የካቲት
ሐሙስ፣ የካቲት 1
እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።—ዮሐ. 15:12
የዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለው ሐሳብ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ቀጥሎ እንዳብራራው ይህ ዓይነቱ ፍቅር ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነው፤ አንድ ክርስቲያን አስፈላጊ ከሆነ ለእምነት ባልንጀራው ሲል ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ ጭምር ሊገፋፋው የሚችል የፍቅር ዓይነት ነው። የአምላክ ቃል ፍቅር ምን ያህል አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ ይጠቁማል። ብዙ ሰዎች በጣም ከሚወዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ “አምላክ ፍቅር ነው።” (1 ዮሐ. 4:8) “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ማቴ. 22:39) “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥ. 4:8) “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።” (1 ቆሮ. 13:8) እነዚህን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ጥቅሶች ይህን ግሩም ባሕርይ ማዳበርና ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ። እውነተኛ ፍቅር የሚመነጨው ከይሖዋ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማሳየት የሚችሉት የይሖዋን መንፈስና በረከት ያገኙ ሰዎች ብቻ ናቸው። (1 ዮሐ. 4:7) ታዲያ ኢየሱስ የእሱ እውነተኛ ተከታዮች እርስ በርሳቸው በሚያሳዩት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ መናገሩ ተገቢ አይደለም? ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ብዙዎች የእሱን እውነተኛ ተከታዮች በመካከላቸው ባለው እውነተኛ ፍቅር ለይተው ማወቅ ችለዋል። w23.03 27-28 አን. 5-8
ዓርብ፣ የካቲት 2
ኃጢአትሽ ይቅር ተብሎልሻል።—ሉቃስ 7:48
ይበልጥ ይቅር ባይ መሆን ያስፈልግህ ይሆን? ሌሎችን በነፃ ይቅር ስላሉና ስላላሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በማንበብና በማሰላሰል መጀመር ትችላለህ። የኢየሱስን ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ሌሎችን በነፃ ይቅር ብሏል። (ሉቃስ 7:47) እንዲሁም በስህተታቸው ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ ለማተኮር መርጧል። በአንጻሩ ግን በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ‘ሌሎችን በንቀት ዓይን ይመለከቱ’ ነበር። (ሉቃስ 18:9) በእነዚህ ምሳሌዎች ላይ ካሰላሰልክ በኋላ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ስለ ሰዎች ሳስብ የሚታየኝ ምናቸው ነው? የትኛው ባሕርያቸው ላይ ለማተኮር እመርጣለሁ?’ አንድን ግለሰብ ይቅር ማለት ከባድ ከሆነብህ የግለሰቡን መልካም ባሕርያት በዝርዝር ለመጻፍ ሞክር። ከዚያም እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ኢየሱስ ይህን ሰው እንዴት ነው የሚመለከተው? በእኔ ቦታ ቢሆን ይቅር ይለው ነበር?’ እንዲህ ማድረጋችን አመለካከታችንን እንድናስተካክል ይረዳናል። የበደለንን ሰው ይቅር ማለት መጀመሪያ ላይ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ማሻሻያ ለማድረግ መጣጣራችንን ከቀጠልን ግን በጊዜ ሂደት ይቅር ባይ መሆን እየቀለለን ይመጣል። w22.04 23 አን. 6
ቅዳሜ፣ የካቲት 3
መልአኩን ልኮ [ራእዩን] በምልክቶች ገለጠለት።—ራእይ 1:1
የራእይ መጽሐፍ የአምላክን ጠላቶች የሚገልጻቸው በምሳሌ ነው። በራእይ መጽሐፍ ላይ አንዳንድ አራዊት እንደተጠቀሱ እናነባለን። ለምሳሌ “ከባሕር ሲወጣ” የታየ አውሬ አለ። ይህ አውሬ “አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች” አሉት። (ራእይ 13:1) ይህን አውሬ ተከትሎ ደግሞ “ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ” ታይቷል። ይሄኛው አውሬ እንደ ዘንዶ የሚናገር ሲሆን “እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ያወርዳል።” (ራእይ 13:11-13) በኋላ ላይ ደግሞ ስለ ሌላ አውሬ እናነባለን፤ ይህን “ደማቅ ቀይ አውሬ” አንዲት አመንዝራ እየጋለበችው እንደሆነ ተገልጿል። እነዚህ ሦስት አራዊት የይሖዋንና የመንግሥቱን የረጅም ጊዜ ጠላቶች ይወክላሉ። ስለዚህ ማንነታቸውን ማወቃችን አስፈላጊ ነው። (ራእይ 17:1, 3) የምልክቶቹን ትርጉም መረዳት ያስፈልገናል። ለዚህ ቁልፉ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ፣ ራሱን እንዲያብራራ መፍቀድ ነው። በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ ምልክቶች ቀደም ብሎ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ ተብራርተዋል። w22.05 8-9 አን. 3-4
እሁድ፣ የካቲት 4
አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ . . . ውደድ።—ማቴ. 22:37
አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምክንያት አገልግሎታቸው ሲገደብ ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ያለብህ የአቅም ገደብ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጥህ ከሆነ ‘ይሖዋ ከእኔ የሚፈልገው ምንድን ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ይሖዋ የሚፈልገው ካለህበት ሁኔታ አንጻር ምርጥህን እንድትሰጠው ብቻ ነው። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በ80ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ እህት በ40ዎቹ ዕድሜ ሳሉ እንደነበረው ማገልገል ባለመቻላቸው ተስፋ ይቆርጡ ይሆናል። ለይሖዋ ምርጣቸውን እየሰጡት ቢሆንም እንደማይደሰትባቸው ይሰማቸዋል። ግን እውነታው እንደዚያ ነው? እስቲ አስበው። እኚህ እህት በ40ዎቹ ዕድሜ እያሉ ለይሖዋ ምርጣቸውን ይሰጡት ነበር፤ አሁንም በ80ዎቹ ዕድሜ ሆነው ምርጣቸውን እየሰጡት ነው። ስለዚህ ለይሖዋ ምርጣቸውን መስጠት አላቋረጡም ማለት ነው። ምርጣችንን ከሰጠነው ይሖዋ “ጎበዝ!” ይለናል። (ከማቴዎስ 25:20-23 ጋር አወዳድር።) ማድረግ በማንችለው ሳይሆን ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ ካተኮርን ደስታችንን መጠበቅ ቀላል ይሆንልናል። w22.04 10 አን. 2፤ 11 አን. 4-6
ሰኞ፣ የካቲት 5
[ቅድስቲቱን] ከተማ፣ አዲሲቱ [ኢየሩሳሌምን] አየሁ።—ራእይ 21:2
ራእይ ምዕራፍ 21 144,000ዎቹን “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ተብላ ከምትጠራ እጅግ ውብ ከተማ ጋር ያመሳስላቸዋል። ይህች ከተማ “የ12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች” የተጻፈባቸው 12 የመሠረት ድንጋዮች አሏት። (ራእይ 21:10-14፤ ኤፌ. 2:20) ይህች ምሳሌያዊት ከተማ ወደር የሌላት ከተማ ናት። የከተማዋ አውራ ጎዳና ንጹሕ ወርቅ ነው፤ ከዕንቁ የተሠሩ 12 በሮች አሏት፤ አጥሮቿና መሠረቶቿ በከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ ናቸው፤ የከተማዋ ልኬትም ፍጹም የተመጣጠነ ነው። (ራእይ 21:15-21) አንድ የቀረ ነገር ያለ ግን ይመስላል። ዮሐንስ ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “በከተማዋ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም፤ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክና በጉ ቤተ መቅደሷ ናቸውና። ከተማዋ የፀሐይም ሆነ የጨረቃ ብርሃን አላስፈለጋትም፤ የአምላክ ክብር ብርሃን ሰጥቷታልና፤ በጉም መብራቷ ነበር።” (ራእይ 21:22, 23) የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አባላት ከይሖዋ ጋር በቀጥታ መገናኘት ይችላሉ።—ዕብ. 7:27፤ ራእይ 22:3, 4፤ w22.05 17 አን. 14-15
ማክሰኞ፣ የካቲት 6
እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።—ቆላ. 3:13
ይሖዋ ፈጣሪያችን፣ ሕግ ሰጪያችንና ዳኛችን ብቻ ሳይሆን አፍቃሪ አባታችንም ነው። (መዝ. 100:3፤ ኢሳ. 33:22) በእሱ ላይ ኃጢአት ብንሠራም እንኳ ከልባችን ንስሐ ከገባን እኛን ይቅር ለማለት ሥልጣኑ ብቻ ሳይሆን ፍላጎቱም አለው። (መዝ. 86:5) ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “ኃጢአታችሁ እንደ ደም ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል” የሚል የሚያጽናና ዋስትና ሰጥቶናል። (ኢሳ. 1:18) ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን ሌሎችን የሚያሳዝን ነገር መናገራችን ወይም ማድረጋችን አይቀርም። (ያዕ. 3:2) ይህ ሲባል ግን ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም ማለት አይደለም። ይቅር ባዮች ከሆንን ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። (ምሳሌ 17:9፤ 19:11፤ ማቴ. 18:21, 22) ትናንሽ ቅሬታዎች በመካከላችን ሲፈጠሩ ይሖዋ ይቅር እንድንል ይፈልጋል። ደግሞም እንዲህ ማድረጋችን ተገቢ ነው። ምክንያቱም ይሖዋ “ብዙ” ጊዜ በነፃ ይቅር ይለናል።—ኢሳ. 55:7፤ w22.06 8 አን. 1-2
ረቡዕ፣ የካቲት 7
አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን [ምሰሉ]።—ዕብ. 6:12
ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ባይኖርብንም ከታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ምሳሌ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ከሁሉ የተሻለው ምሳሌያችን ኢየሱስ ነው። እኛ እንደ እሱ ፍጹማን ባንሆንም ግሩም ከሆኑት ባሕርያቱ እና ካከናወናቸው ነገሮች ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (1 ጴጥ. 2:21) የእሱን ምሳሌ በጥብቅ ለመከተል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን ይሖዋን በተሻለ መንገድ ማገልገል እንችላለን። ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ልንመስላቸው የሚገቡ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን ምሳሌ በአምላክ ቃል ውስጥ እናገኛለን። ንጉሥ ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ” በማለት ጠርቶታል። (ሥራ 13:22) እርግጥ ዳዊት ፍጹም አልነበረም። እንዲያውም ከባባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል። ያም ቢሆን ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ለምን? ምክንያቱም ሰበብ አስባብ አልደረደረም። ከዚህ ይልቅ የተሰጠውን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ተቀብሏል፤ በፈጸመው ኃጢአትም ከልቡ ተጸጽቷል። በመሆኑም ይሖዋ ይቅር ብሎታል።—መዝ. 51:3, 4, 10-12፤ w22.04 13 አን. 11-12
