አመስጋኝ ለመሆን እንዴት ብዙ ምክንያቶች አሉኝ!
በሎቲ ሆል እንደተነገረው
ነገሩ የሆነው በ1963 በሕንድ አገር ከምትገኘው ካልካታ በርማ ውስጥ ወደምትገኘው ራንጉን በመጓዝ ላይ እንዳለን ነበር። በአይሮፕላን ተሳፍረን ካልካታን እንደለቀቅን ወዲያው አንድ ወንድም በአይሮፕላኑ ክንፍ ላይ ዘይት ሲፈስስበት ተመለከተ። ለአይሮፕላኑ ሠራተኞች ነገሩ ሲነገራቸው አይሮፕላኑ በድንገት እንደሚያርፍ አስታወቁ። ይሁን እንጂ አይሮፕላኑ ማረፍ ይችል ዘንድ መጀመሪያ ነዳጁን መጨረስ ነበረበት። አስተናጋጁ “የምትጸልዩ ከሆነ አሁን አድርጉት!” ብሎ ጮኸ። ይሖዋ ፈቃዱ ከሆነ በሰላም እናርፍ ዘንድ ጸለይን። በእርግጥም ደህና አረፍን። በእውነትም አመስጋኞች የምንሆንበት ምክንያት ነበረን።
አዎን አመስጋኝ የምሆንበት ሌላም ብዙ ነገር አለኝ። በ79 ዓመት ዕድሜዬ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት የምጠቀምበት መጠነኛ ጤንነትና ጉልበት አሁንም አለኝ። ከዚህም ሌላ ለይሖዋ ሕዝቦች ሁሉ የጋራ ከሆኑት በረከቶች በተጨማሪ ብዙ ሌሎች ተሞክሮዎችም አሉኝ። በጠቅላላው ከ60 ዓመት በላይ ይሖዋን ማገልገል ውድ ዕጣ ፈንታዬ ሆኗል። ከዚህም ጊዜ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሠራሁት በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ወይም በአቅኚነት ነው።
ይህ ሁሉ የጀመረው ከአባቴ ጋር በካርቦንዴል ኢሊኖይ ስንኖር በነበረበት ጊዜ ነው። አባቴ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት የሚባለው የሃይማኖት ክፍል አባል ነበረ። ቄስ ለመሆን ፍላጎት ነበረው። ይሁን እንጂ ስለ ሥላሴ፣ የነፍስ አለመሞትና የዘላለም ሥቃይ ትምህርቶችን በሚመለከት የራሱ አስተሳሰብ ስለነበረው ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጆች ውስጥ ያጋጠመው ነገር ግራ አጋባው።
በመጨረሻ በ1924 እኔ የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ አቅኚ በነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አማካኝነት የመጣለት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አረካው። አባቴ የስላሴ፣ የሲዖል እሳትና የሰው ነፍስ አትሞትም የሚሉ እምነቶች የሐሰት ትምህርቶች መሆናቸውንና እንደ እሱ የሚሰማቸው ሌሎች ሰዎች መኖራቸውን በማወቁ ተደሰተ። ቤተሰባችን ወዲያውኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (የይሖዋ ምሥክሮች ያኔ የሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ነበር) ጋር አዘውትሮ መሰብሰብ ጀመረ። ስለ ይሖዋና ስለ ቃሉ እውነቱን ማወቄ በእውነት አመስጋኝ የሆንኩበት ነገር ነበር።
