የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es25 ገጽ 7-17
  • ጥር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥር
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ ጥር 1
  • ሐሙስ፣ ጥር 2
  • ዓርብ፣ ጥር 3
  • ቅዳሜ፣ ጥር 4
  • እሁድ፣ ጥር 5
  • ሰኞ፣ ጥር 6
  • ማክሰኞ፣ ጥር 7
  • ረቡዕ፣ ጥር 8
  • ሐሙስ፣ ጥር 9
  • ዓርብ፣ ጥር 10
  • ቅዳሜ፣ ጥር 11
  • እሁድ፣ ጥር 12
  • ሰኞ፣ ጥር 13
  • ማክሰኞ፣ ጥር 14
  • ረቡዕ፣ ጥር 15
  • ሐሙስ፣ ጥር 16
  • ዓርብ፣ ጥር 17
  • ቅዳሜ፣ ጥር 18
  • እሁድ፣ ጥር 19
  • ሰኞ፣ ጥር 20
  • ማክሰኞ፣ ጥር 21
  • ረቡዕ፣ ጥር 22
  • ሐሙስ፣ ጥር 23
  • ዓርብ፣ ጥር 24
  • ቅዳሜ፣ ጥር 25
  • እሁድ፣ ጥር 26
  • ሰኞ፣ ጥር 27
  • ማክሰኞ፣ ጥር 28
  • ረቡዕ፣ ጥር 29
  • ሐሙስ፣ ጥር 30
  • ዓርብ፣ ጥር 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2025
es25 ገጽ 7-17

ጥር

ረቡዕ፣ ጥር 1

የአንድ ሰው አስከሬን ተሸክመው በመውጣት ላይ ነበሩ፤ ሟቹ ለእናቱ አንድ ልጇ ነበር። በተጨማሪም እናቱ መበለት ነበረች።—ሉቃስ 7:12

ኢየሱስ ለእናትየዋ በጣም ያዘነላት ‘ካያት’ በኋላ ነው። (ሉቃስ 7:13) ሆኖም ኢየሱስ ለእናትየዋ በማዘን ብቻ አልተወሰነም። ርኅራኄ አሳይቷታል። በሚያጽናና የድምፅ ቃና “በቃ፣ አታልቅሺ” አላት። ከዚያም እሷን ለመርዳት እርምጃ ወሰደ። ልጁን ከሞት በማስነሳት “ለእናቱ ሰጣት።” (ሉቃስ 7:14, 15) ኢየሱስ የመበለቷን ልጅ ከሞት እንዳስነሳ ከሚገልጸው ዘገባ ምን እንማራለን? ሐዘን ለደረሰባቸው ሰዎች ርኅራኄ ስለማሳየት ግሩም ትምህርት እናገኛለን። ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ትኩረት ሰጥተን በመመልከት እንደ ኢየሱስ ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። የሚያጽናኑ ቃላትን በመናገር እንዲሁም እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ነገር በማድረግ ቅድሚያውን ወስደን ርኅራኄ ልናሳያቸው እንችላለን። (ምሳሌ 17:17፤ 2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 1 ጴጥ. 3:8) ጥቂት ቃላት መናገራችን ወይም ቀለል ያሉ ነገሮችን ማድረጋችን እንኳ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። w23.04 5-6 አን. 13-15

ሐሙስ፣ ጥር 2

ይህ ሕመም ለአምላክ ክብር የሚያመጣ ነው እንጂ በሞት የሚያበቃ አይደለም።—ዮሐ. 11:4

ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር እንደሞተ ቢያውቅም ባለበት ቦታ ለሁለት ቀን ቆየ፤ ከዚያም ወደ ቢታንያ ጉዞ ጀመረ። በመሆኑም ኢየሱስ ቢታንያ በደረሰበት ወቅት አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖታል። ኢየሱስ ወዳጆቹን የሚጠቅምና አምላክን የሚያስከብር ነገር ለማድረግ አቅዷል። (ዮሐ. 11:6, 11, 17) ከዚህ ዘገባ ስለ ወዳጅነት ጥሩ ትምህርት እናገኛለን። ማርያምና ማርታ ወደ ኢየሱስ መልእክተኛ ሲልኩ ኢየሱስን ወደ ቢታንያ እንዲመጣ አልጠየቁትም። ወዳጁ እንደታመመ ብቻ ነው የነገሩት። (ዮሐ. 11:3) አልዓዛር ሲሞት ኢየሱስ ካለበት ቦታ ሆኖ ከሞት ሊያስነሳው ይችል ነበር። ሆኖም ወደ ቢታንያ ሄዶ ከወዳጆቹ ከማርያምና ከማርታ ጎን ለመሆን መርጧል። ሳትጠይቀው የሚደርስልህ ወዳጅ አለህ? እንዲህ ያለው ወዳጅ ‘በመከራ ቀን’ እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ምሳሌ 17:17) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል እኛም ለሌሎች እንዲህ ያለ ወዳጅ እንሁን! w23.04 10 አን. 10-11

ዓርብ፣ ጥር 3

የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ [ነው]።—ዕብ. 10:23

በፈተና ውስጥ ስንሆን ይሖዋ ያዘጋጀው አዲስ ዓለም ጨርሶ እንደማይመጣ ሊሰማን ይችላል። ይህ ማለት እምነታችን ተዳክሟል ማለት ነው? ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ክረምቱ በጣም ከባድ በሚሆንበት ጊዜ በጋ እንደማይመጣ ሊሰማን ይችላል። ያም ቢሆን በጋ መምጣቱ አይቀርም። በተመሳሳይም ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ አዲሱ ዓለም ጨርሶ እንደማይመጣ ሊሰማን ይችላል። እምነታችን ጠንካራ ከሆነ ግን አምላክ የሰጠው ተስፋ መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኞች እንሆናለን። (መዝ. 94:3, 14, 15፤ ዕብ. 6:17-19) እንዲህ ያለው እምነት በሕይወታችን የይሖዋን አምልኮ ማስቀደማችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። ጠንካራ እምነት የሚፈልገው ሌላው ነገር ደግሞ የስብከቱ ሥራችን ነው። ብዙ ሰዎች ስለ መጪው አዲስ ዓለም የሚገልጸው “ምሥራች” የሕልም እንጀራ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ማቴ. 24:14፤ ሕዝ. 33:32) ጥርጣሬያቸው እንዲጋባብን መፍቀድ አይኖርብንም። እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳያጋጥመን እምነታችንን በቀጣይነት ማጠናከር ይኖርብናል። w23.04 27 አን. 6-7፤ 28 አን. 14

