ሚያዝያ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 1
አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል።—ዮሐ. 3:16
ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን በፈቃደኝነት መስጠቱ ታላቅ የፍቅር መገለጫ ነው። (ዮሐ. 15:13) ይሖዋ እና ኢየሱስ የዋሉልንን ውለታ መቼም ቢሆን መክፈል አንችልም። ሆኖም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን አመስጋኝነታችንን ማሳየት እንችላለን። (ቆላ. 3:15) ቅቡዓኑ አስደናቂ ተስፋ እንዲያገኙ መንገድ ስለከፈተላቸው ቤዛውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። (ማቴ. 20:28) በክርስቶስ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት መሠረት በማድረግ ይሖዋ ጻድቃን ናችሁ ብሏቸዋል፤ ልጆቹ አድርጎም ወስዷቸዋል። (ሮም 5:1፤ 8:15-17, 23) ሌሎች በጎችም ለቤዛው አድናቆት አላቸው። በፈሰሰው የክርስቶስ ደም ላይ እምነት ስላላቸው በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም አግኝተዋል፤ እንዲሁም “ታላቁን መከራ አልፈው” በሕይወት የመኖር ተስፋ አላቸው። (ራእይ 7:13-15) ሁለቱም ቡድኖች ለቤዛው ያላቸውን አድናቆት ማሳየት የሚችሉበት አንዱ መንገድ በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት ነው። w22.01 23 አን. 14-15
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 10) ማቴዎስ 21:18, 19፤ 21:12, 13፤ ዮሐንስ 12:20-50
እሁድ፣ ሚያዝያ 2
ክርስቶስ . . . ዋጅቶናል።—ገላ. 3:13
ኢየሱስን ያስጨነቀው የተከሰሰበት ወንጀል ነው። ‘አምላክን ተሳድቧል’ በሌላ አባባል ‘ለአምላክም ሆነ ለስሙ አክብሮት የለውም’ የሚል የሐሰት ክስ ተሰንዝሮበታል። (ማቴ. 26:64-66) በዚህ ክስ እንደሚወነጀል ማወቁ በጣም ስላስጨነቀው አባቱ እንዲህ ካለው የውርደት አሟሟት እንዲያድነው ጠይቆ ነበር። (ማቴ. 26:38, 39, 42) ኢየሱስ አይሁዳውያንን ከእርግማን ነፃ ለማውጣት በእንጨት ላይ መሰቀል ነበረበት። (ገላ. 3:10) አይሁዳውያን የአምላክን ሕግ ለመጠበቅ ቃል ቢገቡም ይህን ሳያደርጉ ቀርተዋል። በመሆኑም የኃጢአተኛው የአዳም ዘሮች መሆናቸው ካስከተለባቸው ኩነኔ በተጨማሪ ሌላ እርግማን ደረሰባቸው። (ሮም 5:12) የአምላክ ሕግ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት የሠራ ሰው ሊገደል እንደሚገባ ይገልጻል። ግለሰቡ ከተገደለ በኋላ አስከሬኑ እንጨት ላይ ሊሰቀል ይችላል። (ዘዳ. 21:22, 23፤ 27:26) በመሆኑም ኢየሱስ እንጨት ላይ መሰቀሉ እሱን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነው ብሔርም እንኳ ከእሱ መሥዋዕት ተጠቃሚ እንዲሆን አጋጣሚ ከፍቷል። w21.04 16 አን. 5-6
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 11) ማቴዎስ 21:33-41፤ 22:15-22፤ 23:1-12፤ 24:1-3
ሰኞ፣ ሚያዝያ 3
ሕይወቴን . . . አሳልፌ [እሰጣታለሁ]።—ዮሐ. 10:17
ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ምን እንዳሳለፈ በዓይነ ሕሊናችን ለመሣል እንሞክር። የሮም ወታደሮች ያለአንዳች ርኅራኄ ደበደቡት። (ማቴ. 26:52-54፤ ዮሐ. 18:3፤ 19:1) ሰውነትን በሚተለትል አለንጋ ገረፉት። ከዚያም በቆሰለው ጀርባው ከባድ እንጨት ተሸክሞ እንዲሄድ አደረጉ። ኢየሱስ ከባዱን እንጨት እየጎተተ ወደሚሰቀልበት ቦታ ማዝገም ጀመረ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን እንጨቱን መሸከም ስላቃተው ወታደሮቹ በአካባቢው የነበረን አንድ ሰው ጠርተው እንጨቱን እንዲሸከምለት አስገደዱት። (ማቴ. 27:32) ኢየሱስ ወደሚሰቀልበት ቦታ ሲደርስ ወታደሮቹ እጆቹንና እግሮቹን በሚስማር እንጨት ላይ ቸነከሯቸው። እንጨቱ ቀጥ ብሎ እንዲቆም ሲደረግ የሰውነቱ ክብደት ሚስማሮቹ በገቡባቸው ቦታዎች ላይ ስለሚያርፍ ሥቃዩ በጣም ይበረታል። ወዳጆቹ በሐዘን ተውጠዋል፤ እናቱም እያለቀሰች ነው፤ የሃይማኖት መሪዎቹ ግን በኢየሱስ ላይ እያፌዙበት ነው። (ሉቃስ 23:32-38፤ ዮሐ. 19:25) ሰዓታት ባለፉ ቁጥር ሥቃዩ እየበረታበት ሄደ። በዚህ ሁኔታ ተሰቅሎ መቆየቱ በልቡና በሳንባው ላይ ከፍተኛ ጫና ስላሳደረ መተንፈስ እንኳ እየከበደው መጣ። ትንፋሹ ቀጥ ሊል ሲል በድል አድራጊነት የመጨረሻውን ጸሎት አቀረበ። ከዚያም ራሱን ዘንበል አድርጎ ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ። (ማር. 15:37፤ ሉቃስ 23:46፤ ዮሐ. 10:18፤ 19:30) በእርግጥም የኢየሱስ አሟሟት የሚያዋርድና በሥቃይ የተሞላ ነበር! w21.04 16 አን. 4
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 12) ማቴዎስ 26:1-5, 14-16፤ ሉቃስ 22:1-6
የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4
ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።—ሉቃስ 22:19
ኢየሱስ ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያቱ ስለ ሁለት ቃል ኪዳኖች ማለትም ስለ አዲሱ ቃል ኪዳን እና ስለ መንግሥት ቃል ኪዳን ገለጸላቸው። (ሉቃስ 22:20, 28-30) እነዚህ ቃል ኪዳኖች ሐዋርያቱና የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ሰዎች በሰማይ ነገሥታትና ካህናት እንዲሆኑ መንገድ ከፍተዋል። (ራእይ 5:10፤ 14:1) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ መካፈል የሚችሉት በእነዚህ ሁለት ቃል ኪዳኖች የታቀፉት ቅቡዓን ቀሪዎች ብቻ ናቸው። ይሖዋ አስደናቂ ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ በሰማይ የማይሞትና የማይበሰብስ ሕይወት ያገኛሉ። እንዲሁም ክብር ከተጎናጸፈው ከኢየሱስ ክርስቶስና ከሌሎቹ 144,000ዎች ጋር ከሁሉ በላይ ደግሞ ራሱ ይሖዋ ባለበት እሱን የማገልገል መብት ይኖራቸዋል! (1 ቆሮ. 15:51-53፤ 1 ዮሐ. 3:2) ቅቡዓኑ፣ እስከ ዕለተ ሞታቸው በታማኝነት መጽናት እንዳለባቸው ያውቃሉ።—2 ጢሞ. 4:7, 8፤ w22.01 21 አን. 4-5
