የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es23 ገጽ 17-26
  • የካቲት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የካቲት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ የካቲት 1
  • ሐሙስ፣ የካቲት 2
  • ዓርብ፣ የካቲት 3
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 4
  • እሁድ፣ የካቲት 5
  • ሰኞ፣ የካቲት 6
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 7
  • ረቡዕ፣ የካቲት 8
  • ሐሙስ፣ የካቲት 9
  • ዓርብ፣ የካቲት 10
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 11
  • እሁድ፣ የካቲት 12
  • ሰኞ፣ የካቲት 13
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 14
  • ረቡዕ፣ የካቲት 15
  • ሐሙስ፣ የካቲት 16
  • ዓርብ፣ የካቲት 17
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 18
  • እሁድ፣ የካቲት 19
  • ሰኞ፣ የካቲት 20
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 21
  • ረቡዕ፣ የካቲት 22
  • ሐሙስ፣ የካቲት 23
  • ዓርብ፣ የካቲት 24
  • ቅዳሜ፣ የካቲት 25
  • እሁድ፣ የካቲት 26
  • ሰኞ፣ የካቲት 27
  • ማክሰኞ፣ የካቲት 28
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
es23 ገጽ 17-26

የካቲት

ረቡዕ፣ የካቲት 1

ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ ነው።—መዝ. 145:18

ይሖዋ የሁሉም አገልጋዮቹ ደህንነት ያሳስበዋል። ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ቅርብ ነው፤ እንዲሁም ስሜታችን ሲደቆስ ያስተውላል። (መዝ. 145:18, 19) ይሖዋ ለነቢዩ ኤልያስ ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠውና እንዴት እንደረዳው እንመልከት። ታማኙ ኤልያስ የኖረው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ላይ ነው። በዚህ ወቅት የይሖዋ አገልጋዮች ከባድ ስደት ይደርስባቸው ነበር፤ ኃያል የሆኑት የአምላክ ጠላቶች በተለይ ኤልያስን የጥቃት ዒላማቸው አድርገውት ነበር። (1 ነገ. 19:1, 2) ኤልያስን ያስጨነቀው ሌላው ነገር ደግሞ ከይሖዋ ታማኝ ነቢያት መካከል የቀረው እሱ ብቻ እንደሆነ ማሰቡ ሊሆን ይችላል። (1 ነገ. 19:10) አምላክ ኤልያስን ለመርዳት ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደ። ይሖዋ መልአኩን በመላክ ኤልያስ ብቻውን እንዳልሆነና ፈሪሃ አምላክ ያላቸው በርካታ እስራኤላውያን እንዳሉ አረጋገጠለት። (1 ነገ. 19:5, 18) ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንደሚያገኙ በመግለጽ አበረታቷቸዋል። (ማር. 10:29, 30) የመንፈሳዊ ቤተሰባችን ራስ የሆነው ይሖዋ ደግሞ እሱን ማገልገል የሚፈልጉትን እንደሚደግፋቸው ቃል ገብቷል።—መዝ. 9:10፤ w21.06 8-9 አን. 3-4

ሐሙስ፣ የካቲት 2

ከአምላክ የሆነ የአምላክን ቃል ይሰማል።—ዮሐ. 8:47

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶቻችን የሐሰት ትምህርቶችን ስለሚያጋልጡ ብዙዎች ይሰናከሉብናል። ቀሳውስት አምላክ ክፉዎችን በገሃነመ እሳት እንደሚያቃጥል ያስተምራሉ። ይህን የሐሰት ትምህርት፣ ሕዝቡ ሁልጊዜም በእነሱ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ለማድረግ ይጠቀሙበታል። የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚያገለግሉት የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ትምህርት ሐሰት መሆኑን ያጋልጣሉ። ቀሳውስት ነፍስ እንደማትሞትም ያስተምራሉ። እኛ ግን ይህ ትምህርት ምንጩ አረማዊ እንደሆነ እናጋልጣለን፤ ደግሞም ነፍስ የማትሞት ከሆነ ትንሣኤ አስፈላጊ አይሆንም። በተጨማሪም ብዙ ሃይማኖቶች የሰው ዕድል አስቀድሞ የተወሰነ እንደሆነ ያስተምራሉ። እኛ ግን የሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት እንዳላቸውና አምላክን ለማገልገል መምረጥ እንደሚችሉ እናስተምራለን። እንዲህ ስናደርግ የሃይማኖት መሪዎች ምን ይሰማቸዋል? አብዛኛውን ጊዜ በጣም ይበሳጫሉ። ለእውነት ፍቅር ካለን የአምላክን ቃል መቀበል አለብን። (ዮሐ. 8:45, 46) ከሰይጣን ዲያብሎስ በተለየ መልኩ እኛ በእውነት ውስጥ ጸንተን እንቆማለን። መቼም ቢሆን ከእምነታችን ጋር የሚጋጭ ነገር አናደርግም። (ዮሐ. 8:44) የአምላክ ሕዝቦች፣ ኢየሱስ እንዳደረገው ‘ክፉ የሆነውን እንዲጸየፉ ጥሩ የሆነውን ደግሞ አጥብቀው እንዲይዙ’ ይጠበቅባቸዋል።—ሮም 12:9፤ ዕብ. 1:9፤ w21.05 10 አን. 10-11