ቅዳሜ፣ ጥር 4

የምንጠይቀውንም ነገር ሁሉ እንደሚሰማን ስለምናውቅ የምንጠይቀውን ነገር እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን።—1 ዮሐ. 5:15

ይሖዋ ጸሎትህን የሚመልስ መሆኑን ተጠራጥረህ ታውቃለህ? ከሆነ፣ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በርካታ ወንድሞችና እህቶች በተለይ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ይሖዋ ጸሎታቸውን የሚሰማ ስለመሆኑ ጥርጣሬ ይገባቸዋል። እኛም በመከራ ውስጥ ስንሆን ይሖዋ ጸሎታችንን እየመለሰልን ያለው እንዴት እንደሆነ ማስተዋል ሊከብደን ይችላል። ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንደሚመልስ እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በጥልቅ እንደሚወደንና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተን ዋስትና ይሰጠናል። (ሐጌ 2:7፤ 1 ዮሐ. 4:10) በጸሎት የእሱን እርዳታ እንድንጠይቅ የጋበዘን ለዚህ ነው። (1 ጴጥ. 5:6, 7) ምንጊዜም ከእሱ ጋር ተቀራርበን እንድንኖር እንዲሁም የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንድንቋቋም ሊረዳን ይፈልጋል። ይሖዋ የአገልጋዮቹን ጸሎት እንደመለሰላቸው የሚያሳዩ በርካታ ዘገባዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ከዚህ ጋር በተያያዘ ወደ አእምሮህ የሚመጣ ምሳሌ አለ? w23.05 8 አን. 1-4

እሁድ፣ ጥር 5

ማርያምም እንዲህ አለች፦ “ነፍሴ ይሖዋን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች።”—ሉቃስ 1:46

ማርያም በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መሥርታ ነበር። እምነቷ በዮሴፍ ላይ የተመካ አልነበረም። ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ታውቅ ነበር። ለማሰላሰልም ጊዜ መድባለች። (ሉቃስ 2:19, 51) ማርያም መንፈሳዊ ሴት መሆኗ ግሩም ሚስት እንድትሆን እንደረዳት ምንም ጥያቄ የለውም። በዛሬው ጊዜም በርካታ ሚስቶች የማርያምን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ኤሚኮ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከማግባቴ በፊት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈልበት የራሴ ፕሮግራም ነበረኝ። ካገባሁ በኋላ ግን የሚጸልየውም ሆነ የቤተሰብ አምልኮ የሚመራው ባለቤቴ ስለሆነ መንፈሳዊነቴ በእሱ ላይ የተመካ መሆን እንደጀመረ አስተዋልኩ። ከይሖዋ ጋር ባለኝ ወዳጅነት ረገድ የራሴን የኃላፊነት ሸክም መሸከም እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ስለዚህ ከአምላኬ ጋር ብቻዬን ሆኜ የምጸልይበት፣ መጽሐፍ ቅዱስን የማነብበትና በእሱ ሐሳቦች ላይ የማሰላስልበት ጊዜ መደብኩ።” (ገላ. 6:5) ሚስቶች፣ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ባጠናከራችሁ መጠን ባሎቻችሁ እናንተን የሚያመሰግኑበትና የሚወዱበት ተጨማሪ ምክንያት ያገኛሉ።—ምሳሌ 31:30፤ w23.05 22 አን. 6

ሰኞ፣ ጥር 6

ይሖዋን መፍራት አስተምራችኋለሁ።—መዝ. 34:11

ፈሪሃ አምላክ ይዘን አልተወለድንም፤ አምላካዊ ፍርሃት ልናዳብረው የሚገባ ነገር ነው። እንዲህ ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ፍጥረትን መመርመር ነው። የአምላክን ጥበብ፣ ኃይሉንና ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር “ከተሠሩት ነገሮች” ስናስተውል ለእሱ ያለን አክብሮትና ፍቅር እያደገ ይሄዳል። (ሮም 1:20) ለአምላካችን ፍርሃት ማዳበር የምንችልበት ሌላው መንገድ አዘውትረን መጸለይ ነው። ይበልጥ በጸለይን መጠን ይሖዋ ይበልጥ እውን ይሆንልናል። አንድን ፈተና ለመቋቋም ብርታት እንዲሰጠን በጠየቅነው ቁጥር ታላቅ ኃይል እንዳለው እናስታውሳለን። ልጁን ስለሰጠን ስናመሰግነው ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን እናስታውሳለን። ይሖዋ አንድን ችግር ለመወጣት እንዲረዳን ምልጃ ስናቀርብ ደግሞ ምን ያህል ጥበበኛ እንደሆነ እናስታውሳለን። እንዲህ ያሉት ጸሎቶች ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አክብሮት ያሳድጉልናል። በተጨማሪም ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት የሚያበላሽ ምንም ነገር ላለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክሩልናል። w23.06 15 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ ጥር 7

ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው።—ኢሳ. 33:22

የሁሉ የበላይ ሕግ አውጪ የሆነው ይሖዋ በዘመናት ሁሉ ለሕዝቡ ግልጽ ሕግጋትን ሲሰጥ ቆይቷል። ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል፣ ክርስቲያኖች ጽኑ አቋም ሊይዙባቸው የሚገቡ ሦስት አቅጣጫዎችን ጠቁሟል፤ እነሱም (1) ከጣዖት አምልኮ መራቅና ይሖዋን ብቻ ማምለክ፣ (2) ለደም ቅድስና አክብሮት ማሳየት እንዲሁም (3) የመጽሐፍ ቅዱስን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መታዘዝ ናቸው። (ሥራ 15:28, 29) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች በእነዚህ ሦስት አቅጣጫዎች ጽኑ አቋም መያዝ የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋን በማምለክና በመታዘዝ ነው። ይሖዋ እሱን ብቻ እንዲያመልኩ እስራኤላውያንን አዟቸዋል። (ዘዳ. 5:6-10) ኢየሱስም በዲያብሎስ በተፈተነበት ወቅት ልናመልክ የሚገባው ይሖዋን ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 4:8-10) ስለዚህ ጣዖት አናመልክም። ደግሞም ለየትኛውም ሰው አምልኮ አከል ክብር አንሰጥም፤ የሃይማኖት መሪዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች ወይም የስፖርቱና የመዝናኛው ዓለም ኮከቦች ጣዖት እንዲሆኑብን አንፈቅድም። የምናመልከው ‘ሁሉንም ነገሮች የፈጠረውን’ ይሖዋን ብቻ ነው።—ራእይ 4:11፤ w23.07 14-15 አን. 3-4

