ነሐሴ
እሁድ፣ ነሐሴ 1
እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ . . . ብቻዬን አልተወኝም።—ዮሐ. 8:29
ኢየሱስ ስደት በደረሰበት ጊዜም እንኳ ውስጣዊ ሰላሙን ይዞ መቀጠል የቻለው አባቱን እያስደሰተ እንዳለ ስላወቀ ነው። የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም ከባድ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር ከመታዘዝ ወደኋላ አላለም። አባቱን ይወድ ስለነበር መላ ሕይወቱ ያተኮረው እሱን በማገልገል ላይ ነበር። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት “የተዋጣለት ሠራተኛ” ሆኖ አምላክን አገልግሏል። (ምሳሌ 8:30) ወደ ምድር ከመጣ በኋላ ደግሞ ሌሎችን ስለ አባቱ በቅንዓት አስተምሯል። (ማቴ. 6:9፤ ዮሐ. 5:17) ይህ ሥራ ለኢየሱስ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶለታል። (ዮሐ. 4:34-36) ይሖዋን በመታዘዝና ‘ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛልን በመሆን’ ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። (1 ቆሮ. 15:58) በስብከቱ ሥራ ‘በእጅጉ ስንጠመድ’ ለችግሮቻችን ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ቀላል ይሆንልናል። (ሥራ 18:5) ለምሳሌ ያህል፣ በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከእኛ የባሱ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ሆኖም ለይሖዋ ፍቅር እያዳበሩ ሲሄዱና ምክሮቹን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሕይወታቸው ስለሚሻሻል ደስተኞች ይሆናሉ። ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ለውጥ ስንመለከት ይሖዋ እኛንም እንደሚንከባከበን ያለን እምነት ይጠናከራል። w19.04 10-11 አን. 8-9
ሰኞ፣ ነሐሴ 2
አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉ።—ሥራ 19:19
እነዚህ ክርስቲያኖች ክፉ መናፍስትን ለመቃወም የሚያስፈልገውን ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ አላመነቱም። አስማት ለመሥራት ይጠቀሙባቸው የነበሩት መጻሕፍት ውድ ዋጋ የሚያወጡ ነበሩ። ሆኖም መጻሕፍቱን ለሰዎች ከመስጠት ወይም ከመሸጥ ይልቅ አቃጥለዋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ይበልጥ ያሳሰባቸው የመጻሕፍቱ ዋጋ ሳይሆን ይሖዋን ማስደሰታቸው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩትን የእነዚህን ክርስቲያኖች ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ከምትሃታዊ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያለውን ማንኛውንም ነገር ማስወገዳችን የጥበብ እርምጃ ነው። ይህም የቡዳ መድኃኒቶችን፣ ክታቦችን አሊያም ሰዎች ራሳቸውን ከክፉ መናፍስት ለመጠበቅ ብለው የሚያደርጓቸውን ወይም የሚያሠሯቸውን ነገሮች ማስወገድን ይጨምራል። (1 ቆሮ. 10:21) በመዝናኛ ምርጫችሁ ረገድ ጠንቃቆች ሁኑ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምዝናናባቸው ነገሮች ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ያላቸው ናቸው?’ መዝናኛ ስትመርጥ፣ ይሖዋ ከሚጠላው ከማንኛውም ነገር ለመራቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ማናችንም ብንሆን ‘በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዘን ለመኖር’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን።—ሥራ 24:16፤ w19.04 22-23 አን. 10-12
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3
ሽማግሌዎችን . . . ይጥራ።—ያዕ. 5:14
ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ የሚገልጽ ሪፖርት ሲደርሳቸው በርካታ ነገሮችን ግምት ውስጥ ያስገባሉ። በዋነኝነት የሚያሳስባቸው የአምላክ ስም ቅድስና ነው። (ዘሌ. 22:31, 32፤ ማቴ. 6:9) በተጨማሪም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ደህንነት በእጅጉ የሚያሳስባቸው ከመሆኑም ሌላ በተፈጸመው ኃጢአት ምክንያት የተጎዱትን መርዳት ይፈልጋሉ። ከዚህም ሌላ፣ ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ የጉባኤው አባል ከሆነና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ከሆነ ሽማግሌዎች ግለሰቡ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ማደስ እንዲችል ለመርዳት ይጥራሉ። (ያዕ. 5:14, 15) በመጥፎ ምኞት ተሸንፎ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ታሟል። በሌላ አነጋገር ከይሖዋ ጋር የነበረው ጤናማ ግንኙነት ተበላሽቷል። ሽማግሌዎች መንፈሳዊ ሐኪሞች ናቸው ሊባል ይችላል። ‘የታመመው ሰው [በዚህ አገባቡ፣ ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ] ፈውስ እንዲያገኝ’ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች የሚሰጡት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያድስ ይረዳዋል፤ ሆኖም ይህ ሊሆን የሚችለው ግለሰቡ ከልቡ ንስሐ ከገባ ብቻ ነው።—ሥራ 3:19፤ 2 ቆሮ. 2:5-10፤ w19.05 10 አን. 10-11
ረቡዕ፣ ነሐሴ 4
እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13
ይሖዋ የእሱን ፈቃድ የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርብን ሊያደርገን ይችላል። በጉባኤያችን ውስጥ ወይም ከጉባኤያችን ውጭ እርዳታ ማበርከት የምንችልበት አንድ ሁኔታ እንዳለ እናስተውል ይሆናል። በመሆኑም ‘እርዳታ ማበርከት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል። ወይም ደግሞ አንድ ከባድ ኃላፊነት እንድንቀበል ተጠይቀን ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ሥራውን በተገቢው መንገድ ማከናወን መቻላችንን እንጠራጠር ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ሐሳብ ካነበብን በኋላ ‘ይህን ጥቅስ ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ ለመመርመር ፈቃደኞች እንደሆንን ሲመለከት ያሰብነውን ነገር በተግባር የማዋል ፍላጎት እንዲያድርብን ይረዳናል። ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ኃይልም ሊሰጠን ይችላል። (ኢሳ. 40:29) ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ችሎታዎቻችንን እንድናሻሽል ሊረዳን ይችላል። (ዘፀ. 35:30-35) ይሖዋ አንዳንድ ኃላፊነቶችን እንዴት መወጣት እንደምንችል በድርጅቱ አማካኝነት ሊያሠለጥነን ይችላል። አንድን ሥራ እንዴት ማከናወን እንደምትችል ግራ ከገባህ እርዳታ ጠይቅ። በተጨማሪም በሰማይ ያለው ለጋሱ አባታችን ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ እንዲሰጥህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል።—2 ቆሮ. 4:7፤ ሉቃስ 11:13፤ w19.10 21 አን. 3-4
