የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es24 ገጽ 108-118
  • ኅዳር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኅዳር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ ኅዳር 1
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 2
  • እሁድ፣ ኅዳር 3
  • ሰኞ፣ ኅዳር 4
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 5
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 6
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 7
  • ዓርብ፣ ኅዳር 8
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 9
  • እሁድ፣ ኅዳር 10
  • ሰኞ፣ ኅዳር 11
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 12
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 13
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 14
  • ዓርብ፣ ኅዳር 15
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 16
  • እሁድ፣ ኅዳር 17
  • ሰኞ፣ ኅዳር 18
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 19
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 20
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 21
  • ዓርብ፣ ኅዳር 22
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 23
  • እሁድ፣ ኅዳር 24
  • ሰኞ፣ ኅዳር 25
  • ማክሰኞ፣ ኅዳር 26
  • ረቡዕ፣ ኅዳር 27
  • ሐሙስ፣ ኅዳር 28
  • ዓርብ፣ ኅዳር 29
  • ቅዳሜ፣ ኅዳር 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
es24 ገጽ 108-118

ኅዳር

ዓርብ፣ ኅዳር 1

ሌሎችን የሚያንጽ . . . መልካም ቃል ብቻ እንጂ የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።—ኤፌ. 4:29

ስድብ ከክርስቲያኖች አንደበት ጨርሶ ሊወጣ አይገባም። ሆኖም አንዳንድ የንግግር ዓይነቶች በቀጥታ ስድብ ላይመስሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሌሎች ባሕሎች፣ ዘሮች ወይም ብሔሮች ስናወራ አንዱን ከሌላው ዝቅ እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። በሽሙጥ በመናገር ሌሎችን እንዳንጎዳም መጠንቀቅ አለብን። ንግግርህ የሚያንጽ ይሁን። ከመተቸት ወይም ከማጉረምረም ይልቅ ማመስገን የሚቀናህ ሁን። እስራኤላውያን አመስጋኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሷቸው ብዙ ነገሮች ነበሯቸው፤ እነሱ ግን ነጋ ጠባ ያጉረመርሙ ነበር። የአጉረምራሚነት መንፈስ ይጋባል። አሥሩ ሰላዮች ይዘው የመጡት መጥፎ ወሬ ያስከተለውን መጥፎ ውጤት ታስታውሳለህ፤ በእነሱ የተነሳ ‘እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴ ላይ ያጉረመርሙ ጀመር።’ (ዘኁ. 13:31 እስከ 14:4) በሌላ በኩል ደግሞ ማመስገን በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። እንግዲያው ሌሎችን ከልብህ ለማመስገን አጋጣሚዎች ፈልግ። w22.04 8 አን. 16-17

ቅዳሜ፣ ኅዳር 2

ስወለድ ጀምሮ ለአንተ በአደራ ተሰጠሁ፤ ከእናቴ ማህፀን ጀምሮ አንተ አምላኬ ነህ።—መዝ. 22:10

ከጥንት ዘመን አንስቶ ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወጣቶች ወዳጆቹ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። የእናንተም ልጆች ከፈለጉ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ይሖዋ ሊረዳቸው ይችላል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ልጆቻችሁ ከእውነት ቤት ቢርቁም እንኳ ይሖዋ እነሱን በፍቅር መከታተሉን ይቀጥላል። (መዝ. 11:4) “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” እንዳላቸው በትንሹ እንኳ ካሳዩ እነሱን ለመርዳት ፈጣን እርምጃ ይወስዳል። (ሥራ 13:48፤ 2 ዜና 16:9) ልጆቻችሁ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው ትክክለኛውን ቃል በትክክለኛው ጊዜ እንድትናገሩ ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 15:23) ወይም ደግሞ በጉባኤያችሁ ያለ አንድ አሳቢ ወንድም ወይም እህት ለልጃችሁ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡት ሊያነሳሳቸው ይችላል። ልጆቻችሁ አዋቂ ከሆኑ በኋላም እንኳ ይሖዋ ልጅ ሳሉ ያስተማራችኋቸውን ነገር እንዲያስታውሱ ሊረዳቸው ይቻላል። (ዮሐ. 14:26) በቃል እና በምግባር ልጆቻችሁን ማሠልጠናችሁን ከቀጠላችሁ ይሖዋ ጥረታችሁን ይባርክላችኋል። w22.04 21 አን. 18

እሁድ፣ ኅዳር 3

ዘንዶው . . . እጅግ [ተቆጣ]።—ራእይ 12:17

ሰይጣን ወደ ሰማይ የሚሄድበት መንገድ እንደተዘጋ ስላወቀ ቁጣውን ምድር ላይ ወዳሉት ቅቡዓን ቀሪዎች አዞረ፤ እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ የአምላክ መንግሥት ወኪሎች ሲሆኑ “ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ” ተሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮ. 5:20፤ ኤፌ. 6:19, 20) በ1918 ሥራውን የሚመሩት ስምንት ወንድሞች በሐሰት ተከሰሱ፤ እያንዳንዳቸውም የረጅም ዓመት እስራት ተፈረደባቸው። የእነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሥራ ‘የሞተ’ ያህል ነበር። (ራእይ 11:3, 7-11) ሆኖም በ1919 መጀመሪያ ላይ እነዚያ ቅቡዓን ወንድሞች ከእስር ተፈቱ፤ በኋላም ከተወነጀሉበት ክስ ነፃ ተደረጉ። ወንድሞች ወዲያውኑ ወደ ሥራ ገቡ፤ ወደ መንግሥቱ ሥራ። ሆኖም ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት በዚህ አላቆመም። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሰይጣን በሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ላይ የስደት “ወንዝ” እየለቀቀ ነው። (ራእይ 12:15) በእርግጥም እያንዳንዳችን “ጽናትና እምነት ማሳየት [የሚያስፈልገን] እዚህ ላይ ነው።”—ራእይ 13:10፤ w22.05 5-6 አን. 14-16