ዓርብ፣ የካቲት 3

ዲያብሎስን . . . ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።—ያዕ. 4:7

በኩራት ወይም በስግብግብነት ወጥመድ እንደተያዝን ብንገነዘብስ? ከእነዚህ ወጥመዶች መውጣት እንችላለን! ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ዲያብሎስ በሕይወት እንዳሉ አጥምዶ የያዛቸው ሰዎች “ከእሱ ወጥመድ ሊወጡ” እንደሚችሉ ገልጿል። (2 ጢሞ. 2:26) ይሖዋ ከሰይጣን ይበልጥ ኃያል እንደሆነ ፈጽሞ አትርሱ። በመሆኑም የይሖዋን እርዳታ ከተቀበልን ዲያብሎስ ከዘረጋው ከየትኛውም ወጥመድ ማምለጥ እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ከሰይጣን ወጥመዶች ለመውጣት ከመሞከር ይልቅ መጀመሪያውኑ በወጥመዱ አለመያዝ የተሻለ ነው። እንዲህ ማድረግ የምንችለው በአምላክ እርዳታ ብቻ ነው። በመሆኑም እነዚህ መጥፎ ባሕርያት በአስተሳሰብህና በድርጊትህ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ጀምረው ከሆነ ለማስተዋል እንዲረዳህ ይሖዋን በየዕለቱ ለምነው። (መዝ. 139:23, 24) እነዚህ ወጥመዶች እንዲይዙህ ፈጽሞ አትፍቀድ! ሰይጣን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት አዳኝ ሆኖ ኖሯል። በቅርቡ ግን ይታሰራል፤ በኋላም ሙሉ በሙሉ ይደመሰሳል። (ራእይ 20:1-3, 10) ያንን ቀን በጉጉት እንጠብቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን በሰይጣን ወጥመዶች ላለመያዝ ንቁዎች እንሁን። ኩራት ወይም ስግብግብነት እንዳይጠናወተን ከፍተኛ ጥረት እናድርግ። ‘ዲያብሎስን ለመቃወም’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲህ ካደረግን ‘እሱም ከእኛ ይሸሻል!’ w21.06 19 አን. 15-17

ቅዳሜ፣ የካቲት 4

የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።—ማቴ. 9:38

አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲቀበልና ይህን እውነት ለሌሎች ሲያካፍል ይሖዋ በጣም ይደሰታል። (ምሳሌ 23:15, 16) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚከናወነውን ሥራ ሲያይ ምንኛ ይደሰት ይሆን! ለምሳሌ ያህል በ2020 የአገልግሎት ዓመት ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ የነበረ ቢሆንም እንኳ 7,705,765 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተመርተዋል፤ ይህም 241,994 ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው እንዲጠመቁ አስችሏል። እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትም በበኩላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ተጨማሪ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ያደርጋሉ። (ሉቃስ 6:40) በእርግጥም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል ይሖዋን እናስደስተዋለን። ደቀ መዛሙርት ማድረግ ጥረት ይጠይቃል፤ ሆኖም ይሖዋ ስለሚረዳን አዲሶች የሰማዩን አባታችንን እንዲወዱ በማስተማሩ ሥራ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። ቢያንስ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ለመምራት ግብ ማውጣት እንችል ይሆን? አመቺ አጋጣሚዎችን ሁሉ ተጠቅመን ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ብንጋብዝ አስገራሚ ውጤት እናገኝ ይሆናል። w21.07 6-7 አን. 14-16

እሁድ፣ የካቲት 5

ለአምላኬ ቤት ካለኝ ፍቅር የተነሳ . . . የግል ሀብቴ የሆነውን ወርቅና ብርም ለአምላኬ ቤት እሰጣለሁ።—1 ዜና 29:3

ንጉሥ ዳዊት የቤተ መቅደሱን ግንባታ ለመደገፍ ከራሱ ሀብት ከፍተኛ መዋጮ አድርጓል። (1 ዜና 22:11-16) ዕድሜያችን በመግፋቱ የተነሳ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ለመካፈል ጉልበት ባይኖረንም አቅማችን በፈቀደ መጠን መዋጮ በማድረግ እነዚህን ፕሮጀክቶች መደገፋችንን መቀጠል እንችላለን። በተጨማሪም ያካበትናቸውን ተሞክሮዎች ለወጣቶች ልንነግራቸው እንችላለን። ልግስና በማሳየት ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስን በሚስዮናዊነት አብሮት እንዲያገለግል የጋበዘው ከመሆኑም ሌላ የስብከትና የማስተማሪያ ዘዴዎቹን አስተምሮታል። (ሥራ 16:1-3) ጳውሎስ የሰጠው ሥልጠና ጢሞቴዎስ ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪና አስተማሪ እንዲሆን ረድቶታል። (1 ቆሮ. 4:17) ጢሞቴዎስም በበኩሉ የጳውሎስን ዘዴዎች ለሌሎች አስተምሯል። w21.09 12 አን. 14-15

ሰኞ፣ የካቲት 6

ቅናትና ጠብ በመካከላችሁ [አለ]።—1 ቆሮ. 3:3

ከደቀ መዝሙሩ አጵሎስ እና ከሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሁለቱም የቅዱሳን መጻሕፍት ጥልቅ እውቀት ነበራቸው። ሁለቱም በብዙዎች ዘንድ የታወቁ ግሩም አስተማሪዎች ነበሩ። እንዲሁም ሁለቱም ብዙ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ረድተዋል። ሆኖም አንዳቸው ሌላውን እንደ ተቀናቃኝ አልተመለከቱም። (ሥራ 18:24) እንዲያውም አጵሎስ ከቆሮንቶስ ከሄደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጳውሎስ ወደዚያ እንዲመለስ ለምኖታል። (1 ቆሮ. 16:12) አጵሎስ ስጦታውን የተጠቀመበት ለትክክለኛው ዓላማ ይኸውም ምሥራቹን ለማስፋፋትና ወንድሞቹን ለማበረታታት ነው። አጵሎስ ትሑት ሰው እንደነበርም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ለምሳሌ አቂላና ጵርስቅላ “የአምላክን መንገድ ይበልጥ በትክክል” ባብራሩለት ወቅት አጵሎስ ክብሩ እንደተነካ እንደተሰማው የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። (ሥራ 18:24-28) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አጵሎስ ጥሩ ሥራ እንዳከናወነ ያውቅ ነበር። ሆኖም እንደሚቀናቀነው አልተሰማውም። ጳውሎስ ትሑት፣ ልኩን የሚያውቅና ምክንያታዊ ሰው እንደነበር ለቆሮንቶስ ጉባኤ ከሰጠው ምክር መገንዘብ ይቻላል።—1 ቆሮ. 3:4-6፤ w21.07 18 አን. 15-17

