የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es23 ገጽ 57-67
  • ሰኔ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሰኔ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 1
  • ዓርብ፣ ሰኔ 2
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 3
  • እሁድ፣ ሰኔ 4
  • ሰኞ፣ ሰኔ 5
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 6
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 7
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 8
  • ዓርብ፣ ሰኔ 9
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 10
  • እሁድ፣ ሰኔ 11
  • ሰኞ፣ ሰኔ 12
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 13
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 14
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 15
  • ዓርብ፣ ሰኔ 16
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 17
  • እሁድ፣ ሰኔ 18
  • ሰኞ፣ ሰኔ 19
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 20
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 21
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 22
  • ዓርብ፣ ሰኔ 23
  • ቅዳሜ፣ ሰኔ 24
  • እሁድ፣ ሰኔ 25
  • ሰኞ፣ ሰኔ 26
  • ማክሰኞ፣ ሰኔ 27
  • ረቡዕ፣ ሰኔ 28
  • ሐሙስ፣ ሰኔ 29
  • ዓርብ፣ ሰኔ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
es23 ገጽ 57-67

ሰኔ

ሐሙስ፣ ሰኔ 1

አንዲት ድሃ መበለት መጥታ በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ከተተች።—ማር. 12:42

ለዚህች መበለት ኑሮ በጣም ከባድ እንደሚሆንባት ምንም ጥያቄ የለውም፤ ምናልባትም መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ ለማግኘት ትቸገር ይሆናል። ያም ቢሆን ወደ አንዱ የመዋጮ ሣጥን ሄዳ ቀስ ብላ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ከተተች፤ እነዚህ ሳንቲሞች ሣጥኑ ውስጥ ሲገቡ ምንም ድምፅ አላሰሙ ይሆናል። ኢየሱስ ይህች ሴት ምን ያህል መዋጮ እንዳደረገች አውቋል፤ መዋጮ ያደረገችው በወቅቱ ከነበሩት ሳንቲሞች ሁሉ በጣም ትንሽ የሆኑትን ሁለት ሌፕተን ሳንቲሞች ነው። ሳንቲሞቹ አንዲት ድንቢጥ እንኳ አይገዙም ነበር፤ በወቅቱ ለምግብነት ከሚሸጡት ወፎች መካከል በጣም ርካሽ የሆኑት ድንቢጦች ነበሩ። ኢየሱስ ይህች መበለት ያደረገችው ነገር ልቡን በጥልቅ ነክቶታል። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ መበለቷን አሳያቸውና “[ከሁሉም] የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች” አላቸው። ቀጥሎም እንዲህ አላቸው፦ “ሁሉም [በተለይም ሀብታሞቹ] የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች።” (ማር. 12:43, 44) ይህች ታማኝ መበለት በዚያ ቀን ያላትን ገንዘብ አሟጥጣ ስትሰጥ፣ ይሖዋ እንደሚንከባከባት ሙሉ በሙሉ እንደምትተማመን አሳይታለች።—መዝ. 26:3፤ w21.04 6 አን. 17-18

ዓርብ፣ ሰኔ 2

ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋታል።—ሥራ 5:28

ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ አዎንታዊ አመለካከት ነበረው፤ ተከታዮቹም ለአገልግሎት አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። (ዮሐ. 4:35, 36) ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ ጋር በነበሩበት ወቅት የስብከቱን ሥራ በቅንዓት አከናውነዋል። (ሉቃስ 10:1, 5-11, 17) ኢየሱስ ከተያዘና ከተገደለ በኋላ ግን ደቀ መዛሙርቱ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የአገልግሎት ቅንዓታቸው ቀዝቅዞ ነበር። (ዮሐ. 16:32) ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አበረታታቸው። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በከፍተኛ ቅንዓት ከመስበካቸው የተነሳ ጠላቶቻቸው በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ተናግረው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን ሥራ የሚመራው ኢየሱስ ነበር፤ ይሖዋም እድገት እንዲያደርጉ በመርዳት ባርኳቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ በዓል በተከበረበት ዕለት 3,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ተጠምቀዋል። (ሥራ 2:41) የደቀ መዛሙርቱም ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ማደጉን ቀጠለ። (ሥራ 6:7) ያም ቢሆን ኢየሱስ የስብከቱ ሥራ በመጨረሻዎቹ ቀናት ይበልጥ ፍሬያማ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል።—ዮሐ. 14:12፤ ሥራ 1:8፤ w21.05 14 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ሰኔ 3

በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።—ማቴ. 11:6

እውነትን እንዳገኘህ የተገነዘብክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ይህን እውነት ሁሉም ሰው እንደሚቀበለው አስበህ ነበር። የነገርካቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ቢቀበሉ በአሁኑ ጊዜ ሕይወታቸው ትርጉም ያለው እንደሚሆን፣ ለወደፊቱም አስደናቂ ተስፋ እንደሚኖራቸው እርግጠኛ ሆነህ ነበር። (መዝ. 119:105) በመሆኑም ያገኘኸውን እውነት ለጓደኞችህና ለቤተሰቦችህ ሁሉ በጉጉት ነገርካቸው። ሆኖም ለመልእክቱ ምን ምላሽ ሰጡ? ብዙዎቹ መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ይህን ስታይ በጣም ተገርመህ መሆን አለበት። ማናችንም ብንሆን ሰዎች የምንሰብከውን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑ ልንገረም አይገባም። ኢየሱስ፣ ከአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ተአምራትን ቢፈጽምም እንኳ በዘመኑ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች አልተቀበሉትም። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል፤ ይህ ተቃዋሚዎቹ እንኳ ሊክዱ የማይችሉት ተአምር ነው። ያም ቢሆን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አልተቀበሉም። እንዲያውም ኢየሱስንም ሆነ አልዓዛርን ለመግደል ተነሱ!—ዮሐ. 11:47, 48, 53፤ 12:9-11፤ w21.05 2 አን. 1-2

እሁድ፣ ሰኔ 4

መሰብሰባችንን ቸል አንበል፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ።—ዕብ. 10:25

በስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ለመገኘት ጥረት አድርግ። የሚቀርበው ትምህርት ያበረታታሃል፤ እንዲሁም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ይበልጥ የመተዋወቅ አጋጣሚ ታገኛለህ። በጉባኤ ውስጥ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑልህ የሚችሉ ወዳጆች ፈልግ፤ እነዚህ ወንድሞች ከአንተ የተለየ ዕድሜና አስተዳደግ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “በዕድሜ በገፉት መካከል ጥበብ” እንደሚገኝ ይናገራል። (ኢዮብ 12:12) በዕድሜ ተለቅ ያሉ ክርስቲያኖችም ከታማኝ ወጣቶች ብዙ የሚማሩት ነገር አለ። ዳዊት ከዮናታን ዕድሜው በጣም ያንስ ነበር፤ ይህ መሆኑ ግን የቅርብ ወዳጅነት ከመመሥረት አላገዳቸውም። (1 ሳሙ. 18:1) ዳዊትና ዮናታን እርስ በርስ መረዳዳታቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። (1 ሳሙ. 23:16-18) በቤተሰቧ ውስጥ ብቸኛ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው አይሪና እንዲህ ብላለች፦ “የእምነት ባልንጀሮቻችን መንፈሳዊ ወላጆቻችን፣ ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ሊሆኑልን ይችላሉ። ይሖዋ የሚያስፈልገንን እርዳታ ለመስጠት በእነሱ ሊጠቀም ይችላል።” ወዳጆችህ ሊያበረታቱህና ሊደግፉህ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልግህ ልትነግራቸው ይገባል። w21.06 10-11 አን. 9-11

ሰኞ፣ ሰኔ 5

እናንተም እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ በሰማይ ያለው አባቴ እንደዚሁ ያደርግባችኋል።—ማቴ. 18:35

ኢየሱስ ስለ አንድ ንጉሥ እና ስለ ባሪያው የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል። ባሪያው መቼም ቢሆን ሊከፍለው የማይችል ብዙ ዕዳ ነበረበት፤ ንጉሡም ዕዳውን ሰረዘለት። በኋላ ላይ ግን ይኸው ባሪያ፣ ከእሱ በጣም ያነሰ ዕዳ ለነበረበት ሌላ ባሪያ ምሕረት ለማሳየት ፈቃደኛ አልሆነም። በመጨረሻም ንጉሡ ምሕረት ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆነውን ባሪያ ወደ ወህኒ ጣለው። ባሪያው ምሕረት ባለማድረጉ የጎዳው ራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ጭምር ነው። በመጀመሪያ፣ ከእሱ የተበደረው ባሪያ “ያለበትን ዕዳ እስኪከፍል ድረስ ወህኒ ቤት” በማሳሰር ደግነት የጎደለው ድርጊት ፈጽሞበታል። ሁለተኛ፣ ሁኔታውን በተመለከቱ ሌሎች ባሪያዎችም ላይ ጉዳት አድርሷል። ኢየሱስ፣ “ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሪያዎች የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ እጅግ አዘኑ” ብሏል። (ማቴ. 18:30, 31) በተመሳሳይም የእኛ ድርጊት ሌሎችን ሊጎዳ ይችላል። የበደለንን ሰው ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ባንሆን ምን ሊፈጠር ይችላል? በመጀመሪያ ለወንድማችን ይቅርታ፣ ትኩረትና ፍቅር መንፈጋችን እሱን ይጎዳዋል። ሁለተኛ፣ ከወንድማችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የሌለን መሆኑ በጉባኤያችን ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች እንዲሳቀቁ ያደርጋል። w21.06 22 አን. 11-12

ማክሰኞ፣ ሰኔ 6

ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋል]።—ራእይ 11:18

ሰይጣን በአምላክ መልክ የተፈጠሩት የሰው ልጆች ራሳቸውን ሲያዋርዱ ማየት ያስደስተዋል። በኖኅ ዘመን “ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛ” ሲመለከት “ሰዎችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም አዘነ።” (ዘፍ. 6:5, 6, 11) ከዚያ ወዲህ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ ተሻሽሏል? በፍጹም! ዲያብሎስ ተቃራኒም ሆነ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ብልግና ጨምሮ ሁሉም ዓይነት የፆታ ብልግና በዓለም ላይ እንደተስፋፋ ሲያይ በጣም እንደሚደሰት ጥያቄ የለውም። (ኤፌ. 4:18, 19) በተለይ የይሖዋ አምላኪ የሆኑ ሰዎች ከባድ ኃጢአት እንዲፈጽሙ በማድረግ ረገድ ሲሳካለት ሰይጣን በጣም ይደሰታል። በሰይጣን አገዛዝ ሥር “ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ” ነው፤ ይህም እንዳይበቃ ደግሞ የሰው ልጆች ይሖዋ በአደራ የሰጣቸውን ምድርንና እንስሳትን እያጠፉ ነው። (መክ. 8:9፤ ዘፍ. 1:28) ይህ ምን ውጤት አስከትሏል? አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የሰው ልጆች በሚያደርጉት ነገር ምክንያት በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ዝርያዎች ከምድር ገጽ ሊጠፉ ይችላሉ። w21.07 12 አን. 13-14

ረቡዕ፣ ሰኔ 7

[ይሖዋ] ይቅርታው ብዙ ነው።—ኢሳ. 55:7

አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ቀደም ሲል በፈጸሙት ኃጢአት የተነሳ በበደለኝነት ስሜት ተውጠዋል። ልባቸው በእጅጉ ስለሚኮንናቸው ንስሐ ቢገቡም እንኳ ይሖዋ ጨርሶ ይቅር ሊላቸው እንደማይችል ይሰማቸዋል። አንተም እንዲህ ያለ ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር ለማሳየት ዝግጁ እንደሆነ ማወቅህ ንጹሕ ሕሊና ይዘህ እሱን በደስታ ማገልገል እንድትችል ይረዳሃል። ይህ ሊሆን የቻለው “የልጁ የኢየሱስ ደም ከኃጢአት ሁሉ” ስለሚያነጻን ነው። (1 ዮሐ. 1:7) ባለብህ አለፍጽምና ምክንያት ተስፋ ከቆረጥክ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ እንደሆነ አልፎ ተርፎም ይህን ለማድረግ እንደሚጓጓ አስታውስ። መዝሙራዊው ዳዊት በታማኝ ፍቅርና በይቅር ባይነት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ብሎ እንደገለጸው ልብ በል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እሱ ለሚፈሩት የሚያሳየው ታማኝ ፍቅር ታላቅ ነውና። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ።”—መዝ. 103:11, 12፤ w21.11 5-6 አን. 12-13

