የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 2/15 ገጽ 21-25
  • የሕንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ምሥራቹን ሰሙ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሕንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ምሥራቹን ሰሙ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • የመጀመሪያ ቆይታችን፣ ሮድሪገዝ
  • ርቀው የሚገኙት የሴሼልስ ደሴቶች
  • ወደ ሪዩኒየን ደሴት መመለስ
  • ማዮቴ፣ የሽቶ ደሴት
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 2/15 ገጽ 21-25

የሕንድ ውቅያኖስ ደሴቶች ምሥራቹን ሰሙ

ከማደካስካር ትዩዩ በሆነ የቅስት ቅርጽ ተያይዘው የሚገኙና በሕንድ ውቅያኖስ ምዕራባዊ ዳርቻ 2.4 ሚሊዮን ካሬ ኪሎሜትር ስፋት ባለው ውቅያኖስ ላይ የሮድሪገዝ፣ የሞሪሸስ፣ የሪዩኒየን፣ የሴሸልስ፣ የማዮቴና የኮሞሮስ ደሴቶች ተሰራጭተው ይገኛሉ። እነዚህ ደሴቶች ይህን በሚያክል ሰፊ ቦታ ላይ ተሠራጭተው የሚገኙ ቢሆኑም ጠቅላላ የመሬት ስፋታቸው 4,480 ካሬ ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። በእነዚህ ደሴቶች ላይ 2.3 ሚልዮን ሕዝብ ስለሚኖር በዓለም ላይ የሕዝብ ክምችት ከሚበዛባቸው ደሴቶች የሚመደቡ ናቸው።

ከእነዚህ ሕዝቦች መካከል ለደሴቲቱ ነዋሪዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ተግተው የሚሠሩት 2,900 የሚያክሉ የይሖዋ ምስክሮች ይገኛሉ። እነዚህ ምስክሮች በቦታ ተራርቀው የሚኖሩ በመሆናቸው በተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚደረግላቸውን ጉብኝትና በቫካኦስ በሚገኘው የሞሪሸስ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚዘጋጅላቸውን ዓመታዊ ስብሰባ በጣም ያደንቃሉ። በእነዚህ ወቅቶች “ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፣ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖር ሆይ፣ [ለይሖዋ (አዓት)] አዲስ መዝሙር፣ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ” የሚሉትን የኢሳይያስ 42:10 ቃላት ትርጉም ያጣጥማሉ።

በቅርቡ ከቅርንጫፍ ቢሮው የተላኩ ተወካዮች ጉባኤዎችን ለመጎብኘትና “በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” የሚለውን በ1 ጴጥሮስ 1:15 ላይ የተመሠረተውን አጠቃላይ መልዕክት የሚገልጹ ተከታታይ ንግግሮችን የያዘ የአንድ ቀን ልዩ ስብሰባ ለማድረግ ወደ ደሴቶቹ ተጉዘው ነበር። ሰፊውን ውቅያኖስ የሚያቋርጠው ጉዞ የሚደረገው አብዛኛውን ጊዜ በአየር ትራንስፖርት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በዘመናዊ የጃምቦ ጀቶች በሌሎች ጊዜያት ደግሞ አነስተኛ በሆኑ አውሮፕላኖች ነው። ትናንሽ ጀልባዎችም የሚያገለግሉበት ግዜ አለ። ከእኛ ጋር ኑና የሩቆቹ የሕንድ ውቅያኖስ ደሴቶች የምሥራቹን እንዴት እንደሚሰሙ ተመልከቱ!

