የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es23 ገጽ 108-118
  • ኅዳር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኅዳር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 1
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 2
  • ዓርብ፣ ኅዳር 3
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 4
  • እሁድ፣ ኅዳር 5
  • ሰኞ፣ ኅዳር 6
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 7
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 8
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 9
  • ዓርብ፣ ኅዳር 10
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 11
  • እሁድ፣ ኅዳር 12
  • ሰኞ፣ ኅዳር 13
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 14
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 15
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 16
  • ዓርብ፣ ኅዳር 17
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 18
  • እሁድ፣ ኅዳር 19
  • ሰኞ፣ ኅዳር 20
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 21
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 22
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 23
  • ዓርብ፣ ኅዳር 24
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 25
  • እሁድ፣ ኅዳር 26
  • ሰኞ፣ ኅዳር 27
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 28
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 29
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
es23 ገጽ 108-118

ኅዳር

ረቡዕ፣ ኅዳር 1

ሁሉም ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ።—ዮሐ. 6:45

ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ይረዳናል። ተቃዋሚ ሲያጋጥመን እንድንረጋጋ ይረዳናል። በተጨማሪም ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ልባቸውን የሚነካ ጥቅስ አስታውሰን እንድናነብላቸው ይረዳናል። ከዚህም ሌላ በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ግድየለሽ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሙን በሥራው ለመቀጠል የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል። (ኤር. 20:7-9) ይሖዋ ለአገልግሎት የሚያስፈልገንን ሥልጠና በመስጠትም ጥሩነቱን አሳይቶናል። በሳምንቱ መሃል ስብሰባችን ላይ የታሰበባቸው የውይይት ናሙናዎች እንሰማለን፤ በአገልግሎት ላይ እንድንጠቀምባቸውም እንበረታታለን። አዲስ ነገር መሞከር መጀመሪያ ላይ ሊያስፈራን ይችላል፤ ስንሞክረው ግን አዲሱ ዘዴ በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎችን እንደሚማርክ ልንገነዘብ እንችላለን። ከዚህም ሌላ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች እንድንካፈል በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ እንበረታታለን፤ ከእነዚህ የአገልግሎት ዘርፎች መካከል አንዳንዶቹን ከዚህ በፊት ሞክረናቸው አናውቅ ይሆናል። ይህም ቢሆን ያልለመድነውን ነገር መሞከር ይጠይቅብናል፤ እንዲህ ስናደርግ ግን ይሖዋ እንዲባርከን አጋጣሚ እንሰጠዋለን። w21.08 27 አን. 5-6

ሐሙስ፣ ኅዳር 2

ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።—ኤፌ. 5:16

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጠንካራ ምክር ሰጥቷል። ይህን ደብዳቤ ከጻፈ በኋላ ቲቶን ላከላቸው። ምክሩን በሥራ ላይ እንዳዋሉት ሲሰማ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! (2 ቆሮ. 7:6, 7) ሽማግሌዎች ከእምነት አጋሮቻቸው ጋር ጊዜ በማሳለፍ ጳውሎስ የተወውን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ከጉባኤ ስብሰባዎች በፊት ቀደም ብሎ ደርሶ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር የሚያንጽ ጭውውት ማድረግ ነው። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚያስፈልጋቸውን ፍቅራዊ ማበረታቻ ለመስጠት ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በቂ ሊሆኑ ይችላሉ። (ሮም 1:12) በተጨማሪም ሽማግሌዎች የአምላክን ቃል ተጠቅመው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በማነጽና ይሖዋ እንደሚወዳቸው ማረጋገጫ በመስጠት የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። አጋጣሚውን ፈልገው እነሱን ለማመስገን ጥረት ያደርጋሉ። ሽማግሌዎች ምክር መስጠት ካስፈለጋቸው ምክሩን የሚሰጡት በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርተው ነው። ወንድሞችና እህቶች ለምክራቸው የሚሰጡት ምላሽ ስለሚያሳስባቸው ምክሩን የሚሰጡት በግልጽ ሆኖም በደግነት ነው።—ገላ. 6:1፤ w22.03 28-29 አን. 11-12

ዓርብ፣ ኅዳር 3

ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል ከእኛ ሳይሆን ከአምላክ የመነጨ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን።—2 ቆሮ. 4:7

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ለመርዳት “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጣቸዋል። ብርታት የምናገኝበት አንዱ መንገድ ጸሎት ነው። በኤፌሶን 6:18 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ጳውሎስ “በማንኛውም ጊዜ” ወደ አምላክ እንድንጸልይ አበረታቶናል። እንዲህ ካደረግን አምላካችን ያበረታናል። አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሆኖ አእምሯችንን ስለሚቆጣጠረው ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ግራ ሊገባን ይችላል። ሆኖም ሐሳባችንን እና ስሜታችንን በቃላት ማስቀመጥ በሚከብደን ጊዜም እንኳ ይሖዋ ወደ እሱ እንድንጸልይ ጋብዞናል። (ሮም 8:26, 27) ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነትም ብርታት ይሰጠናል። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ከቅዱሳን መጻሕፍት ብርታትና መጽናኛ ማግኘት እንችላለን። (ሮም 15:4) የአምላክን ቃል ስናነብና ባነበብነው ነገር ላይ ስናሰላስል፣ ይሖዋ በመንፈሱ ተጠቅሞ ከቃሉ ያነበብነው ነገር ለእኛ ሁኔታ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል።—ዕብ. 4:12፤ w21.05 22 አን. 8-10

ቅዳሜ፣ ኅዳር 4

[አምላክ] ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ኃይል እንድታገኙ በማድረግ . . . ብርታት [ይሰጣችኋል]።—ፊልጵ. 2:13

