ጥር
ሰኞ፣ ጥር 1
በጌታ ልጄ የሆነውን የምወደውንና ታማኝ የሆነውን ጢሞቴዎስን [እልክላችኋለሁ]።—1 ቆሮ. 4:17
ጢሞቴዎስ በይሖዋ አገልግሎት የተዋጣለት እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? ግሩም የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበሩ ነው። (ፊልጵ. 2:19-22) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጢሞቴዎስ ሲናገር ከተጠቀመበት መግለጫ ጢሞቴዎስ ትሑት፣ ታማኝ፣ ትጉና እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን። ለወንድሞች ከልቡ የሚጨነቅ ሰው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ይወደው ነበር፤ እንዲሁም ከባድ የሆኑ ኃላፊነቶችን በአደራ ሰጥቶታል። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ የሚወዳቸውን ባሕርያት የምናዳብር ከሆነ በእሱ ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍና ጉባኤያችንን ይበልጥ መርዳት እንችላለን። (መዝ. 25:9፤ 138:6) ስለዚህ የትኛውን ባሕርይ ማሻሻል እንዳለብህ በጸሎት አስብበት። ማሻሻል የምትፈልገውን አንድ ባሕርይ ምረጥ። የሌሎችን ስሜት ይበልጥ ለመረዳት መጣጣር ትችል ይሆን? ሰላም ፈጣሪና ይቅር ባይ በመሆን ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን? በየትኞቹ አቅጣጫዎች ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ እንዲጠቁምህ የምታምነውን ጓደኛህን መጠየቅ ትችላለህ።—ምሳሌ 27:6፤ w22.04 23 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ ጥር 2
እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር።—ገላ. 6:4
ይሖዋ ደስተኛ እንድንሆን ይፈልጋል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም ደስታ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ አንድ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:22) ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ስለሚያስገኝ በአገልግሎታችን ሙሉ በሙሉ ስንጠመድ እንዲሁም ወንድሞቻችንን በተለያዩ መንገዶች ስንረዳ ጥልቅ ደስታ እናገኛለን። (ሥራ 20:35) በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዱንን ሁለት ነገሮች ጠቅሷል። አንደኛ፣ ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት ይኖርብናል። ለይሖዋ ምርጣችንን እየሰጠነው እስከሆነ ድረስ ልንደሰት ይገባል። (ማቴ. 22:36-38) ሁለተኛ፣ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር መቆጠብ ይኖርብናል። ከጤንነታችን፣ ካገኘነው ሥልጠና ወይም ከተፈጥሯዊ ችሎታችን አንጻር ማከናወን የምንችለው ነገር ምንም ይሁን ምን ይሖዋን ማመስገን አለብን። በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ የአገልግሎት ዘርፎች ረገድ ሌሎች ከእኛ የበለጠ ውጤታማ ከሆኑ ችሎታቸውን ይሖዋን ለማወደስ ስለተጠቀሙበት ልንደሰት ይገባል። w22.04 10 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ጥር 3
መዳናችሁ እየቀረበ [ነው]።—ሉቃስ 21:28
የሐሰት ሃይማኖት ጥፋት ዓለምን የሚያናውጥ አስደንጋጭ ክስተት ይሆናል። (ራእይ 18:8-10) የታላቂቱ ባቢሎን መጥፋት በመላው ዓለም ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣና አንዳንድ ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። ያም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች በዚያ ወቅት ለመደሰት የሚያበቋቸው ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች ይኖሯቸዋል። አንደኛ፣ ለረጅም ዘመን የይሖዋ አምላክ ጠላት ሆና የኖረችው ታላቂቱ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ ተደምስሳለች፤ ሁለተኛ፣ ከዚህ ክፉ ሥርዓት የምንገላገልበት ጊዜ ቅርብ ነው! ዳንኤል ‘እውነተኛው እውቀት እንደሚበዛ’ ተንብዮ ነበር። በእርግጥም በዝቷል! ስለምንኖርበት ዘመን የሚናገሩ ትንቢቶችን በተመለከተ ጥልቅ ግንዛቤ አግኝተናል። (ዳን. 12:4, 9, 10) እነዚህ ትንቢቶች በትክክል መፈጸማቸው ለይሖዋ እና በመንፈስ መሪነት ላስጻፈው ቃሉ ያለንን አድናቆት ይጨምርልናል። (ኢሳ. 46:10፤ 55:11) እንግዲያው ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት በማጥናት እንዲሁም ሌሎችም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲመሠርቱ በመርዳት እምነታችሁን ማጠናከራችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ የሚታመኑበትን ይጠብቃቸዋል፤ ‘ዘላቂ ሰላምም’ ይሰጣቸዋል።—ኢሳ. 26:3፤ w22.07 6-7 አን. 16-17
ሐሙስ፣ ጥር 4
እነሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።—ራእይ 16:16
የራእይ መጽሐፍ የአምላክ መንግሥት በሰማይ እንደተቋቋመና ሰይጣን ከሰማይ እንደተባረረ ይነግረናል። (ራእይ 12:1-9) የሰይጣን መባረር በሰማይ እፎይታ አስገኝቷል፤ ለእኛ ግን ችግሮች አስከትሎብናል። ለምን? ምክንያቱም የሰይጣን ቁጣ በአሁኑ ወቅት ያነጣጠረው በምድር ላይ ይሖዋን በታማኝነት በሚያገለግሉት ላይ ነው። (ራእይ 12:12, 15, 17) የሰይጣንን ጥቃት ተቋቁመን በጽናት ለመቀጠል ምን ይረዳናል? (ራእይ 13:10) የሚረዳን አንዱ ነገር ወደፊት ምን እንደሚከናወን ማወቃችን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በራእይ መጽሐፍ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ በቅርቡ የምናገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች ጠቅሷል። ከእነዚህ በረከቶች አንዱ የአምላክ ጠላቶች መጥፋት ነው። የራእይ መጽሐፍ ገና የመጀመሪያ ቁጥሩ ላይ እንደሚነግረን በውስጡ ያሉት ነገሮች የተጻፉት “በምልክቶች” ወይም በምሳሌያዊ ቋንቋ ነው።—ራእይ 1:1፤ w22.05 8 አን. 1-3