ማክሰኞ፣ የካቲት 7

ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።—ሮም 5:19

አዳምና ሔዋን የአምላክን መመሪያ የጣሱት ሆን ብለው ነው፤ በመሆኑም ከእሱ ቤተሰብ መወገድ ይገባቸዋል። ይሁንና ልጆቻቸውስ? ይሖዋ ከእነሱ መካከል ታዛዥ የሆኑት፣ በእሱ ቤተሰብ ውስጥ እንዲታቀፉ በፍቅር ተነሳስቶ ዝግጅት አደረገ። ይህን ያደረገው በአንድያ ልጁ መሥዋዕት አማካኝነት ነው። (ዮሐ. 3:16) በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት አምላክ ታማኝነታቸውን የጠበቁ 144,000 ሰዎችን ልጆቹ አድርጎ ወስዷቸዋል። (ሮም 8:15-17፤ ራእይ 14:1) በተጨማሪም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ታማኝ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ በታዛዥነት እያደረጉ ነው። እነሱም በሺው ዓመት መጨረሻ ካለው ፈተና በኋላ የአምላክ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። (መዝ. 25:14፤ ሮም 8:20, 21) አሁንም ቢሆን ፈጣሪያቸውን ይሖዋን “አባታችን” ብለው ይጠሩታል። (ማቴ. 6:9) ከሞት የሚነሱ ሰዎችም ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅባቸው የመማር አጋጣሚ ያገኛሉ። ከዚያም የይሖዋን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑት ሰዎች የእሱ ቤተሰብ አባላት ይሆናሉ። w21.08 5 አን. 10-11

ረቡዕ፣ የካቲት 8

ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲያከናውን የተሰጠው አገልግሎት የነበረ ሲሆን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይህን አገልግሎት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ነገር ቆጥሮታል። “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” ሰብኳል። (ሥራ 20:20) ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞም ይሰብክ ነበር! ለምሳሌ ያህል፣ በአቴንስ የአገልግሎት ጓደኞቹን እየጠበቀ ሳለ ምሥራቹን ለተወሰኑ ታዋቂ ሰዎች ሰብኳል፤ ይህም ግሩም ውጤት አስገኝቶለታል። (ሥራ 17:16, 17, 34) ጳውሎስ ‘ታስሮ’ በነበረበት ጊዜ እንኳ በዙሪያው ለነበሩ ሰዎች ሰብኳል። (ፊልጵ. 1:13, 14፤ ሥራ 28:16-24) ጳውሎስ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞበታል። ብዙ ጊዜ ሌሎች አብረውት እንዲያገለግሉ ይጋብዝ ነበር። ለምሳሌ በመጀመሪያ ሚስዮናዊ ጉዞው ላይ ከዮሐንስ ማርቆስ ጋር፣ በሁለተኛው ላይ ደግሞ ከጢሞቴዎስ ጋር አገልግሏል። (ሥራ 12:25፤ 16:1-4) ጳውሎስ ለእነዚህ ወንዶች ጉባኤዎችን ማደራጀት፣ እረኝነት ማድረግ እንዲሁም ውጤታማ አስተማሪ መሆን ስለሚቻልበት መንገድ ለማስተማር የተቻለውን ሁሉ እንዳደረገ ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮ. 4:17፤ w22.03 27 አን. 5-6

ሐሙስ፣ የካቲት 9

[አምላክ] ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም።—ሥራ 17:27

አንዳንዶች በፈጣሪ የማያምኑት ለምን እንደሆነ ሲገልጹ ‘የማላየውን ነገር ማመን አልችልም’ ይላሉ። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ባያዩአቸውም የሚያምኗቸው ነገሮች አሉ። የስበት ኃይልን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፤ የስበት ኃይል ባይታይም መኖሩን የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ አለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው እምነትም በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው፤ የምናምንበት ነገር “በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ” ማስረጃ አለው። (ዕብ. 11:1) ማስረጃውን ራሳችን ለመመርመር ጊዜና ጥረት ይጠይቃል፤ ብዙ ሰዎች ደግሞ ይህን ለማድረግ ተነሳሽነቱ የላቸውም። በመሆኑም አንድ ሰው ማስረጃውን ራሱ ካልመረመረ ‘አምላክ የለም’ የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ይችላል። አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ማስረጃውን ከመረመሩ በኋላ ጽንፈ ዓለምን የፈጠረው አምላክ እንደሆነ አምነዋል። መጀመሪያ ላይ ፈጣሪ የለም ብለው ያመኑት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለ ፍጥረት ስላልተማሩ ይሆናል። አሁን ግን ይሖዋን ማወቅ ችለዋል፤ በዚህም ምክንያት እሱን ወደውታል። እንደ እውነቱ ከሆነ የትምህርት ደረጃችን ምንም ይሁን ምን፣ ሁላችንም በአምላክ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር አለብን። w21.08 14 አን. 1፤ 15-16 አን. 6-7

ዓርብ፣ የካቲት 10

ይሖዋ ለሁሉም ጥሩ ነው፤ ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ይታያል።—መዝ. 145:9

ኢየሱስ፣ ይሖዋ ምሕረት ማድረግ ምን ያህል እንደሚወድ ለማሳየት ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተናግሯል። ልጁ ከቤቱ ወጥቶ “ልቅ የሆነ ሕይወት በመኖር ንብረቱን አባከነ።” (ሉቃስ 15:13) ከጊዜ በኋላ ይህ ወጣት ከኃጢአቱ ንስሐ ገባ፤ ራሱን አዋረደ እንዲሁም ወደ ቤቱ ተመለሰ። ታዲያ አባትየው ምን ያደርግ ይሆን? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “[ልጁ] ገና ሩቅ ሳለም አባቱ አየው፤ በዚህ ጊዜ አንጀቱ ተላወሰ፤ እየሮጠ ሄዶም አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” አባትየው ልጁን አላዋረደውም። ከዚህ ይልቅ ልጁን በምሕረት ይቅር በማለት በድጋሚ የቤተሰቡ አባል እንዲሆን ፈቅዶለታል። አባካኙ ልጅ የፈጸመው ኃጢአት ከባድ ነው፤ ሆኖም ንስሐ በመግባቱ አባቱ ይቅር ብሎታል። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው መሐሪ አባት ይሖዋን ይወክላል። ኢየሱስ ይህን ልብ የሚነካ ምሳሌ በመጠቀም፣ አባቱ ከልባቸው ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ አስተምሯል።—ሉቃስ 15:17-24፤ w21.10 8 አን. 4፤ 9 አን. 6

