የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es23 ገጽ 7-17
  • ጥር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ ጥር 1
  • ሰኞ፣ ጥር 2
  • ማክሰኞ፣ ጥር 3
  • ረቡዕ፣ ጥር 4
  • ሐሙስ፣ ጥር 5
  • ዓርብ፣ ጥር 6
  • ቅዳሜ፣ ጥር 7
  • እሁድ፣ ጥር 8
  • ሰኞ፣ ጥር 9
  • ማክሰኞ፣ ጥር 10
  • ረቡዕ፣ ጥር 11
  • ሐሙስ፣ ጥር 12
  • ዓርብ፣ ጥር 13
  • ቅዳሜ፣ ጥር 14
  • እሁድ፣ ጥር 15
  • ሰኞ፣ ጥር 16
  • ማክሰኞ፣ ጥር 17
  • ረቡዕ፣ ጥር 18
  • ሐሙስ፣ ጥር 19
  • ዓርብ፣ ጥር 20
  • ቅዳሜ፣ ጥር 21
  • እሁድ፣ ጥር 22
  • ሰኞ፣ ጥር 23
  • ማክሰኞ፣ ጥር 24
  • ረቡዕ፣ ጥር 25
  • ሐሙስ፣ ጥር 26
  • ዓርብ፣ ጥር 27
  • ቅዳሜ፣ ጥር 28
  • እሁድ፣ ጥር 29
  • ሰኞ፣ ጥር 30
  • ማክሰኞ፣ ጥር 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
es23 ገጽ 7-17

ጥር

እሁድ፣ ጥር 1

እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው።—ማቴ. 15:14

ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ግብዝነት የሚንጸባረቅባቸው ሃይማኖታዊ ልማዶች በድፍረት አውግዟል። ለምሳሌ ፈሪሳውያን፣ ወላጆቻቸውን ከሚንከባከቡበት መንገድ ይልቅ እጃቸውን የሚታጠቡበት መንገድ ያሳስባቸው ነበር፤ ኢየሱስም የእነሱን ግብዝነት አጋልጧል። (ማቴ. 15:1-11) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩ ሃይማኖታዊ መሪዎች መበሳጨታቸው እውነቱን ከመናገር እንዲያግደው አልፈቀደም። ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንም አጋልጧል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሁሉም ሃይማኖታዊ እምነቶች እንደሆኑ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ብዙዎች ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ እንደሚሄዱና ወደ ሕይወት የሚወስደውን ቀጭን መንገድ የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 7:13, 14) በተጨማሪም አንዳንዶች አምላክን የሚያገለግሉ ቢመስሉም እሱን በትክክለኛው መንገድ እያገለገሉ እንዳልሆኑ በግልጽ ተናግሯል። እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።”—ማቴ. 7:15-20፤ w21.05 9 አን. 7-8

ሰኞ፣ ጥር 2

ዳግመኛ . . . በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም።—1 ሳሙ. 1:18

ሐና፣ ሕልቃና የተባለ ሌዋዊ አግብታ ነበር፤ እሱም በጣም ይወዳት ነበር። ይሁንና ሕልቃና፣ ፍናና የተባለች ሌላም ሚስት ነበረችው። ሕልቃና ሐናን ከፍናና አስበልጦ ይወዳት ነበር፤ ሆኖም “ፍናና ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።” በዚህም የተነሳ ፍናና “[ሐናን] ለማበሳጨት ዘወትር ትሳለቅባት ነበር።” ሐና “እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ” ታዝን ነበር! ያም ቢሆን ሐና ለመበቀል ጥረት እንዳደረገች የሚገልጽ ዘገባ የለም። ይልቁንም ሐና የልቧን አውጥታ ለይሖዋ ነገረችው፤ እሱ ነገሮችን እንደሚያስተካክል በመተማመን ጉዳዩን ለእሱ ተወችው። (1 ሳሙ. 1:2, 6, 7, 10) ከሐና ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድ ሰው ከአንተ ጋር እየተፎካከረ እንደሆነ ብታስተውልስ? የምትሰጠውን ምላሽ የምትወስነው አንተ እንደሆንክ አስታውስ። አንተም መልሰህ መፎካከር አያስፈልግህም። ክፉን በክፉ ከመመለስ ይልቅ ከግለሰቡ ጋር ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርግ። (ሮም 12:17-21) ግለሰቡ ጥሩ ምላሽ ባይሰጥም እንኳ ውስጣዊ ሰላምህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ። w21.07 17 አን. 13-14

ማክሰኞ፣ ጥር 3

ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ተጠበቁ።—ሉቃስ 12:15

የአስቆሮቱ ይሁዳ ስግብግብ መሆኑ አስከፊ ክህደት እንዲፈጽም አድርጎታል። ሆኖም ይሁዳ ከመነሻው መጥፎ ሰው አልነበረም። (ሉቃስ 6:13, 16) የገንዘብ ሣጥኑን እንዲይዝ ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑ ጥሩ ችሎታ ያለውና እምነት የሚጣልበት ሰው እንደነበረ ይጠቁማል። ሆኖም ይሁዳ፣ ኢየሱስ ስለ ስግብግብነት በተደጋጋሚ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ የሰማ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ መስረቅ ጀመረ። (ማር. 7:22, 23፤ ሉቃስ 11:39) ኢየሱስ ከመገደሉ ከጥቂት ጊዜ በፊት የተፈጸመ አንድ ክንውን የይሁዳ ስግብግብነት በግልጽ እንዲታይ አድርጓል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንዲሁም ማርያምና እህቷ ማርታ የሥጋ ደዌ በሽተኛ በነበረው በስምዖን ቤት ተጋብዘው ነበር። እየተመገቡ ሳሉ ማርያም ተነሳችና በኢየሱስ ራስ ላይ እጅግ ውድ የሆነ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ማፍሰስ ጀመረች። ይሁዳና ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት በዚህ በጣም ተበሳጩ። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት እንዲህ የተሰማቸው ገንዘቡን በአገልግሎት ላይ ቢጠቀሙበት እንደሚሻል ስላሰቡ ሊሆን ይችላል። ይሁዳን ያበሳጨው ነገር ግን ሌላ ነበር። ይሁዳ “ሌባ ስለነበረ” ከሣጥኑ ገንዘብ ለመስረቅ ፈልጎ ነበር።—ዮሐ. 12:2-6፤ ማቴ. 26:6-16፤ ሉቃስ 22:3-6፤ w21.06 18 አን. 12-13

