የይሖዋ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ
“በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስ ይሰጣቸው?”—ሉቃስ 11:13
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ተስፋ ምንድን ነው? ይህስ በእርግጥ የሚያጽናና የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?
በ32 እዘአ የበልግ ወራት ላይ ኢየሱስ በይሁዳ ምድር የምሥራቹን ሲሰብክ ሳለ ለደቀመዛሙርቱ ስለ ይሖዋ ለጋስነት ነገራቸው። አንዳንድ ጠንካራ ምሳሌዎችን ተጠቀመና “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” በማለት አስደናቂ ተስፋ ሰጣቸው።—ሉቃስ 11:13
2 እነዚህ በጣም የሚያጽናኑ ቃላት ናቸው! እነዚህ የመጨረሻ ቀናት ያመጡአቸውን መከራዎችና ጭንቀቶች ታግሠን በምንጸናበት፣ የሰይጣንንና የአጋንንቱን ጠላትነት በምንቋቋምበትና፣ የውዳቂ ሥጋችንን ደካማ ዝንባሌዎች በምንታገልበት ጊዜ ሁሉ አምላክ በመንፈሱ እንደሚያጠነክረን ማወቃችን በእርግጥም ልባችንን በደስታ ይሞላዋል። በእርግጥም ይህ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ በታማኝነት ለመጽናት ፈጽሞ አይቻልም ነበር። ይህ መንፈስ ማለትም ይህ የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል ያለውን ኃይል ቀምሰሃልን? የቱን ያህል ሊረዳህ እንደሚችል ተገንዝበሃልን? በዚህስ መንፈስ ሙሉ በሙሉ ትጠቀምበታለህን?
የመንፈስ ቅዱስ ኃይል
3, 4. መንፈስ ቅዱስ ያለውን ኃይል ግለጽ
3 በመጀመሪያ መንፈስ ቅዱስ ያለውን ኃይል እንገንዘብ። ወደ 1954 መለስ እንበል። በደቡብ ፓስፊክ በምትገኘው በቢኪኒ ኦቶል ላይ የአቶሚክ ቦምብ የፈነዳው በዚህ ዓመት ነበር። ቦምቡ እንደፈነዳ ወዲያው ያቺ ውብ ደሴት በከፍተኛ ቃጠሎ ተዋጠች። 15 ሚሊዮን ቲ ኤን ቲ የሚያክል ኃይል ባለው ፍንዳታ ፈራረሰች። ያ ሁሉ አጥፊ ኃይል ከየት መጣ? የቦምቡ አስኳል የተሠራበት የኡራኒየም ቅንጣትና ሃይድሮጅን በከፊል ወደ ኃይል በመለወጡ ምክንያት የተገኘ ኃይል ነበር። የሳይንስ ሊቃውንት በቢኪኒ ያደረጉትን ተቃራኒ አድርገው ቢሆን ኖሮስ ምን ይሆን ነበር? እሳታማውን ኃይል አፍነው በማስቀረት ጥቂት ፓውንዶች ወደሚመዝን ኡራኒየምና ሃይድሮጅን ለውጠውት ቢሆንስ? ይህን ለማድረግ ቢችሉ ኖሮ ከፍተኛ የሥራ ክንውን ይሆን ነበር። ሆኖም ይሖዋ “በመጀመሪያ ሰማይንና ምድርን ሲፈጥር” እጅግ በጣም ከፍተኛ በሆነ መጠን ይሁን እንጂ ያደረገው ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር ነበር።—ዘፍጥረት 1:1
4 ይሖዋ ከፍተኛ መጠን ያለው የኃይል ክምችት አለው። (ኢሳይያስ 40:26) ፍጥረትን በፈጠረበት ጊዜ ጽንፈ ዓለሙ የተሠራባቸውን ቁስ አካላት በሙሉ ለማስገኘት ይህን ታላቅ ኃይል ወደ ቁስ አካል ሳይለውጥ አልቀረም። በዚህ የፍጥረት ሥራው የተጠቀመው በምንድን ነው? በመንፈስ ቅዱስ ነው። “በይሖዋ ቃል ሰማዮች ጸኑ፤ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ” የሚል እናነባለን። (መዝሙር 33:6) ስለ ፍጥረት አፈጣጠር የሚገልጸውም የዘፍጥረት መጽሐፍ ትረካም “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ (ወዲያ ወዲህ እየተንቀሳቀሰ ተንሳፎ) ነበር” ይላል። (ዘፍጥረት 1:2) መንፈስ ቅዱስ በጣም ከፍተኛ የሆነ መጠን ያለው ኃይል ነው!
