የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es23 ገጽ 118-128
  • ታኅሣሥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታኅሣሥ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 1
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 2
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 3
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 4
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 5
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 6
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 7
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 9
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 10
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 11
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 13
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 15
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 16
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 17
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 19
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 21
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 22
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 23
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 24
  • ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25
  • ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 26
  • ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 27
  • ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 28
  • ዓርብ፣ ታኅሣሥ 29
  • ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 30
  • እሁድ፣ ታኅሣሥ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
es23 ገጽ 118-128

ታኅሣሥ

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 1

ድምፄንም ይሰማሉ።—ዮሐ. 10:16

ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ያለውን የቀረበ ግንኙነት በአንድ እረኛና በበጎቹ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር አመሳስሎታል። (ዮሐ. 10:14) ይህ ንጽጽር ተገቢ ነው። ምክንያቱም በጎች እረኛቸውን ያውቁታል፤ ድምፁንም ሰምተው ይከተሉታል። አንድ ቱሪስት ይህን በዓይኑ ተመልክቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ሜዳ ላይ ተሰማርተው የነበሩ በጎችን ቪዲዮ መቅረጽ ስለፈለግን ወደ እኛ እንዲቀርቡ ለማድረግ ሞከርን። በጎቹ ግን ድምፃችንን ስላላወቁት ወደ እኛ አልመጡም። ብዙም ሳይቆይ አንድ ትንሽ ልጅ መጣ፤ ልጁ እረኛቸው ነበር። ልጁ ልክ እንደጠራቸው በጎቹ ተከተሉት።” ይህ ቱሪስት ያጋጠመው ነገር፣ ኢየሱስ በጎቹን ማለትም ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። ኢየሱስ “ድምፄንም ይሰማሉ” ብሎ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ያለው በሰማይ ነው። ታዲያ ድምፁን መስማት የምንችለው እንዴት ነው? የጌታችንን ድምፅ እንደምንሰማ ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ትምህርቶቹን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ነው።—ማቴ. 7:24, 25፤ w21.12 16 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 2

ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል።—ሮም 3:23

ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት የሚያደርስ ግትር ሰው ነበር። በኋላ ላይ ግን ስህተቱን አምኖ በመቀበል አመለካከቱንና ባሕርይውን ለማስተካከል ፈቃደኛ ሆኗል። (1 ጢሞ. 1:12-16) በይሖዋ እርዳታ ጳውሎስ አፍቃሪ፣ ሩኅሩኅና ትሑት እረኛ መሆን ችሏል። ስህተቶቹን እያሰበ ከመብሰልሰል ይልቅ በይሖዋ ይቅር ባይነት ላይ ለማተኮር መርጧል። (ሮም 7:21-25) ከራሱ ፍጽምናን አልጠበቀም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያናዊ ባሕርያቱን ለማሻሻል በትጋት ሠርቷል፤ እንዲሁም በትሕትና በይሖዋ በመታመን ሥራውን አከናውኗል። (1 ቆሮ. 9:27፤ ፊልጵ. 4:13) ሽማግሌዎች የሚሾሙት ፍጹም ስለሆኑ አይደለም። ሆኖም ይሖዋ ስህተታቸውን አምነው እንዲቀበሉና ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ይጠብቅባቸዋል። (ኤፌ. 4:23, 24) አንድ ሽማግሌ የአምላክን ቃል ተጠቅሞ ራሱን በመመርመር አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርበታል። እንዲህ ካደረገ ይሖዋ ደስተኛና ስኬታማ እንዲሆን ይረዳዋል።—ያዕ. 1:25፤ w22.03 29-30 አን. 13-15

እሁድ፣ ታኅሣሥ 3

አትፍረዱ።—ማቴ. 7:1

በአንድ የእምነት ባልንጀራችን ላይ እንደፈረድን ከተገነዘብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ወንድሞቻችንን ልንወዳቸው እንደሚገባ ማስታወስ አለብን። (ያዕ. 2:8) ከዚህም ሌላ ይሖዋ በሌሎች ላይ መፍረዳችንን እንድንተው እንዲረዳን በጸሎት እንለምነው። በውስጣችን የፈረድንበትን ወንድም ለመቅረብ ጥረት በማድረግ ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ እንችላለን። ምናልባትም አብሮን እንዲያገለግል ልንጠይቀው ወይም ቤታችን ልንጋብዘው እንችል ይሆናል። ወንድማችንን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ በጎ ባሕርያቱ ላይ በማተኮር የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ይህን ስናደርግ ጥሩው እረኛ “መፍረዳችሁን ተዉ” በማለት የሰጠንን ትእዛዝ እንደምንሰማ እናሳያለን። በጎች የእረኛቸውን ድምፅ እንደሚሰሙ ሁሉ የኢየሱስ ተከታዮችም የእሱን ድምፅ ይሰማሉ። ‘የትንሹ መንጋ’ አባላትም ሆንን ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል የጥሩውን እረኛ ድምፅ መስማታችንንና መታዘዛችንን እንቀጥል።—ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 10:11, 14, 16፤ w21.12 19 አን. 11፤ 21 አን. 17-18

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 4

ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር [ተወ]።—1 ነገ. 12:8

ሮብዓም የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ሕዝቡ አንድ ጥያቄ አቀረቡለት። ጥያቄያቸው አባቱ ሰለሞን የጫነባቸውን ሸክም እንዲያቀልላቸው ነበር። ሮብዓም ለሕዝቡ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለበት የእስራኤልን ሽማግሌዎች አማከረ፤ ይህም የሚያስመሰግነው ነው። ሽማግሌዎቹ፣ ንጉሡ ሕዝቡ የጠየቁትን ካደረገላቸው ምንጊዜም ከጎኑ እንደሚሆኑ ነገሩት። (1 ነገ. 12:3-7) ሮብዓም ግን ይህ ምክር ያረካው አይመስልም፤ ስለዚህ አብሮ አደጎቹን አማከረ። እነሱም የሕዝቡን ሸክም እንዲያከብድባቸው መከሩት። (1 ነገ. 12:9-11) ሮብዓም የትኛውን ምክር መከተል እንዳለበት ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ ይችል ነበር። እሱ ግን የአብሮ አደጎቹን ምክር ለመቀበል መረጠ። ይህ ያስከተለው መዘዝ ለሮብዓም ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡም ተረፈ። እኛም አንዳንድ ጊዜ የሚሰጠን ምክር ብዙም ላያስደስተን ይችላል። ያም ቢሆን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ ልንቀበለው ይገባል። w22.02 9 አን. 6