ሐሙስ፣ የካቲት 8
[ሰው] ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል።—ኢዮብ 2:4
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሞት ጠላት እንደሆነ ይናገራል። (1 ቆሮ. 15:25, 26) ስለ ሞት ስናስብ እንጨነቅ ይሆናል፤ በተለይ የምንወደው ሰው ወይም እኛ ራሳችን በጠና ስንታመም ሞት ይበልጥ ሊያስፈራን ይችላል። ሞት የሚያስፈራን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ የፈጠረን ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። (መክ. 3:11) ሞትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መፍራት ሕይወታችንን ሊታደግልን ይችላል። ከአመጋገብና አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጋር በተያያዘ ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ፣ ከታመምን ሕክምና እንድናገኝና መድኃኒት እንድንወስድ እንዲሁም ሕይወታችንን አላስፈላጊ አደጋ ላይ እንዳንጥል ሊያነሳሳን ይችላል። ሰይጣን ሕይወታችንን እንደምንወድ ያውቃል። ዕድሜያችንን ለማራዘም ስንል ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ጨምሮ ማንኛውንም ነገር መሥዋዕት ከማድረግ ወደኋላ እንደማንል ተናግሯል። (ኢዮብ 2:5) ሰይጣን ምንኛ ተሳስቷል! ያም ቢሆን “ለሞት የመዳረግ አቅም ያለው” ሰይጣን፣ ለሞት ያለንን ተፈጥሯዊ ፍራቻ ተጠቅሞ ይሖዋን እንድንተው ለማድረግ ይሞክራል።—ዕብ. 2:14, 15፤ w22.06 18 አን. 15-16
ዓርብ፣ የካቲት 9
ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ።—ኤፌ. 4:26
በእገዳ ሥር ስንሆን የምንሰበሰበው በትናንሽ ቡድኖች ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መመሥረት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል። እርስ በርስ ከመጣላት ይልቅ ከሰይጣን ጋር ተዋጉ። ወንድሞቻችሁ የሚሠሯቸውን ስህተቶች ችላ ብላችሁ ለማለፍ ሞክሩ። አለመግባባት ከተፈጠረ ደግሞ ችግሩን ቶሎ ለመፍታት ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 19:11) እርስ በርስ ለመረዳዳት ቅድሚያውን ውሰዱ። (ቲቶ 3:14) በአንድ የአገልግሎት ቡድን ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ለአንዲት እህት እርዳታ በማበርከታቸው መላው የአገልግሎት ቡድን ተጠቅሟል። እንደ ቤተሰብ እርስ በርስ ተቀራርበዋል። (መዝ. 133:1) መንግሥታት እገዳ በጣሉባቸው አገሮች ውስጥ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አሉ። አንዳንዶቹ በእምነታቸው ምክንያት ታስረዋል። ለእነዚህ ወንድሞች፣ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የራሳቸውን ነፃነት አደጋ ላይ ጥለው ለእነሱ መንፈሳዊ፣ ሥጋዊና ሕግ ነክ ድጋፍ ለሚሰጡ ወንድሞች መጸለይ እንችላለን። (ቆላ. 4:3, 18) የምታቀርበው ጸሎት ያለውን ኃይል ፈጽሞ አቅልለህ አትመልከት!—2 ተሰ. 3:1, 2፤ 1 ጢሞ. 2:1, 2፤ w22.12 26-27 አን. 15-16
ቅዳሜ፣ የካቲት 10
አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርም?—ሮም 2:21
ብዙውን ጊዜ ልጆች ወላጆቻቸውን ይኮርጃሉ። እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ወላጅ የለም። (ሮም 3:23) ያም ሆኖ ጥበበኛ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ለመሆን የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች ልክ እንደ ስፖንጅ ስለሆኑ ሁሉንም ነገር በቀላሉ ይይዛሉ። የምንናገረውና የምናደርገው ነገር የማይጣጣም ከሆነ ይህን መገንዘባቸው አይቀርም።” ስለዚህ ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱ ከፈለግን እኛ ራሳችን ለእሱ ያለን ፍቅር ጠንካራና በግልጽ የሚታይ ሊሆን ይገባል። ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ሊያስተምሩ የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አንድሩ የተባለ የ17 ዓመት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ ጸሎት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሁልጊዜ ይነግሩኛል። አባቴ ሁልጊዜ ማታ የራሴን ጸሎት ብጸልይም እንኳ አብሮኝ ይጸልያል። . . . አሁን ይሖዋን በነፃነት ማነጋገርና እሱን እንደ አፍቃሪ አባቴ መመልከት አይከብደኝም።” ወላጆች ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር በልጆቻችሁ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱት። w22.05 28 አን. 7-8
እሁድ፣ የካቲት 11
ጥምቀት . . . እያዳናችሁ ነው።—1 ጴጥ. 3:21