ሰዎችን እንድናስተምር የተሰጠንን ተልእኮ በቁም ነገር እንመለከተዋለን፤ ሆኖም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የምንፈልገውን ያህል እንዳንካፈል የሚያግዱን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ያለንበት ሁኔታ እንደሚገድበን ይሰማን ይሆናል። ለምሳሌ አንዳንድ አስፋፊዎች ከዕድሜ መግፋት ወይም ከጤና ችግር ጋር ይታገላሉ። አንተም እንዲህ ዓይነት ችግር አጋጥሞሃል? ከሆነ በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት የሚቻል መሆኑን እንደተማርን አስታውስ! ስለዚህ ከቤትህ ሳትወጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርና መምራት ትችል ይሆናል። በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ጥናት መምራት ሌላ ጥቅምም አለው። አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቢፈልጉም አብዛኞቹ ወንድሞች አገልግሎት በሚወጡበት ሰዓት ማጥናት አይመቻቸው ይሆናል። ሆኖም ማለዳ ወይም ምሽት ላይ ማጥናት ይችሉ ይሆናል። ታዲያ በዚያ ሰዓት ጥናት መምራት ትችል ይሆን? ኢየሱስ ኒቆዲሞስን በሚመቸው ሰዓት ማለትም ማታ ላይ አስተምሮታል።—ዮሐ. 3:1, 2፤ w21.07 5 አን. 10-11

እሁድ፣ ኅዳር 5

ይህ ሕዝብ ወደ እኔ የሚቀርበው በአፉ ብቻ ነው፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው።—ኢሳ. 29:13

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አለመጾማቸው የመጥምቁ ዮሐንስን ደቀ መዛሙርት አስገርሟቸው ነበር። ኢየሱስም እሱ በሕይወት እስካለ ድረስ ደቀ መዛሙርቱ የሚጾሙበት ምክንያት እንደሌለ ገልጿል። (ማቴ. 9:14-17) ያም ቢሆን ፈሪሳውያንና ሌሎች ተቃዋሚዎቹ ኢየሱስ የእነሱን ልማዶችና ወጎች ባለመከተሉ አውግዘውታል። የታመሙ ሰዎችን በሰንበት በመፈወሱ በጣም ተቆጥተው ነበር። (ማር. 3:1-6፤ ዮሐ. 9:16) እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል ሰንበትን እንደሚያከብሩ በኩራት ይናገራሉ፤ በሌላ በኩል ግን ያለአንዳች እፍረት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ያካሂዳሉ። ይህን በማድረጋቸው ኢየሱስ ስላወገዛቸው በጣም ተቆጥተው ነበር። (ማቴ. 21:12, 13, 15) ኢየሱስ በናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ የሰበከላቸው ሰዎችም፣ ኢየሱስ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመጥቀስ ራስ ወዳድነታቸውንና እምነት የለሽነታቸውን ስላጋለጠባቸው በጣም ተበሳጭተው ነበር። (ሉቃስ 4:16, 25-30) በርካታ አይሁዳውያን ኢየሱስ የጠበቁትን ነገር ባለማድረጉ ተሰናክለውበታል።—ማቴ. 11:16-19፤ w21.05 5-6 አን. 13-14

ሰኞ፣ ኅዳር 6

እሱ የሚሸርበውን ተንኮል እናውቃለን።—2 ቆሮ. 2:11

ይሖዋ ከኩራት እና ከስግብግብነት እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል፤ እንዲህ ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ ከእውነተኛ ታሪኮች እንድንማር በመርዳት ነው። ስለ ስግብግብነት ስናስብ በመጀመሪያ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ሰይጣን ዲያብሎስ ሳይሆን አይቀርም። ሰይጣን የይሖዋ መልአክ የነበረ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ግሩም መብቶች እንደነበሩት ጥያቄ የለውም። እሱ ግን በዚህ አልረካም። ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ተመኘ። ሰይጣን እኛም እንደ እሱ እንድንሆን ስለሚፈልግ ባለን ነገር እንዳንረካ ለማድረግ ይሞክራል። እንዲህ ያለ ጥረት ማድረግ የጀመረው ሔዋንን ባነጋገረበት ወቅት ነው። አፍቃሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ለሔዋንና ለባለቤቷ የተትረፈረፈ ምግብ ሰጥቷቸው ነበር፤ ከአንዱ ዛፍ በቀር “በአትክልቱ ስፍራ ውስጥ ከሚገኘው ዛፍ ሁሉ” እስኪረኩ ድረስ መብላት ይችሉ ነበር። (ዘፍ. 2:16) ሆኖም ሰይጣን፣ ሔዋንን በማታለል ከተከለከለው ዛፍ መብላት እንደሚያስፈልጋት እንድታስብ አደረጋት። ሔዋን በተሰጣት ነገር አልረካችም፤ ተጨማሪ ነገር ፈለገች። ይህም ምን ውጤት እንዳስከተለ እናውቃለን። ሔዋን ኃጢአት ሠራች፤ ከጊዜ በኋላም ሞተች።—ዘፍ. 3:6, 19፤ w21.06 14-15 አን. 2-3፤ 17 አን. 9

ማክሰኞ፣ ኅዳር 7

ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም።—ዘፍ. 1:28

የአምላክ ዓላማ አዳምና ሔዋን ልጆች እንዲወልዱና ምድርን እንዲንከባከቡ ነበር። አዳምና ሔዋን ይሖዋን ቢታዘዙና የእሱን ዓላማ ቢፈጽሙ ኖሮ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ለዘላለም የአምላክ ቤተሰብ አባላት ሆነው መኖር ይችሉ ነበር። አዳምና ሔዋን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የተከበረ ቦታ ነበራቸው። ዳዊት በመዝሙር 8:5 ላይ ይሖዋ ሰውን ስለፈጠረበት መንገድ ሲናገር “ከመላእክት በጥቂቱ አሳነስከው፤ የክብርና የግርማ ዘውድም ደፋህለት” ብሏል። እርግጥ ነው፣ ሰዎች የመላእክትን ዓይነት ኃይል፣ የአእምሮ ብቃትም ሆነ ችሎታ አልተሰጣቸውም። (መዝ. 103:20) ያም ቢሆን ሰዎች ከእነዚህ ኃያል መንፈሳዊ ፍጥረታት የሚያንሱት “በጥቂቱ” ብቻ ነው። የሚያሳዝነው፣ አዳምና ሔዋን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ የነበራቸውን ቦታ አጡ። ይህ በዘሮቻቸው ላይም አስከፊ ውጤት አስከትሏል። ሆኖም የይሖዋ ዓላማ አልተለወጠም። ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ለዘላለም ልጆቹ እንዲሆኑ ይፈልጋል። w21.08 2-3 አን. 2-4

