ዓለም አቀፍ ደስታ
“እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ።” (ኢሳይያስ 65:14) ይህን ቃል በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል የተናገረው ይሖዋ አምላክ ነው። ቃሉም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ በአስደናቂ ሁኔታ በመፈጸም ላይ ነው። የልብ ደስታ ያገኙት ከየት ነው? ለይሖዋ አምላክ ከሚያቀርቡት የአንድነት አምልኮ ነው። ይሖዋ ደስተኛ አምላክ ነው። እርሱንም የሚያመልኩ ሁሉ “ልባቸው [በይሖዋ (አዓት)] ሐሴት ያደርጋል።” (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ ዘካርያስ 10:7)ይህ የደስታና ለአምላክ የማደር መንፈስ አንድ ሕዝብአድርጎ ያስተባብራቸዋል። በአንድነትም የመንግሥቱን ምሥራች ይሰብካሉ፣ ለአምላካቸውም ዓለም አቀፍ የውዳሴ ጩኸት ያሰማሉ።—ራእይ 7:9, 10
“ማንም ሊወስድባቸው የማይችል ደስታ”
በእርግጥም የአምላክን ሰላምና መንግሥት ማሳወቅ ለይሖዋ ምሥክሮች የማያቋርጥ ደስታ የሚያመጣ ሥራ ነው። (ማርቆስ 13:10) እነርሱም “በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ (ይሖዋን) የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት ይታዘዛሉ።—መዝሙር 105:3
ይህን ሥራ ለመሥራት አብዛኛውን ጊዜ የተለያየ እንቅፋት ማሸነፍ አስፈልጓቸዋል። በስፔይን አገር ኢሲድሮ ራሱን ለይሖዋ ወሰነና ለሌሎች ሰዎች ስለ ይሖዋ ለመናገር ፈለገ። ይሁን እንጂ የከባድ መኪና ሾፌር በመሆኑ ቀን ቀን እየተኛ ማታ ማታ ረዥም ርቀት ያለው መንገድ ስለሚጓዝ ያለው ነፃ ጊዜ በጣም አነስተኛ ነው። ኢሲድሮ ለሌሎች የከባድ መኪና ሾፌሮች ለመመስከር ፈለገ። ግን እንዴት ሊያነጋግራቸው ይችላል?
በመኪና ውስጥ ከሌሎች የከባድ መኪና ሾፌሮች ጋር ለመነጋገር የሚያስችለው ሬዲዮ አስገባ። ወዲያው ብዙ ሰዎች በ13 መስመር እንደማይጠቀሙ ተገነዘበና በዚሁ መስመር ለመጠቀም ወሰነ። እርግጥ በሬዲዮ አማካኝነት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲነጋገሩ ሐሳብ ያቀረበላቸው የከባድ መኪና ሾፌሮች በመጀመሪያ ሐሳቡን አልተቀበሉትም ነበር። አንዳንዶች ግን አደመጡት። ቀስ በቀስ ወሬው ተዛመተና ብዙ ሾፌሮች መስመር 13ን መክፈትና ማዳመጥ ጀመሩ። በቅርቡ ቢያንስ አንድ ሾፌር በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ለመግፋት እርምጃ በመውሰድ ላይ እንዳለ ኢሲድሮ አውቆአል።
በኢጣልያ አገር አንድ ሰው በአውቶብስ ላይ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲነጋገር ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሰማ። ሚስቱም በአንድ ጓደኛዋ አማካኝነት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። ባልና ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስን አጠኑና ያጠኑትን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ጉጉት አደረባቸው። ጉጉታቸው በጣም ከፍተኛ ስለነበረ የመንግሥቱን ምሥራች ለሰዎች በመናገር የሚያሳልፉት ብዙ ጊዜ እንዲኖራቸው ባልዬው በሚሠራበት ድርጅት የተሰጠውን ዕድገት ለመቀበል እምቢ አለ። ሚስትየዋም ጥሩ ገቢ የምታገኝበትን ሥራ ተወች። ታዲያ ይህን እርምጃ በመውሰዳቸው ጥሩ ውጤት አግኝተዋልን? አዎ፣ ሰውዬው እንዲህ ይላል፦ እኔና ሚስቴ እውነትን ካወቅንበት ጊዜ ጀምሮ 20 ሰዎች ስለ አምላክ ዓላማ ትክክለኛ ዕውቀት እንዲያገኙ በመርዳት ተደስተናል። እርግጥ ነው፣ ቀኑ መሽቶ ከይሖዋ አገልግሎት ወደ ቤት ስመለስ ድካም ይሰማኛል። ቢሆንም ደስተኛ ነኝ። ይሖዋ ማንም ሊወስድብኝ የማይችል ደስታ ስለሰጠኝ በጣም አመሰግነዋለሁ።”