ተአምራዊ ሥራዎች
5. መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው በምን ከፍተኛ መንገዶች ነው?
5 ዛሬም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ በጣም ከፍተኛ በሆኑ መንገዶች እየሠራ ነው። የይሖዋን ሰማያዊ ድርጅት ይመራል። (ሕዝቅኤል 1:20, 21) መንፈስ ቅዱስም ከሃይድሮጅን ቦምብ እንደሚወጣው ኃይል የይሖዋን ጠላቶች ለማጥፋት ሊያገለግል ይችላል። ይሁን እንጂ በጣም አስደናቂ በሆኑ መንገዶች ሥራ ላይ የዋለባቸው ጊዜያት አሉ።—ኢሳይያስ 11:15፤ 30:27, 28፤ 40:7, 8፤ 2 ተሰሎንቄ 2:8
6. መንፈስ ቅዱስ ሙሴና የእሥራኤል ልጆች በግብጽ ምድር በነበሩበት ሁኔታ የደገፋቸው እንዴት ነው?
6 ለምሳሌ ያህል በ1513 ከዘአበ ይሖዋ የእሥራኤልን ልጆች ነፃ እንዲለቅ እንዲጠይቀው ሙሴን ወደ ፈርዖን ልኮት ነበር። ሙሴ ላለፉት 40 ዓመታት በምድያም ምድር በግ እረኛ ሆኖ ይኖር ነበር። ታዲያ ፈርዖን የአንድን እረኛ ቃል የሚሰማበት ምን ምክንያት አለው? ሙሴ የመጣው ብቻውን እውነተኛ አምላክ በሆነው አምላክ በይሖዋ ስም ስለነበረ ነው። ይህንም ለማረጋገጥ ይሖዋ ተአምራትን እንዲያደርግ ሥልጣን ሰጠው። እነዚህ ተአምራት በጣም አስደናቂ ከመሆናቸው የተነሣ የግብጽ ካህናትም እንኳን “ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው”a ብለው ለመናገርና ኃይሉን ለመቀበል ተገደው ነበር። (ዘጸአት 8:19) ይሖዋ በግብጽ ላይ አሥር መቅሰፍቶችን ያመጣ ሲሆን የመጨረሻው መቅሠፍት ፈርዖን የአምላክን ሕዝቦች ከግብጽ እንዲለቃቸው አስገድዶታል። ፈርዖንን በእልከኝነት ከሠራዊቱ ጋር ሆኖ የእሥራኤልን ሕዝብ ባሳደዳቸው ጊዜ እሥራኤላውያን ቀይ ባሕር በተአምር ተከፍሎላቸው በደረቅ ምድር ተሻገሩ። የግብጽ ሠራዊት ግን ተከትሏቸው ሲገባ በባሕሩ ተዋጠ።—ኢሳይያስ 63:11-14፤ ሐጌ 2:4, 5
7. (ሀ) መንፈስ ቅዱስ ተአምራት ያደረገባቸው አንዳንድ ምክንያቶች ምን ነበሩ? (ለ) በዛሬው ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የሚሠሩ ተአምራት ባይኖሩም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው መገኘታቸው የሚያጽናናን ለምንድን ነው?
