የካቲት
ቅዳሜ፣ የካቲት 1
እሰማችኋለሁ።—ኤር. 29:12
ንጉሥ ሕዝቅያስ በጠና በታመመ ጊዜ ይሖዋ እንዲያድነው ለምኖ ነበር። ይሖዋም ፈወሰው። (2 ነገ. 20:1-6) በሌላ በኩል ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሥጋውን የሚወጋውን እሾህ’ እንዲያስወግድለት ይሖዋን ጠይቆ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ችግሩን አላስወገደለትም። (2 ቆሮ. 12:7-9) ሐዋርያው ያዕቆብና ሐዋርያው ጴጥሮስም በንጉሥ ሄሮድስ የመገደል አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። ያዕቆብ ተገደለ፤ ጴጥሮስ ግን በተአምር ተረፈ። (ሥራ 12:1-11) ‘ይሖዋ ጴጥሮስን አድኖ ያዕቆብ ግን እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን አይነግረንም። በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር ቢኖር ይሖዋ ‘ፈጽሞ ፍትሕን እንደማያጓድል’ ነው። (ዘዳ. 32:4) አንዳንድ ጊዜ ያልጠበቅነው ነገር ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ጸሎታችንን የሚመልስበት መንገድ ምንጊዜም ፍቅርና ፍትሕ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ስለምንተማመን በሚሰጠን መልስ ላይ ጥያቄ አናነሳም።—ኢዮብ 33:13፤ w23.11 21 አን. 6
እሁድ፣ የካቲት 2
ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . ለመታዘዝ ዝግጁ . . . ነው።—ያዕ. 3:17
ያዕቆብ ጥበበኛ ሰዎች “ለመታዘዝ ዝግጁ” እንደሆኑ በመንፈስ መሪነት ጽፏል። ይህ ምን ማለት ነው? ይሖዋ የተወሰነ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች ለመታዘዝ ፈቃደኞች ልንሆን ብሎም ልንጓጓ ይገባል። እርግጥ ነው ይሖዋ፣ እሱ የሰጠንን ትእዛዝ እንድንጥስ የሚጠይቀንን ሰው እንድንታዘዝ አይጠብቅብንም። (ሥራ 4:18-20) ሰዎችን ከመታዘዝ ይልቅ ይሖዋን መታዘዝ ሊቀለን ይችላል። ምክንያቱም ይሖዋ የሚሰጠን መመሪያ ሁልጊዜም ፍጹም ነው። (መዝ. 19:7) ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ግን ፍጹማን አይደሉም። ያም ቢሆን የሰማዩ አባታችን ለወላጆች፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም ለሽማግሌዎች የተወሰነ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (ምሳሌ 6:20፤ 1 ተሰ. 5:12፤ 1 ጴጥ. 2:13, 14) እነሱን ስንታዘዝ ይሖዋን እየታዘዝን ነው ሊባል ይችላል። w23.10 6 አን. 2-3
ሰኞ፣ የካቲት 3
እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት [ናቸው]።—ራእይ 21:5
እምነታችንን ማጠናከር የምንችልበት አንዱ መንገድ በይሖዋ ኃይል ላይ ማሰላሰል ነው። ይሖዋ ቃል የገባውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል አለው። ምክንያቱም እሱ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። (ኢዮብ 42:2፤ ማር. 10:27፤ ኤፌ. 3:20) ለምሳሌ አብርሃምና ሣራ በስተ እርጅናቸው ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ቃል ገብቶላቸዋል። (ዘፍ. 17:15-17) በተጨማሪም ዘሮቹ የከነአንን ምድር እንደሚወርሱ ለአብርሃም ነግሮታል። የአብርሃም ዘሮች የሆኑት እስራኤላውያን በግብፅ ባሪያዎች በነበሩባቸው በርካታ ዓመታት ይህ ቃል ሊፈጸም የሚችል አይመስልም ነበር። ሆኖም ቃሉ ተፈጽሟል። ድንግል ለነበረችው ለማርያም የአምላክን ልጅ እንደምትወልድ ቃል ገብቶላታል፤ ይህም ይሖዋ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ያደርጋል። (ዘፍ. 3:15) ይሖዋ የገባቸውን ቃሎች በመፈጸም ረገድ ባስመዘገበው ታሪክ ላይ ማሰላሰላችን አዲስ ዓለም ለማምጣት ኃይል እንዳለው ያለንን እምነት ያጠናክረዋል።—ኢያሱ 23:14፤ ኢሳ. 55:10, 11፤ w23.04 28 አን. 10-12
ማክሰኞ፣ የካቲት 4
ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴን ስማ፤ እርዳታ ለማግኘት የማቀርበውን ልመና አዳምጥ።—መዝ. 143:1
ይሖዋ ዳዊትን በመታደግ ጸሎቱን መልሶለታል። (1 ሳሙ. 19:10, 18-20፤ 2 ሳሙ. 5:17-25) እኛም እንዲህ ያለ እምነት ሊኖረን ይችላል። (መዝ. 145:18) ይሖዋ በጠበቅነው መንገድ ጸሎታችንን ላይመልስልን ይችላል። ጳውሎስ ‘ሥጋውን የሚወጋውን እሾህ’ አምላክ እንዲያስወግድለት ጸልዮ ነበር። ጳውሎስ ይህን ከባድ ችግር አስመልክቶ ሦስት ጊዜ ጸልዮአል። ታዲያ ይሖዋ ጸሎቱን መልሶለታል? አዎ፣ ግን የመለሰለት ጳውሎስ በጠበቀው መንገድ አይደለም። ችግሩን ከማስወገድ ይልቅ እሱን በታማኝነት ማገልገሉን ለመቀጠል የሚያስፈልገውን ኃይል ሰጥቶታል። (2 ቆሮ. 12:7-10) እኛም አንዳንድ ጊዜ የጸሎታችን መልስ ከጠበቅነው የተለየ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ እኛን መርዳት የሚችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ እንደሚያውቅ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲያውም “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” ይችላል። (ኤፌ. 3:20) በመሆኑም ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን ባልጠበቅነው ጊዜ ወይም ባልጠበቅነው መንገድ ሊሆን ይችላል። w23.05 8-9 አን. 4-6
