ሐምሌ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1
በኋላ . . . በተግሣጽ ሥልጠና ላገኙ ሰዎች የጽድቅን ሰላማዊ ፍሬ ያፈራላቸዋል።—ዕብ. 12:11
ውገዳ የይሖዋ ዝግጅት ነው። ይህ ዝግጅት ኃጢአት የሠራውን ግለሰብ ጨምሮ ሁሉንም ሰው ይጠቅማል። በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች፣ ውሳኔው ትክክል እንዳልሆነ ይናገሩ ይሆናል፤ ሆኖም እንዲህ ያሉት ሰዎች ኃጢአት የሠራው ግለሰብ የፈጸማቸውን ስህተቶች ለመሸፋፈን ይሞክራሉ። ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ እንደሌለን ማስታወስ ይኖርብናል። በመሆኑም ውሳኔውን ያደረጉት ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመከተልና “ለይሖዋ” ለመፍረድ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንዳደረጉ መተማመናችን ጥበብ ይሆናል። (2 ዜና 19:6) ሽማግሌዎች የቤተሰባችሁ አባል ከጉባኤው እንዲወገድ ያደረጉትን ውሳኔ መደገፋችሁ ግለሰቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ ሊረዳው ይችላል። ኤሊዛቤት እንዲህ ብላለች፦ “ለአካለ መጠን ከደረሰው ልጃችን ጋር የነበረንን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ በጣም ከብዶን ነበር። ሆኖም ልጃችን ወደ ይሖዋ ከተመለሰ በኋላ፣ ያኔ መወገዱ ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር ተናግሯል። ከጊዜ በኋላ እንደተናገረው በጣም ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶች አግኝቷል።” w21.09 28-29 አን. 11-12
እሁድ፣ ሐምሌ 2
አንዲት ድሃ መበለት በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ስትከት [አየ]።—ሉቃስ 21:2
እስቲ ስለ ድሃዋ መበለት ቆም ብላችሁ አስቡ። ይህች ሴት ለይሖዋ የበለጠ መስጠት ብትችል ደስ እንደሚላት ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን የቻለችውን ሁሉ አድርጋለች፤ ለይሖዋ ምርጧን ሰጥታዋለች። ኢየሱስም ይህች ሴት ያደረገችውን መዋጮ አባቱ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ያውቅ ነበር። ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ጠቃሚ ትምህርት ይህ ነው፦ ይሖዋ ምርጣችንን ስንሰጠው ማለትም በሙሉ ልባችንና በሙሉ ነፍሳችን ስናገለግለው በጣም ይደሰታል። (ማቴ. 22:37፤ ቆላ. 3:23) ይሖዋ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንደምናደርግ ሲያይ ልቡ ይደሰታል! ይህ መሠረታዊ ሥርዓት አገልግሎትንና ስብሰባዎችን ጨምሮ ለአምልኳችን ከምናውለው ጊዜና ጉልበት ጋር በተያያዘም ይሠራል። ስለ መበለቷ ከሚናገረው ዘገባ ያገኛችሁትን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ ጥረታቸውን እንደሚያደንቅ እንዲያስታውሱ በመርዳት ልታበረታቷቸው የምትችሉ ወንድሞችና እህቶችን ለማሰብ ሞክሩ። ባጋጠማት የጤና እክል ወይም አቅሟ በመድከሙ የተነሳ በአገልግሎት የቀድሞውን ያህል ማድረግ ባለመቻሏ የጥፋተኝነት ወይም የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማት አረጋዊት እህት ትኖር ይሆናል። w21.04 6-7 አን. 17, 19-20
ሰኞ፣ ሐምሌ 3
ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሰው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት ጊዜ . . . የሕይወት አክሊል ይቀበላል።—ያዕ. 1:12
ይሖዋ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ መቼ እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ ትዕግሥት ማሳየቱ እሱን የሚያመልክና የሚያወድስ በሚሊዮኖች የሚቆጠር እጅግ ብዙ ሕዝብ እንዲሰበሰብ አድርጓል። ይሖዋ ለረጅም ጊዜ መጽናቱ እነዚህ ሰዎች እንዲወለዱ፣ ስለ እሱ እንዲማሩና እንዲወዱት እንዲሁም ራሳቸውን ለእሱ እንዲወስኑ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ናቸው። ይሖዋ እስከ መጨረሻው የጸኑትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚባርክበት ጊዜ፣ ለመጽናት ያደረገው ውሳኔ ትክክል እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል! ሰይጣን ብዙ መከራና ሐዘን ቢያደርስም ይሖዋ አሁንም ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው። (1 ጢሞ. 1:11) እኛም ይሖዋ ስሙን የሚያስቀድስበት፣ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበት፣ ክፋትን ሙሉ በሙሉ የሚያስወግድበት እንዲሁም አሁን ላሉብን ችግሮች መፍትሔ የሚያመጣበት ጊዜ እስኪደርስ በምንጠባበቅበት ወቅት ደስተኛ መሆን እንችላለን። እንግዲያው እስከ መጨረሻው ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲሁም የሰማዩ አባታችንም እየጸና መሆኑን በማወቃችን እንጽናና። w21.07 13 አን. 18-19
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4
ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?—ዮሐ. 1:46
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ በርካታ ሰዎች በኢየሱስ አላመኑም። በእነሱ ዓይን ኢየሱስ የአንድ ድሃ አናጺ ልጅ ብቻ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ነው፤ ናዝሬት ያን ያህል ትኩረት የሚሰጣት ከተማ አልነበረችም። ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው ናትናኤል እንኳ “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” ብሏል። ናትናኤል፣ በሚክያስ 5:2 ላይ የሚገኘውን ትንቢት አስታውሶ ሊሆን ይችላል፤ ትንቢቱ እንደሚገልጸው መሲሑ የሚወለደው በናዝሬት ሳይሆን በቤተልሔም ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ፣ የኢየሱስ ጠላቶች ‘ትኩረት ሰጥተው የመሲሑን ትውልድ በዝርዝር ለማወቅ እንደማይሞክሩ’ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳ. 53:8) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ጊዜ ወስደው መረጃዎቹን በሙሉ ቢመረምሩ ኖሮ ኢየሱስ የተወለደው በቤተልሔም እንደሆነና የንጉሥ ዳዊት ዘር መሆኑን ይገነዘቡ ነበር። (ሉቃስ 2:4-7) በእርግጥም በሚክያስ 5:2 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ ኢየሱስ የተወለደው በቤተልሔም ነው። ታዲያ ችግሩ ምን ነበር? ሰዎቹ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መቸኮላቸው ነው። የተሟላ መረጃ አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት ተሰናከሉ። w21.05 2-3 አን. 4-6