ቅዳሜ፣ የካቲት 11

አምላክ ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ . . . ለእነሱ ትኩረት [ሰጠ]።—ሥራ 15:14

በዛሬው ጊዜ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች የአምላክ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ላይ አውጥተዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ፣ ሰዎች በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ የአምላክን ስም እንዳይጠቀሙ እስከመከልከል ደርሰዋል። ለይሖዋ ስም የሚገባውን ክብር እየሰጡ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ ማን ሊክድ ይችላል? ከየትኛውም ሃይማኖት ይበልጥ የአምላክን ስም ለማሳወቅ ጥረት እያደረግን ነው! በዚህ ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ከሚለው መጠሪያችን ጋር ተስማምተን ለመኖር የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። (ኢሳ. 43:10-12) አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ከ240 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች አዘጋጅተናል፤ ይህ ትርጉም የአምላክን ስም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ባወጡባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ መልሶ አስገብቷል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋን ስም የሚያሳውቁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች እናዘጋጃለን! w21.10 20-21 አን. 9-10

እሁድ፣ የካቲት 12

ከወንድሞችህ መካከል አንዱ . . . ድሃ ቢሆን በድሃው ወንድምህ ላይ ልብህ አይጨክንበት ወይም እጅህን አትጠፍበት።—ዘዳ. 15:7

የተቸገሩ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ስንረዳ ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። ይሖዋ ድሆችን ለሚረዱ እስራኤላውያን ወሮታቸውን እንደሚከፍል ቃል ገብቶላቸዋል። (ዘዳ. 15:10) ለተቸገረ የእምነት ባልንጀራችን የምናደርገውን እርዳታ ይሖዋ ለእሱ እንደተሰጠ ስጦታ አድርጎ ይቆጥረዋል። (ምሳሌ 19:17) ለምሳሌ ያህል፣ በፊልጵስዩስ የነበሩት ክርስቲያኖች ጳውሎስ እስር ቤት ሳለ ስጦታ ልከውለት ነበር፤ ጳውሎስ ይህ ስጦታ “ተቀባይነት ያለው መሥዋዕትና አምላክ ደስ የሚሰኝበት” እንደሆነ ተናግሯል። (ፊልጵ. 4:18) በጉባኤያችሁ ውስጥ ስላሉ ወንድሞችና እህቶች በማሰብ ‘የእኔ እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው አለ?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ። ይሖዋ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን፣ ችሎታችንንና ቁሳዊ ሀብታችንን የተቸገሩትን ለመርዳት ስንጠቀምበት ይደሰታል። እንዲህ ያለውን እርዳታ እንደ አምልኳችን ክፍል አድርጎ ይመለከተዋል። (ያዕ. 1:27) እውነተኛው አምልኮ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ሆኖም ከባድ አይደለም። (1 ዮሐ. 5:3) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይህን የምናደርገው ለይሖዋ እንዲሁም ለወንድሞችና እህቶች ባለን ፍቅር ተነሳስተን ነው። w22.03 24 አን. 14-15

ሰኞ፣ የካቲት 13

በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን ያወጣል።—ማቴ. 5:45

ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ርኅራኄ ማሳየት እንድንችል በመጀመሪያ፣ ስላጋጠማቸው ችግር ማሰብ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እህት ከባድ የጤና ችግር ይኖርባት ይሆናል። ስላለባት ችግር ብዙ ጊዜ ባታወራም በአንዳንድ መንገዶች እርዳታ ቢደረግላት ደስ እንደሚላት ጥያቄ የለውም። ምግብ በማዘጋጀት ወይም ቤት በማጽዳት ልንረዳት እንችል ይሆን? አሊያም ደግሞ አንድ ወንድም ከሥራው ተፈናቅሎ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ማንነታችንን ሳናሳውቅ የተወሰነ ገንዘብ ብንሰጠው ሌላ ሥራ እስኪያገኝ ድረስ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ሊረዳው ይችላል። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ርኅራኄ ለማሳየት እነሱ እስኪጠይቁን መጠበቅ አያስፈልገንም። ልክ እንደ ይሖዋ ቅድሚያውን ወስደን ልንረዳቸው እንችላለን። ይሖዋ በየቀኑ ፀሐይ ያወጣልናል፤ እንዲህ እንዲያደርግልን መጠየቅ እንኳ አያስፈልገንም። ደግሞም የፀሐይ ሙቀት የሚጠቅመው አመስጋኝ የሆኑ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሰው ነው። ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ማሟላቱ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው ቢባል አትስማማም? ይሖዋ በጣም ደግና ለጋስ በመሆኑ በእጅጉ እንወደዋለን! w21.09 22-23 አን. 12-13

ማክሰኞ፣ የካቲት 14

ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤ አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።—መዝ. 86:5

የአምላክ ታማኝ ፍቅር ይቅር ባይ እንዲሆን ያነሳሳዋል። ይሖዋ አንድ ኃጢአተኛ ከልቡ ንስሐ እንደገባና በኃጢአት ጎዳና ላይ መመላለሱን እንዳቆመ ሲመለከት ታማኝ ፍቅሩ ግለሰቡን ይቅር እንዲለው ያነሳሳዋል። መዝሙራዊው ዳዊት ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ ለበደላችን የሚገባውንም ብድራት አልከፈለንም።” (መዝ. 103:8-11) ዳዊት የሕሊና ወቀሳ ምን ያህል ከባድ ሸክም እንደሆነ ከራሱ ተሞክሮ ያውቃል። ሆኖም ዳዊት፣ ይሖዋ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ እንደሆነም ተመልክቷል። ይሖዋ ይቅር እንዲል የሚያነሳሳው ምንድን ነው? መልሱን በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እናገኛለን። ዳዊት በጸሎቱ ላይ እንደገለጸው ይሖዋ ይቅር የሚለው እሱን ለሚጠሩ ሁሉ የሚያሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን ስለሌለው ነው። ኃጢአት ስንፈጽም የጸጸት ስሜት ቢሰማን ተገቢ ነው፤ እንዲያውም ይህ ስሜት ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ንስሐ እንድንገባና ስህተታችንን ለማረም እርምጃ እንድንወስድ ያነሳሳናል። w21.11 5 አን. 11-12

