የዋህነትን ልበሱ!
“እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ ምሕረትን ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትህትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12
1-3. ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ 3:12-14 ላይ ስለ የዋህነትና ስለሌሎቹ አምላካዊ ባሕርያት ምን አለ?
ይሖዋ ለሕዝቡ ከሁሉ የበለጠውን ምሳሌያዊ ልብስ ይሰጣቸዋል። እንዲያውም ሞገሱን የሚሹ ሁሉ ጠንካራ ከሆነ የየዋህነት ድርና ማግ የተሠራ ልብስ መልበስ አለባቸው። ይህ ባሕርይ የሚያጽናና ነው። ምክንያቱም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት ጭንቀትን ይቀንሳል። ከጠብ ስለሚጠብቅም ከብዙ ችግር ይከላከላል።
2 ሐዋርያው ጳውሎስ ቅቡዓን ባልንጀሮቹን “እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ፣ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን ትዕግሥትን ልበሱ” በማለት አሳስቦአቸዋል። (ቆላስይስ 3:12) “ልበሱ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ግሥ የጊዜ አገባብ በችኮላ የሚደረግን ድርጊት የሚያመለክት ነው። የተመረጡ፣ የተቀደሱና በአምላክ የተወደዱ ቅቡዓን እንዲህ ዓይነቱን የየዋህነት ባሕርይ ከመልበስ መዘግየት አልነበረባቸውም።
3 ጳውሎስ ጨምሮም፦ “እርስ በርሳችሁም ትዕግሥትን አድርጎ፤ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ። በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ (የፍጹም አንድነት) ማሠሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት” ብሏል። (ቆላስይስ 3:13, 14) ፍቅር፣ የዋህነትና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያት የይሖዋ ምሥክሮች “በኅብረት እንዲቀመጡ” ያስችሏቸዋል።—መዝሙር 133:1-3
የዋህ እረኞች ያስፈልጋሉ
4. እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚለብሱት ከምን ባሕሪያት የተሠራ ምሳሌያዊ ልብስ ነው?
4 እውነተኛ ክርስቲያኖች “ዝሙትን፣ ርኩሰትን፣ ፍትወትን፣ ክፉ ምኞትንና መጎምዠትን በተመለከተ ብልቶቻቸውን ለመግደል” ይጥራሉ። ከቁጣ፣ ከንዴት፣ ከክፋት፣ ከስድብና ከሚያሳፍር ንግግር ድርና ማግ የተሠራውን ማንኛውንም ዓይነት አሮጌ ልብስ ለማስወገድ ይጥራሉ። (ቆላስይስ 3:5-11) “አሮጌውን ሰውነት” (ቃል በቃል “አሮጌው ሰው”) አውልቀው ተስማሚ የሆነውን “አዲሱን ሰውነት” (ወይም ቃል በቃል “አዲሱን ሰው”) ይለብሳሉ። (ኤፌሶን 4:22-24) ከርኅራኄ፣ ከደግነት፣ ከትህትና፣ ከየዋህነትና ከትዕግሥት የተሠራው አዲሱ ልብሳቸው ችግሮችን ለመፍታትና አምላካዊ ሕይወትን ለመኖር ይረዳቸዋል።—ማቴዎስ 5:9፤ 18:33፤ ሉቃስ 6:36፤ ፊልጵስዮስ 4:2, 3
5. የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን አስደሳች ነገር የሆነው ምን ዓይነት አሠራር ስላለ ነው?