ለጥምቀት ዝግጁ ለመሆን መጀመሪያ ልናደርጋቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል አንዱ ለኃጢአታችን ከልብ ንስሐ መግባት ነው። (ሥራ 2:37, 38) እውነተኛ ንስሐ እውነተኛ ለውጥ ለማድረግ ያስችላል። እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ ትንባሆ ማጨስ ወይም ጸያፍ ንግግር ያሉ ይሖዋን የሚያሳዝኑ ልማዶችን አስወግደሃል? (1 ቆሮ. 6:9, 10፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ ኤፌ. 4:29) ለውጥ ለማድረግ መጣጣርህን አታቋርጥ። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናህን ሰው ስለዚህ ጉዳይ አነጋግረው፤ ወይም የጉባኤህን ሽማግሌዎች እንዲረዱህ አሊያም ምክር እንዲሰጡህ ጠይቃቸው። ከቤተሰቦችህ ጋር የምትኖር ወጣት ከሆንክ እንዳትጠመቅ የሚከለክልህን ማንኛውንም መጥፎ ልማድ ለማስወገድ የወላጆችህን እርዳታ ጠይቅ። ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ማዳበርህም አስፈላጊ ነው። ይህም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና ተሳትፎ ማድረግን ይጨምራል። (ዕብ. 10:24, 25) በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቃቱን ካሟላህ በኋላ ደግሞ አዘውትረህ የምትሰብክበት ፕሮግራም ይኑርህ። w23.03 10-11 አን. 14-16
ሰኞ፣ የካቲት 12
ይሖዋ አምላክ እባቡን እንዲህ አለው፦ “ይህን ስላደረግክ . . . የተረገምክ ትሆናለህ።”—ዘፍ. 3:14
በዘፍጥረት 3:14, 15 ላይ ከተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት መካከል “እባቡ” እና የእባቡ “ዘር” ይገኙበታል። እውነተኛ እባብ፣ ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ የተናገረውን ነገር ሊረዳ አይችልም። በመሆኑም ይሖዋ ፍርዱን ያስተላለፈው ማሰብ በሚችል ፍጡር ላይ መሆን አለበት። ይህ ፍጡር ማን ነው? ራእይ 12:9 ማንነቱን በግልጽ ይነግረናል። ጥቅሱ “የጥንቱ እባብ” ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ በቀጥታ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ “ዘር” የሚለውን ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። ይህም ሲባል አንዳንዶች አንድን አካል በጣም ከመምሰላቸው የተነሳ እንደ ልጆቹ ይቆጠራሉ እንደማለት ነው። ከዚህ አንጻር የእባቡ ዘር እንደ ሰይጣን ይሖዋ አምላክንና ሕዝቦቹን የሚቃወሙ መንፈሳዊ ፍጥረታትን እና ሰዎችን ያካትታል። ይህም በኖኅ ዘመን በሰማይ ላይ የነበራቸውን ቦታ የተዉትን መላእክትና እንደ አባታቸው እንደ ዲያብሎስ ዓይነት ባሕርይ ያላቸውን ክፉ ሰዎች ይጨምራል።—ዘፍ. 6:1, 2፤ ዮሐ. 8:44፤ 1 ዮሐ. 5:19፤ ይሁዳ 6፤ w22.07 15 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ የካቲት 13
ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10
ሐዋርያው ጳውሎስ ወንድሞቹን በጣም ይወዳቸው ነበር። እሱ ራሱም የተለያዩ ችግሮችን አስተናግዷል፤ በመሆኑም የእምነት ባልንጀሮቹ ፈተና ሲያጋጥማቸው ሊራራላቸውና ስሜታቸውን ሊረዳላቸው ችሏል። በአንድ ወቅት ጳውሎስ ገንዘብ ስላለቀበት ራሱንና የአገልግሎት አጋሮቹን ለማስተዳደር ሥራ መፈለግ ነበረበት። (ሥራ 20:34) ጳውሎስ ድንኳን የመሥራት ሙያ ነበረው። ቆሮንቶስ ሲደርስ መጀመሪያ ላይ እንደ እሱ ድንኳን ሠሪዎች ከሆኑት ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ይሠራ ነበር። ሆኖም “በየሰንበቱ” ለአይሁዳውያንና ለግሪካውያን ይሰብክ ነበር። ሲላስና ጢሞቴዎስ ከመጡ በኋላ ደግሞ “ጳውሎስ ቃሉን በመስበኩ ሥራ በእጅጉ ተጠመደ።” (ሥራ 18:2-5) ጳውሎስ የሕይወቱ ዋነኛ ዓላማ ይሖዋን ማገልገል መሆኑን ዘንግቶ አያውቅም። ጳውሎስ ተግቶ በመሥራት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ስለነበር ወንድሞቹንና እህቶቹን ማበረታታት ችሏል። የሕይወት ውጣ ውረድ እንዲሁም ቤተሰብን የማስተዳደር ኃላፊነታቸው “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ማለትም ከይሖዋ አምልኮ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ችላ እንዲሉ እንዳያደርጋቸው አሳስቧቸዋል። w22.08 20 አን. 3
ረቡዕ፣ የካቲት 14
ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።—ማር. 13:10
በዛሬው ጊዜ የአምላክ ፈቃድ የመንግሥቱ ምሥራች በመላው ምድር እንዲሰበክ ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ሥራው የይሖዋ ነው፤ ይህ ሥራ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ ይሖዋ የሥራው ኃላፊ አድርጎ የሾመው የሚወደውን ልጁን ነው። ብቃት ያለው መሪ በሆነው በኢየሱስ አመራር ሥር፣ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የስብከቱ ሥራ ይሖዋ በሚፈልገው መጠን እንደሚከናወን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ማቴ. 24:14) ይህን እንዴት እናውቃለን? ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ በገሊላ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ ከተወሰኑ ታማኝ ተከታዮቹ ጋር ተገናኝቶ ነበር። በዚህ ወቅት “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል” አላቸው። ቀጥሎ ምን እንዳላቸው ልብ በሉ፦ “ስለዚህ ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ።” (ማቴ. 28:18, 19) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ የተሰጠው አንዱ ሥልጣን የስብከቱን ሥራ የመምራት ኃላፊነት ነው። ይህ የስብከት ሥራ በኢየሱስ አመራር ሥር እስከ ዘመናችን ድረስ ይቀጥላል። w22.07 8 አን. 1, 3, 4
ሐሙስ፣ የካቲት 15
በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣልና፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ [ይወጣሉ]።—ዮሐ. 5:28, 29