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 13) ማቴዎስ 26:17-19፤ ሉቃስ 22:7-13 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ማቴዎስ 26:20-56
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 5
ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።—ሉቃስ 23:43
ከኢየሱስ ግራ እና ቀኝ የተሰቀሉ ሁለት ወንጀለኞች ነበሩ። (ሉቃስ 23:40, 41) አንደኛው ኢየሱስን “ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” አለው። (ሉቃስ 23:42) ኢየሱስ አባቱ መሐሪ መሆኑን ስላወቀ በሞት አፋፍ ላይ ላለው ለዚህ ወንጀለኛ ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነግሮታል። (መዝ. 103:8፤ ዕብ. 1:3) እኛም ለፈጸምነው ኃጢአት ከልብ ንስሐ ከገባንና በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም አማካኝነት የኃጢአት ይቅርታ እንደምናገኝ እምነት ካለን ይሖዋ ይቅር ሊለንና ምሕረት ሊያሳየን ፈቃደኛ ነው። (1 ዮሐ. 1:7) አንዳንዶች ይሖዋ ጨርሶ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ይሰማቸው ይሆናል። አንተም አልፎ አልፎ እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ እስቲ ይህን ለማሰብ ሞክር፦ ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ አብሮት ለተሰቀለው ወንጀለኛ ምሕረት አሳይቶታል። እምነቱን በተግባር ለማሳየት አጋጣሚ ያላገኘው ይህ ወንጀለኛ ምሕረት ከተደረገለት፣ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹማ ምሕረት እንደሚያደርግላቸው ምንም ጥያቄ የለውም!—መዝ. 51:1፤ 1 ዮሐ. 2:1, 2፤ w21.04 9 አን. 5-6
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ማቴዎስ 27:1, 2, 27-37
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 6
ኢየሱስ . . . “ተፈጸመ!” አለ።—ዮሐ. 19:30
ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ ብዙ ነገሮችን ፈጽሟል። አንደኛ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አረጋግጧል። ኢየሱስ፣ አንድ ፍጹም ሰው ሰይጣን ምንም ዓይነት መከራ ቢያደርስበት ንጹሕ አቋሙን ሙሉ በሙሉ መጠበቅ እንደሚችል አሳይቷል። ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። የእሱ መሥዋዕታዊ ሞት ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በአምላክ ፊት እንደ ጻድቅ እንዲቆጠሩ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ አስገኝቶላቸዋል። ሦስተኛ፣ ኢየሱስ የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል፤ እንዲሁም የአባቱ ስም ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን አድርጓል። እኛም እያንዳንዱን ቀን፣ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ እንደሚያስችል የመጨረሻ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው ይገባል! እንዲህ ካደረግን ከሞት ጋር ብንፋጠጥ እንኳ “ይሖዋ ሆይ፣ ንጹሕ አቋሜን ለመጠበቅ፣ ሰይጣን ውሸታም መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲሁም ስምህን ለማስቀደስና ሉዓላዊነትህን ለመደገፍ የቻልኩትን ሁሉ አድርጌያለሁ!” ማለት እንችላለን። w21.04 12 አን. 13-14
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 15) ማቴዎስ 27:62-66 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ማቴዎስ 28:2-4
ዓርብ፣ ሚያዝያ 7
በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት።—ማቴ. 17:5
ኢየሱስ በሐሰት ከተከሰሰ በኋላ ባልሠራው ወንጀል ጥፋተኛ ነህ ተብሎ ተፈረደበት። ከዚያም ጠላቶቹ ተዘባበቱበት፤ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ አሠቃዩት፤ እንዲሁም በመከራ እንጨት ላይ ሰቀሉት። እጆቹና እግሮቹ በሚስማር ተቸንክረዋል። አንዲት ቃል መናገር፣ ሌላው ቀርቶ መተንፈስ እንኳ ከፍተኛ ሥቃይ ያስከትልበታል። ይሁንና ሊናገር የሚገባው በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ስላለ ከመናገር ወደኋላ አላለም። ከኢየሱስ የመጨረሻ ቃላት በጣም ግሩም ትምህርቶች እናገኛለን! ሌሎችን ይቅር ማለት አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም ይሖዋ ይቅር እንደሚለን መተማመን እንዳለብን እንማራለን። እኛን ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ አፍቃሪ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ግሩም መንፈሳዊ ቤተሰብ በማግኘታችን ታድለናል። ይሁንና እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ እንዲረዱን ልንጠይቃቸው ይገባል። ይሖዋ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በጽናት ለመወጣት እንደሚረዳን እናውቃለን። በተጨማሪም እያንዳንዱን ቀን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የምንችልበት የመጨረሻ አጋጣሚ አድርገን ልንመለከተው እንደሚገባ እንማራለን፤ እንዲሁም ሕይወታችንን በይሖዋ እጅ አደራ እንሰጣለን። w21.04 8 አን. 1፤ 13 አን. 17
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ማቴዎስ 28:1, 5-15
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 8
ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።—ዮሐ. 17:3
የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን ወደ ዘላለም ሕይወት ይመራናል። አንድ ሀብታም ወጣት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለበት ኢየሱስን ሲጠይቀው ኢየሱስ “መጥተህ ተከታዬ ሁን” በማለት መልሶለታል። (ማቴ. 19:16-21) ኢየሱስ እሱ ክርስቶስ መሆኑን ላልተቀበሉ አንዳንድ አይሁዳውያን “በጎቼ . . . ይከተሉኛል። የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 10:24-29) በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን የምናሳየው ትምህርቶቹን በተግባር በማዋልና የእሱን ምሳሌ በመከተል ነው። እንዲህ ካደረግን ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስደው መንገድ ሳንወጣ መኖር እንችላለን። (ማቴ. 7:14) የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ ለመከተል በመጀመሪያ እሱን ማወቅ አለብን። ኢየሱስን “ማወቅ” ቀጣይ የሆነ ሂደት ነው። ስለ ኢየሱስ ባሕርያት፣ ስለ አስተሳሰቡና ስለ መሥፈርቶቹ በመማር ከዕለት ወደ ዕለት እሱን ይበልጥ እያወቅነው መሄድ ይኖርብናል። እውነት ውስጥ የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን ይሖዋንና ልጁን ለማወቅ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠላችን አስፈላጊ ነው። w21.04 4 አን. 9-10
እሁድ፣ ሚያዝያ 9
ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅ [ነበርኩ]።—1 ጢሞ. 1:13
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ባደረጋቸው ነገሮች የተነሳ አንዳንድ ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት ተውጦ መሆን አለበት። “ከኃጢአተኞች . . . ዋነኛ ነኝ” በማለት ተናግሯል፤ ደግሞም እንዲህ የተሰማው መሆኑ አያስገርምም። (1 ጢሞ. 1:15) ጳውሎስ እውነትን ከማወቁ በፊት ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ እየሄደ ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር። ብዙዎችን ወህኒ ቤት አስገብቷል፤ አንዳንዶች ደግሞ እንዲገደሉ የድጋፍ ድምፅ ሰጥቷል። (ሥራ 26:10, 11) ጳውሎስ፣ በእሱ ምክንያት ወላጆቹ ከተገደሉበት አንድ ወጣት ክርስቲያን ጋር ቢገናኝ ምን ሊሰማው እንደሚችል እስቲ አስበው። ጳውሎስ በሠራቸው ስህተቶች ተጸጽቷል፤ ሆኖም ያለፈውን ነገር መቀየር እንደማይችል ያውቅ ነበር። ክርስቶስ ለእሱ ሲል እንደሞተ የተቀበለ ሲሆን “አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው” በማለት በልበ ሙሉነት ጽፏል። (1 ቆሮ. 15:3, 10) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ክርስቶስ ለአንተ ሲል እንደሞተና ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና የመመሥረት አጋጣሚ እንደከፈተልህ አምነህ ተቀበል። (ሥራ 3:19) አምላክ ትኩረት የሚያደርገው አሁን እና ወደፊት በምናከናውናቸው ነገሮች ላይ እንጂ ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች ላይ አይደለም።—ኢሳ. 1:18፤ w21.04 23 አን. 11
ሰኞ፣ ሚያዝያ 10
በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ፤ ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።—1 ዮሐ. 4:1
በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን መሲሑ መሞት እንደሚኖርበት ባይገነዘቡም ይህ ጉዳይ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር፤ ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “ሕይወቱን እስከ ሞት ድረስ አፍስሷልና፤ ከሕግ ተላላፊዎችም ጋር ተቆጥሯል፤ የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸክሟል፤ ስለ ሕግ ተላላፊዎችም ማልዷል።” (ኢሳ. 53:12) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ እንደ ኃጢአተኛ ተቆጥሮ መገደሉ አይሁዳውያንን ሊያሰናክላቸው አይገባም ነበር። በዛሬው ጊዜም እውነታውን ማጣራታችን ላለመሰናከል ይረዳናል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ለአድማጮቹ አንዳንዶች “ክፉውን ሁሉ በውሸት [እንደሚያስወሩባቸው]” ነግሯቸው ነበር። (ማቴ. 5:11) የእነዚህ ውሸቶች ምንጭ ሰይጣን ነው። ሰይጣን፣ ተቃዋሚዎች እውነትን የሚወዱ ሰዎችን ስም እንዲያጠፉ ያነሳሳቸዋል። (ራእይ 12:9, 10) ተቃዋሚዎቻችን የሚናገሩት ውሸት ሊያሳስበን አይገባም። እንዲህ ያሉ ውሸቶች እንዲያሸብሩን ወይም እምነታችንን እንዲያዳክሙት ፈጽሞ ልንፈቅድ አይገባም። w21.05 12 አን. 14, 16
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 11
አትፍሩ፤ እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።—ማቴ. 10:31
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ በይሖዋ እንዲተማመን እርዳው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይሖዋ ስለሚወዳቸው እንደሚረዳቸው ዋስትና ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 10:19, 20, 29, 30) አንተም ለጥናትህ ይሖዋ እንደሚረዳው አረጋግጥለት። ግቦቹን በተመለከተ ወደ ይሖዋ አብረኸው በመጸለይ በይሖዋ ላይ እንዲታመን ልትረዳው ትችላለህ። በፖላንድ የሚኖረው ፍራንቺሼክ እንዲህ ብሏል፦ “አስጠኚዬ በጸሎቱ ላይ ስለ ግቦቼ አዘውትሮ ይጠቅስ ነበር። ይሖዋ የአስጠኚዬን ጸሎት እንደመለሰለት ስመለከት እኔም ወዲያውኑ መጸለይ ጀመርኩ። በጉባኤ ስብሰባዎችና በትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከአዲሱ ሥራዬ እረፍት መውሰድ ባስፈለገኝ ወቅት የይሖዋን እርዳታ አይቻለሁ።” ይሖዋ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በጥልቅ ያስብላቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚመሩ ክርስቲያኖችም ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ለመርዳት የሚያደርጉትን ከፍተኛ ጥረት ያደንቃል፤ እንዲሁም ይህን በማድረጋቸው ይወዳቸዋል። (ኢሳ. 52:7) በአሁኑ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሌለህ ሌሎች አስፋፊዎች ጥናት ሲመሩ በመገኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት ትችላለህ። w21.06 7 አን. 17-18