ረቡዕ፣ ኅዳር 8

“በመንፈሴ እንጂ፣ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም” ይላል . . . ይሖዋ።—ዘካ. 4:6

በዛሬው ጊዜ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶቹ የሚኖሩት ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ውስጥ ነው። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች፣ ወንድሞች ተይዘው “በገዢዎችና በነገሥታት ፊት” ሊቀርቡና ምሥክርነት ሊሰጡ ይችላሉ። (ማቴ. 10:17, 18) ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ሌላ ዓይነት ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። የሚኖሩት የአምልኮ ነፃነት ባለበት አገር ቢሆንም ቤተሰቦቻቸው ተቃውሞ ሊያደርሱባቸው ይችላሉ፤ እንዲህ ያለው ተቃውሞ ዓላማ አምላክን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ ነው። (ማቴ. 10:32-36) ብዙ ጊዜ እንደታየው ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክር ቤተሰቦቻቸውን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚያደርጉት ጥረት ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ሲገነዘቡ መቃወማቸውን ያቆማሉ። እንዲያውም ኃይለኛ ተቃዋሚ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በኋላ ላይ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆነዋል። ተቃውሞ ሲያጋጥማችሁ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ! ደፋሮች ሁኑ! የይሖዋና ኃያል የሆነው ቅዱስ መንፈሱ ድጋፍ ስለማይለያችሁ የምትፈሩበት ምንም ምክንያት የለም! w22.03 16 አን. 8

ሐሙስ፣ ኅዳር 9

እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ።—መዝ. 97:10

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ይሖዋ ‘ትዕቢተኛ ዓይን፣ ውሸታም ምላስና ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆችን’ ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) በተጨማሪም “ይሖዋ ዓመፀኞችንና አታላዮችን ይጸየፋል።” (መዝ. 5:6) ይሖዋ በኖኅ ዘመን የነበረውን በዓመፅ የተሞላ ዓለም እንዲያጠፋ ያነሳሳው ለእነዚህ ባሕርያትና ድርጊቶች ያለው ከፍተኛ ጥላቻ ነው። (ዘፍ. 6:13) በተጨማሪም ይሖዋ ምንም ያልበደሏቸውን ሚስቶቻቸውን በመፍታት ክህደት የሚፈጽሙ ሰዎችን እንደሚጠላ በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት ተናግሯል። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚያቀርቡትን አምልኮ አይቀበልም፤ ለድርጊታቸውም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። (ሚል. 2:13-16፤ ዕብ. 13:4) ይሖዋ “ክፉ የሆነውን [እንድንጸየፍ]” ይፈልጋል። (ሮም 12:9) ‘መጸየፍ’ የሚለው ቃል ጥልቅ ስሜትን የሚገልጽ ቃል ነው፤ አንድን ነገር አጥብቆ መጥላት፣ በዚያ ነገር መዘግነን ማለት ነው። ስለዚህ ይሖዋ ከሚጠላቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ሐሳቡ እንኳ ሊዘገንነን ይገባል። w22.03 4-5 አን. 11-12

ዓርብ፣ ኅዳር 10

እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።—ኢሳ. 30:18

በቅርቡ የሰማዩ አባታችን በመንግሥቱ አማካኝነት አትረፍርፎ ይባርከናል። ይሖዋን የሚጠባበቁ ሁሉ አሁንም ሆነ በመጪው አዲስ ዓለም የተትረፈረፉ በረከቶች ያገኛሉ። የአምላክ ሕዝቦች ወደ አዲሱ ዓለም ሲገቡ በዚህ ዓለም ውስጥ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮችና አስጨናቂ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ይገላገላሉ። የፍትሕ መጓደልም ሆነ ሥቃይ አይኖርም። (ራእይ 21:4) የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት አንጨነቅም፤ ምክንያቱም ሁሉ ነገር ይትረፈረፋል። (መዝ. 72:16፤ ኢሳ. 54:13) ያ ጊዜ ምንኛ አስደሳች ይሆን! ያ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ይሖዋ መጥፎ ልማዶቻችንን እንድናስወግድና እሱን የሚያስደስቱ ባሕርያትን እንድናዳብር በመርዳት በእሱ አገዛዝ ሥር ለሚኖረው ሕይወት እያዘጋጀን ነው። አይዟችሁ፤ ተስፋ አትቁረጡ! አስደሳች ሕይወት ይጠብቃችኋል! ብሩህ ተስፋ ስለተዘረጋልን ይሖዋ ሥራውን እስኪፈጽም ድረስ እሱን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኞች እንሁን! w21.08 13 አን. 17-19

ቅዳሜ፣ ኅዳር 11

መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታልና።—ዕብ. 13:16

በይሁዳ የነበሩ ክርስቲያኖች የሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤ ከደረሳቸው ብዙም ሳይቆይ ቤታቸውን፣ ንግዳቸውን እንዲሁም የማያምኑ ዘመዶቻቸውን ትተው ‘ወደ ተራሮች ለመሸሽ’ ተገድደዋል። (ማቴ. 24:16) በዚያ ወቅት እርስ በርስ መረዳዳት የሚጠይቅ ሁኔታ እንደተፈጠረ አይካድም። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ፣ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን እንዲያካፍሉ ጳውሎስ የሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ያደርጉ ከነበረ አዲሱን ሁኔታ መልመድ እንደማይከብዳቸው ግልጽ ነው። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ምን እንደሚያስፈልጋቸው ሁልጊዜ ላይነግሩን ይችላሉ። ስለዚህ የምንቀረብ እንሁን። በየጉባኤዎቻችን ሌሎችን ለመርዳት ሁልጊዜ ዝግጁ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች አሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች መቼም ቢሆን እያስቸገርናቸው እንደሆነ እንዲሰማን አያደርጉም። አንድ ችግር ሲያጋጥመን እንደሚደርሱልን እንተማመናለን። ደግሞም እኛም እንደ እነሱ ብንሆን ደስ ይለናል! w22.02 23-24 አን. 13-15

