ጥቅምት
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 1
በጉባኤ መካከልም አወድስሃለሁ።—መዝ. 22:22
ድምፃችንን ከፍ አድርገን በመዘመርና በሚገባ ተዘጋጅተን መልስ በመስጠት ሁላችንም ስብሰባዎቻችን ያማሩ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። አንዳንዶች፣ ሰው በተሰበሰበበት መዘመር ወይም መልስ መስጠት ይከብዳቸዋል። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ከሆነ አንዳንዶች ፍርሃታቸውን ለማሸነፍ ምን እንዳደረጉ ተመልከት። አንዳንዶች ከልብ መዘመር እንደሚረዳ አስተውለዋል። የመንግሥቱን መዝሙሮቻችንን የምንዘምርበት ዋነኛው ምክንያት ይሖዋን ማወደስ ነው። ስለዚህ ለሌሎቹ የስብሰባው ክፍሎች እንደምትዘጋጀው ሁሉ መዝሙሮቹን አስቀድመህ ቤትህ ተለማመድ። እንዲሁም ግጥሞቹ ስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ክፍሎች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማስተዋል ሞክር። በተጨማሪም በመዘመር ችሎታህ ላይ ሳይሆን በመልእክቱ ላይ ይበልጥ አተኩር። ተሳትፎ ማድረግ አንዳንዶችን በጣም ሊከብዳቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። ታዲያ ምን ሊረዳህ ይችላል? አዘውትረህ ተሳትፎ ለማድረግ ሞክር። መልስህ አጭር፣ ቀላልና ቀጥተኛ ቢሆን ምንም ስህተት እንደሌለው አስታውስ። ይሖዋ እሱን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለማወደስ የምናደርገውን ልዩ ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። w22.04 7-8 አን. 12-15
ረቡዕ፣ ጥቅምት 2
ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም።—ዕብ. 13:6
‘ረዳት’ የሚለው ቃል እርዳታ ለማግኘት የሚጮኽን ግለሰብ ለመርዳት የሚሮጥን ሰው ያመለክታል። ይሖዋ አንድን የተጨነቀ ሰው ለመርዳት ሲቻኮል እስቲ ይታያችሁ። ይህ አገላለጽ ይሖዋ እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ እንደሆነ አልፎ ተርፎም እንደሚጓጓ በግልጽ ያሳያል። ይሖዋ ከጎናችን ስለሆነ ፈተናዎች ቢያጋጥሙንም በደስታ መጽናት እንችላለን። ይሖዋ የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች ነው? መልሱን ለማግኘት ወደ ኢሳይያስ መጽሐፍ እንሂድ። ምክንያቱም ኢሳይያስ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው ብዙዎቹ ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች ይሠራሉ። በተጨማሪም ኢሳይያስ ብዙ ጊዜ ቀላል አገላለጾችን በመጠቀም ስለ ይሖዋ ተናግሯል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 30ን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በዚህ ምዕራፍ ላይ ኢሳይያስ ግሩም ምሳሌዎችን በመጠቀም ይሖዋ ሕዝቡን የሚረዳው እንዴት እንደሆነ ተናግሯል፤ ይሖዋ (1) ጸሎታችንን በጥሞና በማዳመጥና በመመለስ፣ (2) መመሪያ በመስጠት እንዲሁም (3) አሁንም ሆነ ወደፊት እኛን በመባረክ ይረዳናል። w22.11 8 አን. 2-3
ሐሙስ፣ ጥቅምት 3
ሊደርስብህ ያለውን መከራ አትፍራ። . . . እስከ ሞት ድረስ ታማኝነትህን አስመሥክር፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።—ራእይ 2:10
ኢየሱስ ለሰምርኔስና ለፊላደልፊያ ጉባኤዎች በላከው መልእክት ላይ በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ስደትን መፍራት እንደሌለባቸው ነግሯቸዋል፤ ምክንያቱም ለታማኝነታቸው ወሮታ ይከፈላቸዋል። (ራእይ 3:10) ስደት እንደሚደርስብን መጠበቅና በጽናት ለመወጣት ዝግጁ መሆን አለብን። (ማቴ. 24:9, 13፤ 2 ቆሮ. 12:10) የራእይ መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች ‘በጌታ ቀን’ ማለትም በዘመናችን ስደት እንደሚደርስባቸው መረጃ ይሰጠናል። (ራእይ 1:10) ራእይ ምዕራፍ 12 የአምላክ መንግሥት መወለዱን ተከትሎ በሰማይ ጦርነት እንደተነሳ ይነግረናል። ሚካኤል ማለትም ክብር የተላበሰው ኢየሱስ ክርስቶስና ሠራዊቱ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ተዋጉ። (ራእይ 12:7, 8) በውጤቱም እነዚያ የአምላክ ጠላቶች ተሸንፈው ወደ ምድር ተጣሉ፤ ይህም በምድርና በነዋሪዎቿ ላይ ይህ ነው የማይባል ሰቆቃ አስከትሏል።—ራእይ 12:9, 12፤ w22.05 5 አን. 12-13
ዓርብ፣ ጥቅምት 4
በይሖዋ ዘንድ ፍትሕ ማዛባት [የለም]።—2 ዜና 19:7
ይሖዋ የሚያስተላልፈው ፍርድ ምንጊዜም ፍትሐዊ ነው። ይሖዋ ፈጽሞ አያዳላም። ይቅርታው የተመካው በሰዎች መልክ፣ ሀብት፣ ታዋቂነት ወይም ችሎታ ላይ አይደለም። (1 ሳሙ. 16:7፤ ያዕ. 2:1-4) ማንም ሰው በይሖዋ ላይ ጫና ሊያሳድርበት ወይም በጉቦ ሊደልለው አይችልም። በተጨማሪም ውሳኔ የሚያደርገው በስሜት ተገፋፍቶ አይደለም። (ዘፀ. 34:7) ይሖዋ ከፍተኛ እውቀትና ጥልቅ ማስተዋል ያለው በመሆኑ ከሁሉ የላቀ ዳኛ ነው። (ዘዳ. 32:4) የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች የይሖዋ ይቅርታ በዓይነቱ ልዩ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። በአንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው እነዚህ ጸሐፊዎች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተጠቀሙበት የዕብራይስጥ ቃል “አምላክ ለኃጢአተኞች የሚያሳየውን ይቅርታ ብቻ የሚያመለክት ነው። ይህ ቃል ሰዎች የሚያሳዩትን ውስን ይቅርታ ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም።” ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ሙሉ በሙሉ ይቅር ማለት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። w22.06 4 አን. 10-11