ረቡዕ፣ ጥር 8

ሰውም ይሖዋን በመፍራት ከክፋት ይርቃል።—ምሳሌ 16:6

የሰይጣን ዓለም የሥነ ምግባር ብልግናና ፖርኖግራፊ ተጠናውቶታል። (ኤፌ. 4:19) በመሆኑም አምላካዊ ፍርሃትን ማዳበርና ከክፋት መራቅ ይኖርብናል። ምሳሌ ምዕራፍ 9 ላይ ጥበብና ሞኝነት በሁለት ሴቶች ተመስለዋል። ሁለቱም ተሞክሮ ለሌላቸው ወይም “ማስተዋል ለጎደላቸው” ሰዎች ግብዣ እንደሚያቀርቡ ተደርጎ ተገልጿል። ሁለቱም በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘ወደ ቤቴ መጥታችሁ ምግብ ብሉ’ የሚል ግብዣ ያቀርባሉ። (ምሳሌ 9:1, 4-6) ሆኖም ግብዣውን የሚቀበሉ ሰዎች የሚገጥማቸው ውጤት በእጅጉ የተለያየ ነው። “ማስተዋል የጎደላት ሴት” የምታቀርበውን ግብዣ እንመልከት። (ምሳሌ 9:13-18) ይህች ኀፍረተ ቢስ ሴት ተሞክሮ የሌላቸውን ሰዎች ወደ እሷ መጥተው ምግብ እንዲበሉ ትጋብዛለች። ውጤቱስ ምንድን ነው? ጥቅሱ “በሞት የተረቱት በዚያ እንዳሉ” ይገልጻል። ምሳሌ መጽሐፍ “ጋጠወጥ” እና “ባለጌ” ስለሆነች ሴት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ “ቤቷ ሰውን ይዞ ወደ ሞት ይወርዳል” ይላል። (ምሳሌ 2:11-19) ምሳሌ 5:3-10 ደግሞ ስለ ሌላ “ጋጠወጥ ሴት” ይናገራል፤ እሷም ብትሆን “እግሮቿ ወደ ሞት ይወርዳሉ።” w23.06 21-22 አን. 6-7

ሐሙስ፣ ጥር 9

ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።—ፊልጵ. 4:5

ሽማግሌዎች ምክንያታዊ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል። (1 ጢሞ. 3:2, 3) ለምሳሌ አንድ ሽማግሌ በዕድሜ ከሌሎቹ ሽማግሌዎች ስለሚበልጥ ብቻ ሁልጊዜ የእሱን ሐሳብ መቀበል እንዳለባቸው ሊሰማው አይገባም። የይሖዋ መንፈስ በሽማግሌዎች አካል ውስጥ ባለ በየትኛውም ወንድም እንደሚጠቀምና ለውሳኔ የሚረዳ ጠቃሚ ሐሳብ እንዲናገር ሊመራው እንደሚችል ይገነዘባል። ደግሞም የእሱ ምርጫ ምንም ይሁን ምን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የሽማግሌዎች አካል በአብላጫ ድምፅ የሚያደርገውን ውሳኔ ይደግፋል። ምክንያታዊ የሆኑ ክርስቲያኖች ብዙ በረከቶችን ያገኛሉ። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጥሩ ወዳጅነት ይኖረናል። ጉባኤውም ሰላማዊ ይሆናል። አንድነት ባላቸው የይሖዋ አገልጋዮች መካከል ያለው የባሕርይና የባሕል ልዩነት የደስታ ምክንያት ይሆንልናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ምክንያታዊ የሆነውን አምላካችንን ይሖዋን እንደመሰልነው ስለምናውቅ ልባችን በእርካታ ይሞላል። w23.07 25 አን. 16-17

ዓርብ፣ ጥር 10

ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው . . . ይረዱታል።—ዳን. 12:10

ዳንኤል ትንቢቶችን ያጠናው በትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ተነሳስቶ ማለትም እውነትን ለማወቅ ነበር። በተጨማሪም ዳንኤል ትሑት ነበር፤ ይሖዋ እሱን ለሚያውቁና ንጹሕ በሆኑት የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ ለሚመሩ ሰዎች ማስተዋልን እንደሚሰጣቸው ተገንዝቧል። (ዳን. 2:27, 28) ዳንኤል የይሖዋን እርዳታ በመጠየቅ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዳን. 2:18) ከዚህም ሌላ ዳንኤል ትንቢቶችን ያጠናው በጥልቀት ነው። በወቅቱ የነበሩትን በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ቅዱሳን መጻሕፍት በጥንቃቄ መርምሯል። (ኤር. 25:11, 12፤ ዳን. 9:2) ታዲያ የዳንኤልን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? የልብ ዝንባሌህን መርምር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለማጥናት የሚያነሳሳህ እውነትን ለማወቅ ያለህ ጠንካራ ፍላጎት ነው? ከሆነ ይሖዋ ይረዳሃል። (ዮሐ. 4:23, 24፤ 14:16, 17) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዳልተጻፈ የሚያሳይ ማስረጃ ለማግኘት ሲሉ ትንቢቶችን ይመረምሩ ይሆናል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ካልሆነ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር የራሳቸውን መሥፈርት ማውጣትና በዚያ መመራት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እኛ ግን በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስተን ትንቢቶችን መመርመር ይኖርብናል። w23.08 9-10 አን. 7-8

ቅዳሜ፣ ጥር 11

ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል።—ምሳሌ 24:10

ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድር ከሆነ ይህ ሸክም ሊሆንብን ይችላል። (ገላ. 6:4) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ የምቀኝነትና የፉክክር ስሜት ሊጠናወተን ይችላል። (ገላ. 5:26) የሌሎችን ያህል ለመሥራት ስንል አቅማችንና ሁኔታችን ከሚፈቅድልን በላይ ልንጣጣር እንችላለን። “የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል” ከተባለ ጨርሶ ሊደረስበት የማይችል ግብ ማውጣትማ ምንኛ ልብ የሚያሳምም ይሆናል! (ምሳሌ 13:12) እንዲህ ማድረግ ጉልበታችንን ሊያሟጥጠውና ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ፍጥነታችንን ሊቀንሰው ይችላል። ይሖዋ ከሚጠብቅብህ በላይ ከራስህ አትጠብቅ። ይሖዋ በሌለህ መጠን እንድትሰጥ አይጠብቅብህም። (2 ቆሮ. 8:12) የምታከናውነውን ነገር ከሌሎች ጋር እንደማያወዳድር ተማመን። (ማቴ. 25:20-23) በሙሉ ልብ የምታቀርበውን አገልግሎት፣ ታማኝነትህንና ጽናትህን ከፍ አድርጎ ይመለከታል። w23.08 29 አን. 10-11

