥቃት መጠበቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚያብራሩ ርዕሶች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ወጥተዋል። ሽማግሌዎች ሕፃናትን ከማስነወር ጋር የተያያዙ ኃጢአቶችን ስለሚይዙበት መንገድ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ሰፊ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ወደፊትም ቢሆን ድርጅቱ እንዲህ ያሉ ኃጢአቶች የሚያዙበትን መንገድ እየገመገመ ማስተካከያ ማድረጉን ይቀጥላል። w19.05 9-10 አን. 8-9

ሰኞ፣ ሐምሌ 5

ስለ ሕያዋን . . . ሙታንን መጠየቁ ተገቢ ነው?—ኢሳ. 8:19

ጠላትን ለማሸነፍ እንደሚያስችል ስለታም ሰይፍ ሁሉ የአምላክ ቃልም የሰይጣንን ውሸቶች በማጋለጥ የጠላታችንን ጥረቶች ውድቅ ያደርጋል። (ኤፌ. 6:17) ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ ቃል ‘የሞቱ ሰዎች በሕይወት ያሉትን ሊያነጋግሩ ይችላሉ’ የሚለው ትምህርት ውሸት መሆኑን ያጋልጣል። (መዝ. 146:4) በተጨማሪም አስተማማኝ በሆነ መንገድ ስለ ወደፊቱ ጊዜ መናገር የሚችለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ ይገልጻል። (ኢሳ. 45:21፤ 46:10) የአምላክን ቃል አዘውትረን የምናነብና የምናሰላስልበት ከሆነ ክፉ መናፍስት በሚያስፋፏቸው ውሸቶች አንታለልም፤ እንዲያውም ለእነዚህ ውሸቶች ጥላቻ እናዳብራለን። እንግዲያው ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ንክኪ ካለው ከማንኛውም ነገር ራቁ። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በማንኛውም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት አንካፈልም። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ መናፍስት ጠሪዎች አንሄድም፤ አሊያም በሌላ በየትኛውም መንገድ ተጠቅመን የሞቱ ሰዎችን ለማነጋገር አንሞክርም። ‘ሙታን በሌላ ዓለም እየኖሩ ነው’ በሚለው እምነት ላይ ከተመሠረቱ የቀብር ልማዶች እንርቃለን። በተጨማሪም በኮከብ ቆጠራ ወይም በጥንቆላ አማካኝነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ጥረት አናደርግም። እንዲህ ያሉት ድርጊቶች በሙሉ በጣም አደገኛ እንደሆኑ ብሎም ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር በቀጥታ ሊያነካኩን እንደሚችሉ እናውቃለን። w19.04 21-22 አን. 8-9

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 6

አምላክ እንደ ልባቸው ምኞት . . . ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው።—ሮም 1:24

የዚህን ዓለም ጥበብ የሚከተሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምክንያታዊነት የጎደላቸው እንደሆኑ በመናገር እነዚህን መሥፈርቶች ያቃልላሉ። ምናልባትም ‘አምላክ የፆታ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ከፈጠረን በኋላ ይህን ፍላጎታችንን እንዳናረካ የሚከለክለን ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚያነሱት፣ ‘ሰዎች ውስጣቸው የገፋፋቸውን ነገር ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል’ የሚል የተሳሳተ አመለካከት ስላላቸው ነው። የአምላክ ቃል ግን ከዚህ የተለየ ትምህርት ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለሰው ልጆች ተገቢ ያልሆኑ ውስጣዊ ግፊቶችን የመቆጣጠር ችሎታ በመስጠት እንዳከበራቸው ይገልጻል። (ቆላ. 3:5) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሰዎች የፆታ ስሜታቸውን ተገቢ በሆነ መንገድ ማርካት የሚችሉበትን የጋብቻ ዝግጅት አድርጎላቸዋል። (1 ቆሮ. 7:8, 9) ከዚህ ዓለም ጥበብ በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ጤናማ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል። የፆታ ግንኙነት ደስታ የሚያስገኝ ነገር እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 5:18, 19) በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል በመቆጣጠር እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። ይህም . . . ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን።”—1 ተሰ. 4:4, 5፤ w19.05 22-23 አን. 7-9

ረቡዕ፣ ሐምሌ 7

አንተም በእነሱ ላይ እንደ አውሎ ነፋስ ትመጣለህ፤ አንተና ወታደሮችህ ሁሉ እንዲሁም ከአንተ ጋር ያሉት ብዙ ሕዝቦች።—ሕዝ. 38:9

አምላክ ብሔራት ሕዝቡን እንዲያጠፉ አይፈቅድም። ምክንያቱም ሕዝቡ በእሱ ስም የሚጠሩ ከመሆኑም ሌላ ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲወጡ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ጠብቀዋል። (ሥራ 15:16, 17፤ ራእይ 18:4) በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲወጡ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በመሆኑም የይሖዋ አገልጋዮች በዚህች አመንዝራ ላይ የሚመጣው “መቅሰፍት ተካፋይ” አይሆኑም። ያም ሆኖ እምነታቸውን የሚፈትን ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። (ሕዝ. 38:2, 8) የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች በሙሉ ተጠራርገው ከጠፉ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ከከባድ አውሎ ነፋስ ብቻዋን እንደተረፈች ዛፍ አውላላ ሜዳ ላይ ተጋልጠው ይታያሉ። ይህ ሰይጣንን እንደሚያስቆጣው የታወቀ ነው። ‘በመንፈስ የተነገሩ ርኩሳን ቃላትን’ ማለትም አጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳዎችን ተጠቅሞ ብሔራት ግንባር ፈጥረው በአምላክ ሕዝቦች ላይ እንዲነሱ በማድረግ ቁጣውን ይገልጻል። (ራእይ 16:13, 14) ይህ የብሔራት ጥምረት ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ይባላል። ብሔራት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ፣ አርማጌዶን ተብሎ ወደሚጠራው ምሳሌያዊ ቦታ እንደደረሱ ይቆጠራል።—ራእይ 16:16፤ w19.09 11 አን. 12-13