ሐሙስ፣ ሰኔ 8

ልጆቿ ተነስተው ደስተኛ ይሏታል፤ ባሏ ተነስቶ ያወድሳታል።—ምሳሌ 31:28

አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን በአክብሮት ሊይዛት ይገባል። (1 ጴጥ. 3:7) እንዲህ ማድረግ የሚችልበት አንዱ መንገድ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጣት በማሳየት ነው። ማድረግ ከምትችለው በላይ አይጠብቅባትም። እንዲሁም ከሌሎች ሴቶች ጋር ጨርሶ አያወዳድራትም። አንድ ባል ሚስቱን ከሌሎች ሴቶች ጋር ቢያወዳድራት ምን ሊሰማት ይችላል? ሮዛ የተባለችን እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባሏ ከሌሎች ሴቶች ጋር ብዙ ጊዜ ያወዳድራታል። ባለቤቷ የሚናገረው ቅስም የሚሰብር ንግግር ሮዛ ለራሷ ዝቅተኛ አመለካከት እንዲያድርባትና ማንም እንደማይወዳት እንድታስብ አድርጓት ነበር። “ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተኝ መሆኑን ስለምጠራጠር ሁልጊዜ ‘ይሖዋ ይወድሻል’ ብሎ የሚያስታውሰኝ ያስፈልገኛል” በማለት ተናግራለች። አንድ ክርስቲያን ባል ግን ሚስቱን ያከብራታል። ይህን ማድረጉ ከእሷ ጋርም ሆነ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንደሚነካው ያውቃል። ሚስቱን የሚያከብር ባል እንደሚወዳት ይገልጽላታል፣ ያሞግሳታል እንዲሁም በሰዎች ፊት ያመሰግናታል። w21.07 22 አን. 7-8

ዓርብ፣ ሰኔ 9

በትዕግሥት እጠብቃለሁ።—ሚክ. 7:7

በጣም የሚያስፈልግህ ዕቃ ተልኮልህ ዕቃው ባሰብከው ጊዜ ባይደርስ ታዝናለህ? ሆኖም ይህ የሆነበት አጥጋቢ ምክንያት እንዳለ ብታውቅ በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ አትሆንም? የትዕግሥትን አስፈላጊነት የሚያጎላ አንድ ምሳሌ በምሳሌ 13:11 ላይ እናገኛለን። እንዲህ ይላል፦ “በፍጥነት የተገኘ ሀብት ይመናመናል፤ ጥቂት በጥቂት የሚያጠራቅም ሰው ግን ሀብቱ ይጨምራል።” ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን? ቀስ በቀስ ነገሮችን በትዕግሥት ማከናወን የጥበብ እርምጃ ነው። ምሳሌ 4:18 እንዲህ ይላል፦ “የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።” ይህ ሐሳብ ይሖዋ ዓላማውን ለሕዝቡ የሚገልጸው ቀስ በቀስ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ይሁንና ጥቅሱን አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ውስጥ መንፈሳዊ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ ለመግለጽም ልንጠቀምበት እንችላለን። መንፈሳዊ እድገት ጊዜ የሚወስድ ነገር ስለሆነ ልናጣድፈው አንችልም። w21.08 8 አን. 1, 3-4

ቅዳሜ፣ ሰኔ 10

እነሆኝ! እኔን ላከኝ!—ኢሳ. 6:8

ይህ ሥርዓት ወደ መጨረሻው በተቃረበ መጠን የምናከናውነው ብዙ ሥራ አለን። (ማቴ. 24:14፤ ሉቃስ 10:2፤ 1 ጴጥ. 5:2) ሁላችንም አቅማችን በፈቀደ መጠን በይሖዋ አገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ እንፈልጋለን። ብዙዎች አገልግሎታቸውን እያሰፉ ነው። አንዳንዶች በአቅኚነት ማገልገል ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ በቤቴል ማገልገል ወይም በቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች ግንባታ መካፈል ይፈልጋሉ። በተጨማሪም በርካታ ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት እየተጣጣሩ ነው። (1 ጢሞ. 3:1, 8) ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚያሳዩትን የፈቃደኝነት መንፈስ ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን! (መዝ. 110:3) አንድ መንፈሳዊ ግብ ላይ እስካሁን መድረስ አለመቻልህ ተስፋ አስቆርጦሃል? ከሆነ ስሜትህን ለይሖዋ ንገረው። (መዝ. 37:5-7) በተጨማሪም ለአምላክ በምታቀርበው አገልግሎት ማሻሻያ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ እንዲጠቁሙህ የጎለመሱ ወንድሞችን ጠይቅ፤ ከዚያም ምክራቸውን በተግባር ለማዋል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። እንዲህ ካደረግህ የፈለግኸውን መብት ልታገኝ ወይም ግብህ ላይ ልትደርስ ትችል ይሆናል። w21.08 20 አን. 1፤ 21 አን. 4

እሁድ፣ ሰኔ 11

ይሖዋ . . . ታማኝ [አገልጋዮቹን] አይተዋቸውም።—መዝ. 37:28

መበለት የነበረችው ነቢይቷ ሐና 84 ዓመቷ ቢሆንም “ከቤተ መቅደስ ፈጽሞ አትጠፋም ነበር።” አዘውትራ በቤተ መቅደስ በመገኘቷ ሕፃኑን ኢየሱስን የማየት ልዩ በረከት አግኝታለች። (ሉቃስ 2:36) በዘመናችንም ለወጣቶች ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ታማኝ አረጋውያን አሉ። ጊዜ ወስደን ጥያቄዎችን ከጠየቅናቸው እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ሲካፈሉ ያገኟቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች ሲነግሩን ካዳመጥናቸው ትልቅ ጥቅም እናገኛለን። አረጋውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ጠቃሚ ሚና ይጫወታሉ። ይሖዋ ድርጅቱንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እነሱን በተለያየ መንገድ የባረካቸው እንዴት እንደሆነ ተመልክተዋል። ከሠሯቸው ስህተቶች ጠቃሚ ትምህርቶችን አግኝተዋል። እነዚህን ክርስቲያኖች “የጥበብ ምንጭ” እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው፤ እንዲሁም ከእነሱ ተሞክሮ ተማሩ። (ምሳሌ 18:4) ጊዜ ወስዳችሁ እነሱን በደንብ ለማወቅ ጥረት ካደረጋችሁ እምነታችሁ ይጠናከራል። w21.09 3 አን. 4፤ 4 አን. 7-8፤ 5 አን. 11, 13