ከመሞታቸው በፊት መልካም የሠሩ ጻድቃን ‘የሕይወት ትንሣኤ’ ያገኛሉ፤ ምክንያቱም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሰፍሯል። ይህም ሲባል በዮሐንስ 5:29 መሠረት ትንሣኤ የሚያገኙት “መልካም የሠሩ” ሰዎችና በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ የተጠቀሱት ትንሣኤ የሚያገኙ “ጻድቃን” አንድ ዓይነት ናቸው። ይህ ማብራሪያ በሮም 6:7 ላይ ካለው ሐሳብ ጋር ይስማማል፤ ጥቅሱ “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” ይላል። እነዚህ ጻድቃን ሲሞቱ ኃጢአታቸው ተሰርዞላቸዋል፤ ያስመዘገቡት የታማኝነት ታሪክ ግን አልተሰረዘም። (ዕብ. 6:10) እርግጥ ትንሣኤ ያገኙት ጻድቃን ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈ እንዲቀጥል ከፈለጉ ታማኝነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። w22.09 18 አን. 13, 15
ዓርብ፣ የካቲት 16
[የይሖዋ ሥራ] ሁሉ እምነት የሚጣልበት ነው።—መዝ. 33:4
ነቢዩ ዳንኤል እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ባቢሎናውያን በግዞት ቢወስዱትም ብዙም ሳይቆይ እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆን ረገድ ጥሩ ስም አተረፈ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር ያያቸውን ሕልሞች በይሖዋ እርዳታ በፈታበት ወቅት ደግሞ የሌሎችን አመኔታ ይበልጥ አተረፈ። (ዳን. 4:20-22, 25) ከበርካታ ዓመታት በኋላ ዳንኤል በባቢሎን በቤተ መንግሥቱ ግድግዳ ላይ የታየውን ሚስጥራዊ መልእክት በትክክል በፈታበት ወቅት እምነት የሚጣልበት መሆኑን በድጋሚ አስመሠከረ። (ዳን. 5:5, 25-29) ከጊዜ በኋላም ሜዶናዊው ዳርዮስና ባለሥልጣናቱ፣ ዳንኤል “ልዩ የሆነ መንፈስ” እንዳለው አስተውለዋል። ዳንኤል ‘እምነት የሚጣልበት እንደሆነና ምንም ዓይነት እንከንና ጉድለት እንደሌለበት’ ተናግረዋል። (ዳን. 6:3, 4) ‘የምታወቀው እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆኔ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። እምነት የሚጣልብን ሰዎች ከሆንን ለይሖዋ ውዳሴ እናመጣለን። w22.09 8-9 አን. 2-4
ቅዳሜ፣ የካቲት 17
የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።—ኤፌ. 5:1
ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ ይሖዋ ባወጣቸው መሥፈርቶች መመራታችን ይጠቅመናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እያንዳንዱ ባንክ የገንዘብን ዋጋ በተመለከተ የራሱን መሥፈርት ቢያወጣ ወይም እያንዳንዱ የሕንፃ ተቋራጭ የራሱን የልኬት መሥፈርቶች ቢያወጣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስቲ አስበው! ትርምስ ይፈጠር ነበር። ወይም ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎች ከሕክምና አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ተገቢውን መሥፈርት የማይከተሉ ከሆነ አንዳንድ ታካሚዎች ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። በእርግጥም እምነት የሚጣልባቸው መሥፈርቶች መኖራቸው ጥበቃ ያስገኝልናል። በተመሳሳይም ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ አምላክ ያወጣቸው መሥፈርቶች ጥበቃ ያስገኙልናል። ይሖዋ በእሱ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ይባርካል። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ቃል ገብቷል። (መዝ. 37:29) ሁሉም ሰው የይሖዋን መሥፈርቶች በሚከተልበት ጊዜ የሰው ዘር ምን ያህል አንድነት ያለው፣ ሰላማዊና ደስተኛ እንደሚሆን እስቲ አስበው! ይሖዋ እንዲህ ያለውን ሕይወት እንድታጣጥም ይፈልጋል። በእርግጥም እያንዳንዳችን ጽድቅን የምንወድበት አጥጋቢ ምክንያት አለን! w22.08 27-28 አን. 6-8
እሁድ፣ የካቲት 18
በሁሉም ነገር የማስተዋል ስሜትህን ጠብቅ።—2 ጢሞ. 4:5
ችግሮች ሲያጋጥሙን ለይሖዋና ለድርጅቱ ያለን ታማኝነት ሊፈተን ይችላል። እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት የምንችለው እንዴት ነው? የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ፣ ነቅተን መኖርና በእምነት ጸንተን መቆም ይኖርብናል። በመረጋጋት፣ ቆም ብለን በማሰብ እንዲሁም ነገሮችን በይሖዋ ዓይን ለማየት በመሞከር የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅ እንችላለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ስሜታችን አስተሳሰባችንን አይቆጣጠረውም። የእምነት ባልንጀራችን ምናልባትም ኃላፊነት ያለው ወንድም እንደበደለን ይሰማን ይሆናል። መቼም ግለሰቡ የበደለህ ሊጎዳህ አስቦ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (ሮም 3:23፤ ያዕ. 3:2) ያም ቢሆን ያደረገው ነገር በጣም አስከፍቶህ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ‘አንድ ወንድም እንዲህ ካደረገኝ ይሄ ምኑን የይሖዋ ድርጅት ሆነ?’ የሚል ሐሳብ ወደ አእምሮህ መጥቶ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ብለን እንድናስብ የሚፈልገው ሰይጣን ነው። (2 ቆሮ. 2:11) እንዲህ ያለው አሉታዊ አስተሳሰብ ከይሖዋና ከድርጅቱ እንድንርቅ ሊያደርገን ይችላል። ስለዚህ እንዳንመረር መጠንቀቅ ይኖርብናል። w22.11 20 አን. 1, 3፤ 21 አን. 4
ሰኞ፣ የካቲት 19
ይሖዋን ተስፋ አድርግ።—መዝ. 27:14