5 በዚህ ዓለም የተሳካላቸው የሚባሉት ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ኃይለኞችና እንዲያውም ጨካኞች ናቸው። (ምሳሌ 29:22) በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው! የክርስቲያን ጉባኤ የሚሠራው በንግድ ዓለም ያሉ አንዳንድ ሰዎች እንደሚሠሩት ማለትም በቅልጥፍና ነገር ግን ሰዎችን ሊያሳዝን በሚችል ሁኔታ በማመናጨቅ አይደለም። የጉባኤ አባል መሆን የሚያስደስት ነገር ነው። ይህም ሊሆን ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ ክርስቲያኖች ባጠቃላይና በተለይም መሰል አማኞችን ለማስተማር ብቃት ያላቸው ሰዎች የሚያሳዩት ጥበብ አንደኛው ክፍል የዋህነት ስለሆነ ነው። አዎን “በጥበብ የዋህነት” የሚያስተምሩ የተሾሙ ሽማግሌዎች ከሚሰጡት መመሪያና ምክር ደስታ ይገኛል።—ያዕቆብ 3:13
6. ክርስቲያን ሽማግሌዎች የዋሆች መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
6 የአምላክ ሕዝቦች ሁኔታ በጉባኤው ውስጥ የበላይ ተመልካችነት አደራ የሚሰጣቸው ሰዎች የዋሆች፣ ምክንያታዊና አድማጭ እንዲሆኑ የሚጠይቅ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-3) የይሖዋ አገልጋዮች ገራም እንደሆኑ በጎች ናቸው እንጂ ችኮ እንደሆኑ ፍየሎች፣ ሐሳበ ግትር እንደሆኑ በቅሎዎች ወይም ስግብግብ እንደሆኑ ተኩላዎች አይደሉም። (መዝሙር 32:9፤ ሉቃስ 10:3) በግ መሰል ሰዎች በመሆናቸው በየዋህነትና በርኅራኄ መያዝ አለባቸው። (ሥራ 20:28, 29) አዎን ሽማግሌዎች ለበጎቹ የዋህ (ለስላሳ) ደግ፣ አፍቃሪና ትዕግሥተኞች እንዲሆኑ አምላክ ይጠይቅባቸዋል።—ሕዝቅኤል 34:17-24
7. ሽማግሌዎች ሌሎችን ማስተማር ያለባቸው ወይም በመንፈሳዊ የታመሙትን መርዳት ያለባቸው እንዴት ነው?
7 አንድ ሽማግሌ “የጌታ ባሪያ” በመሆኑ “ለሰዎች ሁሉ ገር፣ ለማስተማር የሚበቃ፣ በትዕግሥትም የሚጸና ሊሆን እንጂ ሊጣላ አይገባውም። ደግሞም ምናልባት እግዚአብሔር እውነትን ያውቁ ዘንድ ንስሐን ይሰጣቸዋልና ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ።” (2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25) ክርስቲያን ሽማግሌዎች በጎቹ የአምላክ ስለሆኑ በመንፈስ የታመሙትን ለመርዳት ሲሞክሩ የርኅራኄ አሳቢነት ማሳየት አለባቸው። ሽማግሌዎች በጎቹን እንደ ቅጥረኛ ሳይሆን እንደ መልካሙ እረኛ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በየዋህነት መያዝ አለባቸው።—ዮሐንስ 10:11-13
8. የዋሁ ሙሴ ምን ደረሰበት? ለምንስ?
8 አንድ ሽማግሌ አንዳንዴ የገርነት መንፈስ መያዙ አስቸጋሪ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። “ሙሴ በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሁት ሰው ነበር።” (ዘኁልቁ 12:3) ሆኖም እሥራኤላውያን በቃዴስ የውሃ እጥረት ባጋጠማቸው ጊዜ ሙሴን ተጣሉት። ከግብጽ ወደ ደረቅ ምድረ በዳ ስለመራቸውም ወቀሱት። ሙሴ በትህትና ብዙ የታገሠ ሰው ቢሆንም በችኩልነትና በኃይል ተናገረ። እሱና አሮን በሕዝቡ ፊት ቆሙና ሙሴ “እናንተ አመጸኞች እንግዲህ ስሙ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውሃ እናወጣላችኋለን” ብሎ በመናገሩ የሕዝቡን ትኩረት ወደ ራሳቸው ሳቡ። ከዚያም ሙሴ ዓለቱን በበትሩ ሁለት ጊዜ መታው። አምላክም ለሕዝቡ እና ለእንሰሶቻቸው “ብዙ ውሃ” አወጣላቸው። ሙሴና አሮን ይሖዋን ስላልቀደሱት ይሖዋ ተከፋ። ስለዚህ ሙሴ እሥራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር መርቶ ለማስገባት መብት አላገኘም።—ዘኁልቁ 20:1-13፤ ዘዳግም 32:50-52፤ መዝሙር 106:32, 33
9. የአንድ ሽማግሌ የዋህነት ፈተና ሊደርስበት የሚችለው እንዴት ነው?
