ኅዳር
ማክሰኞ፣ ኅዳር 1
እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።—ምሳሌ 18:13
ዮናስ ስለነበረበት ሁኔታ ካለን ውስን እውቀት የተነሳ፣ እምነት የማይጣልበት አልፎ ተርፎም ታዛዥ ያልሆነ ሰው ነው ብለን እንፈርድበት ይሆናል። ዮናስን ወደ ነነዌ ሄዶ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ያዘዘው ይሖዋ ራሱ ነው። ዮናስ ግን ይሖዋን ከመታዘዝ ይልቅ መርከብ ተሳፍሮ በተቃራኒ አቅጣጫ ‘ከይሖዋ ፊት ሸሸ።’ (ዮናስ 1:1-3) እናንተ ብትሆኑ ኖሮ ዮናስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሌላ አጋጣሚ ትሰጡት ነበር? አትሰጡት ይሆናል። ይሖዋ ግን ዮናስ ሌላ አጋጣሚ ቢያገኝ የተሻለ እንደሆነ ተሰምቶታል። (ዮናስ 3:1, 2) ዮናስ በአንድ ወቅት ያቀረበው ጸሎት ስለ እሱ ትክክለኛ ማንነት ፍንጭ ይሰጠናል። (ዮናስ 2:1, 2, 9) ዮናስ ብዙ ጸሎቶች አቅርቦ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም በዚህ ወቅት ያቀረበው ጸሎት፣ የተሰጠውን ተልእኮ ትቶ እንደሸሸ ሰው ብቻ አድርገን እንዳንመለከተው ይረዳናል። ዮናስ የተጠቀመባቸው ቃላት ትሑት፣ አመስጋኝ እና ይሖዋን ለመታዘዝ የቆረጠ ሰው እንደነበረ ያሳያሉ። ከዚህ አንጻር ይሖዋ፣ ዮናስ በሠራቸው ስህተቶች ላይ አለማተኮሩ፣ ለጸሎቱ መልስ መስጠቱና እሱን ነቢይ አድርጎ መጠቀሙን መቀጠሉ ምንም አያስገርምም! በእርግጥም ሁሉም ሽማግሌዎች ‘እውነታውን ከመስማታቸው’ በፊት ምክር አለመስጠታቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው! w20.04 15 አን. 4-6
ረቡዕ፣ ኅዳር 2
[ጳውሎስ] ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነሱ ጋር ተወያየ፤ . . . ማስረጃ እየጠቀሰ በማብራራትና በማስረዳት።—ሥራ 17:2, 3
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የክርስትና ትምህርቶችን የተቀበሉ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የአምላክን ቃል ለመረዳት ይጥሩ ነበር። እነዚህ ትምህርቶች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ለራሳቸው አረጋግጠዋል። (ሥራ 17:11, 12፤ ዕብ. 5:14) እምነታቸው የተመሠረተው በስሜት ላይ ብቻ አልነበረም፤ እንዲሁም ይሖዋን የሚያገለግሉት ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር መሆን ስለሚያስደስታቸው ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እምነታቸው የተገነባው ስለ አምላክ ባገኙት “ትክክለኛ እውቀት” ላይ ነበር። (ቆላ. 1:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አይለዋወጥም። (መዝ. 119:160) ለምሳሌ አንድ የእምነት ባልንጀራችን ቢያስቀይመን ወይም ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም እውነት አይቀየርም። ችግር ቢደርስብንም እውነት አይቀየርም። ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በሚገባ መተዋወቅ እንዲሁም እውነት መሆናቸውን እርግጠኛ መሆን ያስፈልገናል። መልሕቅ በማዕበል ወቅት አንድን መርከብ እንዳይናወጥ እንደሚያደርገው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ላይ ያለን ጠንካራ እምነትም በፈተና ወቅት ያጸናናል። w20.07 9 አን. 6-7
ሐሙስ፣ ኅዳር 3
ለሰዎች እንድንሰብክና በተሟላ ሁኔታ እንድንመሠክር አዘዘን።—ሥራ 10:42
ኢየሱስ፣ ለቅቡዓን ወንድሞቹ የምናደርገውን ነገር ለእሱ እንዳደረግነው አድርጎ ይቆጥረዋል። (ማቴ. 25:34-40) ቅቡዓኑን መደገፍ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ፣ ኢየሱስ ለተከታዮቹ በሰጠው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) የክርስቶስ ወንድሞች በዛሬው ጊዜ እየተከናወነ ያለውን ታላቅ ዓለም አቀፍ የስብከት ዘመቻ ዳር ማድረስ የሚችሉት “ሌሎች በጎች” በሚያደርጉላቸው እርዳታ ብቻ ነው። (ዮሐ. 10:16) አንተም የሌሎች በጎች አባል ከሆንክ፣ በዚህ ሥራ በተካፈልክ ቁጥር ለቅቡዓኑ ብቻ ሳይሆን ለኢየሱስም ያለህን ፍቅር እያሳየህ ነው። የይሖዋና የኢየሱስ ወዳጆች መሆናችንን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ እነሱ የሚመሩትን ሥራ በገንዘብ መደገፍ ነው። (ሉቃስ 16:9) ለምሳሌ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ እንችላለን፤ የሚዋጣው ገንዘብ አደጋ ለደረሰባቸው ክርስቲያኖች ቁሳዊ እርዳታ ለመስጠት ይውላል። በተጨማሪም ለጉባኤያችን ወጪዎች የገንዘብ መዋጮ ማድረግና ችግር እንደገጠማቸው የምናውቃቸውን ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ መርዳት እንችላለን።—ምሳሌ 19:17፤ w20.04 24 አን. 12-13
ዓርብ፣ ኅዳር 4
ለአባቶቹ አምላክ ምንም ቦታ አይሰጥም፤ . . . ይልቁንም ለምሽጎች አምላክ ክብር ይሰጣል።—ዳን. 11:37, 38
ልክ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው የሰሜኑ ንጉሥ “ለአባቶቹ አምላክ” ምንም ቦታ አልሰጠም። ይህን ያሳየው እንዴት ነው? የሶቪየት ኅብረት መንግሥት፣ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ለማዳከም ጥረት አድርጓል፤ ዓላማውም ሃይማኖትን ማጥፋት ነበር። የሶቪየት መንግሥት ይህን ግቡን ለማሳካት ሲል ገና በ1918 ትምህርት ቤቶችንና ሃይማኖትን የሚመለከት ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ ይህም ‘አምላክ የለም’ የሚለው ትምህርት ከጊዜ በኋላ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጥ መንገድ ከፍቷል። ታዲያ ይህ የሰሜን ንጉሥ ‘ለምሽጎች አምላክ ክብር የሰጠው’ እንዴት ነው? የሶቪየት ኅብረት መንግሥት፣ ሠራዊቱን ለመገንባትና ግዛቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የኑክሌር መሣሪያዎችን ለማምረት ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል። የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ የደቡቡ ንጉሥ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚጨርሱ የጦር መሣሪያዎችን ቀስ በቀስ አከማችተዋል። የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ የተባበሩበት አንድ ቁልፍ ጉዳይ አለ፤ ይህም ‘ጥፋት የሚያመጣውን ርኩስ ነገር’ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ማቋቋም ነው።—ዳን. 11:31፤ w20.05 6-7 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ኅዳር 5