ሰኞ፣ ኅዳር 4

የታተሙትን ሰዎች ቁጥር ሰማሁ፤ ቁጥራቸው 144,000 [ነበር]።—ራእይ 7:4

ሐዋርያው ዮሐንስ የይሖዋን አገዛዝ የሚደግፉና የዘላለም ሕይወት ሽልማት የሚሰጣቸው ሁለት ቡድኖች በራእይ ተመልክቷል። የመጀመሪያው ቡድን አባላት 144,000 ናቸው። የሚወሰዱት ከምድር ሲሆን ሰማይ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የአምላክ መንግሥት ክፍል ይሆናሉ። ከእሱ ጋር ሆነው ምድርን ያስተዳድራሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:3, 4) ዮሐንስ በራእዩ ላይ በሰማይ በጽዮን ተራራ ላይ ከኢየሱስ ጋር ቆመው አይቷቸዋል። (ራእይ 14:1) ባለፉት ዘመናት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የ144,000ዎቹ ክፍል እንዲሆኑ ሲመረጡ ቆይተዋል። (ሉቃስ 12:32፤ ሮም 8:17) ሆኖም በመጨረሻዎቹ ቀናት በምድር ላይ ቀሪዎች ወይም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ብቻ በሕይወት እንደሚኖሩ ለዮሐንስ ተነግሮታል። (ራእይ 12:17) ታላቁ መከራ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም እነዚህ ቀሪዎች ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ፤ እዚያም ታማኝ ሆነው ምድራዊ ሕይወታቸውን ካጠናቀቁት ከሌሎቹ የ144,000 አባላት ጋር ይቀላቀላሉ። ከዚያም ከኢየሱስ ጋር የአምላክ መንግሥት ተባባሪ ገዢዎች ይሆናሉ።—ማቴ. 24:31፤ ራእይ 5:9, 10፤ w22.05 16 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ ኅዳር 5

ትእዛዛቴን [ስማ]።—ኢሳ. 48:18

ኢየሱስ ተከታዮቹን ለራሳቸው ተገቢ አመለካከት እንዲኖራቸው አስተምሯቸዋል። “የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 10:30) ይህ ሐሳብ በተለይ ራሳችንን ከሌሎች ዝቅ አድርገን የመመልከት ዝንባሌ ካለን በጣም ያጽናናናል። የሰማዩ አባታችን ስለ እኛ በጥልቅ እንደሚያስብና በእሱ ዘንድ ዋጋ እንዳለን ያረጋግጥልናል። የይሖዋ አገልጋዮች ለመሆን ወይም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት ለማግኘት እንደማንበቃ ፈጽሞ ልናስብ አይገባም፤ እንዲህ ማድረግ በይሖዋ ፍርድ ላይ ጥያቄ እንደማንሳት ይሆናል። ከ15 ዓመታት በፊት መጠበቂያ ግንብ ስለ ራሳችን የሚከተለው ዓይነት ተገቢ አመለካከት እንዲኖረን አበረታቶ ነበር፦ “በእርግጥም ትዕቢተኞች እስክንሆን ድረስ ስለ ራሳችን ከልክ ያለፈ ግምት ማሳደር አይኖርብንም፤ እንዲሁም ምንም እንደማንጠቅም በማሰብም ወደ ሌላው ጽንፍ መሄድ አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ የእኛ ዓላማ የራሳችንን ጥንካሬ እንዲሁም ድክመት በማወቅ ምክንያታዊ አመለካከት ማዳበር መሆን ይኖርበታል። w22.05 24-25 አን. 14-16

ረቡዕ፣ ኅዳር 6

ይህን ልመና የማቀርበው . . . ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው።—ዮሐ. 17:21

እያንዳንዳችን ለዚህ አንድነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው? ሰላም ፈጣሪዎች በመሆን ነው። (ማቴ. 5:9፤ ሮም 12:18) በጉባኤ ውስጥ ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ባደረግን ቁጥር የመንፈሳዊው ገነት ውበት እንዲደምቅ እናደርጋለን። በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው ወደ ንጹሕ አምልኮ የሳበው ይሖዋ እንደሆነ አንዘነጋም። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ እንደ ውድ አድርጎ በሚመለከታቸው አገልጋዮቹ መካከል ያለውን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር ተግተን ስንሠራ ሲመለከት ምን ያህል እንደሚደሰት እስቲ አስቡት! (ኢሳ. 26:3፤ ሐጌ 2:7) አምላክ ለአገልጋዮቹ ከሚሰጠው በረከት የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በአምላክ ቃል ውስጥ የምናጠናውን ነገር ልናሰላስልበት ይገባል። በዚህ መልኩ ማጥናታችንና ማሰላሰላችን የተለያዩ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድናዳብር ይረዳናል፤ እነዚህ ባሕርያት በጉባኤ ውስጥ ‘በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችን ከልብ ለመዋደድ’ ያነሳሱናል።—ሮም 12:10፤ w22.11 12-13 አን. 16-18

ሐሙስ፣ ኅዳር 7

በደላቸውን ይቅር እላለሁና፤ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም።—ኤር. 31:34

ይሖዋ ይቅር እንዳለን አምነን ስንቀበል “የመታደስ ዘመን” ይመጣልናል፤ በመሆኑም የአእምሮ ሰላምና ንጹሕ ሕሊና እናገኛለን። እንዲህ ያለው ይቅርታ ሊመጣ የሚችለው ከሰዎች ሳይሆን ‘ከይሖዋ ዘንድ’ ብቻ ነው። (ሥራ 3:19) ይሖዋ ይቅር ሲለን፣ ኃጢአቱ ያልተፈጸመ ያህል ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና ሙሉ በሙሉ ያድሰዋል። ይሖዋ አንዴ ይቅር ካለን በኋላ በዚያ ኃጢአት ድጋሚ አይጠይቀንም ወይም አይቀጣንም። (ኢሳ. 43:25) “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ” ይሖዋ ኃጢአታችንን ከእኛ ያርቃል። (መዝ. 103:12) የይሖዋ ይቅርታ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ስናሰላስል በአመስጋኝነትና በአድናቆት ስሜት እንሞላለን። (መዝ. 130:4) ይሖዋ ይቅር ለማለት የሚወስነው የኃጢአቱን ክብደት መሠረት አድርጎ አይደለም። ይሖዋ አንድን ሰው ይቅር ለማለት የሚወስነው ፈጣሪ፣ ሕግ ሰጪ እና ዳኛ በመሆኑ ያለውን እውቀት መሠረት አድርጎ ነው። w22.06 5 አን. 12-14