ሐሙስ፣ ሐምሌ 8

የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ [ነው]።—1 ቆሮ. 3:20

በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ሰይጣን፣ የፆታ ብልግና ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ በሐሰት አምልኮ ተጠቅሟል። ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል። የሐሰት ሃይማኖቶች፣ የፆታ ብልግናን በቸልታ ማለፋቸው ሳያንስ እንዲህ ያለው ምግባር ተቀባይነት እንዲያገኝም አድርገዋል። በመሆኑም አምላክን እንደሚያገለግሉ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች፣ በግልጽ የተቀመጡትን የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አይከተሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሐሰት ሃይማኖቶች አካሄድ ያስከተለውን ውጤት ገልጿል። (ሮም 1:28-31) ‘መደረግ የማይገባው ነገር’ የሚለው አገላለጽ ግብረ ሰዶምን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ብልግና ያካትታል። (ሮም 1:24-27, 32፤ ራእይ 2:20) እኛ ግን ግልጽ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በጥብቅ መከተላችን በጣም አስፈላጊ ነው! ዓለማዊ ፍልስፍና፣ የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ችላ እንዲባሉ የሚያደርግ አሊያም ከእነዚህ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ ነው። የአምላክን መንፈስ ፍሬ ከማፍራት ይልቅ ‘የሥጋ ሥራዎችን’ እንድንከተል ያበረታታናል። (ገላ. 5:19-23) ሰዎች ኩሩና ትዕቢተኛ እንዲሆኑ ያደርጋል፤ ይህም “ራሳቸውን የሚወዱ” ሰዎች እንዲበዙ አድርጓል። (2 ጢሞ. 3:2-4) እነዚህ ባሕርያት፣ ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ከሚጠብቀው የገርነትና የትሕትና መንፈስ ፍጹም ተቃራኒ ናቸው።—2 ሳሙ. 22:28፤ w19.06 5-6 አን. 12-14

ዓርብ፣ ሐምሌ 9

እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።—ምሳሌ 17:17

ኤልያስ፣ ይሖዋን ያገለገለው አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ሲሆን ከበድ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመውታል። ኤልያስ ካሉበት ኃላፊነቶች አንዳንዶቹን ለኤልሳዕ እንዲሰጠው ይሖዋ ነግሮት ነበር፤ በዚህ መንገድ ይሖዋ፣ ኤልያስ ጭንቀቱን የሚያካፍለው ወዳጅ እንዲያገኝ አድርጓል። እኛም በተመሳሳይ የሚሰማንን ነገር አውጥተን ለምናምነው ወዳጃችን መናገራችን፣ ጭንቀታችን ቀለል እንዲለን ሊረዳን ይችላል። (2 ነገ. 2:2) የልባችሁን የምታካፍሉት ሰው እንደሌለ ከተሰማችሁ፣ ሊያበረታታችሁ የሚችል የጎለመሰ ክርስቲያን ለማግኘት እንዲረዳችሁ ይሖዋን ጠይቁት። ኤልያስ ያጋጠመውን አስጨናቂ ሁኔታ እንዲቋቋምና ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት እንዲያገለግል ይሖዋ ረድቶታል። የኤልያስ ተሞክሮ ተስፋ ይሰጠናል። እኛም በጭንቀት ከመዋጣችን የተነሳ ኃይላችን የሚሟጠጥበትና ስሜታችን የሚደቆስበት ጊዜ ይኖራል። በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ግን እሱን ማገልገላችንን ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል።—ኢሳ. 40:28, 29፤ w19.06 15 አን. 4፤ 16 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 10

ሰውን መፍራት ወጥመድ ነው፤ በይሖዋ የሚታመን ግን ጥበቃ ያገኛል።—ምሳሌ 29:25

የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች በመስበክ ከአሁኑ ድፍረት ማዳበር እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የስብከቱ ሥራ በይሖዋ እንድንታመንና የሰው ፍርሃትን እንድናሸንፍ ስለሚረዳን ነው። ስፖርት ስንሠራ ጡንቻችን እንደሚዳብር ሁሉ ከቤት ወደ ቤት፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድና በንግድ ቦታዎች ስናገለግል ድፍረታችን እየጨመረ ይሄዳል። ለመስበክ የሚያስፈልገንን ድፍረት ከአሁኑ ካዳበርን ወደፊት ሥራችን ቢታገድም እንኳ መስበካችንን ለመቀጠል ዝግጁ እንሆናለን። (1 ተሰ. 2:1, 2) አስደናቂ ድፍረት ያሳየችን አንዲት እህት ምሳሌ በመመልከት ብዙ መማር እንችላለን። ናንሲ ዩወን ቁመቷ ከ1.5 ሜትር አይበልጥም፤ ሆኖም በቀላሉ የምትበረግግ ሴት አልነበረችም። የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበኳን እንድታቆም ቢነገራትም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህም የተነሳ በኮሚኒስት ቻይና ውስጥ ለ20 ዓመታት ታስራለች። ምርመራ ያደረጉባት ባለሥልጣናት “በአገራችን ውስጥ እንደዚህች ዓይነት ግትር ሴት አይተን አናውቅም!” በማለት ተናግረዋል። w19.07 5 አን. 13-14