እሁድ፣ ኅዳር 12

አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት [ጠብቁ]።—ኤፌ. 4:3

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙ ጉባኤዎችና ወረዳዎች እንደ አዲስ ተዋቅረዋል። እኛም ጉባኤ እንድንቀይር ተጠይቀን ከሆነ ወዳጆቻችንን እና ቤተሰቦቻችንን ትተን መሄድ ይከብደን ይሆናል። ሽማግሌዎች እያንዳንዱን አስፋፊ የት መመደብ እንዳለባቸው መለኮታዊ መመሪያ ያገኛሉ? አያገኙም። ይህ መሆኑም መመሪያን መከተል ተፈታታኝ እንዲሆንብን ሊያደርግ ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ሽማግሌዎች እንዲህ ያለ ውሳኔ ሲያደርጉ ይተማመንባቸዋል፤ እኛም ልንተማመንባቸው ይገባል። ሽማግሌዎች የሚያደርጉት ውሳኔ እኛ የምንመርጠው ዓይነት ባይሆንም እንኳ ከእነሱ ጋር መተባበርና ውሳኔያቸውን መደገፍ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ስናደርግ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እናበረክታለን። ጉባኤዎች የሚጠነክሩት፣ ሁሉም አስፋፊዎች የሽማግሌዎች አካል ለሚያደርገው ውሳኔ በትሕትና ሲገዙ ነው። (ዕብ. 13:17) ከዚህም በላይ ደግሞ በይሖዋ እንደምንተማመን የምናሳየው፣ እሱ አምኗቸው እኛን እንዲንከባከቡ ከሾማቸው ሰዎች ጋር ስንተባበር ነው።—ሥራ 20:28፤ w22.02 4-5 አን. 9-10

ሰኞ፣ ኅዳር 13

ለሰዎች ለማንበብ፣ አጥብቀህ ለመምከርና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።—1 ጢሞ. 4:13

የተጠመቅህ ወንድም ከሆንክ የመናገር እና የማስተማር ችሎታህን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ትችል ይሆናል። ይህን ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? ምክንያቱም በማንበብ፣ በመናገርና በማስተማር ላይ ‘ትኩረትህን ሙሉ በሙሉ ማሳረፍህ’ አድማጮችህን ይጠቅማቸዋል። (1 ጢሞ. 4:15) ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ በሚለው ብሮሹር ላይ ያሉትን የንግግር ባሕርያት በሙሉ ለማጥናትና በእያንዳንዱ የንግግር ባሕርይ ላይ ለመሥራት ግብ ማውጣት ትችላለህ። አንዱን የንግግር ባሕርይ መርጠህ ካጠናህ በኋላ ቤት ውስጥ በትጋት ተለማመደው፤ ከዚያም ንግግር ስታቀርብ በዚያ የንግግር ባሕርይ ላይ ለመሥራት ጥረት አድርግ። ረዳት ምክር ሰጪውን ወይም “በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ” ሌሎች ሽማግሌዎችን ምክር ጠይቅ። (1 ጢሞ. 5:17) የንግግር ባሕርዩን በማዳበር ላይ ብቻ ሳይሆን አድማጮችህ እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ በመርዳት ወይም አንድን እርምጃ እንዲወስዱ በማበረታታት ላይ ትኩረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ የአንተም ሆነ የአድማጮችህ ደስታ ይጨምራል። w21.08 24 አን. 17

ማክሰኞ፣ ኅዳር 14

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3

ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ የምናስብ ከሆነ በተሰጥኦዋቸው ወይም በችሎታቸው ከሚበልጡን ሰዎች ጋር አንፎካከርም። ከዚህ ይልቅ አብረናቸው እንደሰታለን። በተለይ ደግሞ ችሎታቸውን የሚጠቀሙበት ይሖዋን ለማገልገልና ለማወደስ ከሆነ ልንደሰት ይገባል። በዚህ መንገድ ሁላችንም ለጉባኤው ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን። የምቀኝነትን ዝንባሌ ለማሸነፍ የሚረዳን ልክን ማወቅ ነው፤ ልካችንን የምናውቅ ከሆነ የማንችላቸው ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን። በመሆኑም ከሌሎች የበለጠ ብቃትና ችሎታ እንዳለን ለማሳየት አንሞክርም። ከዚህ ይልቅ ከእኛ የበለጠ ችሎታ ካላቸው ሰዎች ለመማር እንጥራለን። ለምሳሌ በጉባኤያችን ያለ አንድ ወንድም ግሩም የሕዝብ ንግግር ያቀርባል እንበል። ንግግሩን የሚዘጋጀው እንዴት እንደሆነ ልንጠይቀው እንችላለን። ጣት የሚያስቆረጥም ምግብ የምትሠራ እህትን ደግሞ ሙያዋን እንድታጋራን ልንጠይቃት እንችላለን። w21.07 16 አን. 8-9

ረቡዕ፣ ኅዳር 15

[ይሖዋ] ፈጽሞ ፍትሕን [አያጓድልም።]—ዘዳ. 32:4

በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ይሖዋ በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም የተገኘን አንድ እስራኤላዊ በሞት እንዲቀጣ እንዳዘዘ እናነባለን። የሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ደግሞ ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ የተከናወነውን ነገር ሲናገር ይሖዋ፣ ምንዝር የፈጸመውንና ነፍስ ያጠፋውን ንጉሥ ዳዊትን ይቅር እንዳለው ይገልጻል። (ዘኁ. 15:32, 35፤ 2 ሳሙ. 12:9, 13) በዚህ ጊዜ እንዲህ የሚል ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል፦ ‘ይሖዋ ነፍስ ያጠፋውንና ምንዝር የፈጸመውን ዳዊትን ይቅር ብሎ በአንጻሩ ቀላል የሚመስል ጥፋት የፈጸመውን ሰው እንዲገደል ያዘዘው ለምንድን ነው?’ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድ ታሪክ ሁሉንም ዝርዝር መረጃ የማይነግረን ጊዜ አለ። ለምሳሌ ዳዊት በፈጸመው ኃጢአት ከልቡ እንደተጸጸተ እናውቃለን። (መዝ. 51:2-4) ሆኖም የሰንበትን ሕግ የጣሰው ሰው ምን ዓይነት ሰው ነበር? በድርጊቱ ተጸጽቷል? ከዚያ በፊት የይሖዋን ሕግ ጥሶ ያውቅ ይሆን? አስቀድሞ የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች ችላ ብሎ ይባስ ብሎም አልቀበልም ብሎ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም “ይሖዋ በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ” እንደሆነ እንድንተማመን የሚያደርግ በቂ እውቀት አለን።—መዝ. 145:17፤ w22.02 2-3 አን. 3-4