እሁድ፣ ጥር 12

በውኃ ጥም ልሙት?—መሳ. 15:18

ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ውኃ በማፍለቅ የሳምሶንን ልመና መለሰለት። ሳምሶን ከውኃው ሲጠጣ “ጥንካሬው ተመለሰ፤ ብርታትም አገኘ።” (መሳ. 15:19 ግርጌ) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው፣ ነቢዩ ሳሙኤል ከዓመታት በኋላ የመሳፍንት መጽሐፍን በመንፈስ መሪነት በጻፈበት ወቅትም ይህ ምንጭ ነበር። ይህን ውኃ የተመለከቱ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹ እስከታመኑበት ድረስ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ሁሉ እንደሚረዳቸው አስታውሰው መሆን አለበት። እኛም ምንም ያህል ችሎታ ወይም ተሰጥኦ ቢኖረን አሊያም በይሖዋ አገልግሎት ምንም ያህል ስኬት ብናገኝ ምንጊዜም የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል። ልካችንን ማወቅ እንዲሁም እውነተኛ ስኬት የሚገኘው በይሖዋ በመታመን ብቻ እንደሆነ አምነን መቀበል ይኖርብናል። ሳምሶን ይሖዋ ያዘጋጀለትን ውኃ በጠጣ ጊዜ ጥንካሬ እንዳገኘ ሁሉ እኛም ይሖዋ ባደረገልን ዝግጅቶች በሙሉ ስንጠቀም በመንፈሳዊ እንጠናከራለን።—ማቴ. 11:28፤ w23.09 4 አን. 8-10

ሰኞ፣ ጥር 13

የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል።—ምሳሌ 15:1

የሚፈታተን ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ እንችላለን? ለምሳሌ አንድ ሰው ስለ አምላካችን መጥፎ ነገር ቢናገር ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ቢያጣጥል ምን እናደርጋለን? ይሖዋ መንፈሱን እንዲሁም በገርነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል። ይሁንና ምላሽ የሰጠንበት መንገድ ጥሩ እንዳልነበረ በኋላ ላይ ብንገነዘብስ? ስለ ጉዳዩ በድጋሚ መጸለይ እንዲሁም ሌላ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ምላሽ መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማሰብ እንችላለን። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ቁጣችንን መቆጣጠርና ገርነት ማሳየት እንድንችል ቅዱስ መንፈሱን ይሰጠናል። ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አንደበታችንን እንድንቆጣጠር የሚረዱን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ። የአምላክ መንፈስ እነዚህን ጥቅሶች እንድናስታውስ ሊረዳን ይችላል። (ዮሐ. 14:26) ለአብነት ያህል፣ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ገር እንድንሆን ይረዱናል። (ምሳሌ 15:18) የምሳሌ መጽሐፍ በሚፈታተኑ ሁኔታዎች ውስጥ ራሳችንን መቆጣጠራችን ያለውን ጥቅምም ይገልጻል።—ምሳሌ 10:19፤ 17:27፤ 21:23፤ 25:15፤ w23.09 15 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ ጥር 14

ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም።—2 ጴጥ. 1:12

ሐዋርያው ጴጥሮስ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። ከኢየሱስ ጋር አብሮ ተጉዟል፤ አዳዲስ የስብከት መስኮችን ከፍቷል፤ እንዲሁም የበላይ አካል አባል ሆኖ አገልግሏል። አሁን ወደ ሕይወቱ መገባደጃ እየተቃረበ ነው። በዚህ ወቅት ይሖዋ ተጨማሪ ሥራ ሰጠው። ከ62-64 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በመንፈስ ተመርቶ ሁለት ደብዳቤዎችን ጻፈ። ደብዳቤዎቹ 1 ጴጥሮስ እና 2 ጴጥሮስ ተብለው ይጠራሉ። (2 ጴጥ. 1:13-15) ጴጥሮስ በመንፈስ ተመርቶ ደብዳቤዎቹን በጻፈበት ወቅት የእምነት አጋሮቹ ‘በልዩ ልዩ ፈተናዎች ተጨንቀው’ ነበር። (1 ጴጥ. 1:6) ክፉ ሰዎች የሐሰት ትምህርትንና ርኩስ ምግባርን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ለማስገባት እየሞከሩ ነበር። (2 ጴጥ. 2:1, 2, 14) በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ክርስቲያኖች “የሁሉም ነገር መጨረሻ” ቀርቦባቸዋል፤ ኢየሩሳሌምና የአይሁድ ሥርዓት በሮም ሠራዊት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል። (1 ጴጥ. 4:7) የጴጥሮስ ደብዳቤዎች፣ ክርስቲያኖች በወቅቱ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በጽናት እንዲቋቋሙና ወደፊት ለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች እንዲዘጋጁ እንደረዷቸው ምንም ጥያቄ የለውም። w23.09 26 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ጥር 15

[ክርስቶስ] ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ።—ዕብ. 5:8

እኛም እንደ ኢየሱስ ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥመን መታዘዝን እንማራለን። ለምሳሌ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት በስብሰባ አዳራሾች መሰብሰባችንንና ከቤት ወደ ቤት ማገልገላችንን እንድናቆም መመሪያ በተሰጠን ወቅት መታዘዝ አታግሎህ ነበር? ያም ቢሆን መታዘዝህ ጥበቃ አድርጎልሃል፤ ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር አንድነት እንዲኖርህ አድርጓል፤ እንዲሁም ይሖዋን አስደስቶታል። አሁን ሁላችንም፣ በታላቁ መከራ ወቅት የሚሰጠንን ማንኛውንም መመሪያ ለመታዘዝ ይበልጥ ዝግጁ ነን። እንዲህ ማድረጋችን የሕይወትና የሞት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 36:11) ይሖዋን ለመታዘዝ እንድንመርጥ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ስለምንወደውና እሱን ማስደሰት ስለምንፈልግ ነው። (1 ዮሐ. 5:3) ይሖዋ ላደረገልን መልካም ነገሮች ሁሉ ውለታውን ፈጽሞ ልንከፍለው አንችልም። (መዝ. 116:12) ይሁንና እሱንም ሆነ በእኛ ላይ ሥልጣን የሰጣቸውን ሰዎች ልንታዘዝ እንችላለን። ስንታዘዝ ጥበበኞች መሆናችንን እናሳያለን። ጥበበኛ ሰዎች ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛሉ።—ምሳሌ 27:11፤ w23.10 11 አን. 18-19