ሰኞ፣ ሰኔ 12

ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል።—ኢሳ. 60:22

ኢሳይያስ እንደገለጸው የይሖዋ ሕዝቦች “የብሔራትን ወተት” እየጠጡ ነው። (ኢሳ. 60:5, 16) የተለያየ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ውድ ወንዶችና ሴቶች ወደ እውነት በመምጣታቸው ምሥራቹ በ240 አገራት ሊሰበክ ችሏል፤ ጽሑፎቻችንም ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች እየተዘጋጁ ነው። በምንኖርበት በመጨረሻው ዘመን፣ የብሔራት መናወጥ ሰዎች ውሳኔ እንዲያደርጉ እያስገደዳቸው ነው። በሁሉም ሰው ፊት የተደቀነ ውሳኔ አለ፦ የአምላክን መንግሥት መደገፍ አሊያም በዚህ ዓለም መንግሥታት መተማመን። የይሖዋ ሕዝቦች የሚኖሩበትን አገር ሕግጋት የሚያከብሩ ቢሆንም ከዚህ ዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ ናቸው። (ሮም 13:1-7) ለሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያውቃሉ። ይህ መንግሥት የዓለም ክፍል አይደለም።—ዮሐ. 18:36, 37፤ w21.09 17-18 አን. 13-14

ማክሰኞ፣ ሰኔ 13

ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።—መዝ. 62:8

የምትወዱት ሰው ይሖዋን ሲተው የራሳችሁንም ሆነ የሌሎቹን የቤተሰባችሁን አባላት መንፈሳዊነት ማጠናከራችሁን መቀጠላችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? አዘውትራችሁ የአምላክን ቃል በማንበብና ባነበባችሁት ላይ በማሰላሰል እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ከይሖዋ ብርታት አግኙ። የጆአናን ምሳሌ እንመልከት፤ ጆአና አባቷና እህቷ እውነትን ትተዋል፤ እንዲህ ብላለች፦ “እንደ አቢጋኤል፣ አስቴር፣ ኢዮብ፣ ዮሴፍና ኢየሱስ ስላሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ሳነብ ውስጤ ይረጋጋል። የእነሱ ምሳሌ ያበረታታኛል፤ እንዲሁም አዎንታዊ አመለካከት እንድይዝ ይረዳኛል።” በጭንቀት በምትዋጡበት ጊዜም ወደ ይሖዋ ከመጸለይ ወደኋላ አትበሉ። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ሁኔታውን ከእሱ አመለካከት አንጻር ለማየት እንዲረዳችሁ እንዲሁም ‘ጥልቅ ማስተዋል እንዲሰጣችሁና ልትሄዱበት የሚገባውን መንገድ እንዲያስተምራችሁ’ ለምኑት። (መዝ. 32:6-8) እርግጥ ነው፣ የሚሰማችሁን ሁሉ ግልጥልጥ አድርጋችሁ ለይሖዋ መናገሩ በጣም ይረብሻችሁ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ የሚሰማችሁን ሥቃይ ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳ አስታውሱ። ይሖዋ ልባችሁን በፊቱ እንድታፈሱ ጋብዟችኋል።—ዘፀ. 34:6፤ መዝ. 62:7፤ w21.09 27-28 አን. 9-10

ረቡዕ፣ ሰኔ 14

በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት።—ማቴ. 17:5

በ32 ዓ.ም. ከተከበረው የፋሲካ በዓል በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሐዋርያው ያዕቆብና ሐዋርያው ዮሐንስ አስገራሚ ራእይ ተመለከቱ። በአንድ ረጅም ተራራ ላይ ምናልባትም በሄርሞን ተራራ ላይ ሳሉ ኢየሱስ በፊታቸው ተለወጠ። “ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።” (ማቴ. 17:1-4) አምላክ “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር ሐዋርያቱ ሰሙ። ሦስቱ ሐዋርያት ኢየሱስን እንደሰሙት በሕይወታቸው አሳይተዋል። እኛም የእነሱን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። ይሖዋ ‘የጉባኤው ራስ’ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ፍቅር የሚንጸባረቅበት መመሪያ ስለሚሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ኤፌ. 5:23) እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሐዋርያው ያዕቆብ እና ሐዋርያው ዮሐንስ እኛም ‘ኢየሱስን ለመስማት’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፉ በረከቶችን እናገኛለን፤ ወደፊት ደግሞ ለዘላለም በደስታ እንኖራለን። w21.12 22 አን. 1፤ 27 አን. 19

ሐሙስ፣ ሰኔ 15

በተገቢው መጠን እገሥጽሃለሁ።—ኤር. 30:11

በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ከአባቱ ሚስት ጋር ብልግና የሚፈጽም አንድ ክርስቲያን ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ይህን ሰው ከጉባኤ እንዲያስወግዱት አዟቸዋል። የዚህ ሰው ብልግና በሌሎቹ የጉባኤው አባላት ላይም ተጽዕኖ እያሳደረ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ይህ አስጸያፊ ድርጊት የሚያሳፍር ነገር እንደሆነ አልተሰማቸውም። (1 ቆሮ. 5:1, 2, 13) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ይህ ሰው ከልቡ ንስሐ እንደገባ ተገነዘበ። በመሆኑም ለሽማግሌዎቹ “በደግነት ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። ጳውሎስ፣ ሽማግሌዎቹ ይህን ማድረግ ያለባቸው “ይህ ሰው ከልክ በላይ በሐዘን እንዳይዋጥ” እንደሆነ ገልጿል። ጳውሎስ ንስሐ ለገባው ሰው አዝኖለታል። ግለሰቡ በፈጸመው ኃጢአት ምክንያት በጣም ከመጸጸቱና ከልክ በላይ ከመደቆሱ የተነሳ ምሕረት ለማግኘት መሞከሩን ከናካቴው እንዳይተወው ጳውሎስ ሰግቶ ነበር። (2 ቆሮ. 2:5-8, 11) እንደ ይሖዋ ሁሉ ሽማግሌዎችም ምሕረት ማሳየት ይወዳሉ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ ይሆናሉ፤ ሆኖም ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ምሕረት ያሳያሉ። ሽማግሌዎች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ተግሣጽ የማይሰጡ ከሆነ ግን መሐሪ ሳይሆን ልል ይሆናሉ። w21.10 11 አን. 12-15

