ታኅሣሥ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 1
የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነው።—ያዕ. 1:6
አልፎ አልፎ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝን ሐሳብ መረዳት የሚከብደን ጊዜ ይኖራል። ወይም ደግሞ ይሖዋ እኛ በጠበቅነው መንገድ ለጸሎታችን መልስ ላይሰጠን ይችላል። ይህ ጥርጣሬ እንዲፈጠርብን ያደርግ ይሆናል። የተፈጠረብንን ጥርጣሬ ችላ ብለን ከተውነው እምነታችንን ሊያዳክምብንና ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ሊያበላሽብን ይችላል። (ያዕ. 1:7, 8) የወደፊቱ ተስፋችንም ብሩህ ሆኖ እንዳይታየን ሊያደርግ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ተስፋችንን ከመልሕቅ ጋር አመሳስሎታል። (ዕብ. 6:19) መልሕቅ፣ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ ያለን መርከብ ባለበት እንዲቆምና ከዓለት ጋር እንዳይላተም ይረዳዋል። ሆኖም አንድ መልሕቅ እንዲህ ያለ ጥቅም ሊሰጥ የሚችለው ከመርከቡ ጋር የተያያዘበት ሰንሰለት እስካልተበጠሰ ብቻ ነው። ዝገት የመልሕቁን ሰንሰለት እንደሚበላው ሁሉ ጥርጣሬም እምነታችንን ይበላዋል። ጥርጣሬ ያደረበት አንድ ሰው ተቃውሞ ሲያጋጥመው ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ ያለው እምነት ሊጠፋ ይችላል። እምነታችን ከጠፋ ደግሞ ተስፋችን ይጨልማል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ደግሞ ደስተኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። w21.02 30 አን. 14-15
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 2
አብርሃም በይሖዋ አመነ።—ያዕ. 2:23
አብርሃም ቤተሰቡን ይዞ ከዑር ሲወጣ ዕድሜው ከ70 ዓመት በላይ የነበረ ይመስላል። (ዘፍ. 11:31 እስከ 12:4) ከዚያም መቶ ገደማ ለሚሆኑ ዓመታት በከነአን ምድር ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ድንኳን ውስጥ ኖሯል። አብርሃም የሞተው በ175 ዓመቱ ነው። (ዘፍ. 25:7) ሆኖም የተዘዋወረባትን ምድር ለዘሮቹ እንደሚሰጥ ይሖዋ የገባለት ቃል ሲፈጸም ለማየት አልበቃም። ይጠብቃት የነበረችው ከተማ ማለትም የአምላክ መንግሥት ስትቋቋምም አላየም። ያም ቢሆን አብርሃም “በሕይወቱ ረክቶና ዕድሜ ጠግቦ” እንደሞተ ተገልጿል። (ዘፍ. 25:8) አብርሃም ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም እምነቱ ምንጊዜም ጠንካራ ነበር፤ ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠባበቅም ፈቃደኛ ነበር። አብርሃም መጽናት የቻለው ለምንድን ነው? በሕይወቱ በሙሉ ይሖዋ ጥበቃ ስላደረገለትና እንደ ወዳጁ አድርጎ ስለተንከባከበው ነው። (ዘፍ. 15:1፤ ኢሳ. 41:8፤ ያዕ. 2:22) እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ እየተጠባበቅን ነው። (ዕብ. 11:10) በእርግጥ ይህች ከተማ እስክትገነባ መጠበቅ አያስፈልገንም። የአምላክ መንግሥት በ1914 የተቋቋመ ሲሆን ሰማይን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል። (ራእይ 12:7-10) ሆኖም ምድርን ሙሉ በሙሉ እስኪቆጣጠር መጠበቅ ያስፈልገናል። w20.08 4-5 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 3
በሰው ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀድቶ ያወጣዋል።—ምሳሌ 20:5
ሌሎችን በጥሞና ለማዳመጥ ትሑትና ታጋሽ መሆን ያስፈልገናል። በዚህ ረገድ የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችን ቢያንስ ሦስት ጥቅሞች ያስገኛል። አንደኛ፣ ስለ ሰዎች በችኮላ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ ይረዳናል። ሁለተኛ፣ የወንድማችንን ስሜትና አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሳበትን ምክንያት ስለምንረዳ ይበልጥ እንድናዝንለት ያደርገናል። ሦስተኛ፣ ግለሰቡ ስለ ራሱ ቀደም ሲል የማያውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች እንዲገነዘብ ልንረዳው እንችላለን። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ፣ የራሳችንን ስሜት በትክክል መረዳት የምንችለው በቃላት ስንገልጸው ብቻ ነው። አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአስተዳደጋቸው፣ በባሕላቸው ወይም በባሕርያቸው የተነሳ ስሜታቸውን አውጥተው መናገር ይከብዳቸዋል። በነፃነት የውስጣቸውን የሚነግሩን የተወሰነ ጊዜ ካለፈ በኋላ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና እውነተኛ ስሜታቸውን ማወቅ የምንችለው እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች ሲሆኑ ብቻ ነው። ታጋሽ በመሆን ይሖዋን የምንመስል ከሆነ የወንድሞቻችንን አመኔታ ማትረፍ እንችላለን። በኋላ ላይ ስሜታቸውን አውጥተው ለመናገር ዝግጁ እንደሆኑ ሲሰማቸው ደግሞ በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብናል። w20.04 15-16 አን. 6-7
እሁድ፣ ታኅሣሥ 4
ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ።—ሉቃስ 5:10
ዓሦች ብዙውን ጊዜ የሚገኙት ውኃው በሚስማማቸውና ብዙ ምግብ በሚያገኙበት አካባቢ ነው። አንድ ዓሣ አጥማጅ ሥራውን የሚያከናውንበት ጊዜስ ለውጥ ያመጣል? በፓስፊክ ደሴት የሚኖር አንድ ሚስዮናዊ፣ ዓሣ ከማጥመድ ጋር በተያያዘ ጊዜ መምረጥ እንደሚያስፈልግ ተገንዝቧል። በአካባቢው የሚኖር አንድ ወንድም ይህን ሚስዮናዊ አብሮት ዓሣ እንዲያጠምድ ጋብዞት ነበር። ሚስዮናዊው “ነገ ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ እንገናኝ” አለው። የጋበዘው ወንድም ግን “ያልገባህ ነገር አለ። ዓሣ ለማጥመድ የምንሄደው ለእኛ በሚመቸን ጊዜ ሳይሆን ዓሦቹ በሚገኙበት ጊዜ ነው” ብሎ መለሰለት። በተመሳሳይም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሰው አጥማጆች፣ “ዓሦች” በሚገኙበት ቦታ እና ሰዓት ለመስበክ ጥረት ያደርጉ ነበር። ለምሳሌ የኢየሱስ ተከታዮች በቤተ መቅደስ፣ በምኩራቦች፣ ከቤት ወደ ቤት እንዲሁም በገበያ ስፍራ ይሰብኩ ነበር። (ሥራ 5:42፤ 17:17፤ 18:4) እኛም በክልላችን ውስጥ ስላሉት ሰዎች ማወቅ ይኖርብናል። ፕሮግራማችንን እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ፈቃደኛ መሆናችን እንዲሁም ሰዎችን በምናገኝበት ቦታና ጊዜ መስበካችን አስፈላጊ ነው።—1 ቆሮ. 9:19-23፤ w20.09 4 አን. 8-9