ረቡዕ፣ ጥር 4

እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! . . . ማን ይታደገኛል?—ሮም 7:24

ብዙ ኃላፊነቶች እንደተደራረቡብህና ሁሉንም በተገቢው መልኩ ማከናወን እንደተሳነህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ የጳውሎስ ስሜት ይገባሃል። ጳውሎስን ያስጨንቀው የነበረው የአንድ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን “የጉባኤዎች ሁሉ ሐሳብ” ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-28) ያጋጠመህ ከባድ የጤና እክል ደስታህን አሳጥቶሃል? ጳውሎስ ‘ሥጋውን የሚወጋ እሾህ’ ለረጅም ጊዜ አሠቃይቶት ነበር፤ ጳውሎስ ‘እሾህ’ ያለው ያጋጠመውን የጤና እክል ሊሆን ይችላል፤ ከዚህ መከራ ለመገላገል ይጓጓ ነበር። (2 ቆሮ. 12:7-10) ከአለፍጽምናህ ጋር የምታደርገው ትግል ተስፋ አስቆርጦሃል? ጳውሎስም እንዲህ የተሰማው ጊዜ ነበር። ከአለፍጽምናው ጋር በሚያደርገው የማያባራ ትግል የተነሳ “ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ” ብሏል። (ሮም 7:21-24) ጳውሎስ የተለያዩ ፈተናዎችና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ይሖዋን ማገልገሉን ቀጥሏል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ብርታት ያገኘው እንዴት ነው? ከአለፍጽምናው ጋር መታገል ቢኖርበትም በቤዛው ላይ የማይናወጥ እምነት ነበረው። w21.04 21-22 አን. 7-8

ሐሙስ፣ ጥር 5

የሰው ልጅ . . . የመጣው . . . በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት [ነው]።—ማር. 10:45

ፍጹም ሰው የነበረው አዳም ኃጢአት ሲሠራ እሱም ሆነ ወደፊት የሚወለዱ ልጆቹ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲያጡ አድርጓል። አዳም ኃጢአት የሠራው ሆን ብሎ ስለሆነ ለድርጊቱ ምንም ማስተባበያ ሊያቀርብ አይችልም። ይሁንና ስለ ልጆቹስ ምን ማለት ይቻላል? አዳም በፈጸመው ኃጢአት የእነሱ እጅ የለበትም። (ሮም 5:12, 14) አዳም ለሠራው ኃጢአት ሞት ይገባዋል። ሆኖም ልጆቹ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ማድረግ የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዎ፣ አለ! አዳም ኃጢአት ከፈጸመ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአዳም ዘሮችን ከኃጢአትና ከሞት እርግማን ለማዳን ምን እርምጃ እንደሚወስድ የሚገልጽ ነገር ተናገረ። (ዘፍ. 3:15) ቤዛው ፍጹማን ባንሆንም እንኳ ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት እንድንችል መንገድ ከፍቶልናል። ቤዛው የዲያብሎስን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ለማፈራረስ ያስችላል። (1 ዮሐ. 3:8) ቤዛው ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ለምድር የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። w21.04 14 አን. 1፤ 19 አን. 17

ዓርብ፣ ጥር 6

እያንዳንዳችሁ . . . ተጠመቁ።—ሥራ 2:38

ከበርካታ አገሮች የመጡና የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ እጅግ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ተሰብስበዋል። በዚያ ቀን አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጸመ። አንዳንድ አይሁዳውያን በድንገት በጎብኚዎቹ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ! ከዚህ አስደናቂ ክንውን ይበልጥ ትኩረት የሚስበው ግን እነዚህ አይሁዳውያንና ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገሩት መልእክት ነው። ይህ መልእክት፣ ሕዝቡ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መዳን ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጽ ነው። ሕዝቡ በመልእክቱ ልባቸው በጥልቅ ተነካ። በመሆኑም “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” በማለት ጠየቁ። ጴጥሮስም “እያንዳንዳችሁ . . . ተጠመቁ” የሚል መልስ ሰጣቸው። (ሥራ 2:37, 38) ቀጥሎ የተከናወነው ነገር በጣም አስገራሚ ነው። በዚያ ቀን 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጠምቀው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆኑ። ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ታላቅ ተልእኮ ይኸውም ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የጀመረው በዚህ መንገድ ነው። ይህ ሥራ እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመንም ቀጥሏል። w21.06 2 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ጥር 7

እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን አምላክ ነው፤ ስለዚህ ምስጋና የሚገባው የሚያሳድገው አምላክ እንጂ የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው አይደለም።—1 ቆሮ. 3:6, 7

የምናገለግለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ከባድ በሆነበት ክልል ሊሆን ይችላል። ሰዎች ለመልእክታችን ግድየለሾች ይሆኑ አልፎ ተርፎም ይቃወሙን ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ክልል ውስጥ ስናገለግል አዎንታዊ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል? በዚህ ተነዋዋጭ ዓለም ውስጥ የሰዎች ሁኔታ በቅጽበት ሊቀየር እንደሚችል አስታውስ፤ ቀደም ሲል ለመልእክታችን ፍላጎት ያልነበራቸው ሰዎችም መንፈሳዊ ፍላጎት ሊያዳብሩ ይችላሉ። (ማቴ. 5:3) ቀደም ሲል ጽሑፎቻችንን ለመቀበል ጨርሶ ፈቃደኛ ያልነበሩ ሰዎች በኋላ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ፈቃደኛ ሆነዋል። በተጨማሪም የመከሩ ሥራ ኃላፊ ይሖዋ እንደሆነ እናውቃለን። (ማቴ. 9:38) ይሖዋ መትከላችንን እና ውኃ ማጠጣታችንን እንድንቀጥል ይፈልጋል፤ ሆኖም የሚያሳድገው እሱ ነው። ከዚህም ሌላ በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባይኖረንም እንኳ ይሖዋ ወሮታችንን የሚከፍለን በጥረታችን ላይ እንጂ ባገኘነው ውጤት ላይ ተመሥርቶ አለመሆኑን ማወቃችን በጣም ያበረታታናል! w21.07 6 አን. 14