ረቡዕ፣ ሐምሌ 5
ጻድቅ . . . ቢወቅሰኝ በራስ ላይ እንደሚፈስ ዘይት አድርጌ አየዋለሁ።—መዝ. 141:5
መጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመስማታቸው የተባረኩ ሰዎችን ይጠቅሳል። ኢዮብን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢዮብ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ቢሆንም ፍጹም አልነበረም። ኢዮብ ውጥረት ውስጥ ሲገባ አንዳንድ የተሳሳቱ ነገሮችን ተናግሯል። በዚህም የተነሳ ኤሊሁም ሆነ ይሖዋ ቀጥተኛ ምክር ሰጥተውታል። ታዲያ ኢዮብ ምን ምላሽ ሰጠ? እንዲህ ብሏል፦ “ማስተዋል በጎደለው መንገድ ተናግሬአለሁ። . . . በተናገርኩት ነገር እጸጸታለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬም ንስሐ እገባለሁ።” (ኢዮብ 42:3-6, 12-17) በዕድሜ በጣም የሚያንሰው ቢሆንም የኤሊሁን ምክር መስማቱ ትሑት እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ኢዮብ 32:6, 7) እኛም ምክሩ ለእኛ እንደማይሠራ ሲሰማን ወይም ምክሩን የሰጠን ሰው በዕድሜ ከእኛ በጣም የሚያንስ በሚሆንበት ጊዜ ትሕትና ምክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳናል። ደግሞም የመንፈስ ፍሬ ከማፍራት እንዲሁም ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ከምናከናውንበት መንገድ ጋር በተያያዘ ማሻሻያ ማድረግ የማያስፈልገው ማን አለ? w22.02 11 አን. 8፤ 12 አን. 12
ሐሙስ፣ ሐምሌ 6
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።—ዮሐ. 13:35
በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ ጉባኤው ፍቅርና ሰላም የሰፈነበት ቦታ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፤ እንዲህ ካደረጉ ማንም የባይተዋርነት ስሜት አይሰማውም። የምንናገረውና የምናደርገው ነገር በሌሎች ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል! ታዲያ እውነት ውስጥ ቤተሰብ የሌላቸው ክርስቲያኖች የጉባኤው ክፍል እንደሆኑ እንዲሰማቸው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ቅድሚያውን ወስዳችሁ ከአዲሶች ጋር ጓደኝነት መሥርቱ። ልንወስደው የምንችለው የመጀመሪያ እርምጃ አዲሶች ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ ሞቅ ያለ አቀባበል ማድረግ ነው። (ሮም 15:7) ሆኖም ሞቅ ያለ ሰላምታ መስጠታችን ብቻ በቂ አይደለም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከእነሱ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት እንፈልጋለን። ስለዚህ ለአዲሶች ደግነትና ልባዊ አሳቢነት አሳዩአቸው። በግል ጉዳያቸው ውስጥ ጣልቃ ሳትገቡ ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳት ጥረት አድርጉ። አንዳንዶች ስሜታቸውን አውጥተው መናገር ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል፤ ስለዚህ እንዲያዋሯችሁ አትጫኗቸው። ከዚህ ይልቅ የማያሸማቅቃቸው ጥያቄ በመጠየቅ የልባቸውን አውጥተው እንዲናገሩ አበረታቷቸው፤ መልስ ሲሰጧችሁ ደግሞ በጥሞና አዳምጡ። ለምሳሌ እውነትን የሰሙት እንዴት እንደሆነ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። w21.06 11 አን. 13-14
ዓርብ፣ ሐምሌ 7
ድምፄን . . . ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል።—ዮሐ. 10:16
‘በአንድ እረኛ’ ሥር ያለ “አንድ መንጋ” ሆነን ይሖዋን በአንድነት የማገልገል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን! የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ የተባለው መጽሐፍ ገጽ 165 እንዲህ ይላል፦ “በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ካለው አንድነት እየተጠቀምክ በመሆኑ ይህ አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ የበኩልህን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለብህ።” በመሆኑም “ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን . . . ይሖዋ በሚያያቸው መንገድ ለማየት ጥረት” ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋ ሁላችንንም እንደ ‘ትናንሽ’ ልጆች ውድ አድርጎ ይመለከተናል። አንተስ ወንድሞችህን እና እህቶችህን ውድ እንደሆኑ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? ይሖዋ እነሱን ለመርዳትና ለመንከባከብ የምታደርገውን ማንኛውንም ነገር ያስተውላል እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ማቴ. 10:42) የእምነት ባልንጀሮቻችንን በጣም እንወዳቸዋለን። በመሆኑም “በአንድ ወንድም ፊት የሚያደናቅፍ ወይም የሚያሰናክል ነገር ላለማስቀመጥ ቁርጥ ውሳኔ” አድርገናል። (ሮም 14:13) ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን እናስባለን፤ እንዲሁም ከልባችን ይቅር እንላቸዋለን። በተጨማሪም ማንም ሰው እንዲያሰናክለን አንፍቀድ። ከዚህ በተቃራኒ “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።”—ሮም 14:19፤ w21.06 24 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 8
የሚያሳድገው አምላክ [ነው]።—1 ቆሮ. 3:7