የመጀመሪያ ቆይታችን፣ ሮድሪገዝ

ከሞሪሺየስ ተነስተን አንድ ሰዓት ተኩል ከበረርን በኋላ አንድ የባሕር ውስጥ ጉብታ አየን። ይህ ጉብታ በሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ትንሽ ነጥብ የምታህል ምድር የሚከበውን የባሕር ዳርቻ ክፈፍ የሚያሳይ ነበር። በመጀመሪያ ያረፍነው እዚህ ሮድሪገዝ ደሴት ላይ ነበር።

አውሮፕላን ጣቢያው የተሠራው ፖይንት ኮሬይል ተብሎ በሚጠራ ከመሬት ወደ ባሕሩ ሾጠጥ ብሎ በወጣ የአለት ቁልል ላይ ነው። በዚህ አካባቢ አለቱ በጣም ትላልቅ ከመሆኑ የተነሣ እየተጠረበ ለሕንፃ ሥራ ያገለግላል። አንድ አነስተኛ አውቶቡስ ከአውሮፕላን ጣቢያው ጠባብና ጠመዝማዛ በሆነ መንገድ ወደ ዋናው የወደብ ከተማ ወደ ማቱሪን ወሰደን። አንድ ቦታ ላይ ሆኖ የባሕር ውስጥ ጉብታዎችንና በደሴቱ ዳርቻ የሚገኘውን ባሕር አሻግሮ ማየት ይቻላል። የዝናቡ ወቅት ያለፈው በቅርቡ ስለነበር የኮረብታዎቹ ጥጋ ጥግ በሣር ተሸፍኖ ሣሩን የሚግጡ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎች አልፎ አልፎ ተመስገውበት ይታያሉ።

የአንድ ቀን ልዩ ስብሰባችንን ያደረግነው በፖርት ማቱሪን ከተማ መሃል በሚገኝ በአንድ አነስተኛና ንጹሕ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ነበር። ሥራው በሮድሪገዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው በ1964 ነበር። አሁን በ37,000 ሕዝብ መሃል 36 የምሥራች አስፋፊዎች ይገኛሉ። 53 ሰዎች በስብሰባው ሲገኙ አንድ የ18 ዓመት ወጣት ሲጠመቅ ማየት በጣም የሚያስደስት ነበር። የወጣቱ እናት ማንበብና መጻፍ የማትችል ብትሆንም እውነትን የተቀበለችው በ1969 ነበር። የቤተሰብ ተቃውሞ ቢደርስባትም ይሖዋን በማገልገል ጸንታለች። አሁን ከልጆችዋ መካከል ሁለቱ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነዋል።

ከስብሰባው በኋላ አንድ ሣምንት ያህል በደሴቲቱ እየሰበክን አሳለፍን። ለስብከቱ የተጠቀምንበት ቋንቋ የኛው ቋንቋ የሆነውን የሞሪሺየስ ክሬዎል ነው። በዚህ በሮድሪገዝ ደሴትም የሚነገረው ይኸው ቋንቋ ነው። ከፍታ ካለው ቦታ ተነስቶ እስከ ውቅያኖሱ በሚያሽቆለቁለው አረንጓዴ ሸለቆ ወደሚገኘው ክልላችን የምንደርሰው በአውቶቡስና ከዚያም ጥቂት የእግር መንገድ በመጓዝ ነበር። ከጀርባችን የሚታየው ሰማያዊ ባሕር፣ ነጩ የአለት ጉብታና ደማቅ ሰማያዊ የሆነው ውቅያኖስ በጣም የሚያስደስቱ ናቸው። በጣም ባማረውና ባልተበከለው አየር ስለተበረታታን ድካም አይሰማንም ነበር።

በመስኩ የሚያልፉ ትናንሽ የእግር መንገዶችን ተከትለን ረግረጉን ጅረት ካቋረጥን በኋላ በሸለቆው ውስጥ ወደሚገኙት ብዙ ትናንሽ ቤቶች ደረስን። በእያንዳንዱ ቤት ልባዊ የሆነ አቀራረብ ተደረገልን። ስለዚህ ከባለቤቶቹ ጋር በቅርቡ ስለሚመጡት የመንግሥት ተስፋዎች ለመነጋገር ቻልን። ብዙም ሳንቆይ ወደ ሸለቆው ታችኛ ክፍል ስለደረስን ወደ ቤት የምንመለስበት ጊዜ ደረሰ። ወደመጣንበት ለመመለስ ለብዙ ሰዓቶች በእግራችን መጓዝ ነበረብን። ይሁን እንጂ የአካባቢው ሰዎች ያደረጉልን መስተንግዶ ያንን አቀበት በእግራችን ከመኳተን አዳነን። በጂፕ መኪናቸው ላይ ተሳፍረን እንድንሄድ ጋበዙን።