ዓርብ፣ ሰኔ 16

አትበቀል፤ . . . ቂም አትያዝ።—ዘሌ. 19:18

የስሜት መጎዳት ከቁስል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንዳንዱ ቁስል ቀላል ነው፤ አንዳንዱ ግን ከባድ ነው። ለምሳሌ ሽንኩርት ስንከትፍ ቢላው ጣታችንን ይቆርጠን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ቢያመንም ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ የት ጋ እንደተቆረጥን እንኳ አናስታውሰው ይሆናል። በተመሳሳይም አንዳንድ ጊዜ የሚደርስብን በደል ቀላል ነው። ለምሳሌ ጓደኛችን የሚጎዳን ነገር ይናገር ወይም ያደርግ ይሆናል፤ ሆኖም በደሉን ይቅር ማለት አይከብደንም። ቢላው በደንብ ጎድቶን ከሆነ ግን ቁስሉ መሰፋት እና በፋሻ መታሸግ ሊያስፈልገው ይችላል። በዚህ ጊዜ ቁስሉን የምንነካካው ከሆነ ቁስሉ ይበልጥ እንዲያመረቅዝ እናደርገዋለን። አንድ ሰው ስሜቱ በጥልቅ ሲጎዳ እንዲህ ያለ ነገር ያደርግ ይሆናል፤ ይህ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ስለደረሰበት በደል ነጋ ጠባ እያሰበ ይብሰለሰል ይሆናል። ይሁንና ቂም የሚይዙ ሰዎች የሚጎዱት ራሳቸውን ነው። ቂም ከመያዝ ይልቅ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ምንኛ የተሻለ ነው! w21.12 12 አን. 15

ቅዳሜ፣ ሰኔ 17

በወንድምህ ላይ ለምን ትፈርዳለህ?—ሮም 14:10

አንድ ሽማግሌ የአንድ የእምነት ባልንጀራው አለባበስ ወይም የፀጉር አያያዝ አሳስቦታል እንበል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌው ‘ጉዳዩን ለማንሳት የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አለኝ?’ ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል። የግሉን አመለካከት በሌሎች ላይ መጫን ስለማይፈልግ ስለ ጉዳዩ ሌላን ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ አስፋፊ ያማክራል። ከዚያም አለባበስንና የፀጉር አያያዝን በተመለከተ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር አብረው ይከልሳሉ። (1 ጢሞ. 2:9, 10) ጳውሎስ ክርስቲያኖች በልከኝነት፣ በማስተዋልና ተገቢ በሆነ መንገድ ሊለብሱ እንደሚገባ በመግለጽ ጠቅለል ያለ መሠረታዊ ሥርዓት አስፍሯል። ይሁንና ጳውሎስ ይህን ልበሱ ወይም አትልበሱ የሚል ዝርዝር መመሪያ አላሰፈረም። ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች እስካልተጣሱ ድረስ ክርስቲያኖች የግላቸውን ምርጫ የማድረግ መብት እንዳላቸው ተገንዝቧል። በመሆኑም ሽማግሌዎች የግለሰቡ ምርጫ ልከኝነትና ማስተዋል የሚንጸባረቅበት መሆን አለመሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል። ሁለት የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሁለት የተለያዩ ምርጫዎች ቢያደርጉም ሁለቱም ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። አንድ ነገር ትክክል ነው ወይም ስህተት ነው ብለን የራሳችንን መሥፈርት በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ መጫን የለብንም። w22.02 16 አን. 9-10

እሁድ፣ ሰኔ 18

አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና ምሕረት አሳዩ።—ዘካ. 7:9

አንዳችን ለሌላው ታማኝ ፍቅር እንድናሳይ የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉ። አንዳንዶቹ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት የሚከተሉት ጥቅሶች ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጡናል። “ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት አይለዩህ። . . . ያን ጊዜ በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ ታገኛለህ፤ እንዲሁም ጥሩ ማስተዋል እንዳለህ ታስመሠክራለህ።” “ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ ሰው ራሱን ይጠቅማል።” “ጽድቅንና ታማኝ ፍቅርን የሚከታተል ሰው ሁሉ ሕይወትን . . . ያገኛል።” (ምሳሌ 3:3, 4፤ 11:17 ግርጌ፤ 21:21) እነዚህ ጥቅሶች ታማኝ ፍቅር ማሳየት አስፈላጊ የሆነባቸውን ሦስት ምክንያቶች ይጠቅሳሉ። አንደኛ፣ ታማኝ ፍቅር ማሳየት በአምላክ ዓይን ውድ እንድንሆን ያደርገናል። ሁለተኛ፣ ታማኝ ፍቅር ማሳየታችን ራሳችንን ይጠቅመናል። ለምሳሌ ከሌሎች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። ሦስተኛ፣ ታማኝ ፍቅርን መከታተል የዘላለም ሕይወትን ጨምሮ ለወደፊቱ ጊዜ በረከቶች ያስገኛል። በእርግጥም ይሖዋ “አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና ምሕረት አሳዩ” በማለት የሰጠንን ማሳሰቢያ የምንከተልበት ብዙ ምክንያት አለን። w21.11 8 አን. 1-2

ሰኞ፣ ሰኔ 19

እምነት ጨምርልን።—ሉቃስ 17:5

ከዚህ በፊት ያጋጠሟችሁም ሆነ በአሁኑ ጊዜ እያጋጠሟችሁ ያሉት ፈተናዎች እምነታችሁ በሆነ አቅጣጫ እንደደከመ ካሳዩአችሁ ተስፋ አትቁረጡ። ሁኔታውን እምነታችሁን ለማጠናከር እንደሚያስችል አጋጣሚ አድርጋችሁ ተመልከቱት። በተለይም ከባድ ችግር ሲያጋጥማችሁ ወደ ይሖዋ አጥብቃችሁ ጸልዩ። ይሖዋ በቤተሰቦቻችሁ ወይም በጓደኞቻችሁ አማካኝነት የሚያስፈልጋችሁን እርዳታ ሊሰጣችሁ እንደሚችል አስተውሉ። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟችሁን ፈተናዎች በጽናት ለማለፍ እንዲረዳችሁ ከፈቀዳችሁ ወደፊትም ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማችሁ ለመጽናት እንደሚረዳችሁ ይበልጥ እርግጠኛ ትሆናላችሁ። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እምነት እንደጎደላቸው ጠቁሟቸዋል። ሆኖም ወደፊት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በይሖዋ እርዳታ በጽናት ማለፍ እንደሚችሉ አልተጠራጠረም። (ዮሐ. 14:1፤ 16:33) ከፊታችን ከሚመጣው ታላቅ መከራ ጠንካራ እምነት ይዘው የሚያልፉ እጅግ ብዙ ሕዝብ እንደሚኖሩም እርግጠኛ ነበር። (ራእይ 7:9, 14) በአሁኑ ወቅት ያገኛችሁትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅማችሁ እምነታችሁን የምታጠናክሩ ከሆነ ከእነሱ መካከል መገኘት ትችላላችሁ።—ዕብ. 10:39፤ w21.11 25 አን. 18-19

