ደስተኛው ሕዝብ
በዛሬው ዘመን ደስተኛ ሕዝብ ተብሎ ሊጠራ የሚችል አንድ ብሔር ሊኖር ይችላልን? አመጽን፣ ወንጀልን፣ ድህነትን፣ የአካባቢ መበከልን፣ የሚያሽመደምዱ በሽታዎችን፣ ፖለቲካዊ ምግባረ ብልሹነትን፣ ሃይማኖታዊ ጥላቻን ፈጽሞ አጥፍቻለሁ ብሎ ሊያበስር የሚችል ብሔር ሊኖር ይችላልን? እነዚህንስ ግቦች የመጨበጥ እርግጠኛ ተስፋ ያለው ብሔር ይገኛልን? በፍፁም አይገኝም።
በአሁኑ ጊዜ ስለሚታየው ዓለም አቀፍ ሁኔታስ ምን ሊባል ይቻላል? የሶቪየት ኅብረት ፕሬዘዳንት የሆኑት ሚኻኤል ጎርባቼቭ ባለፈው ሐምሌ 16 ቀን “ከአንድ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምዕራፍ ተሻግረን ጠንካራና ዘላቂ ሰላም ወደሚገኝበት ዘመን በመግባት ላይ ያለን ይመስለኛል” ብለው ነበር። ይሁን እንጂ በዚያው ቀን ታትሞ የወጣው የታይምስ መጽሔት አሁንም ቢሆን ዩናይትድ ስቴትስ እያንዳንዳቸው ከተማይቱን ለማውደም የሚችሉና በሞስኮ ላይ የተነጣጠሩ የኑክሌር አረሮች እንዳሉአት ገልጾአል። ሶቭየቶችም አፀፋውን ለመመለስ በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙ አያጠራጥርም። ብዙዎቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች የኑክሌር ጦር መሣሪያ የማምረት ችሎታ ባገኙበት በአሁኑ ጊዜ በመጀመሪያ የሚተኩሰው ማን ይሆን ብሎ ማሰብ ምንም ዓይነት ደስታ አይሰጥም።
በእውነት ደስተኛ የሆነ ሕዝብ
በታሪክ ውስጥ የዛሬ 3,500 ዓመታት ገደማ በእውነት ደስተኛ የሆነ ሕዝብ ነበር። ይህም ሕዝብ የጥንቱ የእስራኤል ብሔር ነበር። አምላክ ይህን ሕዝብ ከግብጽ ጭቆና ነፃ ባወጣ ጊዜ ሕዝቡ ከሙሴ ጋር ሆኖ የደስታ ዝማሬ ዘምሮ ነበር። አዳኛቸውንና አምላካቸውን ታዝዘው እስከኖሩ ድረስ ይህ ደስታ አይወሰድባቸውም ነበር።—ዘፀአት 15:1-21፤ ዘዳግም 28:1, 2, 15, 47
በሰለሞንም ዘመነ መንግሥት “ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ በልተውም ጠጥተውም ደስ ብሎአቸው ነበር።” የደስታና የሐሴት ዘመን ነበር። በታሪክ ዘመናት በሙሉ ከታነፁት ሕንፃዎች በሙሉ በጣም ባለግርማ የሆነው የይሖዋ አምልኮ ቤተመቅደስ በኢየሩሳሌም የተሠራውም በዚሁ ዘመን ነበር።—1 ነገሥት 4:20፤ 6:11-14
ዘመናዊው ደስተኛ ሕዝብ
የጥንትዋ እሥራኤል በዘመናችን ለሚገኝ አንድ ሕዝብ ጥላ ሆናለች። ይህ ሕዝብ የትኛው ነው? በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው የእሥራኤል ፖለቲካዊ ብሔር ነውን? ይህ በከፍተኛ ትግል የተወጠረው ብሔር ደስተኛ አለመሆኑን ከዓለም ዜናዎች መረዳት ይቻላል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተባለውስ ለአባል አገሮች እውነተኛ ደስታ አስገኝቶላቸዋልን? በዛሬዎቹ የፖለቲካ ብሔራት መካከል እውነተኛ ደስታ የለም። ስግብግብነት፣ ጉቦኝነትና ሸፍጥ በማንኛውም አገር ተስፋፍቶ ይገኛል። በብዙ አገሮችም ተራ ሕዝቦች አለአንዳች ደስታ ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ይማስናሉ።—ምሳሌ 28:15፤ 29:2