ሐሙስ፣ ነሐሴ 5
ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ [ይሆናሉ]።—2 ጢሞ. 3:2
ይህ ዓለም ለራሳችን የተጋነነ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደተናገረው፣ በ1970ዎቹ ዓመታት “ራስ አገዝ መጻሕፍት በብዛት መታተም” የጀመሩ ሲሆን አንዳንዶቹ መጻሕፍት ሰዎች “ማንነታቸውን እንዲቀበሉና ራሳቸውን ለመለወጥ ምንም ዓይነት ጥረት እንዳያደርጉ የሚያበረታቱ ነበሩ።” ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ራስ አገዝ መጽሐፍ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “እስከዛሬ በዓለም ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ውብና ማራኪ ከሆነው እንዲሁም ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጠው ሰው ጋር ፍቅር ይያዝህ፤ ይህ ሰው አንተ ራስህ ነህ።” ይኸው መጽሐፍ፣ ሰዎች “ራሳቸውን እንደ ሃይማኖት አድርገው እንዲከተሉ ማለትም ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንዳለባቸው ለመወሰን በራሳቸው ሕሊና እንዲመሩ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ከሚመራባቸው ሕጎች መካከል ለራሳቸው የሚስማማቸውን ብቻ መርጠው እንዲከተሉ” ያበረታታል። ይህ ሐሳብ ምን ያስታውስሃል? ሰይጣን ሔዋንን ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ አበረታቷት ነበር። “መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ [እንደምትሆን]” ነግሯት ነበር። (ዘፍ. 3:5) በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት በጣም የተጋነነ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ሌላው ቀርቶ አምላክም እንኳ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ሊነግራቸው እንደማይችል ይሰማቸዋል። ይህ ዝንባሌ በተለይም ሰዎች ለጋብቻ ባላቸው አመለካከት ላይ በግልጽ ይታያል። w19.05 23 አን. 10-11
ዓርብ፣ ነሐሴ 6
በጭንቀት ተዋጥኩ፤ አንገቴንም ደፋሁ፤ ቀኑን ሙሉ በሐዘን ተውጬ እመላለሳለሁ።—መዝ. 38:6
ንጉሥ ዳዊት በጭንቀት የተዋጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። እስቲ ስላጋጠሙት ችግሮች እናስብ። በፈጸማቸው በርካታ ስህተቶች የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃይ ነበር። (መዝ. 40:12) የሚወደው ልጁ አቢሴሎም ዓምፆበታል፤ በኋላም አቢሴሎም በዚሁ ምክንያት ሕይወቱን አጥቷል። (2 ሳሙ. 15:13, 14፤ 18:33) እንዲሁም ከቅርብ ወዳጆቹ አንዱ ዳዊትን ክዶታል። (2 ሳሙ. 16:23 እስከ 17:2፤ መዝ. 55:12-14) ዳዊት ከጻፋቸው መዝሙሮች ብዙዎቹ፣ ያደረበትን የተስፋ መቁረጥ ስሜት በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ ላይ ያለውን ጽኑ እምነት የሚያሳዩ ናቸው። (መዝ. 38:5-10፤ 94:17-19) ከጊዜ በኋላ ደግሞ አንድ መዝሙራዊ በክፉዎች አኗኗር መቅናት ጀመረ። ይህ መዝሙራዊ፣ ‘በታላቁ የአምላክ መቅደስ’ ያገለግል የነበረ ሲሆን ከሌዋዊው አሳፍ ዘሮች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። መዝሙራዊው ከመጨነቁ ብዛት፣ ደስታ ርቆትና በሕይወቱ እርካታ አጥቶ ነበር። እንዲያውም አምላክን ማገልገል በረከት የሚያስገኝ ነገር መሆኑን መጠራጠር ጀምሮ ነበር።—መዝ. 73:2-5, 7, 12-14, 16, 17, 21፤ w19.06 17 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 7
[ሰይጣን] የሚሸርበውን ተንኮል እናውቃለንና።—2 ቆሮ. 2:11
ሰይጣን፣ ተፈጥሯዊ ፍላጎታችንን ተጠቅሞ ሊማርከን ይሞክራል። ለራሳችንም ሆነ ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት የሚያስችለንን ትምህርት ለመቅሰም መፈለግ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። (1 ጢሞ. 5:8) ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለውን ትምህርት የምናገኘው ትምህርት ቤት ገብተን በትጋት በማጥናት ነው። ይሁንና ይህን ስናደርግ ጠንቃቆች መሆን አለብን። በብዙ አገሮች የሚሰጠው ትምህርት፣ ጠቃሚ የሆኑ ክህሎቶችን ብቻ ሳይሆን ዓለማዊ ፍልስፍናዎችንም ያካተተ ነው። ተማሪዎች የአምላክን ሕልውና እንዲጠራጠሩ እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዲያጡ የሚያደርግ ትምህርት ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም የሕይወትን አመጣጥ በተመለከተ ሁሉም የተማሩ ሰዎች የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ እንደሚቀበሉ ይነገራቸዋል። (ሮም 1:21-23) እንዲህ ያሉት ትምህርቶች ‘የአምላክን ጥበብ’ የሚጻረሩ ናቸው። (1 ቆሮ. 1:19-21፤ 3:18-20) እኛም የሰይጣን ዓለም የሚያስፋፋው “ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ” ማርኮ እንዳይወስደን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (ቆላ. 2:8) በሰይጣን ዘዴዎች እንዳንታለል ሁልጊዜ እንጠንቀቅ። (1 ቆሮ. 3:18) ሰይጣን ስለ ይሖዋ ያለንን አመለካከት እንዲያዛባው ፈጽሞ አንፍቀድ። ላቅ ያሉትን የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንከተል። በሰይጣን ተታልለን የይሖዋን ምክር ችላ እንዳንል እንጠንቀቅ። w19.06 5 አን. 13፤ 7 አን. 17
እሁድ፣ ነሐሴ 8
ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]።—ማቴ. 28:20
