ከግብፅ የቆሻሻ ክምር የተገኘ ውድ ሀብት
በጣም ውድ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ የቀድሞ የእጅ ጽሑፎች በቆሻሻ ክምር ውስጥ ይገኛሉ ብለህ ታስባለህን? ባለፈው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ በግብጽ አሸዋ መሐል እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞ ነበር። እንዴት?
ከ1778 ጀምሮ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ድረስ በግብፅ አገር በርካታ የፓፒረስ ጽሑፎች በተከታታይ ተገኝተዋል። ይሁን እንጂ እስከ መቶ ዓመት በፊት ድረስ እምብዛም ሥርዓት ያለው ፍለጋ አልተደረገም ነበር። ያኔ ባገሩ ገበሬዎች ብዙ የጥንት ሰነዶች በተከታታይ ይገኙ ስለነበረ በብሪታኒያ የሚደገፈው የግብፅ አሰሳ ድርጅት ሰነዶቹ ጠፍተው ከማለቃቸው በፊት ፍለጋ የሚያደርግ አንድ ጓድ መላክ እንደሚያስፈልግ ተገነዘበ። ሁለት የኦክስፎርድ ምሁራን የሆኑትን በርናርድ ግሬንፌልንና አርተር ኤስ ሃንትን መረጠ። እነርሱም በፋዩም አውራጃ (ከላይ በሚታየው) በሚገኘው የእርሻ ቦታ በስተደቡብ ባለው አካባቢ እንዲፈልጉ ፈቃድ ተቀበሉ።
ቤህኔሳ የሚባለው ሥፍራ የጥንት የግሪክኛ ስሙ ኦክሲሪንኩስ ስለነበር ግሬንፌል ተስፋ የሚጣልበት ቦታ እንደሆነ ተገነዘበ። ኦክሲሪንኩስ በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የክርስትና ዋና ማዕከል ነበር። ብዙ የቀድሞ ገዳማት በአቅራቢያው ይገኙ ስለነበር የዚህ የጠቅላይ ግዛት ከተማ ፍርስራሽ በጣም ሠፊ ነበር። ግሬንፌል እዚህ ቦታ ላይ የክርስትና ጽሑፎች ቁርጥራጮች ይገኛሉ ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ በመቃብር ቦታዎችና በፈረሱ ቤቶች ውስጥ የተደረገው ፍለጋ ምንም ውጤት አላስገኘም። ፍለጋ ሳይደረግባቸው የቀሩት የከተማይቱ የቆሻሻ ክምሮች ብቻ ነበሩ። አንዳንዶቹ የቆሻሻ ክምሮች 30 ጫማ ከፍታ ያላቸው ናቸው። የፓፒረስ ጽሑፎችን ለማግኘት እነዚህን የቆሻሻ ክምሮች መቆፈር ሽንፈት መቀበል መስሎ ታይቶ ነበር። ሆኖም አሳሾቹ ለመሞከር ወሰኑ።
የሀብት ክምችት
በጥር 1897 የሙከራ ቁፋሮ ተደረገና በሰዓቶች በሚቆጠር ጊዜ ውስጥ የጥንት የፓፒረስ ቁርጥራጮች መገኘት ጀመሩ። ከእነዚህም መካከል ደብዳቤዎች፣ የኮንትራት ውሎች፣ የባለሥልጣኖች ሰነዶች ይገኛሉ። ነፋስ ጠራርጎ ባመጣው አሸዋ ተሸፍነዋል። ደረቅ የሆነው የአየር ጠባይ ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት ሳይበላሹ እንዲቆዩ አድርጎአቸዋል።
ከሦስት ወር ትንሽ በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ ብቻ 20 ኩንታል የሚያክል ክብደት ያላቸው ጽሑፎች ከኦክሲሪንኩስ ተገኝተዋል። በሃያ አምስት ትላልቅ ሣጥኖች ውስጥ ተሞልተው ወደ እንግሊዝ አገር ተጫኑ። እነዚህ ቆራጥ ምሁራን ለቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በያንዳንዱ ክረምት ተጨማሪ የጥንት ጽሑፎች ለመሰብሰብ ወደ ግብፅ ይመለሱ ነበር።