ዓርብ፣ ኅዳር 8

ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።—ዕብ. 11:6

ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ሁሉ ግሩም ተስፋ ዘርግቶላቸዋል። በቅርቡ ሕመምን፣ ሐዘንንና ሞትን ያስወግዳል። (ራእይ 21:3, 4) እሱን ተስፋ የሚያደርጉ “የዋሆች” ምድርን ገነት እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። (መዝ. 37:9-11) በተጨማሪም ከአሁኑ እጅግ በላቀ ሁኔታ እያንዳንዳችን ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲኖረን ይረዳናል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ይሁንና ይሖዋ የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም ለማመን የሚያበቃ ምን ምክንያት አለን? ይሖዋ መቼም ቢሆን ቃሉን አያጥፍም። በመሆኑም ‘ይሖዋን ተስፋ ለማድረግ’ የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለን። (መዝ. 27:14) አምላካችን ዓላማውን እስኪፈጽም ድረስ በትዕግሥትና በደስታ በመጠባበቅ ይሖዋን ተስፋ እንደምናደርግ እናሳያለን። (ኢሳ. 55:10, 11) ይሖዋ “ከልብ ለሚፈልጉት” ወሮታቸውን እንደሚከፍላቸው በመተማመን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንጽና። w22.06 20 አን. 1፤ 25 አን. 18

ቅዳሜ፣ ኅዳር 9

አባታችሁ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።—ማቴ. 6:8

ይሖዋ የቤተሰባችን ራስ እንደመሆኑ መጠን በ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ላይ ካስጻፈው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ እኛንም ሆነ ቤተሰባችንን እንደሚወደን የምንተማመን ከሆነ የሚያስፈልገንን ነገር እናጣለን ብለን እንድንጠራጠር የሚያደርገን ምንም ምክንያት የለም። (ማቴ. 6:31-33) ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ሊያሟላልን ይፈልጋል። ደግሞም አፍቃሪና ለጋስ አምላክ ነው! ምድርን ሲፈጥር ለመኖር የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች በመስጠት ብቻ አልተወሰነም። በፍቅር ተነሳስቶ በደስታ እንድንሞላ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮችን ፈጥሮልናል። (ዘፍ. 2:9) አንዳንድ ጊዜ ያለን ገንዘብ ከመተዳደሪያ የማያልፍ ቢሆንም እንኳ ቢያንስ መተዳደሪያችንን እንዳላጣን ማስታወስ ይኖርብናል። ይህ የሆነው ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር ስላሟላልን ነው። (ማቴ. 6:11) በአሁኑ ጊዜ መሥዋዕት የምናደርገው ማንኛውም ቁሳዊ ነገር አፍቃሪው አምላካችን ይሖዋ አሁንም ሆነ ወደፊት ከሚሰጠን በረከት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል።—ኢሳ. 65:21, 22፤ w22.06 15 አን. 7-8

እሁድ፣ ኅዳር 10

ጠንካራ ምግብ [ለጎልማሳ] ሰዎች ነው።—ዕብ. 5:14

ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ የሚያስፈልጋቸው አዲሶች ብቻ አይደሉም። ሁላችንም ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘነውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋላችን “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት” እንድንችል እንደሚረዳን ገልጿል። የሰዎች ሥነ ምግባር እጅግ ባዘቀጠበት በዚህ ዘመን በይሖዋ መሥፈርቶች መመራት ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ኢየሱስ ገንቢ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ የሚያስፈልገንን ብርታት እንድናገኝ ያደርጋል። የዚህ ምግብ ምንጭ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ለአምላክ ስም የሚገባውን ክብር እንሰጣለን። (ዮሐ. 17:6, 26) ለምሳሌ በ1931 “የይሖዋ ምሥክሮች” የሚለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስም መጠቀም ጀምረናል፤ በዚህ መንገድ ለአምላክ ስም ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥና በእሱ ስም መታወቅ እንደምንፈልግ አሳይተናል። (ኢሳ. 43:10-12) ከዚህም ሌላ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስም በቃሉ ውስጥ በተገቢው ቦታ ሁሉ እንዲመለስ አድርጓል። w22.07 11 አን. 11-12

ሰኞ፣ ኅዳር 11

ቃልህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።—መዝ. 119:105

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራችም ያካትታል። ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የሚናገረውን እውነት ከተደበቀ ሀብት ጋር አመሳስሎታል። በማቴዎስ 13:44 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ ከተደበቀ ውድ ሀብት ጋር ይመሳሰላል፤ አንድ ሰው ባገኘው ጊዜ ሸሸገው፤ ከመደሰቱም የተነሳ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ እርሻውን ገዛው።” ሰውየው በወቅቱ ያንን ውድ ሀብት እየፈለገ እንዳልነበር ልብ በል። ሆኖም ሲያገኘው ያንን ውድ ሀብት እጁ ለማስገባት ሲል ትልቅ መሥዋዕት ከፍሏል። እንዲያውም ያለውን ሁሉ ሸጧል። ለምን? ያ ሀብት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ስለተገነዘበ ነው። ይህ ዓለም የሚያቀርብልን ማንኛውም ነገር በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በማገልገል ከምናገኘው ደስታ እንዲሁም ወደፊት በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የዘላለም ሕይወት ከማግኘት ተስፋችን ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና የመመሥረት መብት ምንም ዓይነት መሥዋዕት ቢከፈልለት የሚያስቆጭ አይደለም። ‘እሱን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ ከምንም በላይ ያስደስተናል።—ቆላ. 1:10፤ w22.08 15 አን. 8-9፤ 17 አን. 12