ይህ ወንድምህ . . . ጠፍቶ ነበር፤ ተገኝቷል።—ሉቃስ 15:32
የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን በመፈለጉ ሥራ ማን መካፈል ይችላል? ሽማግሌዎች፣ አቅኚዎች፣ የቤተሰባቸው አባላት እንዲሁም የጉባኤ አስፋፊዎች በሌላ አባባል ሁላችንም እነዚህን ሰዎች በመፈለጉ ሥራ እርዳታ ማበርከት እንችላለን። የቀዘቀዘ ጓደኛ ወይም ዘመድ አለህ? ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ወይም በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ስትካፈል የቀዘቀዘ ሰው አግኝተሃል? ግለሰቡ፣ ሽማግሌዎች መጥተው እንዲያነጋግሩት የሚፈልግ ከሆነ አድራሻውን በአካባቢው ላሉት የጉባኤ ሽማግሌዎች ልትሰጣቸው እንደምትችል ንገረው። ቶማስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በመጀመሪያ፣ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች የሚኖሩበትን ቦታ ያውቁ እንደሆነ የተለያዩ ወንድሞችንና እህቶችን እጠይቃለሁ። አሊያም ደግሞ ወደ ስብሰባዎች መምጣት ያቆመ የሚያውቁት ሰው ካለ እጠይቃቸዋለሁ። የቀዘቀዙ ወንድሞችንና እህቶችን በምጎበኝበት ጊዜ ደግሞ ስለ ልጆቻቸውና ስለ ዘመዶቻቸው እጠይቃቸዋለሁ። አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ስብሰባ ይመጡ ነበር፤ ምናልባትም በአንድ ወቅት ልጆቻቸው አስፋፊዎች ነበሩ። በመሆኑም እነሱም ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።” w20.06 24 አን. 1፤ 25 አን. 6-7
እሁድ፣ ኅዳር 6
ያህ ያከናወናቸውን ሥራዎች አስታውሳለሁ፤ ጥንት የፈጸምካቸውን ድንቅ ተግባሮች አስታውሳለሁ።—መዝ. 77:11
በምድር ላይ ከሚገኙት ፍጥረታት መካከል፣ ቀደም ሲል ያጋጠማቸውን ነገር አስታውሰው ከሁኔታው የሥነ ምግባር ትምህርት የመቅሰም ችሎታ ያላቸው የሰው ልጆች ብቻ ናቸው። የተሻሉ መሥፈርቶችን መከተል ብሎም በአስተሳሰባችንና በአኗኗራችን ላይ ለውጥ ማድረግ የምንችለው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 6:9-11፤ ቆላ. 3:9, 10) እንዲያውም ሕሊናችንን፣ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር እንዲለይ ማሠልጠን እንችላለን። (ዕብ. 5:14) ፍቅርን፣ ርኅራኄንና ምሕረትን ማሳየትን መማር እንችላለን። በተጨማሪም ተገቢ የሆነ የፍትሕ ስሜት ማዳበር እንችላለን። ስጦታ ለሆነው የማስታወስ ችሎታችን አድናቆት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ ይሖዋ እኛን ለመርዳትና ለማጽናናት ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ ለማስታወስ ጥረት ማድረግ ነው። ይህን ማድረጋችን ይሖዋ ወደፊትም እንደሚረዳን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። (መዝ. 77:12፤ 78:4, 7) አድናቆታችንን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ ሌሎች ሰዎች ያደረጉልንን መልካም ነገር አስታውሰን አመስጋኝነታችንን መግለጽ ነው። አመስጋኝ የሆኑ ሰዎች በሕይወታቸው ይበልጥ ደስተኛ እንደሚሆኑ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። w20.05 23 አን. 12-13
ሰኞ፣ ኅዳር 7
ክብራማና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህን የይሖዋን ስም [ፍራ]።—ዘዳ. 28:58
ሙሴ በዓለት ዋሻ ውስጥ ሆኖ፣ የይሖዋን ክብር የማየት አጋጣሚ አግኝቶ ነበር፤ ሙሴ በዚህ ወቅት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስበው። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ስለዚህ ክንውን ሲናገር “ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የትኛውም የሰው ልጅ ከገጠመው አስደናቂ ነገር ሁሉ በላይ እጅግ የሚያስደምም ክስተት ሳይሆን አይቀርም” ይላል። ሙሴ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል” ተብሎ ሲታወጅ ሰምቷል፤ ይህን ሐሳብ የተናገረው አንድ መልአክ ሊሆን ይችላል። (ዘፀ. 33:17-23፤ 34:5-7) ሙሴ፣ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ይሖዋ የሚለውን ስም ሲጠቀም ይህ ክስተት ወደ አእምሮው ሳይመጣ አይቀርም። ይሖዋ ስለሚለው ስም ስናስብ ስለ ስሙ ባለቤት ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። እንደ ኃይል፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር ስላሉት ባሕርያቱ ልናስብ ይገባል። በእነዚህና በሌሎች ባሕርያቱ ላይ ማሰላሰላችን ለእሱ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን ያደርጋል።—መዝ. 77:11-15፤ w20.06 8-9 አን. 3-4
ማክሰኞ፣ ኅዳር 8
በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር።—2 ጢሞ. 3:14