ይሁን እንጂ ብዙ ሳይቆይ አደጋ ወደቀብን። ለአባቴ እነዚህን እውነቶች ያመጣለት ሰው ውሸተኛና ብልግና የሚፈጽም ሆነ። አባቴን አደናቀፈው። እናቴና እኔ ግን አልተደናቀፍንም። በዚህን ጊዜ የ15 ዓመት ዕድሜና የስድስት ልጆች በኩር ነበርኩ። ከእናቴ ጋር እውነትን አጥብቄ ያዝኩ።
በ1927 የክረምት ወራት በቶሮንቶ ካናዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትልቅ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ማስታወቂያ ተነገረ። አባቴ ለመሄድ ገንዘብ የለኝም አለ። እናቴ ግን ቆራጥ ሴት ነበረች። የቤት ዕቃዎች እየዞረች መሸጥ ጀመረችና ስብሰባው በደረሰበት ሰዓት ስምንት ዶላር አጠራቀመች። ያንን ገንዘብ ይዘን በሺህ ማይሎች ርቆ ወደሚገኘው ቶሮንቶ መኪና እየለመንን ለመሄድ ተነሣን። 37 መኪናዎች አለዋውጠን በአምስት ቀናት ውስጥ ስብሰባው ከመጀመሩ ከአንድ ቀን በፊት ደረስን። የነበረን ገንዘብ በጣም አነስተኛ ስለነበረ ነፃ መኝታ ጠይቀን አገኘን። ወንድም ኤ ኤች ማክሚላን ስለ ጉዞአችን ሲሰማ “የባቡር ክፍያው መጠን መጨመር እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አያስጨንቃቸውም” በሚል ርዕስ በስብሰባው ጋዜጣ ላይ አሰፈረው።
እናቴ አባቴን በፖስት ካርዶች አማካኝነት ስለ ስብሰባው ትነግረው ነበርና በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ለሚደረገው የሕዝብ ንግግር በመኪና ተጉዞ ደረሰ። አሁን ወደ ቤታችን ለመድረስ መኪናዎችን መለመን አላስፈለገንም። ምን ዓይነት ስብሰባ ነበር! በዚያ ስብሰባ ልንገኝ በመቻላችን እንዴት አመስጋኝ ነበርኩ! አባቴም መንፈሳዊ ሚዛኑን መልሶ ለማግኘት ስብሰባው ስለረዳው እንዴት አመስጋኝ ነበርኩ!
ለብዙ ዓመታት ሃይማኖቴ ምን እንደሆነ ስጠየቅ በእንግሊዝኛ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማህበር ለሚለው አጠራር ምሕፃረ ቃል የሆኑትን አራት ፊደሎች በመጥራት “IBSA” ነው ብዬ እመልስ ነበር። ይሁን እንጂ በዚያ ስያሜ ፈጽሞ ደስተኛ አልነበርኩም። ስለዚህ በኮሎምቦስ ኦሃዮ በ1931 በተደረገው ስብሰባ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲስ ስም በተቀበልን ጊዜ በጣም አመስጋኝ ነበርኩ።
በትምህርት ቤት የተማርኩት ሞያ
ሕይወቴን ካበለጸጉት በረከቶች መካከል ከሙዚቃ ጋር የተያያዙ ነገሮች ይገኙበታል። ሙዚቃ በጣም እወድ ስለነበረ ፒያኖ መጫወት ገና በልጅነቴ ተማርኩ። ለብዙ ዓመታት በጉባኤ መዝሙር ላይ በአጃቢነት የመጫወት መብት ነበረኝ። የመጠበቂያ ግንብ ማህበር የመንግሥት መዝሙሮችን መቅረጽ ከመጀመሩ በፊት በፓፑዋ ኒው ጊኒ ያገለግል የነበረ አንድ ሚስዮናዊ ወንድም የፓፑዋ ወንድሞች መዘመር ይማሩ ዘንድ በርካታ መዝሙሮችን እንድቀዳ አንድ ጊዜ ጠይቆኝ ነበርና ያንን ማድረግ በጣም ያስደስተኝ ነበር።