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 5
እውነትን በመናገር በሁሉም ነገር ወደ እሱ ይኸውም የአካሉ ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በፍቅር እንደግ።—ኤፌ. 4:15
ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚረዳን አንዱ መንገድ የክርስቲያን ጉባኤ የሚያደርገውን ዝግጅት መደገፍ ነው። እኛን እንዲንከባከቡን ከተሾሙ ወንዶች ጋር የምንተባበር ከሆነ የጉባኤው ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ጋር ያለን ወዳጅነት ይጠናከራል። (ኤፌ. 4:16) ለምሳሌ ያህል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስብሰባ አዳራሾቻችን ያላቸውን አቅም ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው። ለዚህም ሲባል አንዳንድ ጉባኤዎች እንዲዋሃዱ ተደርጓል። ይህ ዝግጅት በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በከፍተኛ መጠን ለመቆጠብ አስችሏል። ይሁንና ዝግጅቱ፣ በአንዳንድ አስፋፊዎች ላይ ለውጥ አስከትሏል። እነዚህ ታማኝ አስፋፊዎች በአንድ ጉባኤ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው ሊሆን ይችላል፤ እንዲሁም በዚያ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተው ይሆናል። በዚህ ዝግጅት ምክንያት ግን በሌላ ጉባኤ እንዲያገለግሉ ተጠይቀዋል። ኢየሱስ፣ እነዚህ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ዝግጅቱን ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን! w20.04 24 አን. 14
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 6
የደቡቡ ንጉሥ ከእሱ ጋር ይጣላል።—ዳን. 11:40 ግርጌ
የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ፣ በዓለም ላይ ኃያል መንግሥት ለመሆን የሚያደርጉትን ሽኩቻ አያቆሙም። ለምሳሌ ያህል፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሶቪየት ኅብረት እና አጋሮቹ በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍል ላይ ተጽዕኖ ባሳደሩበት ወቅት ምን እንደተፈጠረ እንመልከት። የሰሜኑ ንጉሥ ያደረገው ነገር፣ የደቡቡ ንጉሥ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የተባለ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ኅብረት እንዲመሠርት ምክንያት ሆኗል። የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ፣ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው የጦር መሣሪያ በማከማቸት እርስ በርስ መፎካከራቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም በአፍሪካ፣ በእስያና በደቡብ አሜሪካ በተቀሰቀሱ ዓመፆች ውስጥ ተቃራኒ ቡድኖችን በመደገፍ በእጅ አዙር ተዋግተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ሩሲያ እና አጋሮቿ በዓለም ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ እየጨመረ መጥቷል። ከዚህም ሌላ በደቡቡ ንጉሥ ላይ የሳይበር ጥቃት (በኮምፒውተር አማካኝነት የሚሰነዘር ጥቃት) ሰንዝረዋል። ሁለቱ ነገሥታት፣ ኢኮኖሚያቸውንና የፖለቲካ ሥርዓታቸውን የሚጎዳ የኮምፒውተር ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው በመግለጽ አንዳቸው ሌላውን ሲወነጅሉ ቆይተዋል። በተጨማሪም ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክን ሕዝቦች ማጥቃቱን ቀጥሏል።—ዳን. 11:41፤ w20.05 13 አን. 5-6
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 7
እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ ደግሞም እንከባከባቸዋለሁ።—ሕዝ. 34:11
“እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች?” ይሖዋ ይህን ጥያቄ ያቀረበው በነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን ነበር። አምላክ ሕዝቡን “እነዚህ ሴቶች ቢረሱ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም” ብሏቸዋል። (ኢሳ. 49:15) አምላክ ራሱን ከእናት ጋር አነጻጽሮ የሚናገረው ብዙ ጊዜ አይደለም። በዚህ ወቅት ግን እንዲህ አድርጓል። ይሖዋ፣ ለአገልጋዮቹ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ በእናትና በልጇ መካከል ያለውን ዝምድና ተጠቅሟል። አብዛኞቹ እናቶች ሃስሚን የተባለች እህት በተናገረችው ሐሳብ ይስማማሉ፤ እንዲህ ብላለች፦ “ልጃችሁን ስታጠቡ ከልጃችሁ ጋር ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ በጣም ልዩ የሆነ ትስስር ትፈጥራላችሁ።” ይሖዋ ከልጆቹ መካከል አንዱም እንኳ ቢሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቱንና በስብከቱ ሥራ መሳተፉን ሲያቆም ያስተውላል። በመንፈሳዊ ከቀዘቀዙ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል ብዙዎቹ ወደ ጉባኤው ይመለሳሉ፤ በመመለሳቸውም በጣም ደስ ይለናል! ይሖዋ እነዚህ አስፋፊዎች እንዲመለሱ ይፈልጋል፤ የእኛም ፍላጎት ይኸው ነው።—1 ጴጥ. 2:25፤ w20.06 18 አን. 1-3
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 8
ዓይናችን እንዲያተኩር የምናደርገው . . . በማይታዩት ነገሮች ላይ ነው። የሚታዩት ጊዜያዊ ናቸውና፤ የማይታዩት ግን ዘላለማዊ ናቸው።—2 ቆሮ. 4:18
በዓይናችን ልናያቸው የማንችላቸው ውድ ሀብቶች አሉ። እንዲያውም ከሁሉ በላይ ውድ የሆኑት ሀብቶች በዓይን የሚታዩ አይደሉም። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ከቁሳዊ ሀብቶች በእጅጉ ስለሚልቁት ሰማያዊ ሀብቶች ገልጿል። ከዚያም “ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናል” የሚለውን መሠረታዊ እውነታ ተናግሯል። (ማቴ. 6:19-21) ልባችን፣ ውድ አድርገን የምንመለከታቸውን ነገሮች ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ይገፋፋናል። ‘በሰማይ ለራሳችን ሀብት’ የምናከማቸው በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም በማትረፍ ነው። ኢየሱስ እንደተናገረው እንዲህ ያለው ሀብት ፈጽሞ ሊጠፋ ወይም ሊሰረቅ አይችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ዓይናችን በማይታዩት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር’ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (2 ቆሮ. 4:17, 18) የማይታዩት ነገሮች ከተባሉት መካከል በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የምናገኛቸው በረከቶች ይገኙበታል። ታዲያ ለእነዚህ የማይታዩ ሀብቶች አድናቆት እንዳለን እናሳያለን? w20.05 26 አን. 1-2