ከዚህ አድካሚ ጉዞ በኋላ በቫኮአስ ወደሚገኘው ውብ የቤቴል ቤታችን ስንመለስ በጣም ደስ አለን። በቫኮአስ ሁለት የልዩ ስብሰባ ቀኖች በማዘጋጃ ቤቱ አዳራሽ ሊደረጉ ፕሮግራም ወጥቶ ነበር። በመጀመሪያው ቀን 760 ሰዎች ተገኙ። እነሱም በደሴቲቱ ከሚገኙት 12 ጉባኤዎች ከስድስቱ የመጡ ነበሩ። በሚቀጥለው ቀን ያንኑ ፕሮግራም ከሌሎቹ 6 ጉባኤዎች የመጡ 786 ሰዎች አዳመጡ። በሣምንቱ መጨረሻ አራት አዳዲስ ሰዎች ተጠመቁ። ለደሴቲቱ ነዋሪዎች የምሥራቹን የሚያዳርሱ 30 ልዩ አቅኚዎችና 50 የዘወትር አቅኚዎች አሉ።

ርቀው የሚገኙት የሴሼልስ ደሴቶች

ወዲያው 1600 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው በክሪዮል ቋንቋ ዚል አልዋኒየን ሴስል ወደምትባለው በሴሼልስ ደሴቶች ውስጥ ወደምትገኘው የማሔ ደሴት በቀጥታ የምንበርበት ጊዜ ደረሰ። ዚል አልዋኒየን ሴሰል ማለት “ሩቅ የሚገኙ የሴሼልስ ደሴቶች” ማለት ነው። በርቀቱ ምክንያት ቅርንጫፍ ቢሮው የሚያዘጋጀው በዓመት ሁለት ጉብኝቶችን ብቻ ነው። የልዩ ስብሰባው ቀንና የክልል ስብሰባው በጸደይ ወራት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይደረጋሉ። የወረዳ ስብሰባው በዓመቱ ውስጥ ዘግየት ብሎ ይደረጋል። አሁን ይኸውና በጥቅምት አጋማሽ ላይ የወረዳ ስብሰባውን ለማድረግ እዚህ ተገኝተናል። ቀጥሎም ለአንድ ሣምንት ያህል ጉባኤውን እንጎበኛለን። እዚህም የሞሪሺየስን ክሪዮል ለመጠቀም እንችላለን።

ፓርስሊንና ላ ዲግ ከሚባሉት የአቅራቢያው ደሴቶች የመጡ ወንድሞች ቀደም ብለው ደርሰዋል። በስብሰባው ላይ 12 ብሔረሰቦችን የወከሉ ሰዎች መገኘታቸው በጣም አስደስቶናል። የስብሰባው ቦታ አሁን ወደ መንግሥት አዳራሽነት የተለወጠው በፊት ግን የአንድ ወንድም መኪና ማቆሚያ የነበረ ነው። በፕሮግራሙ ክፍል ለመውሰድ ብቃት ያላቸው ጎብኚ ወንድሞችን ጨምሮ ስድስት ወንድሞች ብቻ ስለሆኑ አንዳንዶቹ በአራቱም ቀናት ብዙ ንግግሮችን የመስጠት መብት አግኝተው ነበር። 81 አስፋፊዎች በመጨረሻው የስብሰባ ቀን 216 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ሲያዩ በጣም ተደስተዋል።