እሁድ፣ ጥር 8

ልጆች ከይሖዋ የተገኙ ውርሻ ናቸው።—መዝ. 127:3

ይሖዋ ለሰዎች የመውለድ ችሎታ ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ልጆቻቸው እሱን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት የማስተማር ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ይሖዋ ለመላእክት ብዙ አስደናቂ ችሎታዎችን ቢሰጣቸውም ልጆች የመውለድ መብት አልሰጣቸውም። ስለዚህ ወላጆች፣ ልጆች የማሳደግ መብታቸውን ከፍ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። ወላጆች ቅዱስ አደራ፣ ማለትም ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። (ኤፌ. 6:4፤ ዘዳ. 6:5-7) የይሖዋ ድርጅት ወላጆችን ለመርዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ብዙ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል፤ ከእነዚህም መካከል ጽሑፎች፣ ቪዲዮዎች፣ ሙዚቃዎችና ኢንተርኔት ላይ የወጡ ሌሎች ነገሮች ይገኙበታል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የሰማዩ አባታችንም ሆነ ልጁ ኢየሱስ ልጆችን ይወዷቸዋል። (ሉቃስ 18:15-17) ወላጆች በይሖዋ የሚተማመኑ እንዲሁም ውድ ልጆቻቸውን ተንከባክበው ለማሳደግ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ከሆነ ይሖዋ ይደሰታል። እንዲሁም እንዲህ የሚያደርጉ ወላጆች ልጆቻቸው ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ እንዲከፈትላቸው ያደርጋሉ! w21.08 5 አን. 9

ሰኞ፣ ጥር 9

እምነት . . . የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።—ዕብ. 11:1

አንዳንዶች፣ እምነት ሲባል አንድን ነገር ያለምንም ማስረጃ መቀበል ማለት እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት የሚሰጠው ፍቺ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነት በማስረጃ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይናገራል፤ ስለዚህ ይሖዋን፣ ኢየሱስን ወይም የአምላክን መንግሥት ማየት ባንችልም እንኳ እውን መሆናቸውን የምናምነው ተጨባጭ ማስረጃ ስላለን ነው። (ዕብ. 11:3) የባዮኬሚስትሪ ባለሙያ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር “እምነታችን በጭፍን አመለካከት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ በሳይንስ የተረጋገጡ እውነታዎችን አምነን እንቀበላለን” ብሏል። ‘ፈጣሪ መኖሩን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ካለ ብዙዎች ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረው አምላክ እንደሆነ የማያምኑት ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። አንዳንዶች ይህን የማያምኑት ራሳቸው ማስረጃውን ስላልመረመሩ ነው። አሁን የይሖዋ ምሥክር የሆነው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ፍጥረት በትምህርት ቤት ምንም ነገር ስላልተማርን ‘ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው’ የሚለው ትምህርት እውነት እንዳልሆነ አሰብኩ። . . . ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ የሚያሳየውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ምክንያታዊና አሳማኝ ማስረጃ የተመለከትኩት ወደ 20ዎቹ ዕድሜ ከገባሁ በኋላ ነው።” w21.08 15 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ ጥር 10

ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም።—መዝ. 34:8

መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ እንዲሁም ሌሎች ስላገኙት በረከት ሲናገሩ በመስማት ስለ ይሖዋ ጥሩነት የተወሰነ ነገር ማወቅ እንችላለን። ሆኖም ስለ ይሖዋ ጥሩነት ከሁሉ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት የምንችለው ጥሩነቱን ራሳችን ‘ስንቀምስ’ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል አስበሃል እንበል። እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ ግን ኑሮህን ቀላል ማድረግ ይጠበቅብሃል። የአምላክን መንግሥት ካስቀደምክ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር በሙሉ እንደሚያሟላልህ ኢየሱስ የገባውን ቃል ታውቀዋለህ፤ ሆኖም ይህ ቃል በአንተ ሕይወት ሲፈጸም አላየህም። (ማቴ. 6:33) ያም ቢሆን ኢየሱስ በገባው ቃል ላይ እምነት በማሳደር ወጪህንና የሥራ ሰዓትህን ቀነስክ፤ እንዲሁም በአገልግሎትህ ላይ ትኩረት አደረግክ። እንዲህ ስታደርግ ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚያሟላልህ በራስህ ሕይወት ማየት ትችላለህ። በዚህ መንገድ የይሖዋን ጥሩነት ‘ትቀምሳለህ።’ w21.08 26 አን. 2

ረቡዕ፣ ጥር 11

ትክክለኛውን ትምህርት [አይታገሡም]።—2 ጢሞ. 4:3

በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። በርካታ ቀሳውስት ታዋቂ፣ ሀብታም ወይም በዓለም ዘንድ እንደ ጥበበኛ የሚታዩ ሰዎችን እጃቸውን ዘርግተው ይቀበላሉ። እነዚህ ሰዎች ሥነ ምግባራቸውና አኗኗራቸው ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የማይስማማ ቢሆንም እንኳ ቀሳውስቱ በደስታ ይቀበሏቸዋል። ሆኖም እነዚሁ ቀሳውስት፣ ቀናተኛ እና በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆኑትን የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች በንቀት ይመለከታሉ፤ እንዲህ የሚያደርጉት የአምላክ አገልጋዮች በዓለም መሥፈርት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ባለመሆናቸው ነው። ጳውሎስ እንደገለጸው አምላክ የመረጣቸው ሰዎች ‘የተናቁ’ ናቸው። (1 ቆሮ. 1:26-29) በይሖዋ ዓይን ግን ሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ ውድ ናቸው። በዓለም አስተሳሰብ እንዳንታለል ምን ይረዳናል? (ማቴ. 11:25, 26) ዓለም ለይሖዋ ሕዝቦች ያለው አመለካከት ተጽዕኖ ሊያደርግብን አይገባም። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀመው ትሑት ሰዎችን ብቻ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም። (መዝ. 138:6) ደግሞም ይሖዋ በዓለም ዓይን ጥበበኛ ባልሆኑ ወይም ባልተማሩ ሰዎች ተጠቅሞ ምን ያህል ሥራ እንዳከናወነ ማሰብ ይኖርብናል። w21.05 8 አን. 1፤ 9 አን. 5-6