እሁድ፣ ሐምሌ 11

ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19

አንዳንድ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች የመማር ጉጉት አላቸው፤ በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ብዙዎቹ ሰዎች ግን መጀመሪያ ላይ ያን ያህል ፍላጎት ያላቸው አይመስሉ ይሆናል። ስለዚህ ፍላጎታቸውን ለመቀስቀስ ጥረት ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። በአገልግሎታችን ስኬታማ ለመሆን በሚገባ መዘጋጀት ያስፈልገናል። የምታገኛቸውን ሰዎች ሊማርኩ የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮችን ምረጥ። ከዚያም ምን መግቢያ እንደምትጠቀም ተዘጋጅ። ለምሳሌ ያህል፣ የቤቱን ባለቤት እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ፦ “ስለ አንድ ጉዳይ ያለህን አመለካከት ልጠይቅህ ፈልጌ ነበር። በዛሬው ጊዜ ብዙ ችግሮች ያጋጥሙናል። እነዚህን ችግሮች ሊያስወግድ የሚችል መንግሥት ሊኖር የሚችል ይመስልሃል?” ከዚያም ዳንኤል 2:44⁠ን ጠቅሰህ ልታብራራለት ትችላለህ። አሊያም ደግሞ የምታነጋግረውን ሰው “ጨዋ ልጆችን ለማሳደግ ሚስጥሩ ምን ይመስልሃል?” ልትለው ትችላለህ። ከዚያም ዘዳግም 6:6, 7⁠ን ጠቅሰህ አብራራለት። ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ስንረዳ ወደር የሌለው ደስታ እንደምናገኝ ምንም ጥርጥር የለውም። w19.07 15 አን. 4, 6-7

ሰኞ፣ ሐምሌ 12

ሰው ለራሱ አማልክት ሊሠራ ይችላል? የሚሠራቸው አማልክት እውነተኛ አማልክት አይደሉም።—ኤር. 16:20

በሩቅ ምሥራቅ ለሚኖሩ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች በመስበክ ብዙ ተሞክሮ ያካበተ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ብዙውን ጊዜ፣ በዚህ አካባቢ የሚኖር ሰው ‘በአምላክ አላምንም’ ሲል በአካባቢው ያሉ በርካታ ሰዎች የሚያመልኳቸውን አማልክት እንደማያመልክ መናገሩ ነው። ስለዚህ እኔም አብዛኞቹ አማልክት ሰዎች የፈጠሯቸው እንደሆኑና እውነተኛ እንዳልሆኑ እነግረዋለሁ። ከዚያም በኤርምያስ 16:20 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነብለታለሁ። ቀጥሎም ‘እውነተኛውን አምላክ ሰዎች ከሠሯቸው አማልክት መለየት የምንችለው እንዴት ነው?’ ብዬ እጠይቀዋለሁ። የሚሰጠውን ምላሽ በጥሞና ካዳመጥኩ በኋላ ‘አማልክት መሆናችሁን እንድናውቅ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ንገሩን’ የሚለውን በኢሳይያስ 41:23 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አነብለታለሁ። ከዚያም ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከተናገራቸው ትንቢቶች አንዱን አሳየዋለሁ።” አንድ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ጥበብ ያዘሉ ምክሮች፣ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች እንዲሁም የተፈጥሮ ሕጎች አሳያቸዋለሁ። ከዚያም እነዚህ ነገሮች፣ ሕያውና ጥበበኛ የሆነ ፈጣሪ ለመኖሩ እንዴት ማስረጃ እንደሚሆኑ አስረዳቸዋለሁ። አንድ ሰው የአምላክን መኖር በተመለከተ አመለካከቱ በተወሰነ መጠን እየተለወጠ እንደሆነ ካስተዋልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ምን እንደሚል አሳየዋለሁ።” w19.07 23-24 አን. 14-15

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 13

ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10

አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ከተባሉት መካከል የይሖዋ ስም መቀደስ፣ የዓላማው መፈጸም እንዲሁም የጉባኤው ሰላምና አንድነት ይገኙበታል። (ማቴ. 6:9, 10፤ ዮሐ. 13:35) ሕይወታችን በዋነኝነት ያተኮረው በእነዚህ አስፈላጊ ነገሮች ላይ ከሆነ ይሖዋን እንደምንወደው እያሳየን ነው። ጳውሎስ ‘እንከን የማይገኝብን እንድንሆንም’ መክሮናል። ይህ ሲባል ፍጹም መሆን አለብን ማለት አይደለም። ሆኖም ፍቅራችን እየጨመረ እንዲሄድ የተቻለንን ሁሉ የምናደርግና ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይተን የምናውቅ ከሆነ ይሖዋ እንከን የማይገኝብን እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል። ፍቅራችንን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ ሌሎችን ላለማሰናከል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ነው። “ሌሎችን እንዳታሰናክሉ” የሚለው ምክር በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ማሳሰቢያ ነው። ለመሆኑ ሌሎችን ልናሰናክል የምንችለው እንዴት ነው? የመዝናኛ ምርጫችን፣ አለባበሳችን ሌላው ቀርቶ ሰብዓዊ ሥራችን እንኳ ሌሎችን ሊያሰናክል ይችላል። የምናደርገው ነገር በራሱ ስህተት ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የምናደርገው ምርጫ የሌላን ሰው ሕሊና የሚረብሽና ግለሰቡ እንዲሰናከል የሚያደርግ ከሆነ ጉዳዩን አቅልለን ልንመለከተው አይገባም።—ማቴ. 18:6፤ w19.08 10 አን. 9-11

ረቡዕ፣ ሐምሌ 14

እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።—ራእይ 7:14

ከ1935 አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው እጅግ ብዙ ሕዝብ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ታማኝ ክርስቲያኖች ያቀፈ ቡድን እንደሆነ ተገነዘቡ። (ራእይ 7:9, 10) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ከታላቁ መከራ ለመትረፍ የሺህ ዓመቱ ግዛት ከመጀመሩ በፊት የይሖዋን መንገዶች መማር ይኖርባቸዋል። ወደፊት “መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች [ለማምለጥ]” የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው ማሳየት አለባቸው። (ሉቃስ 21:34-36) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት በተዘረጋላቸው ተስፋ ደስተኞች ናቸው። ታማኝ አምላኪዎቹ የሚያገለግሉት በሰማይ ይሁን በምድር የሚወስነው ይሖዋ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ቅቡዓንም ሆኑ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ሽልማታቸውን ሊያገኙ የቻሉት በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት በተገለጠው የይሖዋ ጸጋ የተነሳ እንደሆነ ይረዳሉ።—ሮም 3:24፤ w19.09 28 አን. 10፤ 29 አን. 12-13