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 5

የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው።—ምሳሌ 20:29

ትሑት የሆነና ልኩን የሚያውቅ ሰው በወጣቶች ተሞክሮ ማነስ ላይ ሳይሆን በጥንካሬያቸው ላይ ያተኩራል። እንደ ተፎካካሪዎቹ ሳይሆን አብረውት እንደሚሠሩ ወንድሞቹ አድርጎ ይመለከታቸዋል። አረጋውያን ወጣቶችን ከይሖዋ እንዳገኟቸው ስጦታዎች አድርገው ይመለከቷቸዋል፤ ለእነዚህ ስጦታዎችም አመስጋኝ ናቸው። አረጋውያን አቅማቸው እየደከመ ሲሄድ ሥራውን ለማከናወንና ጉባኤውን ለማገልገል ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ ያላቸው ወጣቶች በመኖራቸው ደስተኞች ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰችው አረጋዊቷ ናኦሚ የወጣቶችን እርዳታ በአመስጋኝነት በመቀበል ረገድ ግሩም ምሳሌ ትታልናለች። መጀመሪያ ላይ ናኦሚ፣ መበለት የሆነችውን ምራቷን ሩትን ወደ ሕዝቧ እንድትመለስ አበረታታት ነበር። ሆኖም ናኦሚ፣ ሩት አብራት ወደ ቤተልሔም ለመሄድ እንደቆረጠች ስታውቅ የዚህችን ታማኝ ሴት እርዳታ በደስታ ተቀብላለች። (ሩት 1:7, 8, 18) ይህም ለሁለቱም ሴቶች ታላቅ በረከት አምጥቶላቸዋል! (ሩት 4:13-16) አረጋውያን ትሑት መሆናቸው የናኦሚን ምሳሌ ለመከተል ያነሳሳቸዋል። w21.09 10-11 አን. 9-11

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 6

አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም . . . ያሳያችሁትን ፍቅር በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10

በሰማይ ያለው አባታችን እያንዳንዳችን ያለንበትን ሁኔታ ይረዳል። ምናልባት ከምታውቋቸውና ከምትወዷቸው ብዙ ሰዎች የበለጠ ማድረግ ትችሉ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በዕድሜያችሁ፣ በጤናችሁ ሁኔታ ወይም ባለባችሁ የቤተሰብ ኃላፊነት የተነሳ የሌሎችን ያህል ማድረግ አትችሉ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠማችሁ ተስፋ አትቁረጡ። (ገላ. 6:4) ይሖዋ እያንዳንዳችን የምናከናውነውን ሥራ አይረሳም። በትክክለኛው ዝንባሌ ተነሳስተን ምርጣችንን እስከሰጠነው ድረስ በምናደርገው ነገር ደስ ይሰኛል። ይሖዋ ለማድረግ የምናስበውን ነገር እንኳ ያያል። ለእሱ ማቅረብ በምንችለው አምልኮ ደስተኛ እንድንሆንና እንድንረካ ይፈልጋል። ይሖዋ አገልጋዮቹ ችግር ሲያጋጥማቸው እንደሚረዳቸው ስለምናውቅ የአእምሮ ሰላም አለን። (ኢሳ. 41:9, 10) በእርግጥም ከፍጥረት ሁሉ ‘ግርማና ክብር ሊቀበል የሚገባውን’ አፍቃሪውን አባታችንን ስናመልክ ደስተኛ የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን።—ራእይ 4:11፤ w22.03 24 አን. 16፤ 25 አን. 18

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 7

ትእዛዛትህን ለመጠበቅ ፈጠንኩ፤ ፈጽሞ አልዘገየሁም።—መዝ. 119:60

ኢየሱስን መምሰል እንፈልጋለን፤ ሆኖም እሱ የተወውን ምሳሌ በተሟላ መንገድ መከተል ባንችል ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። (ያዕ. 3:2) አንድ የሥነ ጥበብ ተማሪ የአስተማሪውን ሥራ ፍጹም በሆነ መንገድ አስመስሎ መሥራት እንደማይችል የታወቀ ነው። ሆኖም ተማሪው ከስህተቱ ሲማርና የአስተማሪውን ሥራ በተቻለው መጠን ለመከተል ጥረት ሲያደርግ እየተሻሻለ ይሄዳል። እኛም በተመሳሳይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የተማርነውን ነገር በተግባር የምናውል እንዲሁም ያሉብንን ድክመቶች ለማሻሻል የቻልነውን ያህል የምንጥር ከሆነ የኢየሱስን አርዓያ ስኬታማ በሆነ መንገድ መከተል እንችላለን። (መዝ. 119:59) የምንኖረው ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች ግን ይለያሉ። ኢየሱስ ያሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፤ የእሱን ምሳሌ ለመከተልም ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስ የተወውን የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ለመከተል የቻልነውን ያህል የምንጥር ከሆነ የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን። w22.02 24 አን. 16፤ 25 አን. 18

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 8

በደብዳቤዎቹ ውስጥ ለመረዳት የሚከብዱ አንዳንድ ነገሮች አሉ።—2 ጴጥ. 3:16

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ ከሚሰጥባቸው መንገዶች መካከል አንዱ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ይሖዋ በሚያስተምረን ነገር ላይ ለማሰላሰል ጊዜ የምንመድብ ከሆነ የእሱን መመሪያ መቀበልና አገልግሎታችንን መፈጸም እንችላለን። (1 ጢሞ. 4:15, 16) ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ የሚሰጥበት ሌላው መንገድ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45) አንዳንድ ጊዜ ታማኙ ባሪያ የሚሰጠውን መመሪያ ሙሉ በሙሉ መረዳት ሊከብደን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚረዱ ዝርዝር መመሪያዎች ይሰጡን ይሆናል፤ ሆኖም ይህ አደጋ በእኛ አካባቢ እንደማያጋጥም ሊሰማን ይችላል። የሚሰጡን መመሪያዎች እኛ ላለንበት ሁኔታ እንደማይሠሩ በሚሰማን ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብናቸውን ዘገባዎች እናስብ። የአምላክ ሕዝቦች ከሰብዓዊ እይታ አንጻር ጥበብ የጎደለው የሚመስል መመሪያ የተሰጣቸው ጊዜ ነበር፤ መታዘዛቸው ግን የኋላ ኋላ ሕይወታቸውን አትርፎላቸዋል።—መሳ. 7:7፤ 8:10፤ w22.03 18 አን. 15-16