ሐሙስ፣ ጥር 12

የሚያስፈልገኝን ነገር . . . ልካችሁልኛል።—ፊልጵ. 4:16

ሐዋርያው ጳውሎስ ወንድሞቹ ላደረጉለት እርዳታ አመስጋኝ ነበር። ወንድሞቹና እህቶቹ ያደረጉለትን እርዳታ በትሕትና ተቀብሏል። (ፊልጵ. 2:19-22) እናንት አረጋውያን፣ በጉባኤያችሁ ላሉ ወጣቶች አመስጋኝ መሆናችሁን ማሳየት የምትችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ወደምትፈልጉበት ቦታ ሊያደርሷችሁ፣ አስቤዛ ሊገዛዙላችሁ አሊያም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ሊያከናውኑላችሁ እንደሚፈልጉ ከነገሯችሁ እርዳታቸውን በአመስጋኝነት ተቀበሉ። እንዲህ ያለውን እርዳታ የይሖዋ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ወንድሞቻችሁ የሚሰጧችሁን እርዳታ መቀበላችሁ ከእነሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንድትመሠርቱ ሊረዳችሁ ይችላል። እነዚህን ወጣቶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው፤ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል የሚያደርጉት ጥረት ምን ያህል እንደሚያስደስታችሁም ግለጹላቸው። አብራችኋቸው ጊዜ አሳልፉ፤ እንዲሁም በሕይወታችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ተሞክሮ ንገሯቸው። ይህን ስታደርጉ ይሖዋ ወጣቶችን ወደ ጉባኤው ስለሳባቸው “አመስጋኝ መሆናችሁን” ታሳያላችሁ።—ቆላ. 3:15፤ ዮሐ. 6:44፤ 1 ተሰ. 5:18፤ w21.09 12 አን. 12-13

ዓርብ፣ ጥር 13

ከዚህ ርኅራኄም የተነሳ እንደ ንጋት ፀሐይ የሚያበራ ብርሃን ከላይ ይወጣልናል።—ሉቃስ 1:78

ይሖዋ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይወዳቸዋል። እኛ ግን የመንፈሳዊ ቤተሰባችንን አባላት መውደድና ለእነሱ ፍቅራችንን መግለጽ አንዳንድ ጊዜ ሊከብደን ይችላል። ምክንያቱም ሁላችንም ባሕላችንና አስተዳደጋችን የተለያየ ነው። በተጨማሪም ሁላችንም ስህተት ስለምንሠራ ሌሎችን ማበሳጨታችን ወይም ማሳዘናችን አይቀርም። ያም ቢሆን በመንፈሳዊ ቤተሰባችን መካከል ያለው ፍቅር እንዲጠናከር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። እንዴት? ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር በማሳየት ረገድ አባታችንን በመምሰል ነው። (ኤፌ. 5:1, 2፤ 1 ዮሐ. 4:19) ሩኅሩኅ የሆነ ሰው ሌሎችን ለመርዳትና ለማጽናናት የሚያስችል መንገድ ይፈልጋል። ኢየሱስ የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ለሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። (ዮሐ. 5:19) በአንድ ወቅት ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) የኢየሱስ ርኅራኄ ከስሜት ባለፈ በተግባርም ተገልጿል። የታመሙትን ፈውሷል፤ እንዲሁም ‘ለደከሙና ሸክም ለከበዳቸው’ ሰዎች እረፍት ሰጥቷል።—ማቴ. 11:28-30፤ 14:14፤ w21.09 22 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ ጥር 14

[አምላክ] መሐሪ ነው፤ በደላቸውን ይቅር ይል ነበር፤ ደግሞም አላጠፋቸውም።—መዝ. 78:38

ይሖዋ ምሕረት ማሳየት ይወዳል። ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ምሕረቱ ብዙ ነው” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ጳውሎስ እዚህ ጥቅስ ላይ እየተናገረ የነበረው አምላክ ፍጹማን ላልሆኑት ቅቡዓን አገልጋዮቹ ሰማያዊ ተስፋ በመስጠት ስላሳያቸው ምሕረት ነው። (ኤፌ. 2:4-7) ሆኖም የይሖዋ ምሕረት የተገለጸው በዚህ መንገድ ብቻ አይደለም። መዝሙራዊው ዳዊት “ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው፤ ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ይታያል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 145:9) ይሖዋ ሰዎችን ስለሚወድ ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት ባለበት ጊዜ ሁሉ ምሕረት ያደርጋል። ኢየሱስ፣ ይሖዋ ምሕረት ማሳየት ምን ያህል እንደሚወድ ከማንም በላይ ያውቃል። እሱና አባቱ የሰው ልጆች በምድር ላይ በኖሩባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ሁሉ በሰማይ ላይ አብረው ኖረዋል። (ምሳሌ 8:30, 31) ኢየሱስ፣ ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ ሰዎች ምሕረት ሲያሳይ በተደጋጋሚ ተመልክቷል። (መዝ. 78:37-42) ኢየሱስ ማራኪ የሆነውን ይህን የአባቱን ባሕርይ በትምህርቶቹ ላይ ጎላ አድርጎ ገልጿል። w21.10 8-9 አን. 4-5

እሁድ፣ ጥር 15

አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው።—ዮሐ. 12:28

ይሖዋ ራሱ ከሰማይ በሚያስገመግም ድምፅ ስሙን እንደሚያከብረው በመግለጽ ለዚህ ጸሎት መልስ ሰጥቷል። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ የአባቱ ስም እንዲከበር አድርጓል። (ዮሐ. 17:26) እውነተኛ ክርስቲያኖችም የአምላክን ስም የመጠቀምና ለሌሎች የማሳወቅ መብት በማግኘታቸው ኩራት ይሰማቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ “ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ . . . ለእነሱ ትኩረት [ሰጠ]።” (ሥራ 15:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክን ስም የመጠቀምና ለሌሎች የማሳወቅ መብት በማግኘታቸው ኩራት ይሰማቸው ነበር። በአገልግሎታቸውም ሆነ በጻፏቸው መልእክቶች ላይ የአምላክን ስም በስፋት ተጠቅመዋል። እንዲህ በማድረግ የአምላክን ስም የሚያሳውቁት ብቸኛዎቹ ሰዎች እነሱ መሆናቸውን አስመሥክረዋል። (ሥራ 2:14, 21) በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ለይሖዋ ስም የቆሙ ሰዎች መሆናቸውን አሳይተዋል። w21.10 20-21 አን. 8-10