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 9
ትምህርቴ እንደ ዝናብ ይወርዳል።—ዘዳ. 32:2
ሙሴ እስራኤላውያንን ያስተማራቸው ነገር እምነታቸው እንዲጠናከርና መንፈሳቸው እንዲታደስ አድርጓቸው መሆን አለበት። እኛስ ትምህርታችን እንዲህ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ወይም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ስንካፈል መጽሐፍ ቅዱሳችንን ተጠቅመን ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ለሰዎች ልናሳያቸው እንችላለን። ይሖዋን የሚያስከብሩ ግሩም ጽሑፎች ልንሰጣቸው እንዲሁም ቪዲዮዎች ወይም ድረ ገጻችን ላይ የሚገኙ ነገሮችን ልናሳያቸው እንችላለን። በተጨማሪም በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት አሊያም በጉዞ ላይ ስንሆን፣ ስለምንወደው አምላካችንና ስለ ማንነቱ የመናገር አጋጣሚ እናገኝ ይሆናል። ይሖዋ ለሰው ዘሮችና ለምድር ስላለው ፍቅር የተንጸባረቀበት ዓላማ ለምናገኛቸው ሰዎች ስንነግራቸው ከዚህ በፊት ስለ ይሖዋ ፈጽሞ ሰምተው የማያውቁትን ነገር እንዲያውቁ እየረዳናቸው ሊሆን ይችላል። አፍቃሪ ስለሆነው አባታችን እውነቱን ለሌሎች ስንናገር ስሙ እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው። ሰዎች ስለ ይሖዋ የተማሯቸውን ውሸቶች በዚህ መንገድ እናጋልጣለን። በእርግጥም ለሰዎች የምናስተምረው ትምህርት ከምንም በላይ መንፈስን የሚያድስ ነው።—ኢሳ. 65:13, 14፤ w20.06 10 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 10
ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ።—ሚል. 3:7
ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት የትኞቹ ባሕርያት ያስፈልጉናል? ኢየሱስ ቤቱን ትቶ ስለሄደው አባካኝ ልጅ ከተናገረው ምሳሌ አንዳንድ ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 15:17-24) ከጊዜ በኋላ ልጁ ወደ ልቦናው ተመልሶ ወደ ቤቱ ለመመለስ ወሰነ። አባትየው ልጁን ሲያየው እየሮጠ ወደ እሱ በመሄድ አንገቱ ላይ ተጠመጠመ፤ በዚህ መንገድ እንደሚወደው አረጋገጠለት። ልጅየው ሕሊናው ረብሾት እንዲሁም አባቱ እንደ ልጁ ሊቆጥረው እንደማይገባ ተሰምቶት ነበር። ልጁ የልቡን አውጥቶ የተናገረ ሲሆን አባትየውም ስሜቱን ተረድቶለት ነበር። ከዚያም አባትየው ልጁ ወደ ቤት በመመለሱ ምን ያህል እንደተደሰተና እንደ ውድ የቤተሰቡ አባል አድርጎ እንደተቀበለው ልጁ እንዲገነዘብ የሚያደርጉ እርምጃዎችን ወሰደ። በመሆኑም ድግስ ያዘጋጀ ከመሆኑም ሌላ ንስሐ የገባውን ልጁን ጥሩ ልብስ አለበሰው። ይሖዋ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው አባት ነው። የቀዘቀዙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይወዳቸዋል፤ ወደ እሱ እንዲመለሱም ይፈልጋል። እኛም ይሖዋን በመምሰል ወደ ጉባኤው እንዲመለሱ ልንረዳቸው እንችላለን። ይህን ለማድረግ ትዕግሥተኛ መሆን፣ ስሜታቸውን መረዳት እንዲሁም ፍቅር ማሳየት ያስፈልገናል። w20.06 25-26 አን. 8-9
እሁድ፣ ታኅሣሥ 11
ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።—ዮሐ. 8:31, 32
ኢየሱስ አንዳንዶች እውነትን “በደስታ” ቢቀበሉም ፈተና ሲደርስባቸው እምነታቸው እንደሚጠፋ ተናግሯል። (ማቴ. 13:3-6, 20, 21) ምናልባት ኢየሱስን መከተል ተፈታታኝ ሁኔታዎችና መከራ እንደሚያስከትል አልተገነዘቡ ይሆናል። (ማቴ. 16:24) ወይም ደግሞ ክርስትና በበረከት ብቻ የተሞላና ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ይሁንና በዚህ ዓለም ውስጥ ችግር ማጋጠሙ አይቀርም። ያለንበት ሁኔታ ሊቀየርና ለተወሰነ ጊዜ ያህል ደስታችን ሊቀንስ ይችላል። (መዝ. 6:6፤ መክ. 9:11) አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ መሆናቸው በግልጽ ይታያል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የእምነት ባልንጀሮቻቸው ቢጎዷቸው ወይም ክርስቲያናዊ ያልሆነ ምግባር ቢያሳዩም እንኳ እምነታቸው አይናወጥም። (መዝ. 119:165) ፈተና ባጋጠማቸው ቁጥር እምነታቸው ከመዳከም ይልቅ እየተጠናከረ ይሄዳል። (ያዕ. 1:2-4) እንዲህ ያለውን ጠንካራ እምነት መገንባት አለብን። w20.07 8 አን. 1፤ 9 አን. 4-5
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 12
ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን።—ያዕ. 1:5
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን ከመጀመርህ በፊት ከምታነበው ነገር ጥቅም ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ለምሳሌ አንድን ችግር ለመወጣት የሚረዳ ምክር ማግኘት ከፈለግህ በዚህ ረገድ የሚረዱህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በቃሉ ውስጥ ለማግኘት እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። (ፊልጵ. 4:6, 7) ይሖዋ ነገሮችን በዓይነ ሕሊናችን የመሣል አስደናቂ ችሎታ ሰጥቶናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ሕያው እንዲሆንልህ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣልና ራስህን በዋናው ባለታሪክ ቦታ ለማስቀመጥ ጥረት አድርግ። ባለታሪኩ ያየው ነገር እንዲታይህና የተሰማው ስሜት እንዲሰማህ ለማድረግ ሞክር። ከዚያም አሰላስል። ማሰላሰል ማለት ስላነበብከው ነገርና ዘገባው ለአንተ ስለያዘው ትምህርት በጥልቀት ማሰብ ማለት ነው። ማሰላሰልህ ነጥቦቹን ለማያያዝና ርዕሰ ጉዳዩን በጥልቀት ለመረዳት ይረዳሃል። w21.03 15 አን. 3-5
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 13
[አምላክን] አመሰግናለሁ፤ ደግሞም ሌት ተቀን አንተን ዘወትር በምልጃዬ አስታውሳለሁ።—2 ጢሞ. 1:3