ሐሙስ፣ ጥር 16

ሰማይን [እና] ምድርን . . . የሠራውን አምልኩ።—ራእይ 14:7

አንድ መልአክ ቢያነጋግርህ የሚለውን ለመስማት ፈቃደኛ ትሆናለህ? በአሁኑ ወቅት አንድ መልአክ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” እየተናገረ ነው። መልእክቱ ምንድን ነው? “አምላክን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ . . . ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና የውኃ ምንጮችን የሠራውን አምልኩ” የሚል ነው። (ራእይ 14:6, 7) ሁሉም ሰው ሊያመልከው የሚገባው ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ይሖዋ ነው። ይሖዋ በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እሱን የማምለክ ውድ መብት ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ለመሆኑ መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምንድን ነው? ይህን ቤተ መቅደስ በተመለከተ ማብራሪያ ማግኘት የምንችለውስ ከየት ነው? መንፈሳዊው ቤተ መቅደስ በእውን ያለ ሕንፃ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ተቀባይነት ያለው አምልኮ ማቅረብ እንድንችል ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ይኖሩ ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህን ዝግጅት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል። w23.10 24 አን. 1-2

ዓርብ፣ ጥር 17

“በመንፈሴ እንጂ፣ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም” ይላል . . . ይሖዋ።—ዘካ. 4:6

በ522 ዓ.ዓ. የአይሁዳውያን ጠላቶች የይሖዋን ቤተ መቅደስ መልሶ የመገንባቱ ሥራ እንዲታገድ አደረጉ። ሆኖም ዘካርያስ፣ ይሖዋ ኃያል የሆነውን መንፈሱን ተጠቅሞ ማንኛውንም እንቅፋት እንደሚያስወግድላቸው ለአይሁዳውያኑ ዋስትና ሰጣቸው። በ520 ዓ.ዓ. ንጉሥ ዳርዮስ በቤተ መቅደሱ የግንባታ ሥራ ላይ የተጣለውን እገዳ ያነሳ ከመሆኑም ሌላ አይሁዳውያኑ የገንዘብ እርዳታና የባለሥልጣናቱን ድጋፍ እንዲያገኙ አደረገ። (ዕዝራ 6:1, 6-10) ይሖዋ ሕዝቦቹ ቤተ መቅደሱን መልሶ ለመገንባቱ ሥራ ቅድሚያ ከሰጡ እሱ እንደሚረዳቸው አረጋገጠላቸው። (ሐጌ 1:8, 13, 14፤ ዘካ. 1:3, 16) ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን በነቢያቱ ተበረታተው በ520 ዓ.ዓ. ቤተ መቅደሱን መገንባታቸውን ቀጠሉ። ከዚያም አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የግንባታ ሥራውን አጠናቀቁ። አይሁዳውያኑ ተነዋዋጭ በሆነ ጊዜ ውስጥም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቅድሚያ በመስጠታቸው የይሖዋን ድጋፍ አግኝተዋል። በዚህም የተነሳ ይሖዋን በደስታ ማምለክ ችለዋል።—ዕዝራ 6:14-16, 22፤ w23.11 15 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ጥር 18

አባታችን አብርሃም . . . የነበረውን እምነት [ተከትላችሁ] በሥርዓት [ተመላለሱ]።—ሮም 4:12

ብዙ ሰዎች ስለ አብርሃም ሰምተው ቢያውቁም አብዛኞቹ ስለ እሱ የሚያውቁት ነገር ውስን ነው። አንተ ግን ስለ አብርሃም ብዙ ነገር ታውቃለህ። ለምሳሌ አብርሃም ‘እምነት ላላቸው ሁሉ አባት’ ተብሎ እንደተጠራ ታውቃለህ። (ሮም 4:11) ይሁንና እንዲህ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል፦ ‘እኔስ የአብርሃምን ፈለግ መከተልና የእሱ ዓይነት እምነት ማዳበር እችል ይሆን?’ በሚገባ! የአብርሃም ዓይነት እምነት ማዳበር የምንችልበት አንዱ መንገድ የእሱን ምሳሌ በማጥናት ነው። አብርሃም አምላክን በመታዘዝ ወደ ሩቅ አገር ሄዷል፤ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በድንኳን ውስጥ ኖሯል፤ እንዲሁም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆኗል። እነዚህ ነገሮች አብርሃም ጠንካራ እምነት እንደነበረው ያሳያሉ። አብርሃም የነበረው እምነትና ያከናወነው ሥራ የአምላክን ሞገስ ያስገኘለት ከመሆኑም ሌላ የእሱ ወዳጅ ለመባል አብቅቶታል። (ያዕ. 2:22, 23) ይሖዋ አንተን ጨምሮ ሁላችንም እነዚህን በረከቶች እንድናገኝ ይፈልጋል። በመሆኑም ጳውሎስንና ያዕቆብን በመንፈሱ በመምራት አብርሃም ስለተወው ምሳሌ እንዲጽፉ አድርጓቸዋል። w23.12 2 አን. 1-2

እሁድ፣ ጥር 19

ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት።—ያዕ. 1:19

እህቶች፣ የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ አዳብሩ። ክርስቲያኖች ከሌሎች ጋር ውጤታማ በሆነ መንገድ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በዚህ ረገድ ከላይ የተጠቀሰውን ጥሩ ምክር ሰጥቶናል። ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና የምታዳምጡ ከሆነ ‘ስሜታቸውን እንደምትረዱላቸው’ ታሳያላችሁ። (1 ጴጥ. 3:8) ግለሰቡ የተናገረው ሐሳብ ወይም የተሰማው ስሜት በደንብ ካልገባችሁ ተገቢ ጥያቄዎችን ጠይቁ። ከዚያም ከመናገራችሁ በፊት ቆም ብላችሁ አስቡ። (ምሳሌ 15:28 ግርጌ) እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ልናገር ያሰብኩት ነገር እውነተኛና የሚያንጽ ነው? አክብሮትና ደግነት የሚንጸባረቅበት ነው?’ የሐሳብ ልውውጥ በማድረግ ረገድ ጥሩ ችሎታ ካላቸው የጎለመሱ እህቶች ተማሩ። (ምሳሌ 31:26) የሚናገሩበትን መንገድ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ይህን ክህሎት ባዳበራችሁ መጠን ከሌሎች ጋር ያላችሁ ዝምድና ይሻሻላል። w23.12 21 አን. 12