ከስብሰባው በኋላ ከማሔ በስተ ሰሜናዊ ምሥራቅ 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ፕራስሊን ለመሄድ በአንድ ጀልባ ላይ ተሳፈርን። የ18 ሜትር ቁመት የነበራት ጀልባ ታካማክ ከሚባል ዛፍ ግንድ የተሠራች ናት። ይህች የምታምር ጀልባ 50 መንገደኞችንና 400 ኩንታል ጭነት ልትሸከም ትችላለች። የማሄን ወደብ ለቅቀን የጀልባዋን ፊት ከሩቅ አድማስ ላይ ወደምትታየው ፕራስሊን ስናዞር የዲዚል ሞተሩ ከሁለቱ ምሰሶዎች ላይ በሚውለበለቡት ነጫጭ ሸራዎች እየታገዘ ጀልባዋን ሲያፈናጥር ይሰማናል።

ሁለት ሰዓት ተኩል ለሚያክል ጊዜ ከተጓዝን በኋላ በውቢትዋ የሴንት አን ወደብ ወደሚገኘው ጸጥ ያለ ባሕር ለመግባት ወደ ውጭ ወጣ ያለ አንድ የአለት ጉብታ ዞርን። ገና ቆም ስንል ወንድሞቻችን ሲጠብቁን ተመለከትን። በዚህች ትንሽ ደሴት ላይ 13 አስፋፊዎች አሉ። ስምንት እንግዶች ደግሞ ከሌሎቹ የደሴቲቱ ክፍሎች መጥተዋል። ትንሽዋ አዳራሽ ልዩ ንግግሩን ለመስማት በተሰበሰቡ 39 ሰዎች ተሞልታ በማየታችን በጣም ተደሰትን። ወደፊት ጥሩ ዕድገት እንደሚገኝ ይጠቁማል።

እዚህ ፕራስሊን ውስጥ ሳለን ውቢቷን ቫሌ ዴማይን መጎብኘት ነበረብን። ከኮ ዴመር የተባለው ዛፍ የሚበቅለው እዚህ ነው። ይህ ዛፍ በትልቅነቱ ከዓለም አንደኛ የሆነውን 20 ኪሎ የሚመዝን ፍሬ ያፈራል። በጫካው አረንጓዴና ቀዝቃዛ ጥላዎች ሥር ሆነን በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች የሚገኙትን እነዚህን ዛፎች ተመለከትን። ከሁሉ ረጅም የሆነው ዛፍ በ1968 ሲለካ 39 ሜትር ርዝመት እንደነበረው መንግሥት የሰቀለው ማስታወቂያ ይገልጻል። ከእነዚህ ዛፎች አንዳንዶቹ 800 ዓመት ዕድሜ እንደሚኖራቸው ይገመታል። አንዱ ዛፍ ፍሬ ለማፍራት 25 ዓመት ይወስድበታል። ፍሬው እስኪበስል ደግሞ 7 ዓመት ይቆያል። ለጎብኚዎች የሚታደለው ብሮሹር “ፎቶግራፍ ብቻ አንሱ፤ የእግራችሁን ዱካ ብቻ ትታችሁ ሂዱ” ብሎ ማስጠንቀቁ አያስደንቅም።