ሐሙስ፣ ሐምሌ 15

የይሖዋ ደስታ ብርታታችሁ [ነው]።—ነህ. 8:10 ግርጌ

አዲስ ምድብ ተሰጥቷችኋል? በዚህ ምድባችሁ ላይ ውጤታማ መሆን ትችላላችሁ። የአገልግሎት ምድባችሁ የተለወጠው በቀድሞ ምድባችሁ ላይ በደንብ ስላልሠራችሁ ወይም ያን ያህል ጠቃሚ ስላልሆናችሁ እንደሆነ አታስቡ። ይሖዋ በሕይወታችሁ ውስጥ እያደረገላችሁ ያለውን ነገር አስተውሉ፤ እንዲሁም መስበካችሁን ቀጥሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ታማኝ ክርስቲያኖች ምሳሌ ተከተሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች “በሄዱበት ቦታ ሁሉ የአምላክን ቃል ምሥራች [ሰብከዋል]።” (ሥራ 8:1, 4) እናንተም መስበካችሁን ከቀጠላችሁ ጥሩ ውጤት ልታገኙ ትችላላችሁ። አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ ከአንድ አገር እንዲወጡ የተደረጉ የተወሰኑ አቅኚዎች ወደ ጎረቤት አገር ሄዱ፤ በዚያም የእነሱን ቋንቋ የሚናገሩ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ሰዎች አገኙ። በዚህም የተነሳ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ ፈጣን እድገት የሚያደርጉ ቡድኖች መቋቋም ችለዋል። ከምንም በላይ የሚያስደስተን ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና መሆን አለበት። ስለዚህ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና ጠብቃችሁ ኑሩ፤ እንዲሁም ጥበብ፣ መመሪያና እርዳታ ለማግኘት በእሱ መታመናችሁን ቀጥሉ። የቀድሞ የአገልግሎት ምድባችሁን እንድትወዱት ያደረጋችሁ እዚያ ያሉትን ሰዎች ለመርዳት ከልባችሁ ጥረት ማድረጋችሁ እንደሆነ አስታውሱ። በአዲሱ የአገልግሎት ምድባችሁም ከልባችሁ ለመሥራት ጥረት አድርጉ፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ አዲሱን ምድባችሁንም እንድትወዱት እንደሚረዳችሁ ማየት ትችላላችሁ።—መክ. 7:10፤ w19.08 24-25 አን. 15-16

ዓርብ፣ ሐምሌ 16

አባት ለሆነው ይበልጥ በፈቃደኝነት [ልንገዛ] አይገባም?—ዕብ. 12:9

ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ ልንገዛለት ይገባል። ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ለፍጥረታቱ መመሪያዎችን የማውጣት መብት አለው። (ራእይ 4:11) ሆኖም ለይሖዋ እንድንገዛ የሚገፋፋን ሌላም ምክንያት አለ፤ ይህም የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ መሆኑ ነው። በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ሰብዓዊ ገዢዎች ሌሎች ሰዎችን ሲገዙ ቆይተዋል። ከእነዚህ ገዢዎች ጋር ሲነጻጸር ይሖዋ እጅግ ጥበበኛ፣ አፍቃሪ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ ገዢ ነው። (ዘፀ. 34:6፤ ሮም 16:27፤ 1 ዮሐ. 4:8) በሁሉም ነገር ይሖዋን ለመታዘዝ የቻልነውን ሁሉ በማድረግና በራሳችን ማስተዋል እንዳንመካ በመጠንቀቅ ለይሖዋ እንደምንገዛ ማሳየት እንችላለን። (ምሳሌ 3:5) ማራኪ ስለሆኑት የይሖዋ ባሕርያት እያወቅን ስንሄድ ለእሱ መገዛት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያቱ ይሖዋ በሚያደርገው በማንኛውም ነገር ላይ በግልጽ ይታያሉ። (መዝ. 145:9) ስለ ይሖዋ ይበልጥ ባወቅን ቁጥር ለእሱ ያለን ፍቅር እየጨመረ ይሄዳል። ለይሖዋ ፍቅር ካለን ደግሞ ማድረግ ስላለብንና ስለሌለብን ነገር የሚገልጹ ዝርዝር ሕጎች አያስፈልጉንም። w19.09 14 አን. 1, 3

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 17

ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነው።—ማቴ. 11:30

ሰይጣን በሰዎች ላይ ሊሸከሙት የማይችሉት ሸክም ይጭንባቸዋል። ለምሳሌ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንደማይለንና ፈጽሞ ሊወደን እንደማይችል እንድናምን ይፈልጋል። ይህ ውሸት ከባድ ሸክም ከመሆኑም ሌላ ስሜት የሚደቁስ ነው! (ዮሐ. 8:44) ክርስቶስ “ወደ እኔ ኑ” በማለት ያቀረበልንን ግብዣ ስንቀበል የኃጢአት ይቅርታ እናገኛለን። (ማቴ. 11:28) እንደ እውነቱ ከሆነ ደግሞ ይሖዋ ሁላችንንም በጣም ይወደናል። (ሮም 8:32, 38, 39) ሰዎች በይሖዋ እንዲታመኑና ሕይወታቸውን እንዲለውጡ መርዳት እንዴት ያለ እርካታ የሚሰጥ ሥራ ነው! ኢየሱስ እንድንሸከመው የነገረን ሸክም፣ ልንሸከማቸው ከሚገቡን ሌሎች ሸክሞች የተለየ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙዎች በሥራ ሲደክሙ ውለው ማታ ላይ ኃይላቸው የሚሟጠጥ ከመሆኑም በላይ ከሥራቸው ምንም እርካታ አያገኙም። በተቃራኒው ግን ይሖዋንና ክርስቶስን ስናገለግል ከቆየን በኋላ ከፍተኛ እርካታ ይሰማናል። አንዳንዴ በጣም ስለሚደክመን ምሽት ላይ በጉባኤ ስብሰባ ለመገኘት ራሳችንን ማስገደድ ይጠይቅብን ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ከስብሰባ የምንመለሰው ታድሰንና ተበረታተን ነው። አገልግሎት ለመውጣትና መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን ለማጥናት ከምናደርገው ጥረት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ የምናገኘው በረከት ከምንከፍለው መሥዋዕት እጅግ የላቀ ነው! w19.09 20 አን. 1፤ 23-24 አን. 15-16