ዓርብ፣ ጥር 5
ጎግ ሆይ፣ በዘመኑ መጨረሻ በአንተ አማካኝነት በፊታቸው ራሴን በምቀድስበት ጊዜ ብሔራት ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።—ሕዝ. 38:16
የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የሚይዙት ጽኑ አቋም የይሖዋን ተቃዋሚዎች ቁጣ ያስነሳል። በዚህም የተነሳ፣ ጥምረት የፈጠሩ ብሔራት በምድር ዙሪያ ባሉ የአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ብሔራት የሚወስዱት ይህ የእብደት እርምጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ የማጎጉ ጎግ ጥቃት ተብሎ የተገለጸው ነው። (ሕዝ. 38:14, 15) ይሖዋ ለዚህ የጭካኔ ጥቃት ምን ምላሽ ይሰጣል? “ታላቅ ቁጣዬ ይነድዳል” ብሏል። (ሕዝ. 38:18, 21-23) ራእይ ምዕራፍ 19 ከዚያ በኋላ ምን እንደሚከናወን ይነግረናል። ይሖዋ ሕዝቡን ለመታደግና ጠላቶቹን ለመደምሰስ ልጁን ይልከዋል። ኢየሱስ በሚወስደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ “በሰማይ ያሉት ሠራዊቶች” አብረውት ይሆናሉ፤ እነሱም ታማኝ መላእክትና 144,000ዎቹ ናቸው። (ራእይ 17:14፤ 19:11-15) የጦርነቱ ውጤት ምን ይሆናል? ይሖዋን የሚቃወሙ ሰዎችና ድርጅቶች በሙሉ ተጠራርገው ይጠፋሉ።—ራእይ 19:19-21፤ w22.05 17 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ ጥር 6
በአንተና በሴቲቱ መካከል . . . ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ።—ዘፍ. 3:15
አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ አንድ አስደናቂ ትንቢት በመናገር ለዘሮቻቸው ተስፋ ሰጠ። በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ትንቢት እንዲህ ይላል፦ “በአንተና በሴቲቱ መካከል እንዲሁም በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ፤ እሱ ራስህን ይጨፈልቃል፤ አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።” ይህ ትንቢት የሚገኘው በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ሆኖም ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ በሆነ መልኩ ከዚህ ትንቢት ጋር ተያያዥነት አላቸው። የአንድ መጽሐፍ ስፌት ሁሉንም ገጾች ሰብስቦ እንደሚያያይዝ ሁሉ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢትም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ በአንድ የጋራ መልእክት እንዲያያዙ ያደርጋል። ይህ መልእክት ዲያብሎስንና ክፉ የሆኑ ተከታዮቹን የሚደመስስ አንድ አዳኝ እንደሚላክ የሚገልጽ ነው። ይህ ይሖዋን ለሚወዱ ሁሉ በጣም አስደሳች ነው! መጽሐፍ ቅዱስን መመርመራችን ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት እንደሆነና እኛ ከትንቢቱ ተጠቃሚ መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ይረዳናል። w22.07 14 አን. 1-3
እሁድ፣ ጥር 7
ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣል።—ምሳሌ 2:6
ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳት የሚያስፈልገውን ጥበብ እንዲሰጣችሁ ይሖዋን ጠይቁት። (ያዕ. 1:5) ከእሱ የተሻለ መካሪ ልታገኙ አትችሉም። እንዲህ የምንልባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ ሁለቱ ግን እነዚህ ናቸው። አንደኛ፣ የይሖዋን ያህል የወላጅነት ተሞክሮ ያለው የለም። (መዝ. 36:9) ሁለተኛ እሱ የሚሰጠው ጥበብ ያለበት ምክር ምንጊዜም ጠቃሚ ነው። (ኢሳ. 48:17) ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ልጆቻችሁ እሱን እንዲወዱ ለመርዳት የሚያስችላችሁ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦላችኋል። (ማቴ. 24:45) ለምሳሌ “ለቤተሰብ” በሚለው ተከታታይ ርዕስ ሥር ብዙ ጠቃሚ ምክር ማግኘት ትችላላችሁ። ይህ ዓምድ ለበርካታ ዓመታት ንቁ! መጽሔት ላይ ታትሞ ይወጣ የነበረ ሲሆን አሁን ድረ ገጻችን ላይ ይገኛል። jw.org ላይ የሚወጡ ቃለ መጠይቆችና አጭር ድራማዎችም ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ የይሖዋን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ይረዷቸዋል።—ምሳሌ 2:4, 5፤ w22.05 27 አን. 4-5
ሰኞ፣ ጥር 8
ያህ ሆይ፣ አንተ ስህተትን የምትከታተል ቢሆን ኖሮ . . . ማን ሊቆም ይችል ነበር?—መዝ. 130:3
ይሖዋ ይቅር በማለት ረገድ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የለውም። አንደኛ፣ ምንጊዜም ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። ሁለተኛ፣ ሁላችንንም አብጠርጥሮ ያውቀናል። ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቅ እውነተኛ ንስሐ መግባታችንን ከማንም በተሻለ ማወቅ የሚችለው እሱ ነው። ሦስተኛ ደግሞ ይሖዋ ይቅር ሲለን ኃጢአታችንን ሙሉ በሙሉ ይሰርዘዋል። ይህም ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረንና የእሱን ሞገስ እንድናገኝ ይረዳናል። እርግጥ ነው፣ ፍጹም እስካልሆንን ድረስ ኃጢአት መሥራታችንን መቀጠላችን አይቀርም። ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 771 ላይ ያለው ሐሳብ በእጅጉ ያጽናናናል፤ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ የአገልጋዮቹን ሥጋዊ ድክመት በምሕረት ስለሚመለከት በወረሱት አለፍጽምና የተነሳ በሠሯቸው ስህተቶች ዕድሜ ልካቸውን ሲጸጸቱ መኖር አያስፈልጋቸውም። (መዝ 103:8-14፤ 130:3) በአምላክ መንገድ ለመጓዝ ልባዊ ጥረት እስካደረጉ ድረስ መደሰት ይችላሉ። (ፊልጵ 4:4-6፤ 1ዮሐ 3:19-22)” w22.06 7 አን. 18-19