ሰኞ፣ ጥር 20

ራሱን የሚያገል ሰው ሁሉ [ጥበብን] ይቃወማል።—ምሳሌ 18:1

በዛሬው ጊዜ ይሖዋ እኛን ለመደገፍ ቤተሰቦቻችንን፣ ጓደኞቻችንን ወይም ሽማግሌዎችን ሊጠቀም ይችላል። ይሁንና በሐዘን በምንደቆስበት ጊዜ ራሳችንን ማግለል ሊቀናን ይችላል። ብቻችንን መሆን ልንፈልግ እንችላለን። እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። ታዲያ የይሖዋን ድጋፍ ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? ራስህን ላለማግለል ጥረት አድርግ። ራሳችንን ስናገል እይታችን ስለሚጠብ ስለ ራሳችንና ስላጋጠመን ችግር ብቻ ማሰብ ልንጀምር እንችላለን። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በምናደርጋቸው ውሳኔዎችም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሁላችንም በተለይ ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ብቻችንን መሆን የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል። ይሁንና ለረጅም ጊዜ ራሳችንን አግልለን ከቆየን ይሖዋ እኛን ለመደገፍ የሚጠቀምበትን መንገድ ልንዘጋ እንችላለን። እንግዲያው የቤተሰቦችህን፣ የጓደኞችህንና የሽማግሌዎችን እርዳታ ተቀበል። ይሖዋ የሚደግፍህ እነሱን ተጠቅሞ እንደሆነ አስታውስ።—ምሳሌ 17:17፤ ኢሳ. 32:1, 2፤ w24.01 24 አን. 12-13

ማክሰኞ፣ ጥር 21

ራሱን ምላጭ አይንካው።—ዘኁ. 6:5

ናዝራውያን ፀጉራቸውን ላለመቆረጥ ይሳሉ ነበር። ይህም ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ እንደሚገዙ የሚያሳይ ምልክት ነበር። የሚያሳዝነው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ናዝራውያን አድናቆት ወይም ድጋፍ ያላገኙበት ጊዜ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ ናዝራውያን ስእለታቸውን መፈጸምና የተለዩ ሆነው መታየት ድፍረት ጠይቆባቸው ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ የለውም። (አሞጽ 2:12) ለይሖዋ ፈቃድ ስለምንገዛ እኛም በዙሪያችን ካሉት ሰዎች የተለየን መሆናችን አይቀርም። በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ለማሳወቅ ድፍረት ያስፈልገናል። በዓለም ያሉ ሰዎች ባሕርይና ምግባር እየከፋ ሲሄድ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራትና ምሥራቹን ለሌሎች ማወጅ ይበልጥ እየከበደን ሊሄድ ይችላል። (2 ጢሞ. 1:8፤ 3:13) ይሁንና ይሖዋ እሱን ከማያመልኩ ሰዎች በድፍረት የተለየ አቋም ስንይዝ ‘ልቡ እንደሚደሰት’ ምንጊዜም አስታውሱ።—ምሳሌ 27:11፤ ሚል. 3:18፤ w24.02 16 አን. 7፤ 17 አን. 9

ረቡዕ፣ ጥር 22

አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።—ሮም 15:7

በሮም ጉባኤ ውስጥ ያሉት ሰዎች ምን ያህል የተለያዩ እንደነበሩ ለማሰብ ሞክሩ። አንዳንዶቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ የተማሩ አይሁዳውያን ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ከዚህ የተለየ አስተዳደግ ያላቸው አሕዛብ ናቸው። አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ባሪያዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። ሌሎቹ ደግሞ ነፃ ሰዎች ናቸው፤ እንዲያውም ባሪያ አሳዳሪዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ልዩነታቸው ጋሬጣ ሳይሆንባቸው ከልብ መዋደድ የቻሉት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ” ብሏቸዋል። ምን ማለቱ ነበር? “ተቀበሉ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አንድን ሰው ማስተናገድ፣ ወደ ቤት አሊያም ወደ ጓደኛሞች ቡድን እንዲገባ በደግነት መጋበዝ ማለትም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ጳውሎስ፣ የኮበለለውን ባሪያውን አናሲሞስን እንዲቀበለው ለፊልሞና ሲነግረው “በደግነት ተቀበለው” ብሎታል። (ፊልሞና 17) ጵርስቅላና አቂላም ስለ ክርስትና በቂ ግንዛቤ ያልነበረውን አጵሎስን “ይዘውት በመሄድ” በደግነት ተቀብለውታል። (ሥራ 18:26) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ልዩነታቸው እንዲከፋፍላቸው ከመፍቀድ ይልቅ አንዳቸው ሌላውን ተቀብለዋል። w23.07 6 አን. 13

ሐሙስ፣ ጥር 23

ስእለቴን ለይሖዋ እፈጽማለሁ።—መዝ. 116:14

ራስህን ለይሖዋ እንድትወስን የሚያነሳሳህ ዋነኛው ምክንያት ለእሱ ያለህ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር በስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘በትክክለኛ እውቀት’ እና ‘በመንፈሳዊ ግንዛቤ’ ማለትም ለይሖዋ ያለህ ፍቅር እንዲያድግ ባደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተ ነው። (ቆላ. 1:9) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትህ (1) ይሖዋ እውን እንደሆነ፣ (2) መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንዲሁም (3) ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ድርጅቱን እንደሚጠቀም እንድታምን አድርጎሃል። ራሳቸውን ለይሖዋ የሚወስኑ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ትምህርቶች ማወቅ እንዲሁም በቃሉ ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች መመራት ይኖርባቸዋል። ሁኔታቸው በሚፈቅድላቸው መጠን እምነታቸውን ለሌሎች ያካፍላሉ። (ማቴ. 28:19, 20) ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር አድጓል፤ እንዲሁም እሱን ብቻ ለማምለክ ልባዊ ፍላጎት አላቸው። አንተስ እነዚህን ነገሮች እያደረግክ ነው? w24.03 4-5 አን. 6-8