ይሖዋ አስደናቂ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሰጥቶናል። አንዳንዶች የማይሞት መንፈሳዊ አካል ለብሰው በሰማይ ላይ ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። (1 ቆሮ. 15:50, 53) አብዛኞቹ ሰዎች ደግሞ ፍጹም ጤንነትና ደስታ አግኝተው በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያደርጋሉ። (ራእይ 21:3, 4) ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ፣ ተስፋችንን ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተሰጠን ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ነን፤ ምክንያቱም የተስፋችን ምንጭ ይሖዋ ነው። (ሮም 15:13) ይሖዋ የገባልንን ቃል እናውቃለን፤ ቃሉን ምንጊዜም እንደሚፈጽምም እናውቃለን። (ዘኁ. 23:19) ይሖዋ ‘አደርገዋለሁ’ ያለውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ እንዳለው እርግጠኞች ነን። የሰማዩ አባታችን ይወደናል፤ እንድንታመንበትም ይፈልጋል። በይሖዋ ላይ ያለን ተስፋ ጠንካራ ከሆነ ፈተናዎችን መወጣት እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ በድፍረትና በደስታ መጠባበቅ እንችላለን። w22.10 24 አን. 1-3
ማክሰኞ፣ የካቲት 20
እነሱ ዓመፀኛ ሕዝብ፣ . . . የይሖዋን ሕግ ለመስማት እንቢተኛ የሆኑ . . . ናቸው።—ኢሳ. 30:9
ሕዝቡ ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ይሖዋ መከራ እንዲደርስባቸው እንደሚፈቅድ ኢሳይያስ ትንቢት ተናገረ። (ኢሳ. 30:5, 17፤ ኤር. 25:8-11) ደግሞም እንዳለው በባቢሎናውያን በግዞት ተወስደዋል። ይሁንና አንዳንድ ታማኝ አይሁዳውያን ነበሩ፤ ኢሳይያስም ይሖዋ አንድ ቀን መልሶ ሞገስ እንደሚያሳያቸው ነግሯቸዋል። (ኢሳ. 30:18, 19) የሆነውም ይኸው ነው። ይሖዋ የግዞት ዘመናቸው እንዲያበቃ አደረገ። ይሁንና መዳናቸው ወዲያውኑ አልመጣም። “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል” የሚለው አገላለጽ፣ እነዚህ ታማኝ ሰዎች መዳን እስኪመጣላቸው ድረስ የተወሰነ ጊዜ እንደሚያልፍ የሚያሳይ ነው። እንዲያውም የተወሰኑ ቀሪዎች ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት፣ እስራኤላውያን ለ70 ዓመት በባቢሎን በግዞት ከቆዩ በኋላ ነው። (ኢሳ. 10:21፤ ኤር. 29:10) ሕዝቡ ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ፣ ያነቡት የሐዘን እንባ በደስታ እንባ ተተካ። w22.11 9 አን. 4
ረቡዕ፣ የካቲት 21
ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው ደስተኞች ናቸው።—ማቴ. 5:10
በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እያጋጠማቸው ያለው ነገር በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያት ካጋጠማቸው ነገር ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ሐዋርያት ስለ ኢየሱስ በመስበካቸው ተሰደው ነበር። የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ሐዋርያቱ “በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ” በተደጋጋሚ አዘዋቸው ነበር። (ሥራ 4:18-20፤ 5:27, 28, 40) ሆኖም ሐዋርያቱ ‘ለሰዎች እንዲሰብኩና ስለ ክርስቶስ በተሟላ ሁኔታ እንዲመሠክሩ’ ያዘዛቸው ከዳኞቹ የሚበልጥ ሥልጣን ያለው አካል እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ሥራ 10:42) በመሆኑም ሐዋርያቱን ወክለው የሚናገሩት ጴጥሮስና ዮሐንስ፣ ከዳኞቹ ይልቅ አምላክን እንደሚታዘዙ በድፍረት ተናገሩ፤ እንዲሁም ስለ ኢየሱስ መናገራቸውን እንደማያቆሙ ገለጹ። (ሥራ 5:29) ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቃቸው የተነሳ ከተገረፉ በኋላ ሐዋርያቱ “ስለ ስሙ ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው ደስ እያላቸው” ከአይሁዳውያኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወጡ፤ መስበካቸውንም አላቆሙም!—ሥራ 5:41, 42፤ w22.10 12-13 አን. 2-4
ሐሙስ፣ የካቲት 22
ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል።—መዝ. 73:28
ስለ ይሖዋ ስንማር መጀመሪያ ላይ የምንማረው መሠረታዊ እውነቶችን እንደሆነ ግልጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ያለውን እውቀት ‘መሠረታዊ ነገር’ በማለት ጠርቶታል። እንዲህ ሲል ‘መሠረታዊ ትምህርቶችን’ ማቃለሉ አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ ለልጆች ሰውነት ገንቢ ከሆነ ወተት ጋር ማመሳሰሉ ነው። (ዕብ. 5:12፤ 6:1) ሆኖም ይህ ብቻ በቂ አይደለም፤ ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች መሠረታዊ ከሆኑት ትምህርቶች አልፈው እንዲሄዱና በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ጥልቀት ያላቸው እውነቶች እንዲማሩም አበረታቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ላሉት ጥልቀት ያላቸው ትምህርቶች ጉጉት አዳብረሃል? እድገት ለማድረግ እንዲሁም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ መማርህን ለመቀጠል ፈቃደኛ ነህ? ለአብዛኞቻችን ግን ጥናት ቀላል ነገር አይደለም። የአንተስ ሁኔታ እንዴት ነው? ትምህርት ቤት ሳለህ የማንበብና የማጥናት ክህሎትህን በደንብ አዳብረሃል? ማጥናት አስደሳችና ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማሃል? ወይስ ‘መጽሐፍ በማንበብ መማር የምችል ዓይነት ሰው አይደለሁም’ ብለህ ደምድመሃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ይሖዋ ግን ሊረዳህ ይችላል። እሱ ፍጹምና ከማንም የተሻለ አስተማሪ ነው። w23.03 9-10 አን. 8-10