ማክሰኞ፣ ጥር 9
[በስሜ] ምክንያት በነገሥታትና በገዢዎች ፊት ያቀርቧችኋል።—ሉቃስ 21:12
ሰይጣን የሚጠቀመው የመንግሥታትን ተቃውሞ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች እውነትን ሲቀበሉ ‘ቤተሰቦቼ ምን ይሉኛል’ የሚለው ነገር ከአካላዊ ጥቃት ይበልጥ ያስፈራቸዋል። ቤተሰቦቻቸውን በጣም ይወዷቸዋል፤ በመሆኑም ስለ ይሖዋ እንዲያውቁና እሱን እንዲወዱት ይፈልጋሉ። ቤተሰቦቻቸው ስለ እውነተኛው አምላክና ስለ አገልጋዮቹ መጥፎ ነገሮችን ሲናገሩ መስማት በጣም ያሳዝናቸዋል። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ተቃዋሚ የነበሩት ቤተሰቦቻቸው በኋላ ላይ እውነትን ይቀበላሉ። ሆኖም የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በመወሰናችን ምክንያት ቤተሰቦቻችን ሙሉ በሙሉ ቢያገሉንስ? በዚህ ጊዜ ምን ምላሽ እንሰጣለን? በመዝሙር 27:10 ላይ የሚገኘው ግሩም ሐሳብ ያጽናናናል። ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን ማስታወሳችን ተቃውሞ ቢያጋጥመንም እንድንረጋጋ ይረዳናል። ጽናታችንን እንደሚባርክልንም መተማመን እንችላለን። ይሖዋ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ከማንም በላይ ያሟላልናል። w22.06 17 አን. 11-13
ረቡዕ፣ ጥር 10
ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።—1 ጴጥ. 2:21
ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን ሰካራም፣ ሆዳም፣ የአጋንንት ወኪል፣ ሰንበትን የማያከብር፣ አምላክን የሚሳደብ ብለው በሐሰት ወንጅለውታል። (ማቴ. 11:19፤ 26:65፤ ሉቃስ 11:15፤ ዮሐ. 9:16) ሆኖም ኢየሱስ በቁጣ በመናገር ብድር አልመለሰም። እኛም እንደ ኢየሱስ ሰዎች ሲያመናጭቁን አጸፋውን ከመመለስ መቆጠብ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 2:22, 23) እርግጥ ነው፣ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስሜትን መቆጣጠር ቀላል አይደለም። (ያዕ. 3:2) ታዲያ ምን ሊረዳን ይችላል? አገልግሎት ላይ አንድ ሰው በቁጣ ሲናገርህ፣ ከሰጠው ምላሽ ባሻገር ያለውን ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ሳም የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የማነጋግረው ሰው መልእክቱን መስማት ምን ያህል እንደሚያስፈልገው እንዲሁም ነገ ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል ለማሰብ እሞክራለሁ።” አንዳንድ ጊዜ አገልግሎት ላይ ሰዎች የሚቆጡት ጥሩ ስሜት ላይ ባልነበሩበት ሰዓት ላይ ስላነጋገርናቸው ብቻ ሊሆን ይችላል። የሚቆጣ ሰው ሲያጋጥመን አጭር ጸሎት እናቅርብ፤ መረጋጋት እንድንችልና ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳንናገር እንዲረዳን ይሖዋን እንለምነው። w22.04 6 አን. 8-9
ሐሙስ፣ ጥር 11
ወደ አምላክ ቅረቡ።—ያዕ. 4:8
ልጆች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት የሚቻልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ነው። (2 ጢሞ. 3:14-17) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ስለ ይሖዋ መማር የሚችሉበት ሌላም መንገድ እንዳለ ይጠቁማል። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ አንድ አባት በፍጥረት ላይ ተንጸባርቀው የሚታዩትን የይሖዋን ባሕርያት ከእይታው እንዳያርቅ ልጁን አሳስቦታል። (ምሳሌ 3:19-21) ወላጆች፣ ከልጆቻችሁ ጋር ከቤት ወጣ ብላችሁ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስታችሁ የታወቀ ነው። ይህን አጋጣሚ ‘በተሠሩት ነገሮች’ እና አስደናቂ በሆኑት የይሖዋ ባሕርያት መካከል ያለውን ግንኙነት ልጆቻችሁ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ተጠቀሙበት። (ሮም 1:20) ኢየሱስ ፍጥረትን ተጠቅሞ ያስተማረው እንዴት እንደሆነ ልብ በሉ። በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርቱን ቁራዎችንና የሜዳ አበቦችን እንዲመለከቱ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 12:24, 27-30) ለደቀ መዛሙርቱ በሰማይ ስላለው አባቱ ልግስናና ደግነት የሚከተለውን ወሳኝ ትምህርት አስተማራቸው፦ ይሖዋ ለቁራዎችና ለሜዳ አበቦች እንደሚያደርገው ሁሉ ታማኝ አገልጋዮቹንም ይመግባቸዋል እንዲሁም ያለብሳቸዋል። w23.03 20-21 አን. 1-4
ዓርብ፣ ጥር 12
አብ በወልድ አማካኝነት እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ።—ዮሐ. 14:13
በልጁ አማካኝነት ወደ እሱ በጸሎት የመቅረብ መብት ስላገኘን ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን በኢየሱስ አማካኝነት ነው። ይሖዋ በኢየሱስ ስም የቀረቡ ጸሎቶችን ይሰማል እንዲሁም ይመልሳል፤ በተጨማሪም የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ኃጢአታችንን ይቅር ይልልናል። (ሮም 5:1) መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “በሰማያት በግርማዊው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ . . . ሊቀ ካህናት” በማለት ይጠራዋል። (ዕብ. 8:1) ኢየሱስ ‘በአብ ዘንድ ያለን ረዳት’ ነው። (1 ዮሐ. 2:1) ይሖዋ ድክመታችንን የሚረዳልንና ‘ስለ እኛ የሚማልድ’ አዛኝ ሊቀ ካህናት ስለሰጠን በጣም እናመሰግነዋለን። (ሮም 8:34፤ ዕብ. 4:15) የኢየሱስ መሥዋዕት ባይኖር ኖሮ ወደ ይሖዋ በጸሎት መቅረብ አንችልም ነበር። በእርግጥም ይሖዋ ይህን ልዩ ስጦታ ማለትም ውድ ልጁን ስለሰጠን አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥረናል! w22.07 23 አን. 10-12
