የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 8/15 ገጽ 29-31
  • የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለህ ትክዳለህ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለህ ትክዳለህ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መካድ ገዳይ የሆነበት ምክንያት
  • ራሳችሁን አጠናክሩ!
  • አምኖ መቀበልና እርምጃ መውሰድ
  • የሰው ልጅ ከኃጢአት ቀንበር የሚላቀቅበት መንገድ ይኖራልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ሕይወትህን እየለወጠው ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
  • የትም ብትሆን የይሖዋን ድምፅ ስማ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 8/15 ገጽ 29-31

የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለህ ትክዳለህ?

“እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።”​—ሮሜ 7:21-23

ሐዋርያው ጳውሎስ ከላይ ያለውን አምኖ ለመቀበል ትህትናን ጠይቆበታል። ሆኖም ይህን በማድረጉ የአለፍጽምና ዝንባሌዎቹ እንዳያሸንፉት ለመከላከል ርዳታ አግኝቷል።

ዛሬ ያሉት ክርስቲያኖች ሁኔታም እንደዚሁ ነው። ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እውቀት ባወቅንበት ጊዜ ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር በመስማማት በአኗኗራችን አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን አደረግን። ቢሆንም የኃጢአት ዝንባሌዎች ገና ቀርተዋል። ምክንያቱም “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነውና።” (ዘፍጥረት 8:21) በእኛ ላይ ተጽዕኖ የሚያመጡ ለየት ያሉ ዝንባሌዎች እንዳሉብን ለራሳችን አምነን ለመቀበል ቅኖች ነንን? ወይስ ‘እነዚህ ሌሎችን እንጂ እኔን የሚመለከቱ ችግሮች አይደሉም’ ብለን በመደምደም ይህንን እንክዳለን?

እንደዚህ ያለው ራስን የማታለል ዝንባሌ አደገኛ ሊሆን ይችላል። አንድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምሳሌ የኃጢአት ዝንባሌዎቻችንን አምኖ የመቀበልንና የመቆጣጠርን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል።

መካድ ገዳይ የሆነበት ምክንያት

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ብዙ ከተሞች በግንብ የተጠበቁ ነበሩ። ብዙ ጊዜ ከእንጨት የሚሠሩት በሮች ከከተማዋ የውስጠኛ ግንብ ጋር ሲነፃፀሩ በቀላሉ ሊሠበሩ የሚችሉ ክፍሎች ነበሩ። ስለዚህም በከፍተኛ ኃይል ይጠበቁ ነበር። ነዋሪዎቹ በሰላሙ ጊዜ ለትራፊክ አስፈላጊ የሆኑ ብዙ በሮችን ይሠሩ ነበር። ብዙውን ጊዜም የእንጨት በሮች የእሳት አደጋን ለመቋቋም እንዲችሉ በብረት ይሸፈኑ ነበር። ጠባቂዎች የሚመጣውን ጠላት ከሩቁ ለማየት ይችሉ ዘንድ በግድግዳዎቹ ላይ ከፍ ያሉ የመጠበቂያ ግንቦች ይሠሩ ነበር።

እስቲ አስበው፦ የከተማዋ ነዋሪዎች የከተማዋን በሮች የመሰበር ዕድል ቢክዱና በቂ ጥበቃ ሳያደርጉ ቢቀሩ ምን ነገር ይደርሳል? የጠላት ወታደሮች ወደ ከተማዋ በቀላሉ ሊገቡና ሊያሸንፉ ይችላሉ።

ይህ ነገር በእኛም ላይ ሊሠራ ይችላል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ያለብንን ድክመት ያውቃል። “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፣ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።” (ዕብራውያን 4:13) ሰይጣንም ቢሆን በእኛ ላይ ያሉትን የኃጢአት ዝንባሌዎች ማለትም እውነትን የማጣመም፣ ለቁጣ የመቸኮል፣ የጾታ ብልግና ፍላጎት፣ የፍቅረ ነዋይ፣ የኩራት ወይም ሌሎች ዝንባሌዎችን ይመለከታል። የኃጢአት ዝንባሌዎች እንዳሉብን የምንክድ ከሆነ ሰይጣን በእምነታችን ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ይበልጥ የተጋለጥን እንሆናለን። (1 ጴጥሮስ 5:8) የተሳሳቱ ምኞቶች ከተራ ዝንባሌዎች አልፈው ኃጢአትን ከወለዱ ልንሸነፍ እንችላለን። (ያዕቆብ 1:14, 15) ያሉብንን ማናቸውንም ዓይነት ‘የእንጨት በሮች’ በቅንነት አምነን በመቀበል እንደ ጳውሎስ መሆን ያስፈልገናል።

ራሳችሁን አጠናክሩ!