“እስከ ምድር ዳርቻ”
የአምላክ ደስተኛ ሕዝብ አባላት በሙሉ በየትኛውም የምድር ክፍል ‘በምድር ዳርቻ’ የሚኖሩ እንኳን ቢሆን ተመሳሳይ ቅንዓት ያሳያሉ። (ሥራ 1:8) ከሰሜናዊ ግሪንላንድ ይበልጥ ሩቅ የሆኑ አገሮች የሉም ሊባል ይቻላል። በዚህም አገር እንኳን ቢሆን ከአርክቲክ መስመር 320 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኘው 19 አባላት ያሉት የኢሉሊሳት ጉባኤ ይገኛል። እነርሱም ኢጣልያውያኑ ባልና ሚስት የሚሰብኩትን ዓይነት ምሥራች ይሰብካሉ። ባለፈው ዓመት ሰባት ግሪንላንዳውያን ሕይወታቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት በመጠመቃቸው በጣም ተደስተዋል።
ከግሪንላንድ ብዙ ሺህ ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው ሞሪሽየስ የተባለች የሕንድ ውቅያኖስ ደሴትም አንጂኒ ተመሳሳይ ደስታ አግኝታለች። አንጂኒ በመጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞአት ነበር። በሞሪሽየስ አንዲት ያላገባች የሒንዱ ሕንዳዊት ልጃገረድ በክርስቲያን ስብሰባዎች መገኘትና ስለ አምላክ በአደባባይ መመስከር እንደ ነውር የሚታይ ነው። አንጂኒ ግን ተስፋ አልቆረጠችም። ዛሬ ክርስቲያናዊውን አኗኗር መከተል ከጀመረች ከዘጠኝ ዓመት በኋላ አንዳንድ ዘመዶችዋም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምረዋል።
ከአንጂኒ ጋር ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ በሌላው ዓለም ክፍል በሆንዱራስ የሚኖረው ኤሚሊዮ መጠቀስ ይገባዋል። ኤሚሊዮ የሥራ ባልደረቦቹ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲወያዩ ሰማና በውይይቱ ውስጥ እንዲያስገቡት ጠየቃቸው። ማንበብ ስለማይችል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሲነበቡ በደስታ ያዳምጥ ነበር። ክርስቲያናዊው እውነት ወደ ኤሚሊዮ ልብ ጠልቆ ሲገባ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አኗኗሩን አቆመ። ከመጠን በላይ መጠጣቱንም ተወ። የይሖዋ ምሥክሮች ማንበብና መጻፍ አስተማሩት። በአሁኑ ጊዜ የአምላክ ደስተኛ ሕዝብ አባል የሆነ አገልጋይ ነው።
ከሆንዱራስ በስተሰሜን ምዕራብ በሺህ የሚቆጠር ኪሎሜትር ርቃ በምትገኘው በአላስካ አንዲት ኤስኪሞ እናት ይህንኑ ክርስቲያናዊ እውነት ተማረች። ይህች ሴት በጣም ራቅ ባለ ቦታ ትኖር ስለነበረ ከይሖዋ ምሥክሮች ልትገናኝ የምትችለው በፖስታ አማካኝነት ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት በፖስታ ጥናት ጀመረች። ጥያቄዎችዋንም በፖስታ ትልክ ነበር። አሁን ያወቀችውን ለጎረቤቶችዋ በቅንዓት በማካፈል ላይ ነች። እንደነዚህ ያሉትን ምሳሌዎች ዘርዝረን ልንጨርስ አንችልም። በዓለም በሙሉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘ይሖዋን በደስታ ለማገልገል’ እየጎረፉ ነው።—መዝሙር 100:2
“እርስ በርሳችሁ ፍቅር ይኑራችሁ”