ረቡዕ፣ የካቲት 15

በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ።—ማቴ. 6:9

ይሖዋ ስሙን ይወደዋል፤ እንዲሁም ሁላችንም ስሙን እንድናከብረው ይፈልጋል። (ኢሳ. 42:8) ይሁንና ላለፉት 6,000 ዓመታት ገደማ የይሖዋ መልካም ስም ነቀፋ ሲደርስበት ቆይቷል። (መዝ. 74:10, 18, 23) የአምላክ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ነቀፋ የተሰነዘረበት ዲያብሎስ (“ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም አለው) አዳምና ሔዋን የሚያስፈልጋቸውን ነገር አምላክ እንደከለከላቸው በገለጸበት ጊዜ ነው። (ዘፍ. 3:1-5) ከዚያን ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ‘የሰው ልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ነፍጓቸዋል’ የሚል የሐሰት ክስ ሲሰነዘርበት ቆይቷል። ኢየሱስ በአባቱ ስም ላይ እየተሰነዘረ ያለው ነቀፋ አሳስቦት ነበር። ሰማይንና ምድርን የመግዛት መብት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ ደግሞም የእሱ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ ነው። (ራእይ 4:11) ይሁን እንጂ ዲያብሎስ መላእክትንና ሰዎችን በማሳት አምላክ የመግዛት መብት እንደሌለው እንዲያስቡ ለማድረግ ሞክሯል። በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳው ጥያቄ በቅርቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መልስ ያገኛል። በምድር ላይ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ማስፈን የሚችለው የይሖዋ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ሲረጋገጥ የአምላክ ሉዓላዊነት ትክክለኛ እንደሆነ በግልጽ ይታያል። w21.07 9 አን. 5-6

ሐሙስ፣ የካቲት 16

በይሖዋ ሐሴት አደርጋለሁ፤ አዳኜ በሆነውም አምላክ እደሰታለሁ።—ዕን. 3:18

አንድ የቤተሰብ ራስ ለሚስቱና ለልጆቹ በቂ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማቅረብ እንደሚፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። የኢኮኖሚ ችግር አጋጥሟችኋል? ከሆነ ሁኔታው ከባድ እንደሚሆንባችሁ ምንም ጥያቄ የለውም። ያላችሁበት ሁኔታ ተፈታታኝ ቢሆንም አጋጣሚውን እምነታችሁን ለማጠናከር ተጠቀሙበት። ወደ ይሖዋ ጸልዩ፤ በማቴዎስ 6:25-34 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስን ቃላት አንብቡ፤ እንዲሁም አሰላስሉባቸው። በተጨማሪም በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ለሚጠመዱ ሰዎች ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው በሚያረጋግጡ በዘመናችን የተገኙ ተሞክሮዎች ላይ አሰላስሉ። (1 ቆሮ. 15:58) እንዲህ ማድረጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ከእናንተ ጋር ተመሳሳይ ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች እንደረዳቸው ሁሉ እናንተንም እንደሚረዳችሁ ይበልጥ እርግጠኛ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል። ይሖዋ ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል፤ የሚያስፈልጋችሁን ነገር እንዴት እንደሚያሟላላችሁም ያውቃል። በሕይወታችሁ ውስጥ የይሖዋን እርዳታ ስትመለከቱ እምነታችሁ ይጠናከራል፤ ይህም ወደፊት የሚያጋጥሟችሁን ይበልጥ ከባድ የሆኑ ፈተናዎች በጽናት እንድትቋቋሙ ይረዳችኋል። w21.11 20 አን. 3፤ 21 አን. 6

ዓርብ፣ የካቲት 17

ማንም ኃጢአት ቢሠራ . . . በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም . . . ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—1 ዮሐ. 2:1

የቤዛው ትምህርት የብዙ ክርስቲያኖችን እምነት አጠናክሮላቸዋል። በመሆኑም ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም መስበካቸውን ቀጥለዋል፤ እንዲሁም በሕይወታቸው ውስጥ ያጋጠሟቸውን የተለያዩ ፈተናዎች ተቋቁመው እስከ ዕድሜያቸው መጨረሻ ጸንተዋል። እስቲ የሐዋርያው ዮሐንስን ምሳሌ እንመልከት። ስለ ክርስቶስና ስለ ቤዛው የሚገልጸውን እውነት ምናልባትም ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በታማኝነት ሰብኳል። ዮሐንስ በ90ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ በነበረበት ወቅት ለሮም መንግሥት ስጋት እንደሚፈጥር ስለተጠረጠረ በጳጥሞስ ደሴት ላይ ታስሮ ነበር። ጥፋቱ ምን ነበር? ‘ስለ አምላክ መናገሩና ስለ ኢየሱስ መመሥከሩ’ ነው። (ራእይ 1:9) ዮሐንስ እምነትና ጽናት በማሳየት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው መጻሕፍት ላይ ለኢየሱስ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም ለቤዛው ያለውን አድናቆት ገልጿል። በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ስለ ቤዛው ወይም ቤዛው ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች ከ100 ጊዜ በላይ ጠቅሷል። (1 ዮሐ. 2:2) ዮሐንስ ለቤዛው ጥልቅ አድናቆት እንደነበረው በግልጽ ማየት ይቻላል። w21.04 17 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ የካቲት 18