እሁድ፣ ሐምሌ 18

የይሖዋ ቀን የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ [ነው]።—1 ተሰ. 5:2

“የይሖዋ ቀን” ከመጀመሩ በፊት በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ ይሖዋ በስብከቱ ሥራ እንድንጠመድ ይጠብቅብናል። “የጌታ ሥራ [የበዛልን]” ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 15:58) ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚኖሩት ወሳኝ ክንውኖች በተናገረበት ወቅት “አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት” ብሎ ነበር። (ማር. 13:4, 8, 10፤ ማቴ. 24:14) እስቲ አስበው፣ አገልግሎት በወጣህ ቁጥር ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አስተዋጽኦ እያደረግክ ነው! የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ከዓመት ወደ ዓመት የበለጠ ውጤት እያስገኘ ነው። በመጨረሻዎቹ ቀናት በዓለም ዙሪያ ካሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ጋር በተያያዘ የተገኘውን ጭማሪ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በ1914 በ43 አገራት የሚያገለግሉ 5,155 አስፋፊዎች ነበሩ። በዛሬው ጊዜ ግን በ240 አገራት ውስጥ 8.5 ሚሊዮን አስፋፊዎች አሉ! ያም ቢሆን ሥራችን ገና አልተጠናቀቀም። ለሰው ልጆች ችግሮች በሙሉ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ መሆኑን ማወጃችንን መቀጠል አለብን።—መዝ. 145:11-13፤ w19.10 8 አን. 3፤ 9-10 አን. 7-8

ሰኞ፣ ሐምሌ 19

በሁሉም መንገድ በልግስና መስጠት እንድትችሉ አምላክ አትረፍርፎ ይባርካችኋል፤ እኛ በምናከናውነው ሥራ የተነሳ እንዲህ ያለው ልግስና ሰዎች ለአምላክ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል።—2 ቆሮ. 9:11

ይሖዋ፣ ንጉሥ ዳዊት የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት በቤርዜሊ ተጠቅሟል። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከዳዊት ልጅ ከአቢሴሎም እየሸሹ በነበሩበት ወቅት ‘ተርበው፣ ደክሟቸውና ተጠምተው’ ነበር። በዚህ ወቅት አረጋዊ ሰው የነበረው ቤርዜሊና አብረውት የነበሩት ሰዎች፣ ለዳዊትና ለተከተለው ሕዝብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማቅረብ ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። ቤርዜሊ ዕድሜው ስለገፋ ይሖዋ ሊጠቀምበት እንደማይችል አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የአምላክ አገልጋዮች ለመርዳት ሲል ያለውን ነገር በልግስና ሰጥቷል። (2 ሳሙ. 17:27-29) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? በየትኛውም ዕድሜ ላይ ብንገኝ ይሖዋ፣ በአካባቢያችንም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚቸገሩ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት ሊጠቀምብን ይችላል። (ምሳሌ 3:27, 28፤ 19:17) እነዚህን ወንድሞቻችንን በቀጥታ መርዳት ባንችልም እንኳ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ እንችላለን፤ በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ እርዳታ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሲፈጠር ጥቅም ላይ ይውላል።—2 ቆሮ. 8:14, 15፤ w19.10 21 አን. 6

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 20

እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች አሉ፤ ነገር ግን ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።—ምሳሌ 18:24

ከዚህ ቀደም አንድ ሰው ስሜታችንን ጎድቶት ከነበረ የልባችንን አውጥተን ለሌሎች መናገር ከባድ ሊሆንብን ይችላል። (ምሳሌ 18:19) በሌላ በኩል ደግሞ የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ጊዜውም ሆነ ጉልበቱ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ያም ቢሆን የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የማይቻል ነገር እንደሆነ ልናስብ አይገባም። ወንድሞቻችን በመከራ ወቅት ከጎናችን እንዲሆኑ ከፈለግን በአሁኑ ጊዜ እነሱን ማመንን እንዲሁም ለእነሱ የልባችንን አውጥተን መናገርን መልመድ ያስፈልገናል። ይህ እውነተኛ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው። (1 ጴጥ. 1:22) ኢየሱስ ለወዳጆቹ ሐሳቡንና ስሜቱን በመናገር እንደሚተማመንባቸው አሳይቷል። (ዮሐ. 15:15) እኛም ስለሚያስደስቱን፣ ስለሚያሳስቡንና ስለሚያስከፉን ነገሮች ለወዳጆቻችን በመናገር የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። አንድ ሰው ሲያዋራህ በጥሞና አዳምጥ፤ ይህን ስታደርግ ከአመለካከታችሁ፣ ከስሜታችሁና ከግቦቻችሁ ጋር በተያያዘ ብዙ የምትመሳሰሉባቸው ነገሮች እንዳሉ ልታስተውል ትችላለህ። ከሌሎች ጋር ስትጨዋወት የልብህን አውጥተህ የምትናገር ከሆነ ከእነሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት መጠናከሩ አይቀርም።—ምሳሌ 27:9፤ w19.11 4 አን. 8-9