ሐሙስ፣ ኅዳር 16

ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች።—ምሳሌ 11:2

ልኩን የሚያውቅ ሰው ከሚችለው በላይ ለማከናወን አይሞክርም። ይህም ደስታውን እንዳያጣና በትጋት መሥራቱን እንዲቀጥል ያስችለዋል። ልኩን የሚያውቅ ሰው ዳገት ላይ መኪና ከሚነዳ ሾፌር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሾፌሩ ዳገቱን ለመውጣት ማርሽ ቀይሮ ከባድ ማርሽ ማስገባት ያስፈልገዋል። ይህን ማድረጉ ፍጥነቱን እንደሚቀንስበት የታወቀ ነው፤ ሆኖም ወደፊት መሄዱን እንዲቀጥል ያስችለዋል። በተመሳሳይም ልኩን የሚያውቅ ሰው ይሖዋን ማገልገሉን እና ሌሎችን መርዳቱን መቀጠል እንዲችል ለውጥ ማድረግና ፍጥነቱን መቀነስ ያለበት መቼ እንደሆነ ያውቃል። (ፊልጵ. 4:5) የቤርዜሊን ምሳሌ እንመልከት፤ ንጉሥ ዳዊት በቤተ መንግሥቱ እንዲኖር ቤርዜሊን ሲጋብዘው ቤርዜሊ 80 ዓመቱ ነበር። ቤርዜሊ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለነበረ የንጉሡን ግብዣ አልተቀበለም። ቤርዜሊ የአቅም ገደብ እንዳለበት ስለተገነዘበ ወጣቱ ኪምሃም በእሱ ምትክ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲሄድ ሐሳብ አቀረበ። (2 ሳሙ. 19:35-37) በዛሬው ጊዜ ያሉ አረጋውያንም እንደ ቤርዜሊ፣ ወጣቶች በእነሱ ምትክ ሥራውን እንዲያከናውኑ አጋጣሚውን መስጠት ይፈልጋሉ። w21.09 10 አን. 6-7

ዓርብ፣ ኅዳር 17

ከአብ በስተቀር ወልድ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም፤ እንዲሁም ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በስተቀር አብ ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም።—ሉቃስ 10:22

ይሖዋን እንደ አፍቃሪ አባት መመልከት ይከብድሃል? አንዳንዶቻችን ይከብደናል። የአባት ፍቅር ሳናገኝ በማደጋችን የተነሳ አባትን አፍቃሪ አድርጎ ማሰብ ይከብደን ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ስሜታችንን ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልን ማወቃችን በጣም ያጽናናናል። ይሖዋ ወደ እኛ መቅረብ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት የሚያበረታታን ለዚህ ነው። (ያዕ. 4:8) ይሖዋ ይወደናል፤ እንዲሁም ከሁሉ የተሻለ አባት እንደሚሆንልን ቃል ገብቶልናል። ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ ሊረዳን ይችላል። ኢየሱስ ይሖዋን በደንብ ያውቀዋል፤ እንዲሁም ባሕርያቱን ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ያለው ለዚህ ነው። (ዮሐ. 14:9) ኢየሱስ አባታችንን ማክበርና መታዘዝ፣ እሱን ከማሳዘን መቆጠብ እንዲሁም የእሱን ሞገስ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ልክ እንደ ታላቅ ወንድም አስተምሮናል። ከሁሉ በላይ ግን ኢየሱስ፣ ይሖዋ ምን ያህል ደግና አፍቃሪ እንደሆነ በሕይወቱ አሳይቶናል። w21.09 21 አን. 4-5

ቅዳሜ፣ ኅዳር 18

በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆናችሁ ተንከባከቡ።—1 ጴጥ. 5:2

የይሖዋ ሕዝቦች እውነተኛውን አንድ አምላክ በአንድነት እያመለኩ ነው። ይሖዋ ለሽማግሌዎች የጉባኤውን ንጽሕና የመጠበቅ ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ ሽማግሌዎች ግለሰቡ የጉባኤው አስፋፊ ሆኖ መቀጠል ይችል እንደሆነ እና እንዳልሆነ እንዲወስኑ ይሖዋ ይጠብቅባቸዋል። ሽማግሌዎች አንዱ የሚያደርጉት ነገር፣ ግለሰቡ በፈጸመው ኃጢአት ከልቡ መጸጸቱን ማጣራት ነው። ግለሰቡ ‘ንስሐ ገብቻለሁ’ ይል ይሆናል፤ ሆኖም የፈጸመውን ኃጢአት ከልቡ ተጸይፎታል? የሠራውን ኃጢአት ላለመድገም ቆርጧል? ወደ ስህተት የመራው መጥፎ ጓደኝነት ከሆነ ግንኙነቱን ሙሉ በሙሉ ለማቆም ፈቃደኛ ነው? ሽማግሌዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመው ጉዳዩን በጸሎት ያስቡበታል፤ እንዲሁም ስህተት የፈጸመው ግለሰብ፣ ላደረገው ነገር ያለውን ዝንባሌ ይገመግማሉ። ከዚያም ግለሰቡ ጉባኤ ውስጥ ይቀጥል አይቀጥል የሚለውን ይወስናሉ። አንዳንድ ጊዜ እንዲወገድ ይወስኑ ይሆናል።—1 ቆሮ. 5:11-13፤ w22.02 5 አን. 11-12

