ነገሮች በእርግጥ ጥሩ መልክ እየያዙ ነውን?
“የምሥራቁና የምዕራቡ ግንኙነት ይበልጥ እየጨመረ ሲሄድ [የበርሊን] ግንብ የበለጠ ብዙ መተላለፊያ ቀዳዳዎች እየተከፈቱለት ሊሄድ ይችላል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ከመፍረሱ በፊት ብዙ ዓመታት ወይም ብዙ ትውልዶች ሊያልፉ ይችላሉ። ሁለቱ ጀርመኖች እንደገና በፍጹም አንድ ሊሆኑ አይችሉም።” ይህንን የጻፈው መጋቢት 1989 የወጣ አንድ ዝነኛ የሆነ የአሜሪካ የዜና መጽሔት ነው።
ሆኖም ለትውልዶች ይቅርና ለዓመታትም እንኳ ሳይቆይ ከ250 ከሚያንሱ ቀኖች በኋላ ግንቡ መፈራረስ ጀመረ። በሣምንታት ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ፍርስራሾቹ አሁን ወደ ቅርሳ ቅርስነት ደረጃ ዝቅ በማለት በመላው ዓለም የቢሮ ጠረጴዛዎች ጌጥ ሆነዋል።
በከፍተኛ ደረጃ ዝጎ የነበረው የብረት መጋረጃ ከረጅም ጊዜ በኋላ ዓለም አቀፉ ሰላምና ደኅንነት እየቀረበ ለመሆኑ ተስፋዎችን በመስጠት አሁን በመጨረሻ ተከፍቷል። በመካከለኛው ምሥራቅ የፈነዳው የባሕረ ሰላጤው ጦርነትም እንኳ በምዕራቡና በምሥራቁ መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው ጠላትነት ያለፈ ነገር የመሆኑንና አዲስ የዓለም ሥርዓት እየመጣ የመሆኑን ተስፋ አላጨለመውም።
አዲስ ስፋት መጨመር
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አውሮፓን አንድ ለማድረግ እንቅስቃሴ በግልጽ ሲካሄድ ቆይቷል። በ1951 የምዕራብ አውሮፓ አገሮች የአውሮፓን የከሰልና የብረት ማኅበረሰብ ፈጠሩ። ከዚያም ቀጥሎ በ1957 የአውሮፓን የጋራ ገበያ ማኅበር አቋቋሙ። በ1987 የዚህ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ (አሁን 342 ሚልዮን አባላት ያሉት ሆኖአል) 12 አባል አገሮች በ1992 አጠቃላይ የሆነ የኤኮኖሚ አንድነት ለመፍጠር ግብ አድርገዋል። በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ፖለቲካዊ አንድነት ለመፍጠር የሚቻልም መስሎ ይታያል። ይህ በአውሮፓ ውስጥ ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ከነበረው በደም የተበላሸ ታሪክ በተለየ እንዴት ያለ እፎይታን የሚያመጣ ለውጥ ነው!
ይሁን እንጂ በቅርቡ ከተከሰቱት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አንጻር ሲታይ በ1912 ከፍተኛ የሆነ ትርጉም በመያዝ ላይ ይገኛል። በፊት ኮሚኒስት የነበሩ ብዛት ያላቸው የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች በመጨረሻው አንድ በምትሆነው አውሮፓ ውስጥ ይጨመራሉ የሚል ግምት አለ።
መለኮታዊ ድጋፍ አለውን?
አንዳንድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የክርስቲያን ገለልተኝነትን ሥርዓት ወደ ጎን በመተው በምሥራቅ አውሮፓ ለብዙ አሥርተ ዓመታት የነበረው የሃይማኖታዊ ጭቆና በፖለቲካ ውስጥ አስገድዶ እንዲያስገባቸው ፈቅደውለታል። ፍራንክፈርተር አልገማይነ ሳይቱንግ የተባለው የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ በዚህ ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ እንዲህ ይላል፦ “በምሥራቅ ለውጦችን ለማምጣት ክርስቲያኖች ያበረከቱት አስተዋጽዎ የማያከራክር ነው።” ጨምሮም “ያደረጉትም ተሳትፎ በእርግጥ የሚናቅ አይደለም” ብሏል። ይህንንም እንደሚከተለው በማለት በዝርዝር ይገልጸዋል፦ “ለምሳሌ ያህል በፖላንድ ሃይማኖት ራሱን ከሕዝቡ ጋር በማስተባበሩ ቤተክርስቲያን የገዥው ፓርቲ ኃይለኛ ተቃዋሚ ሆና ቆይታለች። በጂዲአር [በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን] ቤተክርስቲያን ለተቃዋሚዎች የሚሆን ነጻ ቦታ አዘጋጅታ ነበር፤ እንዲሁም የአብያተክርስቲያናት ሕንፃዎችን ለድርጅታዊ ዓላማዎች እንዲጠቀሙበት ፈቅዳለች። በቺኮዝሎቫኪያ ክርስቲያኖችና ዴሞክራቶች በእስር ቤት ተገኝተው ከተዋወቁ በኋላ ኃይሎቻቸውን በአንድ ላይ አስተባብረዋል።” “አብያተ ክርስቲያናት የቻኦቼስኮ ታማኝ አገልጋዮች” በነበሩባት በሮማኒያም ቢሆን ሕዝባዊ አመጹን የቀሰቀሰው ነገር ቄስ ላስሎ ቶኬስን ለማሰር የተደረገው ዛቻ ነበር።
በዚህ ጉዳይ ቫቲካንም ተሳትፋለች። ታህሣስ 1989 የወጣው የታይም መጽሔት እንዲህ በማለት አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር፦ “ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ምሥራቅ አውሮፓን ያጥለቀለቀው ነፃነት ወዲያውኑ እንዲመጣ የረዳው የጎርባቼቭ ለቀቅ የማድረግ ፖሊሲ ቢሆንም ዮሐንስ ጳውሎስም ለረጅም ጊዜ ላደረጉት አስተዋጽዎ ምስጋና ይገባቸዋል። . . . በ1980ዎቹ ያደረጓቸው ንግግሮች ከአትላንቲክ እስከ ኡራል በክርስቲያን እምነት የምትመራ አንድ የተባበረች አውሮፓ የሚለውን ጽንሰ አሳብ የሚያጠናክሩ ነበሩ።” በዚህም መሠረት በተለይ በሚያዝያ 1990 ቼኮዝሎቫኪያን በጎበኙበት ወቅት ጳጳሱ ጉብኝታቸው በምሥራቁና በምዕራቡ አዳዲስ በሮችን እንደሚከፍት ያላቸውን ተስፋ ገልጸው ነበር። “በክርስቲያን ሥሮች ላይ የተመሠረተች አንድ የተባበረች አውሮፓ” እንድትፈጠር ያላቸውን ሕልም እውን ለማድረግም የአውሮፓ ጳጳሳት ሲኖዶስ አንድ ዕቅድ እንዲነድፍ መታቀዱንም ገልጸዋል።
በተባበረችው አውሮፓ ምስል ውስጥ አንድ የሆነችው ጀርመን ሙሉ በሙሉ አንድ ለምትሆነው አውሮፓ እንዲያውም ወደፊት አንድ ለሚሆነው ዓለም ቀዳሚ ምሳሌ ልትሆን አትችልምን? በዚህ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ተሳትፎ መኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች እየተፈጸሙ መሆናቸውን አያመለክትምን? በአሁኑ ጊዜ በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ያሉት ቄሶች በአንድ ሰላምንና አስተማማኝ ሁኔታን ለማምጣት በሚደረግ መዋቅር ውስጥ አብረው እየሠሩ መሆናቸው የተረጋገጠ በመሆኑ ይህ በቅርቡ እውን እንደሚሆን ልንጠብቅ አንችልምን? እስቲ እንመልከት።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
በሌፕዚግ የሚገኘው የኒኮላይ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን—በጀርመን ውስጥ ለተደረገው ፖለቲካዊ አመጽ ምሳሌ ነው
የአውሮፓ የጋራ ገበያ አባል አገሮች