ይሁን እንጂ በጣም የምወደው መሣሪያ ክላሪኔት የሚባለው ዋሽንት መሳይ መሣሪያ ነበር። በኮሌጅ ኦርኬስትራ ላይ እሱን መጫወት እወድ ነበር። የኮሌጁ ፕሮፌሰር በጨዋታዬ በጣም ከመደሰቱ የተነሣ ከወንዶች የሙዚቃ ጓድ ጋርም እንድጫወት ጠየቀኝ። በዚያ ዘመን ማንም ሴት በወንዶች የሙዚቃ ጓድ ውስጥ ተጫውታ ስለማታውቅ የጓዱ አባሎች ፕሮፌሰሩ ያቀረበውን ሐሳብ ሲሰሙ አድማ ለማድረግ አቀዱ። ካደሙ እንደሚባረሩ ማሳሰቢያ በተላለፈላቸው ጊዜ ግን ሐሳባቸውን ለወጡ። በአንድ የሙሉ ቀን ሰልፍ ላይ ከሙዚቃ ጓዱ ጋር አብሬ እንድጓዝ በተደረግሁ ጊዜ ሌላ ባሕል ተጣሰ። ጋዜጣም ሁኔታውን ስሜት የሚቀሰቅስ ግምት በመስጠት በትላልቅ ፊደላት “የሴት ሙዚቀኛ በወንዶች ባህር ውስጥ” በሚል አምድ ላይ አወጣ።
በመጨረሻም ለሙዚቃ ፕሮፌሰርነት ቃለ መጠይቅ ተደረገልኝ። ይሁን እንጂ የሙዚቃ አስተማሪ ከሆንኩ ሊነሱ የሚችሉትን ውዝግቦች ለምሳሌ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ሙዚቃዎችን እንዳስተምር ወይም እንዳጫውት ልጠየቅ የምችል መሆኔን በማሰብ ሌላ ሥራ ለመያዝ ወሰንኩ። የዓለምን ታሪክ እንዳስተምር ተመደብኩ። ይሁን እንጂ ያ ለውጥ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በምሄድበት ጊዜ በብዙ አገሮች በስብሰባ ኦርኬስትራ ውስጥ የክላሪኔት መሣሪያዬን እንዳልጫወት አልከለከለኝም።
ከጊዜ በኋላ በዴትሮይ ከተማ ዳርቻ በሚገኝ አንድ ትልቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በዓለም ታሪክ ትምህርት መምህር ሆንኩ፤ በዚህም ምክንያት አንዴ ከአያሌ አዳዲስ የመማሪያ መጻሕፍት መካከል ሁሉንም ተመልክቼ የትኛው እንደሚሻል እንድመርጥና ሐሳብ እንዳቀርብ በርዕሰ መምህሩ ተጠየቅሁ። እነዚህን መጻሕፍት በምመረምርበት ጊዜ የምንጠቀምበት መጽሐፍ የይሖዋን ስም ስምንት ጊዜ ሲጠቅስ አዳዲሶቹ ግን ብዙዎቹን የአረማውያን አሕዛብ አማልክት ለምሳሌ ራ፣ ሞሌክ፣ ዚየስና ጁፒተር የመሳሰሉትን በስም ጠቅሰው የዕብራውያንን አምላክ ግን ያለ ስም እንዳስቀሩት በማየቴ በጣም ተገረምኩ። አሻሻጩ ሲመጣ በመጽሐፉ የይሖዋ ስም ለምን እንዳልተጠቀሰ ጠየቅሁትና “በይሖዋ ምሥክሮች የተነሣ ያንን ስም በመጽሐፋችን ውስጥ አናስገባም” አለኝ። “ደህና፣ እንግዲያውስ መጽሐፉን ትምህርት ቤቱ እንዲገዛው ሐሳብ አላቀርብም” አልኩት። መጽሐፉን በቦርሳው ከተተና ሰተት ብሎ ወጣ።
በኋላም ለርዕሰ መምህሩ አዲስ መጽሐፍ እንደማያስፈልገን ከበርካታ ጥሩ ምክንያቶች ጋር ነገርኩት። እሱም በሐሳቤ ተስማማ። ከጥቂት ወራት በኋላ የዓለም ታሪክ ትምህርት ከሁለተኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት እንዲወጣ ሲወሰን ሁሉም በዚያ ውሳኔ ተደሰቱ። በ14ቱም የትምህርት ቤት ሥርዓቶች ኅብረ ትምህርት የተባለው አዲስ ዓይነት ትምህርት ተተካ። ትምህርት ቤቱ አዲስ የታሪክ መጻሕፍት ገዝቶ ቢሆን ኖሮ ምን ያህል የማያስፈልግ ወጪ ያስከትል ነበር!