በሚቀጥለው ቀን ጧት በ1 ሰዓት ላ ዲግ ወደምትባል ትንሽ ደሴት ለመሄድ ጀልባ ላይ ተሣፈርን። በባሕር ወሽመጡ ላይ ብዙ ትናንሽ ጀልባዎች ከበው ቆመዋል። 2,000 የሚያክሉትን የደሴቷ ነዋሪዎች ከውጪው ዓለም ጋር የሚያገናኙት እነዚህ ጀልባዎች ናቸው። ከ1875 ጀምሮ ከስዊዘርላንድ መጥተው እዚህች ደሴት ላይ መኖር የጀመሩ በዕድሜ የገፉ ባልና ሚስት አገኘን። በበሬ የሚጎተቱ ጋሪዎችን ከመሳፈር ይልቅ በዝናብና በባሕር ሞገድ ብዙ በመታጠቡ ምክንያት የለሰለሰውን ደማቅ ጥቁር አለት እያየን በባሕሩ ዳር ዳር ሄድን። የሽርሽር ቁርስ ከበላን በኋላ ፍላጎት ወዳሳዩ ሰዎች ለመሄድ ብርቅ የሆኑት ዝንብ ለቃሚ ጥቋቁር ወፎች ባሉበት አንድ ትንሽ ክልል አልፈን ተጓዝን። በክሪዮል ቋንቋ የሚሰጠውን ንግግር ለማዳመጥ አሥራ ሦስት ሰዎች ተሰብስበዋል። መንፈሳዊ ዕድገት ለማድረግ እንዲችሉ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ዝግጅት በሙሉ ያጠናቀቁ ባልና ሚስት አገኘን። በእርግጥም ይሖዋ በእነዚህ ሩቅ ደሴቶች ያሉትንም ሳይቀር ከአሕዛብ ሁሉ ምርጥ ምርጦቹን እየሰበሰበ ነው።

ወደ ሪዩኒየን ደሴት መመለስ

ሪዩኒየን በዚህ ጉዞ ላይ ከጎበኘናቸው ደሴቶች ሁሉ በጣም የለማችና የሰለጠነች ደሴት ናት። ወደ የብሱ ስንቀርብ ከዋናው ከተማ ከሴንት ዴኒስ በመጡ መኪናዎች የተጨናነቀውን ባለ አራት ረድፍ ዋና ጎዳና አየን። በባሕሩና በተራራው መሃል ያለውን ቦታ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ሞልተውታል። ይህች ደሴት የ580,000 ሕዝቦች መኖሪያ ናት። ለመንግሥቱ ምስክርነትም ምርታማ መስክ ሆናለች። (ማቴዎስ 9:37, 38) በአሁኑ ጊዜ በ21 ጉባኤዎች ውስጥ 2,000 የሚያክሉ ቀናተኛ አስፋፊዎች አሉ።

የልዩ ስብሰባው ቀን አንድ ትልቅ ጣራ ባለው እስታዲየም ተደረገ። 3,332 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ስናይ ተደሰትን። ራሳቸውን ለጥምቀት ያቀረቡ 67 አዳዲስ ሰዎችን ለማግኘት መቻሉ ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነበር! በደሴቲቱ ላይ ከሚኖሩ ሚስዮናውያን ጋር አብረን በመቆየት ከተደሰትን በኋላ መሄድ ወዳለብን ወደሚቀጥለው ቦታ ለመሄድ ተነሣን።

ማዮቴ፣ የሽቶ ደሴት

ከሁለት ሰዓት በረራ በኋላ 40 ሰዎች የሚጭነው ጀት አውሮፕላናችን የማዮቴ ዋና ከተማ ከሆነችው ከዛኡድዚ ጋር 2 ኪሎሜትር ርቀት ባለው በውሃው ላይ ከፍ ብሎ በተሠራ የመኪና መንገድ በሚገናኘው በፓማንዝ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ ለማረፍ ወደ ታች ማቆልቆል ጀመረ። ሰማያዊው ሰማይ፣ ነጫጭ ደመናዎች፣ ለምለም ሸንተረሮችና ደማቅ ሰማያዊ ቀለም ያለው ውቅያኖስ አንድ ላይ ሲታዩ ሰላማዊ የሆነ የሐሩር አካባቢ ገነታዊ ትርዒት ይታይበታል። ይላንግ ይላንግ የሚባል ጣፋጭ መዓዛ ያለው ዛፍ በመኖሩ ምክንያት ማዮቴ የሽቶ ደሴት የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶአታል። ከዚህ ዛፍ አበባ ተጣርቶ የሚወጣው ቅመም ወደ ፈረንሣይ ተልኮ በዓለም ዕውቅ የሆኑ ሽቶዎችን ለመቀመም ያገለግላል።