ረቡዕ፣ የካቲት 5
በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን [ሰምተው የሚወጡበት] ሰዓት ይመጣል።—ዮሐ. 5:28, 29
ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ አልፎ አልፎ ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። ለምን? በድንገት ለሞት የሚዳርግ በሽታ ሊይዘን ወይም የምንወደውን ሰው በሞት ልናጣ እንችላለን። (መክ. 9:11፤ ያዕ. 4:13, 14) የትንሣኤ ተስፋችን እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመወጣት ይረዳናል። (1 ተሰ. 4:13) ቅዱሳን መጻሕፍት የሰማዩ አባታችን በሚገባ እንደሚያውቀንና በጣም እንደሚወደን ማረጋገጫ ይሰጡናል። (ሉቃስ 12:7) ይሖዋ ትዝታችንና ባሕርያችን እንዳለ ሆኖ መልሶ ሊፈጥረን የሚችለው ምን ያህል ቢያውቀን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ይሖዋ በጣም ስለሚወደን ለዘላለም እንድንኖር አጋጣሚውን ከፍቶልናል፤ ብንሞት እንኳ ከሞት አስነስቶ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል! በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት መጣል የምንችለው ለምንድን ነው? ተስፋውን የሰጠን አምላክ ቃሉን ለመጠበቅ ፍላጎቱም ሆነ ኃይሉ ወይም ችሎታው እንዳለው እርግጠኞች ስለሆንን ነው። w23.04 8-9 አን. 2-4
ሐሙስ፣ የካቲት 6
[ዮሴፍ እና ማርያም] በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም የመሄድ ልማድ ነበራቸው።—ሉቃስ 2:41
ዮሴፍና ማርያም ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማጠናከር በጋራ ጥረት አድርገዋል። በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን ማምለክ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። (ሉቃስ 2:22-24፤ 4:16) በዛሬው ጊዜ ላሉ ባለትዳሮች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትተዋል! እናንተም እንደ ዮሴፍና እንደ ማርያም ልጆች ካሏችሁ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ወይም ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ መመደብ ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል። ሁለታችሁ ብቻ ሆናችሁ የምታጠኑበት ወይም የምትጸልዩበት ጊዜ መመደብ ደግሞ ይበልጥ ከባድ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አብራችሁ ሆናችሁ ይሖዋን ስታመልኩ ከእሱ ጋርም ሆነ በመካከላችሁ ያለው ወዳጅነት እንደሚጠናከር አትዘንጉ። ስለዚህ ለአምልኳችሁ ቅድሚያ ስጡ። በትዳራችሁ ውስጥ ችግር ካጋጠማችሁ አብራችሁ ሆናችሁ የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ያን ያህል ላትነሳሱ ትችላላችሁ። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ አጭርና አስደሳች ውይይት በማድረግ መጀመር ትችላላችሁ። እንዲህ ማድረጋችሁ ጥምረታችሁን ሊያጠናክር እንዲሁም አብራችሁ ሆናችሁ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ያላችሁን ፍላጎት ሊጨምረው ይችላል። w23.05 22 አን. 7-8
ዓርብ፣ የካቲት 7
አብድዩ ይሖዋን በጣም ይፈራ ነበር።—1 ነገ. 18:3
ጤናማ ፍርሃት አብድዩን የረዳው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ሐቀኛና እምነት የሚጣልበት እንዲሆን ረድቶታል፤ በዚህም የተነሳ ንጉሡ በቤቱ ላይ ሾሞታል። (ከነህምያ 7:2 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም አብድዩ ፈሪሃ አምላክ የነበረው መሆኑ አስደናቂ ድፍረት እንዲኖረው ረድቶታል፤ ይህ ባሕርይ ደግሞ በእጅጉ ያስፈልገው ነበር። አብድዩ ይኖር የነበረው በክፉው ንጉሥ በአክዓብ ዘመን ነው። (1 ነገ. 16:30) ከዚህም ሌላ፣ የባአል አምላኪ የነበረችው የአክዓብ ሚስት ኤልዛቤል ይሖዋን በጣም ከመጥላቷ የተነሳ ከሰሜናዊው መንግሥት ንጹሑን አምልኮ ለማስወገድ የተቻላትን ሁሉ ሞክራለች። እንዲያውም በርካታ የአምላክ ነቢያትን ገድላለች። (1 ነገ. 18:4) ኤልዛቤል የአምላክን ነቢያት አሳድዳ መግደል በጀመረችበት ጊዜ አብድዩ መቶዎቹን ነቢያት ወስዶ ‘ሃምሳ ሃምሳ በማድረግ ዋሻ ውስጥ ደበቃቸው፤ እንዲሁም ምግብና ውኃ ይሰጣቸው ነበር።’ (1 ነገ. 18:13, 14) ደፋሩ አብድዩ ተይዞ ቢሆን ኖሮ ያለጥርጥር ይገደል ነበር። መቼም አብድዩ ሰው እንደመሆኑ መጠን እንዳይገደል ፈርቶ መሆን አለበት። ሆኖም አብድዩ ይሖዋንና እሱን የሚያገለግሉትን ሰዎች ከገዛ ሕይወቱ አስበልጦ ይወዳቸው ነበር። w23.06 16 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ የካቲት 8