ለመወያየት የመረጥከው ርዕስ ምንም ይሁን ምን፣ መልእክቱን ስለምትነግራቸው ሰዎች አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማወቃቸው እንዴት እንደሚጠቅማቸው ለማሰብ ሞክር። ከሰዎቹ ጋር ስትወያይ እነሱን ማዳመጥህና አመለካከታቸውን ማክበርህ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረግህ የእነሱን አመለካከት ይበልጥ ለመረዳት ያስችልሃል፤ እነሱም አንተን ለማዳመጥ ይበልጥ ይነሳሳሉ። አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ እስኪሆን ድረስ በተደጋጋሚ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ ሊያስፈልግህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ወደ ሰዎች ቤት ተመልሰን ስንሄድ ላናገኛቸው እንችላለን። በተጨማሪም የቤቱ ባለቤት ከአንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ የሚሆነው በተደጋጋሚ ተገናኝታችሁ ከለመደህ በኋላ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ተክል እንዲያድግ አዘውትሮ ውኃ መጠጣት ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም፣ ፍላጎት ያሳየ አንድ ሰው ለይሖዋና ለክርስቶስ ያለው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ስለ አምላክ ቃል አዘውትረን ልናወያየው ይገባል። w19.07 14 አን. 1፤ 15-16 አን. 7-8
ሰኞ፣ ነሐሴ 9
ሰዎች፣ በሰው ልጅ ምክንያት በሚጠሏችሁ፣ በሚያገሏችሁ፣ በሚነቅፏችሁና ክፉ እንደሆናችሁ አድርገው ያለስማችሁ ስም በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ።—ሉቃስ 6:22
ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ክርስቲያኖች፣ በሌሎች መጠላታቸው በራሱ እንደሚያስደስታቸው መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እውነታውን እየነገረን ነበር። የዓለም ክፍል አይደለንም። የኢየሱስን ትምህርቶች በሕይወታችን ተግባራዊ የምናደርግ ሲሆን እሱ የሰበከውን መልእክትም እንሰብካለን። በዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላናል። (ዮሐ. 15:18-21) የእኛ ዓላማ ይሖዋን ማስደሰት ነው። የሰማዩ አባታችንን ስለወደድን ሰዎች ከጠሉን በዚህ ቅር አይለንም። ሌሎች ስላልወደዱን ብቻ ስለ ራሳችን መጥፎ ስሜት ሊሰማን አይገባም። በስደት ወይም መንግሥታት በሥራችን ላይ በሚጥሉት እገዳ የተነሳ ይሖዋን በነፃነት ማምለክ የማንችልበት ጊዜ የሚመጣው መቼ እንደሆነ አናውቅም። ይሁንና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና በማጠናከር፣ ይበልጥ ደፋሮች ለመሆን ጥረት በማድረግ እንዲሁም የሰዎችን ጥላቻ እንዴት መቋቋም እንደምንችል በመማር ከአሁኑ መዘጋጀት እንደምንችል እናውቃለን። በአሁኑ ጊዜ የምናደርገው ዝግጅት ወደፊት ጸንተን ለመቆም ይረዳናል። w19.07 6 አን. 17-18፤ 7 አን. 21
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 10
ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩን . . . ማመን ይኖርበታል።—ዕብ. 11:6
ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና፣ ስለ አምላክ መኖር ያላቸው እምነት እንዲጠናከር አዘውትረን ልንረዳቸው ይገባል። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው መርዳታችን አስፈላጊ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ስለ አንዳንድ ትምህርቶች በተደጋጋሚ ጊዜ መወያየት ሊያስፈልገን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ ላይ ማንሳት ይኖርብን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶች እንደያዘ፣ ከሳይንስና ከታሪክ አንጻር ትክክል እንደሆነ ወይም ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚጠቅሙ ምክሮች እንዳሉት መጥቀስ እንችላለን። ሃይማኖት ላላቸውም ሆነ ለሌላቸው ሰዎች ፍቅር በማሳየት፣ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ልንረዳቸው እንችላለን። (1 ቆሮ. 13:1) እነዚህን ሰዎች ስናስተምር ዓላማችን አምላክ እንደሚወዳቸውና እነሱም እንዲወዱት እንደሚፈልግ እንዲገነዘቡ መርዳት ነው። ስለ ሃይማኖት ግድ ያልነበራቸው ወይም ሃይማኖት የለሽ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ፍቅር ማዳበር ስለቻሉ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ተጠምቀዋል። ስለዚህ አዎንታዊ አመለካከት ይኑረን፤ እንዲሁም ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ፍቅርና አሳቢነት እናሳይ። ሰዎችን እናዳምጥ። ስሜታቸውንና አመለካከታቸውን ለመረዳት ጥረት እናድርግ። ጥሩ ምሳሌ በመሆን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ እናስተምራቸው። w19.07 24 አን. 16-17
ረቡዕ፣ ነሐሴ 11
መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።—ዕብ. 13:16
የኢየሩሳሌም ቅጥር በተጠገነበት ወቅት ይሖዋ ለሥራው ከተጠቀመባቸው ሰዎች መካከል የሻሉም ሴቶች ልጆች ይገኙበታል። (ነህ. 2:20፤ 3:12) የሻሉም ልጆች አባታቸው ገዢ ቢሆንም ከባድና አደገኛ የሆነውን ሥራ ለማከናወን ፈቃደኞች ሆነዋል። (ነህ. 4:15-18) በዘመናችንም ፈቃደኛ የሆኑ እህቶች ለየት ባለ የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ ይኸውም ለይሖዋ አምልኮ የሚውሉ ሕንፃዎችን በመገንባቱና በመጠገኑ ሥራ መካፈላቸው ያስደስታቸዋል። የእነዚህ እህቶች ችሎታ፣ ቅንዓትና ታማኝነት ለሥራው መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጣቢታ ለሌሎች በተለይም ለመበለቶች “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት” ልግስና እንድታሳይ ይሖዋ አነሳስቷታል። (ሥራ 9:36) ጣቢታ በጣም ለጋስና ደግ ስለነበረች፣ ስትሞት ብዙዎች እጅግ አዝነዋል። ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ ከሞት ሲያስነሳት በጣም ተደሰቱ። (ሥራ 9:39-41) ከጣቢታ ምን ትምህርት እናገኛለን? ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን፣ ወንዶችም ሆንን ሴቶች ሁላችንም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የሚጠቅሙ ነገሮች ማከናወን እንችላለን። w19.10 23 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ነሐሴ 12
ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ በማወቅ እስከ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንከን የማይገኝባችሁ እንድትሆኑና ሌሎችን እንዳታሰናክሉ።—ፊልጵ. 1:10
ሌሎችን ልናሰናክል የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠና አንድ ሰው፣ ለረጅም ጊዜ ከባድ ትግል ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ከመጠጥ ሱስ መላቀቅ ቻለ። ይህ ሰው ሱሱ እንዳያገረሽበት ሲል ሙሉ በሙሉ ከመጠጥ ለመራቅ ወሰነ። ከዚያም እድገት አድርጎ ተጠመቀ። አንድ ቀን አንድ ወንድም ጋበዘውና መጠጥ እንዲጠጣ ለማበረታታት በቅንነት እንዲህ አለው፦ “ራስን መግዛትን ካዳበርክ በልኩ መጠጣት ሊያስፈራህ አይገባም።” ይህ አዲስ ወንድም እንዲህ ያለውን የተሳሳተ ምክር ቢቀበል ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኙትን ምክሮች ተግባራዊ እንድናደርግ ይረዱናል። በዚያ የሚቀርብልን የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይሖዋ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር እንድናስታውስ ይረዳናል። እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል መማራችን እንከን የማይገኝብን ለመሆን ያስችለናል። በተጨማሪም ስብሰባዎች አምላክንና ወንድሞቻችንን እንድንወድ ያበረታቱናል። ልባችን ለአምላክና ለወንድሞቻችን ባለን ፍቅር ሲሞላ ደግሞ እነሱን ላለማሰናከል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። w19.08 10-11 አን. 9, 13-14
ዓርብ፣ ነሐሴ 13
እኔ የአምላክን ጉባኤ አሳድድ ስለነበር ከሐዋርያት ሁሉ የማንስና ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነኝ።—1 ቆሮ. 15:9
አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው የሚተማመኑ ስለሚመስሉ ወይም የተሰማቸውን ነገር ፊት ለፊት ስለሚናገሩ ብቻ ኩሩ ናቸው ማለት ላይሆን ይችላል። (ዮሐ. 1:46, 47) በባሕርያችን ዓይናፋር ሆንም አልሆን ሁላችንም እውነተኛ ትሕትናን ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እስቲ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ በተለያዩ ከተሞች ጉባኤዎችን ለማቋቋም ጳውሎስን በእጅጉ ተጠቅሞበታል። ምናልባትም በአገልግሎት ረገድ ከሌሎች የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ሁሉ ይበልጥ ብዙ ያከናወነው እሱ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ጳውሎስ ከሌሎች ወንድሞቹ እንደሚበልጥ አልተሰማውም። በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም ሊኖረው የቻለው በራሱ ብቃት ወይም ባከናወናቸው ነገሮች የተነሳ ሳይሆን በአምላክ ጸጋ እንደሆነ ገልጿል። (1 ቆሮ. 15:10) ጳውሎስ በትሕትና ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል! ከእሱ እንደሚበልጡ ለማሳየት የሚሞክሩ ሰዎች ላሉበት ለቆሮንቶስ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንኳ ስለ ራሱ በጉራ አልተናገረም።—2 ቆሮ. 10:10፤ w19.09 3 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 14
አባት ለሆነው ይበልጥ በፈቃደኝነት [ልንገዛ] አይገባም?—ዕብ. 12:9
ለይሖዋ መገዛት ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ሁላችንም ኃጢአትንና አለፍጽምናን የወረስን መሆናችን ነው። ይህም የዓመፅ ዝንባሌ እንዲኖረን አድርጓል። አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ በማመፅና የተከለከለውን ፍሬ በመብላት የራሳቸውን መሥፈርት ለማውጣት መርጠዋል። (ዘፍ. 3:22) በዛሬው ጊዜም አብዛኛው የሰው ዘር ይሖዋን ችላ ለማለት እንዲሁም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሱ ለመወሰን መርጧል። ይሖዋን የሚያውቁና የሚወዱ ሰዎችም እንኳ ለእሱ ሙሉ በሙሉ መገዛት ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለ ችግር አጋጥሞት ነበር። (ሮም 7:21-23) እኛም ልክ እንደ ጳውሎስ በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንፈልጋለን። ሆኖም መጥፎ የሆነውን ነገር እንድናደርግ ከሚገፋፋን ውስጣዊ ዝንባሌ ጋር ቀጣይ የሆነ ትግል ማድረግ አለብን። ለይሖዋ መገዛት ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ያደግንበት ባሕል የሚያሳድርብን ተጽዕኖ ነው። በርካታ ሰብዓዊ አስተሳሰቦች ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚጋጩ ሲሆን በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ካላቸው እንዲህ ያሉ አስተሳሰቦች ለመላቀቅ ቀጣይ ትግል ማድረግ ያስፈልገናል። w19.09 15 አን. 4-6
እሁድ፣ ነሐሴ 15
ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ . . . ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን።—ማር. 10:21
አንድ እውነታ አምነን መቀበል ይኖርብናል። ሁላችንም ያለን ኃይል ውስን ነው። በመሆኑም ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር ለማድረግ እንዳንሞክር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለምሳሌ ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ስንል ብዙ በመድከም ኃይላችንን እናባክን ይሆናል። ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?” በማለት ለጠየቀው ሀብታም ወጣት ምን መልስ እንደሰጠው ልብ በሉ። የማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ ወጣቱን ‘እንደወደደው’ ስለሚናገር ይህ ወጣት ጥሩ ሰው መሆን አለበት። ኢየሱስ ለዚህ ወጣት ገዢ ከላይ የሚገኘውን ግብዣ አቀረበለት። ይህ ሰው በቀረበለት ግብዣ ምክንያት ልቡ ቢከፈልም ያለውን “ብዙ ንብረት” ለመተው ፈቃደኛ አልሆነም። (ማር. 10:17-22) በዚህም የተነሳ የኢየሱስን ቀንበር ለመሸከም እንቢተኛ በመሆን “ለሀብት” ባሪያ ሆኖ መገዛቱን ቀጠለ። (ማቴ. 6:24) አንተ ብትሆን ምን ውሳኔ ታደርግ ነበር? በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ እየሰጠናቸው ያሉትን ነገሮች በየጊዜው መለስ ብለን መገምገማችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን ኃይላችንን በጥበብ እየተጠቀምንበት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ያስችለናል። w19.09 24 አን. 17-18