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 5
ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው፤ በሚያረጅበት ጊዜም እንኳ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።—ምሳሌ 22:6
ልጆቻችሁን የምታሳድጉት ብቻችሁን ወይም በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ የታማኝነት ምሳሌያችሁ በዙሪያችሁ ያሉትን እንደሚያጠናክርና እንደሚያነቃቃ አትዘንጉ። ልጃችሁ ለምታደርጉት ጥረት ጥሩ ምላሽ እየሰጠ እንደሆነ ባይሰማችሁስ? ልጆችን ማሠልጠን ጊዜ እንደሚወስድ አትርሱ። አንድ ዘር ስትዘሩ ተክሉ አድጎ ያፈራ እንደሆነ የምትጠራጠሩበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። የተክሉን እድገት መቆጣጠር ባትችሉም ውኃ በማጠጣት ተክሉ እንዲያድግ ሁኔታውን ልታመቻቹለት ትችላላችሁ። (ማር. 4:26-29) በተመሳሳይም የልጆቻችሁን ልብ መንካት መቻላችሁን ትጠራጠሩ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ውጤቱን መቆጣጠር አትችሉም። ሆኖም እነሱን ለማሠልጠን የምትችሉትን ሁሉ ማድረጋችሁን ከቀጠላችሁ በመንፈሳዊ እንዲያድጉ ምቹ ሁኔታ ትፈጥሩላቸዋላችሁ። w22.04 19-20 አን. 16-17
እሁድ፣ ጥቅምት 6
ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።—ምሳሌ 16:18
ሰለሞን ይሖዋን በታማኝነት ያገለግል በነበረበት ወቅት ለራሱ ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። ወጣት እያለ ከአቅሙ በላይ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ በትሕትና በመግለጽ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠው ጸልዮአል። (1 ነገ. 3:7-9) በንግሥናው መጀመሪያ አካባቢም ሰለሞን ኩራት ያለውን አደጋ በሚገባ ያውቅ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሰለሞን ራሱ የሰጠውን ምክር በኋላ ላይ ሳይሠራበት ቀርቷል። ንጉሥ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የኩራት ዝንባሌ ስላደረበት የአምላክን ሕጎች ችላ ማለት ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛው የአምላክ ሕግ አንድ ዕብራዊ ንጉሥ “ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ” ይላል። (ዘዳ. 17:17) ሰለሞን ግን ይህን ሕግ ጥሶ ነበር፤ 700 ሚስቶችና 300 ቁባቶች ነበሩት! (1 ነገ. 11:1-3) ምናልባት ሰለሞን “ምንም አልሆንም” ብሎ አስቦ ይሆን? ውሎ አድሮ ሰለሞን ከይሖዋ መራቅ የሚያስከትለውን መዘዝ አጭዷል።—1 ነገ. 11:9-13፤ w22.05 23 አን. 12
ሰኞ፣ ጥቅምት 7
“ጻድቅ አገልጋዬ በእምነት ይኖራል”፤ ደግሞም “ወደኋላ ቢያፈገፍግ በእሱ ደስ አልሰኝም።”—ዕብ. 10:38
በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። የጽንፈ ዓለሙ ገዢ የመሆን መብት ያለውን ይሖዋን መደገፍ ወይም ጨካኝ ጠላቱ ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጎን መቆም። በዚህ ጉዳይ ላይ መሃል ሰፋሪ መሆን አይቻልም። ሰዎች የሚያደርጉት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ዘላለማዊ ዕጣቸውን ይወስነዋል። (ማቴ. 25:31-33, 46) ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት፣ እንዲድኑ ወይም እንዲጠፉ ምልክት የሚደረግባቸው ውሳኔያቸውን መሠረት በማድረግ ነው። (ራእይ 7:14፤ 14:9-11፤ ሕዝ. 9:4, 6) አንተ የይሖዋን አገዛዝ ለመደገፍ መርጠህ ከሆነ ጥሩ ውሳኔ አድርገሃል። ሌሎችም ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ መርዳት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። የይሖዋን አገዛዝ በታማኝነት የሚደግፉ ሁሉ ይባረካሉ። እንደነዚህ ያሉ አስፈላጊ እውነቶችን መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ይህን ማድረጋችን ይሖዋን እስከ መጨረሻው ለማገልገል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል። በተጨማሪም የተማርነውን ነገር ለሌሎች በማካፈል ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉና በውሳኔያቸው እንዲጸኑ ልንረዳቸው እንችላለን። w22.05 15 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 8
ሰዎች . . . ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲያስወሩባችሁ ደስተኞች ናችሁ።—ማቴ. 5:11
ጠላቶቻችንን ሳይሆን ይሖዋን ልናዳምጥ ይገባል። ኢዮብ ይሖዋ ሲያነጋግረው በጥሞና አዳምጧል። አምላክ ኢዮብን በጉዳዩ ላይ እንዲያመዛዝን ረድቶታል፤ እንዲህ ያለው ያህል ነው፦ ‘የደረሰብህን ነገር በሙሉ አውቃለሁ። አንተን መንከባከብ የሚያቅተኝ ይመስልሃል?’ ኢዮብ ለይሖዋ ጥሩነት ያለውን ጥልቅ አድናቆት የሚያሳይና ትሕትና የሚንጸባረቅበት መልስ ሰጥቷል። “ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን በገዛ ዓይኔ አየሁህ” ብሏል። (ኢዮብ 42:5) ኢዮብ ይህን የተናገረው እዚያው አመድ ላይ እንደተቀመጠ ሳይሆን አይቀርም፤ ሰውነቱን ቁስል ወርሶታል። ያም ቢሆን ይሖዋ ኢዮብን እንደሚወደውና ሞገሱን እንደሚያሳየው አረጋገጠለት። (ኢዮብ 42:7, 8) በዛሬው ጊዜም ሰዎች ሊሰድቡን ወይም ሊያንቋሽሹን ይችላሉ። የእኛን ወይም የድርጅቱን ስም ሊያጠፉ ይችላሉ። ይሖዋ መከራ ቢደርስብንም ታማኝነታችንን እንደማናጓድል እንደሚተማመንብን ከኢዮብ ታሪክ እንማራለን። w22.06 24 አን. 15-16