9 የአንድ ክርስቲያን የዋህነት በተለያዩ መንገዶች ፈተና ሊደርስበት ይችላል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ጢሞቴዎስ “በትዕቢት የተነፉ” እና “ምርመራን (ጥያቄ መጠየቅን) በቃል መዋጋትን (መከራከርን) እንደበሽተኛ የሚናፍቅ“ ሰው ሊነሣ እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር። ጳውሎስ ጨምሮም “ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም፣ ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም አእምሮአቸው ከጠፋባቸውና እውነትን ከተቀሙ ሰዎች ይወጣሉ ብሏል። የበላይ ተመልካቹ ጢሞቴዎስ በቁጣ አንዳች ነገር ሊያደርግ ሳይሆን “ከእነዚህ ነገሮች እንዲሸሽ” እና “ጽድቅንና ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ መጽናትን፣ የዋህነትንም እንዲከታተል” ተመክሮአል።—1 ጢሞቴዎስ 6:4, 5, 11
10. ቲቶ ጉባኤዎችን ስለምን ነገር ማሳሰብ ነበረበት?
10 ሽማግሌዎች የዋሆች መሆን ቢያስፈልጋቸውም ትክክል ለሆነው ነገር ጥብቅ መሆን አለባቸው። ቲቶ እንደዚህ ዓይነት ክርስቲያን ነበር። ከቀርጤስ ጉባኤ ጋር የተባበሩትን ሰዎች “ማንንም የማይሳደቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች (ምክንያታውያን)፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ” እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል። (ቲቶ 3:1, 2) ቲቶ ክርስቲያኖች ለሰው ሁሉ የዋህነትን ማሳየት የሚኖርባቸው ለምን እንደሆነ በማሳየት ይሖዋ ምን ያህል ደግና አፍቃሪ መሆኑን ማስገንዘብ ነበረበት። አምላክ አማኞችን ያዳነው ስለሠሩት የጽድቅ ሥራ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባሳየው ምህረቱ ነበር። የይሖዋ የዋህነትና ትዕግሥት ለእኛም መዳናችን ነው። ስለዚህ እንደ ቲቶ የአሁኑ ጊዜ ሽማግሌዎች ሌሎችን በየዋህነት መንገድ በመያዝና አምላክን በመምሰል ጉባኤዎች ለይሖዋ እንዲገዙ ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል።—ቲቶ 3:3-7፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 15
የዋህነት ጥበበኛውን መካሪ ይመራዋል
11. በገላትያ 6:1, 2 መሠረት ምክር መስጠት የሚኖርበት እንዴት ነው?
11 አንድ ምሳሌያዊ በግ ከተሳሳተ ምን ይደረጋል? ጳውሎስ እንዲህ አለ፦ “ወንድሞች ሆይ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት (አስተካክሉት)። አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ። ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ።” (ገላትያ 6:1, 2) ምክር በየዋህነት መንፈስ ከተሰጠ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናል። ሽማግሌዎች ለመምከር የሚሞክሩት አንድን የተናደደ ሰው ቢሆንም እንኳን “የገራም ምላስ አጥንትን እንደሚሰብር” በመገንዘብ ራስ መግዛትን ማሳየት ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 25:15) አንድ እንደ አጥንት የጠነከረ ሰው በገራም ወይም በለሰለሰ አነጋገር ሊለዝብና ኃይለኛነቱ ሊሰበር ይችላል።
12. አንድ ምክር ሰጪ የዋህ መንፈስ የሚረዳው እንዴት ነው?
12 ይሖዋ የዋህ አስተማሪ ስለሆነ የሱ የማስተማር መንገድ በጉባኤ ውስጥ ውጤታማ ነው። ይህ እውነት መሆኑ በይበልጥ የሚታየው መንፈሳዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች መምከር አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ነው። ደቀመዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጻፈ፦ “ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አኗኗሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።” የዋህነት የሚመነጨው የራስን አቅም በትሕትና ከመገንዘብና “ለላይኛይቱ ጥበብ” አክብሮትና አመስጋኝነት ከማሳየት ነው። የዋህ ወይም ገራምና ትሑት መንፈስ ምክር ሰጪውን ጎጂ አስተያየቶችን ከመስጠትና ከስሕተት ይጠብቀዋል። ምክሩንም ለመቀበል ቀላል ይሆንለታል። —ያዕቆብ 3:13, 17
13. “በጥበበኞች ዘንድ የሚገኘው የዋህነት” ምክር የሚሰጥበትን መንገድ የሚነካው እንዴት ነው?