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 9

አባት ሆይ፣ መንፈሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ።—ሉቃስ 23:46

ኢየሱስ በልበ ሙሉነት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተናግሯል። የወደፊት ሕይወቱ የተመካው በይሖዋ ላይ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር፤ አባቱ እንደሚያስታውሰውም እርግጠኛ ነበር። ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? ሕይወታችሁን በይሖዋ እጅ አደራ ለመስጠት ፈቃደኞች ሁኑ። እንዲህ ለማድረግ ‘በሙሉ ልባችሁ በይሖዋ መታመን’ ያስፈልጋችኋል። (ምሳሌ 3:5) የ15 ዓመት ወጣት የሆነውን ጆሹዋ የተባለ ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጆሹዋ በማይድን በሽታ ተይዞ ነበር። ይህ ወጣት የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ሕክምና ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። ከመሞቱ በፊት እናቱን እንዲህ ብሏት ነበር፦ “እማዬ አሁን በይሖዋ እጅ ነኝ። . . . ይሖዋ በትንሣኤ እንደሚያስነሳኝ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ። እሱ በልቤ ውስጥ ያለውን ያውቃል፤ ከልቤ እወደዋለሁ።” እያንዳንዳችን እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘ሕይወቴን አደጋ ላይ የሚጥል የእምነት ፈተና ቢያጋጥመኝ ይሖዋ እንደሚያስታውሰኝ በመተማመን ሕይወቴን በእጁ አደራ እሰጣለሁ?’ w21.04 12-13 አን. 15-16

እሁድ፣ ታኅሣሥ 10

ሌሎችን የሚያረካ . . . እሱ ራሱ ይረካል።—ምሳሌ 11:25

የይሖዋ ምሥክሮች ከአገልግሎት ብርታት ማግኘት ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ስናካፍል ሰዎቹ ጥሩ ምላሽ ሰጡም አልሰጡ መንፈሳችን ይታደሳል፤ እንዲሁም ብርታት እናገኛለን። አንዳንዶች ባሉበት ሁኔታ የተነሳ በአገልግሎት ብዙ ማከናወን እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆናል። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ምርጥህን እስከሰጠኸው ድረስ እንደሚደሰት አስታውስ። በሕመም ምክንያት ከቤት መውጣት ባንችልም እንኳ ይሖዋ በአገልግሎት ለመካፈል ያለንን ጉጉት ይመለከታል፤ ጥረታችንንም ያደንቃል። ይሖዋ፣ ለሚያስታምሙን ሰዎች ወይም ለሕክምና ባለሙያዎች ለመመሥከር አጋጣሚ ሊከፍትልን ይችላል። አሁን የምናከናውነውን አገልግሎት ቀደም ሲል እናከናውን ከነበረው ጋር የምናወዳድር ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እየረዳን ያለው እንዴት እንደሆነ የምንገነዘብ ከሆነ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በደስታ ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ይኖረናል። ከምንዘራቸው የእውነት ዘሮች መካከል የሚጸድቁትና የሚያድጉት የትኞቹ እንደሆኑ አናውቅም።—መክ. 11:6፤ w21.05 24-25 አን. 14-17

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 11

በፊቱ መጥፎ ነገር በመሥራት የይሖዋን ቃል ያቃለልከው ለምንድን ነው?—2 ሳሙ. 12:9

ይሖዋ ለንጉሥ ዳዊት ብዙ ነገሮች ሰጥቶት ነበር፤ ሀብት፣ ንግሥና እንዲሁም በጠላቶቹ ላይ ድል ሰጥቶታል። ዳዊትም የአምላክን ስጦታዎች ‘ዘርዝሮ ሊጨርሳቸው እንደማይችል’ በአመስጋኝነት ተናግሮ ነበር። (መዝ. 40:5) በአንድ ወቅት ግን ዳዊት ስግብግብነት ስላደረበት ይሖዋ ከሰጠው ተጨማሪ ነገር ፈለገ። ዳዊት ብዙ ሚስቶች የነበሩት ቢሆንም የሌላ ሰው ሚስት ተመኘ። ዳዊት የተመኘው የሂታዊው የኦርዮ ሚስት የሆነችውን ቤርሳቤህን ነው። ዳዊት በራስ ወዳድነት ስለተሸነፈ ከቤርሳቤህ ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ እሷም አረገዘች። ዳዊት ምንዝር መፈጸሙ ሳያንስ ኦርዮ እንዲገደል አደረገ። (2 ሳሙ. 11:2-15) ዳዊት እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ያደርጋል? ይሖዋ የማያየው መስሎት ነው? በአንድ ወቅት ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ የነበረው ዳዊት ለራስ ወዳድነትና ለስግብግብነት እጅ በመስጠቱ ብዙ መከራ ደርሶበታል። ደስ የሚለው ግን ዳዊት ከጊዜ በኋላ ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ገብቷል። የይሖዋን ሞገስ መልሶ በማግኘቱ ምንኛ ተደስቶ ይሆን!—2 ሳሙ. 12:7-13፤ w21.06 17 አን. 10

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12

ብቃታችንን በገዛ ራሳችን ያገኘነው እንደሆነ አድርገን አናስብም፤ ከዚህ ይልቅ አስፈላጊውን ብቃት ያገኘነው ከአምላክ ነው።—2 ቆሮ. 3:5

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ብቃቱ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ምናልባትም አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት በቂ እውቀትና ችሎታ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ጥናት መምራት እንደምትችል እንድትተማመን የሚረዱ ሦስት ነጥቦችን እስቲ እንመልከት። በመጀመሪያ፣ ይሖዋ ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱ እንዳለህ አድርጎ ይመለከትሃል። ሁለተኛ፣ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” የተሰጠው ኢየሱስ እንድታስተምር አዞሃል፤ ይህም እንደሚተማመንብህ ያሳያል። (ማቴ. 28:18) ሦስተኛ፣ ይሖዋ እና ወንድሞችህ ይረዱሃል። ይሖዋ ለኢየሱስ ምን መናገር እንዳለበት አስተምሮታል፤ አንተንም ሊያስተምርህ ይችላል። (ዮሐ. 8:28፤ 12:49) ከዚህም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ለመምራት እንዲረዳህ የመስክ አገልግሎት ቡድንህን የበላይ ተመልካች፣ ጥሩ ችሎታ ያለውን አንድ አቅኚ ወይም ተሞክሮ ያለውን አስፋፊ መጠየቅ ትችላለህ። ጥሩ አስተማሪ ለመሆን የሚረዳህ አንዱ ነገር እነዚህ አስፋፊዎች ጥናት ሲመሩ አብረሃቸው መገኘት ነው። w21.07 6 አን. 12