ዓርብ፣ ጥር 24

አንድ ሥጋ ይሆናሉ።—ዘፍ. 2:24

አቢጋኤል የናባል ሚስት ነበረች። ናባል ኃይለኛና ምግባረ ብልሹ ሰው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ሳሙ. 25:3) እንዲህ ካለ ሰው ጋር መኖር ለአቢጋኤል በጣም ከባድ እንደሚሆንባት ምንም ጥያቄ የለውም። አቢጋኤል ከዚህ ትዳር መገላገል የምትችልበት ቀላል መንገድ ይኖር ይሆን? ወደፊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተሾመው ዳዊት፣ ናባል እሱንና ሰዎቹን ስለሰደባቸው ሊገድለው በመጣ ጊዜ አቢጋኤል እንዲህ ያለ አጋጣሚ አግኝታ ነበር። (1 ሳሙ. 25:9-13) አቢጋኤል በዳዊት ዕቅድ ውስጥ ጣልቃ ሳትገባ መሸሽ ትችል ነበር። ያም ቢሆን እርምጃ ወሰደች፤ ዳዊት ናባልን እንዳይገድለው አሳመነችው። (1 ሳሙ. 25:23-27) አቢጋኤል እንዲህ እንድታደርግ ያነሳሳት ምን ሊሆን ይችላል? አቢጋኤል ይሖዋን ትወደው ነበር፤ እንዲሁም እሱ ለትዳር ላወጣው መሥፈርት አክብሮት ነበራት። ይሖዋ ትዳርን ቅዱስ አድርጎ እንደሚመለከተው ታውቅ ነበር። አቢጋኤል አምላክን ማስደሰት ትፈልግ ነበር፤ ይህም ባለቤቷን ጨምሮ ቤተሰቧን በሙሉ ለመታደግ አቅሟ የፈቀደውን ሁሉ እንድታደርግ አነሳስቷታል። ዳዊት ናባልን እንዳይገድለው ለማድረግ አፋጣኝ እርምጃ ወሰደች። w24.03 16-17 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ ጥር 25

በአፌ ቃል አበረታችሁ ነበር።—ኢዮብ 16:5

በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ሰፋ ያለ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ ሕይወታቸውን ቀላል ለማድረግ እየሞከሩ ያሉ አስፋፊዎች በጉባኤያችሁ ውስጥ አሉ? በጣም ተፈታታኝ ቢሆንባቸውም በትምህርት ቤት ከሌሎች የተለየ አቋም ለመያዝ የሚሞክሩ ደፋር ወጣቶች አሉ? የቤተሰብ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም ታማኝ ለመሆን እየታገሉ ያሉስ ታውቃላችሁ? እንዲህ ያሉ የእምነት አጋሮቻችን ለሚያሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስና ድፍረት አድናቆታችንን በመግለጽ እነሱን ለማበረታታት ያገኘነውን አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀም። (ፊልሞና 4, 5, 7) ይሖዋ እሱን ለማስደሰት ልባዊ ፍላጎት እንዳለንና ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ስእለት ለመፈጸም ስንል አንዳንድ መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኞች እንደሆንን እርግጠኛ ነው። ለእሱ ያለንን ፍቅር በፈቃደኝነት እንድናሳይ አጋጣሚ በመስጠት አክብሮናል። (ምሳሌ 23:15, 16) እንግዲያው ለይሖዋ በፈቃደኝነት ምርጣችንን በመስጠት እሱን ማገልገላችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። w24.02 18 አን. 14፤ 19 አን. 16

እሁድ፣ ጥር 26

መልካም ነገር እያደረገና . . . እየፈወሰ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ።—ሥራ 10:38

ጊዜው 29 ዓ.ም. መገባደጃ አካባቢ ነው። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከጀመረ ብዙም አልቆየም። ኢየሱስና እናቱ ማርያም በቃና በተካሄደ ሠርግ ላይ ተገኝተዋል። ማርያም እንግዶቹን በማስተናገዱ ሥራ ተጠምዳለች። ሆኖም በድግሱ ወቅት አንድ ችግር ተፈጠረ፤ የወይን ጠጅ አለቀባቸው። ማርያም ቶሎ ብላ ወደ ልጇ በመሄድ “የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው። (ዮሐ. 2:1-3) ታዲያ ኢየሱስ ምን ያደርግ ይሆን? ውኃውን ወደ ‘ጥሩ የወይን ጠጅ’ ቀየረው። (ዮሐ. 2:9, 10) ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎች በርካታ ተአምራትንም ፈጽሟል። ተአምር የመፈጸም ችሎታውን ተጠቅሞ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ረድቷል። ሁለቱን ተአምራት ብቻ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ 5,000 ወንዶችን፣ በኋላ ላይ ደግሞ 4,000 ወንዶችን በመገበበት ወቅት በቦታው የነበሩትን ሴቶችና ልጆችም ከቆጠርን የተመገቡት ሰዎች ቁጥር ከ27,000 በላይ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 14:15-21፤ 15:32-38) በሁለቱም ጊዜያት ኢየሱስ ብዙ ሕመምተኞችንም ፈውሷል።—ማቴ. 14:14፤ 15:30, 31፤ w23.04 2 አን. 1-2

ሰኞ፣ ጥር 27

“አትፍራ። እረዳሃለሁ” የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁ።—ኢሳ. 41:13

ከባድ መከራ ሲያጋጥመን በአካላዊም ሆነ በስሜታዊ እንደዛልን የሚሰማን ጊዜ ይኖራል። እንደ ኤልያስ መነሳት ሊከብደንና መተኛት ብቻ ሊያሰኘን ይችላል። (1 ነገ. 19:5-7) በይሖዋ አገልግሎት መካፈላችንን እንድንቀጥል እርዳታ ሊያስፈልገን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ዋስትና ሰጥቶናል። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ያለውን እርዳታ አግኝቷል። ከፈተናዎችና ከጠላቶቹ ጋር በተጋፈጠበት ወቅት ይሖዋን “ቀኝ እጅህ ይደግፈኛል” ብሎታል። (መዝ. 18:35) ይሖዋ ብዙውን ጊዜ የሚደግፈን ሌሎች እንዲረዱን በማነሳሳት ነው። ለምሳሌ ዳዊት በዛለበት ወቅት ጓደኛው ዮናታን ወደ እሱ በመምጣት ስሜታዊ ድጋፍና ማበረታቻ ሰጥቶታል። (1 ሳሙ. 23:16, 17) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ለኤልያስ ተግባራዊ እርዳታ እንዲሰጠው ኤልሳዕን መርጦታል።—1 ነገ. 19:16, 21፤ 2 ነገ. 2:2፤ w24.01 23-24 አን. 10-12

ማክሰኞ፣ ጥር 28

ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣልና፤ ከአፉ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ ይወጣል።—ምሳሌ 2:6