ከአሥራ አምስት ደቂቃ የጀልባ ጉዞ በኋላ ወደ ዋናው ደሴት ለመድረስ ይቻላል። በሚስዮናውያኑ ቤት ቀዝቃዛ መጠጥና ቀለል ያለ ምግብ ከበላንና ከጠጣን በኋላ በደሴቷ ላይ 19 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ በሚደረግ የመጽሐፍ ጥናት ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን። በዕረፍት ያሳለፍነው ጊዜ በዚሁ አበቃ። ከኋላው ክፍት በሆነ ጂፕ መኪና ላይ ተሣፈርንና በጠባብ መንገዶች ላይ በጣም የሚያስፈራ ጉዞ አደረግን። ከመንገዱ መጥበብ የተነሣ ሰዎችን፣ ከብቶችንና ሌሎች ተሽከርካሪዎችን ሳንገጭ የምንስተው ለጥቂት ብቻ ነበር። ይሁንና ፈረንሳዊው ሾፌራችን መንገዱን አሳምሮ ያውቀው ነበር። ወዲያውኑ ቺኮኒ ደረስንና ጥናቱ የሚደረግበት ቤት ባለቤት የሆኑትን ቤተሰቦች አገኘን።

በፊት እስላም የነበረው አባት ከስምንት ልጆቹ ጋር አስተዋወቀን። የሁሉም ታናሽ የሆነው የአራት ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ ለየት ያለ ሰላምታ አሰጣጥ አሳይቶን ነበር። በኋላ ባሕላዊው የሰላምታ አሰጣጥ መሆኑን አወቅን። የአንደኛውን እጁን ጀርባ በሌላው እጁ የውስጥ መዳፍ ላይ አነባብሮና እጆቹን አጎድጉዶ በፊታችን ቆመ። መጀመሪያ እጆቹን ለመጨበጥ ሞከርን። ሚስቴ ደግሞ እጁን ራሷ ላይ ለማድረግ ትሞክር ነበር። ትንሹ ልጅ ምን እያደረግን እንደሆነ ግራ ገብቶት ሳይሆን አይቀርም ትላልቅ ክብ ዓይኖቹን እያንቀዋለለ በትዕግሥት ይጠብቃል። በመጨረሻ ትክክለኛው የባሕላዊ ሰላምታ አሰጣጥ እንዴት እንደሆነ ተረዳንና እጆቹን ራሱ ላይ አደረግን። ጥናቱ 14 ሰዎች በተገኙበት ተጀመረ። በጥናታችን መሃል አንድ ፍላጎት ያለው ሰው መጣና ከሁላችንም ጋር ተጨባበጠ። ይኸው ከባሕላቸው አንዱ መሆኑ ነው።

አሁን እየጨለመ ባለው የገጠር መንገድ ተመልሰን ስንሄድ ፍራፍሬ ተመጋቢ የሆኑ የሌሊት ወፎች ሌሊቱን ሲመገቡ ለማደር ወደ ዛፎቹ ሲበሩ ተመለከትን። በጠመዝማዛው መንገድ ላይ የወደቀው የጃክፍሩት፣ የማንጎ፣ የፓፓያና የዘይቱን ፍሬዎች ጣፋጭ መዓዛ ሸተተን። ይህ ቦታ የቀበሮ ፊት የሚመስል ፊት ያላቸውና ረጅምና የሚቆላለፍ ጅራት ያላቸው ትናንሽ ዝንጀሮ የሚመስሉ እንስሶች መኖሪያ ነው። የኮረብታውን አናት ስንዞር በጣም የሚያስደንቅ ትርዒት እንድናይ ተጋበዝን። የቀይ ብርቱካን ቀለም ያላት ሙሉ ጨረቃ በባሕሩ ዳርቻ ላይ ገና መውጣትዋ ነበር። አንፀባራቂ ብርሃንዋን ፀጥ ባለው ውሃ ላይ ጥላለች። ሾፌራችንም እንኳ ሳይቀር ይህን አስደናቂ ነገር ትርዒት ለማየት ሲል ፍጥነቱን ቀነሰ። በቀሪው መንገዳችን ሁሉ ዞር እያልን እንመለከታት ነበር።