13 ምክር ሰጪው “የጥበብ የዋህነት” መንፈስ ካለው አሳቢነት በጎደለው መንገድ ከመናገር ወይም ከማመናጨቅ ይጠብቀዋል። ሆኖም አንድ ሽማግሌ ወዳጅነት እንዳይደፈርስ አስቦ ወይም ተመካሪውን እንዳይዘልፈው ፈርቶ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረት ቀጥተኛ ምክር በየዋህነት ከመስጠት ለመቆጠብና ተመካሪውን የሚያስደስቱ ነገሮችን ለመናገር መገፋፋት የለበትም። (ምሳሌ 24:24-26፤ 28:23) አምኖን ከአጎቱ ልጅ ያገኘው ምክር ምኞቱን አርክቶለታል፤ ነገር ግን ሕይወቱን አሳጥቶታል። (2 ሳሙኤል 13:1-19, 28, 29) የአሁን ዘመን ሽማግሌዎችም የአንድን ሰው ህሊና ለማረጋጋት በማሰብ ይሖዋ የሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ሥርዓቶች መበረዝ አይገባቸውም። ምክንያቱም ይህ ሕይወቱን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። ሽማግሌዎችም እንደ ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ” ለሌሎች ከመናገር መቆጠብ የለባቸውም። (ሥራ 20:26, 27፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:1-4) አንድ የጎለመሰ ምክር ሰጪ ክርስቲያን አምላካዊ ፍርሐትና በጥበበኞች ዘንድ የሚገኘውን የዋህነት በማሳየት ጻድቅና ትክክለኛ የሆን ምክር ይሰጣል።
14. አንድ ሽማግሌ ሌሎች ሰዎች ራሳቸው ማድረግ የሚገባቸውን ውሳኔ ላለማድረግ መጠንቀቅ የሚኖርበት ለምንድን ነው?
14 ሰማያዊ ጥበብ የታከለበት የዋህነት አንድን ሽማግሌ አስቸጋሪ ወይም ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ከሌሎች ከመጠበቅ ያግደዋል። ሌላው ሰው ራሱ ማድረግ ያለበትን ውሳኔ እሱ ቢያደርገው ጥበብ የጎደለውና የማይገባ መሆኑንም መገንዘብ ይኖርበታል። አንድ ሽማግሌ ለሌሎች ሰዎች ውሳኔ ካደረገ ለሚደርሱት ውጤቶች ተጠያቂ ይሆናል። ለሚደርሰውም ማንኛውም ዓይነት መጥፎ ውጤት ተወቃሽ ይሆናል። አንድ ሽማግሌ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ይኖርበታል። በጉዳዩ ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕግ ከሌለ ምን ማድረግ እንዳለበትና እንደሌለበት የሚወስነው የግለሰቡ የራሱ የማመዛዘን ችሎታና ሕሊና መሆን አለበት። ጳውሎስ እንዳለው “እያንዳንዱ የራሱን ሸክም ይሸከማል።” (ገላትያ 6:5፤ ሮሜ 14:12) ይሁን እንጂ አንድ ምክር የሚሰጠው ሰው በፊቱ ከተደቀኑት በምርጫ የሚወሰኑ ጉዳዮች ጋር የሚዛመዱ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲያመዛዝን የሚረዱት ጥያቄዎችን ሽማግሌው ያቀርብለታል።
15. አንድ ሽማግሌ የአንድን ጥያቄ መልስ ካላወቀ ምን ማድረግ ይኖርበታል?