መስማት የተሳነውን አትርገም ወይም በዓይነ ስውሩ ፊት እንቅፋት አታስቀምጥ።—ዘሌ. 19:14

ይሖዋ፣ ሕዝቡ ለአካል ጉዳተኞች አሳቢነት እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸው ነበር። ለምሳሌ እስራኤላውያን መስማት የተሳነውን እንዳይረግሙ ታዘው ነበር። መርገም የሚለው ሐሳብ በግለሰቡ ላይ ዛቻ መሰንዘርን ወይም መጥፎ ነገር እንዲደርስበት መመኘትን ያመለክታል። መስማት በተሳነው ሰው ላይ እንዲህ ማድረግ ምንኛ አሳፋሪ ነው። ግለሰቡ እየተወራ ያለውን ነገር ስለማይሰማ ለራሱ መከላከያ ማቅረብ አይችልም። የአምላክ አገልጋዮች በዘሌዋውያን 19:14 ላይ “በዓይነ ስውሩ ፊት እንቅፋት አታስቀምጥ” የሚል መመሪያም ተሰጥቷቸዋል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው “በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ የአካል ጉዳተኞች መጠቀሚያ ይደረጉ እንዲሁም ጥቃት ይሰነዘርባቸው ነበር።” ምናልባትም አንዳንዶች በክፋት ተነሳስተው ወይም ሌሎችን ለማሳቅ ብለው በዓይነ ስውራን ፊት እንቅፋት ያስቀምጡ ይሆናል። ይህ እንዴት ያለ ጭካኔ ነው! ይሖዋ ለሕዝቡ እንዲህ ያለ መመሪያ በመስጠት፣ ለአካል ጉዳተኞች ርኅራኄ እንዲያሳዩ እንደሚጠብቅባቸው አስተምሯቸዋል። w21.12 8-9 አን. 3-4

እሁድ፣ የካቲት 19

ያዕቆብም እጅግ ፈራ፤ በጭንቀትም ተዋጠ።—ዘፍ. 32:7

ያዕቆብ ወንድሙ አሁንም ቂም ይዞበት ሊሆን እንደሚችል ስላሰበ ተጨንቆ ነበር። ስለዚህ ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ አጥብቆ ጸለየ። ከዚያም ለኤሳው በርከት ያለ ስጦታ ላከለት። (ዘፍ. 32:9-15) በመጨረሻም ተለያይተው የነበሩት ወንድማማቾች ፊት ለፊት ሲገናኙ ያዕቆብ ቅድሚያውን ወስዶ ለኤሳው አክብሮት አሳየው። ለኤሳው አንዴ ወይም ሁለቴ ሳይሆን ሰባት ጊዜ ሰገደለት! ያዕቆብ ትሕትና እና አክብሮት በማሳየት ከወንድሙ ጋር ታረቀ። (ዘፍ. 33:3, 4) ያዕቆብ ከወንድሙ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ካደረገው ዝግጅትና ወንድሙን ሲያገኘው ከወሰደው እርምጃ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ያዕቆብ ይሖዋ እንዲረዳው በትሕትና ለምኗል። ከዚያም ከወንድሙ ጋር እርቅ ለመፍጠር አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዷል። ያዕቆብ ኤሳውን ሲያገኘው ‘ጥፋተኛው ማን ነው?’ በሚለው ጉዳይ ላይ ከእሱ ጋር ሙግት አልገጠመም። የያዕቆብ ዓላማ ከወንድሙ ጋር መታረቅ ነበር። እኛስ የያዕቆብን ምሳሌ መከተል እንችል ይሆን?—ማቴ. 5:23, 24፤ w21.12 25 አን. 11-12

ሰኞ፣ የካቲት 20

አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል።—1 ዮሐ. 3:20

ኢየሱስ ኃጢአትህን ለማስተሰረይ ሲል እንደሞተ ስታስብ ‘እኔ እንዲህ ያለ ክብር የሚገባኝ ሰው አይደለሁም’ የሚል ስሜት ይፈጠርብህ ይሆናል። እንዲህ የሚሰማህ ለምን ሊሆን ይችላል? ፍጹም ያልሆነው ልባችን እንደማንረባና ማንም ሊወደን እንደማይችል እንድናስብ በማድረግ ሊያታልለን ይችላል። (1 ዮሐ. 3:19) እንዲህ ያለ ስሜት ሲፈጠርብን “አምላክ ከልባችን ይልቅ ታላቅ” እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። የሰማዩ አባታችን ፍቅርና ምሕረት፣ በልባችን ውስጥ ሊያድር ከሚችለው ከየትኛውም አሉታዊ ስሜት የበለጠ ኃይል አለው። ይሖዋ ለእኛ ያለውን አመለካከት ለመቀበል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለዚህ እንዲረዳን አዘውትረን ቃሉን ማንበብ፣ ወደ እሱ መጸለይ እንዲሁም ከታማኝ ሕዝቦቹ ጋር መቀራረብ ያስፈልገናል። እነዚህን ነገሮች ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የይሖዋ ግሩም ባሕርያት ይበልጥ ግልጽ ሆነው እንዲታዩን ያደርጋል። እሱ ምን ያህል እንደሚወደን እንገነዘባለን። በየቀኑ በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላችን አስተሳሰባችንንና ምኞታችንን “ለማቅናት” ስለሚረዳን ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ያደርጋል።—2 ጢሞ. 3:16፤ w21.04 23-24 አን. 12-13

ማክሰኞ፣ የካቲት 21

ወደ አምላክ እጮኻለሁ፤ እሱም ይሰማኛል።—መዝ. 77:1

ጠንካራ እምነት ማዳበር እንዲሁ እውቀት ከመሰብሰብ ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። በተማርነው ነገር ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። የመዝሙር 77 ጸሐፊ ያጋጠመውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። እሱና ወገኖቹ እስራኤላውያን የይሖዋን ሞገስ እንዳጡ ስለተሰማው በጣም ተጨንቆ ነበር። ጭንቀቱ እንቅልፍ ነስቶት ነበር። (ከቁጥር 2-8) ታዲያ ምን አደረገ? ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “በሥራዎችህም ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ፤ ያከናወንካቸውንም ነገሮች አውጠነጥናለሁ።” (ቁጥር 12) እርግጥ ነው፣ ይህ መዝሙራዊ ይሖዋ በቀደመው ጊዜ ለሕዝቡ ያደረጋቸውን ነገሮች በደንብ ያውቅ ነበር፤ ሆኖም በተጨነቀበት ወቅት “አምላክ ሞገሱን ማሳየት ረስቷል? ወይስ ቁጣው ምሕረት ከማሳየት እንዲቆጠብ አድርጎታል?” ብሎ አስቦ ነበር። (ቁጥር 9) መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ባከናወናቸው ነገሮችና በቀደሙት ዘመናት ምሕረትና ርኅራኄ ባሳየበት መንገድ ላይ አሰላሰለ። (ቁጥር 11) ውጤቱ ምን ሆነ? መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ሕዝቡን እንደማይተው ያለው እምነት ተጠናከረ። (ቁጥር 15) w22.01 30-31 አን. 17-18