7 አዎን ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት በሙሴ ዘመንና በሌሎች ዘመናትም ለእሥራኤላውያን ጥቅም ሲል ታላላቅ ተአምራት ሠርቷል። የእነዚህ ተአምራት ዓላማ ምን ነበር? የይሖዋን ዓላማ አራምደዋል፤ ስሙ እንዲታወቅ አድርገዋል፤ ኃይሉንም ገልጠዋል። አንዳንድ ጊዜም ለሙሴ እንደተደረገው አንድ ግለሰብ የይሖዋ ድጋፍ ያለው ወይም በይሖዋ የተላከ መሆኑን በማያጠራጥር መንገድ አረጋግጠዋል። (ዘጸአት 4:1-9፤ 9:14-16) ይሁን እንጂ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተፈጸሙት ተአምራት በጣም ጥቂቶች ነበሩ።b በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበሩት ሰዎች አብዛኞቹ አንድም ተአምር ለማየት አልቻሉም ነበር። በዛሬው ጊዜም ቢሆን ተአምራት አይፈጸሙም። ይሁን እንጂ ዛሬ የማይዘለቁ መስለው ከሚታዩ ችግሮች ጋር በምንታገልበት ጊዜ ይሖዋን በእምነት ከጠየቅነው ሙሴን በፈርዖን ፊት የደገፈውንና ለእሥራኤላውያንም በቀይ ባሕር ላይ መንገድ የከፈተላቸውን ያንኑ መንፈስ እንደሚሰጠን ማወቃችን አያጽናናምን?—ማቴዎስ 17:20
በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ ጽሑፎች
8. በአሥርቱ ትእዛዛት መሰጠት ረገድ መንፈስ ቅዱስ የነበረው ሚና ምን ነበር?
8 ሙሴ እሥራኤላውያን ከግብጽ ነፃ ከወጡ በኋላ ይሖዋ ከእነሱ ጋር ቃል ኪዳን ወደገባበትና ሕጉንም ወደሰጣቸው ወደ ሲና ተራራ መራቸው። በሙሴ በኩል የተሰጣቸው የዚህ ሕግ ማዕከላዊ ክፍል ወይም አስኳል የሆኑት አሥርቱ ትዕዛዛት ነበሩ። የእነዚህ ትዕዛዛት የመጀመሪያ ቅጅም በድንጋይ ጽላት ላይ የተቀረጸ ነበር። ይህ ጽላት የተጻፈው እንዴት ነበር? በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “(ይሖዋም) ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምሥክር ጽላቶች ሰጠው” ይላል።—ዘጸአት 31:18፤ 34:1
9, 10. መንፈስ ቅዱስ የዕብራውያን ቅዱሳን ጽሑፎች በሚጻፉበት ጊዜ የሥራ ድርሻ የነበረው እንዴት ነበር? ይህስ በኢየሱስ ደቀመዛሙርት አነጋገር ላይ በግልጽ የታየው እንዴት ነበር?
9 ከአሥርቱ ትዕዛዛት በተጨማሪም ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት የእሥራኤልን ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ሕይወት የሚመሩ በመቶ የሚቆጠሩ ሕጎችንና ሥርአቶችን ሰጥቶአቸዋል። ገና ወደፊት የሚጨመሩ ጽሑፎችም ነበሩ። በመቶ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነህምያ በሕዝብ ፊት ባቀረበው ጸሎት “ነገር ግን ብዙ ዓመታት (እሥራኤላውያንን) ታገሥሃቸው። በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው” በማለት መሥክሯል። (ነህምያ 9:5, 30) እነዚህ ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተናገሩአቸው ብዙ ትንቢቶች በጽሑፍ ተመዝግበዋል። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ ታሪኮችንና ከልብ የመነጩ የምስጋና መዝሙሮችን በጽሑፍ እንዲያሠፍሩ ታማኝ ሰዎችን ገፋፍቷቸዋል።
10 ጳውሎስ “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ አለበት” ባለ ጊዜ ስለእነዚህ ጽሑፎች መናገሩ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ 2 ሳሙኤል 23:2፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21) በእርግጥም የመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ደቀመዛሙርት እነዚህን ቅዱሳን ጽሑፎች ሲጠቅሱ “መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው” “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ” ወይም ደግሞ “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል” በሚሉትና በመሳሰሉት አባባሎች ይጠቀሙ ነበር። (ሥራ 1:16፤ 4:25፤ 28:25, 26፤ ዕብራውያን 3:7) የቅዱሳን ጽሑፎችን መጻፍ ይመራ የነበረው ያው መንፈስ እነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች እኛንም ይመሩንና ያጽናኑን ዘንድ ተጠብቀው እንዲቆዩ ማድረጉ እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ነው!—1 ጴጥሮስ 1:25
በመንፈስ ቅዱስ ላይ መመካት
11. የመገናኛው ድንኳን በሚሠራበት ጊዜ የትኛው የመንፈስ ሥራ ታይቶአል?
