ከአምላክ በተሰጣችሁ ነፃነት ጸንታችሁ ቁሙ!
“በነፃነት ልንኖር ክርስቶስ ነፃነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፣ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።”—ገላትያ 5:1
1, 2. ከአምላክ የተሰጠው ነፃነት የታጣው እንዴት ነው?
የይሖዋ ሕዝብ ነፃ ሕዝብ ነው። ይሁን እንጂ ከአምላክ ነፃ ለመሆን አይፈልጉም። ምክንያቱም ከአምላክ ነፃ መሆን ማለት የሰይጣን ባሪያ መሆን ማለት ስለሆነ ነው። ከይሖዋ ጋር ላላቸው የተቀራረበ ዝምድና ከፍተኛ ግምት ስለሚሰጡ ይሖዋ በሚሰጣቸው ነፃነት ይደሰታሉ።
2 የመጀመሪያ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራታቸውና የኃጢአትና የሞት እንዲሁም የዲያብሎስ ባሪያዎች በመሆናቸው አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት አጡ። (ዘፍጥረት 3:1-19፤ ሮሜ 5:12) እንዲያውም ሰይጣን መላውን ዓለም ወደ ጥፋት በሚወስደው የኃጢአተኝነት ጎዳና ላይ ጥሏል! አምላክ በሰጣቸው ነፃነት ጸንተው የሚቆሙ ሰዎች ግን ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ ይመላለሳሉ።—ማቴዎስ 7:13, 14፤ 1 ዮሐንስ 5:19
ከእስራት ነፃ መውጣት
3. አምላክ በኤደን ምን ተስፋ ሰጥቶ ነበር?
3 ይሖዋ ስሙን የሚያከብሩ ሰዎች የሰይጣን፣ የኃጢአትና የሞት ባሪያዎች ከመሆን ነፃ እንዲሆኑ ዓላማው ነው። ይህም ዓላማው አምላክ በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን መሣሪያ አድርጐ ለተጠቀመበት እባብ በተናገረው ቃል ተገልጿል፦ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:14, 15) ከይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት የወጣው ዘር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በሞተ ጊዜ ሰኮናው ተቀጥቅጧል። ይህም ሰዎችን ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ለማውጣት የሚያስችለውን ቤዛዊ መስዋዕት አስገኝቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16)ጊዜው ሲደርስ ኢየሱስ የቀድሞውን እባብ የሰይጣንን ራስ ይቀጠቅጣል።—ራዕይ 12:9
4. አብርሃም ያገኘው ነፃነት ምን ዓይነት ነበር? ይሖዋስ ምን ተስፋ ገባለት?
4 ይህ ተስፋ በኤደን ከተነገረ ከ2,000 ያህል ዓመታት በኋላ “የይሖዋ ወዳጅ” የሆነው አብርሃም አምላክን በመታዘዝ የዑርን ከተማ ለቆ ወደ ሌላ ሥፍራ ሄደ። (ያዕቆብ 2:23፤ ዕብራውያን 11:8) ይህን በማድረጉም ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት አገኘ። ከዚያ በኋላ የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆነው የሐሰት ሃይማኖት፣ የብልሹ ፖለቲካና የስግብግብ ንግድ ባሪያ ሆኖ አልኖረም። አምላክ በኤደን በተናገረው ተስፋ ላይ አምላክ የምድር አሕዛብና የምድር ነገዶች በአብርሃምና በዘሩ አማካኝነት ራሳቸውን እንደሚባርኩ ተናገረ። (ዘፍጥረት 12:3፤ 22:17, 18) አብርሃም በይሖዋ ስላመነና ይህም ጽድቅ ሆኖ ስለተቆጠረለት ከኩነኔ ነፃ ሆኗል። (ዘፍጥረት 15:6) በዛሬው ጊዜም ከይሖዋ ጋር መዛመድ ከኩነኔና በሰይጣን ኃይል ከተያዘው ዓለም ነፃ የሚያደርግ ከአምላክ የሚሰጥ ነፃነት ያስገኛል።
ማራኪ የሆነ ምሳሌያዊ ድራማ
5. የይስሐቅ መወለድ ከምን ሁኔታዎች ጋር ተያይዟል?