ሐዋርያው ጳውሎስ ቀደም ሲል ያደረጋቸውን ውሳኔዎች በማሰብ ‘ቀናተኛ ክርስቲያን ባልሆን ኖሮ አልታሰርም ነበር’ ብሎ ሊቆጭ ይችል ነበር። ትተውት በሄዱት በእስያ አውራጃ የነበሩ ሰዎች ምክንያት ምሬት ሊያድርበት ይችል ነበር፤ ወይም ደግሞ ሌሎች ወዳጆቹን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ሊጀምር ይችል ነበር። ጳውሎስ ግን እነዚህን ነገሮች አላደረገም። ጳውሎስ ከሞት ጋር ቢፋጠጥም አንገብጋቢው ጉዳይ ይሖዋን ማስከበር እንደሆነ አልዘነጋም። እንዲሁም ሌሎችን ማበረታታት ስለሚችልባቸው መንገዶች ማሰቡን ቀጥሏል። በተጨማሪም ወደ ይሖዋ አዘውትሮ በመጸለይ በእሱ እንደሚታመን አሳይቷል። ትተውት በሄዱት ሰዎች ላይ ከልክ በላይ ከማተኮር ይልቅ በተለያዩ መንገዶች በታማኝነት ለደገፉት ወዳጆቹ ያለውን ጥልቅ የአድናቆት ስሜት ገልጿል። ከዚህም ሌላ ጳውሎስ የአምላክን ቃል ማጥናቱን ቀጥሏል። (2 ጢሞ. 3:16, 17፤ 4:13) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋና ኢየሱስ እንደሚወዱት ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። w21.03 18 አን. 17-18
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 14
እንክርዳዱ ተሰብስቦ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዚህ ሥርዓት መደምደሚያም እንዲሁ ይሆናል።—ማቴ. 13:40
በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሆነ ጊዜ ላይ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ በሐሰተኛ ክርስቲያኖች እየተዋጠ መጣ፤ እነዚህ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች አረማዊ ትምህርቶችን ማስተማርና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መሸሸግ ጀመሩ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ በቡድን ሆነው ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች በምድር ላይ አልነበሩም። በእንክርዳድ የተመሰለው የሐሰት ክርስትና የተስፋፋ ሲሆን እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ ማወቅ አይቻልም ነበር። (ማቴ. 13:36-43) ይህን ማወቃችን ምን ጥቅም አለው? በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ስለ ሰሜኑና ስለ ደቡቡ ንጉሥ የሚገልጸው ትንቢት ከ2ኛው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ የተነሱትን ገዢዎች ወይም መንግሥታት ሊያመለክት እንደማይችል ይጠቁመናል። ምክንያቱም በዚህ ወቅት እነዚህ ነገሥታት ሊያጠቁት የሚችሉት የአምላክ አገልጋዮች ቡድን አልነበረም። ሆኖም የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በድጋሚ ብቅ እንደሚሉ መጠበቅ እንችላለን። w20.05 3 አን. 5
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 15
ኃያል የሆነ . . . ብሔር ምድሬን ወሮታል።—ኢዩ. 1:6
ኢዩኤል፣ የአንበጣ መንጋ በምድሩ ላይ ያለውን ነገር ሁሉ በመብላት የእስራኤልን ምድር እንደሚያወድም ትንቢት ተናግሯል! (ኢዩ. 1:4) ላለፉት በርካታ ዓመታት፣ ይህ ትንቢት የሚያመለክተው የይሖዋ ሕዝብ ምንም የሚያስቆመው ነገር እንደሌለ የአንበጣ መንጋ የስብከቱን ሥራ የሚያከናውንበትን መንገድ እንደሆነ እናምን ነበር። የስብከቱ ሥራ ‘በምድሩ’ ማለትም በሃይማኖት መሪዎች ቁጥጥር ሥር ባለው ሕዝብ ላይ ውድመት እንደሚያስከትልም እናስብ ነበር። ሆኖም ሙሉውን ትንቢት ስንመረምር በግንዛቤያችን ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እንረዳለን። ይሖዋ የአንበጣውን መንጋ በተመለከተ “የሰሜኑን ሠራዊት [አንበጦቹን] ከእናንተ አርቃለሁ” ብሎ ቃል እንደገባ ልብ በል። (ኢዩ. 2:20) አንበጦቹ የሚያመለክቱት የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በተመለከተ ኢየሱስ የሰጠውን መመሪያ የሚታዘዙትን የይሖዋ ምሥክሮች ከሆነ ይሖዋ እነሱን እንደሚያባርር ቃል የሚገባበት ምን ምክንያት አለ? (ሕዝ. 33:7-9፤ ማቴ. 28:19, 20) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ የሚያባርረው ታማኝ አገልጋዮቹን ሳይሆን የሕዝቡ ጠላት የሆነን ነገር ወይም አካል መሆን አለበት። w20.04 3 አን. 3-5
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 16
ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን።—ያዕ. 1:5
ይሖዋ ለጸሎታችን ወዲያውኑ ምላሽ እንዳልሰጠን ቢሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ያዕቆብ ‘አምላክን ያለማሰለስ መለመን’ እንዳለብን ተናግሯል። ይሖዋ፣ ጥበብ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ስንለምነው እንደጨቀጨቅነው አይሰማውም። እንዲህ በማድረጋችን አይነቅፈንም። የሰማዩ አባታችንን የገጠሙንን ፈተናዎች መቋቋም የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን ስንለምነው ‘በልግስና ይሰጠናል።’ (መዝ. 25:12, 13) ያሉብንን ፈተናዎች ያያል፣ ያዝንልናል እንዲሁም ሊረዳን ይፈልጋል። በእርግጥም ይህ ለደስታችን ምክንያት የሚሆን ነገር ነው! ይሁንና ይሖዋ ጥበብ የሚሰጠን እንዴት ነው? በቃሉ አማካኝነት ነው። (ምሳሌ 2:6) ይህን ጥበብ ለማግኘት የአምላክን ቃልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማጥናት አለብን። ሆኖም እውቀት ከማከማቸት የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። አምላክ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የአምላክ ጥበብ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ ማድረግ አለብን። ያዕቆብ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ . . . ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:22) የአምላክን ምክር ተግባራዊ ስናደርግ ይበልጥ ሰላማዊ፣ ምክንያታዊና መሐሪ እንሆናለን። (ያዕ. 3:17) እነዚህ ባሕርያት ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዱናል። w21.02 29 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 17
እያንዳንዱ የአካል ክፍል [አካሉ] እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ኤፌ. 4:16