ከአምላክ ቃልና ከድርጅቱ የምናገኘውን ምክር በትጋት የምናጠናና በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ ቀስ በቀስ የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ ማዳበር እንችላለን። ስለ አምላክ ያለን እውቀትም እያደገ ይሄዳል። ኢየሱስ የምንሰብከው የመንግሥቱ መልእክት ከትንሽ ዘር ጋር እንደሚመሳሰልና ቅን በሆኑ ሰዎች ልብ ውስጥ ቀስ በቀስ እንደሚያድግ የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “[ዘሪው] እንዴት እንደሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅልና ያድጋል። መሬቱም ራሱ ቀስ በቀስ ፍሬ ያፈራል፤ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ከዚያም ዛላውን በመጨረሻም በዛላው ላይ የጎመራ ፍሬ ይሰጣል።” (ማር. 4:27, 28) ኢየሱስ አንድ ተክል የሚያድገው ቀስ በቀስ እንደሆነ ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበል ሰውም በመንፈሳዊ የሚያድገው ቀስ በቀስ እንደሆነ መግለጹ ነበር። ለምሳሌ ቅን ልብ ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ወደ ይሖዋ በቀረቡ መጠን በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ መልካም ለውጦች ሲያደርጉ እንመለከታለን። (ኤፌ. 4:22-24) ያንን ትንሽ ዘር የሚያሳድገው ግን ይሖዋ እንደሆነ መዘንጋት አይኖርብንም። w21.08 8-9 አን. 4-5
እሁድ፣ ሐምሌ 9
በምኞት ከመቅበዝበዝ ይልቅ ዓይን በሚያየው መደሰት ይሻላል።—መክ. 6:9
ይህ ጥቅስ ደስታ ለማግኘት የሚረዳን ምን እንደሆነ ይናገራል። ‘ዓይኑ በሚያየው የሚደሰት’ ሰው አሁን ያለውን ነገር ያደንቃል። በምኞት የሚቅበዘበዝ ሰው ግን ሊያገኘው የማይችለውን ነገር ሲመኝ ይኖራል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ደስታ ለማግኘት፣ ባለን ነገር እና ልንደርስበት በምንችለው ግብ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። ይሁንና አሁን ባለን ነገር መርካት በእርግጥ ይቻላል? ብዙዎች የማይቻል ይመስላቸዋል፤ ምክንያቱም ሁላችንም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አዲስ ነገር መሞከር እንፈልጋለን። ሆኖም ባለን ነገር መርካት በእርግጥ የሚቻል ነገር ነው። ዓይናችን በሚያየው ነገር ከልባችን መደሰት እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? መልሱን ለማግኘት በማቴዎስ 25:14-30 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ ስለ ታላንቱ የተናገረውን ምሳሌ ልብ እንበል። እንዲሁም ይህ ምሳሌ አሁን ባሉን በረከቶች መደሰት፣ አልፎ ተርፎም ደስታችንን መጨመር ስለምንችልበት መንገድ ምን እንደሚያስተምረን ለማሰብ እንሞክር። w21.08 21 አን. 5-6
ሰኞ፣ ሐምሌ 10
ከፍ ባለውና ቅዱስ በሆነው ስፍራ እኖራለሁ፤ ደግሞም የተሰበረ ልብ ካለውና መንፈሱ ከተደቆሰው ጋር እሆናለሁ።—ኢሳ. 57:15
ይሖዋ ‘የተሰበረ ልብ ላላቸውና መንፈሳቸው ለተደቆሰ’ ሰዎች በጥልቅ ያስብላቸዋል። ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ውድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማበረታታት እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ለእነሱ ልባዊ አሳቢነት በማሳየት ነው። ይሖዋ እሱ ምን ያህል እንደሚወዳቸው እንድናሳያቸው ይፈልጋል። (ምሳሌ 19:17) ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን መርዳት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ በመሆን ነው። ወደ ራሳችን ትኩረት የሚስብ ነገር በማድረግ ሌሎችን ማስቀናት አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ችሎታችንን እና እውቀታችንን ሌሎችን ለማበረታታት እንጠቀምበታለን። (1 ጴጥ. 4:10, 11) ኢየሱስ ተከታዮቹን የያዘበትን መንገድ በመመርመር እኛም ሌሎችን እንዴት መያዝ እንዳለብን መማር እንችላለን። ኢየሱስ እስከ ዛሬ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ሰው ነበር። ያም ቢሆን ‘ገርና በልቡ ትሑት’ ነበር። (ማቴ. 11:28-30) ቀለል ያለ ቋንቋና ማራኪ ምሳሌዎችን በመጠቀም የተራ ሰዎችን ልብ በሚነካ መንገድ አስተምሯል።—ሉቃስ 10:21፤ w21.07 23 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11
ሽማግሌዎችህን . . . ጠይቅ፤ ይነግሩሃል።—ዘዳ. 32:7
ቅድሚያውን ወስዳችሁ አረጋውያንን አነጋግሯቸው። እርግጥ ነው በአሁኑ ወቅት ዓይናቸው ደካማ፣ እርምጃቸው አዝጋሚ፣ ድምፃቸውም ዝግ ያለ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ልባቸው አሁንም ወጣት ነው፤ ደግሞም በይሖዋ ፊት “ጥሩ ስም” አትርፈዋል። (መክ. 7:1) ይሖዋ እነሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸው ለምን እንደሆነ አስታውሱ። ምንጊዜም አክብሮት አሳዩአቸው። ልክ እንደ ኤልሳዕ ሁኑ። ኤልሳዕ ከኤልያስ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን ላይ ከእሱ ላለመለየት ቆርጦ ነበር። ኤልሳዕ ሦስት ጊዜ ኤልያስን “ከአንተ አልለይም” ብሎታል። (2 ነገ. 2:2, 4, 6) አረጋውያንን በደግነት አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ በሌላ አባባል ውስጣቸው ያለውን ቀድተን በማውጣት ትኩረት እንደምንሰጣቸው ማሳየት እንችላለን። (ምሳሌ 1:5፤ 20:5፤ 1 ጢሞ. 5:1, 2) እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ልንጠይቃቸው እንችላለን፦ “ወጣት ሳለህ እውነትን እንዳገኘህ እርግጠኛ እንድትሆን ያደረገህ ምንድን ነው?” “በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህ ነገሮች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ የረዱህ እንዴት ነው?” “በይሖዋ አገልግሎት ምንጊዜም ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ቁልፉ ምንድን ነው ትላለህ?” (1 ጢሞ. 6:6-8) ከዚያም ታሪካቸውን ሲነግሩን በጥሞና ማዳመጥ ይኖርብናል። w21.09 5 አን. 14፤ 7 አን. 15
ረቡዕ፣ ሐምሌ 12
ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ በማድረግ እሱ ደስ ለሚሰኝበት ነገር ብርታት የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።—ፊልጵ. 2:13