ቅዳሜ፣ ጥር 13
እምነት የሚጣልበት ሰው . . . ሚስጥር ይጠብቃል።—ምሳሌ 11:13
እምነት የሚጣልበት ሰው የገባውን ቃል ለመጠበቅ ጥረት ያደርጋል፤ እንዲሁም እውነቱን ይናገራል። (መዝ. 15:4) ሰዎች ይተማመኑበታል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለ እኛ እንደዚያ እንዲሰማቸው እንፈልጋለን። ሌሎች እንዲያምኑን ማስገደድ አንችልም። እንዲያምኑን ከፈለግን አመኔታቸውን ማትረፍ ይኖርብናል። አመኔታ እንደ ገንዘብ ነው ሲባል እንሰማለን። ማትረፍ ከባድ ነው፤ ማጣት ግን ቀላል ነው። ይሖዋ የሕዝቦቹን አመኔታ አትርፏል። “[ሥራው] ሁሉ እምነት የሚጣልበት ነው።” (መዝ. 33:4) እኛም እሱን እንድንመስለው ይጠብቅብናል። (ኤፌ. 5:1) ይሖዋ አፍቃሪና እምነት የሚጣልባቸውን ሰዎች ወዳቀፈው የወንድማማች ማኅበር ስለሳበን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ሁላችንም የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን አመኔታ የማትረፍ ኃላፊነት አለብን። እያንዳንዳችን ፍቅር፣ ትሕትና፣ ማስተዋል፣ ሐቀኝነትና ራስን መግዛት ለማንጸባረቅ ጥረት ስናደርግ በጉባኤው ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን። እንግዲያው አምላካችንን ይሖዋን በመምሰል እምነት የሚጣልብን ሰዎች እንደሆንን ማስመሥከራችንን እንቀጥል። w22.09 8 አን. 1-2፤ 13 አን. 17
እሁድ፣ ጥር 14
[ይሖዋ] ይመለከታል።—መዝ. 33:18
የይሖዋን አገልጋዮች ያቀፈው ትልቅ ቤተሰብ ክፍል ብንሆንም አልፎ አልፎ ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን እንዲሁም ከሐዘን ወይም ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር እንታገል ይሆናል፤ ከእነዚህ ስሜቶች ጋር የምንታገለው ብቻችንን እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርብን በፍጹም አይፈልግም። ነቢዩ ኤልያስን እንዴት እንደያዘው እንመልከት። ይሖዋ፣ ኤልያስ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር አበረታቶታል። “ኤልያስ፣ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” በማለት ሁለት ጊዜ ጠይቆታል። (1 ነገ. 19:9, 13) በሁለቱም ጊዜያት ኤልያስ ስሜቱን ሲገልጽ ይሖዋ አዳምጦታል። ይሖዋ ከኤልያስ ጋር አብሮት እንዳለ በማሳየትና ኃይሉን በመግለጥ ለኤልያስ ምላሽ ሰጥቶታል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ኤልያስ አሁንም በርካታ የእምነት አጋሮች እንዳሉት አረጋግጦለታል። (1 ነገ. 19:11, 12, 18) ኤልያስ ልቡን በይሖዋ ፊት ማፍሰሱ እንዲሁም የይሖዋን ምላሽ መስማቱ እፎይታ እንዳስገኘለት ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ለኤልያስ የተለያዩ ወሳኝ ኃላፊነቶችን ሰጥቶታል። ሃዛኤልን የሶርያ ንጉሥ፣ ኢዩን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሁም ኤልሳዕን ነቢይ አድርጎ እንዲቀባ አዘዘው። (1 ነገ. 19:15, 16) ይሖዋ ለኤልያስ እነዚህን ኃላፊነቶች በመስጠት በአዎንታዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። በተጨማሪም አምላክ፣ ለኤልያስ የቅርብ ወዳጅ እንዲሆነው ኤልሳዕን ሰጥቶታል። w22.08 8 አን. 3፤ 9 አን. 5
ሰኞ፣ ጥር 15
እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።—1 ተሰ. 5:11
ጉባኤያችሁ የስብሰባ አዳራሽ ገንብቶ ወይም አድሶ ያውቃል? ከሆነ በአዲሱ አዳራሽ ያደረጋችሁትን የመጀመሪያ ስብሰባ እንደምታስታውስ ጥያቄ የለውም። ይሖዋን በጣም አመስግነኸው መሆን አለበት። እንዲያውም የደስታ እንባ ስለተናነቀህ የመክፈቻውን መዝሙር መዘመር ከብዶህ ሊሆን ይችላል። በጥራት የተገነቡት የስብሰባ አዳራሾቻችን ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣሉ። ሆኖም በሌላ ዓይነት የግንባታ ወይም የማነጽ ሥራ ስንካፈል ለይሖዋ ይበልጥ ውዳሴ እናመጣለን። ይህ ሥራ ቃል በቃል ሕንፃዎችን ከማነጽ የበለጠ ዋጋ አለው። ሥራው ወደነዚህ የአምልኮ ቦታዎች የሚመጡ ሰዎችን ማነጽን ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ የጻፈው ይህን ምሳሌያዊ የማነጽ ሥራ በአእምሮው ይዞ ነው። ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን በማነጽ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ስሜታቸውን ይረዳላቸው ነበር። እኛም የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል በዛሬው ጊዜ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እናንጽ።—1 ቆሮ. 11:1፤ w22.08 20 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ጥር 16
ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ [ተመላለሱ]።—ቆላ. 1:10