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። (ዮሐ. 13:34, 35) ይሁንና ጠንካራ እምነት ማዳበር ከፈለግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም። እምነታችን የአምላክ ሕዝቦች በሚያሳዩት ክርስቲያናዊ ፍቅር ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ለምን? ለምሳሌ አንድ የእምነት ባልንጀራችን፣ ምናልባትም አንድ ሽማግሌ ወይም አቅኚ ከባድ ኃጢአት ቢሠራስ? አሊያም አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት በሆነ መንገድ ቢጎዱህስ? ወይም ደግሞ አንድ ሰው ከሃዲ ሆኖ እምነታችን እውነት እንዳልሆነ ቢናገርስ? እንዲህ ዓይነት ነገር ቢያጋጥምህ ተሰናክለህ ይሖዋን ማገልገልህን ታቆማለህ? ነጥቡ ይህ ነው፦ በአምላክ ላይ ያለህ እምነት የተመሠረተው ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ሳይሆን ሌሎች ሰዎች በሚያደርጉት ነገር ላይ ብቻ ከሆነ እምነትህ ጠንካራ አይሆንም። እምነትህን ለመገንባት እንደ ስሜት ያለ ደካማ ጥሬ ዕቃ ብቻ ሳይሆን እንደ እውቀትና አሳማኝ ማስረጃ ያሉ ጠንካራ ጥሬ ዕቃዎችንም መጠቀም ይኖርብሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ እውነቱን እንደሚያስተምረን ለራስህ ማረጋገጥ አለብህ።—ሮም 12:2፤ w20.07 8 አን. 2-3
ረቡዕ፣ ኅዳር 9
ደካማ የሆኑትን [እርዱ]።—ሥራ 20:35
ብዙ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ የቀዘቀዙ ሰዎችን ማግኘት እንድንችል መላእክት ይረዱናል። (ራእይ 14:6) በኢኳዶር የሚኖረውን የሲልቭዮን ምሳሌ እንመልከት፤ ሲልቭዮ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ መመለስ እንዲችል አጥብቆ ጸልዮ ነበር። ሲልቭዮ እየጸለየ ሳለ የበሩ ደወል ተደወለ። በሩ ላይ ሁለት የጉባኤ ሽማግሌዎች ቆመው ነበር። እነዚህ ሽማግሌዎች ሲልቭዮ የሚያስፈልገውን እርዳታ ወዲያውኑ መስጠት ጀመሩ። በመንፈሳዊ የደከሙ ሰዎችን ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ስንረዳ ታላቅ ደስታ እናገኛለን። ለቀዘቀዙ ሰዎች ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሳልቫዶር የተባለ አቅኚ የተናገረውን ልብ በል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከደስታዬ የተነሳ እንባዬን መቆጣጠር ያቅተኛል። ይሖዋ ውድ ከሆኑት በጎቹ አንዱን ከሰይጣን ዓለም እንደታደገውና እኔም በዚህ ሥራ ከእሱ ጋር የመተባበር መብት እንዳገኘሁ ሳስብ በጣም እደሰታለሁ።” አንተም ከይሖዋ ሕዝቦች ርቀህ ከሆነ ይሖዋ አሁንም እንደሚወድህ እርግጠኛ ሁን። ይሖዋ የምትመለስበትን ጊዜ እየተጠባበቀ ነው፤ ወደ ቤቱ ስትመለስም እጁን ዘርግቶ በደስታ ይቀበልሃል። w20.06 29 አን. 16-18
ሐሙስ፣ ኅዳር 10
ታላቁን አስተማሪህን ታያለህ።—ኢሳ. 30:20
‘ታላቁ አስተማሪያችን’ የሆነው ይሖዋ እኛን ለማስተማር ሲል የተለያዩ ሰዎች ታሪክ በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል። (ኢሳ. 30:21) አምላክ የሚደሰትባቸው ባሕርያትን ያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች በተዉት ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እንዲህ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ያላሳዩ ሰዎች ምን እንዳጋጠማቸው በመመልከትም የምናገኘው ትምህርት አለ። (መዝ. 37:37፤ 1 ቆሮ. 10:11) ንጉሥ ሳኦል ስላጋጠመው ነገር እናስብ። ሳኦል ወጣት እያለ ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ከቦታው አልፎ የሚሄድ ሰው አልነበረም፤ ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠው እንኳ ለመቀበል አመንትቶ ነበር። (1 ሳሙ. 9:21፤ 10:20-22) ከጊዜ በኋላ ግን ሳኦል ከቦታው አልፎ መሄድ ጀመረ። ይህ መጥፎ ባሕርይ መታየት የጀመረው ንጉሥ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ነው። በአንድ ወቅት ሳኦል፣ ነቢዩ ሳሙኤልን በትዕግሥት መጠበቅ ስላቃተው የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያልተፈቀደለትን ነገር አደረገ። በዚህም ምክንያት የይሖዋን ሞገስ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ንግሥናውን አጣ። (1 ሳሙ. 13:8-14) እኛም ከዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት በመውሰድ ከቦታችን አልፈን ላለመሄድ መጠንቀቃችን የጥበብ እርምጃ ነው። w20.08 10 አን. 10-11
ዓርብ፣ ኅዳር 11
በጌታ ሥራ አመራር እየሰጧችሁ ያሉትን [አክብሯቸው]።—1 ተሰ. 5:12
ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት ወንዶችን “ስጦታ” አድርጎ ለጉባኤው ሰጥቷል። (ኤፌ. 4:8) “ስጦታ” የሆኑ ወንዶች ከተባሉት መካከል የበላይ አካል አባላት፣ የበላይ አካሉ ረዳቶች፣ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ የመስክ አስተማሪዎች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ይገኙበታል። እነዚህ ወንድሞች በሙሉ የይሖዋን ውድ በጎች እንዲንከባከቡና ጉባኤውን እንዲያገለግሉ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ወንድሞች በመንፈስ ቅዱስ የሚሾሙት የተለያዩ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ነው። የተለያዩ የአካል ክፍሎች ለምሳሌ እጅና እግር፣ መላውን አካል የሚጠቅም ሥራ እንደሚያከናውኑ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ወንድሞችም መላውን ጉባኤ የሚጠቅም ሥራ በትጋት ያከናውናሉ። እነዚህ ወንድሞች ለራሳቸው ክብር ለማግኘት አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለማነጽና ለማጠናከር ተግተው ይሠራሉ። (1 ተሰ. 2:6-8) ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የሚያሳዩና መንፈሳዊ የሆኑ እንዲህ ያሉ ወንድሞች ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን! w20.08 21 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ ኅዳር 12
ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19