ዓርብ፣ የካቲት 23
እናንተን ሊያድን የሚችለውን በውስጣችሁ የሚተከለውን ቃል በገርነት ተቀበሉ።—ያዕ. 1:21
ገር ከሆንን የአምላክ ቃል በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ እንፈቅዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምሕረት፣ ስለ ርኅራኄና ስለ ፍቅር የሚያስተምረው ትምህርት ሊቀርጸን የሚችለው ኩራትንና የተቺነት ዝንባሌን ካስወገድን ብቻ ነው። ሌሎችን የምንይዝበት መንገድ የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን እየፈቀድን ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ሊጠቁም ይችላል። ፈሪሳውያኑ የአምላክ ቃል ወደ ልባቸው ዘልቆ እንዲገባ ስላልፈቀዱ “ምንም በደል ባልሠሩት ላይ [ይፈርዱ]” ነበር። (ማቴ. 12:7) በተመሳሳይ እኛም ሌሎችን የምናይበትና የምንይዝበት መንገድ የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን መፍቀድ አለመፍቀዳችንን ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሌሎች ጥሩ ጎን ከመናገር ይልቅ ደካማ ጎናቸውን መናገር ይቀናናል? መሐሪዎችና ይቅር ለማለት ዝግጁ ነን ወይስ ሌሎችን መተቸትና በእነሱ ላይ ቂም መያዝ ይቀናናል? በዚህ መንገድ ራሳችንን መመርመራችን የምናነበው ነገር አስተሳሰባችንን፣ ስሜታችንንና ድርጊታችንን እንዲቀርጸው እየፈቀድን መሆን አለመሆኑን ሊጠቁም ይችላል።—1 ጢሞ. 4:12, 15፤ ዕብ. 4:12፤ w23.02 12 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ የካቲት 24
“አትፍራ። እረዳሃለሁ” የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁ።—ኢሳ. 41:13
የአርማትያሱ ዮሴፍን ምሳሌ እንመልከት። በአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ውስጥ የተከበረ ሰው ነበር። የአይሁድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሆነው የሳንሄድሪን አባልም ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ዮሴፍ ደፋር አልነበረም። “ዮሴፍ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። ሆኖም አይሁዳውያንን ይፈራ ስለነበር ይህን ለማንም አልተናገረም” በማለት ዮሐንስ ተናግሯል። (ዮሐ. 19:38) ዮሴፍ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ቢኖረውም በኢየሱስ ማመኑን ከሌሎች ደብቆ ነበር። ይህን ያደረገው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን የተከበረ ቦታ እንዳያጣ ፈርቶ መሆን አለበት። ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ዮሴፍ ‘ደፍሮ ወደ ጲላጦስ እንደገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው እንደጠየቀ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ማር. 15:42, 43) በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የኢየሱስ ተከታይ እንደሆነ በይፋ ታወቀ። አንተስ እንደ ዮሴፍ የሰው ፍርሃት አሽመድምዶህ ያውቃል? w23.01 30 አን. 13-14
እሁድ፣ የካቲት 25
አብረውህ ያሉ ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ ዘወትር በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙት አገልጋዮችህም እጅግ ደስተኞች ናቸው!—1 ነገ. 10:8
እስራኤላውያን በሰለሞን ግዛት ሥር ስላገኙት ሰላምና ብልጽግና የሚገልጸው ወሬ ወደ ሳባ ንግሥት ጆሮ ደረሰ። በሩቅ አገር የምትኖረው ይህች ንግሥት ሁኔታውን በዓይኗ ማየት ስለፈለገች ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። (1 ነገ. 10:1) የሰለሞንን መንግሥት ከቃኘች በኋላ ከላይ የተጠቀሱትን ቃላት ተናገረች። ሆኖም በሰለሞን የግዛት ዘመን የነበረው ሁኔታ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ግዛት ሥር ለሰው ልጆች ከሚያደርገው ነገር ጋር ሲወዳደር የቅምሻ ያህል ብቻ ነው። ኢየሱስ በሁሉም መንገድ ከሰለሞን ይበልጣል። ሰለሞን ፍጹም ያልሆነ ሰው ነበር፤ ከባድ ስህተቶችንም ሠርቷል። በእነዚህ ስህተቶች ምክንያት በአምላክ ሕዝቦች ላይ መከራ አምጥቷል። ኢየሱስ ግን ፈጽሞ ስህተት የማይሠራ ፍጹም ንጉሥ ነው። (ሉቃስ 1:32፤ ዕብ. 4:14, 15) ክርስቶስ መቼም ቢሆን ኃጢአት እንደማይሠራ እንዲሁም ታማኝ ተገዢዎቹን የሚጎዳ ምንም ነገር እንደማያደርግ አስመሥክሯል። በእርግጥም ኢየሱስ ንጉሣችን በመሆኑ ልዩ ክብር ይሰማናል። w22.12 11 አን. 9-10
ሰኞ፣ የካቲት 26
ተግተው ስለሚጠብቋችሁ . . . በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ።—ዕብ. 13:17