እነዚህን ሰዎች ሁሉ የሳባቸው አንድ ነገር ቢኖር በአምላክ ደስተኛ ሕዝቦች መካከል ያለው ፍቅር ነው። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሎአል። (ዮሐንስ 13:35) ክርስቲያናዊ ፍቅር በእነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዕለታዊ አኗኗር በተለይም በአደጋ ጊዜ ይታያል።
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በታገደበት አንድ የአፍሪካ አገር ከፍተኛ ድርቅ ደርሶ ነበር። አሥር ሺህ ሰዎች ሲሞቱ ብዙ ከብቶች አልቀዋል። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ሕይወታቸውን ሊያቆዩ የቻሉት እንዴት ነው? የዕፀዋትን ሥራ ሥርና የውስጠኛውን የአቮካዶ ፍሬ ቀቅለው በመብላት ነበር። ይሁን እንጂ በሌሎች አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ እርዳታ የመንግሥት ፈቃድ አግኝተው 250 ኩንታል የሚያክል ደራሽ እርዳታ በላኩላቸው ጊዜ ችግራቸው በጣም ተቃለለ። ሥራው የታገደ ቢሆንም ይህ የእርዳታ ጭነት በወታደሮች ታጅቦ ምንም አደጋ ሳይደርስበት ሊደርሳቸው ቻለ።
በእውነትም እነዚህ አፍሪካውያን የይሖዋ ምሥክሮች የወንድሞቻቸው ፍቅር መግለጫ የሆነውን ይህን እርዳታ በደስታ ሲቀበሉ “እነሆ፣ (የይሖዋ) እጅ ከማዳን አላጠረችም፣ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም” የሚለው የኢሳይያስ ቃል ተፈጽሞላቸዋል።—ኢሳይያስ 59:1
ሰላማዊ ሕዝቦች
በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የአምላክ ደስተኛ ሕዝቦች የዚህን ዓለም የጦረኝነት መንፈስ ትተው ‘ሠይፋቸውን ማረሻ’ አድርገው ስለቀጠቀጡ ወደ እነዚህ ሕዝቦች ተስበዋል። (ኢሳይያስ 2:4) በኤልሳልቫዶር ከዚህ በፊት ወታደር የነበረ የአንድ ሰው ቤት በወታደርነቱ ጊዜ በሰበሰባቸው ወታደራዊ ማስታወሻዎች ተሞልቶ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመረ ጊዜ ግን የሰላም ፍላጎት አደረበት። በኋላም ከጦርነት ጋር ዝምድና ያላቸውን ዕቃዎች በሙሉ ከቤቱ አስወግዶ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት ማስፋፋት ጀመረ።
ይኖርበት የነበረው መንደር በመንግሥት ተቃዋሚዎች በተያዘ ጊዜ እሥረኛ ሆኖ ተወሰደ። ከዚህ በፊት ወታደር እንደነበረ ሳይጠቆምበት አልቀረም። ይሁን እንጂ እርሱ አሁን ወታደር አለመሆኑንና ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ምስክር መሆኑን ገለጸ። የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች በቤቱ ውስጥ የጦር መሣሪያ ደብቆአል በማለት ከስሰውት ነበር። ሆኖም በተደረገው ፍተሻ ምንም መሣሪያ ሊገኝበት አልቻለም። ከዚያም የአመጸኞቹ መሪ ጎረቤቶቹን ስለ ሰውየው እንዲነግሩት ጠየቀ። የሰጡት መልስ፦ “በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ እየሰበከ ሲወጣና ሲወርድ ብቻ ነው የምናየው” የሚል ነበር። ሰውዬው ነፃ ተለቀቀ። ቅንዓቱ ሕይወቱን እንዳዳነለት አያጠራጥርም።