ረቡዕ፣ ጥቅምት 9
የበጉ ሠርግ [ደርሷል]።—ራእይ 19:7
ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ በሰማይ ታላቅ የደስታ ጩኸት ይሰማል፤ ሆኖም ከዚያ የበለጠ ደስታ የሚያስገኝ ነገር አለ። (ራእይ 19:1-3) እሱም “የበጉ ሠርግ” ነው፤ እንዲያውም ይህ ክንውን የራእይ መጽሐፍ ታላቅ መደምደሚያ ነው። ሁሉም የ144,000ዎቹ አባላት ከአርማጌዶን ጦርነት በፊት በሰማይ ይሆናሉ። ሆኖም የበጉ ሠርግ የሚደረገው በዚህ ወቅት አይደለም። (ራእይ 21:1, 2) ሠርጉ የሚከናወነው የአርማጌዶን ጦርነት ከተካሄደና የአምላክ ጠላቶች በሙሉ ከጠፉ በኋላ ነው። (መዝ. 45:3, 4, 13-17) የበጉ ሠርግ፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ምን ትርጉም አለው? አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጋብቻ እንደሚጣመሩ ሁሉ በዚህ ምሳሌያዊ ጋብቻም ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስና ‘ሙሽራው’ ማለትም 144,000ዎቹ ይጣመራሉ። ይህ ታላቅ ክንውን፣ ምድርን ለ1,000 ዓመታት የሚያስተዳድረው አዲስ መንግሥት ምሥረታ በዓል ነው።—ራእይ 20:6፤ w22.05 17 አን. 11-13
ሐሙስ፣ ጥቅምት 10
ጌታው . . . እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው!—ማቴ. 24:46
ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሚሾም ትንቢት ተናግሯል። (ማቴ. 24:45) ደግሞም ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል። መሪያችን ለአምላክ ሕዝቦችና ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ‘በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ’ እንዲሰጣቸው ጥቂት ቅቡዓን ወንዶችን ያቀፈ አንድ ቡድን ሾሟል። እነዚህ ወንዶች በሌሎች እምነት ላይ ለማዘዝ አይሞክሩም። (2 ቆሮ. 1:24) ከዚህ ይልቅ የሕዝቡ “መሪና አዛዥ” ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይገነዘባሉ። (ኢሳ. 55:4) ከ1919 አንስቶ ታማኙ ባሪያ የተለያዩ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ለእውነት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ገንቢ የሆነውን መንፈሳዊ ምግብ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲቀምሱ አድርጓል። በ1921 ታማኙ ባሪያ፣ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዲማሩ ለመርዳት የአምላክ በገና (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ አዘጋጀ። ዘመኑ ሲለወጥ ደግሞ ሌሎች ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል። አንተስ የሰማዩን አባታችንን እንድታውቀውና እንድትወደው የረዳህ የትኛው ጽሑፍ ነው? w22.07 10 አን. 9-10
ዓርብ፣ ጥቅምት 11
በፊትህም ለዘላለም ታኖረኛለህ።—መዝ. 41:12
በጽንፈ ዓለም ውስጥ የይሖዋን ያህል ለጋስ የሆነ አካል የለም። ምንም ያህል ብትሰጠው ብዙ እጥፍ አድርጎ ይመልስልሃል። (ማር. 10:29, 30) ጥቂት ጊዜ በቀረው በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥም እንኳ እጅግ አስደሳች፣ የሚክስና አርኪ የሆነ ሕይወት ይሰጥሃል። በዚህ ብቻ አያበቃም። አፍቃሪ የሆነውን አባትህን ለዘላለም ማገልገል የምትችልበት አጋጣሚ ተከፍቶልሃል። በአንተና በአባትህ መካከል ያለው ፍቅር ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል፤ ደግሞም ልክ እንደ እሱ መጨረሻ ለሌለው ጊዜ ትኖራለህ። ራስህን ወስነህ ስትጠመቅ ለአባትህ እጅግ ውድ የሆነ ነገር የመስጠት መብት ታገኛለህ። እስከዛሬ ያገኘሃቸው መልካምና አስደሳች ነገሮች ሁሉ ምንጭ እሱ ነው። አንተም በምላሹ የሰማይና የምድር ባለቤት ለሆነው አምላክ፣ የሌለውን ነገር ልትሰጠው ትችላለህ፤ ይህም በፈቃደኝነት ተነሳስተህ የምታቀርበው የታማኝነት አገልግሎት ነው። (ኢዮብ 1:8፤ 41:11፤ ምሳሌ 27:11) ሕይወትህን ልትጠቀም የምትችልበት ከዚህ የተሻለ መንገድ ይኖራል? w23.03 6 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 12
ወጣቶች በንጽሕና መመላለስ የሚችሉት እንዴት ነው? በቃልህ መሠረት ራሳቸውን በመጠበቅ ነው።—መዝ. 119:9
በጉርምስና ዕድሜ ወቅት የፆታ ስሜት ሊያይል ይችላል፤ እንዲሁም የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽም ሌሎች ከፍተኛ ጫና ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። ሰይጣን ለምኞቶችህ እጅ እንድትሰጥ ይፈልጋል። ታዲያ የሥነ ምግባር ንጽሕናህን ለመጠበቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? (1 ተሰ. 4:3, 4) በምትጸልይበት ወቅት የሚሰማህን ስሜት በሙሉ ግልጥልጥ አድርገህ ለይሖዋ ንገረው፤ እንዲሁም ብርታት እንዲሰጥህ ጠይቀው። (ማቴ. 6:13) ይሖዋ የሚፈልገው ሊረዳህ እንጂ ሊፈርድብህ እንዳልሆነ አስታውስ። (መዝ. 103:13, 14) ችግሮችህን ብቻህን ለመፍታት አትሞክር። ስላጋጠመህ ፈተና ለወላጆችህ ንገራቸው። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ስላሉ የግል ጉዳዮች መናገር ቀላል አይደለም። ሆኖም እንዲህ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብና በውስጡ ባሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ስታሰላስል ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። የይሖዋን አስተሳሰብ ስለምትረዳ ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ሕግ እንደማያስፈልግህ ታስተውላለህ። w22.08 5 አን. 10-12
