መጋቢት
ረቡዕ፣ መጋቢት 1
ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል።—ማቴ. 25:40
በማቴዎስ 25:31-36, 40 ላይ በሚገኘው ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ‘በጎች’ የሚያመለክቱት በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ጻድቃንን ማለትም ሌሎች በጎችን ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች በምድር ላይ የቀሩትን በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ወንድሞች በታማኝነት ይደግፋሉ። ይህን የሚያደርጉበት ዋነኛው መንገድ በዓለም አቀፉ የስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ለእነሱ እገዛ ማድረግ ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በየዓመቱ የመታሰቢያው በዓል ሲቃረብ ባሉት ሳምንታት፣ ሌሎች በጎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ዘመቻ የተሟላ ተሳትፎ በማድረግ የክርስቶስን ወንድሞች እንደሚደግፉ ያሳያሉ። በተጨማሪም በዓሉ በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ሁሉ እንዲከበር ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ። ሌሎች በጎች በእነዚህ መንገዶች ለክርስቶስ ወንድሞች ድጋፍ በማድረጋቸው በጣም ደስተኞች ናቸው። እነዚህ በጎች ኢየሱስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ ያደረጉትን ነገር ሁሉ ለእሱ እንደተደረገ አድርጎ እንደሚቆጥረው ያውቃሉ።—ማቴ. 25:37-40፤ w22.01 22 አን. 11-12
ሐሙስ፣ መጋቢት 2
እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል።—ዮሐ. 14:9
የኢየሱስን ባሕርያትና ሌሎችን የያዘበትን መንገድ ስንኮርጅ ይሖዋን እየመሰልነው ነው፤ ለምሳሌ ኢየሱስ ለሥጋ ደዌ በሽተኛው በጣም አዝኖለታል፤ የሚያሠቃይ ሕመም የነበረባትን ሴት ስሜቷን ተረድቶላታል፤ የሚወዱትን ሰው በሞት ላጡት ሰዎች ደግሞ ርኅራኄ አሳይቷል። (ማር. 1:40, 41፤ 5:25-34፤ ዮሐ. 11:33-35) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን ይበልጥ ስንመስለው ደግሞ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን። የኢየሱስን ፈለግ መከተላችን በዚህ ክፉ ዓለም ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዳናል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው የመጨረሻ ምሽት ላይ “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 16:33) ኢየሱስ ይህን ሲል የዚህ ዓለም አስተሳሰብ፣ ግብና ምግባር ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት አለመፍቀዱን መግለጹ ነበር። ኢየሱስ ምንጊዜም ትኩረት ያደረገው ወደ ምድር በተላከበት ዋነኛ ዓላማ ይኸውም የይሖዋን ስም በማስቀደስ ላይ ነበር። እኛስ? በዚህ ዓለም ላይ ትኩረታችንን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ብዙ ነገሮች አሉ። ሆኖም እንደ ኢየሱስ ምንጊዜም የይሖዋን ፈቃድ በመፈጸም ላይ ትኩረት ካደረግን እኛም ዓለምን ‘ማሸነፍ’ እንችላለን።—1 ዮሐ. 5:5፤ w21.04 3-4 አን. 7-8
ዓርብ፣ መጋቢት 3
ማንኛውም [ነገር] ቢሆን [ከአምላክ] ፍቅር ሊለየን [አይችልም]።—ሮም 8:39
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ‘በእሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንደሚኖረው’ የገባውን ቃል ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 3:16፤ ሮም 6:23) በቤዛው “የሚያምን ሁሉ” ከተባሉት መካከል ጳውሎስም እንደሚገኝበት ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ፣ ንስሐ እስከገቡ ድረስ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎችንም ጭምር ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ ጳውሎስ እርግጠኛ ነበር። (መዝ. 86:5) ጳውሎስ፣ አምላክ ክርስቶስን ቤዛ አድርጎ መስጠቱ ለእሱ ታላቅ ፍቅር ያለው መሆኑን እንደሚያሳይ ያምን ነበር። በገላትያ 2:20 መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የሚያጽናና ሐሳብ ልብ በል። ጳውሎስ “በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው በአምላክ ልጅ ላይ እምነት አለኝ” ብሏል። ጳውሎስ፣ አምላክ ሊወደው እንደማይችል አልተሰማውም። ‘አምላክ ወንድሞቼን ሊወዳቸው እንደሚችል ይገባኛል፤ እኔን ግን ጨርሶ ሊወደኝ አይችልም’ የሚል አመለካከት አልነበረውም። ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል” ብሏቸዋል። (ሮም 5:8) በእርግጥም የአምላክን ፍቅር ሊገድበው የሚችል ምንም ነገር የለም! ጳውሎስ፣ አምላክ ለእሱ ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። ጳውሎስ፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን ምን ያህል በትዕግሥት እንደያዛቸው ያውቅ ነበር። w21.04 22 አን. 8-10
ቅዳሜ፣ መጋቢት 4
አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው።—1 ዮሐ. 5:3