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12
በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል።—መዝ. 1:2
የአምላክን ቃል በእጃችን ማግኘት መቻላችን ትልቅ መብት ነው። ቃሉን አዘውትረን በማንበብ ለዚህ መብት አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። የግል ጥናት ሲመቸን ብቻ የምናደርገው ነገር መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ ጊዜ ልንመድብለት ይገባል። ቋሚ የጥናት ፕሮግራም በመከተል እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ከዚህ ዓለም ‘ጥበበኞችና አዋቂዎች’ በተለየ መልኩ እኛ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ጠንካራ እምነት አለን። (ማቴ. 11:25, 26) ይህን ቅዱስ መጽሐፍ ማጥናታችን፣ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ የሄደው ለምን እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ ይህን ለማስተካከል ምን እንደሚያደርግ ለማወቅ አስችሎናል። እንግዲያው የራሳችንን እምነት ለማጠናከር ብሎም በተቻለ መጠን ብዙዎች በፈጣሪያችን ላይ እምነት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (1 ጢሞ. 2:3, 4) እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖር ሁሉ በራእይ 4:11 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ የሚያስተጋባበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቅ፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ . . . ልትቀበል ይገባሃል።” w21.08 19 አን. 18-20
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 13
በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ።—ሮም 12:10
ሽማግሌዎች እረኞች ስለሆኑ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ምክር የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። የሚሰጡት ምክር ጠቃሚ የሆነና ለተግባር የሚያነሳሳ እንዲሁም ‘ልብን ደስ የሚያሰኝ’ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ። (ምሳሌ 27:9) ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ይወዷቸዋል። ፍቅራቸውን የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ የተሳሳተ ጎዳና የሚከተልን ሰው መምከር ነው። (ገላ. 6:1) ሆኖም አንድ ሽማግሌ ግለሰቡን ከማነጋገሩ በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ ስለጠቀሳቸው የፍቅር ገጽታዎች ቆም ብሎ ማሰቡ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። . . . ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።” (1 ቆሮ. 13:4, 7) ሽማግሌው በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰሉ ምክር የሚሰጥበትን ምክንያት ለመገምገምና የሚመክረውን ወንድም በትክክለኛው መንገድ ለማነጋገር ይረዳዋል። ምክር የሚሰጠው ሰው ሽማግሌው እንደሚያስብለት ከተሰማው ምክሩን መቀበል ላይከብደው ይችላል። w22.02 14 አን. 3፤ 15 አን. 5
ዓርብ፣ ሚያዝያ 14
ዓመፁ፤ ቅዱስ መንፈሱንም አሳዘኑ።—ኢሳ. 63:10
ይሖዋ መላእክትንና ሰዎችን ሲፈጥር ምንም እንከን አልነበረባቸውም፤ ሁሉም ልጆቹ ፍጹም ነበሩ። በኋላ ግን ከመላእክት አንዱ ይኸውም ሰይጣን (“ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም አለው) በይሖዋ ላይ ዓመፀ፤ እንዲሁም ፍጹም የሆኑት አዳምና ሔዋን በይሖዋ ላይ እንዲያምፁ አደረጋቸው። ሌሎች መላእክትና ሰዎችም በዓመፁ ተባበሩ። (ይሁዳ 6) ይሖዋ እንደተከዳ ቢሰማው የሚያስገርም አይደለም። ያም ቢሆን ይሖዋ ጸንቷል፤ እንዲሁም ሁሉንም ዓመፀኞች የሚያጠፋበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ መጽናቱን ይቀጥላል። ልክ እንደ እሱ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለውን ክፋት በጽናት እየተቋቋሙ ያሉት ታማኝ አገልጋዮቹ ያን ጊዜ እፎይ ይላሉ። ሰይጣን ኢዮብም ሆነ ሌሎች ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች አምላክን የሚያገለግሉት ለጥቅማቸው ሲሉ ብቻ እንደሆነ በመናገር ክስ ሰንዝሯል። (ኢዮብ 1:8-11፤ 2:3-5) ዲያብሎስ ዛሬም ቢሆን እንዲህ ያለ ክስ እየሰነዘረ ነው። (ራእይ 12:10) እኛም ፈተና ሲያጋጥመን በመጽናትና ለይሖዋ ባለን ፍቅር ተነሳስተን ለእሱ ታማኝ በመሆን የሰይጣን ክስ ውሸት መሆኑን ማጋለጥ እንችላለን። w21.07 9 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 15
ክፉ ሥራችሁን ከፊቴ አስወግዱ፤ መጥፎ ድርጊት መፈጸማችሁን አቁሙ።—ኢሳ. 1:16