እሁድ፣ ጥቅምት 13
አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት . . . የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ [ነው]።—1 ጢሞ. 5:8
ክርስቲያን የሆነ የቤተሰብ ራስ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነቱን በቁም ነገር ይመለከተዋል። አንተም የቤተሰብ ራስ ከሆንክ ቤተሰብህን መመገብ ወይም የቤት ኪራይ መክፈል ሊያቅትህ እንደሚችል በማሰብ ትጨነቅ ይሆናል። ሥራህን ካጣህ ሌላ ሥራ ላታገኝ እንደምትችል ትፈራም ይሆናል። ወይም በአነስተኛ ገቢ መኖር እንደማትችል በማሰብ በአኗኗርህ ላይ ለውጥ ለማድረግ አመንትተህ ሊሆን ይችላል። ሰይጣን እንዲህ ያለውን ፍርሃት በመጠቀም ብዙ ስኬት አግኝቷል። ሰይጣን፣ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደማያስብልን እና ቤተሰባችንን ለመንከባከብ እንደማይረዳን ሊያሳምነን ይሞክራል። በመሆኑም ሥራችንን ላለማጣት ስንል ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ ማለት እንደሌለብን ልናስብ እንችላለን፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቢያስጥሰንም እንኳ ማለት ነው። w22.06 15 አን. 5-6
ሰኞ፣ ጥቅምት 14
እኛ ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን።—ዕብ. 6:19
አምላካችን “መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ እንደሆነ እናውቃለን። (ዘፀ. 34:6) ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል። (ኢሳ. 61:8) ስንሠቃይ ሲያይ ልቡ በጣም ያዝናል፤ በወሰነው ጊዜም መከራንና ሥቃይን በሙሉ ለማስወገድ ዝግጁ ነው፤ አልፎ ተርፎም ይጓጓል። (ኤር. 29:11) እንዴት ደስ ይላል! ይሖዋን በጣም የምንወደው ለዚህ ነው! እውነትን ለመውደድ የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ምንድን ነው? እውነት ብዙ ጥቅሞችን ያስገኝልናል። አንድ ምሳሌ እናንሳ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለንን ተስፋ ያካትታል። መልሕቅ አንድ መርከብ እንዳይናወጥ አጥብቆ እንደሚይዘው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችንም በሕይወታችን ውስጥ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እንድንረጋጋ ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እየተናገረ ያለው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስላላቸው ሰማያዊ ተስፋ ነው። ሆኖም የተናገረው ሐሳብ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖችም ይሠራል። (ዮሐ. 3:16) ስለ ዘላለም ሕይወት ተስፋ መማራችን ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረው እንደረዳን ምንም ጥያቄ የለውም። w22.08 14-15 አን. 3-5
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15
ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ።—ኤፌ. 4:26
መተማመን የሚመሠረተው በፍቅር ላይ ነው። አንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 በሌሎች ላይ እምነት ለመገንባት ወይም እምነታችንን ለማደስ የሚረዱ የተለያዩ የፍቅር ገጽታዎችን ይገልጻል። (1 ቆሮ. 13:4-8) ለምሳሌ ቁጥር 4 “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው” ይላል። ይሖዋ በእሱ ላይ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜም ጭምር በትዕግሥት ይይዘናል። ታዲያ እኛስ ወንድሞቻችን የሚያበሳጭ ወይም የሚጎዳ ነገር ሲናገሩ ወይም ሲያደርጉብን በትዕግሥት ልንይዛቸው አይገባም? ቁጥር 5 “[ፍቅር] በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም” ይላል። እኛም ወንድሞቻችን የፈጸሙብንን በደል ሁልጊዜ እያስታወስን መኖር የለብንም። መክብብ 7:9 ‘ለቁጣ መቸኮል’ እንደሌለብን ይናገራል። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን የይሖዋን ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት እናድርግ። አምላክ ይወዳቸዋል፤ እንዲሁም ኃጢአታቸውን አይከታተልም። እኛም በዚህ ረገድ አምላክን መምሰል ይኖርብናል። (መዝ. 130:3) በድክመታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ መልካም ጎናቸውንና እምቅ አቅማቸውን እናስተውል።—ማቴ. 7:1-5፤ w22.09 3-4 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ጥቅምት 16
የጭንቀት ጊዜ ይመጣል።—ዳን. 12:1
የዳንኤል መጽሐፍ በፍጻሜው ዘመን አንዳንድ አስደናቂ ክንውኖች የሚከሰቱበትን ቅደም ተከተል ይነግረናል። ለምሳሌ ዳንኤል 12:1 ሚካኤል ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ለአምላክ ሕዝብ እንደቆመ’ ይነግረናል። ይህ የትንቢቱ ክፍል መፈጸም የጀመረው ኢየሱስ በ1914 የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት ጊዜ ነው። ሆኖም ዳንኤል ኢየሱስ ‘እንደሚነሳም’ ተነግሮታል። ይህ የሚሆነው “ብሔራት ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ሆኖ የማያውቅ የጭንቀት ጊዜ” በሚመጣበት ወቅት ነው። ይህ የጭንቀት ጊዜ በማቴዎስ 24:21 ላይ ከተገለጸው “ታላቅ መከራ” ጋር አንድ ዓይነት ነው። ኢየሱስ በዚህ የጭንቀት ጊዜ መጨረሻ ማለትም በአርማጌዶን ወቅት የአምላክን ሕዝቦች ለመታደግ ይነሳል ወይም እርምጃ ይወስዳል። የራእይ መጽሐፍ እነዚህን የአምላክ ሕዝቦች “ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ [እጅግ ብዙ ሕዝብ]” በማለት ይጠራቸዋል።—ራእይ 7:9, 14፤ w22.09 21 አን. 4-5