ይሖዋ ማንኛውንም ነገር አትረፍርፎ የሚያቀርብ ለጋስ አምላክ ነው። በምሳሌ ምዕራፍ 9 ላይ በሴት በተመሰለችው “እውነተኛ ጥበብ” ላይ ይህ ባሕርይ ተንጸባርቋል። ዘገባው ይህች ምሳሌያዊ ሴት የወይን ጠጇን እንደደባለቀች፣ ሥጋዋን በሚገባ እንዳዘጋጀች እንዲሁም ገበታዋን እንዳሰናዳች ይናገራል። (ምሳሌ 9:2) በተጨማሪም በቁጥር 4 እና 5 መሠረት እውነተኛ ጥበብ “ማስተዋል ለጎደለው እንዲህ ትላለች፦ ‘ኑ፣ ያዘጋጀሁትን ምግብ ብሉ።’” ወደ እውነተኛ ጥበብ ቤት ሄደን የምታቀርብልንን ምግብ መመገብ ያለብን ለምንድን ነው? ይሖዋ ልጆቹ ጥበበኛ እንዲሆኑና ከጉዳት እንዲጠበቁ ይፈልጋል። ከመከራ እንድንማርና በጸጸት እንድንዋጥ አይፈልግም። “ለቅኖች ጥበብን እንደ ውድ ሀብት” የሚያከማቸው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 2:7) ለይሖዋ ጤናማ ፍርሃት ካለን እሱን ማስደሰት እንፈልጋለን። ጥበብ የሚንጸባረቅበትን ምክሩን እንሰማለን፤ እንዲሁም በሥራ ላይ እናውላለን።—ያዕ. 1:25፤ w23.06 23-24 አን. 14-15

ረቡዕ፣ ጥር 29

አምላክ . . . የምታከናውኑትን ሥራ . . . በመርሳት ፍትሕ አያዛባም።—ዕብ. 6:10

በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምንችለው ነገር ውስን እንደሆነ ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ልባዊ ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይህን እንዴት እናውቃለን? በዘካርያስ ዘመን ይሖዋ በባቢሎን ያሉት አይሁዳውያን የላኩትን ወርቅና ብር ተጠቅሞ አክሊል እንዲሠራ ለነቢዩ ነግሮት ነበር። (ዘካ. 6:11) ይህ ‘ታላቅ አክሊል’ በልግስና ላደረጉት መዋጮ “ማስታወሻ” ሆኖ ያገለግላል። (ዘካ. 6:14 ግርጌ) ይሖዋ ተነዋዋጭ በሆነ ጊዜ ውስጥ እሱን ለማገልገል የምናደርገውን ልባዊ ጥረት መቼም እንደማይረሳው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ስንኖር ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችም እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን፤ ወደፊት ደግሞ ሁኔታዎች ይበልጥ ሊባባሱ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:1, 13) ያም ቢሆን በጭንቀት ልንዋጥ አይገባም። ይሖዋ በሐጌ ዘመን ለነበሩት ሕዝቦቹ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ . . . አትፍሩ” እንዳላቸው አስታውስ። (ሐጌ 2:4, 5) እኛም የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም አቅማችን የፈቀደውን እስካደረግን ድረስ እሱ ከእኛ ጋር እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w23.11 19 አን. 20-21

ሐሙስ፣ ጥር 30

እኔ ኃጢአተኛ [ነኝ]።—ሉቃስ 5:8

ይሖዋ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ የሠራቸው ስህተቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳይጻፉ ማድረግ ይችል ነበር። ያም ቢሆን ትምህርት እንድናገኝባቸው ሲል እንዲጻፉልን አድርጓል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ልክ እንደ እኛ ያሉ ድክመቶችና ስሜቶች ስላሉት ስለዚህ ሰው መማራችን ይሖዋ ከእኛ ፍጽምና እንደማይጠብቅ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይሖዋ ድክመት ቢኖርብንም እንድንጸና ማለትም ለመሻሻል ጥረት ማድረጋችንን እንድንቀጥል ይፈልጋል። መጽናታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድን ድክመት እንዳሸነፍነው ከተሰማን በኋላም ችግሩ ሊያገረሽብን ይችላል። ሆኖም ለመሻሻል ጥረት ማድረጋችንን አናቆምም። ሁላችንም በኋላ ላይ የምንጸጸትበትን ነገር እናደርጋለን ወይም እንናገራለን፤ ያም ቢሆን ተስፋ ካልቆረጥን ይሖዋ ለውጥ ማድረጋችንን እንድንቀጥል ይረዳናል። (1 ጴጥ. 5:10) ጴጥሮስ ስህተት ቢሠራም ኢየሱስ ርኅራኄ እንዳሳየው መገንዘባችን እኛም ይሖዋን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል። w23.09 20-21 አን. 2-3

ዓርብ፣ ጥር 31

ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር።—ዮሐ. 11:21

ማርታ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እንደተናገረችው ኢየሱስ አልዓዛርን ሊፈውሰው ይችል ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ነገር ለማድረግ አስቧል። “ወንድምሽ ይነሳል” በማለት ቃል ገባላት። በተጨማሪም ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” አላት። (ዮሐ. 11:23, 25) አዎ፣ አምላክ ለኢየሱስ በሕይወትና በሞት ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ቀደም ሲል አንዲትን ትንሽ ልጅ ከሞተች ብዙም ሳይቆይ አስነስቷል። በተጨማሪም አንድን ወጣት ከሞት አስነስቷል፤ ይህንንም ያደረገው ወጣቱ በሞተበት ዕለት ሳይሆን አይቀርም። (ሉቃስ 7:11-15፤ 8:49-55) ሆኖም ከሞተ አራት ቀን የሆነውንና ሰውነቱ መበስበስ የጀመረን ሰው ሊያስነሳ ይችላል? የአልዓዛር ሌላኛዋ እህት የሆነችው ማርያም ኢየሱስን ለማግኘት ወጣች። እሷም እንደ እህቷ “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው። (ዮሐ. 11:32) ኢየሱስ ማርያም እና ሌሎቹ ሰዎች ሲያለቅሱ ሲያይ እጅግ አዘነ። ኢየሱስ ወዳጆቹ ያሉበት ሁኔታ በጣም ስላሳዘነው እንባውን አፈሰሰ። የቤተሰብን አባል በሞት ማጣት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይረዳል። እንባቸውን እንዲያፈስሱ ምክንያት የሆነውን ነገር ለማስወገድ እንደጓጓ ጥያቄ የለውም! w23.04 10-11 አን. 12-13

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