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትመራ ጥናትህ ይሖዋን እንዲወደው እርዳው። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የይሖዋን ባሕርያት ጎላ አድርገህ ለመግለጽ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ፈልግ። ጥናትህ፣ ይሖዋ የሚወዱትን ሰዎች የሚደግፍ ደስተኛ አምላክ እንደሆነ እንዲገነዘብ እርዳው። (1 ጢሞ. 1:11፤ ዕብ. 11:6) የተማረውን ነገር በሥራ ላይ ማዋሉ እንደሚጠቅመው ግለጽለት፤ እንዲሁም ይሖዋ እንዲህ ያለ ጠቃሚ መመሪያ መስጠቱ ለእሱ ያለውን ፍቅር እንደሚያሳይ አብራራለት። (ኢሳ. 48:17, 18) ጥናትህ ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ ሲሄድ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ይበልጥ ይነሳሳል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ አንዳንድ መሥዋዕቶችን መክፈል ያስፈልገዋል። አንዳንድ ጥናቶች ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ብዙዎች ይሖዋን የማይወዱ ጓደኞቻቸውን መተው ያስፈልጋቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮችን የማይወዱ ቤተሰቦቻቸው አግልለዋቸው ይሆናል። ኢየሱስ እሱን የሚከተሉ ሰዎች መካሳቸው እንደማይቀር ቃል ገብቷል። አፍቃሪ የሆነ መንፈሳዊ ቤተሰብ በማግኘት ይባረካሉ።—ማር. 10:29, 30፤ w21.06 4 አን. 8-9
እሁድ፣ መጋቢት 5
ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ።—ዮሐ. 4:35
ሐዋርያው ጳውሎስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ እርሻ ከማልማት ጋር አመሳስሎታል፤ ይህም ዘር ከመዝራት ያለፈ ነገር መሥራት እንደሚጠበቅብን ያመለክታል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ አጠጣ፤ . . . እናንተ በመልማት ላይ ያለ የአምላክ እርሻ ናችሁ” ብሏቸዋል። (1 ቆሮ. 3:6-9) ‘በአምላክ እርሻ’ ውስጥ ስንሠራ ዘር መዝራት ብቻ ሳይሆን ውኃ ማጠጣትና አዘውትረን የተክሉን እድገት መከታተል ይኖርብናል። ያም ቢሆን ዘሩን የሚያሳድገው አምላክ እንደሆነ አንዘነጋም። ለሌሎች እውነትን መስበክ እና ማስተማር እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው! ይህ ሥራ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልናል። በተሰሎንቄ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የረዳው ሐዋርያው ጳውሎስ ስሜቱን በዚህ መንገድ ገልጾታል፦ “ጌታችን ኢየሱስ በሚገኝበት ጊዜ በእሱ ፊት ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም የሐሴታችን አክሊል ምንድን ነው? እናንተ አይደላችሁም? በእርግጥም እናንተ ክብራችንና ደስታችን ናችሁ።”—1 ተሰ. 2:19, 20፤ ሥራ 17:1-4፤ w21.07 3 አን. 5፤ 7 አን. 17
ሰኞ፣ መጋቢት 6
ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ።—ማቴ. 18:10
ይሖዋ እያንዳንዳችንን ወደ ራሱ ስቦናል። (ዮሐ. 6:44) ይህ ምን ትርጉም እንዳለው እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ይሖዋ በዓለም ላይ ያሉትን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመረምር በአንተ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር አገኘ፤ ቅን ልብ እንዳለህና ለእሱ ፍቅር ማዳበር እንደምትችል አስተዋለ። (1 ዜና 28:9) ይሖዋ አንተን ያውቅሃል፣ ስሜትህን ይረዳልሃል እንዲሁም ይወድሃል። ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሖዋ ስለ አንተ በጥልቅ ያስባል፤ በተጨማሪም ለሁሉም ክርስቲያን ወንድሞችህና እህቶችህ ያስባል። ኢየሱስ ይህን ነጥብ በምሳሌ ሲያስረዳ ይሖዋን ከእረኛ ጋር አመሳስሎታል። መቶ በጎች ያሉት እረኛ ከመንጋው መካከል አንዷ በግ ብትጠፋ ምን ያደርጋል? እረኛው “99ኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ” ይሄዳል። በጓን ሲያገኛትም ቢሆን ከመንጋው ተለይታ በመጥፋቷ አይበሳጭባትም። ከዚህ ይልቅ ስላገኛት በጣም ይደሰታል። ነጥቡ ምንድን ነው? እያንዳንዱ በግ በይሖዋ ፊት ትልቅ ዋጋ አለው። ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም” ብሏል።—ማቴ. 18:12-14፤ w21.06 20 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ መጋቢት 7
ወደ አምላክ ቅረቡ።—ያዕ. 4:8
አምላክ ለእኛ ባለው ጽኑ ፍቅር ላይ ስናሰላስል ለይሖዋ ያለን ፍቅር ይጨምራል፤ ከእሱ ጋር የመሠረትነው ዝምድናም ይጠናከራል። (ሮም 8:38, 39) የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል እንነሳሳለን። (1 ጴጥ. 2:21) በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ ኢየሱስ በምድር ላይ ስላሳለፈው የመጨረሻ ሳምንት፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እናነባለን። በዓሉ በሚከበርበት ምሽት የሚሰጠው ንግግር ደግሞ ኢየሱስ ያሳየንን ፍቅር ያስታውሰናል። (ኤፌ. 5:2፤ 1 ዮሐ. 3:16) ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ስለተወው ምሳሌ ስናነብና ስናሰላስል “እሱ በተመላለሰበት መንገድ [ለመመላለስ]” እንነሳሳለን። (1 ዮሐ. 2:6) ከአምላክ ፍቅር ሳንወጣ ለመኖር ያለን ቁርጠኝነት ይጠናከራል። (ይሁዳ 20, 21) አምላክን ለመታዘዝ፣ ስሙን ለማስቀደስና ልቡን ለማስደሰት የምንችለውን ሁሉ በማድረግ በእሱ ፍቅር መኖር እንችላለን። (ምሳሌ 27:11፤ ማቴ. 6:9፤ 1 ዮሐ. 5:3) በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታችን፣ እያንዳንዱን ቀን ይሖዋን ‘መቼም ቢሆን ከአንተ ፍቅር መውጣት አልፈልግም!’ እንደምንለው በሚያሳይ መንገድ ለመኖር ይበልጥ ያነሳሳናል። w22.01 23 አን. 17፤ 25 አን. 18-19
ረቡዕ፣ መጋቢት 8
የምታገለግሉትን . . . ምረጡ።—ኢያሱ 24:15