ማክሰኞ፣ ኅዳር 12

እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?—ዘፍ. 39:9

ዮሴፍ፣ አምላኩ ምንዝርን “እጅግ መጥፎ ድርጊት” አድርጎ እንደሚመለከተው ያወቀው እንዴት ነው? “አታመንዝር” የሚል ግልጽ ትእዛዝ የያዘው የሙሴ ሕግ የተጻፈው ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ ነው። (ዘፀ. 20:14) ያም ቢሆን ዮሴፍ ይሖዋን በደንብ ስለሚያውቀው ስለ ምንዝር ምን እንደሚሰማው ተገንዝቦ ነበር። ለምሳሌ ይሖዋ የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ጥምረት አድርጎ እንደሆነ ዮሴፍ እንደሚያውቅ ጥያቄ የለውም። በተጨማሪም ቅድመ አያቱን ሣራን ሌሎች ወንዶች ሊወስዷት ሲሉ ይሖዋ ሁለት ጊዜ ጣልቃ ገብቶ እንደጠበቃት ዮሴፍ ሰምቶ መሆን አለበት። (ዘፍ. 2:24፤ 12:14-20፤ 20:2-7) ዮሴፍ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ በማሰላሰል በአምላክ ዓይን ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች ማስተዋል ችሏል። ዮሴፍ አምላኩን ይወድ ስለነበር ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ፍቅር ነበረው፤ እንዲሁም በእነዚህ መሥፈርቶች ለመመራት ቆርጦ ነበር። w22.08 26 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ኅዳር 13

በምድር አፈር ውስጥ ካንቀላፉትም መካከል ብዙዎቹ ይነሳሉ፤ አንዳንዶቹ ለዘላለም ሕይወት።—ዳን. 12:2

ይህ ትንቢት ቀደም ሲል እናስብ እንደነበረው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ የሚከናወነውን ምሳሌያዊ ትንሣኤ ማለትም የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ማንሰራራታቸውን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሐሳብ የሚናገረው በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚከናወነው የሙታን ትንሣኤ ነው። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደረገን ምንድን ነው? “አፈር” የሚለው ቃል በኢዮብ 17:16 ላይ ‘መቃብርን’ ለማመልከት ተሠርቶበታል። በመሆኑም ዳንኤል 12:2 የሚናገረው የመጨረሻዎቹ ቀናት ካበቁና የአርማጌዶን ጦርነት ከተካሄደ በኋላ ስለሚኖረው የሙታን ትንሣኤ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ይሁንና ዳንኤል 12:2 አንዳንዶች “ለዘላለም ሕይወት” እንደሚነሱ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል ይሖዋንና ኢየሱስን የሚያውቁ ወይም ማወቃቸውን የሚቀጥሉ እንዲሁም በ1,000 ዓመቱ ወቅት እነሱን የሚታዘዙ ሰዎች በመጨረሻ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ ማለት ነው።—ዮሐ. 17:3፤ w22.09 21-22 አን. 6-7

ሐሙስ፣ ኅዳር 14

[ፍቅር] ሁሉን ያምናል።—1 ቆሮ. 13:7

እንዲህ ሲባል ይሖዋ ሌሎችን በጭፍን እንድናምን ይጠብቅብናል ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሌሎች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን ካስመሠከሩ እንድናምናቸው ይጠብቅብናል። በወንድሞቻችን ላይ እምነት መጣል ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እነሱን በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስትገናኙ ከእነሱ ጋር ተነጋገሩ። አብራችኋቸው አገልግሉ። በትዕግሥት ያዟቸው፤ እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ ስጧቸው። እርግጥ ነው፣ በቅርቡ ለተዋወቃችሁት አንድ ክርስቲያን ሁሉንም የግል ጉዳዮቻችሁን አትነግሩት ይሆናል። ቅርበታችሁ እየጨመረ ሲሄድ ግን ስሜታችሁን አውጥታችሁ መናገር ይበልጥ ቀላል ሊሆንላችሁ ይችላል። (ሉቃስ 16:10) ይሁንና አንድ ወንድም የእናንተን አመኔታ ቢያጓድልስ? በእሱ ላይ ተስፋ ለመቁረጥ አትቸኩሉ። ከዚህ ይልቅ ለጉዳዩ ጊዜ ስጡት። በተጨማሪም የጥቂቶች ምግባር በወንድሞቻችሁ ላይ ያላችሁን እምነት እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ። w22.09 4 አን. 7-8

ዓርብ፣ ኅዳር 15

የይሖዋ ዓይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመላለሳሉ።—2 ዜና 16:9

ሚክያስ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ ኃላፊነት ያላቸው አንዳንድ ወንድሞች አግባብ ያልሆነ ድርጊት እንደፈጸሙበት ተሰምቶት ነበር። ያም ቢሆን የማስተዋል ስሜቱን ጠብቋል፤ ስሜቱንም ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል። ወደ ይሖዋ አዘውትሮ በመጸለይ ቅዱስ መንፈሱንና ለመጽናት የሚያስችለውን ኃይል እንዲሰጠው ይለምን ነበር። ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ከጽሑፎቻችን ላይ ለማግኘትም ጥረት አድርጓል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት እንደበደሉህ ከተሰማህ ለመረጋጋትና በውስጥህ ያለውን ማንኛውንም አሉታዊ ስሜት ለመቆጣጠር ጥረት አድርግ። ግለሰቡ እንደዚያ እንዲናገር ወይም እንዲያደርግ ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ ላታውቅ ትችላለህ። በመሆኑም ወደ ይሖዋ በመጸለይ ራስህን በግለሰቡ ቦታ ለማስቀመጥ እንዲረዳህ ጠይቀው። የእምነት ባልንጀራህ የበደለህ ሆን ብሎ ሊጎዳህ ፈልጎ እንዳልሆነ በማሰብ በደሉን ለመተው ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 19:11) ይሖዋ ያለህበትን ሁኔታ እንደሚረዳና ለመጽናት የሚያስፈልግህን ኃይል እንደሚሰጥህ አስታውስ።—መክ. 5:8፤ w22.11 21 አን. 5