15 አንድ ሽማግሌ ለቀረበለት ጥያቄ መልሱን የማያውቅ ከሆነ ከሀፍረት ለመዳን ብቻ ብሎ መልስ መስጠት የለበትም። የጥበብ የዋህነት ግምት ከመስጠትና ምናልባትም በኋላ ሲያሳዝን የሚችል የተሳሳተ መልስ ከመስጠት ይጠብቀዋል። “ለመናገር ጊዜ አለው ዝም ለማለትም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:7፤ ከምሳሌ 21:23 ጋር አወዳድር) አንድ ሽማግሌ “መናገር” ያለበት ለጥያቄው መልሱን ካወቀ ወይም ትክክለኛ መልስ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ምርምር ካደረገ በኋል ብቻ መሆን አለበት። በቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ የማይገኝላቸውን ጥያቄዎች ሳይመልሱ መተው ጥበብ ነው።—ምሳሌ 12:8፤ 17:27፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:3-7፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:14
የመካሮች መብዛት የሚያስገኘው ጥቅም
16, 17. ሽማግሌዎች እርስ በርስ መመካከራቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
16 ሽማግሌዎችን ጸሎትና ጥናት ጥያቄዎችን እንዲመልሱና አስቸጋሪ ጉዳዮችን በአግባቡ ለመያዝ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። ነገር ግን “መካሮች በበዙበት የታሰበው እንደሚሳካ” መታወስ ይኖርበታል። (ምሳሌ 15:22) ከሌሎች ሽማግሌዎች ጋር መመካከር ተጨማሪ ጥበብ ስለሚያስገኝ በጣም ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 13:20) የሁሉም ሽማግሌዎች ተሞክሮ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እኩል አይደለም። ስለዚህ አነስተኛ ተሞክሮ ያለው ሽማግሌ በተለይ ከበድ ያለ ጉዳይ ሲያጋጥመው የበለጠ እውቀትና ተሞክሮ ያላቸውን ሽማግሌዎች ምክር እንዲጠይቅ የጥበብ የዋህነት ሊገፋፋው ይገባል።
17 ሽማግሌዎች አንድን ከባድ ጉዳይ እንዲመለከቱ በሚጠየቁበት ጊዜ ሚስጥር ሳይገልጡ እርዳታ ሊጠይቁ ይችላሉ። ሙሴ በእሥራኤል ላይ በመፍረድ እንዲረዱት ከሕዝቡ “አዋቂዎችን፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉ” ሰዎችን መርጧል። ሽማግሌዎች ቢሆኑም ሙሴ የነበረውን ያህል እውቀትና ተሞክሮ አልነበራቸውም። ስለዚህ “የከበዳቸውን ነገር ወደ ሙሴ አመጡ። ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ።” (ዘፀአት 18:13-27) በዛሬው ጊዜም አስፈላጊ ከሆነ ከባድ ጉዳይ ያጋጠማቸው ሽማግሌዎች የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያደርጉት ራሳቸው ቢሆኑም ተሞክሮ ካላቸው የበላይ ተመልካቾች እርዳታ መፈለጋቸው ተገቢ ነው።
18. የፍርድ ጉዳዮች በሚታዩበት ጊዜ ተገቢ ውሳኔዎች እንዲደረጉ የሚረዱ ወሳኝ ነገሮች ምንድን ናቸው?
18 የአይሁድ ሚሽናን የመንደር ፍርድ ቤት ዳኞች ቁጥር እንደ ጉዳዩ ክብደት የተለያየ እንደሚሆን ይናገራል። ብዙኃኑ ሊሳሳቱ ስለሚችሉ የቁጥር ብዛት ብቻውን ለትክክለኛነት ዋስትና ባይሆንም አብዛኞቹ ስህተቶች ሊሆኑ ቢችሉም የመካሮች ብዛት ጥቅም አለው። (ዘፀአት 23:2) ተገቢ ውሳኔ እንዲያደርግ የሚረዱት ወሳኝ ነገሮች ቅዱሳን ጽሑፎችና የአምላክ መንፈስ ናቸው። ጥበብና የዋህነት ክርስቲያኖች ለቅዱሳን ጽሑፎችና ለአምላክ መንፈስ እንዲገዙ ይገፋፋቸዋል።
በየዋህነት መመስከር
19. የዋህነት የይሖዋ ሕዝቦች ለሌሎች እንዲመሠክሩ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