በአምላክ ዓይን ጻድቅ መሆን የሚፈልግ ክርስቲያን በንግድ ጉዳዮች ረገድ ሙሉ በሙሉ ሐቀኛ ይሆናል። በተጨማሪም ጻድቅ ሰው ፍትሕን ይወዳል፤ ማንም ላይ ግፍ ሲደርስ ማየት አይፈልግም። ከዚህም ሌላ ጻድቅ ሰው ‘ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ ስለሚፈልግ ከሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ የአምላክን አመለካከት ግምት ውስጥ ያስገባል። መጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ ይናገራል። ይሖዋ “የጽድቅ መኖሪያ” ተብሎ የተጠራው ለዚህ ነው። (ኤር. 50:7) ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ትክክልና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። እኛ ካለን ግንዛቤ በላቀ መልኩ የትኞቹ ነገሮች ትክክል፣ የትኞቹ ነገሮች ደግሞ ስህተት እንደሆኑ በትክክል ያውቃል። (ምሳሌ 14:12፤ ኢሳ. 55:8, 9) ያም ቢሆን የተሠራነው በአምላክ አምሳል ስለሆነ በእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች መመራት እንችላለን። (ዘፍ. 1:27) እንዲህ ማድረግም ያስደስተናል። ለአባታችን ያለን ፍቅር አቅማችን በፈቀደ መጠን እሱን እንድንመስል ያነሳሳናል።—ኤፌ. 5:1፤ w22.08 27 አን. 5-6
ረቡዕ፣ ጥር 17
የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።—ኤፌ. 5:17
የሚያስጨንቅ ወይም የሚያሳዝን ነገር ሲያጋጥመን ከችግራችን ለመሸሽ ትኩረታችንን የሚሰርቅልን ነገር እንፈልግ ይሆናል። እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። ሆኖም ይሖዋ የሚጠላውን ነገር እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5: 10-12, 15, 16) ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ‘ጽድቅ፣ ንጹሕ፣ ተወዳጅና በጎ’ የሆነውን ነገር ማሰባቸውን እንዳያቋርጡ አበረታቷቸዋል። (ፊልጵ. 4:8) ጳውሎስ እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ስለ መዝናኛ ባይሆንም የጻፈው ሐሳብ የመዝናኛ ምርጫችንንም ሊነካው ይገባል። እስቲ እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ጥቅሱ ላይ “ነገር” የሚለው ቃል በሚገኝበት ቦታ ሁሉ “ሙዚቃ፣” “ፊልም፣” “መጽሐፍ” ወይም “ቪዲዮ ጌም” የሚለውን ቃል ተኩ። እንዲህ ማድረጋችሁ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና የሌላቸው መዝናኛዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለመለየት ይረዳችኋል። ላቅ ያሉትን የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል እንፈልጋለን።—መዝ. 119:1-3፤ w22.10 9 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ጥር 18
በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ [ነበር]።—ዮሐ. 2:25
‘ጻድቃን ካልሆኑት ሰዎች’ መካከል አንዳንዶቹ በቀድሞ ሕይወታቸው እጅግ አስከፊ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። በመሆኑም በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታቸውን መምራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ሲባል የአምላክ መንግሥት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር ያዘጋጃል። ጻድቃን ያልሆኑትን ሰዎች የሚያስተምራቸው ማን ነው? እጅግ ብዙ ሕዝብና ከሞት የተነሱት ጻድቃን ናቸው። እነዚህ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንዲጻፍ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና መመሥረትና ራሳቸውን ለእሱ መወሰን አለባቸው። ኢየሱስ ክርስቶስና ቅቡዓኑ እነዚህ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ለሚሰጣቸው ትምህርት የሚሰጡትን ምላሽ በትኩረት ይከታተላሉ። (ራእይ 20:4) ለሚሰጣቸው እርዳታ በጎ ምላሽ የማይሰጡ ሰዎች በሙሉ 100 ዓመት ቢሆናቸው እንኳ ይጠፋሉ። (ኢሳ. 65:20) የሰዎችን ልብ ማንበብ የሚችሉት ይሖዋና ኢየሱስ ማንም ሰው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ችግር እንዲፈጥር አይፈቅዱም።—ኢሳ. 11:9፤ 60:18፤ 65:25፤ w22.09 17 አን. 11-12
ዓርብ፣ ጥር 19
ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ።—ሮም 13:1
በዚህ ጥቅስ ላይ ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ የሚለው አገላለጽ በሌሎች ላይ ኃይልና ሥልጣን ያላቸውን ሰብዓዊ መሪዎች ያመለክታል። ክርስቲያኖች ለእነዚህ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገዛት ይጠበቅባቸዋል። ባለሥልጣናት ሥርዓት ያስጠብቃሉ፤ ሕግ ያስከብራሉ፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ለይሖዋ ሕዝቦች ጥብቅና ይቆማሉ። (ራእይ 12:16) በመሆኑም እነሱ የሚጠይቁትን ቀረጥ፣ ግብር፣ ፍርሃትና ክብር እንድንሰጣቸው ታዘናል። (ሮም 13:7) ሆኖም እነዚህ መንግሥታት ሥልጣን ያላቸው ይሖዋ ስለፈቀደላቸው ብቻ ነው። ኢየሱስ በሮማዊው አገረ ገዢ በጳንጢዮስ ጲላጦስ ፊት በቀረበበት ወቅት ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ግልጽ አድርጓል። ጲላጦስ ኢየሱስን ለመፍታትም ሆነ ለመግደል ሥልጣን እንዳለው በተናገረበት ወቅት ኢየሱስ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን አይኖርህም ነበር” ብሎታል። (ዮሐ. 19:11) እንደ ጲላጦስ ሁሉ በዘመናችን ያሉ መሪዎችና ፖለቲከኞች በሙሉ ሥልጣናቸው የተገደበ ነው። w22.10 14 አን. 6
ቅዳሜ፣ ጥር 20
ክፉዎች አይኖሩም።—መዝ. 37:10