ቅዳሜ፣ ኅዳር 16

ማንነታቸውን ከሚደብቁም እርቃለሁ።—መዝ. 26:4

ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ምረጥ። የጓደኛ ምርጫህ በመንፈሳዊ እድገትህ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ምሳሌ 13:20) በአሁኑ ወቅት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ጁሊየን እንዲህ ብሏል፦ “በወጣትነቴ ከተለያዩ ወንድሞች ጋር አብሬ በማገልገል ጥሩ ጓደኞች ማፍራት ችያለሁ። እነዚህ ጓደኞቼ በቅንዓት ያገለግሉ ነበር። አገልግሎት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ እንድገነዘብ ረዱኝ። . . . በተጨማሪም የዕድሜ እኩዮቼን ብቻ ጓደኛ ማድረጌ ተጨማሪ ጥሩ ጓደኞች የማግኘት አጋጣሚ አሳጥቶኝ እንደነበር ተገነዘብኩ።” በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው መጥፎ ተጽዕኖ እያሳደረብህ እንዳለ ብትገነዘብስ? ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች መንፈሳዊ አመለካከት እንደሌላቸው ተገንዝቦ ነበር፤ በመሆኑም እንዲህ ካሉ ሰዎች እንዲርቅ ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። (2 ጢሞ. 2:20-22) ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት በጣም ውድ ነው። ከፍተኛ ጥረት አድርገን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ማንም ሰው እንዲያበላሽብን ልንፈቅድ አይገባም። w22.08 5-6 አን. 13-15

እሁድ፣ ኅዳር 17

ከሞኝ ሰው ራቅ።—ምሳሌ 14:7

አምላክ የሚሰጠውን ምክር ከሚጠሉ ሰዎች በተለየ መልኩ ለአምላክ አስተሳሰብ እንዲሁም ለሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ ፍቅር እናዳብራለን። መታዘዝ የሚያስገኘውን ውጤት አለመታዘዝ ከሚያስከትለው መዘዝ ጋር ማወዳደራችን ይህን ፍቅር ለማጠናከር ይረዳናል። ሰዎች ይሖዋ የሚሰጠውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር በሞኝነት ችላ በማለታቸው በራሳቸው ላይ ስንት መከራ እንደሚያመጡ ለማሰብ ሞክር። ከዚያም አምላክን በመታዘዝህ ሕይወትህ ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ አስብ። (መዝ. 32:8, 10) ይሖዋ ሁሉም ሰው ጥበብን የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲያገኝ አድርጓል፤ ሆኖም ማንም ጥበብን እንዲሰማ አያስገድድም። ያም ቢሆን ጥበብን አለመስማት የሚያስከትለውን ውጤት ገልጿል። (ምሳሌ 1:29-32) እነዚህ ሰዎች “መንገዳቸው የሚያስከትለውን መዘዝ ይቀበላሉ።” የሚከተሉት የሕይወት ጎዳና ውሎ አድሮ ጭንቀት፣ መከራ፣ በመጨረሻም ጥፋት ያመጣባቸዋል። በሌላ በኩል ግን፣ ጥበብ የሚንጸባረቅበትን የይሖዋን ምክር የሚሰሙና በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች እንዲህ የሚል ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፦ “እኔን የሚሰማ ሰው ግን ተረጋግቶ ይኖራል፤ መከራ ይደርስብኛል የሚል ስጋትም አያድርበትም።”—ምሳሌ 1:33፤ w22.10 21 አን. 11-13

ሰኞ፣ ኅዳር 18

ይሖዋን የሚፈሩ፣ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።—መዝ. 128:1

ይሖዋን እንፈራዋለን ሲባል እሱን በጣም ስለምናከብረው እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ከማድረግ እንቆጠባለን ማለት ነው። (ምሳሌ 16:6) በመሆኑም አምላክ ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ ያወጣውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ መሥፈርት ምንጊዜም ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። (2 ቆሮ. 7:1) ይሖዋ የሚወዳቸውን ነገሮች ካደረግን፣ ከሚጠላቸው ነገሮች ደግሞ ከራቅን ደስተኛ እንሆናለን። (መዝ. 37:27፤ 97:10፤ ሮም 12:9) አንድ ሰው ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው ይሖዋ እንደሆነ ያውቅ ይሆናል። ሆኖም በአምላክ መሥፈርቶች ለመመራት መወሰንም አለበት። (ሮም 12:2) የይሖዋን መሥፈርቶች መከተል ከሁሉ የተሻለ የሕይወት ጎዳና እንደሆነ በእርግጥ እንደምናምን ማሳየት የምንችለው በምግባራችን ነው። (ምሳሌ 12:28) ዳዊት ስለ ይሖዋ የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ እንዲህ ያለ አመለካከት እንደነበረው ያሳያል፦ “የሕይወትን መንገድ አሳወቅከኝ። በፊትህ ብዙ ደስታ አለ፤ በቀኝህ ለዘላለም ደስታ አለ።”—መዝ. 16:11፤ w22.10 8 አን. 9-10

ማክሰኞ፣ ኅዳር 19

ወልድ፣ አብ ሲያደርግ ያየውን ብቻ እንጂ በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ አይችልም።—ዮሐ. 5:19

ኢየሱስ ትሑት ነው፤ ምንጊዜም ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በይሖዋ አገልግሎት ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን ችሏል። “በሰማያትና በምድር ያሉ ሌሎች ነገሮች በሙሉ . . . የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት ነው።” (ቆላ. 1:16) ኢየሱስ በተጠመቀበት ዕለት ከአባቱ ጋር እያለ ያከናወናቸውን ነገሮች እንዳስታወሰ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። (ማቴ. 3:16፤ ዮሐ. 17:5) ሆኖም ይህ ኢየሱስን እንዲታበይ አላደረገውም። እንዲያውም ኢየሱስ ራሱን ከማንም በላይ አድርጎ አያውቅም። ለደቀ መዛሙርቱ ወደ ምድር የመጣው “ለማገልገልና በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል” እንዳልሆነ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 20:28) በተጨማሪም “በራሱ ተነሳስቶ አንድም ነገር ሊያደርግ [እንደማይችል]” መናገሩ ልኩን እንደሚያውቅ የሚያሳይ ነው። በእርግጥም የኢየሱስ ትሕትና አስደናቂ ነው! ሁላችንም ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። w22.05 24 አን. 13