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 13

በትንሽ ነገር ታማኝ የሆነ ሰው በብዙ ነገርም ታማኝ ነው፤ በትንሽ ነገር ታማኝ ያልሆነ ሰው ደግሞ በብዙ ነገርም ታማኝ አይሆንም።—ሉቃስ 16:10

ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረብን ስንሄድ በይሖዋ አሠራር ላይ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ መተማመን ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም በታላቁ መከራ ወቅት የሚሰጡን መመሪያዎች በእኛ አመለካከት እንግዳ የሆኑ፣ ግራ የሚያጋቡ ወይም ምክንያታዊ የማይመስሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያ ጊዜ ይሖዋ በግል ያነጋግረናል ብለን እንደማንጠብቅ የታወቀ ነው። መመሪያ እንደሚሰጠን የምንጠብቀው በሾማቸው ተወካዮቹ አማካኝነት ነው። ያ ወቅት፣ ስለተሰጠን መመሪያ ጥያቄ የምናነሳበት ወይም መመሪያውን በጥርጣሬ ዓይን የምናይበት ጊዜ አይደለም፤ ‘ይህ መመሪያ በእርግጥ ከይሖዋ የመጣ ነው? ወይስ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በራሳቸው ያደረጉት ውሳኔ ነው?’ ብለን የምናስብበት ጊዜ አይደለም። ታዲያ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ በሆነው በዚያ ጊዜ ምን ታደርጉ ይሆን? በአሁኑ ወቅት ለቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች የምትሰጡት ምላሽ ያኔ የሚኖራችሁን አመለካከት ይጠቁማችኋል። በዛሬው ጊዜ በሚሰጠን መመሪያ የምንተማመንና ወዲያውኑ የምንታዘዝ ከሆነ በታላቁ መከራ ወቅትም ተመሳሳይ ነገር ማድረጋችን አይቀርም። w22.02 6 አን. 15

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14

እናንተ ካደረጋችሁት ጋር ሲነጻጸር እኔ ምን አደረግኩ?—መሳ. 8:2

ጌድዮን እና ከእሱ ጋር የነበሩት 300 ሰዎች በይሖዋ እርዳታ ታላቅ ድል አግኝተው ነበር፤ በዚህም ሊኮሩ ይችሉ ነበር። የኤፍሬም ሰዎች ግን ጌድዮንን ከማመስገን ይልቅ በውጊያው ላይ እንዲካፈሉ ስላልጠራቸው ሊጣሉት መጡ። (መሳ. 8:1) ጌድዮን አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወነውን ታላቅ ሥራ የሚያሳይ ምሳሌ ጠቀሰላቸው። በዚህ ጊዜ “ቁጣቸው በረደ።” (መሳ. 8:3) ጌድዮን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሰላም ለማስፈን ሲል ትሕትና ለማሳየት ፈቃደኛ ነበር። ከኤፍሬማውያን እንደምንማረው ይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባው የይሖዋ እንጂ የራሳችን ክብር አይደለም። የቤተሰብ ራሶችና ሽማግሌዎች ከጌድዮን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። አንድ ሰው ባደረግነው ነገር ከተበሳጨብን ጉዳዩን ከእሱ አመለካከት አንጻር ለማየት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በተጨማሪም ግለሰቡ ያከናወናቸውን መልካም ነገሮች ጠቅሰን ልናመሰግነው እንችላለን። እርግጥ ይህን ማድረግ ትሕትና ይጠይቅብናል። ሆኖም ከእኛ ክብር ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ከወንድሞቻችን ጋር ያለን ሰላም ነው። w21.07 16-17 አን. 10-12

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 15

ሰውን በመልካችን . . . እንሥራ።—ዘፍ. 1:26

ይሖዋ በራሱ መልክ በመሥራት አክብሮናል። የተፈጠርነው በአምላክ መልክ ስለሆነ የእሱን ግሩም ባሕርያት ማዳበርና ማንጸባረቅ እንችላለን፤ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ፍቅር፣ ርኅራኄ፣ ታማኝነትና ጽድቅ ይገኙበታል። (መዝ. 86:15፤ 145:17) እንዲህ ያሉትን ባሕርያት ስናዳብር ይሖዋን እናከብረዋለን፤ እንዲሁም ለእሱ ያለንን አመስጋኝነት እናሳያለን። (1 ጴጥ. 1:14-16) የሰማዩን አባታችንን በሚያስደስት መንገድ ስንኖር ደስታና እርካታ እናገኛለን። ከዚህም ሌላ ይሖዋ በመልኩ ስለሠራን ከቤተሰቡ አባላት የሚጠብቃቸውን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንችላለን። ይሖዋ ልዩ መኖሪያ አዘጋጅቶልናል። ይሖዋ የመጀመሪያውን ሰው ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት ምድርን ለሰው ልጆች ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን አድርጎ አዘጋጅቷታል። (ኢዮብ 38:4-6፤ ኤር. 10:12) ይሖዋ አሳቢና ለጋስ ስለሆነ የሚያስደስቱንን መልካም ነገሮች አትረፍርፎ ሰጥቶናል። (መዝ. 104:14, 15, 24) የፈጠራቸውን ነገሮች መለስ ብሎ ሲመለከት ሥራው “መልካም እንደሆነ” አይቷል።—ዘፍ. 1:10, 12, 31፤ w21.08 3 አን. 5-6

