“የብርሃንን ጋሻ ጦር ልበሱ”
“ሌሊቱ አልፏል ቀኑም ቀርቧል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ።”—ሮሜ 13:12
1, 2. አብዛኞቹ የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁድ “እውነተኛውን ብርሃን” የተቀበሉት እንዴት ነበር? ይህንስ ያደረጉት ምን አጋጣሚዎችን ሁሉ ካገኙ በኋላ ነበር?
ኢየሱስ ክርስቶስ “ለሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን” ነው። (ዮሐንስ 1:9) በ29 እዘአ መሲሕ ሆኖ በመጣ ጊዜ አምላክ ለራሱ ምሥክሮች እንዲሆኑ ወደመረጣቸውና ሌላው ቢቀር በስም ለይሖዋ የተወሰኑ ወደነበሩ ሕዝብ ነበር የመጣው። (ኢሳይያስ 43:10) ብዙዎቹ እሥራኤላውያን መሲሑን ይጠባበቁ ነበር። ከመካከላቸው በርከት ያሉት መሲሑን ለይተው የሚያሳውቁትን ትንቢቶች ያውቁ ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ በጣም ብዙ ሰዎች እያዩት ምልክቶችን እያደረገ በፓለስቲና ምድር በሙሉ ሰብኳል። ሊሰሙት ብዙ ሕዝብ ወደሱ ይጎርፉ ነበርና ባዩትና በሰሙት ነገርም ይደነቁ ነበር።—ማቴዎስ 4:23-25፤ 7:28, 29፤ 9:32-36፤ ዮሐንስ 7:31
2 በመጨረሻ ግን አብዛኞቹ አይሁዶች ኢየሱስን ሳይቀበሉት ቀሩ። የዮሐንስ ወንጌል “የእርሱ ወደሆነው መጣ፤ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” ይላል። (ዮሐንስ 1:11) ለምን አልተቀበሉትም? የዚያን ጥያቄ መልስ ማወቃችን የእነሱን ስህተት ከመድገም እንድንቆጠብ ይረዳናል። “የጨለማውን ሥራ እንድናወጣ (እንድናወልቅ) እና የብርሃንን ጋሻ ጦር እንድንለብስ” ይረዳናል። እንዲህ በማድረግም እሥራኤላውያን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከደረሰባቸው ዓይነት መጥፎ ፍርድ እንድናለን።—ሮሜ 13:12፤ ሉቃስ 19:43, 44
የሃይማኖታዊ ባለሥልጣኖች ተቃውሞ
3. የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች “ዕውሮች መሪዎች” ሆነው የተገኙት በምን መንገድ ነው?
3 በእሥራኤላውያን መካከል ብርሃኑን አንቀበልም ለማለት ቀዳሚዎች የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ነበሩ። “በሕጉ የተካኑ” (ማለትም “ሕግ አዋቂዎች”) አስተማሪዎች ከመሆናቸውም በቀር ብዙውን ጊዜ ከአምላክ ሕግ ጋር የሚቃረኑ ደንቦችን በሕዝቡ ላይ ይጭኑበት ነበር። (ሉቃስ 11:45, 46) በመሆኑም “በወጋቸው የአምላክን ቃል ሻሩ።” (ማርቆስ 7:13፤ ማቴዎስ 23:16, 23, 24) ብርሃኑ ዘልቆ እንዳያበራ የሚከለክሉ “ዕውሮች መሪዎች” ሆኑ።—ማቴዎስ 15:14
4, 5. (ሀ) ኢየሱስ መሲሕ ይሆንን እያሉ ብዙ አይሁድ ሲጠያየቁ ፈሪሳውያን ምን አደረጉ? (ለ) ፈሪሳውያን ያሳዩት ምን መጥፎ የልብ ዝንባሌ ነው?
