የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“በጎቹ ድምጹን ይሰማሉ”
◻ ኢየሱስ “በጐቹም ድምጹን ይሰሙታል፤ የራሱንም በጐች በየስማቸው ጠርቶ ይወስዳቸዋል” ብሏል። (ዮሐንስ 10:3) ጨምሮም “የራሴን በጐች አውቃለሁ፤ የራሴም በጐች ያውቁኛል” አለ። (ዮሐንስ 10:14) በግ መሰል ሰዎች ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሲናገራቸው ድምጹን ይሰማሉ። በጣልያን አገር ቅን ልብ ያላቸው ሁለት ሰዎች ይህን መንገድ እንዴት እንደተከተሉ ተመልከቱ፦
በመጨረሻ ሰማ
◻ አልቤርቶ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “ማሪዋና ማጨስና ኤል ኤስ ዲ የተባለውን አደንዛዥ ዕጽ መውሰድ ስጀምር የ16 ዓመት ልጅ ነበርኩ። በ18 ዓመቴ ሄሮይን መጠቀም ጀመርኩ። እነዚህን አደንዛዥ ዕጾች ለማግኘት ማንኛውንም ሊደረግ የሚችል ነገር ሁሉ አድርጌአለሁ። ሰርቄአለሁ፣ ለዕፆቹ በደላላነት ሠርቻለሁ፣ አጭበርብሬአለሁ፣ ያለኝን ዕቃ ሁሉ ሸጫለሁ። ላቆም ግን አልቻልኩም። ለዕረፍት ወደ ውጭ አገር መሄድ፣ በገጠር ረዥም ጊዜ ማሳለፍ ወይም ደግሞ የፍትሕ መጓደልን እንዋጋለን ከሚሉ አክራሪ ቡድኖች ጋር ፖለቲካዊ መጠላለፍ ማድረጌ ማንኛቸውም ሱስን እንዳቆም አልረዱኝም። ጋብቻንም ሞከርኩ፤ ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞው ሁኔታዬ ተመለስኩ። ሴት ልጅ ብትወለድልኝም እንኳን ዕጽ መውሰድ ላቆም አልቻልኩም። እንዲያውም አሁን ተጨማሪ ገንዘብ ስላስፈለገኝ ነገሮች ተባባሱ። ከዚያም በኋላ ሚስቴ ትታኝ ሄደች። ሁለት ዓመታት ብቻዬን ስቀመጥ ልጄን ያየኋት ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር። የዕፅ ደላላዎች ገንዘብ ዕዳ ስለነበረብኝ ያሳድዱኝ ነበር። ከሰው ተገልዬ በመኖሬም በብቸኝነት ሳቢያ በሚመጡ በሽታዎች ብዙ ጊዜ ተሰቃየሁ።
“ከዚያ በኋላ ከጥቂት ዓመታት በፊት የይሖዋ ምሥክሮች የሰጡኝን መጽሐፍ አስታወስኩ። መጽሐፉ እስከ አሁን ነበረኝና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ላነበው ጀመርኩት። በዚህ መንገድ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን አወቅሁትና እንዲረዳኝ ወደሱ ጸለይኩ። የተማርኳቸውን ነገሮች ቀስ በቀስ በሥራ ሳውል የብቸኝነት ስሜት ያመጣብኝን ሕመም ጭንቀቱ እየቀነሰ መጣ። ሥራ አገኘሁና በይሖዋ እርዳታ ቤተሰቤን እንደገና ሰበሰብኩ። ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄድኩና የይሖዋ ምሥክሮች እውነት እንዳላቸው ተገነዘብኩ። ሚስቴና እኔ አብረን ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠናንና በመጨረሻ ተጠመቅን። አሁን የዘወትር አቅኚ ሆነን ተስፋችንን ከሌሎች ጋር መካፈል እንዴት ታላቅ ደስታ አምጥቶልናል!
ለአምላክ ኃይለኛ ስሜት የነበራት ሴት ጸሎቷ መልስ አገኘ
◻ አንዲት ሴት እንዲህ በማለት ገለጸች፦ “በ1958 በደብር ነክ ሥራዎች በተለይም ሮም ውስጥ የመለኮታዊ ፍቅር እመቤታችን መቅደስን ለመሳለም በሚደረገው ጉዞ ረገድ በንቃት እሳተፍ ነበር። ከጊዜ በኋላ የሮማ ገበዝ ለሆነ አለቃ የቅርብ ጓደኛ ሆንኩ። እንዲሁም ከፓፓ ጳውሎስ 6ኛ እና ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ጋር በግል ተነጋግሬአለሁ። ለ25 ዓመታት ወደ ቅዱስ ሥፍራዎች የሚደረጉ ጉዞዎችን በማደራጀት ከሠራሁ በኋላ የምስጋና ሽልማት ተቀበልኩ። ይሁን እንጂ በልባዊ ስሜት ካቶሊክ የነበረኝ እምነት መወላወል ጀመረ። ስርቆትን፣ ማጭበርበርን፣ ለዘመድ ወይም ለባለሥልጣን በማድላት መሥራትን እንዲሁም ሕገወጥ የንግድ ልውውጦችን ተመለከትኩ። የአምላክ ሕግ ብዙ ጊዜ መረገጡን ስመለከት ቤተክርስቲያኗን በተለየ ዓይን መመልከት ጀመርኩ። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ረበሹኝና እምነቴ እየጠፋብኝ ስለሄደ አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ብዙ ጊዜም አለቀስኩ።
“ከዚያ በኋላ ከአራት ዓመት በፊት ወንድ ልጄ ከይሖዋ ምሥክሮች ያገኛቸውን የመጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን ጥቂት ቅጂዎች ይዞልኝ መጣ። መጽሔቶቹ በጣም ስላስደሰቱኝ ሌላም ተጨማሪ እንዲያመጣልኝ ጠየቅኩት። ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ የይሖዋ ምሥክሮችን የመንግሥት አዳራሽ አገኘሁና ከበራፉ ላይ አንድ ሰው መጥቶ እንዲጎበኘኝ የሚጠይቅ ማስታወሻ ትቼ ሄድኩ። ከአራት ቀን በኋላ ምሥክሮቹ መጡ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩና እስከ መጠመቅ ድረስ ዕድገት አደረግሁ። አሁን በመጨረሻ ሁልጊዜ እፈልገው የነበረውን እውነት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ነኝ!”
እነዚህ ግለሰቦች የመልካሙን እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስን ድምጽ ሰሙ፤ “እውነትም አርነት አወጣቸው።”—ዮሐንስ 8:32
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Garo Nalbandian