እንድንሰብክ የሚያነሳሳን አንዱ ምክንያት ሰዎች “ተገፈውና ተጥለው” ማየታችን ነው። እነዚህ ሰዎች ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን እውነት ማወቅ በጣም ያስፈልጋቸዋል። (ማቴ. 9:36) ይሖዋ፣ ሁሉም ዓይነት ሰዎች የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙና እንዲድኑ ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:4) የስብከቱ ሥራችን ሊያስገኝ የሚችለውን ውጤት ስናስብ በዚህ ሕይወት አድን ሥራ ለመካፈል ይበልጥ እንነሳሳለን። የምንሠራው ሥራ የሰዎችን ሕይወት ያድናል። (ሮም 10:13-15፤ 1 ጢሞ. 4:16) ነገር ግን ለሥራችን የሚያስፈልጉት መሣሪያዎች ሊኖሩን ይገባል። መሣሪያዎቹን እንዴት እንደምንጠቀም ማወቅም ይኖርብናል። ኢየሱስ፣ ሰዎችን እንዴት ማጥመድ እንደሚቻል ለደቀ መዛሙርቱ ግልጽ መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል። ምን መያዝ፣ የት መስበክና ምን ማለት እንዳለባቸው ነግሯቸዋል። (ማቴ. 10:5-7፤ ሉቃስ 10:1-11) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት በሥራችን ውጤታማ እንድንሆን ለመርዳት ሲል የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችንን አዘጋጅቶልናል። በተጨማሪም እነዚህን መሣሪያዎች እንዴት እንደምንጠቀም እንማራለን። ይህ ሥልጠና ልበ ሙሉ እንድንሆንና ክህሎታችንን እንድናሻሽል ስለሚረዳን በሥራችን ውጤታማ ለመሆን ያስችለናል።—2 ጢሞ. 2:15፤ w20.09 4 አን. 6-7, 10
እሁድ፣ ኅዳር 13
ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።—3 ዮሐ. 4
ሐዋርያው ዮሐንስ እውነትን እንዲማሩ የረዳቸው ሰዎች ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ እንደሆነ ሲሰማ ምን ያህል ተደስቶ እንደሚሆን አስቡት! እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ብዙ ችግር አጋጥሟቸዋል፤ ዮሐንስም የመንፈሳዊ ልጆቹን እምነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት ያደርግ ነበር። እኛም በተመሳሳይ ልጆቻችንም ሆኑ ጥናቶቻችን ራሳቸውን ለይሖዋ ሲወስኑና እሱን በጽናት ሲያገለግሉ በእጅጉ እንደሰታለን። (3 ዮሐ. 3) በ98 ዓ.ም. አካባቢ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ዮሐንስን ሦስት ደብዳቤዎች እንዲጽፍ አነሳሳው። የእነዚህ ደብዳቤዎች ዓላማ ታማኝ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩና በእውነት ውስጥ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታታት ነበር። ዮሐንስ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በጉባኤዎቹ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ አሳስቦት ነበር። (1 ዮሐ. 2:18, 19, 26) እነዚህ ከሃዲዎች አምላክን እንደሚያውቁ ቢናገሩም የይሖዋን ትእዛዛት አያከብሩም ነበር። w20.07 20 አን. 1-3
ሰኞ፣ ኅዳር 14
በአምላክ እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ።—ዮሐ. 14:1
በምንሰብከው መልእክት ላይ እምነት ስላለን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ይህን መልእክት ለመስበክ እንጓጓለን። ምክንያቱም በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት ተስፋዎች ላይ እምነት አለን። (መዝ. 119:42፤ ኢሳ. 40:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት ትንቢቶች በዘመናችን ሲፈጸሙ ተመልክተናል። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምሩ ሕይወታቸው ምን ያህል እንደተሻሻለም አይተናል። እነዚህ ነገሮች፣ የመንግሥቱ ምሥራች ሁሉም ሰው ሊሰማው የሚገባ መልእክት እንደሆነ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። የመልእክታችን ባለቤት በሆነው በይሖዋ ላይም እምነት አለን፤ ይሖዋ የመንግሥቱ ንጉሥ አድርጎ በሾመው በኢየሱስም እናምናለን። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ይሖዋ ምንጊዜም “መጠጊያችንና ብርታታችን” ነው። (መዝ. 46:1-3) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ይሖዋ የሰጠውን ኃይልና ሥልጣን ተጠቅሞ የስብከቱን ሥራ ከሰማይ እየመራ እንዳለ እርግጠኞች ነን። (ማቴ. 28:18-20) እምነት፣ ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል። w20.09 12 አን. 15-17
ማክሰኞ፣ ኅዳር 15
እሷ ለእኔ መልካም ነገር አድርጋለች። . . . እሷ የምትችለውን አድርጋለች።—ማር. 14:6, 8
እህቶች በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ኢሳ. 1:17) ለምሳሌ ያህል፣ መበለት የሆነች ወይም ከባሏ የተፋታች አንዲት እህት ባሏ ያከናውናቸው የነበሩ አንዳንድ ሥራዎችን ስታከናውን የሚያግዛት ሰው ሊያስፈልጋት ይችላል። በዕድሜ የገፉ አንዲት እህት የሕክምና ባለሙያዎችን ሲያነጋግሩ የሚያግዛቸው ሰው ያስፈልጋቸው ይሆናል። አሊያም ደግሞ በሌሎች ቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ላይ የምትካፈል አቅኚ እህት የሌሎች አቅኚዎችን ያህል አዘውትራ አገልግሎት ባለመውጣቷ አንዳንዶች ቢተቿት የሚሟገትላት ሰው ያስፈልጋታል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ፣ መንፈሳዊ እህቶቹን ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዷቸው ወዲያውኑ ጥብቅና ይቆምላቸው ነበር። ለምሳሌ፣ ማርታ ማርያምን በወቀሰቻት ወቅት ለማርያም ጥብቅና ቆሞላታል። (ሉቃስ 10:38-42) በሌላ ጊዜም አንዳንዶች ማርያም የወሰደችው እርምጃ ስህተት እንደሆነ በማሰብ በወቀሷት ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ ለማርያም ተሟግቶላታል። (ማር. 14:3-9) ኢየሱስ፣ ማርያም ያንን እርምጃ እንድትወስድ ያነሳሳት ምን እንደሆነ ተረድቶ ስለነበር አመስግኗታል። እንዲያውም “በመላው ዓለም ምሥራቹ በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ” ማርያም ያደረገችው መልካም ተግባር እንደሚነገርላት ትንቢት ተናግሯል። w20.09 24 አን. 15-16