ይሖዋ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በመሆኑም የምንሄድበትን የሕይወት ጎዳና መምረጥ እንችላለን። አፍቃሪው አምላካችን እሱን ለማገልገል ስንመርጥ ይደሰታል። (መዝ. 84:11፤ ምሳሌ 27:11) በተጨማሪም የመምረጥ ነፃነታችንን ተጠቅመን ሌሎች በርካታ ጥሩ ውሳኔዎች ማድረግ እንችላለን። የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ቅድሚያ ለመስጠት መምረጥ እንችላለን። በአንድ ወቅት ኢየሱስና ሐዋርያቱ በጣም ስለደከማቸው እረፍት ለማግኘት ጸጥ ወዳለ ቦታ ሄዱ። ሆኖም ማረፍ አልቻሉም። ያሰቡት ቦታ ሲደርሱ በጣም ብዙ ሰዎች እየጠበቋቸው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ለመማር ጓጉተው ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ሰዎቹ ተከትለውት ስለመጡ አልተበሳጨባቸውም። ከዚህ ይልቅ አዘነላቸው። ስለዚህ ኢየሱስ ምን አደረገ? “ብዙ [ነገር] ያስተምራቸው ጀመር።” (ማር. 6:30-34) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሌሎችን ለመርዳት ስንል ጊዜያችንንና ጉልበታችንን መሥዋዕት የምናደርግ ከሆነ የሰማዩን አባታችንን እናስከብራለን።—ማቴ. 5:14-16፤ w21.08 3 አን. 7-8
ሐሙስ፣ መጋቢት 9
እያንዳንዱ ሰው . . . ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።—ገላ. 6:4
ይሖዋ ልዩነት የሚወድ አምላክ ነው። የሰው ልጆችን ጨምሮ አስደናቂ በሆኑት ፍጥረታቱ መካከል የሚታየው ልዩነት ይህን ያረጋግጣል። እያንዳንዳችን ልዩ ነን። በመሆኑም ይሖዋ በፍጹም ከሌሎች ጋር አያወዳድርህም። ልብህን ማለትም ውስጣዊ ማንነትህን ይመረምራል። (1 ሳሙ. 16:7) በተጨማሪም ጥንካሬህን፣ ድክመትህን እና አስተዳደግህን ግምት ውስጥ ያስገባል። እንዲሁም ከአቅምህ በላይ አይጠብቅብህም። እኛም ስለ ራሳችን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት በማዳበር እሱን መምሰል ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን “ጤናማ አስተሳሰብ” ይኖረናል፤ በሌላ አባባል ራሳችንን ከልክ በላይ ከፍም ሆነ ዝቅ አድርገን አንመለከትም። (ሮም 12:3) እርግጥ ነው፣ ከሌሎች መልካም አርዓያነት መማር እንችላለን። ለምሳሌ በአገልግሎቱ ውጤታማ የሆነ ታማኝ ክርስቲያን እናውቅ ይሆናል። (ዕብ. 13:7) ከእሱ ምሳሌ፣ በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። (ፊልጵ. 3:17) ይሁንና የአንድን ሰው መልካም ምሳሌ በመከተልና ራሳችንን ከግለሰቡ ጋር በማወዳደር መካከል ልዩነት አለ። w21.07 20 አን. 1-2
ዓርብ፣ መጋቢት 10
ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ። እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው?—ኢሳ. 40:26
ስለ እንስሳት፣ ስለ ዕፀዋትና ስለ ከዋክብት ምርምር በማድረግ በፈጣሪ ላይ ያለህን እምነት ማጠናከር ትችላለህ። (መዝ. 19:1) ስለ እነዚህ ነገሮች ባጠናህ መጠን፣ ይሖዋ ፈጣሪ ስለመሆኑ ያለህ እምነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። ስለ ፍጥረት ሥራዎች ስታጠና፣ እነዚህ ነገሮች ስለ ፈጣሪያችን ምን እንደሚያስተምሩህ ለማስተዋል ሞክር። (ሮም 1:20) ለምሳሌ ያህል፣ ፀሐይ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነውን ሙቀት ብቻ ሳይሆን ጎጂ የሆኑ አልትራቫዮሌት ጨረሮችም እንደምታመነጭ ታውቅ ይሆናል። እኛ የሰው ልጆች ከእነዚህ ጨረሮች ከለላ ያስፈልገናል። ደግሞም እንዲህ ያለ ከለላ ተዘጋጅቶልናል! እንዴት? ምድራችን የራሷ የሆነ መከለያ አላት፤ ይህም ጎጂ የሆኑ ጨረሮችን ውጦ የሚያስቀር የኦዞን ንጣፍ ነው። ከፀሐይ የሚመጡት አልትራቫዮሌት ጨረሮች በጨመሩ መጠን በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የኦዞን መጠንም እየጨመረ ይሄዳል። እነዚህ ነገሮች በዚህ መልኩ እንዲሠሩ ያደረገ አፍቃሪና ጥበበኛ የሆነ ፈጣሪ መኖር አለበት ቢባል አትስማማም? w21.08 17 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ መጋቢት 11
አምላክን የሚወድ ሁሉ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል።—1 ዮሐ. 4:21
አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላም ለእሱ ፍቅርና አክብሮት ማሳየታችንን መቀጠል አለብን። (1 ዮሐ. 4:20) ይህ ምንን ይጨምራል? ለምሳሌ አንድን ነገር ለማድረግ ያነሳሳውን ውስጣዊ ዝንባሌ አንጠራጠርም። በሌላ አባባል፣ አንድን ነገር ያደረገው በክፋት ወይም በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ ነው ብለን አናስብም። ከዚህ ይልቅ ወንድማችን ከእኛ እንደሚበልጥ በማሰብ አክብሮት እናሳየዋለን። (ሮም 12:10፤ ፊልጵ. 2:3) እርግጥ ነው፣ ለሁሉም ሰው ምሕረትና ደግነት ማሳየት ይኖርብናል። ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ሆነን መኖር ከፈለግን የአምላክን ቃል በሕይወታችን በሥራ ላይ ማዋል አለብን። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ጠላቶቻችንን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ምሕረትና ደግነት ማሳየት እንዳለብን አስተምሯል። (ሉቃስ 6:32-36) ይህን ማድረግ አንዳንድ ጊዜ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ከሆነ በአስተሳሰባችንም ሆነ በምግባራችን ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋን ለመታዘዝና ኢየሱስን ለመምሰል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት ሆነን መኖር እንደምንፈልግ እናሳያለን። w21.08 6 አን. 14-15
እሁድ፣ መጋቢት 12
የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣ እስቲ በዚህ ፈትኑኝ።—ሚል. 3:10
በይሖዋ መታመንን ተማር። ይሖዋ በእሱ ከታመንን እና ምርጣችንን ከሰጠነው የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልን ቃል ገብቷል። መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት የተካፈሉ በርካታ ሰዎችን ታሪክ ይዟል። አብዛኞቹን ሰዎች ይሖዋ ልዩ በሆነ መንገድ የባረካቸው በእሱ እንደሚታመኑ የሚያሳይ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ ነው። ለምሳሌ አብርሃምን ይሖዋ የባረከው “ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም” ይኖርበት የነበረውን ስፍራ ለቆ ከወጣ በኋላ ነው። (ዕብ. 11:8) ያዕቆብም ልዩ በረከት ያገኘው ከመልአኩ ጋር ከታገለ በኋላ ነው። (ዘፍ. 32:24-30) የእስራኤል ብሔር ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገባ በተቃረበበት ጊዜ ደግሞ ሕዝቡ የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር የቻሉት ካህናቱ በኃይል ወደሚፈሰው ወንዝ እግራቸውን ካስገቡ በኋላ ነበር። (ኢያሱ 3:14-16) በይሖዋ ታምነው አገልግሎታቸውን ለማስፋት ጥረት ካደረጉ በዘመናችን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ብዙ ትምህርት ማግኘት ትችላለህ። w21.08 29-30 አን. 12-14