በምንኖርበት አካባቢ ወረርሽኝ ቢከሰት ምን ማድረግ ይኖርብናል? እጃችንን እንደ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀታችንን እንደ መጠበቅ፣ ማስክ እንደ ማድረግና የበሽታው ምልክት ከታየብን ተገልለን እንደ መቆየት ያሉ መመሪያዎችን ልንታዘዝ ይገባል። እነዚህን መመሪያዎች ለመታዘዝ ፈጣን መሆናችን አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ ምን ያህል አድናቆት እንዳለን ያሳያል። ድንገተኛ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት ከወዳጆቻችን፣ ከጎረቤቶቻችንና ከመገናኛ ብዙኃን የተዛቡ መረጃዎችን ልንሰማ እንችላለን። በዚህ ጊዜ “ቃልን ሁሉ” ከማመን ይልቅ መንግሥትና የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የተሻለ ተአማኒነት ያለው መረጃ ማዳመጣችን ተገቢ ነው። (ምሳሌ 14:15) የበላይ አካሉና ቅርንጫፍ ቢሮዎች የጉባኤ ስብሰባዎችንና የስብከቱን ሥራ በተመለከተ መመሪያ ከመስጠታቸው በፊት ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የቻሉትን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ያሉ መመሪያዎችን መታዘዛችን ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከአደጋ ይጠብቃል። በተጨማሪም ጉባኤው በማኅበረሰቡ ዘንድ ጥሩ ስም እንዲያተርፍ ያስችላል።—1 ጴጥ. 2:12፤ w23.02 23 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ የካቲት 27
ይሰማሉ፤ እንዲሁም . . . አምላካችሁን ይሖዋን መፍራት ይማራሉ።—ዘዳ. 31:13
እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡ የሰፈሩት በጣም ሰፊ የሆነ ቦታ ላይ ነበር። ይህ ሁኔታ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ እስራኤላውያን በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ስለሚኖሩ እስራኤላውያን ሁኔታ ማሰባቸውን እንዲያቆሙ ሊያደርግ የሚችል ነበር። ይሖዋ ግን እስራኤላውያን በተለያዩ አጋጣሚዎች አንድ ላይ ተሰብስበው በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ ሲነበብና ሲብራራ የሚያዳምጡበት ዝግጅት አደረገ። (ዘዳ. 31:10-12፤ ነህ. 8:2, 8, 18) አንድ ታማኝ እስራኤላዊ ኢየሩሳሌም ደርሶ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ፣ ምናልባትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የእምነት ባልንጀሮቹን ሲያይ ምን ሊሰማው እንደሚችል አስቡ! በዚህ መንገድ ይሖዋ ሕዝቦቹ አንድ ሆነው እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። በኋላም የክርስቲያን ጉባኤ ሲቋቋም ጉባኤው የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የተለያየ አስተዳደግና የኑሮ ደረጃ ያላቸው ወንዶችና ሴቶችን ያቀፈ ሆነ። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች እውነተኛውን አንድ አምላክ በአንድነት ማምለክ ችለዋል። በኋላ አማኞች የሆኑ ሰዎች የአምላክን ቃል ለመረዳት የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እርዳታ መቀበልና ከእነሱ ጋር አብረው መሰብሰብ ያስፈልጋቸው ነበር።—ሥራ 2:42፤ 8:30, 31፤ w23.02 3 አን. 7
ረቡዕ፣ የካቲት 28
[ይህ] የዘላለም ሕይወት ነው።—ዮሐ. 17:3
ይሖዋ እሱን የሚታዘዙ ሰዎች “የዘላለም ሕይወት” እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። (ሮም 6:23) ይሖዋ በሰጠን ተስፋ ላይ ስናሰላስል ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። እስቲ አስቡት፦ የሰማዩ አባታችን በጣም ስለሚወደን ፈጽሞ ከእሱ ሳንለይ መኖር የምንችልበት አጋጣሚ ከፍቶልናል። አምላክ የሰጠን የዘላለም ሕይወት ተስፋ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። ጠላቶቻችን እንደሚገድሉን ቢዝቱብን እንኳ አቋማችንን አናላላም። ለምን? አንዱ ምክንያት፣ ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ከሞትን እሱ ከሞት እንደሚያስነሳንና ዳግመኛ ያለመሞት ተስፋ እንደሚሰጠን ስለምናውቅ ነው። (ዮሐ. 5:28, 29፤ 1 ቆሮ. 15:55-58፤ ዕብ. 2:15) ይሖዋ ለዘላለም ሊያኖረን እንደሚችል እናውቃለን፤ ምክንያቱም እሱ የሕይወት ምንጭ ከመሆኑም ሌላ ለዘላለም ይኖራል። (መዝ. 36:9) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ እንደሌለው ያሳያል።—መዝ. 90:2፤ 102:12, 24, 27፤ w22.12 2 አን. 1-3
ሐሙስ፣ የካቲት 29
ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት?—ሮም 8:35
የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ፈተናዎች የሚያጋጥሙን መሆኑ አያስገርመንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት” እንዳለብን እንገነዘባለን። (ሥራ 14:22) በተጨማሪም የሚያጋጥሙን አንዳንዶቹ ችግሮች ሙሉ በሙሉ የሚፈቱት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን። በዚያ ጊዜ “ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) ይሖዋ ምንም ዓይነት ፈተና እንዳይደርስብን አይከላከልልንም። ሆኖም ፈተናዎቹን በጽናት እንድንቋቋማቸው ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን እንዳላቸው ልብ እንበል። በመጀመሪያ እሱና ወንድሞቹ ያጋጠሟቸውን የተለያዩ ፈተናዎች ዘረዘረ። ከዚያም “በወደደን በእሱ አማካኝነት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ በድል አድራጊነት እንወጣለን” አለ። (ሮም 8:36, 37) ከዚህ እንደምንረዳው፣ የሚደርስብን ፈተና ገና ባያበቃም እንኳ ይሖዋ ስኬታማ እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። w23.01 14 አን. 1-2