ሰኞ፣ ጥር 16

ይሖዋ በታማኝ ፍቅር ያከናወናቸውን ነገሮች [ተመልከቱ]።—መዝ. 107:43

የአምላክ ታማኝ ፍቅር ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ይህ ሐሳብ በመዝሙር 136 ውስጥ 26 ጊዜ ተጠቅሷል። የመጀመሪያው ቁጥር እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ጥሩ ስለሆነ ምስጋና አቅርቡለት፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (መዝ. 136:1) ከቁጥር 2 እስከ 26 ላይም “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” የሚለው አዝማች ይገኛል። ይህን መዝሙር ስናነብ ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን ያለማቋረጥ ያሳየባቸውን በርካታ መንገዶች እንመለከታለን። “ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” የሚለው አዝማች አምላክ ለሕዝቦቹ የሚያሳየው ፍቅር ጊዜያዊ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። ይሖዋ በአገልጋዮቹ ቶሎ ተስፋ እንደማይቆርጥ ማወቃችን ምንኛ የሚያበረታታ ነው! ከዚህ ይልቅ ከእነሱ ጋር ይጣበቃል፤ በተለይ አገልጋዮቹ መከራ ሲያጋጥማቸው በፍጹም ከጎናቸው አይለይም። ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሚጣበቅ ማወቃችን ደስታና ብርታት ይሰጠናል፤ ይህም የሚያጋጥመንን መከራ ለመቋቋምና በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዛችንን ለመቀጠል ይረዳናል።—መዝ. 31:7፤ w21.11 4 አን. 9-10

ማክሰኞ፣ ጥር 17

ልባችሁ አይረበሽ። . . . እመኑ።—ዮሐ. 14:1

ከፊታችን ስለሚጠብቁን ክንውኖች ማለትም በሐሰት ሃይማኖት ላይ ስለሚደርሰው ጥፋት፣ የማጎጉ ጎግ ስለሚሰነዝረው ጥቃት እንዲሁም ስለ አርማጌዶን ጦርነት ስታስቡ አልፎ አልፎ ፍርሃት ይሰማችኋል? ‘ያንን አስፈሪ ጊዜ ታማኝነቴን ጠብቄ በጽናት አልፈው ይሆን?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? እንዲህ ዓይነት ስጋት አድሮባችሁ የሚያውቅ ከሆነ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኙት የኢየሱስ ቃላት በእጅጉ ይጠቅሟችኋል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ልባችሁ አይረበሽ። . . . እመኑ” ብሏቸዋል። ጠንካራ እምነት ካለን ወደፊት የሚመጡትን ፈተናዎች በልበ ሙሉነት ማለፍ እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች እንዴት እንደምንወጣቸው ማጤናችን፣ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ማለፍ እንድንችል እምነታችንን ለማጠናከር ይረዳናል። ከዚያም እምነታችንን በየትኞቹ አቅጣጫዎች ማጠናከር እንደሚያስፈልገን እናስተውላለን። እያንዳንዱን ፈተና በጽናት ስናልፍ እምነታችን ይጠናከራል። ይህ ደግሞ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ለማለፍ ይረዳናል። w21.11 20 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ጥር 18

ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ።—2 ቆሮ. 12:10

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጽም ጢሞቴዎስን አበረታቶታል፤ ይህ ምክር ለሁሉም ክርስቲያኖች ይሠራል። (2 ጢሞ. 4:5) ያም ቢሆን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ለምሳሌ፣ በሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉባቸው አልፎ ተርፎም ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን አስቡ። የይሖዋ ሕዝቦች ተስፋ አስቆራጭ ከሆኑ የተለያዩ ችግሮች ጋር ይታገላሉ። ለምሳሌ ብዙዎች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለማቅረብ እንኳ ለረጅም ሰዓት መሥራት ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በአገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ቢፈልጉም በሳምንቱ መጨረሻ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አይኖራቸውም። ሌሎች ደግሞ ባደረባቸው ከባድ በሽታ ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ ብዙ ማገልገል አይችሉም፤ እንዲያውም አንዳንዶች ጨርሶ ከቤት መውጣት አይችሉ ይሆናል። ‘አልረባም’ ከሚል ስሜት ጋር የሚታገሉም አሉ። ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ችግሮቻችንን እንድንቋቋምና ሁኔታችን በፈቀደው መጠን እሱን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ኃይል ሊሰጠን ይችላል። w21.05 20 አን. 1-3

ሐሙስ፣ ጥር 19

የአምላካችሁን ስም አታርክሱ።—ዘሌ. 19:12

አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ከአምልኳችን ጋር የሚጋጭ ነገር እንድናደርግ ይጫኑን ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመን ውሳኔ ማድረግ ይጠበቅብናል። በዘሌዋውያን 19:19 ላይ የሚገኝ አንድ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓት እንመልከት፤ ጥቅሱ “ከሁለት የተለያዩ የክር ዓይነቶች የተሠራ ልብስ አትልበስ” ይላል። ይህ ሕግ፣ እስራኤላውያን በዙሪያቸው ካሉ ብሔራት የተለዩ እንዲሆኑ አድርጓል። እርግጥ ክርስቲያኖች ከተለያየ ዓይነት ክር የተሠራ ልብስ ቢለብሱ ስህተት የለውም፤ ለምሳሌ ከጥጥ እና ከሱፍ የተሸመነ ልብስ ልንለብስ እንችላለን። ይሁንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ እምነት ወይም ምግባር ካላቸው ሰዎች ጋር መመሳሰል አንፈልግም። እርግጥ ነው፣ ዘመዶቻችንን እንወዳቸዋለን፤ ለሌሎች ሰዎችም ፍቅር እናሳያለን። ሆኖም የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ወሳኝ በሆኑ የሕይወታችን ዘርፎች ረገድ ከሌሎች የተለየን ለመሆን ፈቃደኞች ነን። ቅዱስ መሆን ከፈለግን እንዲህ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።—2 ቆሮ. 6:14-16፤ 1 ጴጥ. 4:3, 4፤ w21.12 5 አን. 14፤ 6 አን. 16

