የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w91 10/15 ገጽ 10-14
  • የዋሆች ምንኛ ደስተኞች ናቸው!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የዋሆች ምንኛ ደስተኞች ናቸው!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የዋህነትን ቀረብ ብሎ ማየት
  • የዋህነትን እንዴት እንደምናሳድግ
  • የየዋህነት ጥቅሞች
  • የዋህነት ደስታ እንዲስፋፋ ያስችላል
  • ገርነት—ምን ጥቅሞች አሉት?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • የዋህነትን ልበሱ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
  • የዋህነት—እጅግ አስፈላጊ የሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርይ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • “ለሰው ሁሉ የዋህነትን” አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
w91 10/15 ገጽ 10-14

የዋሆች ምንኛ ደስተኞች ናቸው!

“የዋሆች ብፁዓን (ደስተኞች) ናቸው ምድርን ይወርሳሉና።”​—ማቴዎስ 5:5

1. ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ የተናገረለት የየዋህነት ጠባይ ምንድን ነው?

ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ አለ፦ “የዋሆች ደስተኞች ናቸው ምድርን ይወርሳሉና።” (ማቴዎስ 5:5) ይህ የገርነት ጠባይ ወይም የዋህነት የግብዝነት ጨዋነት ሽፋን አይደለም። በተፈጥሮ የሚገኝ ባሕርይም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ አምላክ ፈቃድና አመራር ምላሽ በመስጠት የሚገለጽ እውነተኛ ውስጣዊ ዝግተኝነት ወይም ሰላማዊነት ነው። በእውነት የዋህ የሆኑ ሰዎች ለሌሎች ሰዎች በሚያሳዩት ጠባይ ላይ የሚንጸባረቅ ከፍ ያለ በአምላክ ላይ የመመካት መንፈስ አላቸው።​—ሮሜ 12:17-19፤ ቲቶ 3:1, 2

2. ኢየሱስ የዋሆች ደስተኞች ናቸው ያለው ለምንድን ነው?

2 የዋሆች ምድርን ስለሚወርሱ ኢየሱስ ደስተኞች ብሏቸዋል። ኢየሱስ ፍጹም የሆነ የዋህ የአምላክ ልጅ በመሆኑ ዋነኛው የምድር ወራሽ ነው። (መዝሙር 2:8፤ ማቴዎስ 11:29፤ ዕብራውያን 1:1, 2፤ 2:5-9) ነገር ግን መሲሐዊ “የሰው ልጅ” በመሆኑ በሰማያዊ መንግሥቱ ተባባሪ ገዥዎች ሊኖሩት አስፈልጓል። (ዳንኤል 7:13, 14, 22, 27) እነዚህ ቅቡዓን የዋህ ሰዎች የክርስቶስ “ተባባሪ ገዥዎች” እንደመሆናቸው ምድርን በመውረስ ከኢየሱስ ጋር ተካፋይ ይሆናሉ። (ሮሜ 8:17) ሌሎች የዋህ በግ መሰል ሰዎች በመንግሥቲቱ ምድራዊ ግዛት በምትቋቋመው ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ማቴዎስ 25:33, 34, 46፤ ሉቃስ 23:43) በእርግጥም ይህ ተስፋ ደስተኞች ያደርጋቸዋል።

3. የዋህነትን በሚመለከት አምላክና ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትተውልናል?