በአንድ ወቅት ቴብቱኒስ በሚባል ሥፍራ አንድን መቃብር ሲቆፍሩ እንዳይበሰብሱ በመድኃኒት ከተጠበቁ የአዞ ሬሳዎች በስተቀር ምንም ነገር ሳያገኙ ቀሩ። አንድ ሠራተኛ በብስጭት አንዱን ሬሣ ገነጣጠለው። የአዞው ሬሳ በፓፒረስ ወረቀት ተጠቅልሎ ሲያገኘው ተገረመ። ሌሎች አዞዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የተጠቀለሉ ሆነው አገኛቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ የፓፒረስ ጥቅልሎች ጉሮሮአቸው ውስጥ ተወትፎባቸዋል። የጥንት የሮማና የግሪክ ጽሑፎችን አገኙ። ከእነርሱም ጋር ንጉሣዊ ድንጋጌዎች፣ ከንግድ የሒሳብ መዛግብት ጋር የተያያዙ ውሎችና የግል ደብዳቤዎች ተገኙ።
እነዚህ ሰነዶች ምን ጥቅም አላቸው? አብዛኞቹ የተጻፉት የዘመኑ ተራ ግሪክኛ በነበረው በኮይኔ፣ ተራ በሆኑ ሰዎች የተጻፉ ስለነበሩ ከፍተኛ ፍላጎት ቀስቅሰዋል። የተጠቀሙባቸው አብዛኞቹ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ የግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ማለትም “አዲስ ኪዳን” ላይ ስለተሠራባቸው አንዳንድ ምሁራን ሐሳብ እንዳቀረቡት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያለው ቋንቋ የተለየ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቋንቋ ሳይሆን ማንኛውም ተራ ሰው የሚነጋገርበት ተራ ቋንቋ እንደነበረ በግልጽ ሊታይ ችሎአል። ስለዚህ ቃላቱ በዕለታዊ ሁኔታዎች እንዴት ይሠራባቸው እንደነበረ በማነፃፀር በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስላላቸው ትርጉም በግልጽ ለመረዳት ተችሎአል።
የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎች
የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ጽሑፎችም ተገኝተዋል። እነዚህም አብዛኛውን ጊዜ የተጻፉት ብዙ ለማሳመር ጥረት ሳይደረግ ተራ በሆነ አፃፃፍና ተራ በሆኑ የመፃፊያ መሣሪያዎች ስለነበረ የተራ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ነበሩ። ከተገኙት መካከል አንዳንዶቹን እንመርምር።
ሀንት በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ በትላልቅ ፊደላት የተጻፈ የማቴዎስን ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ቁጥር 1-9, 12, 14-20 አግኝተዋል። እሱም ከተለያዩ ቦታዎች ከተገኙት የፓፒረስ ጽሑፎች የመጀመሪያውን ተራ ቁጥር በመያዝ P1 ተብሎ ተሰይሞአል። በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑት የእጅ ጽሑፎች ወደ መቶ የሚጠጉ ሆነዋል። ሀንት ያገኙአቸው ጥቂት ቁጥሮች ምን ጥቅም አላቸው? ጽሑፉ የተጻፈበት ዘመን ሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ እንደነበረ ከፊደላቱ አፃፃፍ ለመረዳት ተችሎአል። ንባቡም ሲመረመር ዌስትኮትና ሆርት ካወጡት የዘመኑ ጽሑፍ ጋር ተስማምቶአል። አሁን P1 የሚገኘው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፊላደልፊያ ፔንስልቫኒያ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ቤተመዘክር ውስጥ ነው።