5 መካን የነበረችው የአብርሃም ሚስት ሣራ አብርሃም ዘር ይኖረው ዘንድ ገረድዋን አጋርን ልጅ እንድትወልድለት ሰጠችው። አብርሃምም ከአጋር እስማኤልን ወለደ። ይሁን እንጂ አምላክ እስማኤልን የተስፋው ዘር እንዲሆን አልመረጠውም። ከዚህ ይልቅ አብርሃም የ100 ዓመት ዕድሜ፣ ሣራ ደግሞ የ90 ዓመት ዕድሜ ሲሆናቸው ይሖዋ ይስሐቅ የሚባል ልጅ እንዲወልዱ አስቻላቸው። እስማኤል በይስሐቅ ላይ ባሾፈ ጊዜ ከነፃይቱ ሴት ከሣራ የተወለደው የአብርሃም ልጅ ተቀናቃኝ የሌለበት የአብርሃም ዘር እንዲሆን አጋርና ልጅዋ ተባረሩ። ይስሐቅም እንደ አብርሃም እምነት ስላሳየ ከአምላክ የሚሰጠውን ነፃነት አግኝቷል።—ዘፍጥረት 16:1-16፤ 21:1-21፤ 25:5-11
6, 7. የሐሰት አስተማሪዎች የገላትያ ክርስቲያኖችን ስለምን ነገር አሳምነዋቸው ነበር? ጳውሎስ ግን ስለምን ነገር ገለጸ?
6 እነዚህ ሁኔታዎች ለነፃነት አፍቃሪዎች ታላቅ ትርጉም ላላቸው ነገሮች ጥላ የሚሆኑ ነበሩ። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ ከ50 እስከ 52 እዘአ አካባቢ ለገላትያ ጉባኤ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተገልጿል። በዚያ ጊዜ የአስተዳደር አካሉ ለክርስቲያኖች የመገረዝ ግዴታ እንደሌለባቸው ወስኖ ነበር። ቢሆንም የሐሰት አስተማሪዎች መገረዝ አስፈላጊ የሆነ የክርስትና ክፍል ነው በማለት አንዳንድ የገላትያ ሰዎችን አሳምነው ነበር።
7 ጳውሎስ ሰው የሚጸድቀው የሙሴን ሕግ በመፈጸም ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንደሆነ ለገላትያ ሰዎች ነገራቸው። (ገላ 1:1 እስከ 3:14) ሕጉ መተላለፍን የሚያጋልጥና ወደ ኢየሱስ የሚያደርስ ሞግዚት በመሆን አገለገለ እንጂ ከአብርሃም ቃልኪዳን ጋር የተያያዘውን ተስፋ አልሻረም። (ገላ 3:15-25) ኢየሱስ በሞቱ አማካኝነት በሕጉ ሥር የነበሩትን ሰዎች ነፃ በማውጣት የአምላክ ልጆች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ስለዚህ ቀንን፣ ወርን፣ ዘመናትንና ዓመታትን ወደማክበር ሥርዓት መመለስ ወደ ባርነት መመለስ ማለት ነበር። (ገላ 4:1-20) ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጻፈ፦
8, 9. (ሀ) ጳውሎስ በገላትያ 4:21-26 ላይ የተናገረውን በራስህ ቃል ግለጽ። (ለ) በዚህ ምሳሌያዊ ድራማ ላይ በአብርሃምና በሣራ የተመሰለው ማን ወይም ምን ነበር? ተስፋ የተገባው ዘርስ ማን ነበር?