ማክሰኞ፣ ሰኔ 20

የይሖዋ መልአክ አምላክን በሚፈሩ ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል።—መዝ. 34:7

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በተአምራዊ ሁኔታ ጥበቃ ያደርግልናል ብለን አንጠብቅም። አንድ ነገር ግን እናውቃለን፦ በይሖዋ የሚታመን ሰው መቼም ቢሆን ዘላቂ ጉዳት አይደርስበትም። ይሖዋ እኛን የመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ያለን እምነት በቅርቡ ይፈተናል። የማጎጉ ጎግ ማለትም ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ሕይወታችን አደጋ ላይ የወደቀ ሊመስል ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ይሖዋ እኛን ለማዳን ችሎታው እንዳለውና ይህንንም እንደሚያደርግ ልንተማመን ይገባል። ብሔራት፣ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ሆነን እንታያቸው ይሆናል። (ሕዝ. 38:10-12) የጦር ትጥቅም ሆነ የውጊያ ተሞክሮ አይኖረንም። ብሔራት በቀላሉ ሊደመስሱን እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እኛ በእምነት ዓይናችን የሚታየን ነገር ለእነሱ አይታያቸውም፤ ለአምላክ ሕዝብ ጥበቃ ለማድረግ ተዘጋጅቶ በሕዝቡ ዙሪያ የሰፈረውን የመላእክት ጭፍራ ማየት አይችሉም። ደግሞስ እንዴት ሊታያቸው ይችላል? እነሱ መንፈሳዊ እይታ የላቸውም። የሰማይ ሠራዊት እኛን ለማዳን እርምጃ ሲወስዱ ብሔራት ምን ያህል እንደሚደናገጡ አስቡት።—ራእይ 19:11, 14, 15፤ w22.01 6 አን. 12-13

ረቡዕ፣ ሰኔ 21

ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ።—1 ጴጥ. 2:17

ይሖዋ ሁሉንም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል፤ እኛም ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። አቅማችን በፈቀደ መጠን ልንጠነቀቅላቸው እና አሳቢነት ልናሳያቸው ይገባል። አንድን ሰው ቅር እንዳሰኘነው ወይም ስሜቱን እንደጎዳነው ካወቅን ግለሰቡ ‘አትንኩኝ ባይ’ እንደሆነ በማሰብ ጉዳዩን በቸልታ ልናልፈው አይገባም። ይሁንና አንዳንዶች ቶሎ ቅር የሚሰኙት ለምን ሊሆን ይችላል? አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች በአስተዳደጋቸው የተነሳ ራሳቸውን በጣም ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ። አንዳንዶች ደግሞ ወደ እውነት የመጡት በቅርቡ ስለሆነ ሌሎች ሲያስቀይሟቸው ጉዳዩን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው አያውቁም። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ሰላም ለመፍጠር የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን። በሌላ በኩል ደግሞ በሌሎች ቶሎ ቅር የሚሰኝ ሰው፣ ይህ ሊያርመው የሚገባ መጥፎ ባሕርይ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል። ይህን ባሕርይ ማረሙ፣ የአእምሮ ሰላም የሚያስገኝለት ከመሆኑም ሌላ ከወንድሞቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ያደርጋል። w21.06 21 አን. 7

ሐሙስ፣ ሰኔ 22

ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።—መዝ. 145:18

ኢየሱስ ስሜትህን ይረዳልሃል። በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ ስሜታችንን የሚረዳልን ወዳጅ ሲኖረን በጣም ደስ ይለናል፤ በተለይ ደግሞ ይህ ወዳጃችን እኛ ያጋጠመን ዓይነት ችግር ያሳለፈ ከሆነ ይበልጥ ያጽናናናል። ኢየሱስ እንዲህ ያለ ወዳጅ ነው። በራሳችን አቅም ልንወጣው የማንችለው ችግር ሲያጋጥመን የሚሰማንን ስሜት እሱም አልፎበታል። ኢየሱስ ድካማችንን ይረዳል፤ እንዲሁም “እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ” ድጋፍ እንድናገኝ ያደርጋል። (ዕብ. 4:15, 16) ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ አንድ መልአክ ያደረገለትን ድጋፍ እንደተቀበለ ሁሉ እኛም ይሖዋ እኛን ለመርዳት ያደረገውን ዝግጅት ለመቀበል ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ የሚያደርግልን በጽሑፎቻችን፣ በቪዲዮዎች፣ በንግግሮች ወይም አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አሊያም የጎለመሰ ወዳጃችን በሚያካፍለን የሚያበረታታ ሐሳብ አማካኝነት ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 22:39-44) ይሖዋ ‘ከእሱ የሚገኘውን ሰላም’ ይሰጠናል እንዲሁም ያበረታናል። ስንጸልይ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” እናገኛለን።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ w22.01 18-19 አን. 17-19