11 እሥራኤላውያን በሲና ተራራ አጠገብ ሠፍረው ሳሉ ለእውነተኛ አምልኮ ማዕከል የሚሆን የመገናኛ ድንኳን እንዲሠሩ ይሖዋ አዘዛቸው። ታዲያ ይህን የሚፈጽሙት እንዴት ነበር? ሙሴ ለእሥራኤል ልጆች “እዩ፤ ይሖዋ ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር የልጅ ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠራው። በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በዕውቀትም የእግዚአብሔር መንፈስ ሞላበት” ብሏቸዋል። (ዘጸአት 35:30, 31) ባስልኤል የነበረውን የተፈጥሮ ችሎታና ብልሃት መንፈስ ቅዱስ አጠንክሮለት ስለነበረ የዚህን አስደናቂ ሕንፃ አሠራር በተሳካ ሁኔታ ሊቆጣጠር ችሏል።
12. ከሙሴ ዘመን በኋላ መንፈስ ቅዱስ ግለሰቦችን በከፍተኛ መንገድ ያጠነከራቸው እንዴት ነበር?
12 ቆየት ባለው ዘመንም የይሖዋ መንፈስ በሳምሶን ላይ ወርዶ እሥራኤላውያንን ከፍልስጤማውያን እጅ ለማዳን የሚያስችል ከፍተኛ ኃይል ሰጥቶታል። (መሳፍንት 14:5-7, 9፤ 15:14-16፤ 16:28-30) ከዚያ በኋላም ቆየት ብሎ ሰለሞን የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ንጉሥ በሆነ ጊዜ ልዩ የሆነ ጥበብ ተሰጥቶት ነበር። (2 ዜና 1:12, 13) በሰለሞን ግዛት ሥር እስራኤላውያን ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን በልጽገው ነበር። በዚህም ምክንያት በሰለሞን የግዛት ዘመን የተገኙት አስደሳች ሁኔታዎች የአምላክ ሕዝቦች ታላቁ ሰለሞን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ሥር ለሚያገኙአቸው በረከቶች ምሳሌ ሆነዋል።—1 ነገ. 4:20, 25, 29-34፤ ኢሳይያስ 2:3, 4፤ 11:1, 2፤ ማቴዎስ 12:42
13. መንፈስ ባስልኤልን፣ ሳምሶንንና ሰለሞንን እንዳጠነከራቸው የሚገልጸው ታሪክ እኛንስ በዛሬው ጊዜ የሚያበረታታን እንዴት ነው?
13 ይሖዋ እኛም ይህንኑ መንፈስ እንድናገኝ ማስቻሉ በጣም ትልቅ በረከት ነው። የተሰጠንን አንድ አይነት ሥራ ለመፈጸም ወይም በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ብቃት የሌለን ሆኖ በሚሰማን ጊዜ ይሖዋ ለባስልኤል የሰጠውን ዓይነት መንፈስ እንዲሰጠን ልንጠይቀው እንችላለን። በበሽታ ስንሰቃይ ወይም ስደት ሲደርስብን ለሳምሶን እንግዳ የሆነ ታላቅ ኃይል የሰጠው የይሖዋ መንፈስ በተአምራዊ መንገድ ባይሆንም ብርታትና ጥንካሬ ይሰጠናል። ከባድ ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ፣ ወይም አስፈላጊ ውሣኔ ማድረግ በሚኖርብን ጊዜ ለሰለሞን ታላቅ ጥበብ የሰጠውን ይሖዋን የጥበብ እርምጃ እንድንወስድ እንዲረዳን ልንጠይቀው እንችላለን። ከዚያም እንደ ጳውሎስ “ኃይል በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ለማለት እንችላለን። (ፊልጵስዩስ 4:13) ያዕቆብ “ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፤ ለእርሱም ይሰጠዋል” ሲል የተናገረው የተስፋ ቃል ለእኛም ይፈጽምልናል።—ያዕቆብ 1:5
14. በጥንት ዘመንም ሆነ ዛሬ የመንፈስ ቅዱስን ድጋፍ እነማን አግኝተዋል?