ንጉሥ ዳዊት፣ ጥበበኛና ታማኝ የሆነ ንጉሥ ወደፊት ዙፋን ላይ ሲቀመጥ ሕይወት ምን እንደሚመስል በመንፈስ መሪነት ጽፏል። (መዝ. 37:10, 11, 29) ወደፊት ስለሚመጣው ገነት ከሰዎች ጋር ስንወያይ ብዙ ጊዜ መዝሙር 37:11ን እናነባለን። እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ይህን ጥቅስ በተራራው ስብከት ላይ ጠቅሶታል፤ ይህም ጥቅሱ ወደፊት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ይጠቁማል። (ማቴ. 5:5) ይሁንና ዳዊት የተናገራቸው ቃላት፣ በንጉሥ ሰለሞን ዘመን ሕይወት ምን እንደሚመስልም ይጠቁማሉ። በሰለሞን የግዛት ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ‘ወተትና ማር በምታፈሰው’ ምድር ላይ ለየት ያለ ሰላምና ብልጽግና አግኝተዋል። አምላክ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ባወጣኋቸው ደንቦች መሠረት ብትሄዱ . . . በምድሪቱ ሰላም አሰፍናለሁ፤ እናንተም ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ።” (ዘሌ. 20:24፤ 26:3, 6) በሰለሞን የግዛት ዘመን ይህ ቃል ተፈጽሟል። (1 ዜና 22:9፤ 29:26-28) በመዝሙር 37:10, 11, 29 ላይ የሚገኙት ቃላት በጥንት ዘመን ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል፤ ወደፊትም ፍጻሜ ያገኛሉ። w22.12 10 አን. 8
እሁድ፣ ጥር 21
[ጥበብን] አጥብቀው የሚይዟትም ደስተኞች ይባላሉ።—ምሳሌ 3:18
እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን መመሪያ መከተል አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ስኬት ለማግኘት የሚረዳ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል፤ እንዲህ ይላል፦ “ጥበብ ያለበት አመራር ተቀብለህ ለውጊያ ትወጣለህ፤ በብዙ አማካሪዎችም ስኬት ይገኛል።” (ምሳሌ 24:6 ግርጌ) ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጋችን በስብከቱና በማስተማሩ ሥራችን ስኬት ለማግኘት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። አገልግሎታችንን በራሳችን መንገድ ከማከናወን ይልቅ የሚሰጡንን መመሪያዎች ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ እናገኛለን። ተሞክሮ ያላቸው “አማካሪዎች” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ንግግሮችና በሠርቶ ማሳያዎች አማካኝነት ያሠለጥኑናል። በተጨማሪም የይሖዋ ድርጅት፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲረዱ የሚያግዙ ጠቃሚ ጽሑፎችንና ቪዲዮዎችን አዘጋጅቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው ጠቃሚ ምክር ምንኛ አመስጋኞች ነን! እንዲህ ያለውን ግሩም ምክር ባናገኝ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር? እንግዲያው ይሖዋ የሚሰጠውን ጥበብ ምንጊዜም ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ምሳሌ 3:13-17፤ w22.10 23 አን. 18-19
ሰኞ፣ ጥር 22
የተናገርከው ነገር ለምላሴ እጅግ ጣፋጭ ነው፤ ለአፌም ከማር የበለጠ ይጥማል!—መዝ. 119:103
ምግብ በልተን ሲዋሃደን ሰውነታችን እንደሚጠነክር ሁሉ የአምላክን ቃል አጥንተን ስናሰላስልበት መንፈሳዊነታችን ይጠናከራል። ይሖዋ የቃሉን መልእክት እንድንረዳው ይፈልጋል። ይህን ለማድረግ መጸለይ፣ ማንበብና ማሰላሰል ይኖርብናል። በመጀመሪያ የአምላክን ሐሳብ እንዲቀበል ልባችንን ለማዘጋጀት እንጸልያለን። ቀጥሎ መጽሐፍ ቅዱስን እናነባለን። ከዚያም ቆም ብለን በማሰላሰል ስላነበብነው ነገር በጥልቀት እናስባለን። እንዲህ ስናደርግ ውጤቱ ምን ይሆናል? ይበልጥ ባሰላሰልን ቁጥር የአምላክ ቃል ከምሳሌያዊ ልባችን ጋር ይበልጥ ይዋሃዳል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና ማሰላሰላችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ እንዲሁም በቅርቡ ልናውጅ የምንችለውን ኃይለኛ የፍርድ መልእክት ለመናገር ውስጣዊ ጥንካሬ ይሰጠናል። ከዚህም ሌላ፣ ማራኪ በሆኑት የይሖዋ ባሕርያት ላይ ስናሰላስል ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። w22.11 6-7 አን. 16-17
ማክሰኞ፣ ጥር 23
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።—ዮሐ. 13:35
ኢየሱስ ተከታዮቹ ብቻ ሳይሆኑ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ያሉ ሰዎችም እውነተኛ ተከታዮቹን እርስ በርሳቸው ባላቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ለይተው እንደሚያውቋቸው ጠቁሟል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባሉት ሰዎች መካከል ያለው ፍቅር በእርግጥም አስደናቂ ነው። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ፍጹማን አይደሉም። (1 ዮሐ. 1:8) በመሆኑም በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ ባወቅናቸው ቁጥር አንዳንድ ድክመቶቻቸውን የምናይበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። (ሮም 3:23) የሚያሳዝነው አንዳንዶች የሌሎች አለፍጽምና እንዲያሰናክላቸው ፈቅደዋል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንደሚወዳቸው ያሳየው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚቻለውስ እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች የሆንን በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰላችን ተገቢ ነው። እንዲህ ማድረጋችን በተለይ ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ በተሟላ መንገድ ፍቅር ማሳየት እንድንችል ይረዳናል።—ኤፌ. 5:2፤ w23.03 26-27 አን. 2-4
ረቡዕ፣ ጥር 24
ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ።—መዝ. 18:25