ዓርብ፣ ሰኔ 23

ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች . . . ያሳውቋቸው ነበር።—ሥራ 16:4

ይሖዋ ምንጊዜም የሚያደርገው ትክክለኛውን ነገር ነው። ፈተና የሚሆንብን ግን ሰብዓዊ ወኪሎቹ ላይ እምነት መጣል ሊሆን ይችላል። ‘በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ውሳኔ የሚያደርጉት የይሖዋን መመሪያ ተከትለው ነው ወይስ በራሳቸው?’ ብለን የምናስብበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ልናስታውሰው የሚገባ አንድ ሐቅ ግን አለ፦ ይሖዋ በሚያምናቸውና በሾማቸው ምድራዊ ወኪሎቹ የማንተማመን ከሆነ በእሱ እንተማመናለን ማለት አንችልም። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የድርጅቱን ምድራዊ ክፍል የሚመራው ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው የበላይ አካል ሁሉ ይህ ባሪያም በመላው ዓለም የሚገኙ የአምላክ ሕዝቦችን ይመራል እንዲሁም ለጉባኤ ሽማግሌዎች መመሪያ ያስተላልፋል። ሽማግሌዎች ደግሞ የተሰጣቸው መመሪያ በጉባኤዎች ውስጥ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ያደርጋሉ። ከድርጅቱ እና ከሽማግሌዎች የምናገኘውን መመሪያ በመታዘዝ በይሖዋ አሠራር እንደምንተማመን እናሳያለን። w22.02 4 አን. 7-8

ቅዳሜ፣ ሰኔ 24

ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።—ገላ. 6:9

የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ደስታና ክብር ይሰማናል! “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ” አማኞች እንዲሆኑ መርዳት መቻላችን ትልቅ ደስታ ያስገኝልናል። (ሥራ 13:48) ደቀ መዛሙርቱ ስኬታማ የስብከት ዘመቻ አድርገው ሲመለሱ ‘በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት ያደረገውን’ የኢየሱስን ስሜት እንጋራለን። (ሉቃስ 10:1, 17, 21) ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ” በማለት አሳስቦታል። አክሎም “ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህ” ብሎታል። (1 ጢሞ. 4:16) በመሆኑም የስብከቱ ሥራችን ሕይወት አድን ሥራ ነው። የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ስለሆንን ለራሳችን ምንጊዜም ትኩረት መስጠት አለብን። ሁሌም ቢሆን አኗኗራችን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣና ከምንሰብከው ምሥራች ጋር የሚስማማ ሊሆን ይገባል። (ፊልጵ. 1:27) በተጨማሪም ለሌሎች ከመስበካችን በፊት በሚገባ በመዘጋጀት እንዲሁም የይሖዋን በረከት ለማግኘት በመጸለይ ‘ለምናስተምረው ትምህርት ትኩረት እንደምንሰጥ’ እናሳያለን። w21.10 24 አን. 1-2

እሁድ፣ ሰኔ 25

አዲሱን ስብዕና ልበሱ።—ቆላ. 3:10

“አዲሱን ስብዕና” መልበስ ሲባል የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብና ምግባር ማንጸባረቅ ማለት ነው። አዲሱን ስብዕና የለበሰ ሰው የአምላክ መንፈስ ውጤት የሆኑ ባሕርያትን ያንጸባርቃል፤ መንፈስ ቅዱስ በአስተሳሰቡ፣ በስሜቱና በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ ይፈቅዳል። ለምሳሌ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ይሖዋን እና ሕዝቦቹን ይወዳል። (ማቴ. 22:36-39) አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ጊዜም እንኳ ደስታውን ይጠብቃል። (ያዕ. 1:2-4) ሰላም ፈጣሪ ነው። (ማቴ. 5:9) ሌሎችን በትዕግሥትና በደግነት ይይዛል። (ቆላ. 3:13) ጥሩ የሆነውን ነገር ይወዳል፤ ያደርገዋልም። (ሉቃስ 6:35) በሰማዩ አባቱ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው በሥራው ያሳያል። (ያዕ. 2:18) ሌሎች ሲያበሳጩት በገርነት መልስ ይሰጣል፤ ፈታኝ ነገር ሲያጋጥመውም ራሱን ይገዛል። (1 ቆሮ. 9:25, 27፤ ቲቶ 3:2) አዲሱን ስብዕና ለመልበስ በገላትያ 5:22, 23 እንዲሁም በሌሎች ጥቅሶች ላይ ያሉትን ባሕርያት በሙሉ ማዳበር አለብን። w22.03 8-9 አን. 3-4

ሰኞ፣ ሰኔ 26

የእኔን አርዓያ ተከተሉ።—1 ቆሮ. 11:1

ሽማግሌዎች ከቤት ወደ ቤት ከመስበክ በተጨማሪ በማንኛውም ሁኔታ ምሥክርነት ለመስጠት ዝግጁ በመሆን የሐዋርያው ጳውሎስን አርዓያ መከተል ይችላሉ። (ኤፌ. 6:14, 15) ልክ እንደ ጳውሎስ ሁሉ ሽማግሌዎችም በአገልግሎት የሚያሳልፉትን ጊዜ የጉባኤ አገልጋዮችን ጨምሮ ሌሎችን ለማሠልጠን ይጠቀሙበታል። (1 ጴጥ. 5:1, 2) ይሁንና ሽማግሌዎች በተለያዩ ኃላፊነቶች በጣም ከመጠመዳቸው የተነሳ ለስብከቱ ሥራ ጊዜ እንዳያጡ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ ረገድ ሚዛናቸውን ለመጠበቅ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ‘አልችልም’ ብለው መመለስ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ጉዳዩን በጸሎት ካሰቡበት በኋላ አንዳንድ ኃላፊነቶች በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ እንደማድረግ፣ በስብከቱ ሥራ አዘውትሮ እንደመካፈል ወይም ልጆቻቸውን ለስብከቱ ሥራ እንደማሠልጠን ላሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ጊዜ ሊያሳጧቸው እንደሚችሉ ይገነዘቡ ይሆናል። ይሖዋ በሁሉም ነገር ሚዛናዊ ለመሆን የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚረዳላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። w22.03 27 አን. 4, 7፤ 28 አን. 8