ከአንድ የአፍሪካ አገር የመጣ ሪፖርት መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ስለጀመሩ ሁለት ወታደሮች ይገልጻል። አንደኛው በመንግሥቱ ጦር ሠራዊት የሚያገለግል ሲሆን ሌላው ደግሞ ለተቃዋሚ ቡድኖች የሚዋጋ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁለቱም ‘ሠይፋቸውን ማረሻ አድርገው ለመቀጥቀጥ ወሰኑና’ ከውትድርና ተሰናበቱ። በክርስቲያን ስብሰባ ላይ በተገኙበት የመጀመሪያ ቀን የመንግሥት ተቃዋሚ የሆነው ወታደር ሌላውን “እዚህ ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም መልሶ “አንተስ ምን ታደርጋለህ?” አለው። “ከዚያም እርስ በርሳቸው ተቃቅፈው በሰላም ለመተባበር በመቻላቸው የደስታ እንባ አለቀሱ” በማለት ሪፖርቱ ይደመድማል። እነዚህ ወታደር የነበሩ ሁለት ሰዎች “የመድኃኒቴ አምላክ (ይሖዋ) ሆይ፣ ከደም አድነኝ፣ አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች” ብለው እንደ ጸለዩ አያጠራጥርም።—መዝሙር 51:14
“መከራዬን አይተሃልና”
መዝሙራዊው “መከራዬን አይተሃልና፣ ነፍሴንም ከጭንቀት አድነሃታልና በምሕረትህ ደስ ይለኛል ሐሤትም አደርጋለሁ” በማለት ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 31:7) ዛሬም ቢሆን ብዙ ሰዎች የአምላክ ቃል የሚያጋጥማቸውን መከራ እንዲወጡ ስለሚነግራቸው ይደሰታሉ። በፈረንሳይ አገር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ስኪዞፍሬንያ የተባለ የአእምሮ በሽታ ካለባት ሴት ጋር ታጠናለች። ይህች ሴት የሥነ አእምሮ ሕክምና ሲደረግላት ቢቆይም ሕክምናው ምንም አልረዳትም ነበር። ጥናትዋን ከጀመረች ከአንድ ሣምንት በኋላ የሥነ አእምሮ ሐኪምዋ “ይህች ሴት ከመጽሐፍ ቅዱስ የምታስረዳሽ ነገር በእውነት ይገባሻልን?” ብሎ ጠየቃት። ለዚህ ጥያቄው መልስ ለመስጠት የይሖዋ ምሥክርዋ ወደ ሐኪሙ ቢሮ ሄደችና እርሱ በተገኘበት በሽተኛዋን ሴትዮ አስጠናቻት።
ከጥናቱ በኋላ የሥነ አእምሮ ሐኪሙ ለይሖዋ ምሥክሯ እንዲህ አላት፦ “ለብዙ ዓመታት ስለ በሽተኞቼ ሃይማኖት ስከታተል ቆይቼአለሁ። ማንኛውም ሃይማኖት ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳልሰጣቸው ተረድቼአለሁ። የአንቺ ሁኔታ ግን የተለየ ነው። ሚስስ ፒ በየሣምንቱ ሁለት ጊዜ እኔ ዘንድ ትመጣለች። ለዚህም ትከፍለኛለች። አንቺ ግን አለምንም ክፍያ በሰጠሽው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ጥሩ ምክር ከእኔ የተሻለ ውጤት አግኝተሻል። ጥሩ መሻሻል እያሳየች ነው። በዚሁ ቀጥይበት። የእኔ እርዳታ ካስፈለገሽ ሙሉ በሙሉ እንደምተባበርሽ አረጋግጥልሻለሁ።”
መጽሐፍ ቅዱስ “እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ [ይሖዋ ሆይ (አዓት)] በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ። በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል” ይላል። (መዝሙር 89:15, 16) ይህ መዝሙር እውነት እንደሆነ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ ያውቃሉ። ከአፋቸውም ዓለም አቀፍ እልልታ እየወጣ ይሖዋን ያወድሳል። ከእነዚህም ሕዝቦች ጋር ተባብረው ይሖዋን የሚያመሰግኑ ብዙ ሰዎች ከብሔራት ሁሉ እየጎረፉ ነው። አንተስ ለምን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተባብረህ ይህን ደስታቸውን በግልህ አትቀምስም?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በምሥራቅ አውሮፓ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች በራሳቸው ቋንቋ “መጠበቂያ ግንብ” ለማግኘትና ለማጥናት ባገኙት ነፃነት ይደሰታሉ