3 የዋሁ ዋነኛ የምድር ወራሽ ምድርን የሚወርሰው ራሱ የየዋህነት ጠባይ ዋና አብነት ከሆነው ከአባቱ ከይሖዋ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ “ለቁጣ የዘገየና ምሕረቱ (ፍቅራዊ ደግነቱ) የበዛ” እንደሆነ አዘውትረው ይነግሩናል። (ዘጸአት 34:6፤ ነህምያ 9:17፤ መዝሙር 86:15) አምላክ ታላቅ ኃይልና ሥልጣን ያለው ቢሆንም ታላቅ የዋህነት እንዳለው ስለሚያሳይ አምላኪዎቹ የሚቀርቡት ያለምንም ፍርሐት ነው። (ዕብራውያን 4:16፤ 10:19-22) “የዋህና በልቡም ትሁት” የሆነው የአምላክ ልጅ ደቀመዛሙርቱም የዋህ እንዲሆኑ አስተምሯል። (ማቴዎስ 11:29፤ ሉቃስ 6:27-29) እነዚህ የዋሆች የሆኑ የአምላክና የልጁ አገልጋዮች “የክርስቶስን የዋህነትና ደግነት” ኰርጀውታል፤ ስለየዋህነትም ጽፈዋል።​—2 ቆሮንቶስ 10:1፤ ሮሜ 1:1፤ ያዕቆብ 1:1, 2፤ 2 ጴጥሮስ 1:1

4. (ሀ) በቆላስይስ 3:12 መሠረት እውነተኛ የዋህነት ያላቸው ሰዎች ምን አድርገዋል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች መመርመር ይኖርብናል?

4 በአሁኑ ጊዜ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ምድራውያን ባልንጀሮቻቸው የዋሆች መሆን ያስፈልጋቸዋል። ማንኛውንም ዓይነት ክፋት፣ ማታለል ግብዝነት፣ ምቀኝነትና ሐሜት ያስወገዱ በመሆናቸው “አእምሮአቸውን በሚያድሰው ኃይል” እንዲታደሱ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ተረድተዋል። (ኤፌሶን 4:22-24፤ 1 ጴጥሮስ 2:1, 2) “ርህራሄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትንና ትዕግሥትን” እንዲለብሱ በጥብቅ ተመክረዋል። (ቆላስይስ 3:12) ለመሆኑ የዋህነት ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? የዋህ መሆን ጠቃሚ የሆነውስ ለምንድን ነው? ይህስ ባሕርይ ተጨማሪ ደስታ የሚያመጣልን እንዴት ነው?

የዋህነትን ቀረብ ብሎ ማየት

5. የዋህነት እንዴት ሊተረጐም ይችላል?

5 የዋህ የሆነ ግለሰብ በጠባዩና በዝንባሌው ገርና ገራም ነው። በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “የዋህ” “ገር” ተብሎ የተተረጐመው “ፕሬይስ” የሚለው ቅጽል ነው። በጥንቱ ግሪክኛ “ፕሬይስ” የሚለው ገላጭ ቃል ረጋ ያለ ድምፅን ወይም ነፋስን ሊያመለክት ይችላል። ደግና ደርባባ የሆነን ሰውም ሊያመለክት ይችላል። ምሁሩ ደብልዩ ኢ ቫይን እንዲህ ይላሉ፦ “[ፕሬይትስ] የሚለው ስም በመጀመሪያ ደረጃ የሚያመለክተው ለአምላክ የሚገለጸውን ባሕርይ ነው። አምላክ ያደረገውን ነገር ሁሉ ጥሩ መሆኑን ያለአንዳች መከራከርና ተቃውሞ እንድንቀበል የሚያደርገን መንፈስ ወይም ጠባይ ነው። ትርጉሙ ትሕትና ማለት ከሆነው ታፔይኖፍርሱኔ ከሚለው ቃል ጋር በቅርብ የተያያዘ ነው።”

