የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 9/15 ገጽ 24-27
  • ለመሰብሰብ የደረሰ ሰብል የያዙ መስኰች በብራዚል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለመሰብሰብ የደረሰ ሰብል የያዙ መስኰች በብራዚል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • አቅኚዎች በመሰብሰቡ ሥራ ይካፈላሉ
  • የካህናት ተጽዕኖ አዝመራ የመሰብሰብ ሥራውን እየነካው ነው
  • የቀጠለ ጥረት በረከት አምጥቷል
  • ሕይወቶች ተለውጠዋል
  • በመሰብሰቡ ሥራ ሙሉ በሙሉ መካፈል
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 9/15 ገጽ 24-27

ለመሰብሰብ የደረሰ ሰብል የያዙ መስኰች በብራዚል

“ዓይናችሁን አንሱ አዝመራውም አሁን እንደነጣ እርሻውን ተመልከቱ። የሚያጭድ ደመወዝን ይቀበላል። የሚዘራና የሚያጭድም አብረው ደስ እንዲላቸው ለዘላለም ሕይወት ፍሬን ይሰበስባል።” (ዮሐንስ 4:35, 36) በሰፊው የደቡብ አሜሪካ የብራዚል አገር ላይ እነዚያ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢታዊ ቃላት ዛሬም እውነት ናቸው።

በብራዚል የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለአያሌ ዓመታት መልካም ጭማሪ ሲያገኙ ቆይተዋል። በሚያዝያ 1991 ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር 308,973 ሲሆን 401,574 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርተዋል። በመጋቢት 1991 የአዝመራ መሰብሰብ ሥራ የጀመረው የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር በጠቅላላው 897,739 ሰዎች ተሰብስበው ነበር።

እንዲህ ዓይነት መልካም ውጤት የተገኘ ቢሆንም የእርሻው (የመስኩ) ከፊል ገና ስላልተሰበሰበ የሚሰበሰብበትን ጊዜ ይጠብቃል። ከአምስት ሚልዮን በላይ የሆነ ሕዝብ የሚኖረው የይሖዋ ምሥክሮች ጥቂት የስብከት ሥራ ባካሄዱበት ወይም ምንም የስብከት ሥራ ባላካሄዱበት የብራዚል አካባቢዎች ነው። የመሰብሰብን ሥራ ወደነዚህ አካባቢዎችም ለማዳረስ ምን እየተደረገ ነው?

አቅኚዎች በመሰብሰቡ ሥራ ይካፈላሉ

በቅርቡ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የብራዚል የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ማለትም 100 ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎችና 97 የዘወትር አቅኚዎች ወደ 97 ከተሞች ልኳል። ከእነዚህ አብዛኞቹ የሚገኙት ሕዝብ በሚበዛባቸው የአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍሎች ነው። ከተለያዩ ጉባኤዎች የሆኑ የመንግሥት አስፋፊዎችም በእነዚህ አካባቢዎች ለአጫጭር ጊዜያት ለመሥራት ፈቃደኞች ሆነዋል። ሊቋቋሟቸው የሚገቡ መሰናክሎች ቢኖሩም ውጤቶቹ አስደሳች ሆነዋል።

ለምሳሌ ያህል በሚነስ ጌራይስ ግዛት በሚገኘው በሳኦ ጆዋ ዳ ፖንቴ አቅኚዎቹ አንድ የአካባቢው ትምህርት ቤት የሃይማኖት መምህር አነጋገሩ። መልእክቱን ካዳመጠ በኋላ ለሃይማኖት ትምህርት ክፍሉ የሚሆን ከወጣትነትህ የበለጠውን ማግኘት የተሰኘውን መጽሐፍ 50 ቅጂዎች አዘዘ። አቅኚዎቹ ተሰናብተው ሲሄዱ አንድ ሌላ መምህር “እዚህ መልካም ሥራ እየሠራችሁ ስለሆነ መሄድ አልነበረባችሁም። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ማብራሪያ ልትሰጡ የምትችሉት እናንተ ብቻ ናችሁ” አላቸው።