ሐዋርያው ጳውሎስ አኗኗራችንን መቀየራችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት ከፍተኛ ኃይል ያለው መግለጫ ተጠቅሟል። አሮጌውን ስብዕናችንን ‘በእንጨት ላይ መቸንከር’ እንዳለብን ጽፏል። (ሮም 6:6) በሌላ አባባል ክርስቶስ ያደረገውን ማድረግ አለብን። ይሖዋ የሚጠላቸውን ዝንባሌዎችና ልማዶች መግደል ይኖርብናል። ይህን እርምጃ ካልወሰድን ንጹሕ ሕሊናም ሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አይኖረንም። (ዮሐ. 17:3፤ 1 ጴጥ. 3:21) ይሖዋ እኛ እንዲመቸን ሲል መሥፈርቶቹን ዝቅ አያደርግም። ስብዕናችንን መቀየርና ከእሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር ያለብን እኛ ነን። (ኢሳ. 1:17, 18፤ 55:9) ከተጠመቅህ በኋላም ከሥጋዊ ምኞቶችህ ጋር የምታደርገው ውጊያ አያቆምም። እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም በራስህ ጥንካሬ ሳይሆን በይሖዋ መንፈስ ተማመን። (ገላ. 5:22፤ ፊልጵ. 4:6) አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣልና እንዳወለቅነው ለመቀጠል ቆራጥ መሆን ያስፈልገናል። w22.03 5-6 አን. 15-17
እሁድ፣ ሚያዝያ 16
[ይሖዋ] ይደግፍሃል።—መዝ. 55:22
ይሖዋ ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን ከፈለግንና በእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ከተመራን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንደሚያሟላልን ቃል ገብቶልናል። (ማቴ. 6:33) ይሖዋ በገባልን ቃል የምንተማመን ከሆነ ይህ ዓለም የሚያቀርብልን ቁሳዊ ነገሮች ጥበቃ እንደሚሆኑልን ወይም ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኙልን አናስብም። እውነተኛ ሰላም ማግኘት የምንችለው የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። (ፊልጵ. 4:6, 7) ብዙ ነገሮችን ለመግዛት አቅሙ ቢኖረንም እንኳ ‘እነዚህን ዕቃዎች ለመጠቀምም ሆነ ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ጊዜና ጉልበት አለኝ ወይ’ የሚለውን ልናስብበት ይገባል። ለቁሳዊ ንብረቶቻችን ሚዛኑን የሳተ ፍቅር እያዳበርን ይሆን? አምላክ በቤተሰቡ ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንድናበረክት እንደሚጠብቅብን እናስታውስ። በመሆኑም ትኩረታችን እንዲከፋፈል ልንፈቅድ አይገባም። ቁሳዊ ንብረቶቹን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ኢየሱስን ላለመከተል የመረጠውን ሰው መምሰል አንፈልግም፤ ይህ ሰው ይሖዋን የማገልገልና የእሱ ልጅ የመሆን አጋጣሚ አምልጦታል።—ማር. 10:17-22፤ w21.08 6 አን. 17
ሰኞ፣ ሚያዝያ 17
ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ [ስጡ]።—1 ጴጥ. 3:15
ቅዱሳን መጻሕፍትን ስታጠና ስለ ይሖዋ ማንነት እና ስለ ባሕርያቱ ትማራለህ፤ እነዚህ ባሕርያቱ በፍጥረት ሥራዎቹም ላይ እንደተንጸባረቁ ማስተዋልህ አይቀርም። ስለ እነዚህ ባሕርያት መማርህ ይሖዋ ምናብ የፈጠረው ሳይሆን እውን አካል መሆኑን እንድታምን ያደርግሃል። (ዘፀ. 34:6, 7፤ መዝ. 145:8, 9) ይሖዋን ይበልጥ እያወቅኸው ስትሄድ በእሱ ላይ ያለህ እምነት ይጎለብታል፤ ለእሱ ያለህ ፍቅር ይጨምራል፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት ይጠናከራል። በአምላክ ላይ ያለህን እምነት በተመለከተ ለሌሎች ተናገር። ሆኖም የመሠከርክለት ሰው ስለ አምላክ መኖር ጥያቄ ቢያነሳና ምን ብለህ መመለስ እንዳለብህ ግራ ቢገባህስ? በጽሑፎቻችን ላይ የወጣ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያ ለማግኘት ጥረት አድርግ፤ ከዚያም ያገኘኸውን ሐሳብ ለግለሰቡ አካፍለው። ከዚህም ሌላ ተሞክሮ ያለው አንድ የእምነት ባልንጀራህን እንዲረዳህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ግለሰቡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰጠኸውን ማብራሪያ ተቀበለም አልተቀበለ ምርምር ማድረግህ አንተን ይጠቅምሃል። እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል። w21.08 18 አን. 14-15
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 18
ከመንገር . . . ወደኋላ ብዬ አላውቅም።—ሥራ 20:20
ይሖዋን ለማስደሰት፣ የምንወደውን ነገር ሁሉ መሥዋዕት ማድረግ አለብን ማለት አይደለም። (መክ. 5:19, 20) ሆኖም የምንወደውን ነገር መሥዋዕት ማድረግ ስለማንፈልግ ብቻ በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ነገር ከማድረግ ወደኋላ ካልን ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ሰው የሠራውን ዓይነት ስህተት ልንፈጽም እንችላለን፤ ይህ ሰው የተመቻቸ ሕይወት ለመምራት ጥረት ሲያደርግ አምላክን ችላ ብሏል። (ሉቃስ 12:16-21) ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ እንዲረዳን እንጸልያለን፤ እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታችንን ተጠቅመን ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ዕቅድ እናወጣለን። (ምሳሌ 3:21) ይሖዋ በብዙ መንገዶች ይባርከናል። ለእሱ ክብር ለማምጣት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ለይሖዋ በረከቶች አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። (ዕብ. 13:15) ይህም አገልግሎታችንን ማስፋትን ሊጨምር ይችላል፤ እንዲህ ስናደርግ ደግሞ ተጨማሪ በረከቶች እናገኛለን። እንግዲያው ‘ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቀምሰን ማየት’ የምንችልባቸውን መንገዶች በየቀኑ እንፈልግ። (መዝ. 34:8) እንደዚያ ካደረግን እኛም እንደ ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” ማለት እንችላለን።—ዮሐ. 4:34፤ w21.08 30-31 አን. 16-19