ወደዚህ ሥርዓት መጨረሻ እየተቃረብን በሄድን መጠን በጉባኤ ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ሊፈትኑት ይችላሉ። በመሆኑም የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ ይኖርብናል። አንድ የእምነት ባልንጀራህ እንደበደለህ ከተሰማህ፣ በሁኔታው አትመረር። ተግሣጽ ከተሰጠህ፣ ከሚሰማህ የኀፍረት ስሜት አሻግረህ ተመልከት፤ የተሰጠህን ምክር ተቀበል፤ እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ አድርግ። በተጨማሪም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የተደረጉ ማስተካከያዎች በግለሰብ ደረጃ ከነኩህ፣ ማስተካከያዎቹን በሙሉ ልብ ተቀብለህ መመሪያውን ታዘዝ። ታማኝነትህ ሲፈተን በይሖዋና በድርጅቱ መተማመንህን ቀጥል። መረጋጋት፣ ቆም ብለህ ማሰብና ነገሮችን በይሖዋ ዓይን ማየት ይኖርብሃል። ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ። እንዲሁም ራስህን ፈጽሞ ከጉባኤው አታግልል። እንዲህ ካደረግክ፣ ምንም ይምጣ ምን ሰይጣን ከይሖዋም ሆነ ከድርጅቱ ሊለይህ አይችልም።—ያዕ. 4:7፤ w22.11 24-25 አን. 14-16
ሐሙስ፣ ጥር 25
ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ።—1 ጴጥ. 2:17
ሽማግሌዎች፣ ወንድሞች አደጋ ከመከሰቱ በፊት እንዲዘጋጁ ይረዳሉ። ሁሉም የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች ራሳቸውን ከጉዳት ለመጠበቅ እንዲሁም ሽማግሌዎችን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ያደርጋሉ። አንተስ በግለሰብ ደረጃ ምን ማድረግ ትችላለህ? ከምትኖርበት አካባቢ ብዙም ሳይርቅ አደጋ ከተከሰተ እርዳታ ማበርከት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌዎችን ጠይቃቸው። ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አስፋፊዎችን ወይም የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞችን በቤትህ ማሳረፍ ትችል ይሆናል። እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አስፋፊዎች ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማድረስም ትችላለህ። አደጋ የተከሰተው ከምትኖርበት አካባቢ ርቆ ቢሆንም እንኳ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ። እንዴት? በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች በመጸለይ ነው። (2 ቆሮ. 1:8-11) ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ በማድረግ የእርዳታ ሥራውን በገንዘብ መደገፍም ትችል ይሆናል። (2 ቆሮ. 8:2-5) አደጋ ወደደረሰበት አካባቢ ተጉዘህ እርዳታ ማበርከት የምትችል ከሆነ በሥራው ለመካፈል ራስህን ማቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሽማግሌዎችን አማክራቸው። በዚህ ሥራ እንድትካፈል ከተጋበዝክ ሥልጠና ሊሰጥህ ይችላል፤ ከዚያም በምትፈለግበት ጊዜና ቦታ እርዳታ ማበርከት ትችላለህ። w22.12 24 አን. 8፤ 25 አን. 11-12
ዓርብ፣ ጥር 26
በሰው ሁሉ ላይ ከሚደርሰው ፈተና የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም።—1 ቆሮ. 10:13
ይህ ሐሳብ የተጻፈው በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች ነው። ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ ቀደም ሲል አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያንና ሰካራሞች ነበሩ። (1 ቆሮ. 6:9-11) እነዚህ ክርስቲያኖች ከተጠመቁ በኋላ ከየትኛውም መጥፎ ምኞት ጋር መታገል ያላስፈለጋቸው ይመስልሃል? እንደዚያ ሊሆን አይችልም። ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆኑም ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። አልፎ አልፎ ከመጥፎ ምኞቶች ጋር መታገል እንዳስፈለጋቸው ምንም ጥያቄ የለውም። ይህ እኛንም ሊያበረታታን ይገባል። ለምን? ምክንያቱም እየታገልከው ያለኸው መጥፎ ምኞት ምንም ይሁን ምን፣ ሌላ ክርስቲያን ይህን ምኞት አሸንፎታል። በእርግጥም ‘በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞችህ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው እንዳለ ተገንዝበህ በእምነት ጸንተህ መቆም’ ትችላለህ።—1 ጴጥ. 5:9፤ w23.01 12 አን. 15
ቅዳሜ፣ ጥር 27
በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።—ዮሐ. 16:33
ኢየሱስ ተከታዮቹን ይሖዋ እንዲጠብቃቸው ለምኗል። (ዮሐ. 17:11) ይህ ድፍረት የሚሰጠን ለምንድን ነው? ይሖዋ ከየትኛውም ጠላታችን በላይ ኃያል እንደሆነ ስለምናውቅ ነው። (1 ዮሐ. 4:4) ከይሖዋ እይታ የሚያመልጥ ነገር የለም። በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ፍርሃታችንን ማሸነፍና ደፋሮች መሆን እንደምንችል እርግጠኞች ነን። የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ለመናገር የምትሸማቀቅበት ጊዜ አለ? ‘ሌሎች ምን ይሉኛል?’ የሚለው ፍርሃት አስፋፊ ለመሆን ወይም ለመጠመቅ እርምጃ እንዳትወስድ እንቅፋት ሆኖብሃል? እንዲህ ያሉት ስሜቶች ትክክል እንደሆነ የምታውቀውን ነገር ከማድረግ እንዲያግዱህ አትፍቀድ። ወደ ይሖዋ አጥብቀህ ጸልይ። የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስፈልግህን ድፍረት እንዲሰጥህ ጠይቀው። ይሖዋ ጸሎትህን እንዴት እየመለሰልህ እንዳለ ስታይ ብርታትና ድፍረት ታገኛለህ።—ኢሳ. 41:10, 13፤ w23.01 29 አን. 12፤ 30 አን. 14
እሁድ፣ ጥር 28
አላነበባችሁም?—ማቴ. 12:3