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጉባኤውን ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ማግኘቱ እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ይረዳዋል። እያንዳንዱ አስፋፊ ጉባኤው እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል። አንዲት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “‘ልጅን የሚያሳድገው መንደሩ በሙሉ ነው’ የሚል አባባል አለ። ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ይመስለኛል፤ ብዙውን ጊዜ አንድን ሰው ወደ እውነት ለማምጣት የመላው ጉባኤ እርዳታ ያስፈልጋል።” አንድ ልጅ አድጎ አዋቂ እስኪሆን ድረስ የቤተሰቡ አባላት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም አስተማሪዎቹ በሙሉ ይረዱታል። ይህን የሚያደርጉት ልጁን በማበረታታትና አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችን በማስተማር ነው። በተመሳሳይም አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምከር፣ ማበረታታትና ለእነሱ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላሉ። በዚህ መልኩ ጥናቶቹ እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ይረዷቸዋል። (ምሳሌ 15:22) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን የሚመራው አስፋፊ፣ ሌሎች አስፋፊዎች ጥናቱን እንዲረዱት ፈቃደኛ መሆን ያለበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም በርካታ ወንድሞችና እህቶች ለጥናቱ መንፈሳዊ እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። w21.03 8 አን. 1-3
እሁድ፣ ታኅሣሥ 18
“ኃጢአት የለብንም” ብለን የምንናገር ከሆነ ራሳችንን እያታለልን ነው።—1 ዮሐ. 1:8
ወጣት አዋቂ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች ሁለት ዓይነት ሕይወት ከመምራት መቆጠብ አለባቸው። ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት እየመራን በእውነት ውስጥ መመላለስ እንደማንችል ሐዋርያው ዮሐንስ ተናግሯል። (1 ዮሐ. 1:6) አሁንም ሆነ ወደፊት የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን የምናደርገው ነገር በሙሉ በይሖዋ ፊት የተገለጠ መሆኑን እንደምናውቅ በሚያሳይ መንገድ ሕይወታችንን መምራት አለብን። ደግሞም ድብቅ ኃጢአት የሚባል ነገር የለም፤ ምክንያቱም ይሖዋ የምናደርገውን ነገር በሙሉ ይመለከታል። (ዕብ. 4:13) ዓለም ለኃጢአት ያለውን አመለካከት መቃወም ይኖርብናል። በዮሐንስ ዘመን ከሃዲዎች አንድ ሰው ሆን ብሎ በኃጢአት ጎዳና እየተመላለሰ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደሚችል ያስተምሩ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎችም ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። ብዙዎች በአምላክ እንደሚያምኑ ቢናገሩም ይሖዋ ለኃጢአት ያለውን አመለካከት በተለይ ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የሚሰጠውን መመሪያ አይቀበሉም። ይሖዋ እንደ ኃጢአት አድርጎ የሚቆጥራቸውን ድርጊቶች የምርጫ ጉዳይ እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። w20.07 22 አን. 7-8
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 19
በተግባርና በእውነት [እንዋደድ]።—1 ዮሐ. 3:18
መንፈሳዊ እህቶችህ ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው በሚያስፈልጋቸው ወቅት ትሟገትላቸዋለህ? አንድ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። የማያምን ባል ያላት አንዲት እህት አለች እንበል፤ ይህች እህት ብዙውን ጊዜ ጉባኤ የምትደርሰው አርፍዳ እንደሆነና ስብሰባው እንዳለቀም ወደ ቤቷ እንደምትሄድ አንዳንድ አስፋፊዎች አስተውለዋል። ልጆቿን ወደ ስብሰባ የምታመጣቸውም ከስንት አንዴ እንደሆነ ተመልክተዋል። በመሆኑም ከባሏ ጋር በተያያዘ ቆራጥ አቋም ልትወስድ እንደሚገባት በመግለጽ ይነቅፏታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እህታችን አቅሟ የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረገች ነው። ጊዜዋን የምትጠቀምበት መንገድ ሙሉ በሙሉ በእሷ ቁጥጥር ሥር አይደለም፤ ከልጆቿ ጋር በተያያዘም የመጨረሻውን ውሳኔ ማድረግ አትችልም። እህትን እንደምታደንቃት ብትገልጽላት እንዲሁም እያደረገች ያለችውን መልካም ነገር ለሌሎች ብትጠቅስ የሚሰነዘርባትን ነቀፋ ማስቆም ትችል ይሆናል። ሽማግሌዎች፣ ይሖዋ እነዚህ እህቶች በእንክብካቤ እንዲያዙ እንደሚፈልግ ያውቃሉ። (ያዕ. 1:27) በመሆኑም ደንቦችን ከማውጣት ይልቅ በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ለየት ያለ ደግነት በማሳየት እንደ ኢየሱስ ምክንያታዊ ለመሆን ይጥራሉ። (ማቴ. 15:22-28) ቅድሚያውን ወስደው እርዳታ የሚሰጡ ሽማግሌዎች፣ እህቶች እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ያደርጋሉ። w20.09 24-25 አን. 17-19
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 20
[አምላክ] በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነጾር አሳውቆታል።—ዳን. 2:28
ነቢዩ ዳንኤል ምንጊዜም የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል በይሖዋ እርዳታ የናቡከደነጾርን ሕልም በፈታበት ወቅት እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለነበር ክብርና ምስጋና የሰጠው ለይሖዋ ነው። (ዳን. 2:26-28) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ጥሩ ንግግር የመስጠት ችሎታ ሊኖረን ወይም በአገልግሎት ላይ ስኬታማ ልንሆን እንችላለን፤ ሆኖም ክብር ሁሉ ሊሰጠው የሚገባው ይሖዋ መሆኑን አንርሳ። ልካችንን በማወቅ፣ በይሖዋ እርዳታ ባይሆን ኖሮ እነዚህን ነገሮች ማከናወን እንደማንችል አምነን ልንቀበል ይገባል። (ፊልጵ. 4:13) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ስናዳብር የኢየሱስን ግሩም ምሳሌም እየተከተልን ነው። ኢየሱስ የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። (ዮሐ. 5:19, 30) የሰማዩ አባቱን ሥልጣን ለመውሰድ ሞክሮ አያውቅም። ፊልጵስዩስ 2:6 እንደሚገልጸው ኢየሱስ “የሥልጣን ቦታን ለመቀማት ማለትም ከአምላክ ጋር እኩል ለመሆን አላሰበም።” ኢየሱስ ቦታውን የሚያውቅና የአባቱን ሥልጣን የሚያከብር ታዛዥ ልጅ ነው። w20.08 11 አን. 12-13