በትምህርት ቤት በማስተማር ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎች ነበሩኝ። ጥብቅ ሥነ ሥርዓት አስከባሪም ነበርኩ። ይህም በርካታ የዕድሜ ልክ ወዳጅነቶችን አፍርቶልኛል። መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠትም ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩኝ። ይሁን እንጂ በመጨረሻ ጊዜና ሁኔታዎች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሩኝ።
ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች
በትምህርት ቤት ለ20 ዓመታት ካስተማርኩ በኋላ ዓይኖቼ መድከም ጀመሩ። ከዚህም ሌላ ወላጆቼ እንደማስፈልጋቸው ተሰማቸው። ስለዚህ አባቴ ሊሠራ የሚገባው ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ የማስተማር ሥራ እንዳለና ይሖዋም እንዳልራብ ራሱ እንደሚመግበኝ በመግለጽ ወደ ቤቴ (ወደ ወላጆቼ) እንድመጣ ጠየቀኝ። በ1955 ማስተማር ተውኩ። ከዚያም በኋላ መጀመሪያ ካገኘኋቸው በረከቶች አንዱ በአውሮፓ “ድል አድራጊው መንግሥት” በሚል ርዕስ ተከታታይ ስብሰባዎች መካፈል ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ብዙ ስቃይ ካሳለፉት ብዙዎቹ ወንድሞቻችን ጋር ለመገናኘት በመቻሌ እንዴት አመስጋኝ ነበርኩ! በተለይ በረከት የነበረው ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሂትለር የድል ሰልፍ ሊያደርግ አቅዶበት በነበረው በኑረምበርግብ ውስጥ ያለው ዜፐሊንዊይስ ወይም ዜፐሊን ሜዳን ጥቅጥቅ አድርገው ከሞሉት 107,000 መካከል መገኘቱ ነበር።
ያ ጉብኝት ለማድረግ ከታደልኳቸው ብዙ የዓለም ጉብኝቶች የመጀመሪያው ብቻ ነበር። በ1963 እናቴና እኔ በ“ዘላለማዊ ወንጌል” ስብሰባዎች በዓለም ዙሪያ ተጓዥ ከነበሩት 583 ተሰብሳቢዎች መካከል ነበርን። ያ ጉብኝት ከኒው ዮርክ ወደ አውሮፓ ከዚያም ወደ እስያና በሰላማዊ ውቅያኖስ ወዳሉ ደሴቶች አድርጎ ወሰደንና በፖሳዴና ካሊፎርንያ አበቃ። በዚያ ጉዞ ወቅት ነበር በመግቢያው ላይ የተገለጸው አስፈሪ ተሞክሮ ያጋጠመን። ከዚያ በኋላ ያደረግናቸው ጉብኝቶች ደቡብ አሜሪካ፣ ደቡብ ፓስፊክና አፍሪካ ወደተደረጉ ስብሰባዎች ነበር። በእውነትም እነዚህ ጉብኝቶች ሕይወቴን አበልጽገውታል። ከእነዚህ ቦታዎች በብዙዎቹ ስብሰባዎች የሙዚቃ ጓዶች ውስጥ መጫወት መቻል ለሙዚቃ አፍቃሪ ደስታ ነበር።
ወደ አቅኚነት መግባት