ሰኞ፣ መጋቢት 13
“የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?” አትበል።—መክ. 7:10
እናንት አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች፣ ቀደም ሲል ነገሮች እንዴት ይከናወኑ እንደነበረ ታውቃላችሁ፤ ሆኖም አዳዲስ ሁኔታዎችን ለማስተናገድ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ትገነዘባላችሁ። በቅርቡ የተጠመቃችሁ አረጋውያንም ለሌሎች ልታካፍሉ የምትችሉት ብዙ ነገር አላችሁ። ወጣቶች ተሞክሯችሁንና ያገኛችሁትን ትምህርት መስማት ያስደስታቸዋል። ካካበታችሁት ተሞክሮ ‘ለሰዎች ከሰጣችሁ’ ይሖዋም አብዝቶ ይባርካችኋል። (ሉቃስ 6:38) እናንት ውድ አረጋውያን፣ ከወጣቶች ጋር መቀራረባችሁ እርስ በርስ ለመበረታታት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍትላችኋል። (ሮም 1:12) እናንተ የሌላችሁ ነገር እነሱ አላቸው፤ እነሱ የሌላቸው ነገር ደግሞ እናንተ አላችሁ። አረጋውያን በረጅም ዕድሜ ያካበቱት ጥበብና ተሞክሮ አላቸው። ወጣቶች ደግሞ ጉልበትና ብርታት አላቸው። ወጣቶችና አረጋውያን ተባብረው ሲሠሩ ለአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ውዳሴ ያመጣሉ፤ ለመላው ጉባኤም በረከት ይሆናሉ። w21.09 8 አን. 3፤ 13 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ መጋቢት 14
በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁዳውያን መሰናክል . . . ነው።—1 ቆሮ. 1:23
ኢየሱስ የሞተበት መንገድ በርካታ አይሁዳውያንን ያሰናከላቸው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ስለሞተ ወንጀለኛና ኃጢአተኛ አድርገው ተመልክተውታል፤ ስለዚህ መሲሕ መሆኑን አልተቀበሉም። (ዘዳ. 21:22, 23) በኢየሱስ የተሰናከሉት አይሁዳውያን ኢየሱስ ምንም ወንጀል እንዳልሠራ፣ የተከሰሰው በሐሰት እንደሆነ እንዲሁም የፍትሕ መጓደል እንደተፈጸመበት አላስተዋሉም። በኢየሱስ ላይ ለመፍረድ ሸንጎ የተቀመጡት ሰዎች ስለ ፍትሕ ምንም ግድ አልነበራቸውም። የአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰየመው በጥድፊያ ነበር፤ የፍርድ ሂደቱም ተገቢውን አካሄድ የተከተለ አልነበረም። (ሉቃስ 22:54፤ ዮሐ. 18:24) ዳኞቹ በኢየሱስ ላይ የተሰነዘረውን ክስና የቀረበውን ማስረጃ ከአድልዎ ነፃ ሆነው ከማዳመጥ ይልቅ እነሱ ራሳቸው “ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የሐሰት የምሥክርነት ቃል እየፈለጉ ነበር።” (ማቴ. 26:59፤ ማር. 14:55-64) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም እነዚህ ግፈኛ ዳኞች የኢየሱስን መቃብር ይጠብቁ ለነበሩት ሮማውያን ወታደሮች “በርከት ያሉ የብር ሳንቲሞች” በመስጠት መቃብሩ ባዶ ስለሆነበት ምክንያት የሐሰት ወሬ እንዲያናፍሱ አደረጉ።—ማቴ. 28:11-15፤ w21.05 11 አን. 12-13
ረቡዕ፣ መጋቢት 15
ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።—ማቴ. 24:36
ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት በማንኛውም ጊዜ ሊያጠፋው ይችላል። ይሁንና ይሖዋ መታገሡ ብዙ በረከት አስገኝቶልናል! ሁሉም የአዳምና የሔዋን ዘሮች ሲወለዱ ጀምሮ ፍጹማን አይደሉም። ያም ቢሆን ይሖዋ ይወዳቸዋል፤ እንዲሁም ያስብላቸዋል፤ ይህን ክፉ ሥርዓት እንደሚያጠፋም ቃል ገብቷል። (1 ዮሐ. 4:19) ደግሞም በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ቀን ቀጥሯል። ይሖዋ እንደሚወደን ማወቃችን እሱ የቀጠረው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ እኛም አብረነው እንድንጸና ሊያነሳሳን አይገባም? ይሖዋ በጽናት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስም የአባቱን የጽናት ምሳሌ ተከትሏል። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ለእኛ ሲል የተቃውሞ ንግግርን እና ውርደትን በጽናት ተቋቁሟል፤ እንዲሁም በመከራ እንጨት ላይ እስከመሞት ድረስ ጸንቷል። (ዕብ. 12:2, 3) ኢየሱስ እንዲጸና ብርታት የሆነው የይሖዋ የጽናት ምሳሌ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። የይሖዋ ምሳሌ እኛንም ሊያበረታን ይችላል። w21.07 12-13 አን. 15-17
ሐሙስ፣ መጋቢት 16
አባታችሁ መሐሪ እንደሆነ ሁሉ እናንተም መሐሪዎች ሁኑ።—ሉቃስ 6:36
የሰማዩ አባታችን በየዕለቱ ምሕረት ያደርግልናል። (መዝ. 103:10-14) ኢየሱስም ተከታዮቹ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ምሕረትና ይቅር ባይነት አሳይቷቸዋል። ኢየሱስ ለኃጢአታችን ይቅርታ እንድናገኝ ሲል ሕይወቱን እንኳ ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) እኛም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ‘በነፃ ይቅር በማለት’ በመንፈሳዊ ቤተሰባችን ውስጥ ያለው ፍቅር እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። (ኤፌ. 4:32) እርግጥ ነው፣ ሌሎችን ይቅር ማለት አንዳንድ ጊዜ በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። አንዲት እህት “እርስ በርስ በነፃ ይቅር ተባባሉ” የሚለው የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ ይህን ለማድረግ እንደረዳት ተናግራለች። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ርዕሱ ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆን ሲባል መጥፎ ባሕርያቸውን ትክክል እንደሆነ አድርጎ መቀበል ወይም ያደረሱትን ጉዳት አቅልሎ መመልከት ማለት እንዳልሆነ ይገልጻል። ከዚህ ይልቅ፣ ይቅር እንላለን ሲባል በተፈጸመብን በደል ምክንያት ቅሬታ እንዳያድርብንና ሰላማችንን እንዳናጣ ጥረት እናደርጋለን ማለት ነው።” ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በነፃ ይቅር በማለት እንደምንወዳቸው እናሳያለን፤ የሰማዩን አባታችንን ይሖዋንም እንመስላለን። w21.09 23-24 አን. 15-16