ረቡዕ፣ ሐምሌ 21

ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል።—ሕዝ. 2:4

በታላቁ መከራ ወቅት የምንሰብከው መልእክት የሚቀየር ይመስላል። በአሁኑ ወቅት የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበክንና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ እየጣርን ነው። በታላቁ መከራ ወቅት ግን የምናውጀው እንደ በረዶ ድንጋይ ኃይለኛ የሆነ መልእክት ሊሆን ይችላል። (ራእይ 16:21) በሰይጣን ዓለም ላይ ስለሚመጣው ጥፋት እናውጅ ይሆናል። የምናውጀው መልእክት ምን እንደሚሆንና በምን መንገድ እንደምናውጀው በእርግጠኝነት የምናውቀው ጊዜው ሲደርስ ነው። አገልግሎታችንን ለማከናወን ስንጠቀምባቸው የቆየናቸውን ዘዴዎች እንጠቀም ይሆን ወይስ መልእክታችንን በሌላ መንገድ እናውጅ ይሆን? ይህን ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። የምንሰብክበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ የአምላክን የፍርድ መልእክት በድፍረት የማወጅ መብት የሚኖረን ይመስላል! (ሕዝ. 2:3-5) የምንሰብከው መልእክት መንግሥታት እኛን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጸጥ ለማሰኘት እንዲነሱ ሳያደርጋቸው አይቀርም። በአሁኑ ጊዜ አገልግሎታችንን ለማከናወን በይሖዋ እርዳታ እንደምንታመን ሁሉ በዚያን ጊዜም የእሱ ድጋፍ ያስፈልገናል። አምላካችን የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ኃይል እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሚክ. 3:8፤ w19.10 16 አን. 8-9

ሐሙስ፣ ሐምሌ 22

አንዳንዶች . . . ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል።—1 ጢሞ. 6:10

“ስተው ወጥተዋል” የሚለው አገላለጽ፣ አላስፈላጊ ቁሳዊ ነገሮችን ለማከማቸት መሞከር ትኩረታችን እንዲከፋፈል ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማል። እንዲህ ያለው አካሄድ ደግሞ ‘ከንቱና ጎጂ የሆኑ ብዙ ምኞቶች’ በልባችን ውስጥ እንዲያቆጠቁጡ ሊያደርግ ይችላል። (1 ጢሞ. 6:9) እንደነዚህ ያሉ ምኞቶች እንዲያድሩብን ከመፍቀድ ይልቅ ሰይጣን እኛን ለማጥቃት የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መሆናቸውን ማስተዋል ይኖርብናል። ብዙ ቁሳዊ ነገሮች ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ አለን እንበል። ታዲያ ያማሩንን ሆኖም የግድ የማያስፈልጉንን ነገሮች ብንገዛ ስህተት ነው? ስህተት ነው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልናስብባቸው ይገባል፦ አንድን ዕቃ የመግዛት አቅም ቢኖረንም እንኳ ዕቃውን ለመጠቀምም ሆነ በአግባቡ ለመያዝ የሚያስፈልገው ጊዜና ጉልበት አለን? በተጨማሪም ለቁሳዊ ንብረታችን ከልክ ያለፈ ፍቅር እናዳብር ይሆን? ደግሞስ አምላክን ይበልጥ እንዲያገለግል ኢየሱስ ያቀረበለትን ግብዣ መቀበል እንደከበደው ወጣት ሁሉ እኛም ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር እንቅፋት ይሆንብን ይሆን? (ማር. 10:17-22) ከዚህ በተቃራኒ አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ፣ ውድ የሆነውን ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ብንጠቀምበት ምንኛ የተሻለ ይሆናል! w19.11 17-18 አን. 15-16

ዓርብ፣ ሐምሌ 23

የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።—ምሳሌ 21:5

አምላክ ውሳኔህን ዳር ለማድረስ የሚያስፈልግህን “ኃይል” ሊሰጥህ ይችላል። (ፊልጵ. 2:13) ስለዚህ ውሳኔህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ብርታት ለማግኘት ጸልይ። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የሚያስፈልግህን ኃይል እንዲሰጥህ ለምነው። ጸሎትህ ወዲያው መልስ እንዳላገኘ ቢሰማህም እንኳ መጸለይህን አታቋርጥ። ኢየሱስ እንዳለው ‘ደጋግመህ ከለመንክ’ መንፈስ ቅዱስ ‘ይሰጥሃል።’ (ሉቃስ 11:9, 13) በተጨማሪም ዕቅድ አውጣ። ማንኛውንም ሥራ ዳር ለማድረስ ዕቅድ ማውጣት ያስፈልግሃል። ከዚያም በዕቅድህ መሠረት ሥራህን ማከናወን ይኖርብሃል። በተመሳሳይም አንድ ውሳኔ ስታደርግ፣ ውሳኔህን ዳር ለማድረስ ልትወስዳቸው ያሰብካቸውን እርምጃዎች በዝርዝር ጻፍ። በተጨማሪም ከበድ ያሉ ሥራዎችን ከፋፍለህ ማስቀመጥህ ምን ያህል ሥራ እንዳከናወንክ መከታተል ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን፣ እሱ እስኪመጣ ጠብቀው መዋጮ ከማሰባሰብ ይልቅ “በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን” ለመዋጮ የሚሆን የተወሰነ ገንዘብ እንዲያስቀምጡ አበረታቷቸዋል። (1 ቆሮ. 16:2) ከበድ ያሉ ሥራዎችን ከፋፍለህ ማስቀመጥህ ሥራው ከአቅምህ በላይ እንደሆነ እንዳይሰማህም ያደርጋል። w19.11 29 አን. 13-14

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 24

ስምህን የሚያውቁ በአንተ ይታመናሉ፤ ይሖዋ ሆይ፣ አንተን የሚሹትን ፈጽሞ አትተዋቸውም።—መዝ. 9:10

አንድ ሰው የአምላክን ስም እንዲሁም እሱ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን አንዳንድ ነገሮች የሚያውቅ ከሆነ ስለ ይሖዋ ያውቃል ልንል እንችላለን። ይሖዋን በደንብ ማወቅ ግን ከዚህ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። ጊዜ መድበን ስለ ይሖዋ እና አስደናቂ ስለሆኑት ባሕርያቱ መማር ያስፈልገናል። ይሖዋ አንድን ነገር እንዲናገር ወይም እንዲያደርግ ያነሳሳው ምን እንደሆነ መረዳት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። ይህም አስተሳሰባችን፣ ውሳኔያችንና ድርጊታችን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለውና እንደሌለው ለማስተዋል ይረዳናል። ይሖዋ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ከተረዳን በኋላ ደግሞ የተማርነውን በተግባር ማዋል ይኖርብናል። አንዳንድ ሰዎች ይሖዋን ማገልገል በመፈለጋችን ያሾፉብን ይሆናል፤ ከሕዝቦቹ ጋር መሰብሰብ ስንጀምር ደግሞ ይበልጥ ሊቃወሙን ይችላሉ። በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ግን እሱ ፈጽሞ አይተወንም። በአምላክ መታመናችን ከእሱ ጋር የዕድሜ ልክ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። ለመሆኑ ይሖዋን በደንብ ማወቅ እንችላለን? አዎ እንችላለን! w19.12 16-17 አን. 3-4