የምመራህ እኔ ይሖዋ . . . ነኝ።—ኢሳ. 48:17
ይሖዋ በጥንት ጊዜ እንዳደረገው በዛሬው ጊዜም ሕዝቡን መምራቱን ቀጥሏል። ይህን የሚያደርገው በቃሉ እንዲሁም የጉባኤው ራስ በሆነው በልጁ አማካኝነት ነው። ይሁንና አምላክ ሰብዓዊ ወኪሎችንም መጠቀሙን እንደቀጠለ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? በሚገባ። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ የተፈጸሙ አንዳንድ ክንውኖችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ቻርልስ ቴዝ ራስልና ጓደኞቹ 1914 ከአምላክ መንግሥት መቋቋም ጋር በተያያዘ ወሳኝ ዓመት እንደሚሆን ማስተዋል ጀምረው ነበር። (ዳን. 4:25, 26) እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መሠረት አድርገው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምርምር ሲያደርጉ ይሖዋ እንደመራቸው ምንም ጥያቄ የለውም። በ1914 በዓለም ላይ የተፈጸሙት ክንውኖች የአምላክ መንግሥት መግዛት እንደጀመረ አረጋገጡ። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ፈነዳ፤ ከዚያም ቸነፈር፣ የምድር ነውጥና የምግብ እጥረት ተከሰተ። (ሉቃስ 21:10, 11) ይሖዋ ሕዝቡን ለመርዳት ቅን ልብ ያላቸውን እነዚያን ክርስቲያን ወንዶች እንደተጠቀመ በግልጽ ማየት ይቻላል። w24.02 22 አን. 11
እሁድ፣ የካቲት 9
የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል።—መዝ. 34:19
የይሖዋ ሕዝቦች ስለሆንን፣ እሱ እንደሚወደንና ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት እንድንመራ እንደሚፈልግ እርግጠኞች ነን። (ሮም 8:35-39) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ እንደምንጠቀምም እናውቃለን። (ኢሳ. 48:17, 18) ይሁንና ያልጠበቅናቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንስ? ለምሳሌ አንድ የቤተሰባችን አባል ቅር ሊያሰኘን ይችላል። በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የምናከናውነውን ነገር የሚገድብ ከባድ የጤና እክል ሊያጋጥመን ይችላል። በምንኖርበት አካባቢ አውዳሚ የተፈጥሮ አደጋ ሊደርስ ይችላል። ወይም ደግሞ በእምነታችን ምክንያት ስደት ይደርስብን ይሆናል። እንዲህ ያሉ መከራዎች ሲያጋጥሙን እንደሚከተለው ብለን እንጠይቅ ይሆናል፦ ‘ይህ ነገር እየደረሰብኝ ያለው ለምንድን ነው? ያጠፋሁት ነገር አለ? ይሖዋ እኔን መባረኩን አቁሟል ማለት ነው?’ አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ! በርካታ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እንዲህ ያለ ስሜት ተሰምቷቸዋል።—መዝ. 22:1, 2፤ ዕን. 1:2, 3፤ w23.04 14 አን. 1-2
ሰኞ፣ የካቲት 10
ሥርዓትህን በሕይወቴ ዘመን ሁሉ . . . ለመጠበቅ ቆርጫለሁ።—መዝ. 119:112
መጥፎ ነገር ለማድረግ ስንፈተን ሐሳቡን ወዲያውኑ ከአእምሯችን ለማውጣት እንጥራለን፤ ደግሞም ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ከሚያበላሽ ማንኛውም ድርጊት ወዲያውኑ እንርቃለን። ይሖዋ ‘ከልብ እንድንታዘዘው’ ይጠብቅብናል። (ሮም 6:17) መመሪያዎቹ ምንጊዜም ይጠቅሙናል፤ ሕግጋቱም ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም። (ኢሳ. 48:17, 18፤ 1 ቆሮ. 6:9, 10) ዲያብሎስ አካላዊና ስሜታዊ ጥቃት በመሰንዘር አቋማችንን ለማዳከም ይጥራል። ዓላማው እኛን ‘መዋጥ’ ይኸውም ከይሖዋ ጋር ያለንን ግንኙነት ማበላሸት ነው። (1 ጴጥ. 5:8) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ክርስቲያኖች ለአቋማቸው ቆራጥ በመሆናቸው ዛቻ ደርሶባቸዋል፣ ተደብድበዋል እንዲሁም ተገድለዋል። (ሥራ 5:27, 28, 40፤ 7:54-60) ሰይጣን በዛሬው ጊዜም ስደትን መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። በሩሲያና በሌሎች አገራት ያሉት ወንድሞቻችን የሚደርስባቸው ግፍ ይህንን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በተጨማሪም ተቃዋሚዎች በግለሰብ ደረጃ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው። ሰይጣን ፊት ለፊት ከሚሰነዝርብን ጥቃት በተጨማሪ “መሠሪ ዘዴዎች” ይጠቀማል።—ኤፌ. 6:11፤ w23.07 15-16 አን. 6-9
ማክሰኞ፣ የካቲት 11
በሁሉም ነገር . . . በፍቅር እንደግ።—ኤፌ. 4:15