ረቡዕ፣ ኅዳር 16
የበላይ ተመልካቾች ሆናችሁ በማገልገል በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኛ ጠብቁ፤ ሥራችሁን በግዴታ ሳይሆን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት ተወጡ።—1 ጴጥ. 5:2
ጥሩ እረኛ፣ አንድ በግ ከመንጋው ተለይቶ ሊጠፋ እንደሚችል ይገነዘባል። ከመንጋው መካከል አንዱ በግ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመው እረኛው ርኅራኄ በጎደለው መንገድ አይዘውም። ይሖዋ ለተወሰነ ጊዜ ከእሱ ርቀው የነበሩ አንዳንድ አገልጋዮቹን ከረዳበት መንገድ ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት። ነቢዩ ዮናስ የተሰጠውን ኃላፊነት መቀበል ስላልፈለገ ሸሽቶ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ በዮናስ ቶሎ ተስፋ አልቆረጠም። ይሖዋ ልክ እንደ አንድ ጥሩ እረኛ ዮናስን የታደገው ሲሆን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ጥንካሬ እንዲያገኝ ረድቶታል። (ዮናስ 2:7፤ 3:1, 2) በኋላ ላይም አምላክ የቅል ተክልን በመጠቀም፣ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ዮናስን አስተምሮታል። (ዮናስ 4:10, 11) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ሽማግሌዎች በቀዘቀዙ አስፋፊዎች ቶሎ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ በጉ ከመንጋው እንዲባዝን ያደረገው ምን እንደሆነ ለመረዳት ይጥራሉ። በጉ ወደ ይሖዋ ሲመለስ ደግሞ ሽማግሌዎቹ እሱን በፍቅር መንከባከባቸውን ይቀጥላሉ። w20.06 20-21 አን. 10-12
ሐሙስ፣ ኅዳር 17
መጠነኛ እርዳታ ያገኛሉ።—ዳን. 11:34
ሶቪየት ኅብረት በ1991 ከፈራረሰ በኋላ ሰፊ በሆነው ግዛቱ የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች “መጠነኛ እርዳታ” ማለትም ለተወሰነ ጊዜ ነፃነት አግኝተው ነበር። በመሆኑም በነፃነት መስበክ ችለው ነበር፤ በሶቪየት ኅብረት ሥር በነበሩት አገሮች ውስጥ የአስፋፊዎች ቁጥር ብዙም ሳይቆይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሆነ። ሆኖም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሩሲያ እና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ ሆነው ብቅ አሉ። አንድ መንግሥት የሰሜኑ ንጉሥ ወይም የደቡቡ ንጉሥ እንዲባል የሚከተሉትን ሦስት መሥፈርቶች ማሟላት አለበት፦ (1) ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል፤ (2) ድርጊቱ፣ ይሖዋንና ሕዝቦቹን እንደሚጠላ ሊያሳይ ይገባል፤ (3) ከተቀናቃኙ ንጉሥ ጋር መፎካከር አለበት። ሩሲያና አጋሮቿ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፤ በስብከቱ ሥራ ላይ እገዳ ጥለዋል፤ እንዲሁም በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ላይ ስደት እያደረሱ ነው። እንዲህ ማድረጋቸው ይሖዋን እና ሕዝቡን እንደሚጠሉ ያሳያል። በተጨማሪም የደቡቡ ንጉሥ ከሆነው ከአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ጋር እየተፎካከሩ ነው። w20.05 12-13 አን. 3-4
ዓርብ፣ ኅዳር 18
ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16
ማስተማር ደቀ መዛሙርት ከማድረግ ጋር የተያያዘ ሥራ ስለሆነ ጥሩ አስተማሪዎች መሆን እንፈልጋለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እያስጠናን ነው። ከአምላክ ቃል የምናስተምረውን ነገር እንወደዋለን። በመሆኑም ስለምንወደው ነገር ብዙ ለማውራት እንፈተን ይሆናል። ይሁንና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት፣ በጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ሆነ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ጥናቱን የሚመራው ሰው ብዙ ማውራት የለበትም። አስተማሪው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን፣ ጥናቱን የሚመራው ክርስቲያን ራሱን መግዛት ይኖርበታል፤ ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም ርዕሰ ጉዳይ የሚያውቀውን ነገር ሁሉ ላለማብራራት መጠንቀቅ አለበት። (ዮሐ. 16:12) እኛ ራሳችን በተጠመቅንበት ወቅት የነበረንን እውቀት አሁን ካለን እውቀት ጋር ማወዳደር እንችላለን። በዚያ ወቅት የምናውቀው፣ መሠረታዊ የሆኑትን ትምህርቶች ብቻ ሊሆን ይችላል። (ዕብ. 6:1) ዛሬ ያለንን እውቀት ያካበትነው ለዓመታት ስንማር ከቆየን በኋላ ነው፤ እንግዲያው ለአዲሱ ተማሪያችን ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማሳወቅ መሞከር የለብንም። w20.10 14-15 አን. 2-4
ቅዳሜ፣ ኅዳር 19
ይህ አናጺው የማርያም ልጅ [ነው]።—ማር. 6:3
ይሖዋ ለኢየሱስ በጣም ጥሩ ወላጆች መርጦለታል። (ማቴ. 1:18-23፤ ሉቃስ 1:26-38) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ማርያም ከልብ በመነጨ ስሜት የተናገረቻቸው ሐሳቦች ለይሖዋና ለቃሉ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ያሳያሉ። (ሉቃስ 1:46-55) ዮሴፍም ቢሆን ለይሖዋ መመሪያ የሰጠው ምላሽ አምላክን እንደሚፈራና እሱን ማስደሰት እንደሚፈልግ ይጠቁማል። (ማቴ. 1:24) ይሖዋ ለኢየሱስ ሀብታም ወላጆችን እንዳልመረጠለት ልብ በሉ። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ያቀረቡት መሥዋዕት ድሆች እንደነበሩ ይጠቁማል። (ሉቃስ 2:24) ዮሴፍና ማርያም ቢያንስ ሰባት ልጆች የነበሯቸው ከመሆኑ አንጻር ቤተሰቡ በቁሳዊ ያን ያህል እንዳልነበረው መገመት ይቻላል። (ማቴ. 13:55, 56) ይሖዋ ኢየሱስን ከአንዳንድ አደጋዎች የጠበቀው ቢሆንም ምንም ዓይነት ችግር እንዳያጋጥመው አልተከላከለለትም። (ማቴ. 2:13-15) ለምሳሌ ያህል፣ ከኢየሱስ ዘመዶች መካከል አንዳንዶቹ በእሱ ስለማያምኑ መጀመሪያ ላይ የእሱን መሲሕነት አልተቀበሉም ነበር። (ማር. 3:21፤ ዮሐ. 7:5) በተጨማሪም ኢየሱስ የአሳዳጊ አባቱ የዮሴፍ ሞት ያስከተለበትን ሐዘን መቋቋም ሳያስፈልገው አልቀረም። w20.10 26-27 አን. 4-6