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 19
ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።—ምሳሌ 16:18
ሰይጣን ተገቢ ያልሆነ ኩራት እንዲያድርብን ይፈልጋል። ተገቢ ያልሆነ ኩራት እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን እንደ እሱ እንደምንሆንና የዘላለም ሕይወት እንደምናጣ ያውቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አንድ ሰው “በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ የተፈረደበት ዓይነት ፍርድ” ሊፈረድበት እንደሚችል ያስጠነቀቀው ለዚህ ነው። (1 ጢሞ. 3:6, 7) አዲሶችም ሆንን ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን ስናገለግል የቆየን ክርስቲያኖች፣ ማናችንም ይህ ሁኔታ ሊደርስብን ይችላል። ኩራተኛ የሆኑ ሰዎች ራስ ወዳዶች ናቸው። ሰይጣን በተለይ ችግሮች ሲያጋጥሙን ራስ ወዳዶች እንድንሆን ይኸውም በይሖዋ ላይ ሳይሆን በራሳችን ላይ እንድናተኩር ሊገፋፋን ይሞክራል። ለምሳሌ ያህል፣ የሐሰት ውንጀላ ተሰንዝሮብህ ያውቃል? ወይም ኢፍትሐዊ ድርጊት ተፈጽሞብህ ያውቃል? ሰይጣን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ በይሖዋ ወይም በወንድሞችህ ላይ እንድትበሳጭ ይፈልጋል። እንዲሁም ችግሩን መፍታት የምትችልበት ብቸኛው መንገድ ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሰጠህን መመሪያ መከተል ሳይሆን የራስህን እርምጃ መውሰድ እንደሆነ ሊያሳምንህ ይሞክራል።—መክ. 7:16, 20፤ w21.06 15 አን. 4-5
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 20
“እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ፣ በርቱና ሥሩ” ይላል ይሖዋ። “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።—ሐጌ 2:4
ይሖዋ ለነቢዩ ሐጌ ወሳኝ ተልእኮ ሰጥቶት ነበር። ሐጌ በ537 ዓ.ዓ. ከባቢሎን ግዞት ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱት አይሁዳውያን አንዱ ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች ኢየሩሳሌም ከደረሱ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋን ቤት ወይም ቤተ መቅደስ መሠረት ጣሉ። (ዕዝራ 3:8, 10) ብዙም ሳይቆይ ግን የሚያሳዝን ሁኔታ ተፈጠረ። ሕዝቡ በተስፋ መቁረጥና በተቃውሞ ተሸንፈው ሥራውን አቆሙ። (ዕዝራ 4:4፤ ሐጌ 1:1, 2) በመሆኑም ይሖዋ ሕዝቡ ቅንዓታቸውን እንዲያቀጣጥሉና የቤተ መቅደሱን ግንባታ እንዲያጠናቅቁ ለማነሳሳት በ520 ዓ.ዓ. ሐጌን ላከው። (ዕዝራ 6:14, 15) የሐጌ መልእክት ዓላማ ሕዝቡ በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ መርዳት ነበር። “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚለው አገላለጽ ሕዝቡን አበረታቷቸው መሆን አለበት። ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መላእክትን ያቀፈ ሠራዊት አለው፤ ስለዚህ አይሁዳውያኑ እንዲሳካላቸው ከፈለጉ በእሱ መታመን ይኖርባቸዋል። w21.09 15 አን. 4-5
ዓርብ፣ ሚያዝያ 21
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።—ዮሐ. 13:35
በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ፍቅርና አንድነት አላቸው። ከሌላ ከየትኛውም ድርጅት በተለየ መልኩ የወንድማማች ማኅበራችን ብሔር፣ የቆዳ ቀለምና የኑሮ ደረጃ የማይለየው የጠበቀ አንድነት አለው። በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችንና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ ይህን እውነተኛ ፍቅር በግልጽ ማየት ይቻላል። ይህ እውነታ አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ያረጋግጥልናል። (ዮሐ. 13:34) ቅዱሳን መጻሕፍት ‘አንዳችን ለሌላው የጠለቀ ፍቅር እንዲኖረን’ ይመክሩናል። (1 ጴጥ. 4:8) እንዲህ ያለውን ፍቅር የምናሳይበት አንዱ መንገድ እርስ በርስ ይቅር መባባልና አንዳችን የሌላውን ድክመት ችለን ማለፍ ነው። በተጨማሪም ቅር ያሰኙንን ጨምሮ በጉባኤ ውስጥ ላሉ ሁሉ ልግስናና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። (ቆላ. 3:12-14) እንዲህ ያለ ፍቅር ማሳየታችን እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችን የሚረጋገጥበት ዋነኛው መንገድ ነው። w21.10 22 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 22
ልጁን [የሚወድ] ተግቶ ይገሥጸዋል።—ምሳሌ 13:24
ውገዳ፣ ንስሐ ያልገባው ኃጢአተኛ አካሄዱን እንዲያስተካክል ሊረዳው ይችላል? አዎ ይችላል። ከባድ ኃጢአት ፈጽመው የነበሩ ብዙዎች፣ ሽማግሌዎች የወሰዱት ጥብቅ እርምጃ እንዲነቁና ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱ፣ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ እንዲሁም ወደ ይሖዋ እቅፍ እንዲመለሱ እንደረዳቸው ተናግረዋል። (ዕብ. 12:5, 6) እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ እረኛ ከበጎቹ አንዱ እንደታመመ አስተዋለ። እረኛው ለታመመው በግ ሕክምና ለመስጠት በጉን ከመንጋው ለይቶ ማቆየት እንደሚያስፈልግ ያውቃል። ሆኖም በጎች ከመንጋቸው መለየት አይፈልጉም፤ ብቻቸውን ከተገለሉ ሊረበሹ ይችላሉ። ታዲያ እረኛው እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ጨካኝ ያስብለዋል? በጭራሽ አያስብለውም። እረኛው የታመመው በግ ከመንጋው ጋር እንዲቀላቀል ቢያደርግ በሽታው እንደሚዛመት ያውቃል። የታመመውን በግ ለይቶ በማቆየት መንጋው በሙሉ ከበሽታ እንዲጠበቅ ያደርጋል። w21.10 10 አን. 9-10
እሁድ፣ ሚያዝያ 23
ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።—ማቴ. 5:16
አፍቃሪ የሆነ ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል መሆን ትልቅ መብት ነው። በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች አብረውን ይሖዋን እንዲያመልኩ እንፈልጋለን። በመሆኑም የይሖዋንም ሆነ የሕዝቦቹን ስም የሚያጎድፍ ምንም ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ሰዎች ስለ ይሖዋ ለመማርና እሱን ለማገልገል እንዲነሳሱ የሚያደርግ ምግባር ሊኖረን ይገባል። አንዳንዶች የሰማዩን አባታችንን በመታዘዛችን ምክንያት ያቃልሉን ወይም ያሳድዱን ይሆናል። በዚህ የተነሳ ስለ እምነታችን ለሌሎች መናገር የሚያስፈራን ቢሆንስ? የይሖዋና የልጁ እርዳታ እንደማይለየን መተማመን እንችላለን። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት ወይም ምን ብለው መናገር እንዳለባቸው ሊጨነቁ እንደማይገባ ነግሯቸዋል። ሊጨነቁ የማይገባው ለምንድን ነው? ኢየሱስ መልሱን ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና፤ በምትናገሩበት ጊዜ ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ይልቁንም በእናንተ የሚናገረው የአባታችሁ መንፈስ ነው።”—ማቴ. 10:19, 20፤ w21.09 24 አን. 17-18
ሰኞ፣ ሚያዝያ 24
ይሖዋን “አንተ መጠጊያዬና ምሽጌ . . . ነህ” እለዋለሁ።—መዝ. 91:2
ሙሴም ተመሳሳይ አገላለጽ በመጠቀም ይሖዋ መጠጊያችን እንደሆነ ተናግሯል። (መዝ. 90:1 ግርጌ) በተጨማሪም ሙሴ በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ሌላ የሚያጽናና አገላለጽ ተጠቅሟል፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላክ ከጥንት ጀምሮ መሸሸጊያ ነው፤ ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው።” (ዘዳ. 33:27) “ዘላለማዊ ክንዶቹ ከበታችህ ናቸው” የሚለው አገላለጽ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ይሖዋ መጠጊያችን ከሆነ የደህንነት ስሜት ይሰማናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ስሜታችን ከመደቆሱ የተነሳ ቀና ማለት ሊከብደን ይችላል። እንዲህ በሚሰማን ጊዜ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? (መዝ. 136:23) ክንዶቹን ከሥራችን አድርጎ ደግፎ ያነሳናል፤ እንዲሁም በእግራችን እንድንቆም ይረዳናል። (መዝ. 28:9፤ 94:18) ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚደግፈን እናውቃለን፤ ይህም በሁለት መንገዶች እንደሚባርከን እንድናስታውስ ያደርገናል። አንደኛ፣ የምንኖረው የትም ይሁን የት አስተማማኝ መጠጊያ አለን። ሁለተኛ፣ አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን በጥልቅ ያስብልናል። w21.11 6 አን. 15-16
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 25
በልዩ ልዩ ፈተናዎች [ተጨንቃችኋል]።—1 ጴጥ. 1:6
ኢየሱስ በፍትሕ መጓደል ምክንያት የደቀ መዛሙርቱ እምነት እንደሚፈተን ያውቅ ነበር። እንዲህ ያለውን ሁኔታ እንዲቋቋሙ ለመርዳት ሲል አንድ ምሳሌ ነገራቸው። ይህ ምሳሌ በሉቃስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። ኢየሱስ የነገራቸው ምሳሌ፣ ፍትሕ እንዲፈጸምላት አንድን ዓመፀኛ ዳኛ በተደጋጋሚ ትለምን ስለነበረች አንዲት መበለት የሚገልጽ ነው። ይህች ሴት ሳታቋርጥ ከለመነች መፍትሔ እንደምታገኝ እርግጠኛ ነበረች። ከጊዜ በኋላ ዳኛው ልመናዋን ሰማት። ነጥቡ ምንድን ነው? ይሖዋ ዓመፀኛ አይደለም። ከዚህ አንጻር ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ታዲያ አምላክ . . . ቀን ከሌት ወደ እሱ የሚጮኹት ምርጦቹ ፍትሕ እንዲያገኙ አያደርግም?” (ሉቃስ 18:1-8) አክሎም ኢየሱስ “የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ በምድር ላይ በእርግጥ እንዲህ ያለ እምነት ያገኝ ይሆን?” አለ። (ሉቃስ 18:8 ግርጌ) የፍትሕ መጓደል ሲፈጸምብን በመታገሥና በመጽናት እንደ መበለቷ ያለ ጠንካራ እምነት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። እንዲህ ያለ እምነት ካለን፣ ይዋል ይደር እንጂ ይሖዋ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንሆናለን። ጸሎት ኃይል እንዳለውም ማመን ይኖርብናል። w21.11 23 አን. 12፤ 24 አን. 14
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 26
ወጣቶች በንጽሕና መመላለስ የሚችሉት እንዴት ነው? በቃልህ መሠረት ራሳቸውን በመጠበቅ ነው።—መዝ. 119:9
እናንት ወጣቶች፣ አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ መመሪያዎች የማያፈናፍኑ እንደሆኑ ይሰማችኋል? ሰይጣን እንዲህ ብላችሁ እንድታስቡ ይፈልጋል። በሰፊው መንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች በሚያደርጉት ነገር ላይ እንድታተኩሩ ይፈልጋል፤ እነዚህ ሰዎች አስደሳች ሕይወት የሚመሩ ይመስላሉ። አብረዋችሁ ከሚማሩት ልጆች ወይም ኢንተርኔት ላይ ከምታዩአቸው ሰዎች አንጻር፣ ብዙ ነገር እንደቀረባችሁ እንዲሰማችሁ ይፈልጋል። ሰይጣን የይሖዋ መሥፈርቶች በሕይወታችሁ የተሟላ ደስታ ከማግኘት እንዳገዷችሁ እንድታስቡ ይፈልጋል። ሆኖም አንድ ነገር አስታውሱ፤ ሰይጣን በእሱ መንገድ ላይ የሚጓዙ ሰዎች መጨረሻ ላይ ምን እንደሚጠብቃቸው እንዲያውቁ አይፈልግም። (ማቴ. 7:13, 14) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ፣ በሕይወት መንገድ ላይ መጓዛቸውን ለሚቀጥሉ ሰዎች ምን እንዳዘጋጀላቸው በግልጽ ነግሯችኋል።—መዝ. 37:29፤ ኢሳ. 35:5, 6፤ 65:21-23፤ w21.12 23 አን. 6-7
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 27
ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር [በሉ]።—ማቴ. 18:35