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 16

የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው።—ገላ. 5:22, 23

ሁላችንም የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሮም 10:14) በዚህ በጣም አስፈላጊ ሥራ ረገድ ክህሎትህን ማዳበር ትፈልጋለህ? ማስተማር የተባለውን ብሮሹር አጥና፤ እንዲሁም ያገኘኸውን ትምህርት በሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ ግቦች አውጣ። ልታወጣ ከምትችላቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ግቦች መካከል አንዱ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር ነው። (ቆላ. 3:12፤ 2 ጴጥ. 1:5-8) ሁላችንም በይሖዋ አገልግሎት አሁን ከምናከናውነው ይበልጥ ማከናወን ብንችል ደስ እንደሚለን የታወቀ ነው። አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ማገልገል እንችላለን። እስከዚያው ድረስ ግን በተከፈቱልን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም ደስታችንን መጨመር እንዲሁም የምንፈልገውን መብት አለማግኘት የሚያስከትለውን ሐዘን መቀነስ እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘ለደስተኛው አምላካችን’ ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ እናመጣለን። (1 ጢሞ. 1:11) እንግዲያው አሁን ባሉን መብቶች እንደሰት! w21.08 25 አን. 18-20

እሁድ፣ ታኅሣሥ 17

ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩን . . . ማመን ይኖርበታል።—ዕብ. 11:6

ያደግከው እውነት ውስጥ ከሆነ ስለ ይሖዋ ከልጅነትህ ጀምሮ ተምረህ መሆን አለበት። ይሖዋ ፈጣሪ እንደሆነ፣ ግሩም ባሕርያት እንዳሉት እንዲሁም ምድርን ገነት የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተምረሃል። (ዘፍ. 1:1፤ ሥራ 17:24-27) ይሁንና ብዙ ሰዎች አምላክ ፈጣሪ መሆኑን ይቅርና መኖሩን እንኳ አያምኑም። ከዚህ ይልቅ ሕይወት በአጋጣሚ እንደጀመረና ውስብስብ የሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት ቀስ በቀስ እንደተገኙ ያምናሉ። እንዲህ ብለው ከሚያምኑት ሰዎች አንዳንዶቹ ምሁራን ናቸው። እነዚህ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስህተት መሆኑን ሳይንስ እንዳረጋገጠ እንዲሁም በፈጣሪ የሚያምኑት ሞኞችና ያልተማሩ ሰዎች እንደሆኑ ይናገሩ ይሆናል። በይሖዋ ቤት ምንም ያህል ረጅም ጊዜ ብንቆይ ሁላችንም እምነታችንን ለማጠናከር ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን የአምላክን ቃል የሚቃወሙ ሰዎች በሚያስተምሩት “ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ” አንወሰድም።—ቆላ. 2:8፤ w21.08 14 አን. 1-3

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 18

ይሖዋ አምላካችን . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።—ራእይ 4:11

አቤል፣ ኖኅ፣ አብርሃምና ኢዮብ ታዛዥ በመሆን፣ እምነት በማሳየት እንዲሁም መሥዋዕቶችን በማቅረብ ለይሖዋ ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር አሳይተዋል። በግልጽ ማየት እንደምንችለው እነዚህ ሰዎች ለይሖዋ ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል፤ ደግሞም አምልኳቸው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች የሙሴን ሕግ ሰጣቸው። እነዚህ ሕግጋት ይሖዋን እሱ በሚፈልገው መንገድ ማምለክ የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚገልጹ መመሪያዎችን ይዘዋል። ኢየሱስ ከሞተና ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ይሖዋ አገልጋዮቹ የሙሴን ሕግ እንዲታዘዙ መጠበቁን አቆመ። (ሮም 10:4) ክርስቲያኖች አዲስ ሕግ ማለትም “የክርስቶስን ሕግ” መከተል ነበረባቸው። (ገላ. 6:2) ይህን “ሕግ” የሚታዘዙት አድርግ አታድርግ የሚሉ በርካታ ሕጎችን በመታዘዝ ሳይሆን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተልና ትምህርቶቹን ተግባራዊ በማድረግ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ክርስቶስን በመከተል ይሖዋን ለማስደሰት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ይህም ለራሳቸው “እረፍት” ያስገኝላቸዋል።—ማቴ. 11:29፤ w22.03 21 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 19

ብዙ ጊዜ ጭር ወዳሉ ስፍራዎች በመሄድ ይጸልይ ነበር።—ሉቃስ 5:16

ይሖዋ ልጆቹ ሲያነጋግሩት ይሰማቸዋል። ልጁ ምድር ላይ ሳለ ያቀረባቸውን በርካታ ጸሎቶች ሰምቷል። ኢየሱስ ከባድ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ለምሳሌ 12ቱን ሐዋርያቱን ሲመርጥ ያቀረበውን ጸሎት ሰምቶታል። (ሉቃስ 6:12, 13) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ኢየሱስ በጭንቀት በተዋጠበት ጊዜ ያቀረበውን ጸሎት ሰምቶታል። ኢየሱስ ልክ አልፎ ከመሰጠቱ በፊት፣ ከፊቱ የሚጠብቀውን ከባድ ፈተና በተመለከተ ወደ አባቱ አጥብቆ ጸልዮ ነበር። ይሖዋ የኢየሱስን ጸሎት ከመስማት ባለፈ ውድ ልጁን ለማበረታታት መልአክ ልኮለታል። (ሉቃስ 22:41-44) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል፤ እንዲሁም በትክክለኛው ጊዜና ከሁሉ በተሻለው መንገድ መልስ ይሰጣቸዋል። (መዝ. 116:1, 2) በሕንድ የምትኖር አንዲት እህት በሕይወቷ ውስጥ ይህን ያየችው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ይህች እህት በከባድ ጭንቀት ትዋጥ ነበር፤ እንዲሁም ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ አጥብቃ ጸልያ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ጭንቀትን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ የሚናገረው የግንቦት 2019 JW ብሮድካስቲንግ ልክ የሚያስፈልገኝን እርዳታ ሰጥቶኛል። ይህ ቪዲዮ የጸሎቴ መልስ ነበር።” w21.09 21-22 አን. 6-7

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 20

ወደ ተራሮች [ሽሹ]።—ሉቃስ 21:21

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እነዚያ ክርስቲያኖች ያላቸውን ነገር ሁሉ ጥለው መጥተው እንደ አዲስ ኑሮን መጀመር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው መገመት ትችላለህ? ይሖዋ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው መተማመን ነበረባቸው። ሆኖም ይህን ለማድረግ ሊረዳቸው የሚችል ነገር ነበር። ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ከመክበባቸው ከአምስት ዓመታት በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚከተለውን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷቸው ነበር፦ “አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ ባሏችሁ ነገሮች ረክታችሁ ኑሩ። እሱ ‘ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏልና። ስለዚህ በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’ እንላለን።” (ዕብ. 13:5, 6) ከሮማውያን ወረራ በፊት የጳውሎስን ምክር ተግባራዊ አድርገው የነበሩ ክርስቲያኖች በአዲሱ አካባቢ ቀለል ያለ ኑሮ መልመድ ከባድ እንደማይሆንባቸው የታወቀ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ይሖዋ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸው እርግጠኞች ነበሩ። w22.01 4 አን. 7, 9