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 21
ሽልማቱን እንድታገኙ በዚሁ ሁኔታ ሩጡ።—1 ቆሮ. 9:24
ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ የሚሮጡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሌሎች ሊያዩ ከማይችሉት፣ ምናልባትም ከማይረዱት የግል ችግር ጋር እየታገሉ ነው። አቅም የሚያሳጣ ችግር ቢኖርብህም ሌሎች ችግርህን እንደማይረዱልህ ከተሰማህ የሜፊቦስቴ ምሳሌ ያበረታታሃል። (2 ሳሙ. 4:4) ሜፊቦስቴ የአካል ጉዳተኛ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ ንጉሥ ዳዊት በተሳሳተ መንገድ ስለተረዳው በደል አድርሶበታል። ያም ቢሆን በደረሱበት ነገሮች የተነሳ ምሬት እንዲያድርበት አልፈቀደም፤ ከዚህ ይልቅ በሕይወቱ ላጋጠሙት መልካም ነገሮች አድናቆት ነበረው። ንጉሥ ዳዊት ቀደም ሲል ላሳየው ደግነትም አመስጋኝ ነበር። (2 ሳሙ. 9:6-10) በመሆኑም ዳዊት በተሳሳተ መንገድ ተረድቶት በበደለው ወቅት ነገሩን ሰፋ አድርጎ ለመመልከት ጥረት አድርጓል። ሜፊቦስቴ፣ ዳዊት የሠራው ስህተት እንዲመረር አላደረገውም። እንዲሁም ዳዊት ባደረገበት ነገር የተነሳ ይሖዋን አልወቀሰም። ሜፊቦስቴ ትኩረት ያደረገው ይሖዋ የቀባውን ንጉሥ ለመደገፍ ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ነበር። (2 ሳሙ. 16:1-4፤ 19:24-30) ይሖዋ ግሩም የሆነው የሜፊቦስቴ ታሪክ በቃሉ ውስጥ እንዲመዘገብ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው።—ሮም 15:4፤ w20.04 26 አን. 3፤ 30 አን. 18-19
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 22
ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።—1 ቆሮ. 3:9
በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሚስዮናውያን፣ ልዩ አቅኚዎች ወይም የዘወትር አቅኚዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾማሉ። የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ የሙሉ ጊዜ ሥራቸው ለማድረግ ወስነዋል። አብዛኞቹ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ከቁሳዊ ነገር አንጻር ብዙ ባይኖራቸውም ይሖዋ በሕይወታቸው ውስጥ አትረፍርፎ ባርኳቸዋል። (ማር. 10:29, 30) እነዚህን ውድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን፤ የጉባኤው ክፍል በመሆናቸውም አመስጋኞች ነን! የተሾሙ ወንድሞችና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖች በጉባኤው ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ እንደሚያበረክቱ ተመልክተናል፤ ይሁንና በጉባኤው ውስጥ ቦታ ያላቸው እነሱ ብቻ ናቸው? በፍጹም! ምሥራቹን የሚሰብክ እያንዳንዱ አስፋፊ በአምላክ ዘንድም ሆነ በጉባኤው ውስጥ አስፈላጊ ሚና አለው። (ሮም 10:15፤ 1 ቆሮ. 3:6-8) እንዲያውም ጉባኤው ከተቋቋመባቸው ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ሰዎችን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጢሞ. 2:4) በጉባኤው ውስጥ ያሉ የተጠመቁም ሆኑ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች በሙሉ ለዚህ ሥራ ቅድሚያ ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ።—ማቴ. 24:14፤ w20.08 21 አን. 7-8
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 23
እኔ እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።—ማቴ. 28:20
በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ኢየሱስ ይረዳናል። እንዲያውም ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ የብርታት ምንጭ ይሆነናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለመቋቋም የሚከብድ ችግር የሚገጥመን ጊዜ አለ። ለምሳሌ፣ የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ሐዘኑ ለጥቂት ቀናት ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ዓመታት ሊቀጥል ይችላል። አንዳንዶች በእርጅና የተነሳ ከባድ ሁኔታ የሚገጥማቸው ጊዜ አለ። ሌሎች ደግሞ በመንፈስ ጭንቀት የሚዋጡበት ጊዜ ይኖራል። ሆኖም ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ በጣም አስጨናቂ ሁኔታ የገጠመንን ጊዜ ጨምሮ “ሁልጊዜ” አብሮን እንደሆነ እናውቃለን፤ ይህ ደግሞ ለመጽናት ብርታት ይሰጠናል። (ማቴ. 11:28-30) ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት እንደሚረዳን የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል። (ዕብ. 1:7, 14) ለምሳሌ ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ‘ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ’ ስንሰብክ መላእክት ይደግፉናል እንዲሁም ይመሩናል።—ማቴ. 24:13, 14፤ ራእይ 14:6፤ w20.11 13-14 አን. 6-7
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 24
በሰው ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ቀድቶ ያወጣዋል።—ምሳሌ 20:5
ጥናታችን የሚማረው ነገር የመነጨው በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው የአምላክ ቃል መሆኑን እንዲያውቅ እንፈልጋለን። (1 ተሰ. 2:13) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ተማሪው ስለሚማረው ነገር ምን እንደሚሰማው እንዲገልጽ አበረታታው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ሁልጊዜ አንተ ከማብራራት ይልቅ አንዳንዶቹን ጥቅሶች እሱ እንዲያብራራ ጠይቀው። ተማሪው የአምላክን ቃል በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችል እንዲያስተውል እርዳው። ጥናትህ ስላነበባቸው ጥቅሶች ያለውን አመለካከት እና ስሜት እንዲገልጽ ለማበረታታት የአመለካከት ጥያቄዎች አቅርብለት። (ሉቃስ 10:25-28) ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልትጠይቀው ትችላለህ፦ “ይህ ጥቅስ ስለ የትኛው የይሖዋ ባሕርይ አስተምሮሃል?” “ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መማርህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?” “አሁን ስለተማርከው ነገር ምን ይሰማሃል?” ቁም ነገሩ፣ ተማሪው ብዙ ነገር ማወቁ ሳይሆን የተማረውን ነገር መውደዱና ተግባራዊ ማድረጉ ነው። አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን አድርጉ። የማስተማር ችሎታህን ማሻሻል የምትፈልግ ከሆነ ትሑት መሆን ይኖርብሃል። w20.10 15 አን. 5-6