ሐሙስ፣ ጥቅምት 17
በእኔ ላይ ኃጢአት የሠራውን ሁሉ ከመጽሐፌ ላይ እደመስሰዋለሁ።—ዘፀ. 32:33
በአሁኑ ወቅት በሕይወት መጽሐፍ ላይ የሰፈሩ ስሞች ሊደመሰሱ ወይም ሊሰረዙ ይችላሉ። ይሖዋ ስሞቹን መጀመሪያ ላይ የሚጽፈው በእርሳስ ነው ሊባል ይችላል። (ራእይ 3:5 ግርጌ) ስማችን በምሳሌያዊ ሁኔታ በብዕር በቋሚነት እስኪጻፍ ድረስ ከዚህ መጽሐፍ ሳይሰረዝ እንዲቆይ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ከተጻፉት ቡድኖች መካከል አንዱ በሰማይ ላይ ከኢየሱስ ጋር እንዲገዙ የተመረጡትን ሰዎች ያቀፈ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ‘የሥራ ባልደረቦቹ’ ከጻፈው ሐሳብ እንደምንማረው ከኢየሱስ ጋር አብረው ለመግዛት የተመረጡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስማቸው በአሁኑ ወቅት በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል። (ፊልጵ. 4:3) ሆኖም ስማቸው በዚህ ምሳሌያዊ መጽሐፍ ውስጥ እንዲቆይ ታማኝነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ከዚያም ከመሞታቸው በፊት ወይም ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻው ማኅተም ሲደረግባቸው ስማቸው በቋሚነት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ይጻፋል።—ራእይ 7:3፤ w22.09 15 አን. 3, 5-6
ዓርብ፣ ጥቅምት 18
ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!—ሉቃስ 11:28
አንድ ሰው የምትወዱትን ምግብ ሠራላችሁ እንበል። ሆኖም በመቸኮላችሁ ወይም አእምሯችሁ በሌላ ሐሳብ በመወጠሩ የተነሳ ምግቡን ምንም ሳታጣጥሙት በልታችሁ ጨረሳችሁ። በልታችሁ ከጨረሳችሁ በኋላ በጣም በጥድፊያ እንደበላችሁ ትገነዘባላችሁ፤ ‘ምን አለ ቀስ ብዬ እያንዳንዱን ጉርሻ ባጣጣምኩት ኖሮ’ ብላችሁ ታስባላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስን በምታነቡበት ጊዜም በጣም በችኮላ ከማንበባችሁ የተነሳ መልእክቱን ሳታጣጥሙ ቀርታችሁ ታውቃላችሁ? ጊዜ ወስዳችሁ የአምላክን ቃል በማንበብ ተደሰቱ፤ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ ሣሉ፤ የሚሰማውን ድምፅ ለመስማት ሞክሩ፤ እንዲሁም ስለምታነቡት ነገር ቆም ብላችሁ አስቡ። በዚህ መልኩ ማንበባችሁ ደስታችሁን ይጨምርላችኋል። ኢየሱስ በተገቢው ጊዜ ምግብ እንዲያቀርብ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ሾሞታል፤ ደግሞም የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበልን ነው። (ማቴ. 24:45) ታማኙ ባሪያ የሚያዘጋጃቸው ነገሮች በሙሉ በዋነኝነት የተመሠረቱት በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በአምላክ ቃል ላይ ነው።—1 ተሰ. 2:13፤ w22.10 7-8 አን. 6-8
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 19
ከልክ በላይ በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎችን ፌዝ . . . ጠግበናል።—መዝ. 123:4
መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ፌዘኞች እንደሚበዙ ይናገራል። (2 ጴጥ. 3:3, 4) እነዚህ ሰዎች ‘መጥፎ ምኞታቸውን ይከተላሉ።’ (ይሁዳ 7, 17, 18) የፌዘኞችን ጎዳና ከመከተል መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ የተቺነት ዝንባሌ ካላቸው ሰዎች ጋር ጊዜ አለማሳለፍ ነው። (መዝ. 1:1) ይህም ሲባል ከሃዲዎችን ከመስማት ወይም እነሱ ያዘጋጁትን ማንኛውንም ነገር ከማንበብ እንቆጠባለን ማለት ነው። ካልተጠነቀቅን የተቺነት ዝንባሌ በቀላሉ ልናዳብር እንዲሁም ይሖዋንና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ መጠራጠር ልንጀምር እንደምንችል እንገነዘባለን። እንዲህ ካለው አካሄድ ለመራቅ እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘አዲስ መመሪያ ወይም ማብራሪያ ሲሰጠን አሉታዊ ነገር መናገር ይቀናኛል? አመራር ከሚሰጡት ወንድሞች ላይ ስህተት የመለቃቀም ዝንባሌ አለኝ?’ እንዲህ ያሉ ዝንባሌዎችን ቶሎ ብለን የምናርም ከሆነ ይሖዋ ይደሰትብናል።—ምሳሌ 3:34, 35፤ w22.10 20 አን. 9-10
እሁድ፣ ጥቅምት 20
የእስራኤል ቤት . . . ሊሰሙህ አይፈልጉም።—ሕዝ. 3:7
የአምላክ መንፈስ፣ ሕዝቅኤል በክልሉ ውስጥ ላሉ “ግትርና ልበ ደንዳና” ሰዎች እንዲሰብክ ኃይል ሰጥቶታል። ይሖዋ ሕዝቅኤልን እንዲህ ብሎታል፦ “ፊትህን ልክ እንደ እነሱ ፊት ጠንካራ አድርጌዋለሁ፤ ግንባርህንም ልክ እንደ እነሱ ግንባር አጠንክሬዋለሁ። ግንባርህን እንደ አልማዝ፣ ከባልጩትም ይበልጥ ጠንካራ አድርጌዋለሁ። አትፍራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሳ አትሸበር።” (ሕዝ. 3:8, 9) ይሖዋ ለሕዝቅኤል እንዲህ ያለው ያህል ነበር፦ ‘የሰዎቹ ልበ ደንዳናነት ተስፋ እንዲያስቆርጥህ አትፍቀድ። እኔ አበረታሃለሁ።’ ከዚያም የአምላክ መንፈስ ሕዝቅኤልን ወደሚሰብክበት ክልል ወሰደው። ሕዝቅኤል “[የይሖዋ] ብርቱ እጅ በእኔ ላይ አርፋ ነበር” በማለት ጽፏል። ሕዝቅኤል መልእክቱን እስኪያብላላው ድረስ አንድ ሳምንት ፈጅቶበታል። (ሕዝ. 3:14, 15) ከዚያም ይሖዋ ወደ ሸለቋማው ሜዳ እንዲሄድ አዘዘው፤ በዚያም ‘መንፈስ ወደ ውስጡ ገባ።’ (ሕዝ. 3:23, 24) አሁን ሕዝቅኤል አገልግሎቱን ለመጀመር ዝግጁ ሆነ። w22.11 4-5 አን. 8-9