የአምላክን ቃል እያጠናህ ስትሄድ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርም ያድጋል። ይህ ፍቅር ደግሞ የተማርከውን በተግባር እንድታውል ያነሳሳሃል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርተህ የተሻሉ ውሳኔዎችን ማድረግ ትችላለህ። አምላክን ማስደሰት ስለምትፈልግ በአመለካከትህና በምግባርህም ላይ ለውጥ ታደርጋለህ። አንድ ልጅ የሚወደውን ወላጁን እንደሚኮርጅ ሁሉ አንተም በሰማይ ያለውን አባትህን ለመምሰል ጥረት ታደርጋለህ። (ኤፌ. 5:1, 2) ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ክርስቲያን ስሆን ከነበረበት ጨምሯል? ከተጠመቅሁበት ጊዜ ወዲህ በአስተሳሰቤና በድርጊቴ ይሖዋን ይበልጥ እየመሰልኩት ነው? ለምሳሌ ለወንድሞቼና ለእህቶቼ ፍቅር በማሳየት ረገድ እንዴት ነኝ?’ ‘መጀመሪያ ላይ የነበረህ ፍቅር’ በተወሰነ ደረጃ ተቀዛቅዞ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሟቸዋል። ሆኖም ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠባቸውም፤ በእኛም ተስፋ አይቆርጥብንም። (ራእይ 2:4, 7) እውነትን ስንሰማ የነበረንን ፍቅር መልሰን ማቀጣጠል እንደምንችል ያውቃል። w23.07 8 አን. 2-3
ረቡዕ፣ የካቲት 12
ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ።—መዝ. 86:5
ሐዋርያው ጴጥሮስ በተከታታይ ስህተቶችን ሠርቶ ነበር። በመጀመሪያ፣ ጴጥሮስ ከልክ በላይ በራሱ ተማምኗል፤ ሌሎቹ ሐዋርያት ኢየሱስን ቢክዱት እንኳ እሱ ታማኝ እንደሚሆን በመግለጽ ጉራውን ነዛ። (ማር. 14:27-29) ከዚያም ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ነቅቶ መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል። (ማር. 14:32, 37-41) በኋላም ኢየሱስን ጠላቶቹ ሲይዙት ጴጥሮስ ጥሎት ሸሸ። (ማር. 14:50) በመጨረሻም ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ኢየሱስን ካደው፤ ይባስ ብሎም ‘አላውቀውም’ ብሎ ማለ። (ማር. 14:66-71) ጴጥሮስ የኃጢአቱን ክብደት ሲገነዘብ ምን ተሰማው? ምርር ብሎ አለቀሰ። (ማር. 14:72) ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን በኃጢአቱ የተነሳ ከመውቀስ ይልቅ ተጨማሪ ኃላፊነት እንደሚቀበል ነገረው። (ዮሐ. 21:15-17) ጴጥሮስ ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ገብቶታል፤ ሆኖም በራሱ ተስፋ አልቆረጠም። ለምን? ጌታው ኢየሱስ ተስፋ እንዳልቆረጠበት እርግጠኛ ስለነበረ ነው። እኛ ከዚህ ምን እንማራለን? ይሖዋ እሱ እንደሚወደንና ይቅር እንደሚለን እንድንተማመን ይፈልጋል።—ሮም 8:38, 39፤ w24.03 18-19 አን. 13-15
ሐሙስ፣ የካቲት 13
እሷ [የገደለቻቸው] እጅግ ብዙ ናቸው።—ምሳሌ 7:26
የፆታ ብልግና ለኀፍረት፣ ለከንቱነት ስሜት፣ ላልተፈለገ እርግዝና እንዲሁም ለቤተሰብ መፍረስ ሊዳርግ ይችላል። በእርግጥም፣ ማስተዋል ከጎደላት ሴት ‘ቤት’ መራቅ የጥበብ እርምጃ ነው። የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ ብዙ ሰዎች ለመንፈሳዊ ሞት ከመዳረጋቸውም በተጨማሪ ቃል በቃል ያለዕድሜያቸው እንዲቀጩ በሚያደርግ በሽታ ሊያዙ ይችላሉ። (ምሳሌ 7:23) ምሳሌ ምዕራፍ 9 ቁጥር 18 ላይ ‘እንግዶቿ በመቃብር ጥልቅ ውስጥ እንደሚገኙ’ ይናገራል። ታዲያ ብዙዎች ለዚህ ሁሉ መከራ የሚዳርገውን የዚህችን ሴት አታላይ ግብዣ የሚቀበሉት ለምንድን ነው? (ምሳሌ 9:13-18) ወደ ፆታ ብልግና የሚመራው አንዱ ነገር ፖርኖግራፊ ነው። አንዳንዶች ፖርኖግራፊ መመልከት ምንም ጉዳት እንደሌለው ይሰማቸዋል። ሆኖም ፖርኖግራፊ ጎጂ፣ የሚያዋርድና ሱስ የሚያስይዝ ነገር ነው። የብልግና ምስሎች በቀላሉ ከአእምሮ አይፋቁም። በተጨማሪም ፖርኖግራፊ መጥፎ ምኞቶችን ከመግደል ይልቅ ያቀጣጥላቸዋል። (ቆላ. 3:5፤ ያዕ. 1:14, 15) ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ብዙ ሰዎች የፆታ ብልግና መፈጸማቸው አይቀርም። w23.06 23 አን. 10-11
ዓርብ፣ የካቲት 14
እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።—ዳን. 2:44
አንዳንድ ብሔራት አልፎ አልፎ የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃያል መንግሥት ቢገዳደሩትም እንኳ እሱን ተክተው የዓለም ኃያል መንግሥት አይሆኑም። እንዲህ የምንለው፣ የአምላክን መንግሥት የሚያመለክተው ድንጋይ የምስሉን እግሮች ማለትም የአንግሎ አሜሪካን ጥምር መንግሥት እንደሚያደቅ ትንቢቱ ስለሚገልጽ ነው። (ዳን. 2:34, 35, 44, 45) ከብረትና ከሸክላ ስለተሠሩት እግሮች የሚናገረው የዳንኤል ትንቢት እንደተፈጸመ ታምናለህ? ከሆነ እምነትህ በአኗኗርህ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። በቅርቡ በሚጠፋ ዓለም ውስጥ ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ጥረት አታደርግም። (ሉቃስ 12:16-21፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) ይህን ትንቢት መረዳትህ የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ያለውን አስፈላጊነት ለመገንዘብም ይረዳሃል። (ማቴ. 6:33፤ 28:18-20) ይህን ትንቢት ካጠናህ በኋላ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የማደርጋቸው ውሳኔዎች የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ እንደሚያጠፋ እርግጠኛ እንደሆንኩ ያሳያሉ?’ w23.08 11 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ የካቲት 15
እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።—ሮም 14:12
ልክህን የምታውቅ ሁን፤ ጤናህና ያለህበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ ማከናወን የምትችለውን ነገር ሊገድብብህ እንደሚችል አምነህ ተቀበል። ዕድሜህ ወይም የጤንነትህ ሁኔታ የሚገድብህ ከሆነ ልክ እንደ ቤርዜሊ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ‘አልችልም’ ለማለት ፈቃደኛ ሁን። (2 ሳሙ. 19:35, 36) እንደ ሙሴ የሌሎችን እርዳታ ተቀበል፤ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ ሥራህን ለሌሎች አካፍል። (ዘፀ. 18:21, 22) በዚህ መልኩ ልክህን እንደምታውቅ ማሳየትህ ምክንያታዊ ያልሆነ ግብ በማውጣት ራስህን እንዳታደክም ይረዳሃል። በተጨማሪም ሌሎች ለሚያደርጉት መጥፎ ውሳኔ ኃላፊነት መውሰድ የለብንም። ለሌሎች ውሳኔ ማድረግ አንችልም፤ እንዲሁም የሚያደርጉት መጥፎ ውሳኔ ከሚያስከትልባቸው መዘዝ ሁልጊዜ ልንከልላቸው አንችልም። ለምሳሌ አንድ ልጅ ይሖዋን ማገልገሉን ለማቆም ሊወስን ይችላል። ይህ ውሳኔው ወላጆቹን በጣም እንደሚጎዳቸው ጥያቄ የለውም። ሆኖም ልጃቸው ባደረገው መጥፎ ውሳኔ ራሳቸውን የሚወቅሱ ወላጆች ላያቸው ላይ ከባድ ሸክም እየጫኑ ነው። ይሖዋ ይህን ሸክም እንዲሸከሙ አይጠብቅባቸውም። w23.08 29 አን. 11-12
እሁድ፣ የካቲት 16
ሳምሶን . . . ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ።—መሳ. 16:4
ሳምሶን እንደ እኛው ፍጽምና የጎደለው ሰው ነበር፤ ስለዚህ የተሳሳተ ውሳኔ ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። በተለይ በአንድ ወቅት ያደረገው ውሳኔ አስከፊ መዘዝ አስከትሎበታል። ሳምሶን ለተወሰነ ጊዜ መስፍን ሆኖ ካገለገለ በኋላ “በሶረቅ ሸለቆ የምትገኝ ደሊላ የምትባል አንዲት ሴት ወደደ።” ቀደም ሲል ሳምሶን አንዲት ፍልስጤማዊት አጭቶ ነበር። ሆኖም ይህ ጥምረት ‘ከይሖዋ ነበር’፤ ይሖዋ “ከፍልስጤማውያን ጋር ግጭት የሚፈጠርበትን አጋጣሚ እየፈለገ” ነበር። በኋላ ላይ ሳምሶን፣ ጋዛ በተባለችው የፍልስጤም ከተማ ውስጥ በአንዲት ዝሙት አዳሪ ቤት አድሯል። በዚያ ወቅት ሳምሶን የከተማዋን በሮች ነቅሎ እንዲወስድ አምላክ ኃይል ሰጥቶታል፤ ይህም ከተማዋን አዳክሟታል። (መሳ. 14:1-4፤ 16:1-3) የደሊላ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም እስራኤላዊት ሳትሆን አትቀርም። ደሊላ ከፍልስጤማውያን ብዙ ገንዘብ በመቀበል ሳምሶንን ለእነሱ አሳልፋ ለመስጠት ተስማማች። w23.09 5 አን. 12-13
ሰኞ፣ የካቲት 17
ጥልቅ ማስተዋል ሰውን ቶሎ እንዳይቆጣ ያደርገዋል።—ምሳሌ 19:11
ጥልቅ ማስተዋል ገርነት እንድናሳይ ይረዳናል። ጥልቅ ማስተዋል ያለው ሰው ሌሎች እምነቱን በተመለከተ በጥያቄ ሲያፋጥጡት ራሱን ይቆጣጠራል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ ከጥያቄያቸው በስተ ጀርባ ሌላ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ምላሽ ከመስጠታችን በፊት ግለሰቡ ያንን ጥያቄ እንዲጠይቅ ያነሳሳውን ምክንያት ላናውቅ እንደምንችል መገንዘብ ይኖርብናል። (ምሳሌ 16:23) ጌድዮን ለኤፍሬም ሰዎች የሰጠውን ምላሽ እንደ ምሳሌ እንመልከት። የኤፍሬም ሰዎች ጌድዮን ከአምላክ ጠላቶች ጋር ለመዋጋት ሲወጣ ያልጠራቸው ለምን እንደሆነ በቁጣ ጠየቁት። ይሁንና ይህን ያህል የተበሳጩት ለምንድን ነው? ክብራቸው እንደተነካ ስለተሰማቸው ይሆን? ያም ሆነ ይህ፣ ጌድዮን ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት በማድረግ በገርነት ምላሽ ሰጥቷቸዋል። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ቁጣቸው በረደ።”—መሳ. 8:1-3፤ w23.09 16 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ የካቲት 18
በየዕለቱ በእኔ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር።—ምሳሌ 8:30
ይሖዋና ኢየሱስ ከየትኛውም አባትና ልጅ ይበልጥ ይቀራረባሉ። ይሖዋ ልጁ ሲንገላታ፣ ሲጠላ እና ፈተና ሲደርስበት ሲያይ በጣም አዝኖ መሆን አለበት። ልጃቸውን በሞት ያጡ ወላጆች እንዲህ ያለው ሁኔታ መሪር ሐዘን እንደሚያስከትል ያውቃሉ። በትንሣኤ ላይ ጠንካራ እምነት አለን። ሆኖም ይህ እምነታችን የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ የሚደርስብንን ሐዘን አያስቀርልንም። ይህ ምሳሌ፣ ይሖዋ ውድ ልጁ በ33 ዓ.ም. ተሠቃይቶ ሲገደል የተሰማውን ስሜት ለመረዳት ያስችለናል። (ማቴ. 3:17) የመታሰቢያው በዓል እስኪደርስ ድረስ በቤዛው ላይ ያተኮረ የግል ጥናት ወይም የቤተሰብ አምልኮ ፕሮጀክት ለማካሄድ ለምን አትሞክርም? በመታሰቢያው በዓል ዕለት ደግሞ ለዚያ ቀን የተዘጋጀውን ልዩ የማለዳ አምልኮ ፕሮግራም መመልከትህን አትርሳ። ለመታሰቢያው በዓል ልባችንን ካዘጋጀን ሌሎችም ከዚህ በዓል እንዲጠቀሙ መርዳት እንችላለን።—ዕዝራ 7:10፤ w24.01 11 አን. 10-12