6. የዋህነት ደካማነት አይደለም ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

6 የዋህነት ደካማነት አይደለም። ምሁሩ ዊሊያም ባርክሌይ ሲጽፉ እንዲህ ይላሉ፦ “ፕራውስ በሚለው ቃል ውስጥ ገራምነት ወይም ለስላሳነት አለ። ነገር ግን ከገራምነቱ ወይም ከለስላሳነቱ በስተጀርባ ብረትን የሚያክል ጥንካሬ አለ።” የዋህ ለመሆን ጥንካሬ ይጠይቃል። የአምላክ የዋህ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ረገድ ምሳሌ ትቶልናል። “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራንም ሲቀበል አልዛተም። ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1 ጴጥሮስ 2:23) እኛም እንደ የዋሁ ኢየሱስ፣ አምላክ ከሚሰድቡንና ከአሳዳጆቻችን ጋር እንደሚፋረድልን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (1 ቆሮንቶስ 4:12, 13) እኛም ስደት ደርሶበት እንደነበረው እንደ እስጢፋኖስ ታማኞች ከሆንን ይሖዋ እንደሚደግፈንና ለዘለቄታው ጉዳት እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ በመገንዘብ ልንረጋጋ እንችላለን።​—መዝሙር 145:14፤ ሥራ 6:15፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7, 13

7. ምሳሌ 25:28 የዋህነት ስለጐደለው ግለሰብ ምን ያመለክታል?

7 ኢየሱስ የዋህ ነበር። ሆኖም ትክክል ለሆነው ነገር ጸንቶ በመቆም ረገድ ጠንካራ ነበር። (ማቴዎስ 21:5፤ 23:13-39) “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ያለው ማንኛውም ሰው በዚህ ረገድ ኢየሱስን ይመስላል። (1 ቆሮንቶስ 2:16) አንድ ሰው የዋህ ካልሆነ ክርስቶስን ሊመስል አይችልም። ከዚህ ይልቅ የሚከተሉትን ቃላት የሚመስል ይሆናል፦ “ቅጥር እንደሌላት እንደፈረሰች ከተማ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።” (ምሳሌ 25:28) እንዲህ ዓይነቱ የዋህነት የጐደለው ግለሰብ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እርምጃ እንዲወስድ በሚያደርጉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ለመወረር የተጋለጠ ነው። የዋህ ሰው ደካማ ወይም ልፍስፍስ ያልሆነ ሰው ሲሆን “የለዘበች መልስ ቁጣን እንደምትመልስና ሻካራ ቃል ግን ቁጣን እንደምታስነሳ” ያውቃል።​—ምሳሌ 15:1

8. የዋህ መሆን ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው?

8 አለፍጽምናንና ኃጢአትን ስለወረስን የዋህ መሆን ቀላል አይደለም። (ሮሜ 5:12) የይሖዋ አገልጋዮች ከሆንን ስደት በማስነሣት የዋህነታችንን ከሚፈትኑ የክፉ መናፍስት ኃይሎች ጋር መጋደል ይኖርብናል። (ኤፌሶን 6:12) አብዛኞቻችንም የምንሠራው በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም መጥፎ መንፈስ ባላቸው ሰዎች መሃል ነው። (1 ዮሐንስ 5:19) ታዲያ የዋህነትን ልናሳድግ የምንችለው እንዴት ነው?

የዋህነትን እንዴት እንደምናሳድግ

9. የዋህነትን ለማሳደግ ምን አመለካከት ሊረዳን ይችላል?

9 የየዋህነትን ባሕርይ የማሳየት ግዴታ እንዳለብን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነት ከኖረን ይህን ባሕርይ ለማሳደግ ይረዳናል። በየዕለቱ የዋህነትን ለመኰትኮት መጣር አለብን። አለዚያ የዋህነትን እንደ ደካማነት እንደሚመለከቱት ሰዎች ልንሆንና የተሳካ ውጤት የሚገኘው እብሪተኛ፣ ጥብቅና እንዲያውም ጨካኝ ከመሆን ነው ብለን ልናስብ እንችላለን። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ትዕቢትን ያወግዛል። ጥበበኛው ምሳሌም “ቸር (ፍቅራዊ ደግነት ያለው) ሰው ለራሱ መልካም ያደርጋል፤ ጨካኝ ግን ሥጋውን ይጐዳል” ይላል። (ምሳሌ 11:17፤ 16:18) ሰዎች በጭካኔውና የዋህ ባለመሆኑ ላለመጐዳት ሲሉ ከኃይለኛ ወይም ሻካራ፣ ጥብቅና ክፉ ከሆነ ሰው ይርቃሉ።

10. የዋህ እንድንሆን ከተፈለገ ለምን መገዛት አለብን?