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 21

[የይሖዋ ምሕረት] በሥራው ሁሉ ላይ ይታያል።—መዝ. 145:9

መሐሪ ሰው ሲባል ወደ አእምሯችን የሚመጣው ደግ፣ አሳቢ፣ ሩኅሩኅና ለጋስ የሆነ ሰው ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረውን ምሳሌ እናስታውስ ይሆናል። ከሌላ አገር የመጣው ይህ ሰው በዘራፊዎች እጅ ለወደቀው አይሁዳዊ “ምሕረት በማሳየት” ረድቶታል። ሳምራዊው ለቆሰለው አይሁዳዊ ‘በጣም ስላዘነለት’ ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ረድቶታል። (ሉቃስ 10:29-37) ይህ ምሳሌ የአምላካችን ግሩም ባሕርይ ስለሆነው ስለ ምሕረት ያስተምረናል። ምሕረት የአምላክ ፍቅር አንዱ መገለጫ ነው፤ ይሖዋ በየዕለቱ በተለያዩ መንገዶች ምሕረት ያሳየናል። ምሕረት የሚገለጽበት ሌላም መንገድ አለ። ምሕረት፣ ቅጣት የሚገባው ሰው ይቅርታ እንዲደረግለት የሚያስችል በቂ ምክንያት እስካለ ድረስ ቅጣቱ እንዲቀርለት ማድረግንም ያመለክታል። ይሖዋ በዚህ መንገድ ምሕረት እንዳሳየን በሕይወታችን በግልጽ ተመልክተናል። መዝሙራዊው “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም” ብሏል። (መዝ. 103:10) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ኃጢአት ለሠራ ግለሰብ ጠንከር ያለ ተግሣጽ የሚሰጥበት ጊዜ አለ። w21.10 8 አን. 1-2

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 22

ታማኝ ፍቅሬ ከአንቺ አይለይም።—ኢሳ. 54:10

ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳየው ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና ላላቸው ሰዎች ማለትም ለአገልጋዮቹ ብቻ ነው። ንጉሥ ዳዊትና ነቢዩ ዳንኤል የተናገሩት ሐሳብ ይህን ያሳያል። ለምሳሌ ዳዊት “ለሚያውቁህ ታማኝ ፍቅርህን . . . ዘወትር አሳያቸው” ብሏል። በተጨማሪም “ይሖዋ . . . እሱን ለሚፈሩት ታማኝ ፍቅሩን ከዘላለም እስከ ዘላለም ያሳያል” ብሏል። ዳንኤልም ቢሆን እንዲህ ብሏል፦ “እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ለሚወዱህ፣ ትእዛዛትህንም ለሚያከብሩ . . . ታማኝ ፍቅር የምታሳይ . . . አምላክ ነህ።” (መዝ. 36:10፤ 103:17፤ ዳን. 9:4) እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ስለሚያውቁት፣ ስለሚፈሩት፣ ስለሚወዱት እና ትእዛዛቱን ስለሚያከብሩ ነው። ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን የሚያሳየው ለሕዝቦቹ ማለትም ለእውነተኛ አገልጋዮቹ ብቻ ነው። ይሖዋን ማገልገል ከመጀመራችን በፊት አምላክ ለሁሉም ሰዎች ከሚያሳየው ፍቅር ተጠቅመናል። (መዝ. 104:14) እሱን ማምለክ ከጀመርን በኋላ ደግሞ ታማኝ ፍቅሩንም አሳይቶናል። w21.11 4 አን. 8-9

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 23

ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ።—ማቴ. 4:10

ምንም ይምጣ ምን፣ ኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተናገረውን ሐሳብ ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። በዘመናችን በርካታ ሰዎች ታዋቂ የሃይማኖት መሪዎችን ይከተላሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለእነዚህ ሰዎች ያላቸው አድናቆት ከአምልኮ አይተናነስም። ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ይጎርፋሉ፣ መጽሐፎቻቸውን ይገዛሉ እንዲሁም እነሱን ለመደገፍ ብዙ ገንዘብ ይሰጣሉ። አንዳንድ ሰዎች ከእነሱ አንደበት የሚወጣውን ማንኛውም ቃል ያለአንዳች ጥርጣሬ ይቀበላሉ። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ራሱ ፊታቸው ቢቆም እንኳ ይህን ያህል መደሰታቸው ያጠራጥራል! ከዚህ በተቃራኒ እውነተኛዎቹ የይሖዋ አምላኪዎች የቀሳውስት ሥርዓት የላቸውም። አመራር የሚሰጡንን ሰዎች የምናከብር ቢሆንም ኢየሱስ “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” በማለት ያስተማረውን ግልጽ ትምህርት እንቀበላለን። (ማቴ. 23:8-10) ለሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ለፖለቲካ ገዢዎች ከልክ ያለፈ ክብር አንሰጥም። በተጨማሪም እነዚህ ሰዎች የሚያራምዱትን ሃይማኖታዊ ወይም ፖለቲካዊ አቋም አንደግፍም። ከዚህ ይልቅ የገለልተኝነት አቋማችንን በመጠበቅ ከዓለም የተለየን ለመሆን ጥረት እናደርጋለን። ይህ አቋማችን ክርስቲያን ነን ከሚሉ በርካታ ሃይማኖቶች የተለየን ያደርገናል።—ዮሐ. 18:36፤ w21.10 20 አን. 6-7

እሁድ፣ ታኅሣሥ 24

እኔ አምላክህ ይሖዋ ነኝ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ።—ዘፀ. 20:2, 3