በሚቀጥለው ጧት ከሚስዮናውያኑ ጋር ወደ ስብከት ሄድን። መጀመሪያ ያነጋገርነው ፈረንሳይኛ ጥሩ አድርጎ የሚናገር አንድ ወጣት መምህር ነው። እሱ ወለሉ ላይ ተቀምጦ እኛን አልጋው ላይ አስቀመጠን። የሚቀጥለው ጥናትም ከአንድ ወጣት ሰው ጋር ነበር። በትንሽዋ ክፍሉ ውስጥ ባለው ወለል ላይ የተነጠፈ ፍራሽ ላይ እንድንቀመጥ ጋበዘን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የእግራችንን መደንዘዝና በጀርባችን ላይ የሚንቆረቆረውን ላብ መታገስ አቃተን። ከሚቀጥለው ቤት የሚመጣው ሙዚቃ እያንቧረቀብን በከፊል በፈረንሳይኛና በከፊል ደግሞ በማሆሪያን ቋንቋ በሚመራው ጥናት ላይ ሐሳባችንን ለመሰብሰብ አስቸግሮን ነበር።

በመጨረሻ የጎበኘነው የጎረቤት ደሴት ከሆነችው ከኮሞሮስ ለመጣ አንድ ወጣት ነበር። ፈረንሳይኛ ጥሩ አድርጎ ለመናገር ባለመቻሉ ይቅርታ ጠየቀንና ብሮሹሩን አውጥቶ ለማጥናት ተዘጋጀ። ሚስዮናዊው አንድ ነገር ሊነግረኝ ሲጀምር በመሃል አቋረጠና አንቀጹን ሊያነብ መሆኑን ተናገረ። በተዘዋዋሪ መንገድ ዝም እንድንል መናገሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች ሁሉ እስላሞች ናቸው። ቢሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚማሩትን ነገር ሁሉ ያደንቃሉ።

የሚያጠኑት ሰዎች በአብዛኛው ወጣት ወንዶች እንደሆኑና የሚያጠኑ ወጣት ሴቶች ግን ጥቂት የሆኑት ለምን እንደሆነ ተገርመን ነበር። ይህ የሆነው በማኅበራዊና በቤተሰብ ባሕሎች ምክንያት መሆኑ ተነገረን። ብዙ ሚስት ማግባት በሃይማኖቱም ሆነ በባሕሉ የተፈቀደ በመሆኑና እያንዳንዷም ሚስት የምትኖረው በራስዋ ቤት ስለሆነ የአባትዬው ተጽዕኖ አነስተኛ እንደሆነና ሁሉን ነገር የምትቆጣጠረው እናት እንደሆነች ተነገረን። በባሕሉ መሠረት ልጃገረዶች እስኪያገቡ ድረስ በእናታቸው ቤት እንደሚኖሩና ወንዶች ልጆች ግን ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ከቤት ወጥተው በራሳቸው ባንጋ (ጎጆ) ወይም ከሌሎች ወንዶች ልጆች ጋር ተዳብለው እንደሚኖሩ አወቅን። እንዲህ ባለው ሁኔታ ወጣት ወንዶች ከፈለጉ ለማጥናት ነፃ ሲሆኑ ይህን የመሰለ ነፃነት ያላቸው ልጃገረዶች ግን ጥቂቶች ናቸው።