19 የዋህነት የይሖዋ አገልጋዮች የተለያየ ጠባይ ላላቸው ሰዎች እንዲመሰክሩ ይረዳቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 9:22, 23) ኢየሱስ በየዋህነት ያስተምር ስለነበር ትሁት ሰዎች ጨካኝ የሃይማኖት መሪዎችን የሚፈሩትን ያህል እሱን አይፈሩትም ነበር። (ማቴዎስ 9:36) በእርግጥ የሱ ገራም ወይም የዋህ ዘዴዎች የሳቡት “በጎችን” ነበር እንጂ ክፉ “ፍየሎችን” አልነበረም። (ማቴዎስ 25:31-46፤ ዮሐንስ 3:16-21) ኢየሱስ በፍየል መሰሎቹ ግብዞች ላይ ኃይለኛ አነጋገር የተጠቀመ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች በዛሬው ጊዜ የአምላክን የፍርድ መልእክቶች ሲያውጁ ኢየሱስ የነበረው ማስተዋልና ሥልጣን ስለሌላቸው ገራምና የዋህ መሆን ይገባቸዋል። (ማቴዎስ 23:13-36) ዛሬም ሰዎች በየዋህነት የሚሰበከውን የመንግሥት መልእክት ሲሰሙ ኢየሱስ እንደሰሙት በግ መሰል ሰዎች “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ ሁሉ ያምናሉ።”—ሥራ 13:48
20.አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በየዋህነት ትምህርት ሲሰጠው የሚጠቀመው እንዴት ነው?
20 ለሌሎች በየዋህነት በመመሥከርና በማስተማር እንዲሁም ምክንያታዊ አስተሳሰብን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ ሥርዓቶችንና እውነትን ይዞ ወደነሱ በመቅረብ ጥሩ ውጤቶች ተገኝተዋል። ጴጥሮስ ሲጽፍ “ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ። ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት(ከጥልቅ አክብሮት ጋር) ይሁን” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 3:15) በየዋህነት መንፈስ ትምህርት የሚሰጠው ተማሪ ሐሳቡ በኃይለኛ አነጋገርና በክርክር ሳይበታተንና ሳይሰናከል በትምህርቱ ላይ ሊያተኩር ይችላል። እንደ ጳውሎስ በየዋህነት የሚያስተምሩ አገልጋዮች “አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ አንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም” ሊሉ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:3) አንዳንዴ ተቃዋሚዎችም እንኳን ሳይቀሩ በየዋህነት ለሚያስተምሯቸው ምላሽ ይሰጣሉ።
ከሁሉም ይፈለጋል
21, 22. የየዋህነት ሁሉንም የይሖዋ ሕዝቦች የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
21 የዋህነት ከይሖዋ ድርጅት ውጭ ያሉ ሰዎችን ለመሳብ ተብሎ ብቻ የሚለበስ መሆን አይገባውም። ይህ ባሕርይ በአምላክ ሕዝቦች መሃል ላለው ዝምድናም አስፈላጊ ነው። (ቆላስይስ 3:12-14፤ 1 ጴጥሮስ 4:8) የዋህ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በስምምነት አብረው ሲሠሩ ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ይታነጻሉ። ለሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የዋህነትና ሌሎችንም አምላካዊ ባሕሪያት ማሳየት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ለሁሉም የተሰጠው “አንድ ሕግ” ነው።—ዘፀአት 12:49፤ ዘሌዋውያን 24:22
22 የዋህነት ለአምላክ ሕዝቦች ሰላምና ደስታ ያስገኛል። ስለዚህ የዋህነት ሁሉም ክርስቲያኖች በቤት በጉባኤና የትም ቦታ የሚለብሱት ልብስ ከተሠራበት ድርና ማግ ውስጥ መገኘት ይኖርበታል። አዎ፣ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ የዋህነት መልበስ ያስፈልጋቸዋል።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የዋህ መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
◻ የዋህነት አንድን ጥበበኛ ምክር ሰጪ የሚመራው እንዴት ነው?
◻ የጥበበኛ መካሮች ብዛት ጥቅሙ ምንድን ነው?
◻ በየዋህነት መመሥከር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ሕዝቦች በግ መሰል ስለሆኑ በየዋህነት መያዝ ያስፈልጋቸዋል
[ምንጭ]
Garo Nalbandian
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዋህነት የይሖዋ ሕዝቦችን በተለያየ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች ለመመስከር ያስችላቸዋል