ሰኞ፣ ጥቅምት 21
ይሖዋ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? . . . ጭቆናንስ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ?—ዕን. 1:2, 3
ነቢዩ ዕንባቆም ብዙ ችግሮች አጋጥመውታል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ይሖዋ የሚያስብለት መሆኑን ተጠራጥሮ የነበረ ይመስላል። በመሆኑም በጸሎት ልቡን ለይሖዋ አፈሰሰ። ይሖዋ የታማኝ አገልጋዩን ልባዊ ጸሎት መልሶለታል። (ዕን. 2:2, 3) ዕንባቆም በይሖዋ የማዳን ሥራዎች ላይ ካሰላሰለ በኋላ ደስታው ተመለሰለት። ይሖዋ እንደሚያስብለትና የትኛውንም ፈተና ለመቋቋም እንደሚረዳው እርግጠኛ ሆነ። (ዕን. 3:17-19) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ችግሮች ሲያጋጥሟችሁ ወደ ይሖዋ በመጸለይ የሚሰማችሁን ንገሩት። ከዚያም የእሱን እርዳታ ፈልጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችላችሁን ኃይል እንደሚሰጣችሁ መተማመን ትችላላችሁ። ይሖዋ እንደረዳችሁ ስታዩ ደግሞ በእሱ ላይ ያላችሁ እምነት ይጠናከራል። ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዛችሁ ከቀጠላችሁ ችግርም ሆነ ጥርጣሬ ከይሖዋ ሊለያችሁ አይችልም።—1 ጢሞ. 6:6-8፤ w22.11 15 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22
እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።—ሉቃስ 23:43
ኢየሱስና ከጎኑ የተሰቀሉት ሁለት ወንጀለኞች ሊሞቱ እያጣጣሩ በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ናቸው። (ሉቃስ 23:32, 33) ሁለቱም ወንጀለኞች በኢየሱስ ላይ ሲያሾፉበት ነበር። (ማቴ. 27:44፤ ማር. 15:32) ሆኖም አንደኛው አመለካከቱን ቀየረ። እንዲህ አለ፦ “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ።” ኢየሱስም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን መልስ ሰጠው። (ሉቃስ 23:39-43) ኢየሱስ ለወንጀለኛው የተናገራቸው ቃላት፣ በገነት ውስጥ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል እንድናስብ ያነሳሱናል። ሰላም ከሰፈነበት የንጉሥ ሰለሞን ግዛት፣ ገነትን በተመለከተ አንዳንድ ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን። በተጨማሪም ከሰለሞን የሚበልጠው ኢየሱስ ከተባባሪ ገዢዎቹ ጋር ሆኖ ምድርን ውብ ገነት እንደሚያደርጋት መጠበቅ እንችላለን። (ማቴ. 12:42) በእርግጥም “ሌሎች በጎች” በገነት ውስጥ ለመኖር ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።—ዮሐ. 10:16፤ w22.12 8 አን. 1፤ 9 አን. 4
ረቡዕ፣ ጥቅምት 23
እርዳታ ለማግኘት በምትጮኹበት ጊዜ በእርግጥ ሞገስ ያሳያችኋል።—ኢሳ. 30:19
ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ወደ እሱ ስንጮኽ በጥሞና እንደሚያዳምጠንና ለምናቀርበው ምልጃ በአፋጣኝ መልስ እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል። አክሎም “ጩኸታችሁን እንደሰማም ይመልስላችኋል” ብሏል። እነዚህ የሚያበረታቱ ቃላት፣ አባታችን ወደ እሱ የሚጮኹትን ለመርዳት እንደሚፈልግ አልፎ ተርፎም እንደሚጓጓ ያስታውሱናል። ይህን ማወቃችን በደስታ ለመጽናት ይረዳናል። ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ጸሎት ትኩረት ይሰጣል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በኢሳይያስ ምዕራፍ 30 የመጀመሪያ ክፍል ላይ ይሖዋ ሕዝቡን እያነጋገረ የነበረው በቡድን ደረጃ ስለሆነ ጥቅሱ ላይ ያለው ግስ የብዙ ቁጥር ነው። ይሁንና ቁጥር 19 ላይ መልእክቱ የተላለፈው ለግለሰቦች ነው። ጥቅሱ በበኩረ ጽሑፉ “ፈጽሞ አታለቅስም”፤ “በእርግጥ ሞገስ ያሳይሃል” እንዲሁም “ይመልስልሃል” ይላል። ይሖዋ አፍቃሪ አባት ስለሆነ በግለሰብ ደረጃ ያስብልናል፤ የእያንዳንዳችንን ጸሎትም በጥሞና ያዳምጣል።—መዝ. 116:1፤ ኢሳ. 57:15፤ w22.11 9 አን. 5-6
ሐሙስ፣ ጥቅምት 24
እንደ እባብ ጠንቃቆች፣ እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ።—ማቴ. 10:16
ተቃውሞ ቢኖርም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ መካፈላችን ደስታና ሰላም ያስገኝልናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ባለሥልጣናት ሐዋርያቱ መስበካቸውን እንዲያቆሙ ባዘዟቸው ወቅት እነዚህ ታማኝ ሰዎች አምላክን ለመታዘዝ መርጠዋል። መስበካቸውን ቀጥለዋል፤ ይህ ሥራም ደስታ አስገኝቶላቸዋል። (ሥራ 5:27-29, 41, 42) እርግጥ በሥራችን ላይ ገደብ ከተጣለ፣ በምንሰብክበት ወቅት ጠንቃቃ መሆን ይኖርብናል። ሆኖም አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን ይሖዋን ከማስደሰት እንዲሁም ሕይወት አድን መልእክት ከመናገር የሚገኘውን ሰላም እናጣጥማለን። በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ ሰላም ማግኘት እንደምንችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን፣ የሚያስፈልገን የሰላም ዓይነት ይሖዋ ብቻ ሊሰጠው የሚችለው ሰላም እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ወረርሽኝ፣ አደጋ ወይም ስደት ሲያጋጥምህ በይሖዋ ታመን። ድርጅቱን የሙጥኝ በል። የተዘረጋልህን ግሩም የወደፊት ተስፋ አሻግረህ ተመልከት። እንዲህ ካደረግክ ‘የሰላም አምላክ ከአንተ ጋር ይሆናል።’—ፊልጵ. 4:9፤ w22.12 21 አን. 17-18