እሁድ፣ ታኅሣሥ 25
በማለዳ ዘርህን ዝራ፤ እስከ ምሽትም ድረስ እጅህ ሥራ አይፍታ።—መክ. 11:6
የመንግሥቱ የስብከት ሥራ የሚጠናቀቀው ይሖዋ ከወሰነለት ጊዜ አንዳች ሳይዘገይ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በኖኅ ዘመን የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። ይሖዋ፣ ከወሰነው ጊዜ ዝንፍ እንደማይል አሳይቷል። ይሖዋ የጥፋት ውኃው የሚጀምርበትን ጊዜ የወሰነው ከ120 ዓመት ገደማ በፊት ነበር። ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ኖኅን መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። ምናልባትም የጥፋት ውኃው ከመጀመሩ በፊት ባሉት 40 ወይም 50 ዓመታት በሙሉ ኖኅ ሥራውን በትጋት አከናውኗል። በዘመኑ የነበሩት ሰዎች መልእክቱን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆኑም ኖኅ የማስጠንቀቂያ መልእክቱን ማወጁን ቀጥሎ ነበር፤ ይሖዋ ወደ መርከቡ እንዲገባ እስኪነግረው ድረስ በዚህ ሥራ ተካፍሏል። ይሖዋ፣ ልክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ‘በሩን ዘጋው።’ (ዘፍ. 6:3፤ 7:1, 2, 16) በቅርቡ ይሖዋ የመንግሥቱ የስብከት ሥራ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል፤ በሰይጣን ሥርዓት ላይ ‘በሩን ይዘጋበታል’፤ ከዚያም ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያመጣል። እስከዚያው ድረስ ግን እንደ ኖኅ ያሉ እጃቸው ሥራ እንዲፈታ ያልፈቀዱ የአምላክ አገልጋዮችን ምሳሌ እንከተል። በሥራው ላይ ትኩረት እናድርግ፣ ታጋሾች እንሁን እንዲሁም በይሖዋና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ይኑረን። w20.09 13 አን. 18-19
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 26
ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን።—1 ቆሮ. 14:40
ማን ራስ እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባይኖር ኖሮ የይሖዋ ቤተሰብ ሥርዓትና ደስታ የሌለው ይሆን ነበር። ለምሳሌ ‘አንድን ውሳኔ የማድረግና ግንባር ቀደም ሆኖ ውሳኔውን የማስፈጸም ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ግራ መጋባት ይፈጥር ነበር። አምላክ ያቋቋመው የራስነት ሥርዓት እንዲህ ያለ ጥሩ ዝግጅት ከሆነ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሴቶች እንደተጨቆኑ የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ብዙ ወንዶች ይሖዋ ለቤተሰብ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ከመጠበቅ ይልቅ የአካባቢያቸውን ወጎችና ልማዶች ስለሚከተሉ ነው። በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስተው ሚስቶቻቸውን የሚበድሉም አሉ። ለምሳሌ አንድ ባል፣ ሌሎች ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጡት ለማድረግ ወይም ወንድነቱን ለማሳየት ሲል ሚስቱን ሊጨቁን ይችላል። ሚስቴ እንድትወደኝ ማስገደድ ባልችልም እንድትፈራኝ ማድረግ እችላለሁ ብሎ ያስብ ይሆናል። ስለዚህ እያስፈራራ እንደፈለገ ሊቆጣጠራት ይሞክራል። እንዲህ ያለው አመለካከትና ድርጊት ሴቶች የሚገባቸውን አክብሮት እንዲነፈጉ ያደርጋል፤ በተጨማሪም ይሖዋ ካሰበው ነገር ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነው።—ኤፌ. 5:25, 28፤ w21.02 3 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 27
የሚያስጨንቃችሁን . . . ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።—1 ጴጥ. 5:7
የሚያስጨንቅ ነገር ያጋጠማቸው ክርስቲያኖች ወደ ይሖዋ በመጸለይ እፎይታ ሊያገኙ ይችላሉ። ይሖዋም ‘ከሰው የመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ በመስጠት ጸሎታቸውን ይመልስላቸዋል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል ባለው ቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የተጨነቀውን ልባችንን ያረጋጋልናል። (ገላ. 5:22) ወደ ይሖዋ ስትጸልዩ የሚሰማችሁን ሁሉ ንገሩት። ችግራችሁን ለይታችሁ ጥቀሱ፤ ችግሩ የፈጠረባችሁን ስሜትም ግለጹለት። ችግሩ መፍትሔ እንዳለው ከተሰማችሁ መፍትሔውን ለማግኘት ጥበብ እንዲሰጣችሁ እንዲሁም መፍትሔውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ብርታት እንዲሰጣችሁ ለምኑት። ችግሩን መፍታት ከአቅማችሁ በላይ ከሆነ፣ ስለ ጉዳዩ ከልክ በላይ እንዳትጨነቁ እንዲረዳችሁ ይሖዋን ጠይቁት። በጸሎታችሁ ላይ የምትፈልጉትን ነገር ለይታችሁ የምትጠቅሱ ከሆነ ይሖዋ የሚሰጣችሁን መልስ ማየት ቀላል ይሆንላችኋል። ጸልያችሁ ቶሎ መልስ ሳታገኙ ብትቀሩ ተስፋ አትቁረጡ። ይሖዋ በጸሎታችሁ ላይ የምትፈልጉትን ነገር ለይታችሁ እንድትጠቅሱ ብቻ ሳይሆን ስለ ጉዳዩ ደጋግማችሁ እንድትጸልዩም ይፈልጋል።—ሉቃስ 11:8-10፤ w21.01 3 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 28
[ኢየሱስ] እንዲህ አላቸው፦ “ስጦታው ያላቸው ካልሆኑ በስተቀር ይህን ሁሉም ሰው ሊቀበለው አይችልም።”—ማቴ. 19:11
በዛሬው ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ባለትዳሮችና ቤተሰቦች አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ያላገቡ በርካታ ወንድሞችና እህቶችም ይገኛሉ። ታዲያ ላላገቡ ክርስቲያኖች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረውን አመለካከት እንመልከት። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አላገባም ነበር። ሳያገባ በመኖር ሙሉ ጊዜውንና ትኩረቱን ለአገልግሎቱ ሰጥቷል። ኢየሱስ ማግባትም ሆነ ነጠላነት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ብቃት እንደሆነ አስተምሮ አያውቅም። ሆኖም አንዳንድ ክርስቲያኖች ላለማግባት ሊመርጡ እንደሚችሉ ተናግሯል። (ለማቴዎስ 19:12 የተዘጋጀውን ለጥናት የሚረዳ መረጃ ተመልከት።) ኢየሱስ ላላገቡ የአምላክ አገልጋዮች አክብሮት ነበረው። ያላገቡ ሰዎችን ዝቅ አድርጎ አልተመለከታቸውም፤ የሚጎድላቸው ነገር እንዳለም አልተሰማውም። እንደ ኢየሱስ ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስም አገልግሎቱን ያከናወነው ነጠላ ሆኖ ነው። ጳውሎስ ክርስቲያኖች ቢያገቡ ስህተት እንደሆነ አስተምሮ አያውቅም። ይህ የግል ውሳኔ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። w20.08 28 አን. 7-8