10 የዋህ ለመሆን ለአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም ለአምላክ ሠራተኛ ኃይል ግፊት መገዛት አለብን። ይሖዋ ምድር ሰብልን እንድታፈራ እንዳስቻላት ሁሉ አገልጋዮቹንም የመንፈሱን ፍሬዎች የዋህነትንም ጭምር እንዲያፈሩ ያስችላቸዋል። ጳውሎስ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ የዋህነት (የውሃት) ራስን መግዛት ነው። እነዚህንም የሚከለክል ሕግ የለም” ሲል ጽፎአል። (ገላትያ 5:22, 23) አዎን የዋህነት አምላክን የሚያስደስቱ ሰዎች ከሚያፈሩአቸው የመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ነው። (መዝሙር 51:9, 10) የዋህነት ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል! ለማስረዳት ያህል ቶኒ የሚባል ጠበኛ፣ ሰዎችን የሚዘልፍ ሱስ የሚያስይዙ ዕፆችን በድብቅ የሚነግድ፣ የሞተር ብስክሌት ወንበዴዎችን የሚመራና በተደጋጋሚ እሥር ቤት የሚገባ ወሮበላ ነበር። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘትና በአምላክ መንፈስ በመታገዝ የዋህ ጠባይ ያለው የይሖዋ አገልጋይ ወደመሆን ተለወጠ። የቶኒ ታሪክ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። ታዲያ አንድ የየዋህነት ጉድለት የባሕሪው ዋና ገጽታ ሆኖ የቆየ ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል?

11. የዋህነትን በማሳደግ ረገድ ጸሎት ምን ሚና ይጫወታል?

11 የአምላክን መንፈስና የአምላክ መንፈስ ፍሬ የሆነውን የየዋህነት ባሕርይ ለማግኘት ከልብ መጸለይ ይህን ባሕርይ ለመኰትኰት ይረዳናል። ኢየሱስ እንዳለው መጠየቃችንን መቀጠል ሊያስፈልገን ይችል ይሆናል፤ ይሖዋ አምላክም የለመንነውን ይሰጠናል። ኢየሱስ ሰብዓዊ አባቶች ለልጆቻቸው መልካም ስጦታ እንደሚሰጡ ከገለጸ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንኪያስ እናንተ (ከአምላክ ጋር ስትወዳደሩ ኃጢአተኞች ስትሆኑ) ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚያምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስ ይሰጣቸው?” (ሉቃስ 11:9-13) ለራሳችንና አብረውን ላሉት ሰዎች ደስታ የሚያስገኘውን የየዋህነት ባሕርይ የጠባያችን ቋሚ ገጽታ እንድናደርገው ጸሎት ሊረዳን ይችላል።

12. ሰዎች ፍጹማን ያለመሆናቸውን ማስታወስ የዋሆች እንድንሆን ሊረዳን የሚችለው ለምንድን ነው?

12 ሰዎች ፍጹማን ያለመሆናቸውን ማስታወስ የዋሆች እንድንሆን ይረዳናል። (መዝሙር 51:5) እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች ፍጹም በሆነ ሁኔታ ልናስብና ልንሠራ አንችልም። ስለዚህ የሌሎችን ችግር እንደራሳችን ችግር አድርገን መቁጠርና እነሱ ለእኛ ሊያደርጉልን በምንፈልግበት መንገድ ልናደርግላቸው ይገባናል። (ማቴዎስ 7:12) ሁላችንም እንደምንሳሳት ማወቃችን ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ይቅር ባዮችና የዋሆች እንድንሆን ሊያደርገን ይገባል። (ማቴዎስ 6:12-15፤ 18:21, 22) ከሁሉ በላይ አምላክ ለእኛ ፍቅርና የዋህነት የሚያሳየን በመሆኑ አመስጋኞች አይደለንምን?​—መዝሙር 103:10-14

13. አምላክ ሰዎችን ነፃ ምርጫ ያላቸው አድርጎ የፈጠራቸው መሆኑን አምነን መቀበላችን የዋህነትን እንድንኮተኩት ሊያግዘን የሚችለው እንዴት ነው?