እንድንሰብክ እና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ትእዛዝ ለማክበር አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ስታደርግ ለአምላክ ያለህን ፍቅር ታሳያለህ። (1 ዮሐ. 5:3) እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ አነሳስቶሃል። ይህን ትእዛዝ መታዘዝ ቀላል ነበር? ላይሆን ይችላል። ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ወጥተህ የመጀመሪያውን በር ስታንኳኳ ፈርተህ ነበር? መሆን አለበት። ሆኖም ኢየሱስ ይህን ሥራ እንድታከናውን እንደሚፈልግ ስላወቅክ ትእዛዙን አክብረሃል። ደግሞም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በስብከቱ ሥራ መካፈል እየቀለለህ እንደመጣ ጥያቄ የለውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራትን በተመለከተስ ምን ይሰማሃል? ስታስበው እንኳ ይጨንቅሃል? ሊሆን ይችላል። ሆኖም ፍርሃትህን ለማሸነፍ እንዲረዳህና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጥህ ይሖዋን ከጠየቅከው እሱ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የመካፈል ፍላጎትህ እንዲያድግ ይረዳሃል። w21.07 3 አን. 7
ሐሙስ፣ ሐምሌ 13
በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት [ይደረግባቸው]።—ራእይ 13:16
በጥንት ዘመን የነበሩ ባሪያዎች የማን ንብረት መሆናቸውን ለማሳወቅ ቋሚ ምልክት ይደረግባቸው ነበር። በተመሳሳይም በዘመናችን የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ በእጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምሳሌያዊ ምልክት እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም ሰው ከዚህ ዓለም መንግሥታት ጎን እንደሚቆምና እንደሚደግፋቸው በአስተሳሰቡና በድርጊቱ እንዲያሳይ ይጠበቅበታል። እኛስ ይህን ምሳሌያዊ ምልክት ተቀብለን ከፖለቲካዊ መንግሥታት ጎን እንቆም ይሆን? ይህን ምልክት ለመቀበል ፈቃደኛ የማይሆኑ ሁሉ አስቸጋሪና አደገኛ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። የራእይ መጽሐፍ “ምልክቱ . . . ካለው ሰው በስተቀር ማንም መግዛት ወይም መሸጥ” እንደማይችል ይናገራል። (ራእይ 13:17) ይሁን እንጂ የአምላክ ሕዝቦች፣ በራእይ 14:9, 10 ላይ የተገለጸውን ምልክት በሚቀበሉ ሰዎች ላይ ይሖዋ ምን እርምጃ እንደሚወስድባቸው ያውቃሉ። በመሆኑም ይህንን ምልክት ከመቀበል ይልቅ በምሳሌያዊ መንገድ በእጃቸው ላይ “የይሖዋ ነኝ” ብለው ይጽፋሉ። (ኢሳ. 44:5) ለይሖዋ ያለን ታማኝነት የማይናወጥ መሆኑን ለማረጋገጥ ጊዜው አሁን ነው። የማይናወጥ ታማኝነት ካለን ይሖዋም በደስታ ንብረቱ አድርጎ ይቀበለናል! w21.09 18 አን. 15-16
ዓርብ፣ ሐምሌ 14
ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል።—ምሳሌ 27:17
የሌሎችን እርዳታ መቀበላችን አገልግሎታችንን ለማከናወን ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የስብከትና የማስተማር ዘዴዎቹን ለጢሞቴዎስ አካፍሎት ነበር፤ እንዲሁም ጢሞቴዎስ እነዚህን ዘዴዎች ለሌሎችም እንዲያሳይ አበረታቶታል። (1 ቆሮ. 4:17) እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ተሞክሮ ያላቸው ክርስቲያኖች እርዳታ ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም ይሖዋ እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል። በአገልግሎት በተካፈላችሁ ቁጥር የይሖዋን አመራር ለማግኘት ጸልዩ። ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ባይረዳን ኖሮ ማናችንም ምንም ነገር ማከናወን አንችልም ነበር። (መዝ. 127:1፤ ሉቃስ 11:13) ወደ ይሖዋ ስትጸልዩ የምትፈልጉትን ነገር ለይታችሁ ጥቀሱ። ለምሳሌ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያለውና ለመስማት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ለማግኘት እንዲረዳችሁ ልትጸልዩ ትችላላችሁ። ለግል ጥናት ጊዜ መመደባችንም አስፈላጊ ነው። የአምላክ ቃል “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]” ይላል። (ሮም 12:2) ስለ አምላክ ያወቅነው ነገር እውነት እንደሆነ እርግጠኞች በሆንን መጠን በአገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር ስንነጋገር ይበልጥ በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። w21.05 18 አን. 14-16
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 15
ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ [አይደለም]።—1 ቆሮ. 15:58
ምናልባት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይኖርህ ይሆናል። ጥናትህን ለመርዳት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ብታደርግም እንዲሁም ስለ እሱ ብትጸልይም ጥናትህ እድገት ላያደርግ ይችላል። በዚህም ምክንያት ጥናታችሁን ለማቋረጥ ትገደድ ይሆናል። አሊያም ደግሞ እስካሁን ድረስ ለጥምቀት ብቁ እንዲሆን የረዳኸው አንድም ሰው ላይኖር ይችላል። ታዲያ የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማህ ወይም ይሖዋ አገልግሎትህን እንዳልባረከልህ ልታስብ ይገባል? ይሖዋ በስብከቱ ሥራ ውጤታማ መሆን አለመሆናችንን የሚለካው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ይሖዋ የሚመለከተው የምናደርገውን ጥረትና የምናሳየውን ጽናት ነው። ይሖዋ የሥራችንን ስኬታማነት የሚመዝነው ሌሎች በሚሰጡት ምላሽ ሳይሆን በምናሳየው ትጋትና ፍቅር ላይ ተመሥርቶ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አምላክ ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።” (ዕብ. 6:10) የምናከናውነው ሥራ ጥሩ ውጤት ባያስገኝ እንኳ ይሖዋ ያደረግነውን ጥረትና ያሳየነውን ፍቅር አይረሳም። እንግዲያው ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተናገረው ሐሳብ ለእኛም እንደሚሠራ እናስታውስ። w21.10 25 አን. 4-6