ረቡዕ፣ ኅዳር 20

ወደ ይሖዋ ይመለስ።—ኢሳ. 55:7

ይሖዋ ይቅር ለማለት ወይም ላለማለት ሲወስን ‘ኃጢአተኛው ድርጊቱን የፈጸመው ስህተት መሆኑን እያወቀ ነው ወይ’ የሚለውን ከግምት ያስገባል። ኢየሱስ በሉቃስ 12:47, 48 ላይ ይህን ነጥብ በግልጽ ተናግሯል። በክፋት ተነሳስቶ፣ ድርጊቱ ይሖዋን እንደሚያሳዝን እያወቀ ኃጢአት የሚፈጽም ሰው ኃጢአቱ ከባድ ይሆንበታል። እንዲህ ያለው ሰው ይቅር ላይባል ይችላል። (ማር. 3:29፤ ዮሐ. 9:41) ታዲያ እንዲህ ካደረግን ይቅር ልንባል አንችልም ማለት ነው? በፍጹም! ይሖዋ ‘ኃጢአተኛው ከልቡ ንስሐ ገብቷል ወይ’ የሚለውንም ከግምት ያስገባል። ንስሐ መግባት ሲባል “ሐሳብን፣ አመለካከትን ወይም ዓላማን መቀየር” ማለት ነው። መጥፎ ነገር በመፈጸማችን ወይም ትክክለኛውን ነገር ሳናደርግ በመቅረታችን ምክንያት የሚሰማንን የጸጸት ወይም የሐዘን ስሜት ያካትታል። ንስሐ የገባ ሰው የሚያዝነው በፈጸመው መጥፎ ድርጊት የተነሳ ብቻ ሳይሆን እንደዚያ ያለ ኃጢአት እስኪፈጽም ድረስ መንፈሳዊነቱ በመዳከሙም ጭምር ነው። w22.06 5-6 አን. 15-17

ሐሙስ፣ ኅዳር 21

የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።—2 ጢሞ. 3:12

ጠላቶቻችን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችን በተመለከተ ውሸት ወይም የተዛባ መረጃ ያሰራጫሉ። (መዝ. 31:13) አንዳንድ ወንድሞች ታስረዋል፤ እንዲሁም የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በሐሰት ተከሶ በታሰረበት ጊዜ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። አንዳንዶቹ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም በታሰረበት ወቅት እሱን መደገፋቸውን አቁመው ነበር። (2 ጢሞ. 1:8, 15፤ 2:8, 9) ጳውሎስ ምን ሊሰማው እንደሚችል ለማሰብ ሞክሩ። ጳውሎስ ለእነሱ ሲል ብዙ መከራ አሳልፏል፤ እንዲያውም ሕይወቱን ሳይቀር አደጋ ላይ ጥሏል። (ሥራ 20:18-21፤ 2 ቆሮ. 1:8) ጳውሎስን እንደተዉት ሰዎች ፈጽሞ መሆን አንፈልግም! ስለዚህ ሰይጣን በተለይ ኃላፊነት ያላቸውን ወንድሞች የጥቃቱ ዒላማ ቢያደርጋቸው ልንደነቅ አይገባም። ሰይጣን እንዲህ ያለ ጥቃት የሚያደርስባቸው ንጹሕ አቋማቸውን እንዲያጎድፉ ለማድረግና እኛን ለማስፈራራት ነው። (1 ጴጥ. 5:8) ወንድሞቻችሁን መደገፋችሁን ቀጥሉ፤ እንዲሁም በታማኝነት ከእነሱ ጋር ተጣበቁ።—2 ጢሞ. 1:16-18፤ w22.11 16-17 አን. 8-11

ዓርብ፣ ኅዳር 22

ትንሽ እንኳ አምላክን አትፈራም?—ሉቃስ 23:40

ከኢየሱስ ጎን ተሰቅሎ የነበረው ንስሐ የገባው ወንጀለኛ አይሁዳዊ ነው ብለን መደምደም እንችላለን። አይሁዳውያን የሚያመልኩት አንድ አምላክ ነበር፤ አሕዛብ ግን ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር። (ዘፀ. 20:2, 3፤ 1 ቆሮ. 8:5, 6) ወንጀለኛው ከአሕዛብ ወገን ቢሆን ኖሮ፣ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ጥያቄ የሚጠይቀው “ትንሽ እንኳ አማልክትን አትፈራም?” ብሎ ነበር። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ የተላከው ለአሕዛብ ሳይሆን “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ነው። (ማቴ. 15:24) አምላክ ሙታንን እንደሚያስነሳ ለእስራኤላውያን ነግሯቸው ነበር። ንስሐ የገባው ወንጀለኛ ይህን ሳያውቅ አይቀርም። ከተናገረው ነገር መረዳት እንደምንችለው፣ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት አስነስቶ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሚያደርገው አስቧል። ሰውየው አምላክ እሱንም ከሞት እንደሚያስነሳው ተስፋ አድርጎ መሆን አለበት። ንስሐ የገባው ወንጀለኛ፣ አይሁዳዊ እንደመሆኑ መጠን ስለ አዳምና ሔዋን እንዲሁም ይሖዋ መኖሪያ አድርጎ ስለሰጣቸው ገነት ማወቁ አይቀርም። በመሆኑም ወንጀለኛው፣ ኢየሱስ በሉቃስ 23:43 ላይ የጠቀሰው ገነት ምድር ላይ ያለ ውብ የአትክልት ቦታ እንደሆነ ተገንዝቦ መሆን አለበት።—ዘፍ. 2:15፤ w22.12 8-9 አን. 2-3