እሁድ፣ ኅዳር 19

አዲሱን ስብዕና ልበሱ።—ቆላ. 3:10

የተጠመቅነው ከጥቂት ቀናት በፊትም ሆነ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት ሁላችንም ይሖዋ የሚወደው ዓይነት ስብዕና እንዲኖረን እንፈልጋለን። እንዲህ ዓይነት ስብዕና ለማዳበር አስተሳሰባችንን መቆጣጠር ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ስብዕናችንን በዋነኝነት የሚቀርጸው አስተሳሰባችን ነው። አዘውትረን የምናስበው ሥጋዊ ምኞታችንን ስለማርካት ከሆነ መጥፎ ነገር መናገራችን ወይም ማድረጋችን አይቀርም። (ኤፌ. 4:17-19) በሌላ በኩል ደግሞ አእምሯችን በጥሩ ሐሳቦች የተሞላ ከሆነ አነጋገራችንና ድርጊታችን አባታችንን ይሖዋን የሚያስደስት ይሆናል። (ገላ. 5:16) ይሁንና አንድም መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯችን እንዳይገባ ማድረግ አንችልም። ሐሳቡ ወደ ድርጊት እንዳይመራን መምረጥ ግን እንችላለን። ከመጠመቃችን በፊት ይሖዋ የሚጠላውን አነጋገርና ምግባር መተው ነበረብን። እንዲህ ማድረጋችን አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣል በጣም አስፈላጊ ነው። ይሖዋን በሚገባ ለማስደሰት ግን አዲሱን ስብዕና መልበስም ይኖርብናል። w22.03 8 አን. 1-2

ሰኞ፣ ኅዳር 20

በዚህ ጉዳይ ንጹሕ መሆናችሁን በሁሉም ረገድ አስመሥክራችኋል።—2 ቆሮ. 7:11

ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ ክርስቲያን እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ማወቅ ለሽማግሌዎች ቀላል አይደለም። ለምን? ሽማግሌዎች ልብ ማንበብ አይችሉም፤ ስለዚህ ወንድማቸው ለፈጸመው ኃጢአት ያለውን አመለካከት ሙሉ በሙሉ እንደቀየረ ለማወቅ የሚያስችል በግልጽ የሚታይ ማስረጃ ያስፈልጋቸዋል። ሽማግሌዎች የግለሰቡ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ድርጊት ሙሉ በሙሉ መቀየሩን የሚያሳይ ማስረጃ ያስፈልጋቸዋል። ግለሰቡ አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያደርግ ረዘም ያለ ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል። ከጉባኤ የተወገደ አንድ ግለሰብ እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ለማሳየት አዘውትሮ በስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዲሁም የሽማግሌዎችን ምክር በመከተል አዘውትሮ መጸለይ እና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ይኖርበታል። በተጨማሪም ወደ ኃጢአት ከመሩት ነገሮች ለመራቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት። ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ በርትቶ ከሠራ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደሚለው እንዲሁም ሽማግሌዎች ወደ ጉባኤው እንደሚመልሱት እርግጠኛ መሆን ይችላል። w21.10 6 አን. 16-18

ማክሰኞ፣ ኅዳር 21

በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር . . . ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ። አትስገድላቸው።—ዘፀ. 20:4, 5

ኢየሱስ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ስላለው በሰማይ ሳለም ሆነ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እሱን ብቻ አምልኳል። (ሉቃስ 4:8) ደቀ መዛሙርቱም ይሖዋን ብቻ እንዲያመልኩ አስተምሯል። ኢየሱስም ሆነ ታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ምስሎችን ለአምልኮ ተጠቅመው አያውቁም። አምላክ መንፈስ ስለሆነ የሰው ልጆች የሚሠሩት ማንኛውም ነገር የይሖዋን ክብር በጥቂቱም እንኳ ሊያንጸባርቅ አይችልም! (ኢሳ. 46:5) ይሁንና ቅዱሳን ተብለው የሚጠሩ አካላትን ምስል መሥራትንና ለእነሱ መጸለይን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ከአሥርቱ ትእዛዛት መካከል በሁለተኛው ላይ ይሖዋ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተናግሯል። አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ይህን ትእዛዝ መረዳት አይከብዳቸውም። የታሪክ ምሁራን የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አምላክን ብቻ ያመልኩ እንደነበር ይናገራሉ። በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተዉትን የአምልኮ ሥርዓት ይከተላሉ። w21.10 19-20 አን. 5-6

ረቡዕ፣ ኅዳር 22

በጣሪያ ላይ ያለ ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለመውሰድ አይውረድ።—ማቴ. 24:17

ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችን “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት [የምትከበብበት]” ጊዜ እንደሚመጣ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ሉቃስ 21:20-24) ይህ በሚሆንበት ጊዜ “ወደ ተራሮች [መሸሽ]” ነበረባቸው። ከተማዋን ለቅቀው መሸሻቸው ሕይወታቸውን ያተርፍላቸዋል፤ ያም ቢሆን መሥዋዕት የሚያደርጉት ነገር ነበር። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የወጣ መጠበቂያ ግንብ ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “እርሻቸውንና ቤታቸውን የተዉ ሲሆን ንብረታቸውን ለመሰብሰብ ሲሉ እንኳ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። በይሖዋ ጥበቃና ድጋፍ በመታመን ጠቃሚ ከሚመስል ከማንኛውም ነገር ሁሉ በፊት የእሱን አምልኮ አስቀድመዋል።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ለቁሳዊ ነገሮች ባለን አመለካከት ረገድ ወደፊት የሚመጡ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በጣም አስፈላጊ የሆኑት ያሉን ቁሳዊ ነገሮች ናቸው ወይስ ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነው በአምላክ ጎን ለቆሙ ሰዎች የሚመጣው መዳን ነው? አዎን፣ ሽሽታችን አንዳንድ ችግሮችን ወይም እጦትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። . . . አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁዎች መሆን አለብን።” w22.01 4 አን. 7-8