እሁድ፣ ኅዳር 20
ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም።—ዕብ. 13:5
ብቻህን እንደሆንክና በችግርህ ከጎንህ የሚቆም እንደሌለ ተሰምቶህ ያውቃል? የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችን ጨምሮ ብዙዎች እንደዚያ ተሰምቷቸው ያውቃል። (1 ነገ. 19:14) እንዲህ ከተሰማህ ይሖዋ “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት የገባውን ቃል አስታውስ። እንግዲያው “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም” ብለን በሙሉ ልብ መናገር እንችላለን። (ዕብ. 13:5, 6) ይህ ሐሳብ ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳ ላሉ የእምነት ባልንጀሮቹ በ61 ዓ.ም. ከጻፈው ደብዳቤ ላይ የተወሰደ ነው። ጥቅሱ በመዝሙር 118:5-7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ያስታውሰናል። እንደ መዝሙራዊው ሁሉ ጳውሎስም ይሖዋ ረዳቱ እንደሆነ በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። ለምሳሌ ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ከመጻፉ ከሁለት ዓመት በፊት፣ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ አደገኛ ጉዞ አድርጎ ነበር። (ሥራ 27:4, 15, 20) ይህን ጉዞ ከመጀመሩ በፊት ባለው ጊዜም ሆነ በጉዞው ወቅት ይሖዋ ጳውሎስን ለመርዳት በተለያዩ መንገዶች ተጠቅሟል። w20.11 12 አን. 1-2
ሰኞ፣ ኅዳር 21
“የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?” አትበል።—መክ. 7:10
የቀድሞው ሕይወታችን የተሻለ እንደሆነ እያሰብን መብሰልሰል ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው? በትዝታ የምንኖር ከሆነ የምናስታውሰው በቀድሞው ሕይወታችን የገጠሙንን ጥሩ ነገሮች ብቻ ይሆናል። የጥንቶቹን እስራኤላውያን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ከግብፅ ከወጡ በኋላ፣ በዚያ ያሳለፉት ሕይወት ምን ያህል በመከራ የተሞላ እንደነበረ ወዲያውኑ ረሱ። እስራኤላውያኑ ያስታወሱት በዚያ ሳሉ ይበሉት የነበረውን ጥሩ ምግብ ነበር። እንዲህ ብለው ነበር፦ “በግብፅ እያለን በነፃ እንበላው የነበረው ዓሣ እንዲሁም ኪያሩ፣ ሐብሐቡ፣ ባሮ ሽንኩርቱ፣ ቀይ ሽንኩርቱና ነጭ ሽንኩርቱ በዓይናችን ላይ ዞሯል!” (ዘኁ. 11:5) እውነት ይህን ምግብ ያገኙት “በነፃ” ነበር? አልነበረም። እንዲያውም እስራኤላውያን ባሮች ነበሩ፤ ግብፃውያን ከባድ ጭቆና ያደርሱባቸው ነበር። (ዘፀ. 1:13, 14፤ 3:6-9) በኋላ ላይ ግን ያን የመከራ ዘመን ረስተው የቀድሞውን ጊዜ መናፈቅ ጀመሩ። ይሖዋ ባደረገላቸው መልካም ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ የቀድሞውን ዘመን እያሰቡ “. . . ድሮ ቀረ” ማለት ጀመሩ። ይሖዋ እንዲህ ያለ ዝንባሌ በማሳየታቸው አልተደሰተም።—ዘኁ. 11:10፤ w20.11 25 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ኅዳር 22
ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ ተስፋ የቆረጡትንም ያድናል።—መዝ. 34:18 ግርጌ
አንዳንድ ጊዜ፣ ሕይወት “አጭርና በመከራ የተሞላ” መሆኑን ስናስብ እንጨነቅ ይሆናል። (ኢዮብ 14:1) ከዚህ አንጻር አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢሰማን የሚያስገርም አይደለም። በጥንት ዘመን የኖሩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችም እንደዚህ ተሰምቷቸው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ሞትን እስከ መመኘት ደርሰዋል። (1 ነገ. 19:2-4፤ ኢዮብ 3:1-3, 11፤ 7:15, 16) ሆኖም የሚታመኑበት አምላካቸው ይሖዋ በተደጋጋሚ አጽናንቷቸዋል እንዲሁም አጠንክሯቸዋል። የእነሱ ታሪክ የተመዘገበልን እኛን ለማጽናናት እና ለማስተማር ነው። (ሮም 15:4) የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ያጋጠመውን እንመልከት። የዮሴፍ ሕይወት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ፤ በአባቱ የተወደደ ልጅ የነበረው ዮሴፍ፣ ጣዖት አምላኪ የሆነ አንድ ግብፃዊ ባለሥልጣን ባሪያ ሆነ። (ዘፍ. 37:3, 4, 21-28፤ 39:1) ከዚያም የጶጢፋር ሚስት፣ ዮሴፍ ሊደፍራት እንደሞከረ በመግለጽ በሐሰት ወነጀለችው። ጶጢፋርም ጉዳዩን ሳያጣራ ዮሴፍን እስር ቤት አስገባው፤ እዚያም ዮሴፍ በብረት ታሰረ። (ዘፍ. 39:14-20፤ መዝ. 105:17, 18) በእርግጥም ዮሴፍን ያጋጠመው መከራ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር። w20.12 16-17 አን. 1-4
ረቡዕ፣ ኅዳር 23
ስምህ ይቀደስ።—ማቴ. 6:9