ረቡዕ፣ የካቲት 22

በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸው።—ሉቃስ 20:38

ይሖዋ በሞት ያንቀላፉ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን በተመለከተ ምን ይሰማዋል? እንደገና ሊያያቸው ይናፍቃል! (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ወዳጁን አብርሃምን ምን ያህል እንደሚናፍቀው ማሰብ ትችላለህ? (ያዕ. 2:23) “ፊት ለፊት” ያነጋግረው የነበረውን ሙሴንስ? (ዘፀ. 33:11) ይሖዋ ዳዊትና ሌሎቹ ዘማሪዎች ማራኪ የሆኑ የውዳሴ መዝሙሮችን ሲዘምሩ ለመስማት ምንኛ ይጓጓ ይሆን! (መዝ. 104:33) እነዚህ የአምላክ ወዳጆች በሞት ቢያንቀላፉም ይሖዋ አልረሳቸውም። (ኢሳ. 49:15) ስለ እነሱ እያንዳንዱን ነገር ያስታውሳል። አንድ ቀን ከሞት ያስነሳቸዋል፤ በዚያ ጊዜ፣ ለእሱ የሚያቀርቡትን ልባዊ ጸሎት ይሰማል፤ አምልኳቸውንም ይቀበላል። የምትወደውን ሰው ሞት ነጥቆህ ከሆነ ይህ ሐሳብ እንደሚያጽናናህ ተስፋ እናደርጋለን። በኤደን ዓመፅ በተነሳበት ወቅት ይሖዋ ሁሉ ነገር የሚስተካከልበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ሁኔታዎች እየተባባሱ እንደሚሄዱ አውቆ ነበር። ይሖዋ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የተስፋፋውን ክፋት፣ የፍትሕ መጓደልና ዓመፅ ይጠላል። w21.07 10 አን. 11፤ 12 አን. 12

ሐሙስ፣ የካቲት 23

በተግባርና በእውነት [እንዋደድ]።—1 ዮሐ. 3:18

ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መውደዳችን ለቤዛው አድናቆት እንዳለን ያሳያል። እንዴት? ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ የሰጠው ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችንም ጭምር ነው። ኢየሱስ ለእነሱ ሲል ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑ በጣም እንደሚወዳቸው ያሳያል። (1 ዮሐ. 3:16-18) ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችለው እነሱን በምንይዝበት መንገድ ነው። (ኤፌ. 4:29, 31 እስከ 5:2) ለምሳሌ፣ ሲታመሙ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥማቸው አሊያም ሌላ ከባድ መከራ ሲደርስባቸው እንረዳቸዋለን። ሆኖም አንድ የእምነት ባልንጀራችን በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ቅር ብንሰኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? አንድ የእምነት ባልንጀራህ ቢበድልህ ቂም ትይዛለህ? (ዘሌ. 19:18) ከሆነ የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ አድርግ፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላ. 3:13) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ባልን ቁጥር፣ ለቤዛው ልባዊ አድናቆት እንዳለን ለሰማያዊው አባታችን እያሳየነው ነው። w21.04 18 አን. 12-13

ዓርብ፣ የካቲት 24

የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።—1 ጴጥ. 4:10

በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ነገር እናከናውን እንዲሁም ብዙዎች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ እንረዳ ይሆናል። ያም ቢሆን በሥራችን ስኬታማ መሆን የቻልነው ይሖዋ ስለባረከን ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን። ከአጵሎስና ከሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ ሌላም ትምህርት እናገኛለን፤ በጉባኤ ውስጥ ያለን ኃላፊነት በጨመረ መጠን ሰላም ለማስፈን ማድረግ የምንችለው ነገርም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። የተሾሙ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ጥረት ሲያደርጉ ደስ ይለናል፤ ይህን የሚያደርጉት የሚሰጡት ምክር በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ እንዲሁም በእነሱ ላይ ሳይሆን አርዓያችን በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ እንድናተኩር በመርዳት ነው። (1 ቆሮ. 4:6, 7) ሁላችንም ከአምላክ ያገኘነው ተሰጥኦ ወይም ችሎታ አለን። እርግጥ የምናበረክተው ድርሻ ትንሽ እንደሆነ ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ለአንድ ልብስ ጥንካሬ እያንዳንዱ ስፌት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሁሉ እያንዳንዳችን የምናከናውነው አነስተኛ ተግባርም ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንግዲያው የፉክክር መንፈስን ከውስጣችን ነቅለን ለማውጣት ጥረት እናድርግ። በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ኤፌ. 4:3፤ w21.07 19 አን. 18-19