ሰኞ፣ ነሐሴ 16
አስቀድሞም ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።—ማር. 13:10
የመንግሥቱ የስብከት ሥራችን ይሖዋ በቃ እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ይቀጥላል። ለመሆኑ ሰዎች ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ የሚችሉበት አጋጣሚ ክፍት ሆኖ የሚቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው? (ዮሐ. 17:3) ይህን ማወቅ አንችልም። ሆኖም ታላቁ መከራ እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ፣ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን ሰምተው የአምላክ አገልጋይ የመሆን አጋጣሚ እንደሚኖራቸው እናውቃለን። (ሥራ 13:48) ታዲያ እነዚህን ሰዎች ጊዜው ከማለቁ በፊት ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሰዎች እውነትን ለማስተማር የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ በድርጅቱ በኩል እያቀረበልን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሳምንቱ መሃል ስብሰባ አማካኝነት በየሳምንቱ ሥልጠና እናገኛለን። ለሰዎች ስንመሠክርና ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግ ምን ማለት እንዳለብን በዚህ ስብሰባ ላይ እንማራለን። ፍላጎት ካሳየ አንድ ሰው ጋር ጥሩ ውይይት ካደረግን በኋላ ትራክት ወይም መጽሔት ሰጥተነው ከሄድን ግለሰቡ በቀጣዩ ጊዜ እስክንገናኝ ድረስ ጽሑፉን እያነበበው ሊቆይ ይችላል። እያንዳንዳችን በየወሩ በመንግሥቱ የስብከት ሥራ የመጠመድ ኃላፊነት አለብን። w19.10 9 አን. 7፤ 10 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 17
መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።—ዕብ. 13:16
ይሖዋ፣ ስምዖን ለተባለ በኢየሩሳሌም የሚኖር ታማኝ አገልጋዩ መሲሑን ሳያይ እንደማይሞት ቃል ገብቶለት ነበር። አረጋዊው ስምዖን መሲሑን ለበርካታ ዓመታት ሲጠባበቅ ስለነበር እንዲህ ያለ ተስፋ ሲሰጠው በጣም ተበረታትቶ መሆን አለበት። ደግሞም እምነት በማሳየቱና በመጽናቱ ተክሷል። አንድ ቀን ስምዖን “በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መጣ።” በዚያም ሕፃኑን ኢየሱስን አገኘ፤ ይሖዋም ክርስቶስ የሚሆነውን ይህን ልጅ በተመለከተ ትንቢት እንዲናገር ስምዖንን ተጠቀመበት። (ሉቃስ 2:25-35) ስምዖን፣ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን የማየት አጋጣሚ ባይኖረውም እንኳ ላገኘው መብት አመስጋኝ ነበር፤ ወደፊት ደግሞ ከዚህም የላቀ በረከት ያገኛል! ይህ ታማኝ ሰው፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የኢየሱስ አገዛዝ ለምድር ሕዝቦች ሁሉ የሚያመጣውን በረከት ይመለከታል። (ዘፍ. 22:18) እኛም ብንሆን ይሖዋ በየትኛውም መንገድ ቢጠቀምብን እሱ ለሚሰጠን መብት አመስጋኞች ልንሆን ይገባል። w19.10 22 አን. 7፤ 23 አን. 12
ረቡዕ፣ ነሐሴ 18
ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ።—ምሳሌ 4:23
ሀብታምም ሆንን ድሃ ልባችንን መጠበቅ ያስፈልገናል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የገንዘብ ፍቅር እንዳያድርብህ ተጠንቀቅ። ሰብዓዊ ሥራህን ለአምላክ ከምታቀርበው አገልግሎት እንዳታስቀድም ጥንቃቄ አድርግ። ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት አዝማሚያ እንዳለህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በስብሰባዎች ወይም በአገልግሎት ላይ እያለሁ ብዙውን ጊዜ ስለ ሥራዬ አስባለሁ? ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን በቂ ገንዘብ የማስቀመጥ ጉዳይ ሁልጊዜ ያስጨንቀኛል? ገንዘብና ቁሳዊ ነገሮች በትዳሬ ውስጥ ችግር እንዲፈጠር እያደረጉ ነው? ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል የሚሆን ጊዜ ለማግኘት እስካስቻለኝ ድረስ ሌሎች ዝቅ አድርገው የሚመለከቱትን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ?’ (1 ጢሞ. 6:9-12) በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በምታሰላስልበት ወቅት፣ ይሖዋ እንደሚወድህና እሱን ለሚያመልኩት ሰዎች “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል እንደገባ አስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው።—ዕብ. 13:5, 6፤ w19.10 29 አን. 10
ሐሙስ፣ ነሐሴ 19
ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል።—ምሳሌ 27:17
ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን ስንሠራ እንዲሁም ያሏቸውን ግሩም ባሕርያት ስንመለከት ከእነሱ መማራችንና ይበልጥ መቀራረባችን አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ከጓደኛህ ጋር አገልግሎት ላይ ሆናችሁ ጓደኛህ ለእምነቱ በድፍረት ጥብቅና ሲቆም ወይም ስለ ይሖዋ እና ስለ ዓላማዎቹ ከልቡ ሲናገር ስትመለከት ምን ይሰማሃል? ጓደኛህን ይበልጥ እንደምትወደው የታወቀ ነው። የ23 ዓመት ወጣት የሆነችው አደሊን፣ ካንዲስ የተባለችውን ጓደኛዋን ብዙም ወዳልተሰበከበት ክልል ሄደው እንዲያገለግሉ ጠየቀቻት። አደሊን እንዲህ ብላለች፦ “ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እንዲቀጣጠልና ከአገልግሎታችን የምናገኘው ደስታ እንዲጨምር ፈልገን ነበር። ሁለታችንም በመንፈሳዊ የሚያነቃቃን ነገር አስፈልጎን ነበር።” ታዲያ አብረው በማገልገላቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው? አደሊን እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ ምን እንደተሰማን፣ ከሰዎች ጋር ካደረግነው ውይይት ትኩረታችንን የሳበው ምን እንደሆነ እንዲሁም በአገልግሎታችን ላይ የይሖዋን እጅ ያየነው እንዴት እንደሆነ እንወያይ ነበር። በምናደርገው ውይይት ሁለታችንም የምንደሰት ሲሆን ጭውውታችን ይበልጥ ለመተዋወቅም ረድቶናል።” w19.11 5 አን. 10-11
ዓርብ፣ ነሐሴ 20
ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ።—ኤፌ. 6:16