13 አምላክ ሰዎችን ነፃ ምርጫ ያላቸው አድርጎ እንደፈጠራቸው አምነን መቀበልም የዋህነትን እንድንኮተኩት ይረዳናል። ይህም ማንም የይሖዋን ሕጎች ችላ ብሎ ከቅጣት ነፃ እንዲሆን ባያስችልም፣ ሕዝቦቹ በፍላጎታቸው፣ በሚወዱትና በሚጠሉት ነገር ረገድ መለያየት እንዲኖር ያስችላል። ስለዚህ ማንም ሰው እኛ ከሁሉም የተሻለ ነው ከምንለው አኗኗርና ጠባይ ጋር እንዲስማማ የማይገደድ መሆኑን እንቀበል። ይህ መንፈስ የዋሆች እንድንሆን ይረዳናል።

14. የዋህነትን በሚመለከት ቁርጥ ውሳኔአችን ምን መሆን ይኖርበታል?

14 የዋህነትን ላለመተው ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይህን ባሕሪ መኮትኮታችንን እንድንቀጥልበት ይረዳናል። ለይሖዋ መንፈስ ግፊት መገዛት በአስተሳሰባችን ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። (ሮሜ 12:2) የዋህና የክርስቶስን መሰል መንፈስ ከእንግዲህ ‘ከመዳራት፣ ከሥጋ ምኞት (ፍትወት)፣ ከስካር፣ ከዘፈን (ፈንጠዝያ)፣ ያለልክም ከመጠጣትና ነውር ካለበት (ሕገወጥ) ጣዖት ማምለክና’ ከመሳሰሉት ድርጊቶች እንድንቆጠብ ይረዳናል። ለገንዘብ፣ ለማህበራዊ ወይም ለሌላ ጥቅም ወይም ስለ አምላካዊነታችን ሰዎች የስድብ አስተያየት ስለሰነዘሩብን የዋህነትን ፈጽሞ መተው የለብንም። (1 ጴጥሮስ 4:3-5) የዋህነታችንን እንዳናጣና የአምላክን መንግሥት ከመውረስ ወይም በረከቶችን ከማግኘት እንዳንቀር ምንም ነገር “የሥጋን ሥራ” እንድንሠራ እንዲያደርገን አንፍቀድ። (ገላትያ 5:19-21) ለሰማያዊ ሕይወት የተቀባንም ሆን ምድራዊ ተስፋ ያለን የዋህ የአምላክ ሕዝቦች የመሆንን መብት ሁልጊዜ ከፍተኛ ዋጋ እንስጠው። ለዚህም ሲባል አንዳንድ የየዋህነት ጥቅሞችን እንመልከት።

የየዋህነት ጥቅሞች

15. በምሳሌ 14:30 መሠረት የዋህ መሆን ጥበብ የሚሆነው ለምንድን ነው?