ኢየሱስ በጸሎታችን ላይ ቅድሚያ ልንሰጠው እንደሚገባ የጠቀሰው ይህን ሐሳብ ነው። ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? አንድን ነገር መቀደስ ሲባል ቅዱስና ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። ሆኖም አንዳንዶች ‘የይሖዋ ስም ቀድሞውንስ ቢሆን ቅዱስና ንጹሕ አይደለም እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት፣ ስም ምን ነገሮችን እንደሚያካትት መመርመር ያስፈልገናል። ስም፣ በወረቀት ላይ ከሚሰፍረው ቃል ወይም ከስሙ አጠራር ያለፈ ነገርን ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል” እንደሚል ልብ በል። (ምሳሌ 22:1፤ መክ. 7:1) ስም ይህን ያህል ትልቅ ቦታ ያለው ለምንድን ነው? ሰዎች ስለ ስሙ ባለቤት ያላቸውን አመለካከትም ስለሚያካትት ነው። በመሆኑም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር፣ አንድ ስም የሚጻፍበት ወይም የሚጠራበት መንገድ ሳይሆን ስሙ ሲነሳ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚመጣው ነገር ነው። ሰዎች ስለ ይሖዋ ውሸት ሲናገሩ ስሙን እያጠፉ ነው። w20.06 3 አን. 5-7
ሐሙስ፣ ኅዳር 24
እጅግ ተረብሻለሁ፤ ይሖዋ ሆይ፣ ይህ እስከ መቼ ድረስ ነው? ብዬ እጠይቅሃለሁ።—መዝ. 6:3
አንዳንድ ጊዜ፣ የሚሰማን ከፍተኛ ውጥረት አስተሳሰባችንን ሊቆጣጠረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘የማገኘው ገቢ ቤተሰቤን ለማስተዳደር ባይበቃኝስ?’ ‘ብታመምና መሥራት ቢያቅተኝ ወይም ከሥራ ብቀነስስ?’ እያልን እንጨነቅ ይሆናል። ‘በፈተና ተሸንፌ የአምላክን ሕግ ብጥስስ?’ ብለንም እንሰጋ ይሆናል። በተጨማሪም በቅርቡ ሰይጣን በእሱ ቁጥጥር ያሉ ሰዎችን ተጠቅሞ በአምላክ ሕዝብ ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፤ ‘ይህ በሚሆንበት ወቅት ታማኝ እሆናለሁ?’ የሚለው ጉዳይም ሊያስጨንቀን ይችላል። ከዚህ አንጻር ‘እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች በተወሰነ መጠንም ቢሆን መጨነቅ ስህተት ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “አትጨነቁ” እንዳላቸው እናውቃለን። (ማቴ. 6:25) ታዲያ ይህ ሲባል ጨርሶ ጭንቀት የሚባል ነገር እንዳይሰማን ይጠብቅብናል ማለት ነው? እንዲህ ማለት አይደለም። ደግሞም አንዳንድ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በጭንቀት የተዋጡባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ሆኖም በዚህ ምክንያት ይሖዋ አላዘነባቸውም። (1 ነገ. 19:4) በመሠረቱ ኢየሱስ “አትጨነቁ” ያለው እኛን ለማረጋጋት ነው። በኑሮ ጭንቀት ከመዋጣችን የተነሳ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት እንዲነካብን አይፈልግም። w21.01 3 አን. 4-5
ዓርብ፣ ኅዳር 25
የሴት . . . ራስ ወንድ [ነው]።—1 ቆሮ. 11:3
አንድ ባል ቤተሰቡን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋና በኢየሱስ ፊት ተጠያቂ ነው። (1 ጴጥ. 3:7) ይሖዋ የጽንፈ ዓለማዊው ቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ልጆቹ የሚመሩባቸውን መሥፈርቶች የማውጣትና የማስፈጸም ሥልጣን አለው። (ኢሳ. 33:22) ኢየሱስም የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ስለሆነ መሥፈርቶች የማውጣትና የማስፈጸም መብት አለው። (ገላ. 6:2፤ ቆላ. 1:18-20) ከዚሁ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አንድ የቤተሰብ ራስ ቤተሰቡን የሚመለከቱ ውሳኔዎች የማድረግ ሥልጣን አለው። (ሮም 7:2፤ ኤፌ. 6:4) ሆኖም ሥልጣኑ ገደብ አለው። ለምሳሌ ያህል፣ የሚያወጣቸው ደንቦች በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው። (ምሳሌ 3:5, 6) እንዲሁም አንድ የቤተሰብ ራስ የቤተሰቡ አባላት ላልሆኑ ሰዎች ደንብ የማውጣት ሥልጣን የለውም። (ሮም 14:4) በተጨማሪም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆቹ አድገው ከቤት ከወጡ በኋላ አክብሮት እንዲያሳዩት ቢጠበቅባቸውም በእሱ የራስነት ሥርዓት ሥር አይሆኑም።—ማቴ. 19:5፤ w21.02 2-3 አን. 3-5
ቅዳሜ፣ ኅዳር 26
የራሱ ለሆኑት . . . የሚያስፈልጋቸውን ነገር [ያቅርብ]።—1 ጢሞ. 5:8
አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ ያለውን ፍቅር የሚያሳይበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ነው። ያም ቢሆን ቁሳዊ ነገሮች የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ሊያሟሉ እንደማይችሉ ማስታወስ አለበት። (ማቴ. 5:3) ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ በነበረበት ወቅት ማርያም እንክብካቤ እንድታገኝ ፈልጎ ነበር። በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ሆኖ እየቃተተ በነበረበት በዚያ ወቅት ማርያምን እንዲንከባከባት ለሐዋርያው ዮሐንስ አደራ ሰጠው። (ዮሐ. 19:26, 27) የቤተሰብ ራስ የሆነ አንድ ወንድም ብዙ ከባድ ኃላፊነቶች ሊኖሩበት ይችላል። ሰብዓዊ ሥራውን በትጋት ማከናወን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም በሥራ ቦታ የሚያሳየው ምግባር የይሖዋን ስም እንደሚነካ ያውቃል። (ኤፌ. 6:5, 6፤ ቲቶ 2:9, 10) በጉባኤ ውስጥም ኃላፊነቶች ይኖሩት ይሆናል፤ ለምሳሌ እረኝነት ማድረግና በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅበት ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማጥናቱ በጣም አስፈላጊ ነው። የቤተሰቡ አባላት የእነሱን ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያደርገውን ጥረት ማድነቃቸው አይቀርም።—ኤፌ. 5:28, 29፤ 6:4፤ w21.01 12 አን. 15, 17
እሁድ፣ ኅዳር 27
[ባለሙያ ሚስት] የቤተሰቧን እንቅስቃሴ በደንብ ትከታተላለች።—ምሳሌ 31:27