እሁድ፣ ሐምሌ 25

ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው።—መዝ. 127:3

አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ማስተማር ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ሆኖም ልጆችን ስጦታ አድርጎ ለወላጆች የሰጠው ይሖዋ ስለሆነ እነሱን ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። ይሖዋ ወላጆች የሚያቀርቡትን ጸሎት ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነው። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በጽሑፎቻችን እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በመንፈሳዊ የጎለመሱና ምሳሌ የሚሆኑ ሌሎች ወላጆች በሚሰጡት ምክር አማካኝነት ጸሎታቸውን ይመልስላቸዋል። ‘ልጅ ማሳደግ የ20 ዓመት ፕሮጀክት ነው’ ሲባል እንሰማለን፤ ሆኖም ወላጅ ምንጊዜም ወላጅ ነው። ወላጆች ለልጆቻቸው መስጠት ከሚችሏቸው ውድ ነገሮች መካከል ፍቅር፣ ጊዜና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ሥልጠና ይገኙበታል። እያንዳንዱ ልጅ ለሥልጠናው የሚሰጠው ምላሽ ይለያያል። ሆኖም ይሖዋን የሚወዱ ወላጆች ያሳደጓቸው በርካታ ልጆች በእስያ እንደምትኖረው እንደ ጆአኖ ማ ይሰማቸዋል፤ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ተግሣጽ ስለሰጡኝ እና ይሖዋን እንድወደው ስላስተማሩኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ስለወለዱኝ ብቻ ሳይሆን ትርጉም ያለው ሕይወት እንድመራ ስለረዱኝም አመስጋኝ ነኝ።” (ምሳሌ 23:24, 25) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ክርስቲያኖችም የእሷን ስሜት ይጋራሉ። w19.12 27 አን. 21-22

ሰኞ፣ ሐምሌ 26

እኛ ከአምላክ በምናገኘው መጽናኛ በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች [እናጽናና]።—2 ቆሮ. 1:4

ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች ለማግኘት ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም። ሌሎችን ማጽናናት ቢያስፈራንም እንኳ ይህን ማድረግ ይኖርብናል። በጣም አስጨናቂ ሁኔታ ያጋጠመውን ሰው ለማጽናናት ምን ማለት ወይም ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ እንጋባ ይሆናል። ሆኖም ለሌሎች እንደምናስብ የምናሳይ ከሆነ ማጽናኛ በመስጠት ረገድ ይሳካልናል። ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየቀረብን ስንሄድ የዓለም ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱና ሕይወት ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:13) ከዚህም ሌላ ፍጹማን ባለመሆናችን በምንሠራቸው ስህተቶች የተነሳ ማጽናኛ ሊያስፈልገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ በታማኝነት መጽናት እንዲችል የረዳው አንዱ ነገር የእምነት ባልንጀሮቹ የሰጡት ማጽናኛ ነው። እኛም የእነዚህን ክርስቲያኖች ምሳሌ በመከተል ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ መርዳት እንችላለን።—1 ተሰ. 3:2, 3፤ w20.01 12-13 አን. 17-19

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 27

ሐዋርያት ነን የሚሉትን [ፈትነሃል]።—ራእይ 2:2

ቅቡዓን ሌሎች የተለየ ክብር እንዲሰጧቸው አይጠብቁም። (ፊልጵ. 2:2, 3) ይሖዋ እነሱን ሲቀባቸው፣ መመረጣቸውን ሰው ሁሉ እንዲያውቅ እንዳላደረገ ይገነዘባሉ። በመሆኑም አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን፣ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን አንዳንዶች ወዲያውኑ ባያምኑ ሊገረም አይገባም። እንዲያውም ይህ ክርስቲያን፣ ከአምላክ ልዩ ኃላፊነት እንዳገኘ የሚናገርን ሰው ቶሎ ማመንን መጽሐፍ ቅዱስ እንደማያበረታታ ይገነዘባል። አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን የሌሎችን ትኩረት ወደ ራሱ መሳብ ስለማይፈልግ ከሰዎች ጋር ሲተዋወቅ ቅቡዕ መሆኑን አይናገርም። ሰማያዊ ሽልማቱን እያነሳም አይኩራራም። (1 ቆሮ. 4:7, 8) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በመፈለግ ከእነሱ ጋር ስለ ጥሪያቸው ለማውራት ወይም የራሳቸውን ቡድኖች አቋቁመው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥረት አያደርጉም። (ገላ. 1:15-17) ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ የጉባኤው አንድነት ይናጋል። እንዲህ ያለው አካሄድ፣ የአምላክ ሕዝቦች ሰላምና አንድነት እንዲኖራቸው ከሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ጋር ይጋጫል።—ሮም 16:17, 18፤ w20.01 28 አን. 6-7