15 የዋህ ሰው የልብ የአእምሮና የሰውነት እርጋታ አለው። ይህ የሆነበት ምክንያት ጠብ ውስጥ ስለማይገባ፣ በሌሎች ሰዎች ድርጊት ስለማይበሳጭ ወይም ማቆሚያ በሌለው ጭንቀት ራሱን ስለማያሰቃይ ነው። የዋህነት ስሜቶቹን እንዲቆጣጠር ይረዳዋል። ይህም ለአእምሮም ሆነ ለአካል ጠቃሚ ነው። አንድ ምሳሌ “ትሁት (የረጋ) ልብ የሥጋ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 14:30) የየዋህነት ጉድለት ወደ ንዴት ሊመራና የደምን ግፊት ከፍ ሊያደርግ ወይም የምግብ አለመፈጨት ችግር፣ አስም፣ የዓይን ሕመምና ሌሎች ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። የዋህ የሆነ ክርስቲያን ልቡናውንና የማሰብ ችሎታውን የሚጠብቅለትን “የአምላክ ሰላም” ጨምሮ የተለያዩ ጥቅሞችን ያገኛል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) የዋህ መሆን በጣም ታላቅ ጥበብ ነው።

16-18. የዋህነት ከሌሎች ጋር ባለን ዝምድና ላይ ምን ውጤት አለው?

16 የየዋህነት ጠባይ ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና ያሻሽልልናል። ምናልባት አንድ ወቅት የፈለግነውን እስክናገኝ ድረስ ሰዎችን የመጫን ወይም የመጨቃጨቅ ልማድ ኖሮብን ይሆናል። ትሕትናና የዋህነት ስለጐደለን ሰዎች ተናደውብን ይሆናል። እንዲህ ያለ ልማድ ከነበረን በተደጋጋሚ አለመግባባትና ንትርክ ውስጥ ገብተን ቢሆን ሊያስደንቀን አይገባም። ይሁን እንጂ አንድ ምሳሌ እንዲህ ይላል፦ “እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል። ጆሮ ጠቢ (ነገረኛ) በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል። ከሰል ፍምን እንጨትም እሳትን እንደሚያበዛ እንዲሁ ቁጡ ሰው ጠብን ያበዛል።” (ምሳሌ 26:20, 21) የዋሆች ከሆንን “እንጨት ወደ እሳቱ በመጨመር” እና ሌሎችን በማስቆጣት ፈንታ ከእነሱ ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖረናል።

17 የዋህ ሰው ጥሩ ወዳጆች ሊያገኝ ይችላል። ሰዎች ከሱ ጋር መሆን ደስ ይላቸዋል። ምክንያቱም አዎንታዊ ወይም ይሆናል ባይ ዝንባሌ አለው እንዲሁም ቃላቶቹ የሚያጽናኑና እንደ ማር የሚጣፍጡ ናቸው። (ምሳሌ 16:24) ኢየሱስ እንዲህ ያለ ሰው ነበር። እሱ እንዲህ ሊል ችሎ ነበር፦ “ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ። ከእኔም ተማሩ። እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና ለነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴዎስ 11:29, 30) ኢየሱስ ሻካራ ወይም ጨካኝ ሰው አልነበረም። ቀንበሩም ጨቋኝ አልነበረም። ወደ እሱ የሚመጡ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ይያዛሉ፤ በመንፈሳዊም ይጽናናሉ። ሁኔታው ከአንድ የዋህ ክርስቲያን ጓደኛችን ጋር አብረን ከመሆን ጋር ይመሳሰላል።

18 የዋህነት በእምነት መሰሎቻችን ዘንድ ያስወድደናል። ያለጥርጥር አብዛኞቹ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ወደ ጳውሎስ የተሳቡት ‘በክርስቶስ የዋህነትና ደግነት’ ስለለመናቸው ነው። (2 ቆሮንቶስ 10:1) የተሰሎንቄ ሰዎች ጳውሎስን የተቀበሉት የዋህና ገራም መምህር ስለሆነ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። (1 ተሰሎንቄ 2:5-8) የኤፌሶን ሽማግሌዎች ከጳውሎስ ብዙ እንደተማሩና በጣም ይወዱት እንደነበረ አያጠያይቅም። (ሥራ 20:20, 21, 37, 38) በሌሎች ዘንድ የሚያስወድድህን የየዋህነት ባሕርይ ታሳያለህን?