ይሁን እንጂ በዛሬው ዘመን በጣም ደስተኛ የሆነ ሕዝብ አለ። የዚህ ሕዝብ ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሕዝቦቹ ሲናገር “ከዚህ ዓለም አይደላችሁም” ስላለ ይህ ብሔር ፖለቲካዊ አይደለም። (ዮሐንስ 15:19) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ የሆነው በስም ብቻ ሲሆን ይህ ደስተኛ ሕዝብ ግን ‘ከብዙ ሕዝቦች፣ ነገዶችና ቋንቋዎች’ የተውጣጡ ሰላም ወዳድ ሰዎችን አሰባስቦ አንድ ሕዝብ አድርጎአል። (ራእይ 7:4, 9) የዚህ ሕዝብ ቁጥር በአሁኑ ጊዜ አራት ሚልዮን ስለደረሰ 159 አባላት ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት ከሆኑት 60 አገሮች ሕዝብ የሚበልጥ ሕዝብ አለው። የእነዚህ አራት ሚልዮን የሚያክሉት ሕዝቦች የትውልድ ቋንቋ ከ200 የሚበልጥ ቢሆንም ሁሉም አንዱን “ንፁሕ ልሣን” በመናገር አንድ ሆነዋል።—ሶፎንያስ 3:9
ይህን የሚያክል የተለያየ ባሕል ያላቸው ሰዎች በአንድ የጋራ ቋንቋ መናገራቸው እንግዳ ነገር አይደለምን? ይህ የሚያስተባብር ቋንቋ የመጪውን የጽድቅ መንግሥት መልእክት ስለሚጨምር እንግዳ ነገር አይሆንም። ይህ ደስተኛ ሕዝብ ‘ከምድር ዳር’ በሙሉ የተውጣጣ ሲሆን በዓለም በሙሉ ‘የይሖዋ ምሥክሮች’ በሚል ስያሜ ይታወቃል። (ኢሳይያስ 43:5-7, 10፤ ዘካርያስ 8:23) እነዚህን ሕዝቦች በማንኛውም የምድር ክፍል ልታገኛቸው ትችላለህ።
የአምላክ ነቢይ በኢሳይያስ 2:2-4 ላይ “ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን” እያሉ ከብሔራት በሙሉ ስለሚጎርፉ ብዙ ሕዝቦች ገልጾአል። እነርሱም ሰዎች ሁሉ ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚሰጠውን መመሪያ እንዲቀበሉና ፈቃዱን እንዴት እንደሚያደርጉ እንዲማሩ በቅንዓት ይጋብዛሉ። የዚህ አንድ ብሔር ሕዝቦች ‘ሠይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ አድርገው ስለሚቀጠቅጡና ዳግመኛ ጦርነት ስለማይማሩ’ የእውነተኛ ሰላምን መንገድ ይከተላሉ። በእርግጥም ደስተኛ ሕዝብ ነው!
አንተም ብትሆን ከዚህ ደስታ ልትካፈል ትችላለህ። ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ አጥፊ መንግሥታትንና ሰዎችን አጥፍቶ ገነትን በምድር ላይ መልሶ ስለሚያቋቁምበትና በፍጥነት እየቀረበ ስለመጣው ቀን ልትማር ትችላለህ። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) የይሖዋ ምሥክሮች አሁንም እንኳ ቢሆን አንድ የተባበረ ሕዝብ በመሆን ለዚህ እውነተኛ ሰላም ለሚገኝበት አስደናቂ ዘመን ከሚደረገው የዝግጅት ሥራ ከፍተኛ ደስታ ያገኛሉ። ይህም በሚቀጥሉት ገጾች ተገልጾአል።