4 ብዙ እሥራኤላውያን ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ ይሆንን? እያሉ ሲያመነቱ በነበሩበት ወቅት በነገሩ የተደናገጡት ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለመያዝ ሎሌዎቻቸውን ላኩ። ሎሌዎቹ “እንደዚህ ሰው ማንም እንዲሁ ከቶ አልተናገረም” እያሉ ባዶ እጃቸውን ተመለሱ። ፈሪሳውያኑ ምንም ፍንክች ሳይሉ ሎሌዎቹን “እናንተ ደግሞ ሳታችሁን? ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን? ነገር ግን ሕግ የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” ብለው መለሱላቸው። የሳንሄድሪን (የአይሁድ ሸንጐ) አባል የሆነ ኒቆዲሞስ የተባለ ሰው አንድ ሰው ሳይጠየቅና የሚሰጠው ምላሽ ሳይሰማ በእርሱ ላይ መፍረድ ሕገወጥ እንደሆነ በመግለጽ ተቃወማቸው። ፈሪሳውያን ግን በንቀት ወደሱ ዞር ብለው፦ “አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሳ መርምርና እይ አሉት።”—ዮሐንስ 7:46-52
5 ለአምላክ በተወሰነ ሕዝብ መካከል የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ያደረጉት ለምንድነው? ምክንያቱም የልባቸው ዝንባሌ መጥፎ ስለነበረ ነው። (ማቴዎስ 12:34) ለተራው ሕዝብ የነበራቸው የንቀት አስተያየት ሐሳበ ግትሮች መሆናቸውን አጋልጦባቸዋል። “ከአለቆች ወይስ ከፈሪሳውያን በእርሱ ያመነ አለን?” ማለታቸው መሲሑ እውነተኛ ሊሆን የሚችለው እነሱ ከተቀበሉት ብቻ እንደሆነ የሚያስመስል የትዕቢት አነጋገር ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ የተወለደው መሲሑ እንደሚወለድ በትንቢት አስቀድሞ በተነገረለት ቦታ ማለት በቤተልሔም መሆኑን በቀላሉ መርምረው ሊረዱ ሲችሉ ከገሊላ በመምጣቱ ብቻ ስሙን ሊያጠፉ በመሞከራቸው አጭበርባሪዎች ነበሩ።—ሚክያስ 5:2፤ ማቴዎስ 2:1
6, 7. (ሀ) የሃይማኖት መሪዎቹ ስለ አልዓዛር ትንሣኤ የተሰማቸው እንዴት ነበር? (ለ) የሃይማኖት መሪዎች ጨለማን እንደሚያፈቅሩ ለማጋለጥ ኢየሱስ ምን አለ?
6 እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ለብርሃን የነበራቸው ግትር ተቃውሞ ኢየሱስ አልአዛርን ከሙታን ባስነሳበት ጊዜ በማያሻማ ሁኔታ ይፋ ሆኖአል። ኢየሱስ ፈሪሃ አምላክ ላለው አንድ ሰው እንዲህ ያለ ተአምር ማድረጉ በእርግጥ የይሖዋ ድጋፍ ያለው ለመሆኑ ማስረጃ በሆናቸው ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን ሊታያቸው የቻለው የነሱ ከፍተኛ ሥልጣን ወይም ማዕረግ አደጋ ላይ ሊወድቅ መቻሉ ብቻ ነበር። እንዲህ ተባባሉ፦ “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፣ የሮሜ ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ።” (ዮሐንስ 11:44, 47, 48) ስለዚህ ብርሃኑን ሊያጠፉ የሚችሉ መስሎአቸው ኢየሱስንም ሆነ አልአዛርን ሊገድሉአቸው ተማከሩ።—ዮሐንስ 11:53, 54፤ 12:9, 10
7 ስለዚህ እነዚህ የአምላክ ሕዝብ የሃይማኖት መሪዎች በግትርነታቸው፣ በትዕቢታቸው፣ በኩራታቸው፣ በምክንያተ ቢስነታቸውና በራስ ወዳድነታቸው ምክንያት ከብርሃኑ ራቁ። ኢየሱስ በአገልግሎቱ መጨረሻ ገደማ “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ ወዮላችሁ፤ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ” በማለት ጥፋተኛነታቸውን አጋልጧል።—ማቴዎስ 23:13
ራስ ወዳድነትና ኩራት
8. በናዝሬት የሕዝቡን መጥፎ የልብ ሁኔታ ያጋለጠው ምን ሁኔታ ነበር?