19. የዋህነት የይሖዋ ሕዝቦች በድርጅቱ ውስጥ ቦታቸውን እንዲጠብቁ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

19 የዋህነት የይሖዋን ሕዝቦች ታዛዦች እንዲሆኑና በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ቦታቸውን እንዲጠብቁ ይረዳቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:5-8, 12-14፤ ዕብራውያን 13:17) የዋህነት በትዕቢት ላይ ከተመሠረተውና ይሖዋን ከሚያስቀይመው ክብር የመፈለግ ዝንባሌ ይገታናል። (ምሳሌ 16:5) የዋህ ሰው ራሱን ከመሰል አማኞች የበላይ አድርጎ አይመለከትም፣ እነርሱን በማዋረድም እሱ ልቆ ለመታየት አይሞክርም። (ማቴዎስ 23:11, 12) በዚህ ፋንታ ኃጢአተኛነቱንና የአምላክ የቤዛ ዝግጅት የሚያስፈልገው መሆኑን አምኖ ይቀበላል።

የዋህነት ደስታ እንዲስፋፋ ያስችላል

20. የዋህነት በቤተሰብ ሕይወት ላይ ምን ውጤት አለው?

20 የአምላክ አገልጋዮች የሆኑ ሁሉ የዋህነት ደስታን የሚያስፋፋ የአምላክ መንፈስ ፍሬ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ሕዝቦች ፍቅርና የዋህነት የመሳሰሉትን ባሕርያት ስለሚያሳዩ ብዙ ደስተኛ ቤተሰቦች በመሃላቸው ይገኛሉ። ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው በየዋህነት ሲተያዩ ልጆቻቸው ሻካራ ቃላትና ድርጊቶች በሞሉበት ቤተሰብ ውስጥ ሳይሆን እርጋታ በሰፈነበት ሁኔታ ያድጋሉ። አባት ለልጆቹ በየዋህነት ወይም ለስለስ ባለ መንፈስ ምክር ሲሰጣቸው ይህ በአእምሮአቸው ላይ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል። የዋህ መንፈስም የባሕርያቸው ክፍል ሊሆንላቸው ይችላል። (ኤፌሶን 6:1-4) የዋህ ጠባይ ባሎች ሚስቶቻቸውን በመውደድ እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል። ሚስቶችም ለባሎቻቸው እንዲገዙ ይረዳቸዋል። ልጆችም ለወላጆቻቸው እንዲታዘዙ ይገፋፋቸዋል። የዋህነት የቤተሰብ አባሎች ለደስታ ተጨማሪ ምክንያት የሆነው የይቅር ባይነት መንፈስ እንዲኖራቸው ያደርጋል።​—ቆላስይስ 3:13, 18-21

21. ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን 4:1-3 ላይ ምን ምክር ሰጥቷል?

21 የዋህ ጠባይ ያላቸው ቤተሰቦችና ግለሰቦች ባሉባቸው ጉባኤዎች ውስጥ ደስታ እንዲሰፍን ምክንያት ይሆናሉ። ስለዚህ የይሖዋ ሕዝቦች የዋሆች ለመሆን ልባዊ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። እንዲህ እያደረግህ ነውን? ሐዋርያው ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች መሰሎቹን “በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም እርስ በርሳቸው በፍቅር በመታገሥ በሰላም ማሠሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ በመትጋት” ለሰማያዊ ጥሪያቸው እንደሚገባ እንዲመላለሱ ለምኗቸዋል። (ኤፌሶን 4:1-3) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም የዋህነትንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርዮችን ማሳየት አለባቸው። ወደ እውነተኛ ደስታ የሚያደርሰው መንገድ ይኸው ነው። የዋሆች በእርግጥም ደስተኞች ናቸው!

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

◻ የዋሆች ደስተኞች የሆኑት ለምንድን ነው?

◻ የዋህ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?

◻ የዋህነት እንዴት ሊያድግ ይችላል?

◻ የየዋህነት አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