ረቡዕ፣ የካቲት 19
ያጠነክራችኋል።—1 ጴጥ. 5:10
ከይሖዋ ኃይል ማግኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ወደ እሱ በጸሎት መቅረብ ነው። ይሖዋም ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ በመስጠት ጸሎታችንን ይመልስልናል። (2 ቆሮ. 4:7) ቃሉን ማንበባችንና ማሰላሰላችንም ሊያጠነክረን ይችላል። (መዝ. 86:11) አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያስተላለፈልን መልእክት “ኃይለኛ ነው።” (ዕብ. 4:12) ወደ ይሖዋ ስትጸልይና ቃሉን ስታነብ ለመጽናት፣ ደስታህን ለመጠበቅ ወይም የተሰጠህን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልግህን ጥንካሬ ታገኛለህ። ይሖዋ ነቢዩ ዮናስን ያጠነከረው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ዮናስ ይሖዋ ከሰጠው ከባድ ኃላፊነት ለመሸሽ ሞክሯል። በዚህም ምክንያት እሱም ሆነ አብረውት በመርከብ ላይ የተሳፈሩት ሰዎች በኃይለኛ ማዕበል የተነሳ ሊሞቱ ተቃርበው ነበር። ከዚያም መርከበኞቹ ወደ ባሕሩ ሲወረውሩት አንድ ዓሣ ነባሪ ዋጠው። ዮናስ ብቻውን በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሳለ ጥንካሬ ለማግኘት ምን አደረገ? ጸለየ።—ዮናስ 2:1, 2, 7፤ w23.10 13 አን. 4-6
ሐሙስ፣ የካቲት 20
የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል።—1 ጴጥ. 4:7
ሐዋርያው ጴጥሮስ ደብዳቤዎቹን የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች ቢሆንም ይሖዋ እነዚህ ደብዳቤዎች የቃሉ ክፍል እንዲሆኑ አድርጓል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜም ከእነዚህ ደብዳቤዎች ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ሮም 15:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ ምንም ዓይነት እምነት በሌላቸው ሰዎች ተከበናል። ለበርካታ ዓመታት መጨረሻውን በጉጉት ስንጠባበቅ በመቆየታችን የተነሳ ተቃዋሚዎች ያሾፉብን ይሆናል። አንዳንድ ተቺዎች ደግሞ መጨረሻው ጨርሶ እንደማይመጣ ይናገራሉ። (2 ጴጥ. 3:3, 4) አገልግሎት ላይ ያገኘነው ሰው፣ የሥራ ባልደረባችን ወይም የቤተሰባችን አባል እንዲህ ያለ ነገር ሲናገር ከሰማን እምነታችን ሊናጋ ይችላል። ጴጥሮስ በዚህ ረገድ ምን ሊረዳን እንደሚችል ተናግሯል። አንዳንዶች ይሖዋ ይህን ሥርዓት ለማጥፋት እንደዘገየ ይሰማቸው ይሆናል። ጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ይረዱናል። ምክንያቱም ጴጥሮስ፣ ይሖዋ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከሰዎች አመለካከት በእጅጉ የተለየ እንደሆነ ገልጿል። (2 ጴጥ. 3:8, 9) በይሖዋ ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው። ይሖዋ ታጋሽ ነው፤ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። እሱ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ግን ይህ ሥርዓት ይጠፋል። w23.09 26-27 አን. 2-5
ዓርብ፣ የካቲት 21
ቀስ በቀስ እንዳንወሰድ ለሰማናቸው ነገሮች ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ . . . ነው።—ዕብ. 2:1
ሐዋርያው ጳውሎስ በይሁዳ ይኖሩ ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ የጻፈላቸው ለምንድን ነው? በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ ሳይሆን አይቀርም። አንደኛ፣ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ስለፈለገ ነው። ብዙዎቹ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት የአይሁድ እምነት ተከታዮች ነበሩ። ክርስቲያን በመሆናቸው የተነሳ የቀድሞ የሃይማኖት መሪዎቻቸው አፊዘውባቸው ሊሆን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ክርስቲያኖች አምልኮ የሚያቀርቡበት የሚያስደምም ቤተ መቅደስ፣ ለአምላክ መሥዋዕት የሚያቀርቡበት መሠዊያ እንዲሁም የሚያገለግሏቸው ካህናት አልነበሯቸውም። ይህ ሁኔታ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ተስፋ ሊያስቆርጣቸውና እምነታቸውን ሊያዳክመው ይችላል። (ዕብ. 3:12, 14) ምናልባትም አንዳንዶቹ ወደ አይሁድ እምነት ለመመለስ ተፈትነው ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ፣ ጳውሎስ እነዚህ ዕብራውያን ክርስቲያኖች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን “ጠንካራ ምግብ” ማለትም አዳዲስ ወይም ጥልቅ የሆኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለመረዳት ጥረት እያደረጉ እንዳልሆነ ተናግሯል። (ዕብ. 5:11-14) አንዳንዶቹ ያኔም የሙሴን ሕግ መከተላቸውን አላቆሙ ይሆናል። w23.10 24-25 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ የካቲት 22