በጥንት ዘመን አንድ ወታደር ጋሻውን ሳይዝ ቢመለስ ውርደት ይሆንበት ነበር። ሮማዊው የታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ “ጋሻ ሳይዙ ከጦርነት መመለስ ከሁሉ የከፋ ውርደት ነበር” በማለት ጽፏል። ወታደሮች ጋሻቸውን አጥብቀው የሚይዙበት አንዱ ምክንያት ይህ ነበር። የእምነት ጋሻችንን አጥብቀን መያዝ እንድንችል፣ አዘውትረን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም ስለ ይሖዋ ስምና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች መናገር ይኖርብናል። (ዕብ. 10:23-25) በተጨማሪም የአምላክን ቃል በየቀኑ ትኩረት ሰጥተን ማንበብ እንዲሁም በውስጡ የሚገኘውን ምክርና መመሪያ በመላ ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ አለብን። (2 ጢሞ. 3:16, 17) እንዲህ ካደረግን ሰይጣን የሚጠቀምበት የትኛውም መሣሪያ ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም። (ኢሳ. 54:17) ‘ትልቁ የእምነት ጋሻችን’ የሚሰነዘርብንን ጥቃት ይከላከልልናል። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ጸንተን እንቆማለን። እንዲሁም በየቀኑ የምንገጥመውን ውጊያ ከማሸነፍም አልፈን ወደፊት ኢየሱስ ከሰይጣንና ከተከታዮቹ ጋር በሚያካሂደው ጦርነት ድል ሲነሳ ከእሱ ጎን የመሰለፍ መብት እናገኛለን።—ራእይ 17:14፤ 20:10፤ w19.11 19 አን. 18-19
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 21
ቡጢ የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም።—1 ቆሮ. 9:26
በጽሑፍ የሰፈረ ግልጽ የሆነ ዕቅድ ውሳኔህን በተግባር ማዋል እንድትችል ይረዳሃል። (1 ቆሮ. 14:40) ለምሳሌ የሽማግሌዎች አካላት በስብሰባቸው ላይ የሚያደርጉትን እያንዳንዱን ውሳኔ የሚመዘግብ አንድ ሽማግሌ እንዲመድቡ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ ሽማግሌ፣ አንድን ሥራ እንዲያከናውኑ የተመደቡትን ወንድሞችና ሥራው እንዲጠናቀቅ የታሰበበትን ቀንም በጽሑፍ ያሰፍራል። ይህን መመሪያ የሚከተሉ ሽማግሌዎች ውሳኔያቸውን ተግባራዊ ማድረግ ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸዋል። አንተም ከግል ጉዳዮችህ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ አካሄድ መከተል ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ በየዕለቱ ልታከናውናቸው ያሰብካቸውን ሥራዎች የያዘ ፕሮግራም ማዘጋጀትና እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን ባሰብክበት ቅደም ተከተል መሠረት ማስፈር ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ የጀመርከውን ለመጨረስ ብቻ ሳይሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር ለማከናወንም ያስችልሃል። ይሁንና ተግተህ መሥራት ያስፈልግሃል። ዕቅድህን ተግባራዊ ማድረግና የጀመርከውን ዳር ማድረስ ጥረት ይጠይቃል። (ሮም 12:11) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የማስተማር ችሎታውን ለማሻሻል ‘የተቻለውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርግ’ እንዲሁም በሚያደርገው ጥረት ‘እንዲጸና’ ጢሞቴዎስን መክሮታል። ይህ ምክር ከሌሎች መንፈሳዊ ግቦች ጋር በተያያዘም ይሠራል።—1 ጢሞ. 4:13, 16፤ w19.11 29-30 አን. 15-16
እሁድ፣ ነሐሴ 22
አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር እንደሚነጋገር ይሖዋ ከሙሴ ጋር ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር።—ዘፀ. 33:11
ሙሴ እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ እንዲያወጣ በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ ለማድረግ ብቃት እንደሌለው ተሰምቶት ነበር፤ በተደጋጋሚ ጊዜም ለይሖዋ ይህንን ነግሮታል። በዚህ ጊዜ አምላክ ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ መልስ የሰጠው ሲሆን የሚያስፈልገውን እርዳታም አድርጎለታል። (ዘፀ. 4:10-16) በውጤቱም ሙሴ ኃይለኛ የሆኑ የፍርድ መልእክቶችን ለፈርዖን ማድረስ ችሏል። ከዚያም ይሖዋ እስራኤላውያንን በማዳን እንዲሁም ፈርዖንንና ሠራዊቱን በቀይ ባሕር ውስጥ በማስመጥ ኃይሉን ሲገልጥ ሙሴ ተመልክቷል። (ዘፀ. 14:26-31፤ መዝ. 136:15) ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣቸው በኋላ በተደጋጋሚ ያጉረመርሙ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ ከግብፅ ባርነት ነፃ ያወጣቸውን እነዚህን ሰዎች በታላቅ ትዕግሥት እንደያዛቸው ሙሴ ተመልክቷል። (መዝ. 78:40-43) ከዚህም ሌላ ይሖዋ የሙሴን ጥያቄ ለማስተናገድ ሲል ሐሳቡን በመቀየር አስደናቂ ትሕትና አሳይቷል፤ ሙሴም ይህን አስተውሎ መሆን አለበት። (ዘፀ. 32:9-14) ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ ይዞ ከወጣ በኋላም ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና በጣም ተጠናክሯል፤ እንዲያውም በሰማይ ያለውን አባቱን ያየው ያህል ነበር።—ዕብ. 11:27፤ w19.12 17 አን. 7-9
ሰኞ፣ ነሐሴ 23
ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እዚያም ታዩታላችሁ።—ማቴ. 28:7
ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አብዛኞቹ የገሊላ ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም ብዛት ያላቸውን ሰዎች በኢየሩሳሌም በሚገኝ የግለሰብ ቤት ከመሰብሰብ ይልቅ በገሊላ ባለ ተራራ ላይ መሰብሰብ ይበልጥ ምክንያታዊ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ከዚያ ስብሰባ በፊት በኢየሩሳሌም በሚገኝ የግለሰብ ቤት ውስጥ 11 ሐዋርያቱን አግኝቷቸው ነበር። ኢየሱስ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ ለሐዋርያቱ ብቻ ለመስጠት ቢያስብ ኖሮ ይህን እዚያው ኢየሩሳሌም እያሉ ሊነግራቸው ይችል ነበር፤ ሐዋርያቱን ጨምሮ ሴቶቹንና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱን በገሊላ ወደሚገኝ ተራራ መጥራት አያስፈልገውም ነበር። (ሉቃስ 24:33, 36) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርት ስለ ማድረግ የሰጠው ትእዛዝ የሚመለከተው በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን ብቻ አይደለም። ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ለተከታዮቹ መመሪያውን ከሰጣቸው በኋላ “እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በዛሬው ጊዜ በስፋት እየተከናወነ ነው። እስቲ አስበው! በየዓመቱ ወደ 300,000 የሚጠጉ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮችና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ! w20.01 2 አን. 1፤ 3 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 24