ዓርብ፣ መጋቢት 17
[አምላክን] የሚያመልኩ . . . በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።—ዮሐ. 4:24
ኢየሱስ ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ለሚገልጸው እውነት ፍቅር ነበረው። ከዚህ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ይኖር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ይህን እውነት ለሌሎች አሳውቋል። (ዮሐ. 18:37) የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮችም ለእውነት ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው። (ዮሐ. 4:23) እንዲያውም ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስትናን “የእውነት መንገድ” በማለት ጠርቶታል። (2 ጴጥ. 2:2) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ለእውነት ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው ከእውነት ጋር የሚቃረኑ ሃይማኖታዊ ሐሳቦችን፣ ወጎችንና የግል አመለካከቶችን አይቀበሉም ነበር። (ቆላ. 2:8) በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም የሚያምኑበት ነገርና አኗኗሯቸው፣ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ፤ በዚህ መንገድ ‘በእውነት ውስጥ እንደሚመላለሱ’ ያሳያሉ። (3 ዮሐ. 3, 4) በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ስለ እውነት የተሟላ ወይም ፍጹም ግንዛቤ እንዳላቸው አይናገሩም። ከመሠረተ ትምህርትና ከድርጅታዊ አሠራር ጋር በተያያዘ ስህተት የሠሩባቸው ጊዜያት አሉ። መስተካከል ያለበት ነገር እንዳለ ሲገነዘቡ ግን አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርገዋል። w21.10 21-22 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ መጋቢት 18
በይሖዋ የሚታመን ሰው . . . ታማኝ ፍቅሩ ይከበዋል።—መዝ. 32:10
ጥንታዊ ከተሞች በቅጥር መከበባቸው ለነዋሪዎቹ ጥበቃ ያስገኝ ነበር። በተመሳሳይም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ዙሪያችንን በመክበብ፣ ታማኝነታችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ነገሮች መንፈሳዊ ጥበቃ ያስገኝልናል። በተጨማሪም የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ወደ ራሱ እንዲስበን ያነሳሳዋል። (ኤር. 31:3) መዝሙራዊው ዳዊት የአምላክ ሕዝቦች የሚያገኙትን ጥበቃ ለመግለጽ ሌላም ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ታማኝ ፍቅር የሚያሳየኝ አምላክ አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው።” በተጨማሪም ዳዊት ስለ ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “እሱ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየኝ አምላኬና ምሽጌ፣ አስተማማኝ መጠጊያዬና ታዳጊዬ፣ ጋሻዬና መጠለያዬ . . . ነው።” (መዝ. 59:17፤ 144:2) ዳዊት የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ከመጠጊያ እና ከምሽግ ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው? የምንኖረው የትም ይሁን የት ይሖዋ የእሱ አገልጋዮች እስከሆንን ድረስ ከእሱ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና ይዘን መቀጠል እንድንችል የሚያስፈልገንን ጥበቃ ሁሉ ያደርግልናል። w21.11 6 አን. 14-15
እሁድ፣ መጋቢት 19
በሥራዎችህም ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ።—መዝ. 77:12
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በባሕር ላይ እየተጓዙ ሳሉ ማዕበል አጋጥሟቸው ነበር። ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ ደቀ መዛሙርቱ በየትኛው አቅጣጫ እምነታቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልጋቸው ለማስተማር ተጠቀመበት። (ማቴ. 8:23-26) በማዕበሉ ምክንያት ጀልባዋ በውኃ ተሞልታ ልትሰጥም ተቃርባ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ ለጥ ብሎ ተኝቶ ነበር። በፍርሃት የተዋጡት ደቀ መዛሙርቱ ቀስቅሰው እንዲያድናቸው ጠየቁት፤ በዚህ ጊዜ ጌታ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?” በማለት በደግነት ተግሣጽ ሰጣቸው። እናንተስ በሕይወታችሁ ውስጥ “ኃይለኛ ማዕበል” አጋጥሟችኋል? በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት መከራ ደርሶባችሁ ይሆናል። ወይም ደግሞ ምሳሌያዊ ማዕበል አጋጥሟችሁ ይሆናል፤ ምናልባትም ባጋጠማችሁ ከባድ የጤና ችግር ምክንያት ተስፋ ቆርጣችሁና ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ግራ ገብቷችሁ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ በጭንቀት ትዋጡ ይሆናል፤ ያም ቢሆን የሚሰማችሁ ጭንቀት በይሖዋ ከመታመን እንቅፋት እንዲሆንባችሁ አትፍቀዱ። ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ይሖዋን አነጋግሩት። ይሖዋ ከዚህ ቀደም የረዳችሁ እንዴት እንደሆነ በማሰላሰል እምነታችሁን አጠናክሩ። (መዝ. 77:11) ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተዋችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ። w21.11 22 አን. 7, 10