ወጣት ሴቶችን . . . እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው።—1 ጢሞ. 5:2
አንዳንድ ሴቶች፣ ሳያገቡ ለመኖር ሊመርጡ ይችላሉ። (ማቴ. 19:10-12) ይሖዋና ኢየሱስ ያላገቡ ክርስቲያኖችን ዝቅ አድርገው እንደማይመለከቷቸው እርግጠኛ ሁኑ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ያላገቡ እህቶች በጉባኤያቸው ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። እነዚህ ክርስቲያን ሴቶች ለሌሎች ያላቸው ፍቅርና አሳቢነት ለብዙዎች መንፈሳዊ እህቶችና እናቶች እንዲሆኑ ያነሳሳቸዋል። (ማር. 10:29, 30) አንዳንዶች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነዋል። ክርስቲያን ሴቶች በዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። (መዝ. 68:11) ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ከአሁኑ ዕቅድ ማውጣት ትችሉ ይሆን? አቅኚ፣ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ ወይም ቤቴላዊ ሆናችሁ ልታገለግሉ ትችሉ ይሆናል። ግባችሁን በተመለከተ ጸልዩ። እንዲህ ያለ ግብ ላይ መድረስ የቻሉ ክርስቲያኖችን አነጋግሩ፤ እንዲሁም ብቃቱን ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ለማወቅ ሞክሩ። ከዚያም ምክንያታዊ የሆነ ዕቅድ አውጡ። ግባችሁ ላይ መድረሳችሁ በይሖዋ አገልግሎት በርካታ ግሩም አጋጣሚዎችን ይከፍትላችኋል። w23.12 22 አን. 16-17
እሁድ፣ የካቲት 23
አስቀድሞም ምሥራቹ . . . መሰበክ አለበት።—ማር. 13:10
ወደ ታላቁ መከራ ይበልጥ እየተቃረብን ስንሄድ በስብከቱ ሥራ እንድንካፈል የተሰጠንን ትእዛዝ መፈጸማችን ይበልጥ አንገብጋቢ እንደሆነ መገንዘባችን አስፈላጊ ነው። ይሁንና የገንዘብ ችግር ካጋጠመን ወይም በስብከቱ ሥራችን ላይ ተቃውሞ ከተነሳ በአገልግሎታችን ላይ ትኩረት ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ታዲያ የመንግሥቱን ሥራ እንድናስቀድም የሚረዳን ምንድን ነው? “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” ከጎናችን እንደሆነ ምንጊዜም እርግጠኞች መሆናችን አስፈላጊ ነው። ከራሳችን ፍላጎት ይልቅ የመንግሥቱን ሥራ ማስቀደማችንን ከቀጠልን እሱ ይረዳናል። በመሆኑም የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። (ሐጌ 2:4) ይሖዋ ሕይወት አድን በሆነው ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ላይ እንድናተኩር ይፈልጋል። ሐጌ የይሖዋ ሕዝቦች የቤተ መቅደሱን መሠረት በድጋሚ የመጣል ያህል እንደ አዲስ በንጹሕ አምልኮ መካፈል እንዲጀምሩ አበረታቷቸዋል። እንዲህ ካደረጉ ይሖዋ ‘እንደሚባርካቸው’ ቃል ገብቶላቸዋል። (ሐጌ 2:18, 19) እኛም ይሖዋ ለሰጠን ሥራ ቅድሚያ ከሰጠን እሱ ጥረታችንን እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w23.11 16 አን. 8፤ 17 አን. 11
ሰኞ፣ የካቲት 24
ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል።—ሮም 3:23
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ላሉ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ተናግሯል። ታዲያ አንድ ሰው ጻድቅ ወይም ነቀፋ የሌለበት ተደርጎ መቆጠርና የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ይህን ጥያቄ ለመመለስ የአብርሃምን ምሳሌ ጠቅሷል። ይሖዋ፣ አብርሃም ጻድቅ እንደሆነ የተናገረው በከነአን ምድር ይኖር በነበረበት ወቅት ነው። ይሖዋ አብርሃምን ጻድቅ አድርጎ የቆጠረው ለምንድን ነው? አብርሃም የሙሴን ሕግ ሙሉ በሙሉ ስለጠበቀ ነው? እንዳልሆነ የታወቀ ነው። (ሮም 4:13) ሕጉ ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው አምላክ አብርሃምን ጻድቅ ብሎ ከጠራው ከ400 ዓመት በኋላ ነው። ታዲያ አምላክ አብርሃምን ጻድቅ አድርጎ የቆጠረው ምንን መሠረት አድርጎ ነው? የጸጋ አምላክ የሆነው ይሖዋ፣ አብርሃም እምነት በማሳየቱ ጻድቅ አድርጎ ቆጥሮታል።—ሮም 4:2-4፤ w23.12 3 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ የካቲት 25
በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ።—1 ዜና 17:2