የልዩ ስብሰባው ቀን የሚደረገው እሁድ ዕለት ነበር። ዕለቱ የጀመረው በጥሩ የአየር ሁኔታ ቢሆንም እኩለ ቀን ላይ ደመናው ተሰባሰበና ማካፋት ጀመረ። ዝናቡ ሙቀቱን ቀዝቀዝ የሚያደርግ ስለነበረ ቅር የተሰኘ ሰው አልነበረም። እዚህም ብዙ መንፈሣዊ ብልጽግና ለመመልከት ችለናል። 36 የሚያክሉት አስፋፊዎችና አቅኚዎች 83 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው 3 አዳዲስ ሰዎች ሲጠመቁ በማየታቸው በጣም ተደስተዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ ከተደረጉት አቢይ ክንውኖች አንዱ በምድር ላይ በደስታ ለዘላለም ኑር! የተሰኘው ብሮሹር በቋንቋቸው መውጣቱ ነበር። ይህ ብሮሹር በማሆሪያ ቋንቋ የተዘጋጀ የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማህበር ጽሑፍ ከመሆኑም በላይ የመጀመሪያው በማሆሪያ የተጻፈ ጽሑፍ ነው። በሮማ ሆሄያት ከተጻፈው ጽሑፍ ግርጌ የአረብኛ ፊደላት ተጽፈዋል። ሰዎቹ በትምህርት ቤት የአረብኛን ቋንቋ ሳይሆን የአረብኛን ፊደል ይማራሉ። በአረብኛ ጸሎታቸውን ሊደግሙና ቁርአንንም ሊያነቡ ይችላሉ። ሆኖም የሚያነቡትን ነገር ትርጉም አይረዱም። በብሮሹሩ ውስጥ የአረብኛውን ጽሑፍ ሲያነቡና ትርጉሙ የሚገባቸው መሆኑን ሲመለከቱ በጣም ይደነቃሉ። የሚያነቡት ጽሑፍ በአረብኛ ፊደላት የተጻፈ ይሁን እንጂ ቋንቋው የራሳቸው የማሆሪያን ቋንቋ ነው። የሚያነቡትን ነገር ትርጉም ሲረዱ ፊታቸው ሲያበራ ማየት በጣም ያስደስታል።

ብሮሹሮቹን ለማበርከት በጣም ቀላል ነው። ራቅ ብለው ከሚገኙት ገጠሮች በአንዱ የሚኖር አንድ ሰው ለአንዲት ሴት ስንሰብክ ወደኛ ቀረበ። ወንድማችንን በማሆሪያን ቋንቋ በቁጣ ይናገረው ጀመር። በጣም የሚቃወም ይመስላል። ሰውየው ለጥቂት ጊዜ እጁን እያወዛወዘ ተናገረ። ወንድም በኋላ እንዳስረዳን ሰውየው “በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ መጥታችሁ እየጠየቃችሁን እንዴት የምትነግሩንን ልናስታውስ እንችላለን? ቶሎ ቶሎ እየመጣችሁ መናገር አለባችሁ” ይለው ነበር።

እነዚያ የመጨረሻ ቃላት የእኛንም ስሜት የሚገልጹ ናቸው። ይሖዋ በእርግጥ በመንግሥቱ ምሥራች አማካኝነት ከአሕዛብ የተመረጡትን እየሰበሰበ ነው። የደሴቶቹ ነዋሪዎች በትልቅ ውቅያኖስ የተገለሉ ቢሆኑም ሠሪያቸውና ሰማያዊ አባታቸው ለሆነው ለይሖዋ አምላክ በሚያርገው ታላቅ የምስጋና ጩኸት ላይ የራሳቸውን ድምፅ እያከሉበት ነው።​—ሐጌ 2:7

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሴሸልስ

የሕንድ ውቅያኖስ

ኮሞሮስ

ማዮቴ

ማዳጋስካር

ሞሪሸስ

ሪዩኒየን

ሮድሪገዝ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፕራስሊን ሴንት አን ያለው ወደ ባሕር ሾጠጥ ብሎ የገባው ዓለታማ መሬት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በላ ዲግ ሴሸልስ በበሬ የሚጎተት የጋሪ “ታክሲ”

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማዮቴ በአዲሱ ብሮሹር መስበክ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