ሰኞ፣ መጋቢት 20
አትስረቁ።—ዘሌ. 19:11
አንድ ሰው የሌላን ሰው ንብረት እስካልወሰደ ድረስ ይህን ሕግ እንደታዘዘ ይሰማው ይሆናል። ይሁንና በሌሎች መንገዶች ይሰርቅ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ትክክለኛ ያልሆነ ሚዛን ወይም መለኪያ በመጠቀም ደንበኞቹን የሚያታልል ነጋዴ ከእነሱ እየሰረቀ ነው ሊባል ይችላል። ዘሌዋውያን 19:13 “ባልንጀራህን አታጭበርብር” ይላል፤ ይህም በስርቆትና ሐቀኝነት በጎደለው ንግድ መካከል ያለውን ግንኙነት ይጠቁማል። ስለዚህ አንድ ሰው ከንግድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚያጭበረብር ከሆነ እየሰረቀ ነው ማለት ነው። ስምንተኛው ትእዛዝ መስረቅ ስህተት መሆኑን በግልጽ ይናገራል፤ በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ ከዚህ ሕግ በስተ ጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ይጠቁማል። እኛም ይሖዋ ሐቀኝነት ስለ ማጉደልና ስለ መስረቅ ባለው አመለካከት ላይ ቆም ብለን ማሰባችን ይጠቅመናል። ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በዘሌዋውያን 19:11-13 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ አንጻር በሕይወቴ ውስጥ ላስተካክለው የሚገባ ነገር አለ? ከንግድ እንቅስቃሴዬ ወይም ከሥራ ልማዴ ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገኝ ይሆን?’ w21.12 9-10 አን. 6-8
ማክሰኞ፣ መጋቢት 21
ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።—ቆላ. 3:13
በግልህ በምታቀርበው ጸሎት ላይ በቀኑ ውስጥ የሠራሃቸውን ስህተቶች አስበህ ይሖዋ ይቅር እንዲልህ ጠይቀው። እርግጥ ከባድ ኃጢአት ፈጽመህ ከሆነ የሽማግሌዎች እርዳታም ያስፈልግሃል፤ ሽማግሌዎች ጆሮ ሰጥተው ያዳምጡሃል። እንዲሁም በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክር ይሰጡሃል። ሽማግሌዎቹ አብረውህ በመጸለይ ይሖዋ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት በመንፈሳዊ ‘እንዲፈውስህ’ ልመና ያቀርባሉ። (ያዕ. 5:14-16) በተጨማሪም በቤዛው ላይ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። የአምላክ ልጅ ስለደረሰበት ከፍተኛ ሥቃይ ስታስብ በእጅጉ ታዝን ይሆናል። ሆኖም ኢየሱስ ስለከፈለው መሥዋዕት ይበልጥ ባሰላሰልክ መጠን ለእሱም ሆነ ለአባቱ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል። በየዓመቱ በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ በመገኘት እንዲሁም ሌሎችም በዚህ በዓል ላይ እንዲገኙ በቅንዓት በመጋበዝ ለቤዛው ያለንን አድናቆት ማሳደግ እንችላለን። ይሖዋ ስለ ልጁ ሌሎችን የማስተማር መብት የሰጠን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! w21.04 18-19 አን. 13-16
ረቡዕ፣ መጋቢት 22
ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።—ማር. 6:34
እስቲ ኢየሱስ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት፤ ከተራራ ሲወርድ ብዙ ሰዎች ሊያገኙት መጡ። ታዲያ ኢየሱስ ምን ተሰምቶት ይሆን? ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሮ ነበር። ስለዚህ በጣም ደክሞት መሆን አለበት፤ ሆኖም በሕዝቡ መካከል ያሉትን ድሆችና የታመሙ ሰዎች ሲመለከት አንጀቱ አልቻለም። ሕዝቡን መፈወስ ብቻ ሳይሆን ንግግር ሰጣቸው፤ ይህ ንግግር እስከ ዛሬ ከቀረቡት ሁሉ ቀስቃሽ የሆነውና የተራራው ስብከት ተብሎ የሚጠራው ንግግር ነው። (ሉቃስ 6:12-20) ኢየሱስ ብቻውን መሆን የሚፈልግበትን ጊዜም ለሌሎች ሰጥቷል። ወዳጁ የሆነው አጥማቂው ዮሐንስ እንደተገደለ ሲሰማ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ [የዮሐንስን ሞት] ሲሰማ ብቻውን ለመሆን በጀልባ ተሳፍሮ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ።” (ማቴ. 14:10-13) ሆኖም እጅግ ብዙ ሰዎች እሱ ሊሄድበት ወዳሰበው ገለል ያለ ስፍራ ቀድመውት መጡ። (ማር. 6:31-33) ሕዝቡ መንፈሳዊ ማበረታቻ በጣም እንደሚያስፈልጋቸው ኢየሱስ አስተውሎ ነበር፤ ደግሞም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ወዲያውኑ አድርጎላቸዋል።—ሉቃስ 9:10, 11፤ w22.02 21 አን. 4, 6
ሐሙስ፣ መጋቢት 23
ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም [ኑሩ]።—ሮም 12:18
አንድ የእምነት ባልንጀራችንን ቅር እንዳሰኘነው ብንገነዘብ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ይኖርብናል። ከወንድማችን ጋር ሰላም ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት እንዲባርክልን ይሖዋን ልንለምነው እንችላለን። በተጨማሪም ራሳችንን መመርመር ያስፈልገናል። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ኩራቴን ዋጥ አድርጌ በትሕትና ይቅርታ ለመጠየቅና ሰላም ለመፍጠር ፈቃደኛ ነኝ? ቅድሚያውን ወስጄ ከወንድሜ ወይም ከእህቴ ጋር ለመታረቅ ጥረት ባደርግ ይሖዋ እና ኢየሱስ ምን ይሰማቸዋል?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ኢየሱስን እንድንሰማ እንዲሁም ትሑት ሆነን የእምነት ባልንጀራችንን እንድናነጋግረውና ሰላም እንድንፈጥር ይረዳናል። ከወንድማችን ጋር ሰላም ለመፍጠር ስንሄድ በትሕትና ልናነጋግረው ይገባል። (ኤፌ. 4:2, 3) የወንድማችን ቅሬታ እንዲወገድ የማድረግ ግብ ይዘን እናነጋግረው። ዋናው ነገር ከወንድማችን ጋር ሰላም መፍጠራችን እንጂ ‘ጥፋተኛው ማን ነው?’ የሚለው እንዳልሆነ ልናስታውስ ይገባል።—1 ቆሮ. 6:7፤ w21.12 26 አን. 13-16