ቅዳሜ፣ የካቲት 25

ወንድምሽ ይነሳል።—ዮሐ. 11:23

በሞት ያጣሃቸውን የምትወዳቸውን ሰዎች እንደገና እንደምታገኛቸው እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ኢየሱስ በሐዘን ልባቸው የተሰበረ ወዳጆቹን ሲያጽናና እንባውን ማፍሰሱ ትንሣኤ በጉጉት የሚጠብቀው ነገር እንደሆነ ያረጋግጥልናል! (ዮሐ. 11:35) ሐዘን የደረሰባቸውን መደገፍ ትችላለህ። ኢየሱስ ከማርታና ከማርያም ጋር አልቅሷል፤ ከዚህም በተጨማሪ አዳምጧቸዋል እንዲሁም በሚያጽናና መንገድ አነጋግሯቸዋል። (ዮሐ. 11:25-27) እኛም ሐዘን ለደረሰባቸው ይህን ማድረግ እንችላለን። በአውስትራሊያ የሚኖር ዳን የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴን በሞት ካጣሁ በኋላ የሌሎች ድጋፍ አስፈልጎኝ ነበር። ብዙ ባለትዳሮች ቀንም ሆነ ማታ ጊዜያቸውን ሰጥተው ያዳምጡኝ ነበር። ሐዘኔን እንድገልጽ አጋጣሚ ሰጥተውኛል፤ ማልቀሴም አላሳፈራቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ተግባራዊ እርዳታ ለማድረግ ራሳቸውን ያቀርቡ ነበር። ለምሳሌ እኔ እንደማልችል በሚሰማኝ ጊዜ መኪናዬን ያጥቡልኝ፣ አስቤዛ ይገዙልኝ እንዲሁም ምግብ ያበስሉልኝ ነበር። ደግሞም ብዙ ጊዜ አብረውኝ ይጸልዩ ነበር። እውነተኛ ወዳጆች እንዲሁም ‘ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም’ ሆነውልኛል።”—ምሳሌ 17:17፤ w22.01 16 አን. 8-9

እሁድ፣ የካቲት 26

ሕይወት የሚያስገኝ ወቀሳን የሚሰማ፣ በጥበበኛ ሰዎች መካከል ይኖራል።—ምሳሌ 15:31

ይሖዋ የሚመኝልን የሚጠቅመንን ነገር ነው። (ምሳሌ 4:20-22) በቃሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወይም በአንድ የጎለመሰ የእምነት ባልንጀራችን ተጠቅሞ ሲመክረን ፍቅሩን እየገለጸልን ነው። (ዕብ. 12:9, 10) በምክሩ ላይ እንጂ በአሰጣጡ ላይ አታተኩሩ። አንዳንድ ጊዜ ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ችግር እንዳለው ይሰማን ይሆናል። እርግጥ፣ ምክር የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በተቻለ መጠን የሚመከረው ሰው ምክሩን መቀበል ቀላል እንዲሆንለት ሊያደርግ ይገባል። (ገላ. 6:1) ተመካሪዎቹ እኛ ከሆንን ግን ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ባያስደስተንም እንኳ በመልእክቱ ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ ነው። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ምክሩ የተሰጠበትን መንገድ ባልወደውም እንኳ ከተናገረው ነገር የማገኘው ትምህርት ይኖር ይሆን? ምክር ሰጪው ያሉትን ድክመቶች በማለፍ ከምክሩ ጥቅም ማግኘት እችል ይሆን?’ ምንም ዓይነት ምክር ቢሰጠን ከምክሩ ጥቅም ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ነው። w22.02 12 አን. 13-14

ሰኞ፣ የካቲት 27

የይሖዋ ማሳሰቢያ አስተማማኝ ነው፤ ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል።—መዝ. 19:7

ይሖዋ መጥፎ አስተሳሰቦችንና ልማዶችን ለማስወገድ ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅብን ያውቃል። (መዝ. 103:13, 14) ሆኖም በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት ማንነታችንን ለመቀየር የሚያስፈልገንን ጥበብ፣ ብርታትና እርዳታ ይሰጠናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ ራስህን በደንብ መርምር። የአምላክ ቃል እንደ መስታወት ነው፤ አስተሳሰብህን፣ አነጋገርህንና ድርጊትህን ለመገምገም ይረዳሃል። (ያዕ. 1:22-25) ይሖዋም ቢሆን ሁልጊዜ አንተን ለመርዳት ዝግጁ ነው። ልብህን ስለሚያውቅ ከማንም በተሻለ ሊረዳህ የሚችለው እሱ ነው። (ምሳሌ 14:10፤ 15:11) ስለዚህ ወደ እሱ የመጸለይና ቃሉን በየቀኑ የማጥናት ልማድ አዳብር። የይሖዋ መሥፈርቶች እንደሚበጁህ ራስህን አሳምን። ይሖዋ የሚጠይቀን ነገር ሁሉ ለእኛው ጥቅም ነው። የእሱን መሥፈርቶች የሚከተሉ ሁሉ ለራሳቸው አክብሮት ይኖራቸዋል፣ ሕይወታቸው ትርጉም ያለው ይሆናል እንዲሁም እውነተኛ ደስታ ያገኛሉ።—መዝ. 19:8-11፤ w22.03 4 አን. 8-10

ማክሰኞ፣ የካቲት 28

የመከላከያ ግንቦቿን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ለመጪዎቹ ትውልዶች መናገር ትችሉ ዘንድ፣ የማይደፈሩ ማማዎቿን በሚገባ አጢኑ።—መዝ. 48:13

የአምልኮ ቦታዎችን ስንገነባና ስንጠግን ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የማደሪያ ድንኳኑንና ከዚያ ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን መሥራት ‘ቅዱስ ሥራ’ እንደሆነ ይናገራል። (ዘፀ. 36:1, 4) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ የስብሰባ አዳራሾችንና ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን የመገንባቱን ሥራ እንደ ቅዱስ አገልግሎት ይቆጥረዋል። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሥራ በመካፈል ሰፋ ያለ ጊዜ ያሳልፋሉ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለመንግሥቱ ሥራ የሚያበረክቱትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እናደንቃለን። እርግጥ ነው፣ በስብከቱ ሥራም ይካፈላሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ አቅኚ የመሆን ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። የጉባኤ ሽማግሌዎች እነዚህ ትጉ ወንድሞችና እህቶች ብቃቱን እስካሟሉ ድረስ አቅኚ ሆነው እንዲያገለግሉ ከመሾም ወደኋላ ባለማለት የግንባታ ሥራዎችን እንደሚደግፉ ማሳየት ይችላሉ። የግንባታ ሙያ ኖረንም አልኖረን ሁላችንም ሕንፃዎቹ ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆኑና ጥሩ ይዞታ ላይ እንዲገኙ በማድረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። w22.03 22 አን. 11-12

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