በ1955 ከአውሮፓ ከተመለስኩ በኋላ ከእናቴ ጋር ለአንድ ዓመት በአቅኚነት ሥራ ተካፋይ ሆንኩ። ከዚያም ማህበሩ በምዕራብ ፍሎሪዳ ውስጥ በሚገኘው በአፖላቺ ኮላ ከምትገኝ ትንሽ ጉባኤ ጋር እንድሠራ ጠየቀኝ። ለሰባት ዓመታት አንዲት ሌላ እህትና እኔ እዚያ ባለው ሥራ እርዳታ ስናበረክት ቆየን። ወዲያውም ቁጥሩ እየጨመረ የሄደውን ጉባኤ ለማስተናገድ እንዲቻል የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት ተቻለ። እድገቱ ቀጠለና በአጭር ጊዜ ውስጥ በፖርት ሴንት ጆ ሌላ ጉባኤ ተቋቋመ። በምዕራብ ፍሎሪዳ ከሦስት ጉባኤዎች ጋር በመሥራት አሥራ አንድ ዓመት አሳለፍኩ።
አንድ ጊዜ ለክልል ስብሰባ ቦታ እንድንፈልግ በክልል የበላይ ተመልካቹ ተጠየቅሁና በፖርት ሴንት ጆ ስመ ጥር የሆነውን ሴንቴኒያል ሕንፃ በ25 ብር ብቻ ኪራይ ለማግኘት ቻልኩ። ይሁን እንጂ ካፊቴሪያም ያስፈልገን ነበርና የትምህርት ቤቱን የካፊቴሪያ አገልግሎት መጠቀም አሰብን። ሆኖም የትምህርት ቤቱ ተቆጣጣሪ እንደ ተቃወመ ደረስኩበት። ከትምህርት ቤቱ ቦርድ ጋር በስብሰባ ማነጋገር እንዳለብኝ ተነገረኝ። ከንቲባውም ካፊቴሪያውን እንድንጠቀምበት ስለፈለጉ ወደ ስብሰባው መጡ። በካፊቴሪያው እንዳንጠቀም ተቃውሞ የሚያስነሣው ችግር ምን እንደሆነ ከንቲባው ሲጠይቁ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በትምህርት ቤት ውስጥ ሃይማኖታዊ ቡድን ተጠቅሞ ስለማያውቅ ነው ብሎ መለሰ። ከንቲባው መልሴን ለመስማት ወደኔ ዞር አሉ። ባጋጣሚ በሌሎች ከተሞች ባደረግናቸው ስብሰባዎች በትምህርት ቤት እንደተጠቀምን የሚያሳዩ በርካታ የግብዣ ወረቀቶች ይዤ ስለነበር እነርሱን አሳየሁ። ከዚያም ሐዋርያው ጳውሎስ በትምህርት ቤት አዳራሽ እንደሰበከ የሚናገረውን ሥራ 19:9ን ጠቀስኩ። ይህም ነገሩን ዘጋው። ቦርዱ ካፊቴሪያውን በ36 ዶላር እንድንከራይ ከከንቲባው ጋር ተስማማ።
በ13 ዓመት ዕድሜዬ ስጠመቅ “እባክህ አምላኬ አንድ ሰው እንኳን ወደ እውነት ላምጣ” ብዬ ጸልዬ ነበር። ብዙ ሰዎች አቋማቸውን ለይሖዋና ለመንግሥቱ እንዲያደርጉ በመርዳት ስለተባረክሁ ያ ጸሎት በብዙ እጥፍ እየተመለሰልኝ ነበር። ሆኖም በተደጋጋሚ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዬ ሕይወቱን ወደመወሰንና ወደ መጠመቅ ደረጃ ሊደርስ ሲል ወደሌላ ጉባኤ እመደብ ነበር። ቢሆንም የመትከል፣ የመዝራትና የማጠጣት መብት ነበረኝ። ከእነዚህ ተማሪዎች ብዙዎቹም የዕድሜ ልክ ወዳጆች ሆነዋል። እንደነዚህ በመሰሉ ፍሬያማ ሥራዎች መካፈል በእውነት አመስጋኝ የምሆንበት ብዙ ምክንያቶች አምጥቶልኛል።
የዜና ማሠራጫ የሰጠው እርዳታ
የዜና ማሠራጫዎች በብዙ ቦታዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ብዙ ጊዜ መጥፎ ወሬ ያሠራጫሉ። አሁን በማገለግልበት አካባቢ በዴ ላንድ ፍሎሪዳ የሚገኙት የዜና ማሠራጫዎች ግን ለመመስከር የረዱኝ መሆኑን ልናገር እወዳለሁ። ለምሳሌ ያህል እናቴና እኔ ከእነዚያ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ጉብኝቶች በአንዱ ሳለን ላካባቢው ጋዜጣ ረዥም ደብዳቤ ላክን። እነዚህ መልእክቶች ከፎቶግራፎቹ ጋር ወዲያውኑ ታተሙ። አቀራረቡ ደግሞ የመንገደኛው ጋዜጠኛ ዓይነት ነበር። ይሁን እንጂ እነዚያን አጋጣሚዎች ስለ ይሖዋ ስምና መንግሥት ለመመስከር ተጠቀምንባቸው።