የበደሉንን ይቅር ማለት እንዳለብን እናውቃለን፤ ትክክለኛው እርምጃ ይህ ነው። ይሁንና ይህን ማድረግ ይከብደን ይሆናል። ሐዋርያው ጴጥሮስም እንዲህ የተሰማው ጊዜ ሳይኖር አይቀርም። (ማቴ. 18:21, 22) ታዲያ ይቅር ለማለት ምን ሊረዳን ይችላል? በመጀመሪያ፣ ይሖዋ ስንት ጊዜ ይቅር እንዳለህ አሰላስል። (ማቴ. 18:32, 33) ይቅርታው የሚገባን ሰዎች ባንሆንም በነፃ ይቅር ይለናል። (መዝ. 103:8-10) “እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን።” በመሆኑም ይቅር ማለት ለምርጫ የተተወ ነገር አይደለም። ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር ማለት ግዴታ ነው። (1 ዮሐ. 4:11) ሁለተኛ፣ ይቅር ማለት በሚያስገኘው ጥቅም ላይ አሰላስል። ይቅር ማለታችን የበደለንን ሰው ያስደስተዋል፤ የጉባኤውን አንድነት ለመጠበቅ ያስችላል፤ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ይዘን ለመቀጠል ያስችለናል፤ እንዲሁም ከላያችን ላይ ትልቅ ሸክም የወረደልን ያህል ሆኖ እንዲሰማን ያደርጋል። (2 ቆሮ. 2:7፤ ቆላ. 3:14) ሦስተኛ፣ ይቅር እንድንል መመሪያ ወደሰጠን አምላክ ጸልይ። ሰይጣን ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር ያለህን ሰላም እንዲያደፈርሰው አትፍቀድ። (ኤፌ. 4:26, 27) ሰይጣን በዚህ ረገድ እንዳይሳካለት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። w21.06 22 አን. 11፤ 23 አን. 14
ዓርብ፣ ሚያዝያ 28
አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ።—1 ሳሙ. 23:17
ዳዊት ሕይወቱን ለማትረፍ እየሸሸ ነው። ኃያል የሆነው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል፣ ዳዊትን ለመግደል ቆርጦ ተነስቷል። በአንድ ወቅት ዳዊት ምግብ ሲያልቅበት ወደ ኖብ ከተማ ሄዶ አምስት ዳቦ እንዲሰጡት ጠየቀ። (1 ሳሙ. 21:1, 3) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዳዊትና አብረውት ያሉት ሰዎች በዋሻ ውስጥ ለመሸሸግ ተገድደው ነበር። (1 ሳሙ. 22:1) ዳዊት እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የወደቀው እንዴት ነው? ዳዊት በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ እና ብዙ ድሎች ማግኘቱ ሳኦልን በቅናት አሳብዶት ነበር። በተጨማሪም ሳኦል፣ ባለመታዘዙ የተነሳ የእስራኤል ንጉሥ እንዳይሆን ይሖዋ እንደናቀው እንዲሁም ይሖዋ ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ እንደቀባው ያውቅ ነበር። (1 ሳሙ. 23:16, 17) ሳኦል የእስራኤል ንጉሥ በመሆኑ ታላቅ ሠራዊት እና ብዙ ደጋፊዎች ነበሩት፤ በመሆኑም ዳዊት ሕይወቱን ለማትረፍ መሸሽ ነበረበት። ሳኦል አምላክ ዳዊትን ለማንገሥ ያለውን ዓላማ ማክሸፍ እንደሚችል አስቦ ይሆን? (ኢሳ. 55:11) መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አይልም። አንድ ነገር ግን በእርግጠኝነት እናውቃለን፦ ሳኦል ራሱን ችግር ውስጥ እየከተተ ነበር። ምክንያቱም ከአምላክ ጋር የሚዋጉ መቼም ቢሆን አያሸንፉም! w22.01 2 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 29
ኒቆዲሞስ . . . በማታ ወደ ኢየሱስ [መጣ]።—ዮሐ. 3:1, 2
ኢየሱስ አገልግሎቱን በትጋት አከናውኗል። ሰዎችን ይወድ ስለነበር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያስተምራቸው ነበር። (ሉቃስ 19:47, 48) ይህን ለማድረግ ያነሳሳው ምንድን ነው? ኢየሱስ ለሰዎች ርኅራኄ ነበረው። አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስን ለመስማት በጣም ብዙ ሰዎች ይመጡ ስለነበር እሱና ደቀ መዛሙርቱ “እህል እንኳ መቅመስ አልቻሉም” ነበር። (ማር. 3:20) በአንድ ወቅት፣ ከሚያስተምራቸው ሰዎች አንዱ የሚመቸው ምሽት ላይ ስለነበር በዚያ ሰዓት ሊያስተምረው ፈቃደኛ ሆኗል። ኢየሱስ ሲያስተምር ከሰሙት ሰዎች አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርቱ አልሆኑም። ያም ቢሆን ኢየሱስ ለሰሙት ሰዎች ሁሉ የተሟላ ምሥክርነት ሰጥቷል። እኛም በዛሬው ጊዜ ሁሉም ሰው ምሥራቹን ለመስማት አጋጣሚ እንዲያገኝ ማድረግ እንፈልጋለን። (ሥራ 10:42) ለዚህም ሲባል አገልግሎታችንን የምናከናውንበትን መንገድ ማስተካከል ሊያስፈልገን ይችላል። ሁልጊዜ እኛ በሚመቸን ሰዓት ላይ ከማገልገል ይልቅ ሰዎች ሊገኙ በሚችሉበት ሰዓት ላይ ለመስበክ ፕሮግራማችንን ማስተካከል አለብን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ይደሰትብናል። w22.01 17 አን. 13-14
እሁድ፣ ሚያዝያ 30
ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።—መክ. 8:9
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ማመን ይከብዳቸዋል። የፍትሑና የፖለቲካው ሥርዓት ለሀብታሞችና አቅም ላላቸው ሲያዳላ ድሆችን ግን እንደሚበድል ይመለከታሉ። አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች የሚያደርጉት ነገርም ቢሆን ብዙዎችን ለሐዘን ዳርጓል። ይህ ሁኔታ አንዳንዶች በአምላክ ላይም ጭምር እምነት እንዲያጡ አድርጓል። በመሆኑም አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ስንጀምር የሚገጥመን አንዱ ተፈታታኝ ነገር፣ ግለሰቡ በይሖዋና በምድራዊ ወኪሎቹ ላይ እምነት እንዲያዳብር መርዳት ነው። እርግጥ ነው፣ በይሖዋ እና በድርጅቱ ላይ እምነት መገንባት የሚያስፈልጋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብቻ አይደሉም። በእውነት ውስጥ በርካታ ዓመታት ያሳለፍን ክርስቲያኖችም እንኳ የይሖዋ አሠራር ምንጊዜም ትክክል መሆኑን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም። አንዳንድ ጊዜ ይህን እምነታችንን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። w22.02 2 አን. 1-2