ዓርብ፣ ጥር 20

ወደ ሕይወት የሚወስደው በር . . . ጠባብ፣ መንገዱም ቀጭን ነው።—ማቴ. 7:14

ወደ ሕይወት የሚወስደውን መንገድ ማግኘት ይቻላል። ኢየሱስ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” ብሏል። (ዮሐ. 8:31, 32) አንተም ብዙኃኑን ከመከተል ይልቅ እውነትን ለማግኘት ጥረት ማድረግህ የሚያስመሰግን ነው። አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ለማወቅ ቃሉን በጥልቀት አጥንተሃል፤ እንዲሁም የኢየሱስን ትምህርቶች ሰምተሃል። ይሖዋ ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች እንድትርቅ እንዲሁም አረማዊ ምንጭ ባላቸው በዓላትና ልማዶች መካፈልህን እንድትተው እንደሚፈልግ ተምረሃል። በተጨማሪም ይሖዋ የሚጠብቅብንን ነገር ማድረግና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ከሌላቸው ልማዶች መላቀቅ ተፈታታኝ ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበሃል። (ማቴ. 10:34-36) እነዚህን ለውጦች ማድረግ አታግሎህ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሰማያዊውን አባትህን ስለምትወደው ለውጥ ለማድረግ ጥረት ማድረግህን ቀጠልክ። ይሖዋ ይህን ሲያይ ምንኛ ተደስቶብህ ይሆን!—ምሳሌ 27:11፤ w21.12 22 አን. 3፤ 23 አን. 5

ቅዳሜ፣ ጥር 21

ልጄ ሆይ፣ አዳምጥ፤ የምናገረውንም ተቀበል።—ምሳሌ 4:10

ሙሴ ከባድ ስህተት ከሠራ በኋላ የተሰጠውን እርማት በመቀበል ጥሩ ምሳሌ ትቷል። በአንድ ወቅት ይሖዋን ማክበር እስኪያቅተው ድረስ ቁጣውን መቆጣጠር አቅቶት ነበር። በዚህም የተነሳ ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከለከለ። (ዘኁ. 20:1-13) ሙሴ፣ ውሳኔውን እንደገና እንዲያስብበት ለይሖዋ ጥያቄ ሲያቀርብ “ዳግመኛ ስለዚህ ጉዳይ እንዳታነሳብኝ” አለው። (ዘዳ. 3:23-27) ሙሴ በዚህ አልተበሳጨም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ውሳኔ ተቀብሏል፤ ይሖዋም እስራኤላውያንን ለመምራት በእሱ መጠቀሙን ቀጥሏል። (ዘዳ. 4:1) ምክር ከመቀበል ጋር በተያያዘ ሙሴ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ሙሴ የሚጓጓለትን ነገር ቢያጣም ታማኝ ሆኖ በመቀጠል የይሖዋን ምክር እንደተቀበለ አሳይቷል። እንደ ሙሴ ያሉ ታማኝ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ መከተላችን ይጠቅመናል። (ምሳሌ 4:11-13) ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም እንዲሁ አድርገዋል። w22.02 11 አን. 9-10

እሁድ፣ ጥር 22

ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።—ዮሐ. 11:35

በ32 ዓ.ም. የክረምት ወቅት፣ የኢየሱስ ወዳጅ የነበረው አልዓዛር ታመመ እና ሞተ። (ዮሐ. 11:3, 14) አልዓዛር ማርያምና ማርታ የተባሉ ሁለት እህቶች ነበሩት፤ ኢየሱስም ይህን ቤተሰብ በጣም ይወደው ነበር። ማርታ ኢየሱስ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ወዲያውኑ ልትቀበለው ወጣች። ከዚያም “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው፤ ማርታ ይህን ስትል ምን ያህል በሐዘን ተውጣ እንደሚሆን አስበው። (ዮሐ. 11:21, 32-33) ኢየሱስ ማርያምና ማርታ በወንድማቸው ሐዘን ምን ያህል እንደተደቆሱ ማየቱ እንባውን እንዲያፈስስ አድርጎት መሆን አለበት። አንተም የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ይሖዋ ስሜትህን ይረዳልሃል። ኢየሱስ የአባቱ “ትክክለኛ አምሳያ” ነው። (ዕብ. 1:3) ኢየሱስ እንባውን ሲያፈስስ የአባቱን ስሜት አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ይሖዋ ማዘንህን እንደሚያስተውል እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ከዚህም ባለፈ ግን ስሜትህን ይጋራል፤ የተሰበረውን ልብህን ሊጠግንልህ ይፈልጋል።—መዝ. 34:18፤ 147:3፤ w22.01 15-16 አን. 5-7

ሰኞ፣ ጥር 23

እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው።—ሮም 10:17

ጊዜ መድበህ ይሖዋን የምታነጋግረው፣ የምታዳምጠውና ስለ እሱ የምታስብ ከሆነ በእጅጉ ትጠቀማለህ። አንደኛ፣ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታህ ይሻሻላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) ሁለተኛ፣ የማስተማር ችሎታህ ይሻሻላል። ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስተምር አንዱ ዋነኛው ግባችን ጥናታችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርብ መርዳት ነው። የሰማዩ አባታችንን ባነጋገርነውና ባዳመጥነው መጠን ይበልጥ እንወደዋለን፤ ጥናታችን እሱን እንዲወደው ለመርዳትም የተሻለ ብቃት ይኖረናል። ኢየሱስን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። ስለ አባቱ ይናገር የነበረው ሞቅ ባለ እና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለነበር ታማኝ ተከታዮቹ ይሖዋን መውደድ ቀላል ሆኖላቸዋል። (ዮሐ. 17:25, 26) ሦስተኛ፣ እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል። አምላክን እንዲመራህ፣ እንዲያጽናናህ ወይም እንዲደግፍህ ስትለምነው ምን እንደሚፈጠር ለማሰብ ሞክር። ይሖዋ ለጸሎትህ ምላሽ በሰጠህ ቁጥር በእሱ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል።—1 ዮሐ. 5:15፤ w22.01 30 አን. 15-17