ነቢዩ ናታን ከላይ ያለውን ሐሳብ በተናገረበት በዚያው ሌሊት ይሖዋ ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ዳዊት እንዳልሆነ ለናታን ነገረው። (1 ዜና 17:3, 4, 11, 12) ዳዊት ይህን ሲሰማ ምን አደረገ? ልጁ ሰለሞን ፕሮጀክቱን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን ገንዘብና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ላይ ትኩረት አደረገ። (1 ዜና 29:1-5) ይሖዋ ቤተ መቅደሱን የሚገነባለት እሱ እንዳልሆነ ለዳዊት ከነገረው በኋላ ወዲያውኑ ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ከዘሮቹ መካከል አንዱ ለዘላለም እንደሚነግሥ ቃል ገባለት። (2 ሳሙ. 7:16) በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት ዳዊት፣ ንጉሡ ኢየሱስ ከእሱ የትውልድ መስመር እንደመጣ ሲያውቅ በጣም እንደሚደሰት ጥያቄ የለውም! ከዚህ ዘገባ እንደምንማረው፣ በይሖዋ አገልግሎት ያሰብነውን ሁሉ ማከናወን ባንችልም እንኳ አምላካችን ጨርሶ ያልጠበቅናቸውን በረከቶች አዘጋጅቶልን ሊሆን ይችላል። w23.04 15-16 አን. 8-10
ረቡዕ፣ የካቲት 26
ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልም።—መዝ. 94:14
በምትፈራበት ጊዜ በተለይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማንበብህ ያጽናናህ ይሆናል። ለምሳሌ በኢዮብ፣ በመዝሙርና በምሳሌ መጽሐፍ እንዲሁም ኢየሱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 6 ላይ በተናገራቸው ቃላት ውስጥ የሚያበረታታ ሐሳብ ማግኘት ትችላለህ። ወደ ይሖዋ የምትጸልይና ቃሉን የምታነብ ከሆነ እሱ የሚሰጥህን ማጽናኛ ማጣጣም ትችላለህ። በሕይወታችን ውስጥ ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ይሖዋ እንደሚደርስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መቼም ቢሆን ብቻችንን አይተወንም። (መዝ. 23:4) ይሖዋ እንደሚጠብቀን፣ አጽንቶ እንደሚያቆመን፣ እንደሚደግፈን እንዲሁም እንደሚያጽናናን ቃል ገብቶልናል። ኢሳይያስ 26:3 ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ሙሉ በሙሉ በአንተ የሚመኩትን ትጠብቃለህ፤ በአንተ ስለሚታመኑ ዘላቂ ሰላም ትሰጣቸዋለህ።” እንግዲያው በይሖዋ ታመን፤ እንዲሁም አንተን ለመርዳት ያደረጋቸውን ዝግጅቶች በሙሉ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ በመከራ ወቅትም ብርታት ማግኘት ትችላለህ። w24.01 25 አን. 16-17
ሐሙስ፣ የካቲት 27
አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል።—ኢሳ. 54:17
በመንፈስ መሪነት የተነገሩት ከላይ የተጠቀሱት ቃላት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ነው። የሚከተለው የሚያጽናና ሐሳብም የሚናገረው ስለ ዘመናችን ነው፦ “ልጆችሽም ሁሉ ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ፤ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። በጽድቅ ጽኑ ሆነሽ ትመሠረቺያለሽ። . . . ምንም ነገር አትፈሪም፤ የሚያሸብርሽም ነገር አይኖርም፤ ወደ አንቺ አይቀርብምና።” (ኢሳ. 54:13, 14) “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣንም እንኳ የይሖዋ ሕዝቦች እያካሄዱ ያሉትን የማስተማር ሥራ ሊያስቆመው አይችልም። (2 ቆሮ. 4:4) ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቁሟል፤ ደግሞም ከዚህ በኋላ ፈጽሞ አይበከልም። ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። እኛን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል። w24.02 4 አን. 10
ዓርብ፣ የካቲት 28
ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም።—ማቴ. 10:37
ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ራሳችንን ስንወስን ለይሖዋ የገባነውን ስእለት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ይህ ደግሞ ከቤተሰብ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎችና የምንወስዳቸውን እርምጃዎች ይነካል። ከቤተሰቦቻችን ጋር በተያያዘ ያለብንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነት በትጋት እንወጣለን፤ ሆኖም የቤተሰቦቻችንን ፍላጎት ይሖዋ ከሚጠብቅብን ነገር ፈጽሞ አናስቀድምም። (ማቴ. 10:35, 36፤ 1 ጢሞ. 5:8) በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ይሖዋን ለማስደሰት ስንል ቤተሰቦቻችንን የሚያስከፋ ውሳኔ ልናደርግ እንችላለን። የቤተሰብን ዝግጅት የመሠረተው ይሖዋ ነው፤ ደስተኛ ቤተሰብ እንዲኖረንም ይፈልጋል። (ኤፌ. 3:14, 15) እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግን የይሖዋን መመሪያ መከተል ይኖርብናል። ይሖዋ ቤተሰቦቻችሁን እየተንከባከባችሁ እንዲሁም ለእነሱ ፍቅርና አክብሮት እያሳያችሁ እሱን ለማገልገል የምትከፍሉትን መሥዋዕት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ፈጽሞ አትጠራጠሩ።—ሮም 12:10፤ w24.02 18 አን. 11, 13