ቅዳሜ፣ ኅዳር 23

እነዚህ ሁሉ . . . በአንድ ልብ ተግተው ይጸልዩ ነበር።—ሥራ 1:14

የስብከቱን ሥራ ማከናወን የቻልነው የአምላክ መንፈስ ስለረዳን ብቻ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን የስብከት ሥራችንን ለማስቆም ጦርነት አውጆብናል። (ራእይ 12:17) በሰብዓዊ አመለካከት ሲታይ ሰይጣንን ፈጽሞ ልናሸንፈው የምንችል አይመስልም። ሆኖም በስብከቱ ሥራችን አማካኝነት ድል እያደረግነው ነው! (ራእይ 12:9-11) እንዴት? በአገልግሎት ስንካፈል የሰይጣንን ዛቻ እንደማንፈራ እናሳያለን። በስብከቱ ሥራ በተካፈልን ቁጥር ሰይጣን ድል ይደረጋል። ይህም፣ መንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሰጠንና የይሖዋ ሞገስ እንዳለን ያሳያል። (ማቴ. 5:10-12፤ 1 ጴጥ. 4:14) የአምላክ መንፈስ በአገልግሎት ላይ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና እንድንወጣ ሊረዳን ይችላል። (2 ቆሮ. 4:7-9) ታዲያ የአምላክን መንፈስ በቀጣይነት ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚሰማ በመተማመን መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን አዘውትረን ልንለምነው ይገባል። w22.11 5 አን. 10-11

እሁድ፣ ኅዳር 24

ወንድሞች፣ ይህን እናሳስባችኋለን፦ በሥርዓት የማይሄዱትን አስጠንቅቋቸው፤ የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ።—1 ተሰ. 5:14

ሰላም ፈጣሪ ለመሆን ጥረት በማድረግ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ይሖዋን በይቅር ባይነቱ ለመምሰል ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋ ለኃጢአታችን ሲል ልጁ እንዲሞት ከፈቀደ እኛስ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሲበድሉን ይቅር ልንላቸው አይገባም? በአንደኛው የኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ክፉ ባሪያ መሆን አንፈልግም። ጌታው ያን ሁሉ ዕዳ ቢተውለትም እሱ ግን በጣም ትንሽ ዕዳ ያለበትን እንደ እሱ ያለ ባሪያ ሊምረው አልፈለገም። (ማቴ. 18:23-35) በጉባኤ ካለ አንድ ሰው ጋር አለመግባባት አጋጥሞህ ከነበረ ከመታሰቢያው በዓል በፊት ሰላም ለመፍጠር ለምን ቅድሚያውን አትወስድም? (ማቴ. 5:23, 24) እንዲህ ማድረግህ ይሖዋና ኢየሱስን ከልብህ እንደምትወዳቸው ያሳያል። w23.01 29 አን. 8-9

ሰኞ፣ ኅዳር 25

ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል።—ምሳሌ 19:17

ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማወቅ የምትችሉበት አንዱ መንገድ በዘዴ ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው። (ምሳሌ 20:5) በቂ ምግብ፣ መድኃኒት ወይም ሌሎች ቁሳቁሶች አሏቸው? ከሥራቸው የመፈናቀል አደጋ ተደቅኖባቸዋል? ወይም የቤት ኪራይ መክፈል ተቸግረዋል? መንግሥት የሚሰጠውን ድጎማ ለማግኘት በማመልከት ረገድ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል? ይሖዋ ሁላችንም ሌሎችን እንድናበረታታና እንድንረዳ ጋብዞናል። (ገላ. 6:10) ቀላል በሚመስል መንገድ እንኳ ፍቅራችንን መግለጻችን የታመሙ ወንድሞቻችንን በእጅጉ ሊያበረታታቸው ይችላል። ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ አንድን ወንድም ለማበረታታት ፖስት ካርድ ወይም ሥዕል ሊልክ ይችላል። አንድ ወጣት ለአንዲት እህት ሊላላክላት ወይም ዕቃ ሊገዛላት ይችል ይሆናል። ወይም ደግሞ ለታመመ ወንድማችን ምግብ ልናዘጋጅ እንችል ይሆናል። ሽማግሌዎች በወረርሽኝ ወቅት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሥራ ይበዛባቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ሽማግሌዎችን ለማመስገን ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል። ‘እርስ በርስ ለመበረታታት እንዲሁም እርስ በርስ ለመተናነጽ’ የበኩላችንን ድርሻ መወጣታችን ምንኛ ጠቃሚ ነው!—1 ተሰ. 5:11፤ w22.12 22 አን. 2፤ 23 አን. 5-6

ማክሰኞ፣ ኅዳር 26

እጅግ ተሳስታችኋል።—ማር. 12:27

ሰዱቃውያን የመጀመሪያዎቹን አምስት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጠንቅቀው ቢያውቁም በመንፈስ መሪነት በተጻፉት በእነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን አስፈላጊ እውነቶች ችላ ብለዋቸዋል። ለምሳሌ ስለ ሙታን ትንሣኤ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ ምን ምላሽ እንደሰጣቸው እንመልከት። እንዲህ ሲል ጠይቋቸዋል፦ “ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም?” (ማር. 12:18, 26) ሰዱቃውያን ይህን ዘገባ ብዙ ጊዜ አንብበውት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፤ ኢየሱስ ያነሳላቸው ጥያቄ ግን ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሆነውን የትንሣኤን ትምህርት ችላ ብለውት እንደነበር አጋልጧል። (ሉቃስ 20:38) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ወይም ዘገባ ስናነብ ከዚያ ምንባብ የምናገኛቸውን ትምህርቶች ሁሉ ለመረዳት ንቁ መሆን አለብን። መሠረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን ብቻ ሳይሆን በዘገባው ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ ጥልቀት ያላቸው እውነቶችንና መሠረታዊ ሥርዓቶችንም ማስተዋል እንፈልጋለን። w23.02 11 አን. 9-10