ዓርብ፣ መጋቢት 24
ከተማዋን አይቶ አለቀሰላት።—ሉቃስ 19:41
ኢየሱስ አብዛኞቹ የአገሩ ሰዎች መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ያውቅ ነበር፤ ልቡ ያዘነው ለዚህ ነው። በዚህ አካሄዳቸው የተነሳ ኢየሩሳሌም ጥፋት እንደሚደርስባት፣ ከጥፋቱ የተረፉት አይሁዳውያንም ቢሆኑ በግዞት እንደሚወሰዱ ያውቅ ነበር። (ሉቃስ 21:20-24) የሚያሳዝነው ልክ ኢየሱስ እንደጠበቀው ሕዝቡ በአብዛኛው አልተቀበሉትም። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ሰዎች በአብዛኛው ለመንግሥቱ መልእክት ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ? እውነትን ለማስተማር ለምታደርገው ጥረት በጎ ምላሽ የሚሰጡት ጥቂቶች ናቸው? ከሆነ ኢየሱስ እንባውን እንዳፈሰሰ ከሚገልጸው ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? ይሖዋ ለሰዎች ያስባል። የኢየሱስ እንባ ይሖዋ ለሰዎች ምን ያህል እንደሚያስብ ያስታውሰናል። ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።” (2 ጴጥ. 3:9) በዛሬው ጊዜም ለሰዎች ምሥራቹን ለመንገርና ልባቸውን ለመንካት በምናደርገው ጥረት እስከ መጨረሻው በመቀጠል ባልንጀሮቻችንን እንደምንወድ እናሳያለን።—ማቴ. 22:39፤ w22.01 16-17 አን. 10-12
ቅዳሜ፣ መጋቢት 25
አንተን የሙጥኝ እላለሁ፤ ቀኝ እጅህ አጥብቆ ይይዘኛል።—መዝ. 63:8
ቀደም ሲል ይሖዋ ለሕዝቡ ባደረገውና በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ባደረገልህ ነገር ላይ ስታሰላስል እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል። ከሁሉ በላይ ግን ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ይጨምራል። ከየትኛውም ባሕርይ የበለጠ ፍቅር ይሖዋን እንድትታዘዘው፣ እሱን ለማስደሰት ስትል መሥዋዕትነት እንድትከፍል እንዲሁም ማንኛውንም መከራ በጽናት እንድትቋቋም ያነሳሳሃል። (ማቴ. 22:37-39፤ 1 ቆሮ. 13:4, 7፤ 1 ዮሐ. 5:3) በእርግጥም ለእኛ ከይሖዋ ጋር ከመሠረትነው የጠበቀ ወዳጅነት የሚበልጥብን ምንም ነገር የለም። (መዝ. 63:1-7) ጸሎት፣ ጥናትና ማሰላሰል የአምልኳችን ክፍል እንደሆኑ አትርሳ። ልክ እንደ ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችልህ ጸጥ ያለ ስፍራ ፈልግ። ትኩረት የሚከፋፍሉ አላስፈላጊ ነገሮችን አርቅ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ስትካፈል ትኩረትህን መሰብሰብ እንድትችል የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። ጊዜህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የምትጥር ከሆነ ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት በመስጠት አብዝቶ ይክስሃል።—ማር. 4:24፤ w22.01 31 አን. 18-20
እሁድ፣ መጋቢት 26
ክፉ የሆነውን ተጸየፉ።—ሮም 12:9
አስተሳሰባችን በድርጊታችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ኢየሱስ ወደ ከባድ ኃጢአት የሚመሩ ሐሳቦችን እንድናስወግድ ያስተማረን ለዚህ ነው። (ማቴ. 5:21, 22, 28, 29) ፍላጎታችን የሰማዩን አባታችንን ማስደሰት እንደሆነ ግልጽ ነው። እንግዲያው ማንኛውም መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯችን ሲገባ በዚያው ቅጽበት ማስወጣታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ኢየሱስ “ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል” ብሏል። (ማቴ. 15:18) በእርግጥም ንግግራችን ውስጣዊ ማንነታችንን በግልጽ ያሳያል። ስለዚህ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘እውነቱን መናገሬ ችግር ውስጥ የሚያስገባኝ ቢሆንም እንኳ ከመዋሸት እቆጠባለሁ? ከትዳር ጓደኛዬ ውጭ ማንንም ላለማሽኮርመም እጠነቀቃለሁ? የብልግና ንግግርን እንደ ተላላፊ በሽታ እርቃለሁ? አንድ ሰው ሲያበሳጨኝ በረጋ መንፈስ እመልሳለሁ?’ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰልህ ጠቃሚ ነው። ስድብን፣ ውሸትንና የብልግና ንግግርን ለማስወገድ የቻልከውን ያህል ስትጥር አሮጌውን ስብዕና ገፎ መጣል ቀላል ይሆንልሃል። w22.03 5 አን. 12-14
ሰኞ፣ መጋቢት 27
ምክር በሚሹ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።—ምሳሌ 13:10
አንድ ሰው ቀርቦ እስኪያነጋግራቸው ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸው ሄደው ምክር የሚጠይቁ ሰዎች፣ ብዙውን ጊዜ ይህን ከማያደርጉ ሰዎች የበለጠ መንፈሳዊ እድገት ያደርጋሉ። እንግዲያው ቅድሚያውን ወስዳችሁ ምክር ጠይቁ። የእምነት አጋሮቻችን ምክር እንዲሰጡን የምንጠይቀው መቼ ሊሆን ይችላል? እስቲ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንመልከት። (1) አንዲት እህት፣ ተሞክሮ ያላትን አንዲት አስፋፊ ጥናቷ ላይ ጋበዘቻት፤ በኋላ ላይ ከማስተማር ችሎታዋ ጋር በተያያዘ ማሻሻል የሚኖርባት ነገር ካለ ምክር ጠየቀቻት። (2) አንዲት ያላገባች እህት ልብስ መግዛት ፈልጋለች፤ ስለዚህ ምርጫዋን በተመለከተ በሐቀኝነት አስተያየት እንድትሰጣት አንዲትን የጎለመሰች እህት ጠየቀቻት። (3) አንድ ወንድም ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር ሊያቀርብ ነው። አንድን ተሞክሮ ያለው ተናጋሪ፣ ንግግሩን አዳምጦ የሚያሻሽላቸው ነገሮች ካሉ እንዲነግረው ይጠይቀዋል። ለብዙ ዓመታት ንግግር የሰጠ ወንድምም እንኳ ተሞክሮ ያላቸውን ወንድሞች ምክር መጠየቁና ምክሩን ተግባራዊ ማድረጉ ይጠቅመዋል።—ምሳሌ 19:20፤ w22.02 13 አን. 15-17
ማክሰኞ፣ መጋቢት 28
ብቻዬን [አይደለሁም]፤ ከዚህ ይልቅ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው።—ዮሐ. 8:16