በዚህ መልካም ሥራ የተደሰተው ሁሉም ሰው አልነበረም። ለምሳሌ ያህል ዳይ አሪዮዴ ሞንቴስ ክላሎስ በተሰኘው የአካባቢው ጋዜጣ በፊተኛው ገጽ ላይ “ለዓመፅና (ለሃይማኖታዊ) አድልዎ ቅስቀሳ ያደረገ ቄስ ተከሰሰ” በሚል ርዕስ የወጣውን ደብዳቤ ተመልከት። ደብዳቤው እንዲህ አለ፦ “በቤተክርስቲያን ውስጥ (ቄሱ) ለምእመናኑ በቂ የሆነ የካቶሊካዊና ክርስቲያናዊ የወንጌል መመሪያ ሳይሰጥ ሌላ ኑፋቄና ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ሰዎችን የማውገዝ ልማድ አለው። በከተማው ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች አገልጋዮቹ ካቶሊኰችን በመጥፎ ሁኔታ የማያስቸግሩ ሆነው ሳሉ በቅዳሴው ላይ በኃይል ነቀፋቸው።” የአንቀጹ ጸሐፊ የሃይማኖት ሊቅ (ቲኦሎጂያን) ሲሆን እንደ ቄሱ ዓይነት ጠላትነት ባለማሳየት በአቅኚዎቹ የቀረበ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር ላይ ተገኝቷል። ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ሰዎችንም ይዞ መጥቷል። ሁሉም በስብሰባው ተደስተዋል።

አራት ወንድሞች ከፎርታሌዛ በአይሮፕላን ከየብስ 250 ማይል ርቃ ወደምትገኝ ፈርናንዶ ዴ ሮንዛ ደሴት ተጓዙ። የደሴቷ 1,500 ነዋሪዎች ከ15 ዓመታት ከሚበልጥ ጊዜ ወዲህ ጥሩ ምሥክርነት አግኝተው አያውቁም። በ10 ቀናት ውስጥ ወንድሞች 50 መጻሕፍትን፣ 245 መጽሔቶችንና ብሮሹሮችን አደሉ፤ 15 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም አስጀመሩ። የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የደረሰው ወንድሞች እዚያ ከደረሱ በኋላ ነበርና አሥራ ሁለት ሰዎች በበዓሉ ላይ ተገኙ። አቅኚዎቹ ከይሖዋ እርዳታ ጋር ሥራው በቅርቡ ጸንቶ እንደሚመሠረት ተስፋ ያደርጋሉ። አንዳንድ ወንድሞችም ወደዚያ ደሴት ስለመዛወር እያሰቡ ነው።

የካህናት ተጽዕኖ አዝመራ የመሰብሰብ ሥራውን እየነካው ነው

በሪዮ ዴ ጃኔሮ ውስጥ የሚገኘው የአርፖዶር ጉባኤ የመንግሥት አስፋፊዎች ቡድን 125 ማይል ያህል ርቀው በሚገኙ የሚናስገራይስ ግዛት አያሌ ከተሞች ውስጥ ሁለት ሣምንት በስብከት ለማሳለፍ በፈቃደኝነት ዘመቱ። የአካባቢው ሕዝብ በጣም እንግዳ ተቀባዮችና ደጐች ሆነው ሲያገኙአቸው ተደሰቱ። ወንዶቹ አምላክ ወይም ስሙ ይሖዋ በተጠቀሰ ቁጥር ባርኔጣቸውን የማንሣት ልማድ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ለአምላክ ካላቸው አክብሮት የተነሣ ካህናት በቀላሉ ሊያግባቡአቸው ይችሉ ነበር።

በአንድ ከተማ ቄሱ የይሖዋ ምሥክሮችን እንዳያዳምጡ ወይም ሊያደርጉት አስበው ወደነበረው ትልቅ ስብሰባ እንዳይሄዱ ሕዝቡን ነገራቸው፤ እንደዚሁም ስብሰባው በሚካሄድበት ሰዓት ላይ ቅዳሴ ለማካሄድ ቀጠረ። የቅዳሴውም ማስታወቂያ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በድምጽ ማጉያ ሙሉ ተሠራጨ ይህን ያህል ጥረት ቢያደርግም ከጐብኚዎች በተጨማሪ 29 የአካባቢው ነዋሪዎች ስብሰባውን ተካፈሉ።