የአምላክ ቃል፣ አንዲት ባለሙያ ሚስት ስላላት ድርሻ ሲናገር የቤቱን ሥራ በኃላፊነት እንደምትከታተል፣ መሬት እንደምትገዛና እንደምታስተዳድር እንዲሁም እንደምትነግድ ይገልጻል። (ምሳሌ 31:15, 16, 18) ይህች ሚስት ሐሳቧን የመግለጽ ነፃነት እንደሌላት ባሪያ አይደለችም። ከዚህ ይልቅ ባሏ እምነት ይጥልባታል፤ እንዲሁም የምትሰጠውን ሐሳብ ያዳምጣል። (ምሳሌ 31:11, 26) አንድ ባል ሚስቱን እንዲህ በአክብሮት የሚይዛት ከሆነ ለእሱ መገዛት አስደሳች ይሆንላታል። ኢየሱስ ታላላቅ ነገሮችን ያከናወነ ቢሆንም ለይሖዋ የራስነት ሥልጣን መገዛቱ ዝቅ እንደሚያደርገው አልተሰማውም። (1 ቆሮ. 15:28፤ ፊልጵ. 2:5, 6) በተመሳሳይም የኢየሱስን ምሳሌ የምትከተል አንዲት ባለሙያ ሚስት ለባሏ መገዛቷ ዝቅ እንደሚያደርጋት አይሰማትም። ባሏን የምትደግፈው እሱን ስለምትወደው ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት ይሖዋን ስለምትወድና ስለምታከብር ነው። ሆኖም ለባሏ የምትገዛ አንዲት ክርስቲያን ሚስት ባሏ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች ወይም መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚቃረን ነገር እንድታደርግ ቢጠይቃት ከእሱ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አትሆንም። w21.02 11 አን. 14-15፤ 12 አን. 19
ሰኞ፣ ኅዳር 28
መከራ ጽናትን [ያስገኛል]።—ሮም 5:3
በታሪክ ዘመናት ሁሉ የአምላክ አገልጋዮች ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ስደትን ለመቋቋም ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያት የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መስበካቸውን እንዲያቆሙ ቢያዝዛቸውም ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው እንዲታዘዙ’ ያነሳሳቸው ለእሱ ያላቸው ፍቅር ነው። (ሥራ 5:29፤ 1 ዮሐ. 5:3) በዛሬው ጊዜ፣ ጨካኝና ኃያል በሆኑ መንግሥታት ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞቻችንም ሁኔታውን በጽናት እንዲቋቋሙ የሚረዳቸው እንዲህ ያለው ጽኑ ፍቅር ነው። ዓለም ሲጠላን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ እንደሰታለን። (ሥራ 5:41፤ ሮም 5:4, 5) ብዙውን ጊዜ ለመቋቋም በጣም ከባድ የሚሆንብን ከቤተሰባችን አባላት የሚደርስብን ተቃውሞ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስንጀምር አንዳንዶቹ የቤተሰባችን አባላት እንደተታለልን ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎቹ ደግሞ አእምሯችንን እንደሳትን ያስቡ ይሆናል። (ከማርቆስ 3:21 ጋር አወዳድር።) ይባስ ብሎም ከባድ ስደት ያደርሱብን ይሆናል። እንዲህ ያለው ተቃውሞ ሊያስገርመን አይገባም። ምክንያቱም ኢየሱስ “የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ” በማለት ተናግሯል።—ማቴ. 10:36፤ w21.03 21 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ኅዳር 29
ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ [እና] ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት።—ያዕ. 1:19
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ከተጋበዝክ አስጠኚውና ጥናቱ ሲነጋገሩ በትኩረት አዳምጥ። አስፈላጊ ሲሆን ሐሳብ መስጠት የምትችለው እንዲህ ካደረግክ ብቻ ነው። እርግጥ አስተዋይ መሆን አለብህ። ለምሳሌ ብዙ ማውራት፣ አስጠኚው ሲያስረዳ ጣልቃ መግባት ወይም ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ማንሳት አይኖርብህም። ሆኖም አጠር ያለ ሐሳብ፣ ምሳሌ ወይም ጥያቄ በማንሳት ነጥቡ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ብዙም የምትጨምረው ሐሳብ እንደሌለ ይሰማህ ይሆናል። ያም ቢሆን ጥናቱን ማመስገንህና አሳቢነት ማሳየትህ እድገት እንዲያደርግ በእጅጉ ሊረዳው ይችላል። ጥናቱን እንደሚጠቅመው ከተሰማህ፣ እንዴት እውነትን እንደሰማህ ወይም አንድን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዴት እንደተወጣህ አሊያም በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን እጅ ያየኸው እንዴት እንደሆነ በአጭሩ ልትነግረው ትችላለህ። (መዝ. 78:4, 7) ተሞክሮህ ጥናቱን በእጅጉ ሊረዳው ይችላል። እምነቱን ሊያጠናክርለት እንዲሁም እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ሊያነሳሳው ይችላል። w21.03 10 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ኅዳር 30
ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።—ማቴ. 28:19
በአገልግሎት ላይ ለምናገኘው ማንኛውም ስኬት ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው? ጳውሎስ የቆሮንቶስ ጉባኤን በተመለከተ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቶናል፤ “እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን አምላክ ነው፤ ስለዚህ ምስጋና የሚገባው የሚያሳድገው አምላክ እንጂ የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው አይደለም” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በአገልግሎታችን ለምናገኘው ማንኛውም ስኬት ሁልጊዜ እውቅና ልንሰጥ የሚገባው ለይሖዋ ነው። ከአምላክ፣ ከክርስቶስና ከመላእክት ጋር ‘አብረን የመሥራት’ መብታችንን እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (2 ቆሮ. 6:1) ምሥራቹን ለሌሎች ማካፈል የምንችልባቸውን አጋጣሚዎች በትጋት በመፈለግ ነው። የእውነትን ዘር መዝራት ብቻ ሳይሆን ማጠጣትም አለብን። አንድ ሰው ፍላጎት እንዳለው ካስተዋልን፣ ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ እንጥራለን፤ ዓላማችን ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምር መርዳት ነው። ግለሰቡ በጥናቱ እየገፋ ሲሄድ በአስተሳሰቡና በዝንባሌው ላይ ለውጥ እንዲያደርግ ይሖዋ ይረዳዋል፤ ይህን የማየት አጋጣሚ ማግኘታችን ያስደስተናል። w20.05 30 አን. 14, 16-18