14 በተጨማሪም ሙሴ ሕዝቡን በሚዳኝበት ጊዜ የይሖዋ መንፈስ በሱ ላይ ነበር። ሙሴን የሚያግዙ ሌሎች ሰዎች በተሾሙ ጊዜም ይሖዋ “በአንተ ላይ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ። አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ” ብሎ ነበር። (ዘኁልቁ 11:17) በመሆኑም እነዚያ ሰዎች በራሳቸው ጥንካሬና ብርታት ብቻ መሥራት አላስፈለጋቸውም። መንፈስ ቅዱስ ደግፏቸዋል። ከዚያ በኋላም ቢሆን የይሖዋ መንፈስ በሌሎች ግለሰቦች ላይ ሆኖ ስለሰራባቸው ወቅቶች እናነባለን። (መሳፍንት 3:10, 11፤ 11:29) ሳሙኤል ዳዊትን የእሥራኤል ንጉሥ እንዲሆን በቀባው ጊዜ ስለሆነው ነገር ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የይሖዋም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ።” (1 ሳሙኤል 16:13) ዛሬም የቤተሰብ፣ የጉባኤ፣ ወይም ድርጅታዊ የሆኑ ከባድ ኃላፊነቶች ያሉባቸው ሰዎች ግዴታዎቻቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ የአምላክ መንፈስ አገልጋዮቹን እንደሚደግፋቸው በማወቃቸው ሊጽናኑ ይችላሉ።
15. መንፈስ ቅዱስ የይሖዋን ድርጅት (ሀ) በሐጌና በዘካርያስ ዘመን (ለ) በዛሬው ዘመን ያጠነከረው እንዴት ነው?
15 ከሙሴ ዘመን በኋላ አንድ ሺህ ዓመት ያህል ቆይቶ ከእሥራኤል ልጆች መሃል ታማኞች የሆኑት ቤተ መቅደሱን እንደገና የመሥራት ተልእኮአቸውን ለመፈጸም ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰዋል። (እዝራ 1:1-4፤ ኤርምያስ 25:12፤ 29:14) ይሁን እንጂ አስቸጋሪ እንቅፋቶች ስላጋጠሙአቸው ለብዙ ዓመታት ቤተ መቅደሱን እንደገና ለመሥራት አልቻሉም ነበር። በመጨረሻም ይሖዋ አይሁዳውያን በራሳቸው ብርታትና ኃይል እንዳይመኩ ለማሳሰብ ነቢያቱን ሐጌንና ዘካርያስን አስነሣላቸው። ታዲያ ሥራው የሚከናወነው እንዴት ነበር? “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።” (ዘካርያስ 4:6) ቤተ መቅደሱም በአምላክ መንፈስ ድጋፍ ተሠራ። ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክ ሕዝቦች ብዙ ሥራ ለማከናወን ችለዋል። የምሥራቹ ስብከት በምድር በሙሉ ተስፋፍቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ እውነትና ስለ ጽድቅ በመማርና በመሠልጠን ላይ ናቸው። በየጊዜው ታላቅ ስብሰባዎች ይዘጋጃሉ። የመንግሥት አዳራሾችና ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይሠራሉ። ይህ ሁሉ ሥራ በአብዛኛው የተከናወነው ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ እያጋጠመ ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሥራ ሁሉ የሚፈጸመው በወታደራዊ ኃይል ወይም በሰው አቅም ሳይሆን በአምላክ መንፈስ መሆኑን ስለሚያውቁ ተስፋ አልቆረጡም።
የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን
16. የቅድመ ክርስትና የይሖዋ አገልጋዮች በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ረገድ ምን ተሞክሮ ነበራቸው?