8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን ባጠቃላይ በነበራቸው መጥፎ የልብ ዝንባሌ ምክንያት ብርሃኑን አንቀበልም በማለት የሃይማኖት መሪዎቻቸውን ምሳሌ ተከትለዋል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ኢየሱስ በናዝሬት ከተማ በሚገኝ አንድ ምኩራብ ውስጥ ንግግር እንዲያደርግ ተጋብዞ ነበር። እርሱም ከትንቢተ ኢሳይያስ አንድ ክፍል መርጦ አነበበና አብራራው። መጀመሪያ ላይ የተሰበሰቡት ሰዎች በሙሉ አዳመጡት። ይሁን እንጂ የነሱን ራስ ወዳድነትና እምነት ማጣት የሚያጋልጥ ተመሳሳይ ታሪክ በጠቀሰላቸው ጊዜ በጣም ተቆጡና ሊገድሉት ፈለጉ። (ሉቃስ 4:16-30) ኩራታቸው በሌሎቹ መጥፎ ጠባዮቻቸው ላይ ተጨምሮ ብርሃኑን እንዳይቀበሉ አገዳቸው።
9. የብዙዎቹ የገሊላ ሰዎች የተሳሳተ የልብ ግፊት የተጋለጠው እንዴት ነበር?
9 በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ብዙ ሰዎች በተአምር መግቧል። የዚህ ተአምር የዓይን ምሥክሮች የነበሩ ሰዎች “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው” አሉ። (ዮሐንስ 6:10-14) ኢየሱስ በጀልባ ወደሌላ ቦታ በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ተከተሉት። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ብዙዎቹን እንዲከተሉት የገፋፋቸው ምክንያት ለብርሃኑ ያላቸው ፍቅር አለመሆኑን ያውቅ ነበር። እንዲህ አላቸው፦ “የምትፈልጉኝ እንጀራን ስላበላኋችሁና ስለጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክትን ስላያችሁ አይደለም።” (ዮሐንስ 6:26) ይከተሉት ከነበሩት መካከል ብዙዎቹ ወደ ዓለም ስለተመለሱ የተናገረው ትክክል መሆኑ ተረጋግጦአል። (ዮሐንስ 6:66) “ምን ጥቅም ላገኝበት እችላለሁ” የሚል የስስት ዝንባሌ ስለነበራቸው ብርሃኑ ተጋረደባቸው።
10. አብዛኞቹ አሕዛብ ብርሃኑን የተቀበሉት እንዴት ነበር?
10 ያመኑት አይሁድ ኢየሱስ ከሞተና ከተነሣ በኋላ አይሁድ ብርሃኑን ለሌሎች አይሁዳውያን ማዳረስ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ብርሃኑን የተቀበሉት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስና ሌሎች “የአሕዛብ ብርሃን” በመሆን ያገለገሉ አማኝ አይሁዶች የምሥራቹን ወደ ሌሎች አገሮች ሁሉ አሰራጩ። (ሥራ 13:44-47) አይሁዳውያን ያልሆኑ ብዙ ሰዎች ብርሃኑን ተቀበሉ። ቢሆንም አቀባበላቸው በአጠቃላይ ሲታይ ጳውሎስ “ለአሕዛብ ሞኝነት የሆነውን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” በማለት እንደገለጸው ሆኗል። (1 ቆሮንቶስ 1:22, 23) አይሁድ ያልሆኑ ብዙ ሕዝቦች በአረመኔያዊ አጉል እምነቶች ወይም በዓለማዊ ፍልስፍናዎች ታውረው ስለነበረ ብርሃኑን አልተቀበሉም።—ሥራ 14:8-13፤ 17:32፤ 19:23-28
“ከጨለማ ወደ ብርሃን ተጠሩ”
11, 12. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብርሃኑን በጥሩ ሁኔታ የተቀበሉት እነማን ነበሩ? ዛሬስ እነማን በተመሳሳይ ሁኔታ እየተቀበሉት ነው?