ቅዱስ መሆን የሚፈልግ ክርስቲያን ሁሉ፣ ማንም ወይም ምንም ነገር ከአምላኩ ጋር ካለው ዝምድና እንዳይበልጥበት መጠንቀቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራ እንደመሆናችን መጠን ቅዱስ ስሙን የሚያስነቅፍ ወይም የሚያሰድብ ማንኛውንም ነገር ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። (ዘሌ. 19:12፤ ኢሳ. 57:15) እስራኤላውያን ይሖዋን እንደ አምላካቸው አድርገው እንደሚቀበሉት የሚያሳዩት የሰጣቸውን በርካታ ሕጎች በማክበር ነበር። ዘሌዋውያን 18:4 እንዲህ ይላል፦ “ድንጋጌዎቼን ተግባር ላይ አውሉ፤ ደንቦቼንም በመጠበቅ በእነሱ ሂዱ። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።” በምዕራፍ 19 ውስጥ ለእስራኤላውያን የተሰጡት አንዳንድ ‘ደንቦች’ ይገኛሉ። ለምሳሌ ከቁጥር 5-8 እንዲሁም ቁጥር 21, 22 ስለ እንስሳት መሥዋዕቶች ይናገራሉ። እነዚህ መሥዋዕቶች ‘የይሖዋን ቅዱስ ነገር በማያረክስ’ መንገድ መቅረብ ነበረባቸው። እነዚህን ጥቅሶች ማንበባችን ይሖዋን ለማስደሰትና ዕብራውያን 13:15 እንደሚናገረው ለእሱ ተቀባይነት ያለው የውዳሴ መሥዋዕት ለማቅረብ ሊያነሳሳን ይገባል። w21.12 5-6 አን. 14-15

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 25

ከወጣትነት [ሚስትህ] ጋር ደስ ይበልህ።—ምሳሌ 5:18

በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት ባለትዳሮች፣ በይሖዋ እንደሚተማመኑ ካሳዩ ክርስቲያኖች ተሞክሮ ብዙ መማር ይችላሉ። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያገለገሉ አንዳንድ ባለትዳሮች አሉ። ግባችሁን መገምገም እንዳለባችሁ የሚሰማችሁ ከሆነ ለምን ምክር አትጠይቋቸውም? በይሖዋ እንደምትታመኑ የምታሳዩበት አንዱ መንገድ ይህ ነው። (ምሳሌ 22:17, 19) ትዳር የይሖዋ ስጦታ እንደሆነ አስታውሱ። (ማቴ. 19:5, 6) ይሖዋ ባለትዳሮች በዚህ ስጦታ እንዲደሰቱ ይፈልጋል። ወጣት ባለትዳሮች፣ ሕይወታችሁን ስለምትመሩበት መንገድ ለምን ቆም ብላችሁ አታስቡም? ይሖዋ ለሰጣችሁ ስጦታዎች ሁሉ ያላችሁን አድናቆት ለማሳየት አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ እያደረጋችሁ ነው? ይሖዋን በጸሎት አነጋግሩት። በተጨማሪም ካላችሁበት ሁኔታ ጋር የሚስማሙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት ቃሉን መርምሩ። ከዚያም ይሖዋ የሚሰጣችሁን ምክር በሥራ ላይ አውሉ። ሕይወታችሁ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ካደረጋችሁ አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንደምትመሩ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ! w21.11 18-19 አን. 16, 18

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 26

ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን።—ያዕ. 3:2 ግርጌ

ያዕቆብ ለራሱ ተገቢው አመለካከት ነበረው። ያዕቆብ ያደገበት ቤተሰብ ወይም ያገኛቸው መብቶች ከሌሎች ልዩ እንደሚያደርጉት ወይም ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ እና እህቶቹ እንደሚያስበልጡት አልተሰማውም። የእምነት ባልንጀሮቹን “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ” ሲል ጠርቷቸዋል። (ያዕ. 1:16, 19፤ 2:5) በሌሎች ዘንድ እንከን የሌለበት መስሎ ለመታየት አልሞከረም። የምናገኘው ትምህርት፦ ሁላችንም ኃጢአተኞች እንደሆንን አስታውሱ። ከምናስተምራቸው ሰዎች የተሻልን እንደሆንን አድርገን ማሰብ የለብንም። ለምን? ጥናታችን ጨርሶ እንደማንሳሳት እንዲሰማው ካደረግን መቼም ቢሆን የአምላክን መሥፈርቶች ማሟላት እንደማይችል ሊሰማው ይችላል። ከዚህ ይልቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መከተል እንቸገር የነበረበት ጊዜ እንደነበረና ይሖዋ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንድንወጣ እንዴት እንደረዳን ልንነግረው እንችላለን። ይህም እሱም የይሖዋ አገልጋይ መሆን እንደሚችል እንዲሰማው ያደርጋል። w22.01 11-12 አን. 13-14

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 27

ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር።—ፊልጵ. 2:5

አስተሳሰባችን እንደ ኢየሱስ እየሆነ ሲሄድ በድርጊታችንም ይበልጥ እየመሰልነው እንሄዳለን፤ እንዲሁም የእሱን ዓይነት ስብዕና እያዳበርን እንሄዳለን። (ዕብ. 1:3) ‘ኢየሱስ እኮ ፍጹም ነው። መቼም ቢሆን እሱን ሙሉ በሙሉ መምሰል አልችልም!’ ብለን እናስብ ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የሚከተሉትን ነጥቦች አስታውስ። አንደኛ፣ የተፈጠርከው በይሖዋና በኢየሱስ አምሳል ነው፤ በመሆኑም ምርጫህ እስከሆነ ድረስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እነሱን መምሰል ትችላለህ። (ዘፍ. 1:26) ሁለተኛ፣ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል ነው። በዚህ መንፈስ እርዳታ፣ በራስህ ቢሆን ኖሮ ጨርሶ ማከናወን የማትችላቸውን ነገሮች ማድረግ ትችላለህ። ሦስተኛ፣ ይሖዋ በአሁኑ ወቅት የመንፈስ ፍሬ ውጤት የሆኑትን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ እንድታንጸባርቅ አይጠብቅብህም። እንዲያውም አፍቃሪው አባታችን ምድራዊ ተስፋ ላላቸው ሰዎች ፍጽምና ላይ ለመድረስ 1,000 ዓመት ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 20:1-3) ይሖዋ በአሁኑ ወቅት ከእኛ የሚጠብቀው፣ የምንችለውን ሁሉ እንድንጥርና እሱ በሚሰጠን እርዳታ እንድንተማመን ነው። w22.03 9 አን. 5-6