16 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ከክርስትና በፊት የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች የአምላክ መንፈስ ያለውን ኃይል በሚገባ ተገንዝበው ነበር። የተጣሉባቸውን ከባድ ግዴታዎች እንዲፈጽሙና የአምላክን ፈቃድ እንዲያከናውኑ እንዲረዳቸው በአምላክ መንፈስ ላይ ተመክተዋል። ሕጉና ሌሎች ቅዱሳን ጽሑፎችም በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነትና መሪነት የተጻፉ መሆናቸውንና በዚህም ምክንያት የአምላክ ቃል መሆናቸውን አውቀው ነበር። (መዝሙር 119:105) በክርስትና ዘመን የነበሩት የአምላክ አገልጋዮችስ?
17, 18. በክርስትና ዘመን እንዴት ያሉ የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ተአምራዊ መግለጫዎች ታይተዋል? እነዚህ ተአምራዊ መግለጫዎችስ ለምን ዓላማ አገልግለዋል?
17 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠርም የመንፈስ ቅዱስ አስደናቂ ሥራዎች ታይተው ነበር። ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ትንቢት ይናገሩ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:1, 3) ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ እሱ የተናገራቸውን ነገር እንደሚያስታውሳቸውና ተጨማሪ የእውነት ገጽታዎችንም እንደሚያስተምራቸው በገባላቸው ቃል ወይም ተስፋ መሠረት በርካታ መጻሕፍት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተጽፈዋል። (ዮሐንስ 14:26፤ 15:26, 27፤ 16:12, 13) በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን በሰፊው እንደምንወያይበት ብዙ ተአምራትም ተፈጽመዋል። በእርግጥም በመጀመሪያው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ብዙ አስደናቂ ተአምራት ተፈጽመዋል። በ2 ከዘአበ አካባቢ ላይ አንድ ልዩ ወንድ ልጅ የሚወለድበት ጊዜ ደረሰ። ለዚህም ምልክት እንዲሆን እናቱ ድንግል መሆን ነበረባት። ይሁን እንጂ አንዲት ድንግል እንዴት ልትጸንስ ትችላለች? በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነበር። ታሪኩ “የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበር፣ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ጸንሳ ተገኘች” ይላል።—ማቴዎስ 1:18፤ ሉቃስ 1:35, 36
18 ኢየሱስ ካደገ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አጋንንት ያወጣ፣ ሕሙማንን ይፈውስ፣ ሙታንንም ያስነሣ ነበር። ከተከታዮቹም መካከል አንዳንዶቹ ተአምራትንና ድንቅ ሥራዎችን ያደርጉ ነበር። እነዚህ ልዩ ችሎታዎች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ነበሩ። እነዚህ ተአምራቶች የተደረጉበት ዓላማ ምን ነበር? ቀደም ባሉት ዘመናት እንደተፈጸሙት ተአምራት የአምላክን ዓላማዎች አራምደዋል፣ ኃይሉንም ገልጸዋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ከአምላክ የተላከ መሆኑን አረጋግጠዋል። በኋላም የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክ ምርጥ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጠዋል።—ማቴዎስ 11:2-6፤ ዮሐንስ 16:8፤ ሥራ 2:22፤ 1 ቆሮንቶስ 12:4-11፤ ዕብራውያን 2:4፤ 1 ጴጥሮስ 2:9
19. መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለፈጸሙአቸው ተአምራት በሚናገረው ታሪክ እምነታችን የሚጠናከረው እንዴት ነው?