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ባጠቃላይ ሲታይ ጥሩ የተቀባይነት መንፈስ ባይኖርም ቀና ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች “ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን ተጠርተዋል።” (1 ጴጥሮስ 2:9) ከእነዚህ አንዱ የነበረው ሐዋርያው ዮሐንስ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” በማለት ጽፏል። (ዮሐንስ 1:12) እነዚህ ብርሃን አፍቃሪዎች በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀው ወደፊት ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊ መንግሥቱ አብሮ የመግዛት ተስፋ ያላቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆኑ።
12 በዘመናችን ከእነዚህ ቅቡዓን የአምላክ ልጆች የመጨረሻዎቹ ቀሪዎች የሆኑት ተሰብስበው የዳንኤልን ትንቢት በመፈጸም ላይ ናቸው። “ብዙ ሰዎችን ወደ ጽድቅ” እየመለሱ እንደ ከዋክብት ደምቀው በመታየት ላይ ናቸው። (ዳንኤል 12:3) ብርሃናቸው በስፋት እንዲዳረስ በማድረጋቸው ከአራት ሚልዮን የሚበልጡ “ሌሎች በጐች” ወደ እውነት እንዲሳቡና በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲያገኙ አስችለዋል። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ “ሌሎች በጐች”ም በተራቸው ብርሃኑን በዓለም ዙሪያ ያዳርሳሉ። ስለዚህ ይህ ብርሃን ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ ደምቆ በመታየት ላይ ነው። እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዘመናችንም “[ብርሃኑን] ጨለማ አላሸነፈውም።”—ዮሐንስ 1:5
“በአምላክ ዘንድ ጨለማ የለም”
13. ሐዋርያው ዮሐንስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል?
13 ነገር ግን “እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም። ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን። እውነትም አናደርግም” በማለት የሰጠውን የሐዋርያው ዮሐንስን ማስጠንቀቂያ መርሳት የለብንም። (1 ዮሐንስ 1:5, 6) በግልጽ እንደምናየው ክርስቲያኖችም አይሁድ በተጠመዱበት ዓይነት ወጥመድ ሊጠመዱና በስም ብቻ የአምላክ ምሥክሮች ሆነው የጨለማን ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ።
14, 15. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የታዩት ምን የጨለማ ሥራዎች ነበሩ? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
14 እውነትም እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ደርሶ ነበር። በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ አሳሳቢ መከፋፈል ተነስቶ እንደነበረ እናነባለን። (1 ቆሮንቶስ 1:10-17) ሐዋርያው ዮሐንስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እርስበርስ እንዳይጣሉ ማስጠንቀቅ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ያዕቆብም ከድሆች አብልጠው ለሃብታሞች እንዳያዳሉ አንዳንዶችን መምከር አስፈልጎታል። (ያዕቆብ 2:2-4፤ 1 ዮሐንስ 2:9, 10፤ 3 ዮሐንስ 11, 12) በተጨማሪም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጸው ኢየሱስ በትንሹ እስያ የሚገኙ ሰባት ጉባኤዎችን በመረመረበት ጊዜ ክህደት፣ ጣኦትን ማምለክ፣ ብልግናና የሀብት ፍቅርን ጨምሮ ሌሎች የጨለማ ሥራዎች ሾልከው መግባታቸውን ገልጿል። (ራእይ 2:4, 14, 15, 20-23፤ 3:1, 15-17) በእነዚያ የክርስቲያን ጉባኤ የጨቅላነት ዘመኖች አንዳንዶች ስለተወገዱና ሌሎች ደግሞ “በውጭ ወዳለው ጨለማ” ስለተወሰዱ ብርሃንን የተዉት ጥቂቶች አልነበሩም።—ማቴዎስ 25:30፤ ፊልጵስዩስ 3:18፤ ዕብራውያን 2:1፤ 2 ዮሐንስ 8-11
15 እነዚህ ሁሉ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ዘገባዎች የሰይጣን ዓለም ጨለማ ወደ ግለሰብ ክርስቲያኖች አስተሳሰብ ወይም ወደመላው ጉባኤ እንኳን ሳይቀር ሰርጐ ሊገባ የሚችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ያሳያሉ። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ፈጽሞ እንዳይደርስብን ነቅተን መጠበቅ አለብን። ይሁን እንጂ ይህ ሊደርስብን የሚችለው እንዴት ነው?
አዲሱ ባሕርይ
16. ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች ምን ጠንካራ ምክር ሰጠ?