የተሳሳቱ ዝንባሌዎች መኖራቸውን አውቆ ምንም እርምጃ አለመውሰዱ ዋጋ አይኖረውም። ይህ ነገር ራሱን በመስታወት ተመልክቶ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ቦታዎች እንዳሉ ከተረዳ በኋላ አስፈላጊ የሆነውን ማስተካከያ ሳያደርግ ዘወር ብሎ እንደሚሄድ ሰው መሆን ነው። (ያዕቆብ 1:23-25) አዎን፣ ራሳችንን በኃጢአት ዝንባሌዎች ከመሸነፍ ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ያስፈልገናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ትንንሽ ከተሞች ወይም “ጥገኛ ከተሞች” ብዙውን ጊዜ ግንብ አልነበራቸውም። (ዘኁልቁ 21:25, 32፤ መሳፍንት 1:27፤ 1 ዜና መዋዕል 18:1፤ ኤርምያስ 49:2) የእነዚህ ከተሞች ነዋሪዎች ድንገተኛ የጠላት ጥቃት ቢመጣባቸው በግንብ ወደታጠረው ከተማ ለመሸሽ ይችሉ ነበር። የተመሸጉት ወይም ጠንካራ ግንብ ያላቸው ከተሞች በአካባቢው ላሉ ሰዎች ሁሉ እንደ መሸሸጊያ ሆነው ያገለግሉ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክን እንደ ግንብ፣ እንደ መሸሸጊያ ይኸውም መጠለያ ለማግኘት ልንሮጥና ልንሸሸግበት እንደሚገባ ግድግዳ አድርጎ ይገልጸዋል። (ምሳሌ 18:10፤ ዘካርያስ 2:4, 5) ስለዚህ ይሖዋ የአገልጋዮቹ ዋነኛ መከላከያ ነው። (1 ተሰሎንቄ 5:17) ሌላው የእርዳታ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በአምላክ ቃል በመጠቀም ደካማ የሆንባቸውን ክልሎች በተመለከተ ልዩ ጥናት ብናደርግ እንጠቀማለን። በተጨማሪም ከእኛ የግል ‘የእንጨት በሮች’ ሁኔታ ጋር ግንኙነት ያላቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ርዕሰ ትምህርቶች በተደጋጋሚ ለመመርመር ጊዜ ልንመድብ እንችላለን።

እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ ላይ እንደሚቆም ጠባቂ ጠላትን ከሩቁ ለመመልከትና እርምጃ ለመውሰድ እንችላለን። እንዴት? ፈተና ወይም ተጽዕኖ እንዲደርስብን ከሚያደርጉ ሁኔታዎች በመራቅ ነው። ለምሳሌ ያህል የአልኮል መጠጦችን በመጠኑ ብቻ ለመጠጣት ጥረት የሚያደርግ አንድ ሰው እነዚህ መጠጦች ከሚዘወተሩባቸው ወይም ከሚበረታቱባቸው ቦታዎች መራቅ ሊመርጥ ይችላል።

ይህ ሁሉ ጥረትን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ የአለፍጽምናን ዝንባሌዎች ለመቋቋም ሰውነቱን ‘መጎሰም’ አስፈልጎት ከነበረ እኛስ ብንሆን ጥረት ማድረግ አያስፈልገንምን? ስለ ኃጢአት ዝንባሌዎቻችን የምናደርገው እንደዚህ ያለው ንቃት የተሞላበት ትኩረት የሐዋርያው ጴጥሮስን መመሪያ እየተከተልን መሆናችንን የሚያንፀባርቅ ነው። “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ።”​—1 ቆሮንቶስ 9:27፤ 2 ጴጥሮስ 3:14

አምኖ መቀበልና እርምጃ መውሰድ

ጥረት ብታደርግም ሁሉም የአለፍጽምና ዝንባሌዎችህ ሊጠፉ ባለመቻላቸው ተስፋ አትቁረጥ። ፍጹሞች እስካልሆንን ድረስ በጳውሎስ ላይ እንደታየው የተሳሳቱ ዝንባሌዎች በተወሰነ መጠን መኖራቸው አይቀርም። ሆኖም እነዚህን ለማሸነፍና ኃጢአትን እንዳይወልዱ ለማድረግ ጥረታችንን መቀጠል ያስፈልገናል።

ይሁን እንጂ የአለፍጽምናን ሁኔታ በመቀበልና እርሱን እንዲቀጥል በመፍቀድ መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ ንቁ ሁን። ይህ ሁኔታ በደረቱ ውስጥ ደካማ ልብ ባለው ሰው ምሳሌ ሊገለጽ ይችላል። ይህ ሰው በተቻለው መጠን ልቡን በጥሩ ሁኔታ ለመጠበቅ በመሞከር ተጨባጩን ሁኔታ መቀበል ይኖርበታል። ቃል በቃል ልቡ ደካማ ስለሆነ ሁሉንም ገደቦች ትቶ እንደፈለገኝ መኖር እችላለሁ ብሎ አያስብም።

ስለዚህ ኃይል ልናገኝ የምንችለው ዓይናችንን ጨፍነን የኃጢአት ዝንባሌዎችን በመካድ ሳይሆን እነዚህ ዝንባሌዎች እንዳሉብን አምነን በመቀበልና እነርሱን ለማሸነፍ እርምጃ በመውሰድ ነው። ከሆነ በቀላሉ ልትፈተንባቸውና ግፊት ሊያመጡብህ የሚችሉትን አካባቢዎች ለራስህና ለይሖዋ አምነህ ለመግለጽ አትፍራ። ይህን በማድረግህ ራስህን ጠላህ ወይም ይሖዋ ለአንተ ያለው ፍቅር ቀዘቀዘ ማለት አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሞገሱን ለማግኘት ከልብህ በመጨነቅ ወደ አምላክ ስትቀርብ እርሱም የበለጠ ወደ አንተ ይቀርባል።​—ያዕቆብ 4:8

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ የመጊዶ ሥዕል የጥንታዊ ከተሞችን የተመሸጉ በሮችና የመከላከያ ግንቦች ያሳያል

[ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