ኢየሱስ ፈሪሳውያን ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላቸው አረዳድ የተሳሳተ እንደሆነ ለማጋለጥ “አላነበባችሁም?” የሚለውን ጥያቄ ተጠቅሟል። (ማቴ. 12:1-7) በዚያ ወቅት ፈሪሳውያኑ፣ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሰንበትን እንደጣሱ ተናግረው ነበር። በምላሹም ኢየሱስ ሁለት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎችንና በሆሴዕ ላይ የሚገኝ ጥቅስ ጠቀሰላቸው፤ በዚህ መንገድ ኢየሱስ ፈሪሳውያኑ የሰንበትን ሕግ ዓላማ እንዳልተረዱና ምሕረት እንዳላሳዩ ጠቁሟል። እነዚህ ሰዎች በሚያነቡት የአምላክ ቃል ሊቀረጹ ያልቻሉት ለምን ነበር? ምክንያቱም ኩራተኞች የነበሩ ከመሆኑም ሌላ ቃሉን ያነቡ የነበረው ሌሎችን የመተቸት ዓላማ ይዘው ነው። ይህ ዝንባሌያቸው የሚያነቡትን ነገር እንዳያስተውሉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። (ማቴ. 23:23፤ ዮሐ. 5:39, 40) ማቴዎስ 19:4-6 ላይም ኢየሱስ ፈሪሳውያኑን “አላነበባችሁም?” በማለት ጠይቋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ስለ ፍጥረት የሚገልጸውን ዘገባ ያነበቡ ቢሆንም ዘገባው አምላክ ለጋብቻ ስላለው አመለካከት የሚያስተምረውን ትምህርት አላስተዋሉም ነበር። ኢየሱስ የተናገረው ነገር መጽሐፍ ቅዱስን በትክክለኛው ዝንባሌ ማንበብ እንዳለብን ያስተምረናል። ከፈሪሳውያኑ በተቃራኒ ቅኖችና ለመማር ዝግጁዎች መሆን አለብን። w23.02 12 አን. 12-13
ሰኞ፣ ጥር 29
የማመዛዘን ችሎታ ምንጊዜም ይጠብቅሃል።—ምሳሌ 2:11
ይሖዋ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ከባድ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የሚረዱ መመሪያዎችን ይዟል። (ዘፀ. 21:28, 29፤ ዘዳ. 22:8) አንድ ሰው የሌላን ሰው ሕይወት ያጠፋው ሳያስበው ቢሆንም ድርጊቱ ከባድ መዘዝ ያስከትልበት ነበር። (ዘዳ. 19:4, 5) አንድ ሰው ሳያስበውም እንኳ በፅንስ ላይ ጉዳት ቢያደርስ ግለሰቡ እንዲቀጣ ሕጉ ያዛል። (ዘፀ. 21:22, 23) ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያሳዩት ይሖዋ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ ይፈልጋል። በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። ስለት ያላቸው ነገሮችን፣ መርዛማ ኬሚካሎችን ወይም መድኃኒቶችን በተገቢው መንገድ እናስወግዳለን፤ በተጨማሪም እንዲህ ያሉትን ነገሮች ልጆች የማይደርሱበት ቦታ እናስቀምጣለን። እሳትን፣ ትኩስ ፈሳሾችንና የተለያዩ መሣሪያዎችን ስንጠቀም ጥንቃቄ እናደርጋለን፤ ደግሞም እነዚህን ነገሮች አደጋ ሊያደርሱ በሚችሉበት ሁኔታ ትተናቸው አንሄድም። በመድኃኒት፣ በመጠጥ ወይም በእንቅልፍ እጦት ምክንያት የማመዛዘን ችሎታችን በተዛባበት ሁኔታ ወይም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በእጃችን ይዘን እየነካካን መኪና አንነዳም። w23.02 21-22 አን. 7-9
ማክሰኞ፣ ጥር 30
በገዛ ዓይኖችህ . . . ታላቁን አስተማሪህን ታያለህ።—ኢሳ. 30:20
ይሖዋ ታጋሽ፣ ደግና የሌሎችን ሁኔታ የሚረዳ አስተማሪ ነው። በተማሪዎቹ ጥሩ ጎን ላይ ትኩረት ያደርጋል። (መዝ. 130:3) ደግሞም ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንድናደርግ አይጠብቅብንም። ልዩ ስጦታ የሆነውን አንጎላችንን የፈጠረው እሱ እንደሆነ አስታውስ። (መዝ. 139:14) ፈጣሪያችን ለዘላለም መማራችንን እንድንቀጥልና ከዚህም ደስታ እንድናገኝ ይፈልጋል። ከዚህ አንጻር ከወዲሁ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ‘ጉጉት ማዳበራችን’ ጥበብ ነው። (1 ጴጥ. 2:2) ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አውጣ፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት ያወጣኸውን ፕሮግራም በጥብቅ ተከተል። (ኢያሱ 1:8) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይሖዋ ጥረትህን ስለሚባርክልህ ስለ እሱ ማንበብና መማር ይበልጥ አስደሳች እየሆነልህ ይሄዳል። እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም። እውቀት መቅሰም የሚያስገኘው ዋነኛ ጥቅም ስለ ይሖዋ ይበልጥ እንድታውቅ እንዲሁም ለእሱ ያለህ ፍቅርና በእሱ ላይ ያለህ እምነት እንዲያድግ ማስቻል ነው። (1 ቆሮ. 8:1-3) መማርህን ስትቀጥል ይሖዋ እምነት እንዲጨምርልህ አዘውትረህ ጠይቀው። (ሉቃስ 17:5) ይሖዋ እንዲህ ላሉ ጸሎቶች መልስ ይሰጣል። w23.03 10 አን. 11, 13
ረቡዕ፣ ጥር 31
ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ [ተጠቀሙበት]።—ቆላ. 4:5
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሥርዓቱን መደምደሚያ የሚጠባበቁት እጃቸውን አጣጥፈው በመቀመጥ አልነበረም። ኢየሱስ የሚሠሩት ሥራ ሰጥቷቸዋል። ምሥራቹን “በኢየሩሳሌም፣ በመላው ይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንዲሰብኩ አዟቸዋል። (ሥራ 1:6-8) የኢየሱስ ተከታዮች የተሰጣቸው ሥራ በጣም ሰፊ ነው! በዚህ ሥራ ራሳቸውን በማስጠመድ ጊዜያቸውን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቅመውበታል። ለራሳችን ትኩረት የምንሰጥበት አንዱ አቅጣጫ የጊዜ አጠቃቀማችንን ቆም ብለን ማሰብ ነው። ማናችንም ብንሆን “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ሊያጋጥሙን ይችላሉ። (መክ. 9:11) ሕይወታችን ድንገት ሊቀጭ ይችላል። የይሖዋን ፈቃድ በማድረግና ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት በማጠናከር ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። (ዮሐ. 14:21) “ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ . . . ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል። (1 ቆሮ. 15:58) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ መጨረሻው ማለትም የሕይወታችን ወይም የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ መቼም ይምጣ መቼ ምንም የሚቆጨን ነገር አይኖርም።—ማቴ. 24:13፤ ሮም 14:8፤ w23.02 18-19 አን. 12-14