16 ጳውሎስ የኤፌሶንን ክርስቲያኖች ‘በልቦና (የአእምሮ) ጨለማ ውስጥ እንዳይሆኑና ከእግዚአብሔር ሕይወት እንዳይርቁ’ አሳስቧቸዋል። ወደዚያ ጨለማ እንዳይመለሱ ለብርሃኑ የሚገባ የልብ ዝንባሌ መኰትኰት ነበረባቸው። ጳውሎስ “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው (ባሕርይ) አስወግዱ፣ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ። ለእውነትም በሚሆን ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው (ባሕርይ) ልበሱ” ብሏቸዋል።—ኤፌሶን 4:18, 22-24
17. በዛሬው ጊዜ እኛ ወደ ጨለማ ከመመለስ ልንጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
17 እዚህ ላይ ጳውሎስ የመከረው መሠረታዊ ቀዶ ጥገና እንዲያደርጉ ነው። ከዚህ በፊት የራሳችን ክፍል የነበረውን አሮጌ ባሕርይ ቆርጠን ጥለን “አእምሮአችንን የሚያንቀሳቅስ አዲስ የሆነ መንፈስ” ማሳደግ ማለት ነው። ይህን የተናገረውም ገና ፍላጎት ላሳዩ አዳዲሶች ሳይሆን ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ነበር። የባሕርይ ለውጥ ማድረግ በጥምቀት አያቆምም። መቀጠል ያለበት ሂደት ነው። አዲሱን ባሕርይ መኰትኰታችንን ካቆምን አሮጌው ባሕርይ ከትዕቢቱ፣ ከዕብሪቱና ከወራዳነቱ ጋር እንደገና ማገርሸቱ አይቀርም። (ዘፍጥረት 8:21፤ ሮሜ 7:21-25) ይህም ወደ ጨለማው ሥራ ወደ መመለስ ሊመራ ይችላል።
“በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን”
18, 19. ኢየሱስና ጳውሎስ “የብርሃን ልጆች” የሚታወቁበትን መንገድ የገለጹት እንዴት ነው?
18 አምላክ ካልፈረደልን የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደማንችል አስታውስ። ይህ የአምላክ ፍርድ ደግሞ ለብርሃኑ ባለን የፍቅር መጠን ላይ የተመካ ነው። ኢየሱስም ይህን ሲያመለክት እንዲህ ብሎአል፦ “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፣ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም። እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።—ዮሐንስ 3:19-21
19 ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች “የብርሃኑ ፍሬ በበጐነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና . . . እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” በማለት ስለጻፈ ከላይ የተጠቀሰውን የኢየሱስ ሐሳብ ደግፏል። (ኤፌሶን 5:8, 9) ስለዚህ ሥራችን የብርሃን ልጆች ወይም የጨለማ ልጆች መሆናችንን ያሳያል። ይሁን እንጂ ትክክለኛ ሥራ ሊፈልቅ የሚችለው ከጥሩ ልብ ብቻ ነው። ልባችንን መጠበቅ የባሕርይ ለውጥ ማድረጋችንን መቀጠልና አእምሮአችንን ስለሚያንቀሳቅሰው መንፈስም መጠንቀቅ የሚገባን በዚህ ምክንያት ነው።—ምሳሌ 4:23
20, 21. (ሀ) በክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ የተወለዱ ልጆችን የሚያጋጥማቸው ምን ትግል አለ? (ለ) ከክርስቲያን ወላጆች የተወለዱ ልጆች ሁሉ የሚያጋጥሟቸው ምን ውሣኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች ናቸው?