ማክሰኞ፣ ጥር 24

አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ።—ቆላ. 3:9

ይሖዋ መጥፎ ሐሳቦችንና ልማዶችን እንድናስወግድ የሚያሳስበን በጣም ስለሚወደን ነው፤ በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆንም ይፈልጋል። (ኢሳ. 48:17, 18) ለመጥፎ ምኞቶች እጅ የሚሰጡ ሰዎች ራሳቸውንም ሆነ የሚወዷቸውን ሰዎች እንደሚጎዱ ያውቃል። መዘዙ ለእኛም ሆነ ለሌሎች መትረፉ ያሳዝነዋል። ስብዕናችንን ለመቀየር ስንወስን አንዳንድ ወዳጆቻችንና ቤተሰቦቻችን ያፌዙብን ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3, 4) ‘የፈለግከውን የማድረግ መብት እኮ አለህ! ሌሎች እንዲመሩህ ለምን ትፈቅዳለህ?’ ይሉን ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋን መሥፈርቶች የማይቀበሉ ሰዎችም በሌሎች ተጽዕኖ ሥር ናቸው። በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም እንዲቀርጻቸው እየፈቀዱ ነው። (ሮም 12:1, 2) ሁላችንም ያሉን አማራጮች ሁለት ናቸው፦ አሮጌውን ስብዕና ለብሰን ለመቀጠል ከመረጥን በኃጢአትና በሰይጣን ዓለም ቁጥጥር ሥር እንሆናለን። ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ይሖዋ እንዲለውጠንና የተሻለ ስብዕና ለማዳበር እንዲረዳን መፍቀድ ነው።—ኢሳ. 64:8፤ w22.03 3 አን. 6-7

ረቡዕ፣ ጥር 25

የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ . . . የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።—ዕብ. 4:12

በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላችን ስላለንበት ሁኔታ ተገቢውን አመለካከት ለማዳበር ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ ባለቤቷን በሞት ያጣችን አንዲት እህት እንዴት እንደረዳት እንመልከት። የኢዮብን መጽሐፍ በማንበብ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት እንደምትችል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ነገራት። እህታችን መጽሐፉን ስታነብ መጀመሪያ ላይ፣ ኢዮብ የተሳሳተ አመለካከት በመያዙ እንደፈረደችበት ተናግራለች። ታሪኩን ስታነብ “አይ ኢዮብ! የራስህ ችግር ብቻ ነው እንዴ የሚታይህ?” በማለት እየገሠጸችው ነበር። በኋላ ግን የእሷም አመለካከት ከኢዮብ ጋር በጣም ተመሳሳይ እንደሆነ አስተዋለች። ይህም አመለካከቷን ለማስተካከል የረዳት ከመሆኑም ሌላ ባለቤቷን ማጣቷ ያስከተለባትን ሐዘን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሰጥቷታል። ይሖዋ ክርስቲያኖችን የሚያበረታበት ሌላው መንገድ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በመጠቀም ነው። ጳውሎስ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ እንደሚጓጓ ጽፏል።—ሮም 1:11, 12፤ w21.05 22 አን. 10-11፤ 24 አን. 12

ሐሙስ፣ ጥር 26

ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለይሖዋ ሰባት ቀን በዓሉን ታከብራለህ።—ዘዳ. 16:15

የጥንቶቹ እስራኤላውያን እንዲህ ተብለው ነበር፦ “በመካከልህ ያሉ ወንዶች ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ . . . አምላክህ ይሖዋ በመረጠው ስፍራ ፊቱ ይቅረቡ።” (ዘዳ. 16:16) እስራኤላውያን በበዓላቱ ላይ ለመገኘት ሲሄዱ ቤታቸውንና እርሻቸውን የሚጠብቅላቸው ሰው አልነበረም። ሆኖም ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቶላቸዋል፦ “የአምላክህን የይሖዋን ፊት ለማየት . . . በምትወጣበት ጊዜ ማንም ምድርህን አይመኝም።” (ዘፀ. 34:24) ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት በማሳደር በዓመታዊ በዓላቱ ላይ ይገኙ ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው ብዙ በረከት ያስገኝላቸዋል፤ ስለ አምላክ ሕግ ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት፣ በእሱ ጥሩነት ላይ ማሰላሰልና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር እርስ በርስ መበረታታት የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ያገኙ ነበር። እኛም መሥዋዕትነት ከፍለን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ተመሳሳይ በረከቶችን እናገኛለን። አጭርና ትርጉም ያለው ሐሳብ ለመስጠት ተዘጋጅተን ስንሄድ ደግሞ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚደሰት አስቡት። w22.03 22 አን. 9

ዓርብ፣ ጥር 27

በፈተና ላይ ላሉት ሊደርስላቸው ይችላል።—ዕብ. 2:18

ይሖዋ፣ ኢየሱስ ሊቀ ካህናታችን በመሆን ወደፊት ለሚጫወተው ሚና እያሠለጠነው ነበር። ኢየሱስ እጅግ ከባድ በሆነ ፈተና ውስጥ አምላክን መታዘዝ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። የደረሰበት ፈተና በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ እርዳታ ለማግኘት “በከፍተኛ ጩኸትና እንባ” ጸልዮአል። ኢየሱስ ራሱ በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ስላለፈ ‘ፈተና ላይ ስንሆን’ ስሜታችንን ሊረዳልን እንዲሁም ‘ሊደርስልን’ ይችላል። ይሖዋ ‘በድካማችን ሊራራልን የሚችል መሐሪ ሊቀ ካህናት’ ስለሾመልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ዕብ. 2:17፤ 4:14-16፤ 5:7-10) ይሖዋ ልጁ ይህን ያህል እንዲሠቃይ የፈቀደው ለአንድ ወሳኝ ጥያቄ መልስ ለማስገኘት ሲል ነው፤ ጥያቄው ‘እጅግ ከባድ የሆነ ፈተና ቢደርስበትም እንኳ ለአምላክ ታማኝ መሆን የሚችል ሰው አለ?’ የሚል ነው። ሰይጣን ‘ይህን ማድረግ የሚችል ሰው የለም!’ ባይ ነው። ይህ የአምላክ ጠላት የሰው ልጆች አምላክን የሚያገለግሉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው እንደሆነና ይሖዋን እንደማይወዱት ተናግሯል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4, 5) ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አሳይቷል። w21.04 17 አን. 7-8

ቅዳሜ፣ ጥር 28

ስለዚህ ሂዱና . . . ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ . . . ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]።—ማቴ. 28:19, 20