የአጐራባቿ ከተማ ደግሞ ፈጽሞ የተለየች ነበረች። እዚያ ካህኑ (ቄሱ) ለሕዝቡ የይሖዋ ምሥክሮች ሊያነጋግሯቸው ሲመጡ እንዲያዳምጧቸው ነገራቸው። ውጤቱም በመጀመሪያው ስብሰባ ላይ 168 ሰዎች እንዲካፈሉ አድርጓል። በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች መታሰቢያውን እንዴት እንደሚያከብሩ በጥንቃቄ እንዲመለከቱ ነገራቸው። ምክንያቱንም ሲነግራቸው “በትክክለኛው መንገድ ነው የሚያከብሩት” አላቸው። በዚያ አካባቢ በተደረገው የሁለት ሳምንት የምሥክርነት ሥራ 1,014 መጻሕፍት፣ 1,052 መጽሔቶችና ብሮሹሮች ታድለዋል።

የቀጠለ ጥረት በረከት አምጥቷል

ከአንድ ወር በኋላ 34 የመንግሥት አስፋፊዎች በመጀመሪያ ጉብኝታቸው ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጀመሩላቸውን ሰዎች ለመንከባከብ ተመለሱ። የመሪነቱን ሥራ የወሰደው ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “ፍላጎት ያሳዩት ሰዎች በምስጋናና ዓይኖቻቸው የደስታ እንባ አቅርረው ሲቀበሉን ማየት በጣም ስሜት የሚነካ ነበር።” አንዲት እህት እሷና ሌሎች ምሥክሮች ምሳ እየተጋበዙ እንዳሉ አንዲት ሴት ቀርባ “እንባ ባቀረሩ ዓይኖች መጥተን ከሷ ጋር እንድናጠና ለመነችን” በማለት ታስታውሳለች። አንዲት ሌላ ወይዘሮ እዚያ በነበሩበት ወቅት በሳምንት ሦስት ጊዜ ታጠና ነበር። ለእያንዳንዱ የጥናት ጊዜም ለጥናቷ ተዘጋጅታ አስጠኚዋን ትጠብቅ ነበር። ወይዘሮዋ ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ይሖዋ መጸለይ እንደጀመረች ትናገራለች። ጨምራም “ሁልጊዜ በልቤ ስጠባበቀው የነበረው ይህ ነው” ትላለች።

በኋላ ሁለት አቅኚዎች በዚያ አካባቢ ለታየው ፍላጎት እንክብካቤ እንዲያደርጉ ተመደቡ። እንደመጀመሪያው ምዕተ ዓመት እዘአ ሁሉ “ለዘላለም ሕይወት [ትክክለኛ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ (አዓት)] አመኑ” (ሥራ 13:48) የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ኢየሱስ እንደመሠከረላት ሳምራዊት ሴት እነዚህም የተማሩትን ለሌሎች መናገር ጀምረዋል። (ዮሐንስ 4:5-30) ዛሬ ሁለቱ አቅኚዎች ከእነሱ ጋር የሚያገለግሉ ስድስት ሰዎችና በሳምንታዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ የሚገኙ በአማካይ ሃያ ሰዎች አሏቸው።

በዚህ ልዩ ሥራ ስሜታቸው የተነቃቃው 29 የአርፖዶር ጉባኤ አስፋፊዎች ሙቱም በምትባል 300 ማይል ያህል ርቀት ላይ ወደምትገኝ ከተማ ለመስበክ ሄዱ። “አቀባበሉ በእርግጥም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ነበር” ይላል ቡድኑን የሚመራው ሽማግሌ። “ብዙ ሰዎች በጥሞናና በፍላጎት ከማዳመጣቸው የተነሣ 170 ጥናቶች ተጀመሩ። ከእነሱ ብዙዎቹ እንደሚቀጥሉም ይሰማናል።” በሁለት ሣምንት ውስጥ አስፋፊዎቹ እያንዳንዳቸው በአማካይ 90 ሰዓት ሰበኩ፤ 1,100 ጽሑፎችንም ለሕዝቡ አደሉ። በወንድሞች የተሰጠውን ንግግር ለማዳመጥ 181 ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል።