ረቡዕ፣ ኅዳር 27

ታላቅ የምሥክሮች ደመና በዙሪያችን [አለልን]።—ዕብ. 12:1

በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተጠቀሱት ምሥክሮች ሁሉ ከባድ መከራ አጋጥሟቸው ነበር፤ ሆኖም ዕድሜያቸውን በሙሉ ለይሖዋ ታማኝ ሆነው ኖረዋል። (ዕብ. 11:36-40) ታዲያ ጽናታቸውና ትጋታቸው ከንቱ ሆኗል? በጭራሽ! አምላክ የገባቸው ቃሎች በሙሉ ሲፈጸሙ በሕይወት ዘመናቸው ማየት ባይችሉም እንኳ ይሖዋን ተስፋ ማድረጋቸውን ቀጥለው ነበር። ደግሞም የይሖዋን ሞገስ እንዳገኙ እርግጠኞች ስለነበሩ ይሖዋ የገባቸው ቃሎች ሲፈጸሙ ማየታቸው እንደማይቀር ቅንጣት ታክል አልተጠራጠሩም። (ዕብ. 11:4, 5) የእነሱ ምሳሌ ይሖዋን ተስፋ ማድረጋችንን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል። የምንኖርበት ዓለም ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ ነው። (2 ጢሞ. 3:13) ሰይጣን የአምላክን ሕዝቦች መፈተኑን አላቆመም። ከፊታችን የሚጠብቀን ፈተና ምንም ይሁን ምን ‘ተስፋችንን የጣልነው ሕያው በሆነው አምላክ ላይ’ እንደሆነ በመተማመን ይሖዋን በትጋት ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ጢሞ. 4:10፤ w22.06 25 አን. 17-18

ሐሙስ፣ ኅዳር 28

መሞቴ . . . ምን የሚያስገኘው ጥቅም አለ? አፈር ያወድስሃል?—መዝ. 30:9

ጤንነታችንን የምንንከባከብበት አንዱ ምክንያት በሙሉ አቅማችን ይሖዋን ማገልገል ስለምንፈልግ ነው። (ማር. 12:30) ስለዚህ ጤንነታችንን እንደሚጎዱ ከምናውቃቸው ነገሮች እንርቃለን። (ሮም 12:1) እርግጥ ጤንነታችንን ለመንከባከብ የፈለግነውን ያህል ጥረት ብናደርግም ሙሉ ጤንነት ላይኖረን ይችላል። ሆኖም በስጦታ ላገኘነው ሕይወት አድናቆት እንዳለን ለሰማዩ አባታችን ማሳየት እንፈልጋለን፤ ስለዚህ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን። ሕመምና እርጅና በአንድ ወቅት እናከናውናቸው የነበሩ በርካታ ነገሮችን እንዳናከናውን ሊያግዱን ይችላሉ። በዚህም የተነሳ ቅስማችን ሊሰበርና ልናዝን እንችላለን። ሆኖም ተስፋ ቆርጠን ጤንነታችንን የመንከባከቡን ጉዳይ ፈጽሞ ችላ ልንል አይገባም። ለምን? ምክንያቱም ምንም ያህል ዕድሜያችን ቢገፋ ወይም ጤንነታችን ቢቃወስ ልክ እንደ ንጉሥ ዳዊት ይሖዋን ማወደስ እንችላለን። ፍጹማን ባንሆንም አምላካችን ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! (ማቴ. 10:29-31) አምላካችን ብንሞት እንኳ መልሶ ሊያስነሳን ይጓጓል። (ኢዮብ 14:14, 15) በሕይወት እስካለን ድረስ ጤንነታችንን መንከባከብና ሕይወታችንን ከአደጋ መጠበቅ እንፈልጋለን። w23.02 20-21 አን. 3-5

ዓርብ፣ ኅዳር 29

መንፈስ ቅዱስን የሚሳደብ ሁሉ ለዘላለም ይቅር አይባልም።—ማር. 3:29

የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ አርማጌዶንን በሕይወት ካለፉ በኋላም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይኖራል? አዎ። (ራእይ 7:14) ኢየሱስ እነዚህ በግ መሰል ሰዎች “ወደ ዘላለም ሕይወት” እንደሚሄዱ ተናግሯል። (ማቴ. 25:46) ሆኖም ከአርማጌዶን በሕይወት የሚያልፉት እነዚህ ሰዎች ወዲያውኑ የዘላለም ሕይወት አያገኙም። በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት ኢየሱስ “እረኛቸው ይሆናል፤ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል።” የክርስቶስን አመራር የሚከተሉና በመጨረሻው ፍርድ ወቅት ለይሖዋ ታማኝ ሆነው የሚገኙ ሰዎች ስማቸው በቋሚነት በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይጻፋል። (ራእይ 7:16, 17) በፍየሎች የተመሰሉት ሰዎች በአርማጌዶን ይጠፋሉ። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች “ወደ ዘላለም ጥፋት” እንደሚሄዱ ተናግሯል። (ማቴ. 25:46) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ “[እነዚህ ሰዎች] ዘላለማዊ ጥፋት ተፈርዶባቸው ከጌታ ፊት ይወገዳሉ” በማለት ጽፏል።—2 ተሰ. 1:9፤ 2 ጴጥ. 2:9፤ w22.09 16 አን. 7-8

ቅዳሜ፣ ኅዳር 30

ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።—መክ. 3:1

የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ቤተሰቦች ዘና ብለው አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ ያስችላሉ፤ ይህም ቤተሰቦች እርስ በርስ ይበልጥ እንዲቀራረቡ ይረዳል። ይሖዋ የሚያስደስቱንን ነገሮች የምናደርግባቸው ውብ የሆኑ ቦታዎችን ፈጥሮልናል። ብዙ ቤተሰቦች ወደ መናፈሻ ቦታዎች፣ ገጠራማ አካባቢዎች፣ ተራሮች ወይም ሐይቆች ሄደው መዝናናት ያስደስታቸዋል። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ወላጆችም ሆኑ ልጆች ከዚህ በፊት አድርገውት በማያውቁት መጠን በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ይደሰታሉ። እንደ አሁኑ እንስሳትን የምንፈራበት ምንም ምክንያት አይኖርም፤ እነሱም እኛን አይፈሩንም። (ኢሳ. 11:6-9) ይሖዋ በሠራቸው ነገሮች ለዘላለም እንደሰታለን። (መዝ. 22:26) ሆኖም ወላጆች፣ ልጆቻችሁ በፍጥረት ሥራዎች እንዲደሰቱ ለማድረግ ያ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ አያስፈልጋችሁም። ፍጥረትን ተጠቅማችሁ ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ የምታስተምሯቸው ከሆነ ንጉሥ ዳዊት በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ መስማማታቸው አይቀርም፦ “ይሖዋ ሆይ . . . ከአንተ ሥራ ጋር የሚወዳደር አንድም ሥራ የለም።”—መዝ. 86:8፤ w23.03 25 አን. 16-17

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