ከመንገድ ወደ መንገድ ምሥክርነቴን በሚመለከትም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። አንዱ የምቀመጥበት ሌላው ደግሞ ጽሑፎቻችንን የምደረድርበት ሁለት የአትክልት ቦታ ዓይነት ወንበሮች የነበሩበት አንድ የመንገድ ላይ ማዕዘን ነበረኝ። አንድ ጊዜ በአካባቢው ጋዜጣ ላይ “የዲላንዷ ሎቲ ምሥክሮች የሆኑ ወላጆቿን ሥራ ቀጥላበታለች” በሚል አምድ ሥር ከፎቶግራፍ ጋር ግማሽ ገጽ የሚሆን አንቀጽ ወጥቶ ነበር። በቅርቡም በ1987 በሌላ ጋዜጣ ላይ “ሎቲ ሆል ለክርስቶስ የተከለለ የራሷ ማዕዘን አላት” በሚል ርዕስ ሥር ከትልቅ የከለር ፎቶግራፍ ጋር ግማሽ ገጽ አንቀጽ ነበረው። በተከታዩ ዓመትም ሌላ ጋዜጣ በፊት ለፊቱ (የመጀመሪያው) ገጽ ላይ “ምን ጊዜም እዚያው ናት” እና “ጡረታ የወጣችው የትምህርት ቤት መምህርት በመስክ ወንበሯ ላይ ተቀምጣ የመንገድ ማዕዘን ምድብ ቦታዋን ለይሖዋ ምሥክር ሚሲዮናዊ ሥራዋ ትጠቀምበታለች” ከሚሉ አስተያየቶች ጋር የኔን ፎቶግራፍ አውጥቶ ነበር። እንደዚሁም አራት ጊዜ የአካባቢው ቴሌቪዥን ጣቢያ እኔ ምሥክርነት ስሰጥ የሚያሳይ ፎቶግራፍ አቅርቧል። በተወሰነ መጠን ይሁን እንጂ እስከ አሁንም በሁሉም የመንግሥቱ አገልግሎት ዘርፎች ማለትም ከቤት ወደ ቤት፣ ተመላልሶ መጠየቅና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እካፈላለሁ። ይሁን እንጂ በዕድሜ መግፋት ምክንያትና አካላዊ ድካም የተነሣ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ጊዜ የማሳልፈው በመንገድ ላይ ሥራው ነው።
መለስ ብዬ ሳስበው አመስጋኝ ለመሆን በእውነትም ብዙ ምክንያቶች እንዳሉኝ ልናገር እገፋፋለሁ። ለይሖዋ ሕዝቦች ሁሉ የጋራ ከሆኑት በረከቶች በተጨማሪ የትምህርት ቤት መምህርት የነበርኩ እንደመሆኔ በብዙ ወጣቶች ላይ ጥሩ ግፊት የማሳደር መብት አግኝቼአለሁ። በዓለም ዙሪያ በበርካታ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትን (የመካፈልን) ደስታ አግኝቻለሁ። እጅግ ፍሬያማ የሆነ የአቅኚነት አገልግሎትም ነበረኝ። ከሙዚቃ ጋር በተያያዘ ጉዳይም ተባርኬአለሁ። ከዚህም በላይ በዜና ማሰራጫ አማካኝነት ልሰጥ የቻልኩት ምሥክርነትም አለ። በእውነትም ከመዝሙራዊው ዳዊት ጋር እንደሚከተለው ለማለት እችላለሁ፦ “የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ። በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።”—መዝሙር 69:30