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 29
አምላክ ፍቅር ነው።—1 ዮሐ. 4:16
ሐዋርያው ዮሐንስ ባሳለፈው ረጅም ዕድሜ ብዙ ነገር አይቷል። እምነቱን ሊያዳክሙ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውታል። ሆኖም የኢየሱስን ትእዛዛት ለመጠበቅ ምንጊዜም የቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር፤ ከእነዚህ ትእዛዛት አንዱ ደግሞ ወንድሞቹንና እህቶቹን እንዲወድ የተሰጠው ትእዛዝ ነው። ዮሐንስ እንዲህ ዓይነት ታዛዥነት ስላሳየ ይሖዋና ኢየሱስ እንደሚወዱት እንዲሁም ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጡት እርግጠኛ ነበር። (ዮሐ. 14:15-17፤ 15:10) ሰይጣንም ሆነ እሱ ያዋቀረው ሥርዓት ዮሐንስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ፍቅር እንዳይኖረው እንዲሁም ፍቅሩን በቃልም ሆነ በተግባር እንዳይገልጽ አላገዱትም። እንደ ዮሐንስ ሁሉ እኛም የምንኖረው በጥላቻ የተሞላው ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ነው። (1 ዮሐ. 3:1, 10) ሰይጣን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር እንዲጠፋ ለማድረግ ይጥራል፤ ሆኖም እኛ እስካልፈቀድንለት ድረስ ይህ ሊሳካለት አይችልም። እንግዲያው ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመውደድ እንዲሁም ፍቅራችንን በአንደበትም ሆነ በተግባር ለመግለጽ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን የይሖዋ ቤተሰብ ክፍል መሆን የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን፤ ይህ ደግሞ ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል።—1 ዮሐ. 4:7፤ w21.01 13 አን. 18-19
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 30
ጽናትን . . . የሚሰጠው አምላክ [ነው]።—ሮም 15:5
በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥ ሕይወት ከባድ ሊሆንብን ይችላል፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑብን ሊሰማን ይችላል። (2 ጢሞ. 3:1) ሆኖም መጨነቅ ወይም መፍራት አይኖርብንም። ይሖዋ ያለንበትን ሁኔታ በደንብ ያውቃል። በምንወድቅበት ጊዜ፣ ኃያል በሆነው ቀኝ እጁ አጥብቆ እንደሚይዘን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳ. 41:10, 13) እንግዲያው ይሖዋ እንደሚደግፈን ሙሉ በሙሉ በመተማመን ከቅዱሳን መጻሕፍት ብርታት ማግኘትና የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና መወጣት እንችላለን። በድርጅታችን የተዘጋጁ ቪዲዮዎችና ድራማዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች እንዲሁም “በእምነታቸው ምሰሏቸው” የተባለው ዓምድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ሕያው እንዲሆኑልን ይረዱናል። እነዚህን ታሪኮች መመልከት፣ ማዳመጥ ወይም ማንበብ ከመጀመርህ በፊት አንተን የሚጠቅሙ ነጥቦችን ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ራስህን በዋናው ባለታሪክ ቦታ በማስቀመጥ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። እነዚህ ውድ የአምላክ አገልጋዮች ምን እርምጃ እንደወሰዱ እንዲሁም ይሖዋ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲቋቋሙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ አሰላስል። ከዚያም ያገኘኸውን ትምህርት ከአንተ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተግባር አውለው። ይሖዋን ላደረገልህ እርዳታ አመስግነው። በተጨማሪም ሌሎችን ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በመፈለግ ይሖዋ ላደረገልህ እርዳታ ያለህን አድናቆት አሳይ። w21.03 19 አን. 22-23
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 31
ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው።—መዝ. 127:3
ባለትዳሮች ከሆናችሁና ልጅ መውለድ የምትፈልጉ ከሆነ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ይሖዋ ውድ የሆነን ሕይወት በኃላፊነት ሊሰጠን የሚችል ትሑትና መንፈሳዊ አመለካከት ያለን ሰዎች ነን?’ (መዝ. 127:4) ወላጆች ከሆናችሁ ደግሞ ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁ፦ ‘ጠንክሮ የመሥራትን አስፈላጊነት ለልጆቼ እያስተማርኩ ነው?’ (መክ. 3:12, 13) ‘ልጆቼን ሊያጋጥማቸው ከሚችለው አካላዊና ሥነ ምግባራዊ አደጋ ለመጠበቅ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ?’ (ምሳሌ 22:3) ልጆቻችሁ ምንም ተፈታታኝ ሁኔታ እንዳያጋጥማቸው ልትከልሏቸው አትችሉም። ሆኖም ከአምላክ ቃል ምክር ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በማስተማር በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች ቀስ በቀስ ልታዘጋጇቸው ትችላላችሁ። (ምሳሌ 2:1-6) ለምሳሌ ያህል፣ የቅርብ ዘመዳችሁ ይሖዋን ማገልገሉን ቢያቆም የአምላክን ቃል ተጠቅማችሁ ለይሖዋ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት ለልጆቻችሁ አስተምሯቸው። (መዝ. 31:23) አሊያም ደግሞ የምትወዱትን ሰው በሞት ካጣችሁ ልጆቻችሁ የአምላክ ቃል ሐዘንን ለመቋቋምና ሰላም ለማግኘት የሚረዳው እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ እርዷቸው።—2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 2 ጢሞ. 3:16፤ w20.10 27 አን. 7