ዓርብ፣ ጥቅምት 25
አዲሱን ስብዕና [ልበሱ]።—ኤፌ. 4:24
ይህ ጥረት ይጠይቃል። የመረረ ጥላቻን፣ ቁጣን፣ ንዴትን እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ባሕርያትን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:31, 32) እንዲህ ማድረግ ከባድ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት ሥር የሰደዱ ናቸው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሰዎች ‘በቀላሉ የሚቆጡ’ እንደሆኑ ይናገራል። (ምሳሌ 29:22) ሥር የሰደዱ ባሕርያትን ለማስወገድ ከተጠመቅን በኋላም ጥረት ማድረግ ሊጠይቅብን ይችላል። (ሮም 7:21-23) ይሖዋ እንደሚሰማህና እንደሚረዳህ በመተማመን የሚያታግልህን ባሕርይ በተመለከተ ጸልይ። (1 ዮሐ. 5:14, 15) ይሖዋ ያንን ባሕርይ በተአምራዊ መንገድ ባያስወግድልህም እንኳ ለዚያ መጥፎ ባሕርይ እጅ እንዳትሰጥ ሊያበረታህ ይችላል። (1 ጴጥ. 5:10) በሌላ በኩል ደግሞ፣ አሮጌው ስብዕና እንዲያገረሽብህ ሊያደርጉህ ከሚችሉ ነገሮች በመራቅ ከጸሎትህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ። በተጨማሪም አእምሮህ በመጥፎ ምኞቶች ላይ እንዲያውጠነጥን አትፍቀድለት።—ፊልጵ. 4:8፤ ቆላ. 3:2፤ w23.01 10 አን. 7, 9-10
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 26
አምላክን የሚወድ ሁሉ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል።—1 ዮሐ. 4:21
ፍቅራችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል ነው። ላገኘነው ሰው ሁሉ እንሰብካለን። ሰዎች ዘራቸው፣ ብሔራቸው፣ የኑሮ ደረጃቸው ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ቦታ ምንም ሆነ ምን ማንንም ሳንመርጥ ሁሉንም ሰው እናናግራለን። በዚህ መንገድ የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም እናደርጋለን፤ “የእሱ ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።” (1 ጢሞ. 2:4) ለአምላክና ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ማሳየት ነው። በግለሰብ ደረጃ ትኩረት እንሰጣቸዋለን፤ ችግር ሲያጋጥማቸው ደግሞ እናግዛቸዋለን። የሚወዱትን ሰው በሞት ሲያጡ እናጽናናቸዋለን፤ ሲታመሙ እንጠይቃቸዋለን እንዲሁም ተስፋ ሲቆርጡ እናበረታታቸዋለን። (2 ቆሮ. 1:3-7፤ 1 ተሰ. 5:11, 14) “ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል” እንዳለው ስለምናውቅ ሁሌም እንጸልይላቸዋለን።—ያዕ. 5:16፤ w23.01 28-29 አን. 7-8
እሁድ፣ ጥቅምት 27
እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።—1 ተሰ. 5:11
አንድ የግንባታ ባለሙያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ክህሎቱን እያሻሻለ እንደሚሄድ ሁሉ እኛም ሌሎችን በማነጽ ረገድ ችሎታችንን ማሻሻል እንችላለን። ወንድሞቻችን የሚያጋጥማቸውን ፈተና በጽናት እንዲቋቋሙ ለመርዳት፣ ቀደም ሲል የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት የተቋቋሙ ሰዎችን ምሳሌ ልናካፍላቸው እንችላለን። (ዕብ. 11:32-35፤ 12:1) ሌሎች ስላሏቸው መልካም ባሕርያት በመናገር፣ ሰላማችን አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ እንዲሁም አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ለጉዳዩ እልባት በማበጀት ሰላም ማስፈን እንችላለን። (ኤፌ. 4:3) በተጨማሪም ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በማካፈል፣ ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት እንዲሁም በመንፈሳዊ የተዳከሙትን በመርዳት የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን እምነት ማጠናከር እንችላለን። በመንፈሳዊው የግንባታ ወይም የማነጽ ሥራ በምንካፈልበት ጊዜ ደስታና እርካታ እናገኛለን። በጊዜ ሂደት ከሚያረጁትና ከሚፈራርሱት ሕንፃዎች በተለየ መልኩ መንፈሳዊው የማነጽ ሥራችን የሚያስገኘው ውጤት ለዘላለም ይዘልቃል። w22.08 22 አን. 6፤ 25 አን. 17-18
ሰኞ፣ ጥቅምት 28
ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣልና፤ ከአፉ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ ይወጣል።—ምሳሌ 2:6
ኢየሱስ ከአምላክ ቃል ላይ የምናነበውን ነገር መረዳት ከፈለግን ሊኖረን የሚገባ አንድ አስፈላጊ ባሕርይ እንዳለ ጠቁሟል፤ ይህም ማስተዋል ነው። (ማቴ. 24:15) ማስተዋል ምንድን ነው? አንድ ሐሳብ ከሌላው ጋር የሚዛመደው ወይም የሚለያየው እንዴት እንደሆነ የመለየት እንዲሁም ፊት ለፊት የማይታይን ነገር የመረዳት ችሎታ ነው። ኢየሱስ እንደጠቆመው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ ለመረዳት ማስተዋል ያስፈልገናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከምናነበው ከእያንዳንዱ ሐሳብ የተሟላ ጥቅም ለማግኘትም ይህ ባሕርይ ያስፈልገናል። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ማስተዋል ይሰጣል። ስለዚህ ወደ እሱ በመጸለይ ይህን ባሕርይ ለማዳበር እንዲረዳችሁ ለምኑት። ከጸሎታችሁ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ የምትችሉት እንዴት ነው? የምታነቡትን ነገር በጥንቃቄ አጢኑ፤ እንዲሁም ከምታውቋቸው ነገሮች ጋር እንዴት እንደሚዛመድ አስቡ። የምታነቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ትርጉም ለመረዳት እንዲሁም እንዴት ተግባራዊ ልታደርጉት እንደምትችሉ ለማስተዋል ጥረት አድርጉ። (ዕብ. 5:14) በማስተዋል የምታነቡ ከሆነ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ያላችሁ ግንዛቤ እያደገ ይሄዳል። w23.02 10 አን. 7-8