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጠመቅ እንዲችል የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሥራ ላይ ማዋል አለበት። ጥናቱ የተማረውን ነገር በሥራ ላይ የሚያውል ከሆነ ኢየሱስ በምሳሌው ላይ እንደጠቀሰው “አስተዋይ ሰው” ይሆናል፤ ይህ ሰው ቤቱን በዓለት ላይ ለመገንባት ሲል በጥልቀት ቆፍሯል። (ማቴ. 7:24, 25፤ ሉቃስ 6:47, 48) ጥናትህ በሕይወቱ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ እርዳው። (ማር. 10:17-22) ኢየሱስ ሀብታም ሰው ንብረቱን ሁሉ መሸጥ ከባድ እንደሚሆንበት ያውቅ ነበር። (ማር. 10:23) ያም ቢሆን ኢየሱስ ለሀብታሙ ሰው ይህን ከባድ ለውጥ እንዲያደርግ ነግሮታል። ለምን? ይህን ሰው ስለወደደው ነው። አንዳንድ ጊዜ ጥናታችን አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ዝግጁ እንዳልሆነ ስለሚሰማን የተማረውን ነገር በሥራ ላይ እንዲያውል ከማበረታታት ወደኋላ እንል ይሆናል። (ቆላ. 3:9, 10) ሆኖም ስለ ጉዳዩ ቶሎ ማንሳታችን ጥናታችን ቶሎ ብሎ ለውጥ ማድረግ እንዲጀምር ሊረዳው ይችላል። ጥናትህ ለውጥ እንዲያደርግ ማበረታታትህ እንደምታስብለት ያሳያል።—መዝ. 141:5፤ ምሳሌ 27:17፤ w21.06 3 አን. 3, 5

እሁድ፣ ጥር 29

ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ [ትቶላችኋል]።—1 ጴጥ. 2:21

ሐዋርያው ጴጥሮስ እየተናገረ የነበረው ኢየሱስ መከራን በጽናት በመቋቋም ረገድ ስለተወው ምሳሌ ነው። ሆኖም ኢየሱስን መምሰል የምንችልባቸው ሌሎች ብዙ መንገዶች አሉ። (1 ጴጥ. 2:18-25) እንዲያውም ኢየሱስ በመላው ሕይወቱ ማለትም በተናገራቸውና ባደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ልንከተለው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል። ይሁንና ፍጹማን ካለመሆናችን አንጻር የኢየሱስን ምሳሌ በእርግጥ መከተል እንችላለን? በሚገባ! ጴጥሮስ ያበረታታን ‘የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ እንድንከተል’ እንጂ ፍጹም በሆነ መንገድ እንድንከተል አለመሆኑን ልብ እንበል። ፍጹማን ባንሆንም እንኳ አቅማችን በፈቀደ መጠን የኢየሱስን ፈለግ በጥንቃቄ ለመከተል ጥረት ካደረግን ሐዋርያው ዮሐንስ እንደተናገረው ‘ኢየሱስ በተመላለሰበት መንገድ መመላለስ’ እንችላለን። (1 ዮሐ. 2:6) የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ይረዳናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ አምላክን የሚያስደስት ሕይወት መምራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። (ዮሐ. 8:29) በመሆኑም የኢየሱስን ፈለግ ስንከተል ይሖዋን እናስደስታለን። የሰማዩ አባታችን ደግሞ የእሱ ወዳጆች ለመሆን ልባዊ ጥረት ወደሚያደርጉ ሰዎች እንደሚቀርብ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ያዕ. 4:8፤ w21.04 3 አን. 4-6

ሰኞ፣ ጥር 30

ይሖዋ በሕዝቡ ደስ ይሰኛል።—መዝ. 149:4

ይሖዋ ያሉንን መልካም ባሕርያት ያስተውላል፤ ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንደምንችል ያውቃል፤ እንዲሁም ወደ ራሱ ይስበናል። ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ ከሆንን ለዘላለም ወዳጃችን ይሆናል! (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ እንደሚወደንና እንደሚደግፈን እርግጠኞች ከሆንን በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች ቢያጋጥሙንም እንኳ እሱን በሙሉ ልባችን ለማገልገል እንገፋፋለን። በሌላ በኩል ግን፣ አምላክ የሚያስብልን መሆኑን ከተጠራጠርን ‘ጉልበታችን እጅግ ይዳከማል።’ (ምሳሌ 24:10) ከዚህም ሌላ ተስፋ ከቆረጥንና ይሖዋ እንደማይወደን ከተሰማን ለሰይጣን ጥቃቶች ተጋላጭ እንሆናለን። (ኤፌ. 6:16) በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች ይሖዋ የሚወዳቸው መሆኑን በመጠራጠራቸው ምክንያት በመንፈሳዊ ተዳክመዋል። አምላክ የሚወደን መሆኑን መጠራጠር ብንጀምር ምን ማድረግ ይኖርብናል? እንዲህ ያለውን ሐሳብ ወዲያውኑ ከአእምሯችን ልናወጣው ይገባል። ይሖዋ እንዲህ ያለውን ‘እረፍት የሚነሳ ሐሳብ’ እንዲያስወግድልህ እንዲሁም ‘ልብህንና አእምሮህን የሚጠብቅልህን የአምላክ ሰላም’ እንዲሰጥህ ልትጠይቀው ትችላለህ። (መዝ. 139:23 ግርጌ፤ ፊልጵ. 4:6, 7) በተጨማሪም እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አስታውስ። w21.04 20 አን. 1, 4፤ 21 አን. 5, 6

ማክሰኞ፣ ጥር 31

ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ [የሚያደርገው] አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13

የይሖዋ ምሥክር የሆንከው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ‘ምሥራቹን’ ሰማህ፤ ምናልባትም የሰማኸው ከወላጆችህ፣ ከሥራ ባልደረባህ፣ አብሮህ ከሚማር ልጅ አሊያም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት አማካኝነት ሊሆን ይችላል። (ማር. 13:10) ከዚያም አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን አስጠናህ፤ ይህን ለማድረግ ብዙ ጊዜና ጥረት ጠይቆበት ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ይሖዋን መውደድ ጀመርክ፤ እሱ እንደሚወድህም ተማርክ። በዚህ መንገድ ይሖዋ ወደ እውነት ስቦሃል፤ አሁን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለሆንክ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለህ። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ አንድን ሰው ተጠቅሞ እውነትን ስላስተማረህ እንዲሁም እንደ አገልጋዩ አድርጎ ስለተቀበለህ አመስጋኝ እንደሆንክ ምንም ጥያቄ የለውም። እውነትን ስላወቅን ሌሎችም አብረውን በሕይወት መንገድ ላይ እንዲጓዙ የመርዳት መብት አግኝተናል። ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ብዙም አይከብደን ይሆናል፤ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና መምራት በጣም ከባድ ሊሆንብን ይችላል። w21.07 2 አን. 1-2

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