ከአንድ ኮዴክስ ወይም ጥንታዊ መጽሐፍ ላይ የተገኘ የፓፒረስ ጽሑፍ በስተግራ በኩል ባለው ቅጠል ላይ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1 በከፊልና በስተቀኝ ባለው ቅጠል ላይ ደግሞ ምዕራፍ 20ን በከፊል የያዘ ነው። የጠፉትን የወንጌል ክፍሎች እንደገና ለማገጣጠም የተደረገው ሙከራ በመጀመሪያ መላው ወንጌል 25 ወረቀቶች እንደነበሩትና ጥንት ጀምሮ ምዕራፍ 21ንም ይጨምሩ እንደነበረ ያመለክታል። P5 የሚል ተራ ቁጥር ተሰጥቶታል። የተጻፈበት ዘመንም ሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ እንደሆነ የተገመተ ሲሆን አሁን በእንግሊዝ አገር ለንደን ውስጥ ብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል።
ሮሜ 1:1-7ን የያዘው የፓፒረስ ቁራጭ በጣም ትላልቅ በሆኑ ፊደላት የተጻፈ ከመሆኑ የተነሣ የአንድ ተማሪ መለማመጃ ሳይሆን እንደማይቀር አንዳንድ ምሁራን ገምተዋል። አሁን P10 የሚል ተራ ቁጥር የተሰጠው ሲሆን የተጻፈበት ዘመንም ከአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ወዲህ እንደሆነ ተገምቶአል።
ወደ ዕብራውያን የተጻፈውን ደብዳቤ ሲሶ ያህል የሚይዘው ጽሑፍ ብዛት ካላቸው ግኝቶች አንዱ ነው። የተጻፈውም ሊቪ የተባለው የሮማ ታሪክ ፀሐፊ የጻፈው ጽሑፍ ከተጻፈበት ጥቅልል በስተጀርባ ነው። በአንድ ጥቅልል ላይ ሆኖ በፊት ለፊቱ ባለው ገጽና በስተጀርባው እንዲህ የተለያዩ ነገሮች የተጻፉበት ለምንድን ነው? በእነዚህ ዘመናት የመጻፊያ ቁሳቁሶች እጥረትና የመግዣ ዋጋ ውድነት ምክንያት አሮጌ ፓፒረስ እንዳይባክን ይጠቀሙበት ስለነበረ ነው። አሁን P13 በመባል የተመዘገበ ሲሆን የተጻፈበት ዘመንም ሦስተኛው ወይም አራተኛው መቶ ዘመን እዘአ እንደሆነ ተገምቶአል።
በጣም ትናንሽ በሆኑ ፊደላት የተጻፈ ሮሜ ምዕራፍ 8 እና 9ን የያዘ አንድ የፓፒረስ ቅጠል የወጣው ርዝመቱ 11 ሳንቲ ሜትር እና ስፋቱ 5 ሳንቲ ሜትር ብቻ ከሆነ መጽሐፍ ነው። በኪስ ሊያዝ በሚችል መጠን የተዘጋጁ የቅዱሳን ጽሑፎች መጻሕፍት በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩ ይመስላል። ይህም P27 የሚል ቁጥር የተሰጠው ሲሆን በአጠቃላይ መልኩ ከኮዴክስ ቫቲካነስ ጋር ይስማማል።
ከግሪክ ሰፕቱጀንት የጥንት ጽሑፎች የወጡ አራት ቅጠሎች በከፊል የዘፍጥረትን ስድስት ምዕራፎች ይዘዋል። ይህ የጥንት ጽሑፍ የተጻፈው በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ እንደሆነ ስለተገመተና እነዚህ ምዕራፎች ከኮዴክስ ቫቲካነስ ውስጥ ስለማይገኙና በኮዴክስ ሲናይቲከስ ውስጥ ደግሞ ተሟልተው ስለማይገኙ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው። እነዚህ ቅጠሎች ዛሬ ፓፒረስ 656 የሚል ቁጥር ተሰጥቶአቸው በእንግሊዝ ኦክስፎርድ በቦድሊያን ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ።
እነዚህ ቁርጥራጮች ሁሉ እስከ አሁን ካሉን የቀድሞ የእጅ ጽሑፎች ጋር ሲተያዩ የጎላ ልዩነት አይታይባቸውም። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በዚህ የጥንት ዘመን በግብፅ ሩቅ ክፍሎች ሳይቀር በተራ ሰዎች መሐል ተሠራጭተው እንደነበረ ያረጋግጣሉ። የአምላክ ቃል አስተማማኝና ትክክለኛ ስለመሆኑ ያለንን እምነትም ያጠነክራሉ።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዮሐንስ ምዕራፍ አንድን በከፊል የያዙ በፋዩም የተገኙ የፓፒረስ ቅጠሎች
[ምንጭ]
By permission of the British Library
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.