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29
ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።—ሥራ 17:28
አንድ ወዳጃችሁ በጣም የቆየ ሆኖም ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጣ ሥዕል ሰጣችሁ እንበል። ሥዕሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ቀለሙ ለቋል፣ ቆሻሻ ነክቶታል፣ የተወሰነ መሰነጣጠቅም አለው። ያም ሆኖ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያወጣል። ይህን ሥዕል ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቱትና በጥንቃቄ እንደምትይዙት የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ይሖዋ ውድ የሆነ ስጦታ ሰጥቶናል፤ ይህም የሕይወት ስጦታ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ልጁን ለእኛ ቤዛ እንዲሆን በመስጠት ሕይወታችንን ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው አሳይቷል። (ዮሐ. 3:16) የሕይወት ምንጭ ይሖዋ ነው። (መዝ. 36:9) ሐዋርያው ጳውሎስም “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው” በማለት ይህን እውነታ አረጋግጧል። (ሥራ 17:25, 28) ከዚህ አንጻር ሕይወት የአምላክ ስጦታ ነው ማለታችን ተገቢ ነው። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በሕይወት ለመቀጠል የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሰጥቶናል። (ሥራ 14:15-17) ሆኖም ተአምራዊ በሆነ መንገድ ሕይወታችንን አይጠብቅልንም። ከዚህ ይልቅ በተቻለን መጠን አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነታችንን እንድንንከባከብ ይጠብቅብናል።—2 ቆሮ. 7:1፤ w23.02 20 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ጥቅምት 30
የምነግርህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፈው።—ኤር. 30:2
ይሖዋ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ይሖዋ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት የሚረዱ ጥበብ ያዘሉ ምክሮችን ሰጥቶናል። ስለ ወደፊቱ ጊዜም ግሩም ተስፋ ሰጥቶናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ባሕርያቱን ገልጦልናል። እሱ ባሉት ግሩም ባሕርያት ላይ ስናሰላስል ልባችን በጥልቅ ይነካል፤ በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት በመመሥረት ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንነሳሳለን። (መዝ. 25:14) ይሖዋ ሰዎች እንዲያውቁት ይፈልጋል። በጥንት ዘመን ሕልሞችን፣ ራእዮችን አልፎ ተርፎም መላእክትን በመጠቀም ራሱን ለሰዎች ገልጧል። (ዘኁ. 12:6፤ ሥራ 10:3, 4) ሆኖም እነዚህ ሕልሞች፣ ራእዮች ወይም በመላእክት በኩል የመጡ መልእክቶች በጽሑፍ ካልሰፈሩ እንዴት ልናጠናቸው እንችላለን? በእርግጥም ይሖዋ፣ እሱ እንድናውቅ የሚፈልገውን መልእክት ሰዎች ‘በመጽሐፍ እንዲጽፉ’ ማድረጉ ተገቢ ነው። “የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም” ስለሆነ እሱ ሐሳቡን ለእኛ ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ዘዴ ከሁሉ የተሻለና ጠቃሚ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝ. 18:30፤ w23.02 2 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ጥቅምት 31
ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35
ጠቃሚ ግቦች አውጣ። እምነትህን ለማጠናከርና ይበልጥ ጎልማሳ ለመሆን የሚረዱህን ግቦች አውጣ። (ኤፌ. 3:16) ለምሳሌ የግል ጥናት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ልማድህን ለማሻሻል ትወስን ይሆናል። (መዝ. 1:2, 3) ወይም ደግሞ አዘውትረህ መጸለይና የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል እንደሚያስፈልግህ ታስተውል ይሆናል። ምናልባትም ከመዝናኛ ምርጫ ወይም ከጊዜ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ይበልጥ ራስህን መግዛት ያስፈልግህ ይሆናል። (ኤፌ. 5:15, 16) ሌሎች ሰዎችን ስትረዳ ይበልጥ ጎልማሳ ትሆናለህ። ለምሳሌ በጉባኤህ ውስጥ ያሉ አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ግብ ማውጣት ትችላለህ። ምናልባትም ልትላላክላቸው ወይም በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አጠቃቀም ረገድ ልታግዛቸው ትችል ይሆናል። የመንግሥቱን ምሥራች በማካፈል ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎችም ፍቅር ማሳየት ትችላለህ። (ማቴ. 9:36, 37) ሁኔታህ የሚፈቅድልህ እስከሆነ ድረስ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ግብ አውጣ። w22.08 6 አን. 16-17