ሐሙስ፣ ኅዳር 23

አምላክ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ ምንኛ ክቡር ነው!—መዝ. 36:7

እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ስሙንና ባሕርያቱን በማወጅ ራሱን ለሙሴ ገለጠለት። እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ፣ ይሖዋ፣ መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነ አምላክ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ፣ ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ፣ ስህተትን፣ መተላለፍንና ኃጢአትን ይቅር የሚል።” (ዘፀ. 34:6, 7) በእነዚህ ማራኪ ቃላት አማካኝነት ይሖዋ ለሙሴ ስለ ታማኝ ፍቅሩ ልዩ ነገር ነግሮታል። ይህ ነገር ምን ይሆን? ይሖዋ ስለ ራሱ ሲናገር ታማኝ ፍቅር እንዳለው ብቻ ሳይሆን “ታማኝ ፍቅሩ . . . እጅግ ብዙ” እንደሆነም ገልጿል። ይህ ዓይነቱ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ይገኛል። (ዘኁ. 14:18፤ ነህ. 9:17፤ መዝ. 86:15፤ 103:8፤ ኢዩ. 2:13፤ ዮናስ 4:2) በሁሉም ቦታዎች ላይ ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ይሖዋን ብቻ ነው፤ ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም። ይሖዋ ታማኝ ፍቅሩን በዚህ መንገድ ጎላ አድርጎ መግለጹ ትኩረት የሚስብ አይደለም? w21.11 2-3 አን. 3-4

ዓርብ፣ ኅዳር 24

ስለ ሕይወታችሁ . . . አትጨነቁ።—ማቴ. 6:25

ባለትዳሮች ሐዋርያው ጴጥሮስ እና ሚስቱ ከተዉት ምሳሌ መማር ይችላሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገናኘ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ማድረግ ነበረበት። ጴጥሮስ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ዓሣ በማጥመድ ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ሥራውን ትቶ እንዲከተለው ሲጠይቀው ጴጥሮስ የቤተሰቡን ሁኔታ ከግምት ማስገባት ነበረበት። (ሉቃስ 5:1-11) ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር አብሮ እየተጓዘ ለመስበክ ወሰነ። ከሁኔታዎች መረዳት እንደምንችለው ደግሞ ሚስቱም ውሳኔውን ደግፋለታለች። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የጴጥሮስ ሚስት ቢያንስ አልፎ አልፎ ከጴጥሮስ ጋር ትጓዝ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። (1 ቆሮ. 9:5) በተጨማሪም ግሩም ክርስቲያን ሚስት መሆኗ ጴጥሮስ ለክርስቲያን ባሎችና ሚስቶች ምክር ሲሰጥ የመናገር ነፃነት እንዲኖረው እንደረዳው ጥያቄ የለውም። (1 ጴጥ. 3:1-7) ጴጥሮስም ሆነ ሚስቱ፣ ይሖዋ በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን ካስቀደሙ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያሟላላቸው በገባው ቃል ላይ እምነት እንደነበራቸው በግልጽ መመልከት ይቻላል።—ማቴ. 6:31-34፤ w21.11 18 አን. 14

ቅዳሜ፣ ኅዳር 25

የእኔን አርዓያ ተከተሉ።—1 ቆሮ. 11:1

ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንድሞቹ ፍቅር ነበረው። እነሱን ለመርዳት በትጋት ይሠራ ነበር። (ሥራ 20:31) በዚህም የተነሳ የእምነት ባልንጀሮቹም ለጳውሎስ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው። በአንድ ወቅት የኤፌሶን ሽማግሌዎች ጳውሎስን ድጋሚ እንደማያዩት ሲያውቁ ‘እጅግ አልቅሰው’ ነበር። (ሥራ 20:37) በዛሬው ጊዜ ያሉ ትጉ ሽማግሌዎችም ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ጥልቅ ፍቅር አላቸው፤ በተጨማሪም እነሱን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (ፊልጵ. 2:16, 17) አንዳንድ ጊዜ ግን ሽማግሌዎች ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ምን ይረዳቸዋል? ትጉ የሆኑ ሽማግሌዎቻችን የጳውሎስን ምሳሌ መመርመራቸው ይጠቅማቸዋል። ጳውሎስ ከሌሎች ሰዎች የተለየ ኃይል አልነበረውም። ጳውሎስ ፍጹም አልነበረም፤ በዚህም የተነሳ አንዳንዴ መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ያታግለው ነበር። (ሮም 7:18-20) በተጨማሪም የተለያዩ ችግሮችን መጋፈጥ አስፈልጎታል። ያም ሆኖ ጳውሎስ ተስፋ አልቆረጠም ወይም ደስታውን አላጣም። ሽማግሌዎች የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣትና ደስታቸውን ሳያጡ ይሖዋን ማገልገላቸውን መቀጠል ይችላሉ። w22.03 26 አን. 1-2

እሁድ፣ ኅዳር 26

ሰንበቶቼን [ጠብቁ]። እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።—ዘሌ. 19:3

ዘሌዋውያን 19:3 ሰንበትን ስለመጠበቅ ይናገራል። ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ስላልሆኑ ሳምንታዊውን ሰንበት ማክበር አይጠበቅባቸውም። ሆኖም እስራኤላውያን ሰንበትን የጠበቁት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይህን ማድረጋቸው ምን ጥቅም እንዳስገኘላቸው ማጥናታችን በእጅጉ ይጠቅመናል። እስራኤላውያን በሰንበት ቀን ከዕለት ተዕለት ሥራቸው አርፈው በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር። ኢየሱስ በሰንበት ቀን የአምላክን ቃል ለማንበብ ባደገበት ከተማ ወደሚገኝ ምኩራብ የሄደው ለዚህ ነው። (ዘፀ. 31:12-15፤ ሉቃስ 4:16-18) አምላክ በዘሌዋውያን 19:3 ላይ ‘ሰንበቶቼን ጠብቁ’ በማለት የሰጠው መመሪያ ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ጊዜ ገዝተን ለመንፈሳዊ ነገሮች ትኩረት እንድንሰጥ ሊያነሳሳን ይገባል። በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባችሁ ይሰማችኋል? ዘወትር ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ የምትመድቡ ከሆነ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይኖራችኋል፤ ይህ ደግሞ ቅዱስ ለመሆን ወሳኝ ነው። w21.12 5 አን. 13