መንፈሳችን ተደቁሶ በነበረበት ጊዜ አስታወሰን።—መዝ. 136:23
በወጣትነት ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በሚሄድ ከባድ ሕመም መያዝ። በጉልምስና ዕድሜ ሥራ ማጣት። በዕድሜ መግፋት ምክንያት በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ማከናወን አለመቻል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ከዚህ በኋላ ምንም እንደማትጠቅም ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ደስታህን ሊቀንሱብህ፣ ለራስህ አክብሮት እንድታጣ ሊያደርጉህ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለህን ግንኙነት ሊያበላሹብህ ይችላሉ። ይህ ዓለም ሰይጣን ለሰው ሕይወት ያለውን አመለካከት ያንጸባርቃል። ሰይጣን ለሰው ልጆች አክብሮት ኖሮት አያውቅም። የአምላክን ትእዛዝ መጣስ ሞት እንደሚያስከትል በሚገባ እያወቀ ለሔዋን እንዲህ ብታደርግ ነፃነት እንደምታገኝ ነግሯታል፤ ይህ እንዴት ያለ ጭካኔ ነው! ይህ ዓለም ሁልጊዜም ቢሆን በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ነው። ከዚህ አንጻር በርካታ የዓለም መሪዎች ልክ እንደ ሰይጣን፣ በሚያዋርድና ክብርን ዝቅ በሚያደርግ መንገድ ሰዎችን የሚይዙ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ ለራሳችን አክብሮት እንዲኖረን ይፈልጋል፤ ዋጋ እንደሌለን እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም ይደግፈናል።—ሮም 12:3፤ w20.01 14 አን. 1-4
ረቡዕ፣ ነሐሴ 25
በይሖዋ ስም ትንቢት አትናገር፤ አለዚያ በእጃችን ትጠፋለህ።—ኤር. 11:21
ኤርምያስ ቢያንስ ለ40 ዓመታት ያህል የኖረው ዓመፀኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ነው፤ ከእነዚህም መካከል ጎረቤቶቹ፣ ምናልባትም በትውልድ ከተማው በአናቶት ያሉ አንዳንድ ዘመዶቹ ይገኙበታል። (ኤር. 12:6) ያም ቢሆን ኤርምያስ ራሱን ከሌሎች አላገለለም። እንዲያውም ታማኝ ጸሐፊው ለሆነው ለባሮክ ስሜቱን አውጥቶ ነግሮታል፤ እኛም ኤርምያስ ምን ተሰምቶት እንደነበር ማወቅ ችለናል። (ኤር. 8:21፤ 9:1፤ 20:14-18፤ 45:1) ባሮክ፣ ኤርምያስ ስለገጠሙት አስገራሚ ክንውኖች በሚጽፍበት ወቅት ሁለቱ ሰዎች አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እየጨመረ እንደሄደ መገመት አያዳግትም። (ኤር. 20:1, 2፤ 26:7-11) ኤርምያስ በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጣውን ጥፋት በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት እስራኤላውያንን በድፍረት ያስጠነቅቅ ነበር። (ኤር. 25:3) ይሖዋ፣ ሕዝቡ ንስሐ ለመግባት እንዲነሳሱ ሲል ማስጠንቀቂያዎቹን በጥቅልል ላይ እንዲጽፍ ለኤርምያስ ነገረው። (ኤር. 36:1-4) ይህ ሥራ የተወሰኑ ወራት ሳይፈጅ አልቀረም፤ ኤርምያስና ባሮክ አምላክ በሰጣቸው በዚህ ሥራ አብረው በሚካፈሉበት ወቅት እምነታቸውን የሚያጠናክሩ ውይይቶች አድርገው እንደሚሆን አያጠራጥርም። w19.11 2-3 አን. 3-4
ሐሙስ፣ ነሐሴ 26
ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።—ማቴ. 23:12
ለቅቡዓን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? አንድ ሰው የክርስቶስ ቅቡዕ ወንድም ቢሆንም እንኳ ለዚህ ግለሰብ ከልክ ያለፈ አክብሮት መስጠት ስህተት ነው። (ማቴ. 23:8-11) መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎችን ‘በእምነታቸው እንድንመስላቸው’ ቢያበረታታንም ማንኛውንም ሰው መሪያችን አድርገን መከተል እንዳለብን አይናገርም። (ዕብ. 13:7) እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች “እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው” እንደሚገባ ይገልጻል። እንዲህ ያለ ክብር የሚሰጣቸው ግን በመንፈስ ስለተቀቡ ሳይሆን ‘በመልካም ሁኔታ ስለሚያስተዳድሩ’ እንዲሁም ‘በመናገርና በማስተማር ተግተው ስለሚሠሩ’ ነው። (1 ጢሞ. 5:17) የተቀቡ ክርስቲያኖችን ከልክ በላይ የምናደንቃቸው ወይም ትኩረት የምንሰጣቸው ከሆነ እንዲጨንቃቸው እናደርጋለን። ከዚህ የባሰው ደግሞ እንዲህ ያለው ትኩረት፣ ኩሩ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። (ሮም 12:3) ማናችንም ብንሆን የክርስቶስ ቅቡዕ ወንድሞች እንዲህ ያለ ከባድ ስህተት እንዲሠሩ ምክንያት መሆን አንፈልግም!—ሉቃስ 17:2፤ w20.01 28 አን. 8
ዓርብ፣ ነሐሴ 27
ከእነዚህ ውጫዊ ችግሮች በተጨማሪ . . . የሚያስጨንቀኝ የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ ነው።—2 ቆሮ. 11:28
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲጨነቅ ሊያደርጉት የሚችሉ ብዙ ነገሮች ነበሩ። ወንድሞቹና እህቶቹ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች እረፍት ነስተውት ነበር። (2 ቆሮ. 2:4) በተቃዋሚዎቹ እጅ የተደበደበበትና እስር ቤት የተጣለበት ጊዜ አለ። ‘በትንሽ ነገር ለመኖር’ መገደድን ጨምሮ እንዲጨነቅ የሚያደርጉ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመውታል። (ፊልጵ. 4:12) ቢያንስ ሦስት ጊዜ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞት ስለነበር በመርከብ ሲሄድ ምን ያህል ሊጨነቅ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። (2 ቆሮ. 11:23-27) ታዲያ ጳውሎስ ጭንቀትን መቋቋም የቻለው እንዴት ነው? ጳውሎስ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ቢጨነቅም ችግሮቻቸውን በሙሉ ብቻውን ለማስተካከል አልሞከረም። ጳውሎስ አቅሙን የሚያውቅ ሰው ነበር። እንደ ጢሞቴዎስና ቲቶ ያሉ እምነት የሚጣልባቸው ወንዶች ጉባኤውን ከመንከባከብ ጋር በተያያዘ እንዲያግዙት ዝግጅት አድርጓል። እነዚህ ወንድሞች ያከናወኑት ሥራ ጳውሎስ ጭንቀቱ ቀለል እንዲልለት አድርጎ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።—ፊልጵ. 2:19, 20፤ ቲቶ 1:1, 4, 5፤ w20.02 23 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 28