ማክሰኞ፣ ሰኔ 27

ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ።—ማቴ. 10:28

መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና በነበረበት ወቅት የይሖዋ ምሥክር መሆን አስፈርቶህ ነበር? ምናልባት ፈጽሞ ከቤት ወደ ቤት መስበክ እንደማትችል ተሰምቶህ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ቤተሰቦችህና ጓደኞችህ እንዳይቃወሙህ ፈርተህ ይሆናል። እንደዚህ ተሰምቶህ ከነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ እንዲህ ቢሰማው ስሜቱን መረዳት አይከብድህም። ኢየሱስ ሰዎች እንዲህ ያለ ፍርሃት ሊያድርባቸው እንደሚችል ገልጿል። ሆኖም ተከታዮቹ በፍርሃት ተሸንፈው ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንዳይሉ አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 10:16, 17, 27) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ስለ እምነቱ ለሌሎች እንዲናገር ደረጃ በደረጃ አሠልጥነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት በላካቸው ወቅት ፍርሃት አድሮባቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ የት እንደሚሰብኩና የሚሰብኩት መልእክት ምን እንደሆነ በመንገር ረድቷቸዋል። (ማቴ. 10:5-7) አንተስ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ጥናትህ የት መስበክ እንደሚችል እንዲያስተውል እርዳው። ለምሳሌ ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስታጠኑ ‘ይህን መረጃ ብትነግረው ሊጠቀም የሚችል ሰው ታውቃለህ?’ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ። ከዚያም ይህን እውነት በቀላሉ ማስረዳት የሚችለው እንዴት እንደሆነ በማሳየት እንዲዘጋጅ እርዳው። w21.06 6 አን. 15-16

ረቡዕ፣ ሰኔ 28

ብሔራትንም ሁሉ አናውጣለሁ፤ በብሔራትም ሁሉ መካከል ያሉ የከበሩ ነገሮች ይመጣሉ።—ሐጌ 2:7

“ሱቆችና ረጅም ዘመን የኖሩ ሕንፃዎች በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የፍርስራሽ ክምር ሆኑ።” “ሁሉም ሰው ተሸብሮ ነበር፤ . . . ብዙ ሰዎች መናወጡ የቆየው ለሁለት ደቂቃ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። እኔ ግን ለረጅም ጊዜ የቆየ ነበር የመሰለኝ።” እነዚህን ሐሳቦች የተናገሩት በ2015 በኔፓል ከተከሰተው የምድር መናወጥ የተረፉ ሰዎች ናቸው። በዛሬው ጊዜ ከዚህ በጣም የተለየ መናወጥ ሲከሰት እየተመለከትን ነው፤ ይህ ነውጥ ብሔራትን ሁሉ የሚነካ ነው። ነቢዩ ሐጌ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደገና ሰማያትን፣ ምድርን . . . አናውጣለሁ።’” (ሐጌ 2:6) ሐጌ በትንቢቱ ላይ የገለጸው ነውጥ ከምድር መናወጥ የተለየ ነው፤ ምክንያቱም የምድር መናወጥ ውጤቱ ውድመት ብቻ ነው። ሐጌ የተናገረለት መናወጥ ግን መልካም ውጤት ያስገኛል። ይሖዋ ራሱ እንዲህ ብሏል፦ “ብሔራትንም ሁሉ አናውጣለሁ፤ በብሔራትም ሁሉ መካከል ያሉ የከበሩ ነገሮች ይመጣሉ፤ ደግሞም ይህን ቤት በክብር እሞላዋለሁ።” w21.09 14 አን. 1-3

ሐሙስ፣ ሰኔ 29

እናንተ በፈተናዎቼ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል።—ሉቃስ 22:28

ከአንድ ሰው ጋር ጠንካራ ወዳጅነት እንዲኖረን ከፈለግን አዘውትረን ልባዊ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ይኖርብናል። ከይሖዋ ጋር ካለን ወዳጅነት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለይሖዋ ስሜታችንን፣ ሐሳባችንንና ጭንቀታችንን አውጥተን በጸሎት ስንነግረው በእሱ እንደምንተማመን እንዲሁም እንደሚወደን እርግጠኞች እንደሆንን እናሳያለን። (መዝ. 94:17-19፤ 1 ዮሐ. 5:14, 15) ከታማኝ ወዳጆችህ ጋር ተቀራረብ፤ እነሱ ከይሖዋ ያገኘሃቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። (ያዕ. 1:17) የሰማዩ አባታችን “ምንጊዜም አፍቃሪ” የሆኑ ወንድሞችና እህቶች በመስጠት በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ያሳየናል። (ምሳሌ 17:17) ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ድጋፍ ስላደረጉለት ክርስቲያኖች ሲናገር “በእጅጉ አጽናንተውኛል” ብሏል። (ቆላ. 4:10, 11 ግርጌ) ክርስቶስ ኢየሱስም እንኳ የወዳጆቹ እርዳታ አስፈልጎታል፤ በመሆኑም መላእክትና ሰዎች ላደረጉለት እርዳታ አመስጋኝ ነበር። (ሉቃስ 22:43) ለአንድ የጎለመሰ ወዳጃችን ጭንቀታችንን አውጥተን ማካፈላችን የድክመት ምልክት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጥበቃ ይሆንልናል። w21.04 24-25 አን. 14-16

ዓርብ፣ ሰኔ 30

[ፍቅር] ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።—1 ቆሮ. 13:7

አንድ የእምነት ባልንጀራህ ያደረገው ነገር በጣም ቢያስከፋህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ሰላም ለመፍጠር የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ለይሖዋ የልብህን አውጥተህ ንገረው። ቅር ያሰኘህን ሰው በተመለከተ ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ እንዲሁም የግለሰቡን መልካም ባሕርያት ይኸውም በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅ ያደረጉትን ባሕርያት ለማየት እንዲረዳህ ጸልይ። (ሉቃስ 6:28) ወንድምህ ያደረሰብህን በደል ችለህ ማለፍ ከከበደህ እንዴት ብታነጋግረው የተሻለ እንደሚሆን ቆም ብለህ አስብ። ምንጊዜም ቢሆን፣ ወንድምህ የጎዳህ ሆን ብሎ እንዳልሆነ ማሰቡ የተሻለ ነው። (ማቴ. 5:23, 24) ወንድምህን የምታነጋግረው ስለ እሱ መጥፎ አመለካከት ይዘህ መሆን የለበትም። ይሁንና ወንድምህ ሰላም ለመፍጠር ፈቃደኛ ባይሆንስ? ወንድምህን ‘ለመቻል’ ጥረት ማድረግህን ቀጥል። በወንድምህ ተስፋ አትቁረጥበት። (ቆላ. 3:13) ከሁሉ በላይ ደግሞ ፈጽሞ ቂም አትያዝ፤ ምክንያቱም ቂም መያዝ ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ያበላሸዋል። ምንም ነገር እንዲያሰናክልህ አትፍቀድ። ይህን ስታደርግ ከማንኛውም ነገር በላይ ይሖዋን እንደምትወደው ታሳያለህ።—መዝ. 119:165፤ w21.06 23 አን. 15

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