ጥቂት ወራት ቆይቶ ጉባኤው በሙቱም መሃል ከተማ የሚገኝ አንድ ጥሩ ቤት ለመንግሥት አዳራሽነትና የአቅኚዎች ቤት አድርገው ለመጠቀም ተከራዩ። እዚያ በተመደቡት ሁለት አቅኚ እኅቶች ወደማህበሩ የተላከው የመጀመሪያው ሪፖርት በከፊል እንዲህ ይነበባል፦ “ብዙ ሰዎች ጥናት የጀመሩ ስለሆነ ተጨማሪ አቅኚዎች ያስፈልጉናል። የሪዮ ዴ ጃኔሮ ወንድሞች በወር አንድ ጊዜ እየረዱንም እንኳ ሥራው ገና ከፍተኛ ነው። የምሥራቹ ከሚነገራቸው አሥር ባለቤቶች ውስጥ ዘጠኙ ተመልሰን እንድናስተምራቸው ይጠይቁናል። ስብሰባዎችን ለመምራትም እርዳታ ያስፈልገናል።” አሁን አንድ ሌላ አቅኚ ተልኮላቸዋል።

ሕይወቶች ተለውጠዋል

እውነት ሥር ሰዶ መልካም ፍሬ ሲያገኝ ማየት በጣም የሚያበረታታ ነው። አንድ ፍላጎት ያሳየ ሰው እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት ካጋጠሙኝ ነገሮች ሁሉ የበለጠ ነው። ሕይወቴ ወደተሻለ ሁኔታ ስለተለወጠ የሚያስተኛ ክኒን መውሰድ አላስፈለገኝም። . . . ላደረጋችሁልኝ ነገር ሁሉ ይሖዋ ሽልማታችሁን ይስጣችሁ።”

ሌላዋ ግለሰብ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ይሖዋ ዓይኖቼን እንዴት እንደከፈተልኝ በእውነት እደነቃለሁ። በዚህ ሳምንት የሴት አያቴን በሞት ያጣሁ ብሆንም አሁን እንደገና እንደማገኛት ተስፋ አለኝ። ለመጠመቅ እያሰብኩ ነው፤ ግን መጀመሪያ በደንብ መዘጋጀት እፈልጋለሁ። እዚህ መጥታችሁ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የሚወስደውን ጠባብ መንገድ ስላሳያችሁን ይሖዋ ይባርካችሁ።” ሌላው ሰውም እንዲህ አለ፦ “ከወር በፊት ሲጋራ ማጨስ እንዳቆምኩ እንድታውቁ እፈልጋለሁ። በላካችሁልኝ መጽሔት ተደስቻለሁ። ማጨስ እንዳቆም የረዳኝ ብዙ ጥሩ ነገር በውስጧ ነበራት።” በእርግጥም የመስበኩ ሥራ ለመደሰት ምክንያት የሚሰጥ ነው።

ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ በረከቶች ያለትግል አልመጡም። ለምሳሌ ያህል አንዲት ወይዘሮና ሴት ልጅዋ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ሲጀምሩ ወደ ምሥክሮቹ ስብሰባ ከሄዱ ከቤተክርስቲያን እንደሚያስወጣቸው ያካባቢው ቄስ አስጠነቀቃቸው። ማስፈራሪያውን ችላ ብለው ወደ ስብሰባዎቹ ሄዱ። ከዚያ በኋላ የቀድሞ ወዳጆቻቸው አገለሏቸው (ማለትም ከእነሱ ጋር ማንኛውንም ማህበራዊ ግንኙነት አቋረጡ።) አንዳንዶቹ እንደውም በእነሱ አነጋገር “ያ ይሖዋ” በካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለማይገኝ አብደዋል ብለው አሳጡአቸው። ወይዘሮዋ በካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የይሖዋን ስም ማግኘት ስላልቻለች ጐረቤቶቿን ከአቅኚዎቹ ጋር በምታጠናበት ቀን እንዲመጡ ጋበዘቻቸው። አንዷ ሴት የፖውሊናስ የካቶሊክ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እትም ይዛ መጣች። በዘጸአት 6:3 የግርጌ ማስታወሻ ላይ የአምላክን ስም ባነበበች ጊዜ በቤቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ተቀበለች።