ልጆች ሆይ፣ . . . ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።—ኤፌ. 6:1
ይሖዋ እኛም እሱን እንድንታዘዘው ይጠብቅብናል። ይሖዋ ስለፈጠረን፣ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስለሚያሟላልን እንዲሁም ከየትኛውም ወላጅ የበለጠ ጥበበኛ ስለሆነ ልንታዘዘው ይገባል። ይሁን እንጂ ይሖዋን እንድንታዘዝ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለእሱ ያለን ፍቅር ነው። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋን እንድንታዘዝ የሚያነሳሱ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም እሱ ይህን እንድናደርግ አያስገድደንም። ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ስንታዘዘው ይደሰታል። ወላጆች ልጆቻቸውን ከአደጋ መጠበቅ ይፈልጋሉ። ደንቦች የሚያወጡት ለዚህ ነው። ልጆች እነዚህን ደንቦች ሲታዘዙ፣ በወላጆቻቸው እንደሚተማመኑና ለእነሱ አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ። ከዚህ አንጻር፣ እኛም የሰማዩ አባታችን ያወጣቸውን መሥፈርቶች ማወቃችንና በእነሱ መሠረት ሕይወታችንን መምራታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይህን ስናደርግ ይሖዋን እንደምንወደውና እንደምናከብረው የምናሳይ ከመሆኑም ሌላ ራሳችንንም እንጠቅማለን። (ኢሳ. 48:17, 18) ከዚህ በተቃራኒ ግን ይሖዋንና መሥፈርቶቹን የማይቀበሉ ሰዎች ጉዳት ላይ ይወድቃሉ።—ገላ. 6:7, 8፤ w20.02 9-10 አን. 8-9
እሁድ፣ ነሐሴ 29
እባክህ አገልጋይህ እንድታናግርህ ፍቀድላት፤ የአገልጋይህንም ቃል ስማ።—1 ሳሙ. 25:24
አንድ ሰው በአደገኛ ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንደሆነ ብናይ እንደ አቢጋኤል በድፍረት መናገር አለብን። (መዝ. 141:5) በአክብሮት መናገር ቢኖርብንም ምክሩን አለዝበን አናቀርብም። በፍቅር ተነሳስተን አስፈላጊውን ምክር ስንሰጥ እውነተኛ ጓደኛ መሆናችንን እናሳያለን። (ምሳሌ 27:17) በተለይ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ያሉ የተሳሳተ ጎዳና የሚከተሉ አስፋፊዎችን ለማነጋገር ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል። (ገላ. 6:1) ሽማግሌዎች እነሱም ፍጹማን እንዳልሆኑና ምክር የሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንደሚኖር በትሕትና ይቀበላሉ። ሆኖም ይህ እውነታ ተግሣጽ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ከመውቀስ ወደኋላ እንዲሉ ሊያደርጋቸው አይገባም። (2 ጢሞ. 4:2፤ ቲቶ 1:9) አንድን ሰው ሲመክሩ ከይሖዋ ያገኙትን የመናገር ችሎታ በመጠቀም ግለሰቡን በጥበብና በትዕግሥት ለማስተማር ጥረት ያደርጋሉ። ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ያነሳሳቸዋል። (ምሳሌ 13:24) ሆኖም በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ነገር የይሖዋን መሥፈርቶች በመደገፍ እሱን ማክበራቸውና ጉባኤውን ከጉዳት መጠበቃቸው ነው።—ሥራ 20:28፤ w20.03 20 አን. 8-9
ሰኞ፣ ነሐሴ 30
ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።—ፊልጵ. 4:13
ይሖዋ፣ ሙሴን የእስራኤላውያን ነፃ አውጪ እንዲሆን አድርጎታል። ሆኖም ይሖዋ ሙሴን የተጠቀመበት መቼ ነው? ሙሴ “የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ” በመማሩ ሕዝቡን ለመምራት ብቃት እንዳለው በተሰማው ጊዜ ነበር? (ሥራ 7:22-25) አይደለም፤ ይሖዋ ሙሴን የተጠቀመበት ትሑትና ገር ሰው እንዲሆን ሥልጠና ከሰጠው በኋላ ነው። (ሥራ 7:30, 34-36) ይሖዋ፣ በግብፁ ኃያል ገዢ ፊት ለመቆም የሚያስችል ድፍረት ለሙሴ ሰጥቶታል። (ዘፀ. 9:13-19) ይህ ዘገባ፣ ይሖዋ የሚጠቀመው አምላካዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ በሚጥሩ እንዲሁም ብርታት ለማግኘት በእሱ በሚታመኑ ሰዎች እንደሆነ ያሳያል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ፣ የተለያዩ ሚናዎችን እንዲጫወቱ አገልጋዮቹን ተጠቅሞባቸዋል። አንተንስ ምን እንድትሆን ያደርግህ ይሆን? ይህ በአብዛኛው የተመካው ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆንህ ላይ ነው። (ቆላ. 1:29) ራስህን በፈቃደኝነት ካቀረብክ ይሖዋ ቀናተኛ ወንጌላዊ፣ ውጤታማ አስተማሪ፣ ጥሩ አጽናኝ፣ የተዋጣለት ሠራተኛ፣ አሳቢ ወዳጅ ወይም ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል። w19.10 21 አን. 5፤ 25 አን. 14
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 31
ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።—ዮሐ. 15:15
ጥሩ ወዳጆች ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ይረዱናል። እንዲህ ያሉ ወዳጆችን ማፍራት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ እኛ ራሳችን ጥሩ ወዳጆች ሆነን መገኘት ነው። (ማቴ. 7:12) ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ሳንቆጥብ ሌሎችን በተለይም ‘የተቸገሩትን’ እንድንረዳ ያበረታታናል። (ኤፌ. 4:28) ሌሎችን በመርዳት ላይ ትኩረት ስናደርግ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። (ሥራ 20:35) በዚህ መልኩ የምናፈራቸው ወዳጆች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይደግፉናል፤ እንዲሁም ውስጣዊ ሰላማችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዱናል። ኢዮብ ስለደረሰበት መከራ ሲናገር ኤሊሁ እንዳዳመጠው ሁሉ ወዳጆቻችንም ያስጨነቀንን ነገር ስንናገር በትዕግሥት ያዳምጡናል። (ኢዮብ 32:4) ወዳጆቻችን ውሳኔዎችን እንዲያደርጉልን መጠበቅ የለብንም፤ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጡን ማዳመጣችን ጥበብ ነው። (ምሳሌ 15:22) ንጉሥ ዳዊት ወዳጆቹ ያደረጉለትን እርዳታ በትሕትና ተቀብሏል፤ እኛም በኩራት ተሸንፈን ወዳጆቻችን የሚሰጡንን እርዳታ ከመቀበል ወደኋላ ማለት የለብንም። (2 ሳሙ. 17:27-29) በእርግጥም እንዲህ ያሉ ወዳጆች የይሖዋ ስጦታዎች ናቸው።—ያዕ. 1:17፤ w19.04 11 አን. 12፤ 12 አን. 14-15