እሁድ፣ ሐምሌ 16
አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ፈጽሞ አላባርረውም።—ዮሐ. 6:37
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ደግነቱን እና ፍቅሩን ያሳያል። ችሎታቸው እና ያሉበት ሁኔታ እንደሚለያይ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሁሉም ተመሳሳይ ኃላፊነት መሸከም ወይም በአገልግሎት ላይ እኩል ውጤት ማግኘት እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ያም ቢሆን እያንዳንዳቸው በሙሉ ነፍስ ያደረጉትን ጥረት አድንቋል። ኢየሱስ ስለ ታላንቱ የተናገረው ምሳሌ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳለው ያሳያል። በምሳሌው ላይ ጌታው ለባሪያዎቹ ሥራ የሰጠው “ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው” ነው። በትጋት ከሠሩት ሁለት ባሪያዎች አንዱ ከሌላኛው የበለጠ ትርፍ አግኝቷል። ያም ቢሆን ጌታው ሁለቱንም ያመሰገናቸው ተመሳሳይ የአድናቆት ቃላት በመጠቀም ነው፤ “ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ!” ብሏቸዋል። (ማቴ. 25:14-23) ኢየሱስ እኛንም ደግነት እና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይይዘናል። ችሎታችን እና ያለንበት ሁኔታ እንደሚለያይ ያውቃል፤ እንዲሁም ምርጣችንን ስንሰጥ ይደሰታል። እኛም ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ጠቃሚ ነው። w21.07 23 አን. 12-14
ሰኞ፣ ሐምሌ 17
በጌታዬ ላይ እጄን አላነሳም።—1 ሳሙ. 24:10
ንጉሥ ዳዊት ምሕረት ያላሳየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ኃይለኛ ሰው የነበረው ናባል ስለ ዳዊት በንቀት በተናገረበት ብሎም ለእሱና ለሰዎቹ ምግብ ለመስጠት እንቢ ባለበት ጊዜ ዳዊት በጣም ተበሳጭቶ ናባልንም ሆነ በቤቱ ያሉትን ወንዶች በሙሉ ለመግደል ተነስቶ ነበር። ሆኖም ደግና ትዕግሥተኛ የሆነችው የናባል ሚስት አቢጋኤል አፋጣኝ እርምጃ በመውሰዷ ዳዊት በራሱ ላይ የደም ዕዳ ከማምጣት ሊቆጠብ ችሏል። (1 ሳሙ. 25:9-22, 32-35) ዳዊት በተበሳጨበት ወቅት ‘ናባልና በቤቱ ያሉ ወንዶች በሙሉ ሞት ይገባቸዋል’ ብሎ እንደፈረደ ልብ እንበል። በኋላ ደግሞ ዳዊት በናታን ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ሰው ሞት እንደሚገባው ፈርዶበታል። ከዚህ ዘገባ ጋር በተያያዘ ‘እንደ ዳዊት ያለ ሩኅሩኅ ሰው እንዲህ ያለ ምሕረት የለሽ ፍርድ ያስተላለፈው ለምንድን ነው?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ዳዊት በወቅቱ የነበረበትን ሁኔታ እንመልከት። በዚያ ወቅት ዳዊት ሕሊናው እየወቀሰው ነበር። አንድ ሰው ምሕረት የለሽ መሆኑና ለመፍረድ መቸኮሉ ጥሩ መንፈሳዊ ጤንነት እንደሌለው ያሳያል። w21.10 12 አን. 17-18, 20
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 18
እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።—1 ጴጥ. 1:16
የዛሬው የዕለት ጥቅስ በቅድስና ረገድ ወደር የሌለው ምሳሌ የሆነውን ይሖዋን መምሰል እንደምንችል ያስገነዝበናል። በምግባራችን ቅዱሳን መሆን ይኖርብናል። ፍጹማን ስላልሆንን ይህን ማድረግ እንደማንችል ይሰማን ይሆናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ራሱም ቢሆን አንዳንድ ስህተቶች ሠርቷል፤ ሆኖም የእሱ ምሳሌ ቅዱሳን መሆን እንደምንችል ያሳያል። ብዙዎች፣ “ቅዱስ” ስለሚባሉ ሰዎች ሲያስቡ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ሃይማኖታዊ ልብስ የለበሰ፣ ፊቱ የማይፈታ እና ደስታ የራቀው ሰው ነው። ሆኖም እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል አይደለም። የአምላክ ቃል፣ ቅዱስ የሆነውን ይሖዋን “ደስተኛው አምላክ” በማለት ይጠራዋል። (1 ጢሞ. 1:11) አገልጋዮቹም “ደስተኛ” እንደሆኑ ይገልጻል። (መዝ. 144:15) ኢየሱስ የተለየ ሃይማኖታዊ ልብስ የሚለብሱና ጽድቃቸውን ለሌሎች ለማሳየት የሚጥሩ ሰዎችን አውግዟል። (ማቴ. 6:1፤ ማር. 12:38) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅድስና ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ያስችለናል። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ልንፈጽመው የማንችል ትእዛዝ እንደማይሰጠን እርግጠኞች ነን። w21.12 2 አን. 1, 3
ረቡዕ፣ ሐምሌ 19
አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ . . . ውደድ።—ማር. 12:30
ይሖዋ ብዙ ስጦታዎችን በደግነት ሰጥቶናል፤ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ስጦታዎቹ መካከል አንዱ ደግሞ እሱን የማምለክ መብታችን ነው። የይሖዋን ‘ትእዛዛት በመጠበቅ’ እሱን እንደምንወደው እናሳያለን። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋ እንድንጠብቅ ከሚፈልጋቸው ትእዛዛት መካከል ኢየሱስ የሰጠው ትእዛዝ ይገኝበታል፤ ኢየሱስ ሰዎችን እያጠመቅን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ አዞናል። (ማቴ. 28:19) በተጨማሪም እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ትእዛዝ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 13:35) ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች፣ በመላው ዓለም ያሉ አምላኪዎቹን ያቀፈው ቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ ይፈቅድላቸዋል። (መዝ. 15:1, 2) ለሌሎች ፍቅር አሳይ። ፍቅር የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ፍቅር ያሳየን እኛ እሱን ከማወቃችን እንኳ በፊት ነው። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ለሌሎች ፍቅር በማሳየት እሱን መምሰል እንችላለን። (ኤፌ. 5:1) ለሰዎች ፍቅር ማሳየት ከምንችልባቸው ወሳኝ መንገዶች አንዱ፣ ጊዜው ከማለፉ በፊት ስለ ይሖዋ እንዲማሩ መርዳት ነው። (ማቴ. 9:36-38) እንዲህ ስናደርግ የይሖዋ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ እንከፍትላቸዋለን። w21.08 5-6 አን. 13-14