20 ይህ ጉዳይ በአንዳንድ ረገድ ከይሖዋ ውስን ምሥክሮች ለተወለዱ ልጆች ከፍተኛ ትግል የሚጠይቅባቸው ጉዳይ ሆኖአል። ለምን? በአንድ በኩል እነዚህ ልጆች ግሩም በረከት አግኝተዋል። ምክንያቱም አንድ ሰው ከሕፃንነቱ ጀምሮ እውነትን ያወቀ ከሆነ በሰይጣን ዓለም ጨለማ ውስጥ መኖር ምን ማለት እንደሆነ በራሱ ተሞክሮ ማየት አያስፈልገውም ማለት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) በሌላ በኩል ግን እንዲህ ባለው ሁኔታ ያደጉ አንዳንድ ልጆች እውነትን በዘፈቀደ ይይዙትና ብርሃንን ከልብ ማፍቀርን ሳይማሩ ይቀራሉ። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ የአብዛኞቹ አይሁድ ሁኔታ እንዲህ ያለ ነበር። በይሖዋ ውስን ሕዝብ መካከል ስላደጉ መጠነኛ የሆነ የእውነት እውቀት ነበራቸው። ይሁን እንጂ ያ እውነት ወደ ልባቸው ሥር ሰዶ አልገባም ነበር።—ማቴዎስ 15:8, 9
21 ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በብርሃኑ ውስጥ የማሳደግ ኃላፊነት በአምላክ ፊት አለባቸው። (ዘዳግም 6:4-9፤ ኤፌሶን 6:4) ቢሆንም ልጁ ራሱ ከጨለማ ይበልጥ ብርሃንን ማፍቀር መቻል ይኖርበታል። የእውነትን ብርሃን የራሱ ሊያደርገው ይገባል። እያደገ በሄደ ቁጥር የሰይጣን ዓለም አንዳንድ ገጽታዎች ማራኪ መስለው ሊታዩት ይችላሉ። የእኩዮቹ የግድየለሽነት ወይም ከኃላፊነት ነፃ የሆነ አኗኗር አስደሳች መስሎ ሊታየው ይችላል። በትምህርት ቤት የሚሰጠው ሁሉን ነገር እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ትምህርት ሊያሳስተው ይችላል። ይሁን እንጂ ከብርሃኑ ውጭ የሆነችውን “ምድር ጨለማ እንደሸፈናት” ፈጽሞ መርሳት የለበትም። (ኢሳይያስ 60:2) ይህ የጨለመ ዓለም የኋላ ኋላ የሚሰጠው ምንም ጥሩ ነገር አይኖረውም።—1 ዮሐንስ 2:15-17
22. ይሖዋ ወደ ብርሃን የሚመጡትን በአሁኑ ጊዜ የሚባርካቸው እንዴት ነው? ለወደፊቱስ የሚባርካቸው እንዴት ነው?
22 ንጉሥ ዳዊት እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን፤ ምህረትህን [ፍቅራዊ ደግነትህን (አዓት)] በሚያውቁህ ላይ . . . ዘርጋ።” (መዝሙር 36:9, 10) ብርሃንን የሚያፈቅሩ ሰዎች ይሖዋን ወደማወቅ ይደርሳሉ። ይህም ሕይወትን ያሰጣቸዋል። (ዮሐንስ 17:3) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱ ይደግፋቸዋል። ታላቁ መከራ በሚፈነዳበት ጊዜ ደግሞ ወደ አዲሲቱ ዓለም ያስገባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ የሰይጣንን ዓለም ጨለማ ከሸሸን ይህ ሁሉ ይፈጸምልናል። በአዲሲቱ ዓለም የሰው ዘር በገነት ውስጥ ፍጹም የሆነ ሕይወት ያገኛል። (ራእይ 21:3-5) በዚያን ጊዜ የሚፈረድላቸው ሁሉ በይሖዋ ብርሃን ሙቀት ለዘላለም የመደሰት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። እንዴት ዓይነት ክብራማ ተስፋ ነው! ይህስ በአሁኑ ጊዜ “የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንድንለብስ” የሚገፋፋን እንዴት ያለ ጠንካራ ምክንያት ነው!—ሮሜ 13:12
ታስታውሳለህን?
◻ በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ብዙ አይሁድ ብርሃኑን አንቀበልም ያሉት ለምን ነበር?
◻ ብርሃኑ በዘመናችን እስከምን ደረጃ ድረስ እያበራ ነው?
◻ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ምሳሌዎች ራስ ወዳድነትንና ኩራትን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጡናል?
◻ በብርሃኑ ፀንተን ለመኖር ከፈለግን ምን ያስፈልገናል?
◻ ብርሃኑን የሚያፈቅሩ ሰዎች ምን በረከቶች ይጠብቋቸዋል?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ አይሁዶች ለብርሃኑ እሺ የሚል መልስ አልሰጡም
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባለፉት ዘመናት ደቀ መዛሙርት በማድረግ ብርሃኑ እንዲበራ የተለያዩ ዘዴዎች በሥራ ላይ ውለዋል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“አሮጌውን ሰው አስወግዱ፤ አዲሱን ሰው ልበሱ”