በመሰብሰቡ ሥራ ሙሉ በሙሉ መካፈል

እምብዛም ባልተሠራባቸው ቀበሌዎች በሠራተኞቹ በራሳቸው ላይ ምን ውጤት ነበረው? አንዱ የመንግሥት አገልግሎት አስፋፊ እንዲህ አለ፦ “ይህ የሥራ እንቅስቃሴ እምነታችንንና ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠንከር ረድቶናል። ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች እንድንለውጥም ረድቶናል።” ሌላ አስፋፊም እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “ያ የአሥራ አራት ቀን ጊዜ ለአንድ ዓላማ ይኸውም ተጨማሪ ትሁታን ሰዎችን ለመፈለግ አንድ ቤተሰብ ሆነው ለሚያገለግሉ ወንድሞች ያለኝን ፍቅር ጨምሮልኛል። ብዙውን ጊዜም ዓይኖቻቸው እንባ አቅርረው ለእውነት እውነተኛ ጥማት በማሳየት መልእክታችንን የሚቀበሉትን ሰዎችም ይበልጥ እንድወዳቸው አድርጎኛል። ከሁሉም በላይም ይሖዋ እሱን እንድናገለግል መብት በመስጠቱ ፍቅሩ ተሰምቶኛል።”

እምብዛም ባልተሠራባቸው ቀበሌዎች በመስበኩ ሥራ የተካፈለ አንድ ሽማግሌ በዚያና በትላልቅ ከተሞች መካከል ያለውን የኑሮ ልዩነት ጠቁሟል። እንዲህ አለ፦ “ወደነዚህ ቦታዎች ዘልቀው በመግባት ለመሥራት ሲሉ በመዛወራቸው የብዙ ወንድሞች ሕይወት እንዴት ሊበለጽግ እንደቻለ በማሰብ ከመገረም ልቆጠብ አልችልም። ዓመፅ የሚባል ነገር እዚህ የለም። በትናንሽ መካከለኛ ስፋት ባላቸው ከተሞች መኖር ይህን ያህል ቀላል ከመሆኑ የተነሣ በጣም ባነሰ ወጭ እንድንኖር ብቻ ሳይሆን ከወንድሞቻችን ጋር አዘውትረን እንድንገናኝና ለመንፈሳዊ ሥራዎች የበለጠ ጊዜ እንድናውል ያስችለናል። ሌሎች ጡረታ የወጡ ወንድሞች አነስተኛ የቤተሰብ ኃላፊነት ያላቸው ወጣቶች ወይም የመተዳደሪያ ሥራቸው ለመዛወር የሚፈቅድላቸው ወጣት ሰዎች ይህን ልዩ መብት ተጠቅመው ለራሳቸው፣ ለይሖዋና ለጐረቤቶቻቸው ደስታ ሊያመጡ ይችሉ ይሆን?”

ይህ በብራዚል እምብዛም ካልተሠራባቸው ቀበሌዎች የመጣ ሪፖርት እርሻው ለመሰብሰብ እንደነጣ ያረጋግጣል። በሁለት ዓመት ብቻ በዚህ መስክ የተደረገው ሥራ 191 አዳዲስ ጉባኤዎችንና ራቅ ባሉ ገለልተኛ ቦታዎች የሚኖሩ ቡድኖችን አፍርቷል። ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ ይቀራል። ይሁን እንጂ ተጨማሪ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በፍሬያማው የመሰብሰብ ሥራ ሲካፈሉ ይሖዋ ያለጥርጥር በረከቱን መስጠቱን ይቀጥላል። አንተስ በዚህ የመሰብሰብ ሥራ ከፍተኛ ድርሻ ሊኖርህ ይችላልን?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ካርታ]

ከሪዮ ዲ ጃኔሮ የመጡ ደስተኛ ምስክሮች በመከሩ ተካፋይ ሆኑ

[ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ብራዚል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚናስ ጌራይስ ገጠር ምስክርነት ሲሰጥ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