ይሖዋ፣ ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሁሉ ፍቅር እንዳሳየውና እንደተንከባከበው ሁሉ ለእኛም ፍቅር ያሳየናል እንዲሁም ይንከባከበናል። (ዮሐ. 5:20) ይሖዋ የኢየሱስን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ሥጋዊ ፍላጎት በሙሉ አሟልቶለታል። በተጨማሪም ይሖዋ ልጁን እንደሚወደውና እንደሚደሰትበት ከመግለጽ ወደኋላ አላለም። (ማቴ. 3:16, 17) ኢየሱስም የሚወደው ሰማያዊ አባቱ ከጎኑ እንደሆነ ስለሚያውቅ መቼም ቢሆን ብቻውን እንደሆነ ተሰምቶት አያውቅም። ሁላችንም ልክ እንደ ኢየሱስ የይሖዋን ፍቅር በተለያዩ መንገዶች አይተናል። እስቲ አስበው፤ ይሖዋ ወደ ራሱ ስቦናል፤ እንዲሁም ደስተኛ እንድንሆንና የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እንድናገኝ ሲል አፍቃሪ የሆነና አንድነት ያለው መንፈሳዊ ቤተሰብ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 6:44) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ ያቀርብልናል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለኑሮ የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች እንድናገኝ ይረዳናል። (ማቴ. 6:31, 32) ይሖዋ ስላሳየን ፍቅር ስናስብ እኛም ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። w21.09 22 አን. 8-9
ረቡዕ፣ መጋቢት 29
አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ።—ቆላ. 3:9
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመርህ በፊት ሕይወትህ ምን ይመስል ነበር? ብዙዎቻችን ያንን ሕይወታችንን ማሰብ እንኳ አንፈልግም። አስተሳሰባችንና ስብዕናችን የተቀረጸው ዓለም ትክክል እና ስህተት ብሎ ባወጣቸው መሥፈርቶች ነበር። “በዓለም ውስጥ ያለተስፋና ያለአምላክ” እንኖር ነበር። (ኤፌ. 2:12) መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና ግን የሰማዩ አባትህ በጣም እንደሚወድህ ተማርክ። ይሖዋን ለማስደሰት እንዲሁም የእሱን አገልጋዮች ያቀፈው ቤተሰብ አባል ለመሆን በአኗኗርህና በአመለካከትህ ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ተገነዘብክ። በሕይወትህ ውስጥ ላቅ ያሉትን የእሱን መሥፈርቶች መከተል እንዳለብህ አወቅህ። (ኤፌ. 5:3-5) ፈጣሪያችንና ሰማያዊ አባታችን የሆነው ይሖዋ፣ የቤተሰቡ አባላት ሊያሳዩት የሚገባውን ምግባር የመወሰን መብት አለው። ደግሞም ከመጠመቃችን በፊት “አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ [ገፈን ለመጣል]” ጥረት እንድናደርግ ይጠብቅብናል። w22.03 2 አን. 1-3
ሐሙስ፣ መጋቢት 30
ሌሎች በጎች አሉኝ።—ዮሐ. 10:16
ሌሎች በጎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ታዳሚ ሆነው በመገኘታቸው ደስተኛ ናቸው፤ በተስፋቸው ላይ ለማሰላሰልም አጋጣሚ ያገኛሉ። የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ዕለት የሚሰጠውን ንግግር ለማዳመጥ ይጓጓሉ፤ ምክንያቱም ንግግሩ በአብዛኛው የሚያተኩረው ክርስቶስ እና 144,000 ተባባሪ ገዢዎቹ በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ለታማኝ የሰው ልጆች በሚያደርጉት ነገር ላይ ነው። እነዚህ ተባባሪ ገዢዎች በንጉሣቸው በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው ምድር ገነት እንድትሆን እንዲሁም የሰው ዘር ፍጽምና ደረጃ ላይ እንዲደርስ በሚከናወነው ሥራ ትልቅ እገዛ ያበረክታሉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት የመታሰቢያው በዓል ታዳሚዎች እንደ ኢሳይያስ 35:5, 6፤ 65:21-23 እና ራእይ 21:3, 4 ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ላይ በማሰላሰል ምን ያህል እንደሚደሰቱ አስቡት። ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖራቸውን ሕይወት በዓይነ ሕሊናቸው መሣላቸው የወደፊቱ ተስፋቸው ይበልጥ እውን እንዲሆንላቸው ያደርጋል፤ ይሖዋን እስከ መጨረሻው ለማገልገል ያላቸው ቁርጠኝነትም ይጠናከራል።—ማቴ. 24:13፤ ገላ. 6:9፤ w22.01 21 አን. 5-7
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ማቴዎስ 26:6-13
ዓርብ፣ መጋቢት 31
የሰው ልጅ . . . የመጣው . . . በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት [ነው]።—ማር. 10:45
ቤዛው ምንድን ነው? አዳም ያጣውን ነገር ለማስመለስ ኢየሱስ የከፈለው ዋጋ ነው። (1 ቆሮ. 15:22) ቤዛው የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? በሙሴ ሕግ ውስጥ በተገለጸው የይሖዋ የፍትሕ መሥፈርት መሠረት ሕይወት ስለ ሕይወት መከፈል ስላለበት ነው። (ዘፀ. 21:23, 24) አዳም ያጣው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ነው። ስለዚህ በአምላክ ሕግ መሠረት ፍትሕ እንዲፈጸም ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አደረገ። (ሮም 5:17) በመሆኑም በቤዛው ለሚያምኑ ሁሉ “የዘላለም አባት” ሆነ። (ኢሳ. 9:6፤ ሮም 3:23, 24) ኢየሱስ በሰማይ ላለው አባቱና ለእኛ ታላቅ ፍቅር ስላለው ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዮሐ. 14:31፤ 15:13) እንዲህ ዓይነት ፍቅር ያለው መሆኑ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ለመሆን እንዲሁም የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም አነሳስቶታል። ኢየሱስ ይህን ማድረጉ ይሖዋ መጀመሪያ ላይ ለሰው ልጆችና ለምድር የነበረው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል። w21.04 14 አን. 2-3
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ማቴዎስ 21:1-11, 14-17