ሐሙስ፣ ሐምሌ 20
[ከዚህ] የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።—ዮሐ. 15:13
ኢየሱስ ለይሖዋ ያለው ጥልቅ ፍቅር ለአባቱም ሆነ ለእኛ ሲል መሥዋዕት እንዲከፍል አነሳስቶታል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ሕይወቱን የመራበት መንገድ ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። በእያንዳንዱ ቀን ለሁሉም ሰው ሌላው ቀርቶ ለሚቃወሙት ሰዎችም ጭምር ፍቅርና ርኅራኄ ያሳይ ነበር። ሰዎችን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማሩ ለእነሱ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ዋነኛ መንገድ ነው። (ሉቃስ 4:43, 44) ኢየሱስ በኃጢአተኞች እጅ ተሠቃይቶ ለመሞት ፈቃደኛ መሆኑ ለአምላክ እና ለሰዎች ያለውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳያል። ይህን በማድረጉም ሁላችንም የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ተከፍቶልናል። ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንነውና የተጠመቅነው የሰማዩን አባታችንን ስለምንወደው ነው። በመሆኑም ልክ እንደ ኢየሱስ ሰዎችን የምንይዝበት መንገድ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም” ሲል ጽፏል።—1 ዮሐ. 4:20፤ w22.03 10 አን. 8-9
ዓርብ፣ ሐምሌ 21
የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።—ኤፌ. 5:15, 16
ከይሖዋ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚያስደስተን ነገር ቢሆንም እንቅፋት የሚሆንብን አንድ ነገር አለ፤ ጊዜያችን በጣም የተጣበበ ነው። በመሆኑም ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚሆን ጊዜ ማግኘት ሊከብደን ይችላል። ሰብዓዊ ሥራ፣ የቤተሰብ ኃላፊነት እና ሌሎች አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ጊዜያችንን በጣም ስለሚይዙብን ለመጸለይ፣ ለማጥናት ወይም ለማሰላሰል ጊዜ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል። ሳይታወቀን ጊዜያችንን የሚሻማብን ሌላም ነገር አለ። ጠንቃቆች ካልሆንን በራሳቸው ምንም ስህተት የሌለባቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የምንጠቀምበትን ጊዜ ሊሰርቁብን ይችላሉ። በመዝናኛ የምናሳልፈውን ጊዜ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሁላችንም አልፎ አልፎ ዘና ማለታችን ይጠቅመናል። ሆኖም ጤናማ መዝናኛም እንኳ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምናውለው ጊዜ እስክናጣ ድረስ ጊዜያችንን ሊሻማብን ይችላል። በመሆኑም ለመዝናኛ ከተገቢው ያለፈ ቦታ እንዳንሰጥ መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ምሳሌ 25:27፤ 1 ጢሞ. 4:8፤ w22.01 26 አን. 2-3
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 22
አብሯችሁ የሚኖረውን የባዕድ አገር ሰው እንደ አገራችሁ ተወላጅ አድርጋችሁ ተመልከቱት፤ እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁም ውደዱት።—ዘሌ. 19:34
ይሖዋ እስራኤላውያን ባልንጀራቸውን እንዲወዱ መመሪያ ሲሰጣቸው ሌሎች እስራኤላውያንን ብቻ እንዲወዱ ማዘዙ አልነበረም። እስራኤላውያን በመካከላቸው የሚኖሩትን የባዕድ አገር ሰዎችም እንዲወዱ ታዘዋል። በዘሌዋውያን 19:33, 34 ላይ ይህ መመሪያ በግልጽ ሰፍሯል። እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሰዎችን ‘እንደ አገራቸው ተወላጅ አድርገው ሊመለከቷቸው’ እንዲሁም ‘እንደ ራሳቸው አድርገው ሊወዷቸው’ ይገባ ነበር። ለምሳሌ ያህል እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሰዎችንም ሆነ በአገራቸው ያሉ ድሆችን ከእርሻቸው እንዲቃርሙ ሊፈቅዱላቸው እንደሚገባ ሕጉ ያዝዝ ነበር። (ዘሌ. 19:9, 10) የባዕድ አገር ሰዎችን ስለመውደድ የሚገልጸው መሠረታዊ ሥርዓት በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያኖችም ይሠራል። (ሉቃስ 10:30-37) እንዴት? በዛሬው ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአገራቸው ተሰደዋል፤ ምናልባትም አንተ በምትኖርበት አካባቢ አንዳንድ ስደተኞች ይኖሩ ይሆናል። እነዚህን ሰዎች በአክብሮት ልንይዛቸው ይገባል። w21.12 12 አን. 16
እሁድ፣ ሐምሌ 23
ይሖዋን የሚሹ . . . መልካም ነገር አይጎድልባቸውም።—መዝ. 34:10
በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ በመታመን የእሱን መመሪያ የመከተል ልማድ ካለን ወደፊትም እኛን ለማዳን ችሎታው እንዳለው ይበልጥ እንተማመናለን። ለምሳሌ በወረዳ ወይም በክልል ስብሰባ ላይ ለመገኘት አሠሪያችን እረፍት እንዲሰጠን መጠየቅ ያስፈልገን ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በአገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ የሥራ ፕሮግራማችንን እንዲያስተካክልልን አሠሪያችንን ማነጋገር ያስፈልገን ይሆናል። እነዚህን ነገሮች ማድረግ እምነትና በይሖዋ መታመን ይጠይቃል። አሠሪያችን ጥያቄያችንን ባይቀበለውና ከሥራ ብንባረርስ? ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይጥለንና እንደማይተወን እንዲሁም መሠረታዊ ፍላጎታችንን ሁልጊዜ እንደሚያሟላልን እንተማመናለን? (ዕብ. 13:5) በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ ብዙዎች ይሖዋ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንዴት እንደደረሰላቸው የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ሲናገሩ እንሰማለን። በእርግጥም ይሖዋ ታማኝ ነው። ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለሆነ የወደፊቱን ጊዜ የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለንም። በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ እስካስቀደምን ድረስ አምላካችን መቼም ቢሆን አይተወንም። w22.01 7 አን. 16-17