19 ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቶቹ ተአምራዊ የመንፈስ አሠራር መግለጫዎች በጉባኤው የልጅነት ወይም የጨቅላነት ዕድሜ ብቻ የሚኖሩና ወደፊት የሚያልፉ መሆናቸውን ተናግሮ ስለነበር ዛሬ በመንፈስ ቅዱስ የሚሠሩ እንዲህ ዓይነት ተአምራቶችን አናይም። (1 ቆሮንቶስ 13:8-11) እንደገናም በኢየሱስና በሐዋርያቱ የተፈጸሙት ተአምራት በታሪክነት ከመታወስ የበለጠ ጥቅም አላቸው። በኢየሱስ አገዛዝ ሥር በአዲሲቱ ዓለም ውስጥ በሽታና ሞት እንደማይኖሩ አምላክ በሰጠን ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ያጠነክሩልናል።—ኢሳይያስ 25:6-8፤ 33:24፤ 65:20-24
ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚገኝ ጥቅም
20, 21. ከመንፈስ ቅዱስ ዝግጅቶች ተጠቃሚ ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?
20 ይህ መንፈስ በእርግጥም በጣም ታላቅ ኃይል ያለው ነው። ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉት ክርስቲያኖች ከዚህ መንፈስ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው? መጀመሪያ ነገር ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን መለመን እንደሚኖርብን ተናግሯል። ታዲያ ለምን አንለምንም? ይሖዋ ይህን ድንቅ ስጦታ እንዲሰጥህ ጭንቀት በሚያጋጥምህ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ለምነው። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ እንዲያነጋግርህ መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ። (ከዕብራውያን 3:7 ጋር አወዳድር) መንፈስ ቅዱስ በሕይወትህ ውስጥ ተጽዕኖ ማሳደር ይችል ዘንድ በምታነበው ነገር ላይ አሰላስል። (መዝሙር 1:1-3) በተጨማሪም በአምላክ መንፈስ ላይ ከሚታመኑ ሰዎች ጋር በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች አብረህ ተሰብሰብ። መንፈስ ቅዱስ አምላካቸውን “ይሖዋን በጉባኤ” የሚባርኩ ሰዎችን አብዝቶ ያጠነክራቸዋል፣ ያበረታቸዋልም።—መዝሙር 68:26
21 በእርግጥም ይሖዋ ለጋስ አምላክ አይደለምን? መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠን ከለመንነው እንደሚሰጠን ነግሮናል። በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ልናገኘው የምንችለው ይህ ብርቱ አጋዥ ኃይል እያለልን በራሳችን ጥበብና ብርታት መመካት እንዴት ያለ ታላቅ ሞኝነት ነው! ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከአምላክ መንፈስ ጋር ግንኙነት ያላቸውና እኛን የሚነኩ ሌሎች ጉዳዮች አሉ። እነዚህ ጉዳዮችም በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን ውይይት ይደረግባቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “የእግዚአብሔር ጣት” የሚለው አገላለጽ አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው መንፈስ ቅዱስን ነው። ከሉቃስ 11:20 እና ማቴዎስ 12:28 ጋር አወዳድሩ።
b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ተአምራት አብዛኞቹ በሙሴ፣ በኢያሱ፣ በኤልያስና በኤልሳዕ እንዲሁም በኢየሱስና በሐዋርያቱ ዘመን የተፈጸሙ ናቸው።
የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልትመልስ ትችላለህን?
◻ ይሖዋ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያለውን ቁስ አካል በሙሉ የፈጠረው እንዴት ነው?
◻ በቅድመ ክርስትና ዘመን መንፈስ ቅዱስ የሠራባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ መንፈስ ቅዱስ በጥንት ዘመን ያደረጋቸውን ነገሮች ማወቃችን ዛሬ የሚያጽናናን እንዴት ነው?
◻ ከመንፈስ ቅዱስ ዝግጅቶች ተጠቃሚ የምንሆነው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለሳምሶን ከሰው በላይ ጥንካሬ የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ለእኛም ለሚያስፈልገን ነገር ሁሉ ኃይል ሊሰጠን ይችላል።