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 28

ይሖዋ ሆይ፣ ገና ቃል ከአፌ ሳይወጣ፣ እነሆ፣ አንተ ሁሉን ነገር አስቀድመህ በሚገባ ታውቃለህ።—መዝ. 139:4

ጸሎት ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር የምንችልበት አንዱ አቅጣጫ ብቻ ነው። የአምላክን ቃል ማጥናታችን እና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችንም ወደ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። በጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የምታሳልፈውን ጊዜ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ማድረግ የምትችለው ነገር አለ? እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ስብሰባ ላይ ስሆን ወይም በማጠናበት ወቅት ብዙውን ጊዜ ትኩረቴን የሚከፋፍለው ምንድን ነው?’ ምናልባት ትኩረታችንን የሚከፋፍለው የስልክ ጥሪዎችን መቀበል አሊያም በስልካችን ወይም በሌላ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ለሚላኩልን ኢሜይሎችና ሌሎች የጽሑፍ መልእክቶች መልስ መስጠት ይሆን? በምታጠናበት ወቅት ወይም ስብሰባ ላይ ሆነህ ሐሳብህ የሚዋልል ከሆነ ይሖዋ ትኩረትህን ለመሰብሰብ እንዲረዳህ ጠይቀው። የሚያስጨንቅ ነገር አጋጥሞህ ከሆነ ጭንቀትህን ትተህ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ቀላል ላይሆንልህ ይችላል፤ እንዲህ ማድረግህ ግን አስፈላጊ ነው። ልብህን ብቻ ሳይሆን ‘አእምሮህንም’ የሚጠብቅልህ ሰላም ለማግኘት ጸልይ።—ፊልጵ. 4:6, 7፤ w22.01 29-30 አን. 12-14

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 29

ጆሮህን አዘንብል፤ የጥበበኞችንም ቃል አዳምጥ።—ምሳሌ 22:17

ንጉሥ ዖዝያ ምክር አልሰማም። ለካህናቱ ብቻ ወደተፈቀደው የቤተ መቅደሱ ክፍል ገባ፤ በዚያም ዕጣን ለማጠን ሞከረ። የይሖዋ ካህናትም “ዖዝያ ሆይ፣ አንተ ለይሖዋ ዕጣን ማጠንህ ተገቢ አይደለም! ዕጣን ማጠን ያለባቸው ካህናቱ ብቻ ናቸው” አሉት። ታዲያ ዖዝያ ምን አደረገ? የተሰጠውን ምክር በትሕትና ተቀብሎ ወዲያውኑ ከቤተ መቅደሱ ቢወጣ ኖሮ ይሖዋ ይቅር ሊለው ይችል ነበር። “ዖዝያ ግን እጅግ ተቆጣ።” ዖዝያ ምክሩን ያልሰማው ለምንድን ነው? ንጉሥ ስለሆነ የፈለገውን ነገር የማድረግ መብት እንዳለው ተሰምቶት ሳይሆን አይቀርም። ይሖዋ ግን ጉዳዩን እንደዚህ አላየውም። ዖዝያ በእብሪተኝነቱ የተነሳ በሥጋ ደዌ ተመታ፤ “እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ።” (2 ዜና 26:16-21) ከዖዝያ ታሪክ እንደምንማረው ማንም እንሁን ማን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር የማንቀበል ከሆነ የይሖዋን ሞገስ እናጣለን። w22.02 9 አን. 7

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 30

ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል።—ሥራ 3:19

‘አሮጌው ስብዕና’ ያለው ሰው በጥቅሉ ሲታይ አስተሳሰቡና ድርጊቱ ሥጋዊ ነው። (ቆላ. 3:9) ራስ ወዳድ፣ ግልፍተኛ፣ ምስጋና ቢስና ኩሩ ሊሆን ይችላል። ፖርኖግራፊ እንዲሁም የብልግና እና የዓመፅ ፊልሞች ማየት ያስደስተዋል። ይህ ሰው አንዳንድ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት የታወቀ ነው፤ በተናገረው ወይም ባደረገው መጥፎ ነገር የሚጸጸትበት ጊዜም ይኖራል። ያም ሆኖ የአስተሳሰብና የምግባር ለውጥ ለማድረግ ተነሳሽነቱ የለውም። (ገላ. 5:19-21፤ 2 ጢሞ. 3:2-5) ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ማናችንም ብንሆን መጥፎ ሐሳቦችንና ምኞቶችን ከልባችንና ከአእምሯችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አንችልም። በኋላ ላይ የሚጸጽተንን ነገር የምናደርግበት ወይም የምንናገርበት ጊዜ አለ። (ኤር. 17:9፤ ያዕ. 3:2) ያም ቢሆን አሮጌውን ስብዕና ገፈን መጣላችን ሥጋዊ አስተሳሰቦችና ልማዶች በእኛ ላይ ኃይል እንዳይኖራቸው ያደርጋል። ከዚያ በኋላ ስብዕናችን ይቀየራል።—ኢሳ. 55:7፤ w22.03 3 አን. 4-5

እሁድ፣ ታኅሣሥ 31

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3

ሽማግሌዎች፣ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ያሏቸውን መልካም ባሕርያት ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ፍጹም እንዳልሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም እያንዳንዳቸው የሚደነቅ ባሕርይ አላቸው። እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ለአንድ ወንድም ወይም ለአንዲት እህት እርማት መስጠት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሊኖር ይችላል። ሆኖም ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ግለሰቡ በሚናገራቸውና በሚያደርጋቸው የሚያበሳጩ ነገሮች ላይ ላለማተኮር ጥረት ማድረግ አለባቸው። ከዚህ ይልቅ ወንድም ለይሖዋ ባለው ፍቅር፣ አምላክን ለማገልገል ሲል እያሳየ ባለው ጽናት እንዲሁም መልካም ለማድረግ ባለው አቅም ላይ ማተኮራቸው የተሻለ ነው። አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ፍቅር እንዲሰፍን ያደርጋሉ። ይሖዋ ከእናንተ የሚጠብቀው ፍጽምናን ሳይሆን ታማኝነትን እንደሆነ አስታውሱ። (1 ቆሮ. 4:2) አምላክ በእሱ አገልግሎት የምታከናውኑትን ነገር እንደሚያደንቅም መተማመን ትችላላችሁ። ይሖዋ “ቅዱሳንን በማገልገልም ሆነ ወደፊትም ማገልገላችሁን በመቀጠል የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር” ፈጽሞ አይረሳም።—ዕብ. 6:10፤ w22.03 31 አን. 19, 21

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