ረቡዕ፣ ሐምሌ 28

እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ።—ሉቃስ 21:28

የሐሰት ሃይማኖቶች ከጠፉ በኋላ በሆነ ወቅት ላይ ሰዎች፣ የራሳቸው የሃይማኖት ድርጅቶች ጠፍተው ሳለ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት አለመጥፋቱን ያስተውላሉ፤ ይህም ሊያበሳጫቸው ይችላል። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን ተቃውሞ መገመት አያዳግትም፤ ሰዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾችም ጭምር ቁጣቸውን ይገልጹ ይሆናል። መንግሥታትም ሆኑ ገዢያቸው የሆነው ሰይጣን የእኛ ሃይማኖት ብቻ ከጥፋት በመትረፉ ይጠሉናል። ሃይማኖቶችን በሙሉ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ይረዳሉ። በመሆኑም ትኩረታቸውን በእኛ ላይ ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት መንግሥታት የማጎጉ ጎግ ሆነው ይነሳሉ። ኃይላቸውን አስተባብረው በመነሳት በይሖዋ ሕዝብ ላይ ከባድ ጥቃት ይሰነዝራሉ። (ሕዝ. 38:2, 14-16) በዚያ ወቅት ስለሚኖረው ሁኔታ ዝርዝር ነገሮችን ስለማናውቅ፣ ሊፈጠሩ ስለሚችሉት ነገሮች አሁን ላይ ሆነን ስናስብ ስጋት ሊያድርብን ይችላል። ይሁን እንጂ እርግጠኛ የምንሆንበት አንድ ነገር አለ፦ ታላቁን መከራ መፍራት አያስፈልገንም። ይሖዋ ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችሉንን መመሪያዎች ይሰጠናል።—መዝ. 34:19፤ w19.10 16 አን. 10-11

ሐሙስ፣ ሐምሌ 29

ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ ያደረግካቸው ድንቅ ሥራዎች፣ ለእኛ ያሰብካቸው ነገሮችም ብዙ ናቸው።—መዝ. 40:5

ለይሖዋ ያለን አመስጋኝነት ከስሜት ባለፈ በንግግራችንና በተግባራችን ሊገለጽ ይገባል። ይህን ማድረጋችን በዛሬው ጊዜ ካሉ ብዙ ሰዎች የተለየን እንድንሆን ያደርገናል። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች አምላክ ላደረገላቸው በርካታ ነገሮች ምንም አድናቆት የላቸውም። እንዲያውም “በመጨረሻዎቹ ቀናት” እንደምንኖር ከሚጠቁሙት ነገሮች አንዱ ሰዎች የማያመሰግኑ መሆናቸው ነው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) እንዲህ ያለ ዝንባሌ ፈጽሞ እንዳይጋባብን እንጠንቀቅ! ይሖዋ ሁሉም ልጆቹ ተስማምተው እንዲኖሩ ይፈልጋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቀውም አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር ነው። (ዮሐ. 13:35) “እነሆ፣ ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!” ብሎ እንደጻፈው መዝሙራዊ ይሰማናል። (መዝ. 133:1) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የምንወድ ከሆነ ይሖዋን እንደምንወድ እናሳያለን። (1 ዮሐ. 4:20) ‘አንዳቸው ለሌላው ደግ የሆኑና ከአንጀት የሚራሩ’ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ያሉበት ቤተሰብ አባል መሆን ምንኛ አስደሳች ነው!—ኤፌ. 4:32፤ w20.02 9 አን. 6-7

ዓርብ፣ ሐምሌ 30

ይሖዋም ሐናን አሰባት።—1 ሳሙ. 2:21

ሐናን ጭንቀት የፈጠረባት ነገር ወዲያውኑ አልተስተካከለም። ከፍናና ጋር በአንድ ቤት መኖሯ አልቀረም። የፍናና አመለካከትም ቢሆን እንደተለወጠ መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም። በመሆኑም ሐና ጣውንቷ የምትሰነዝራቸውን ልብ የሚያቆስሉ ቃላት ተቋቁማ መኖር ሳያስፈልጋት አይቀርም። ሆኖም ሐና ውስጣዊ ሰላሟን መልሳ ማግኘትና ሰላሟን ጠብቃ መኖር ችላለች። ሐና ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ከተወችው በኋላ መጨነቋን አቁማለች። ይሖዋ እንዲያጽናናትና እንዲያረጋጋት ፈቅዳለች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ይሖዋ፣ ልጆች እንድትወልድ በማድረግ ሐናን ባርኳታል። (1 ሳሙ. 1:2, 6, 7, 17-20) ጭንቀት የፈጠረብን ነገር ባይስተካከልም እንኳ ሰላማችንን መልሰን ማግኘት እንችላለን። አጥብቀን መጸለያችንን እና በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችንን ብንቀጥልም አንዳንድ ችግሮች ላይቀረፉ ይችላሉ። ከሐና ምሳሌ መማር እንደምንችለው ግን ይሖዋ የተጨነቀውን ልባችንን እንዳያረጋጋልን ምንም ዓይነት ነገር ሊያግደው አይችልም። ይሖዋ ፈጽሞ አይረሳንም፤ ይዋል ይደር እንጂ ለታማኝነታችን ወሮታውን ይከፍለናል።—ዕብ. 11:6፤ w20.02 22 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 31

ጥበበኛን ሰው አስተምረው፤ ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል።—ምሳሌ 9:9

ሽማግሌዎች፣ ሌሎች ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ እንዲወስዱ ለመርዳት ሲሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከማካፈል ወደኋላ አይሉም። ታዲያ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በድፍረት መናገራቸው ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? የኤሊን ምሳሌ እንመልከት፤ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ በጣም የሚወዳቸው ሁለት ልጆች ነበሩት። ሆኖም ልጆቹ ለይሖዋ ምንም አክብሮት አልነበራቸውም። የኤሊ ልጆች በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ካህን ሆነው የማገልገል ትልቅ ኃላፊነት ነበራቸው። ሆኖም ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመውበታል፤ ለይሖዋ ለሚቀርበው መሥዋዕት ከፍተኛ ንቀት ነበራቸው፤ አልፎ ተርፎም የፆታ ብልግና ይፈጽሙ ነበር። (1 ሳሙ. 2:12-17, 22) በሙሴ ሕግ መሠረት የኤሊ ልጆች ሞት ይገባቸው ነበር፤ ሆኖም ኤሊ መጠነኛ ተግሣጽ ብቻ በመስጠት በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ፈቀደላቸው። (ዘዳ. 21:18-21) ታዲያ ይሖዋ ኤሊ ስላደረገው ነገር ምን ተሰማው? ኤሊን “ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ያከበርከው ለምንድን ነው?” ብሎታል። ይሖዋ እነዚያ ክፉ ልጆች እንዲገደሉ ወሰነ።—1 ሳሙ. 2:29, 34፤ w20.03 19 አን. 4-5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