ሰኞ፣ ኅዳር 27

እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም።—ሉቃስ 5:32

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ኢየሱስ ሀብትና ሥልጣን ካላቸው ሰዎች ጋር ተመግቧል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከድሆችና ከተጨቆኑ ሰዎች ጋርም ብዙ ጊዜ አሳልፏል። በተጨማሪም ብዙዎች እንደ ኃጢአተኛ አድርገው ለሚቆጥሯቸው ሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። ተመጻዳቂ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ባደረገው ነገር ተሰናክለዋል። ደቀ መዛሙርቱን “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” በማለት ጠይቀዋቸው ነበር። ኢየሱስም በምላሹ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ተናገረ። (ሉቃስ 5:29-31) ኢየሱስ ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ፣ መሲሑ በዓለም ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት እንደማያገኝ ተናግሮ ነበር። ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች የናቁትና ያገለሉት . . . ሰው ነበር። ፊቱ የተሰወረብን ያህል ነበር። ሰዎች ናቁት፤ እኛም ከቁብ አልቆጠርነውም።” (ኢሳ. 53:3) መሲሑን “ሰዎች” እንደሚንቁት ተነግሯል፤ ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ኢየሱስ ተቀባይነት እንደማያገኝ መጠበቅ ነበረባቸው። w21.05 8-9 አን. 3-4

ማክሰኞ፣ ኅዳር 28

ይሖዋም ያስነሳዋል።—ያዕ. 5:15

በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን ምክር ቶሎ ተግባራዊ አያደርጉም ነበር። (ያዕ. 1:22) ሌሎች ለሀብታሞች ያዳሉ ነበር። (ያዕ. 2:1-3) አንደበታቸውን መቆጣጠር የሚቸገሩም ነበሩ። (ያዕ. 3:8-10) እነዚህ ከባድ ችግሮች ቢሆኑም ያዕቆብ በእምነት ባልንጀሮቹ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። በደግነት ሆኖም በግልጽ ምክር ሰጥቷቸዋል። በመንፈሳዊ የሚንገዳገዱ ካሉም የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቁ አበረታቷቸዋል። (ያዕ. 5:13, 14) የምናገኘው ትምህርት፦ እውነታውን ከግምት አስገቡ፤ ሆኖም ለሌሎች አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ብዙ ሰዎች፣ የተማሩትን ተግባራዊ ማድረግ ያታግላቸው ይሆናል። (ያዕ. 4:1-4) መጥፎ ልማዶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ማስወገድና የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት ማዳበር ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ጥናቶቻችንን ሊያስተካክሉት የሚገባውን ነገር በድፍረት ልንነግራቸው ይገባል። በተጨማሪም ምንጊዜም ስለ እነሱ አዎንታዊ መሆን ይኖርብናል፤ ይሖዋ ትሑት ሰዎችን ወደ ራሱ እንደሚስብና በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—ያዕ. 4:10፤ w22.01 11 አን. 11-12

ረቡዕ፣ ኅዳር 29

ችግረኛው የሚያሰማውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን ሁሉ፣ እሱ ራሱ ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።—ምሳሌ 21:13

ሁሉም ክርስቲያኖች እንደ ይሖዋ ምሕረት ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ። ለምን? አንዱ ምክንያት ይሖዋ ምሕረት የማያሳዩ ሰዎችን ጸሎት የማይሰማ መሆኑ ነው። ሁላችንም ብንሆን ይሖዋ ጸሎታችንን እንዲሰማልን እንፈልጋለን፤ በመሆኑም ምሕረት የለሽ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። እየተሠቃየ ያለን ክርስቲያን ላለመስማት ጆሯችንን ከመድፈን ይልቅ “ችግረኛው የሚያሰማውን ጩኸት” ለመስማት ምንጊዜም ፈጣን መሆን አለብን። በተጨማሪም የሚከተለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ምክር ማስታወስ ይኖርብናል፦ “ምሕረት የማያደርግ ሰው ያለምሕረት ይፈረድበታል።” (ያዕ. 2:13) ትሑቶች በመሆን፣ ምሕረት ምን ያህል እንደሚያስፈልገን የምናስታውስ ከሆነ እኛም ምሕረት ለማሳየት መነሳሳታችን አይቀርም። በተለይ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ወደ ጉባኤው ሲመለስ ምሕረት ማሳየት ይኖርብናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ደግነትና ምሕረት ያሳዩ ሰዎችን ምሳሌ መመርመራችን፣ ምሕረት የለሽ ከመሆን ይልቅ ምሕረት እንድናሳይ ይረዳናል። w21.10 12 አን. 16-17

ሐሙስ፣ ኅዳር 30

ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ።—ማቴ. 26:36

ኢየሱስ አገልግሎቱን ሊያጠናቅቅ ሲል በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ ማሰላሰልና መጸለይ የሚችልበት ጸጥ ያለ ስፍራ ለማግኘት ሄደ። በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ቦታ አገኘ። በዚህ አጋጣሚ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ጸሎት ወቅታዊ ምክር ሰጣቸው። ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ በደረሱበት ወቅት በጣም መሽቶ ምናልባትም እኩለ ሌሊት አልፎ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ነቅታችሁ ጠብቁ” ካላቸው በኋላ ሊጸልይ ሄደ። (ማቴ. 26:37-39) እሱ እየጸለየ ሳለ ግን እነሱ እንቅልፍ ወሰዳቸው። ኢየሱስ ተኝተው ሲያገኛቸው “ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ” በማለት በድጋሚ አሳሰባቸው። (ማቴ. 26:40, 41) በጭንቀት እንደተዋጡና እንደደከማቸው ተረድቶላቸው ነበር። ኢየሱስ እንዳዘነላቸው በሚያሳይ መንገድ “ሥጋ . . . ደካማ ነው” አላቸው። ከዚያ በኋላም ኢየሱስ ሁለት ጊዜ ሊጸልይ ሄደ፤ ሲመለስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሲጸልዩ ሳይሆን ተኝተው አገኛቸው።—ማቴ. 26:42-45፤ w22.01 28 አን. 10-11

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