ሰኞ፣ ሐምሌ 24
የምትፈርዱት ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ [ነው]።—2 ዜና 19:6
በሽማግሌዎች ላይ ያለን እምነት የሚፈተነው መቼ ነው? በጣም የምንቀርበው አንድ ሰው ተወገደ እንበል። ‘ሽማግሌዎች ጉዳዩን በደንብ አጣርተውታል?’ የሚል ጥርጣሬ ሊፈጠርብን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ‘የሰጡት ፍርድ ይሖዋ ጉዳዩን ቢያየው ኖሮ የሚሰጠው ዓይነት ፍርድ ነው?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ታዲያ ላደረጉት ውሳኔ ተገቢውን አመለካከት ለመያዝ ምን ሊረዳን ይችላል? ውገዳ የይሖዋ ዝግጅት እንደሆነ እንዲሁም ጉባኤውን አልፎ ተርፎም የተወገደውን ሰው እንደሚጠቅመው ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ንስሐ ያልገባ ኃጢአተኛ በጉባኤ ውስጥ እንዲቀጥል ቢፈቀድለት በሌሎች ላይም መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (ገላ. 5:9) ከዚህም ሌላ የኃጢአቱን ክብደት መገንዘብ ሊከብደው ይችላል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚያስፈልገውን የአስተሳሰብና የድርጊት ለውጥ ለማድረግ አይነሳሳም። (መክ. 8:11) ሽማግሌዎች አንድ ሰው እንዲወገድ ሲወስኑ ይህን ኃላፊነታቸውን አክብደው እንደሚመለከቱት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w22.02 5 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 25
የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም።—ማቴ. 12:20
በተለይ አንድ ግለሰብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰጠውን ምክር ለመቀበል ሲያንገራግር ትዕግሥትና ደግነት ማሳየት አስፈላጊ ነው። አንድ ሽማግሌ የሰጠው ምክር ወዲያውኑ ተቀባይነት ካላገኘ ወይም ተግባር ላይ ካልዋለ እንዳይበሳጭ መጠንቀቅ አለበት። ሽማግሌው በግሉ በሚያቀርበው ጸሎት ላይ ይሖዋ ምክር የተሰጠውን ግለሰብ እንዲባርከው እንዲሁም ምክሩ ያስፈለገበትን ምክንያት እንዲረዳና ተግባራዊ እንዲያደርግ እንዲረዳው መለመኑ የተሻለ ነው። ምክር የተሰጠው ግለሰብ ስለ ምክሩ ለማሰብ ጊዜ ያስፈልገው ይሆናል። ሽማግሌው ታጋሽና ደግ ከሆነ የሚመከረው ሰው ምክሩ በተሰጠበት መንገድ ላይ አያተኩርም፤ ከዚህ ይልቅ ምክሩ በያዘው መልእክት ላይ ማተኮር ይችላል። እርግጥ ነው፣ ምክሩ ምንጊዜም በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። ምንጊዜም ግባችን ውጤታማ ብቻ ሳይሆን ‘ልብን ደስ የሚያሰኝ’ ምክር መስጠት እንደሆነ አትርሱ።—ምሳሌ 27:9፤ w22.02 18 አን. 17፤ 19 አን. 19
ረቡዕ፣ ሐምሌ 26
የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል።—ምሳሌ 13:12
አንድን ፈተና ወይም ድክመት ለማሸነፍ ኃይል እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ ከጸለይን በኋላ የምንፈልገው መፍትሔ እንደዘገየብን ሊሰማን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ጸሎታችንን ቶሎ የማይመልስልን ለምንድን ነው? ይሖዋ የምናቀርበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት በእሱ ላይ እምነት እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ አድርጎ ይመለከተዋል። (ዕብ. 11:6) ይሖዋ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድና ፈቃዱን ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነትም ማየት ይፈልጋል። (1 ዮሐ. 3:22) ስለዚህ አንድን መጥፎ ልማድ ወይም ድክመት ለማሸነፍ እንዲረዳን ይሖዋን ከጠየቅነው በኋላ ታጋሽ መሆንና ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ሊኖርብን ይችላል። ኢየሱስ አንዳንዶቹ ጸሎቶቻችን ወዲያውኑ ምላሽ ላያገኙ እንደሚችሉ ጠቁሟል። እንዲህ ብሏል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ ደጋግማችሁ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይሰጠዋልና፤ የሚፈልግ ሁሉ ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ሁሉ ይከፈትለታል።”—ማቴ. 7:7, 8፤ w21.08 8 አን. 1፤ 10 አን. 9-10
ሐሙስ፣ ሐምሌ 27
ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።—መዝ. 119:97
በፈጣሪህ ላይ እምነት ለማዳበር የአምላክን ቃል ማጥናትህን መቀጠል ይኖርብሃል። (ኢያሱ 1:8) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች በትኩረት አጥና፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑን ልብ በል። እንዲህ ማድረግህ አፍቃሪና ጥበበኛ የሆነ አምላክ እንደፈጠረንና መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈሱ እንዳስጻፈው ያለህን እምነት ያጠናክረዋል። (2 ጢሞ. 3:14፤ 2 ጴጥ. 1:21) የአምላክን ቃል ስታጠና፣ የሚሰጣቸው ምክሮች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ለማስተዋል ሞክር። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብን መውደድ ጎጂ እንደሆነና “ብዙ ሥቃይ” እንደሚያስከትል ከረጅም ጊዜ በፊት አስጠንቅቋል። (1 ጢሞ. 6:9, 10፤ ምሳሌ 28:20፤ ማቴ. 6:24) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ የገንዘብ ፍቅር እንዳያድርብን የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንኛ ጠቃሚ ነው! በሕይወትህ ውስጥ የጠቀሙህ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መጥቀስ ትችላለህ? የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ባስተዋልን መጠን አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን በሰጠን ጊዜ የማይሽረው ጥበብ ያዘለ ምክር ላይ ይበልጥ እንተማመናለን። (ያዕ. 1:5) ይህም ሕይወታችን ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ያደርግልናል።—ኢሳ. 48:17, 18፤ w21.08 17-18 አን. 12-13
ዓርብ፣ ሐምሌ 28
አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10
ዕድሜህ እየገፋ ከሆነ ይሖዋ ከዚህ ቀደም ያከናወንከውን ሥራ እንደማይረሳው እርግጠኛ ሁን። የስብከቱን ሥራ በቅንዓት ደግፈሃል። ቅስም የሚሰብሩ ችግሮችን ጨምሮ ብዙ ፈተናዎችን በጽናት ተቋቁመሃል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ መሥፈርቶች ጎን ቆመሃል፤ ከባድ ኃላፊነቶችን ተወጥተሃል፤ እንዲሁም ሌሎችን አሠልጥነሃል። በፍጥነት ከሚጓዘው የይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ለመሄድ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርገሃል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖችን ደግፈሃል እንዲሁም አበረታተሃል። ለምታሳየው ታማኝነት ይሖዋ አምላክ በጣም ይወድሃል። ይሖዋ ‘ታማኝ አገልጋዮቹን እንደማይተዋቸው’ ቃል ገብቷል! (መዝ. 37:28) ለአረጋውያን “ፀጉራችሁ እስኪሸብትም ድረስ እሸከማችኋለሁ” የሚል ዋስትና ሰጥቷል። (ኢሳ. 46:4) እንግዲያው ዕድሜህ ስለገፋ ብቻ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጠቃሚ ሥራ ማከናወን እንደማትችል ሊሰማህ አይገባም። አሁንም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከት ትችላለህ! w21.09 3 አን. 4
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 29
ይሖዋ . . . ለሚፈሩት ምሕረት አሳይቷል።—መዝ. 103:13
ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው ወደር የለሽ ጥበብ ስላለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት” እንደሆነ ይናገራል። (ያዕ. 3:17) ልክ እንደ አፍቃሪ ወላጅ ይሖዋ፣ ምሕረት ማሳየቱ ልጆቹን እንደሚጠቅማቸው ያውቃል። (ኢሳ. 49:15) ይሖዋ ምሕረት የሚያሳይ መሆኑ ሰዎች ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ተስፋ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ስለዚህ ይሖዋ ወደር የለሽ ጥበብ ያለው በመሆኑ፣ ምሕረት ለማድረግ የሚያስችል ምክንያት እስካለ ድረስ ምሕረት ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋ ምሕረት ፍጹም ሚዛናዊ ነው። ይሖዋ ጥበበኛ ነው፤ ስለዚህ መሐሪ መሆኑ ልል እንዲሆን አያደርገውም። አንድ የአምላክ አገልጋይ ሆን ብሎ የኃጢአት ጎዳና መከተል ጀመረ እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ ‘እንዲህ ካለው ሰው ጋር መግጠማችሁን ተዉ’ የሚል ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 5:11) ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤው ይወገዳሉ። ይህ እርምጃ መወሰዱ ታማኝ የሆኑት ወንድሞችና እህቶች ከጉዳት እንዲጠበቁ ከማድረጉም ሌላ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ለማስከበር ያስችላል። w21.10 9-10 አን. 7-8
እሁድ፣ ሐምሌ 30
አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው [ይወዳል]።—2 ቆሮ. 9:7
የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ መዋጮ ስናደርግ ለይሖዋ አምልኮ እያቀረብን ነው። እስራኤላውያን ባዶ እጃቸውን ይሖዋ ፊት ሊቀርቡ አይገባም ነበር። (ዘዳ. 16:16) ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን ስጦታ ይዘው መሄድ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ መንገድ እነሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት ለተደረጉት ዝግጅቶች አድናቆት እንዳላቸው ያሳያሉ። እኛስ ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና ለተደረጉልን መንፈሳዊ ዝግጅቶች ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ሁኔታችን በፈቀደልን መጠን ለጉባኤያችንና ለዓለም አቀፉ ሥራ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ለመስጠት ፈቃደኝነቱ ካለ ስጦታው ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው አንድ ሰው ባለው መጠን ሲሰጥ እንጂ በሌለው መጠን ሲሰጥ አይደለም።” (2 ቆሮ. 8:4, 12) የምናደርገው መዋጮ የቱንም ያህል ትንሽ ቢሆን ከልባችን የመነጨ እስከሆነ ድረስ ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ማር. 12:42-44፤ w22.03 24 አን. 13
ሰኞ፣ ሐምሌ 31
የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።—1 ተሰ. 5:14
ሽማግሌዎች የይሖዋ ሕዝቦች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በሙሉ ሊያስወግዱ አይችሉም። ያም ቢሆን ይሖዋ ሽማግሌዎች የእሱን በጎች ለማበረታታትና ለመጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ ይፈልጋል። ታዲያ ሽማግሌዎች ብዙ ሥራ ቢኖርባቸውም ለወንድሞችና ለእህቶች አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ጊዜ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ ተከተሉ። ጳውሎስ ወንድሞቹን ለማመስገንና ለማነጽ አጋጣሚ ይፈልግ ነበር። ሽማግሌዎች የይሖዋን ሕዝቦች በፍቅር በመንከባከብ የእሱን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ ነው። (1 ተሰ. 2:7) ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እንደሚወዳቸውና ይሖዋም እንደሚወዳቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮ. 2:4፤ ኤፌ. 2:4, 5) በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን እንደ ወዳጅ በመቁጠር አብሯቸው ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ስለሚያስፈሩት ነገሮችና ስለ ድክመቶቹ በግልጽ በመናገር እንደሚያምናቸው አሳይቷል። (2 ቆሮ. 7:5፤ 1 ጢሞ. 1:15) ያም ቢሆን ጳውሎስ በራሱ ችግሮች ላይ አላተኮረም። ከዚህ ይልቅ ወንድሞቹን በመርዳት ላይ አተኩሯል። w22.03 28 አን. 9-10