8 “እናንተ ከሕግ በታች ልትኖሩ የምትወዱ፣ ሕጉን አትሰሙምን? እስቲ ንገሩኝ። አንዱ [እስማኤል] ከባሪያይቱ [ከአጋር]ና አንዱም [ይስሐቅ] ከጨዋይቱ [ከሣራ] የሆኑ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደነበሩት ተጽፎአልና። ነገር ግን የባሪያይቱ ልጅ እንደ ሥጋ ተወልዶአልና፣ የጨዋይቱ ግን በተስፋው ቃል ተወልዶአል። ይህም ነገር ምሳሌ ነው፤ እነዚህ ሁለት ሴቶች እንደ ሁለቱ ኪዳኖች ናቸውና። ከደብረ ሲና የሆነችው አንዲቱ [የሕጉ ቃል ኪዳን] ለባርነት ልጆችን ትወልዳለች፣ እርሷም አጋር ናት። ይህችም አጋር በዓረብ ምድር ያለችው [አምላክ ከእሥራኤላውያን ጋር ቃል ኪዳን የተጋባባት] ደብረ ሲና ናት፤ አሁንም ያለችውን ኢየሩሳሌምን ትመስላለች፣ ከልጆችዋ [ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ዝርያዎች] ጋር በባርነት ናትና። [ሌላው ቃል ኪዳን ከአብርሃም ጋር ዘሩን በሚመለከት የተገባው ቃል ኪዳን ነው።] ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት እርስዋም እናታችን ናት።”—ገላትያ 4:21-26
9 በዚህ ምሳሌያዊ ድራማ ውስጥ አብርሃም የይሖዋ ምሳሌ ነው። “ነፃይቱ ሴት” ሣራ የአምላክን “ሴት” ወይም ቅዱሱን ጽንፈ ዓለማዊ ድርጅት ታመለክታለች። እርሷም የምሳሌያዊቱ ሴትና የታላቁ አብርሃም ዘር የሆነውን ክርስቶስን ወልዳለች። (ገላትያ 3:16) ኢየሱስ ከእርኩስ አምልኮ፣ ከኃጢአትና ከሰይጣን ነፃ የሚወጡበትን መንገድ ለማሳየት እውነትን አስተምሯል፣ የሐሰት ሃይማኖትንም አጋልጧል። ኢየሩሳሌምና ልጆችዋ ግን እሱን ስላልተቀበሉ በሃይማኖታዊ ባርነት ውስጥ ቀሩ። (ማቴዎስ 23:37, 38) ኢየሱስን የተከተሉ አይሁድ ግን የአለፍጽምና፣ የኃጢአትና የሞት ባሪያዎች መሆናቸውን ካጋለጠው ከሕጉ ነፃ ወጡ። ኢየሱስ ከአምላክ ሴት የተገኘ መሲሐዊ ንጉሥና ‘ለተማረኩት ነፃነትን የሚያውጅ’ ነፃ አውጭ እንደሆነ የሚቀበሉ ሰዎች ሁሉ በእርግጥም ነፃ ናቸው!—ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ሉቃስ 4:18, 19
የባርነትን ቀንበር አስወግዱ
10, 11. ክርስቶስ ተከታዮቹን ነፃ ያወጣቸው ከምን የባርነት ቀንበር ነበር? ዛሬስ ምን ተመሳሳይ ነፃነት ልናገኝ እንችላለን?
10 ጳውሎስ ታላቁ ይስሐቅ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ሆነው የአብርሃምን ዘር ለሚመሠርቱት ሰዎች እንዲህ ብሏል፦ “ላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ግን በነፃነት የምትኖር ናት። እርስዋም እናታችን ናት። . . . እኛም ወንድሞች ሆይ፣ እንደ ይስሐቅ የተስፋ ቃል ልጆች ነን። ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው [እስማኤል] እንደ መንፈስ የተወለደውን [ይስሐቅን] በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው። . . . የጨዋይቱ ልጆች ነን እንጂ የባሪያይቱ አይደለንም። በነፃነት ልንኖር ክርስቶስ [ከሕጉ] ነፃ አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፣ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ” ብሏል።—ገላትያ 4:26 እስከ 5:1
11 ማንኛውም የኢየሱስ ተከታይ ለሕጉ ተገዢ ቢሆን ኖሮ በባርነት ቀንበር ነበር። ባሁኑ ጊዜ ያለው የባርነት ቀንበር የሐሰት ሃይማኖት ቀንበር ነው፤ ሕዝበ ክርስትናም የጥንቷን ኢየሩሳሌምና ልጆችዋን ትመስላለች። ቅቡአን ቀሪዎች ግን የአምላክ ነፃ ሰማያዊ ድርጅት የሆነችው የላይኛይቱ ኢየሩሳሌም ልጆች ናቸው። እነሱና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸው የዚህ ዓለም ክፍል ስላልሆኑ በሰይጣን ባርነት ውስጥ አይደሉም። (ዮሐንስ 14:30፤ 15:19፤ 17:14, 16) በእውነትና በኢየሱስ መስዋዕት አማካኝነት ነፃ ስለወጣን አምላክ ለሰጠን ነፃነት ጸንተን እንቁም።
ከአምላክ ለሚሰጠው ነፃነት የጸና አቋም መያዝ
12. አማኞች ምን ዓይነት እርምጃ ይወስዳሉ? አሁን ስለምን ነገር እንወያያለን?
12 ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን እውነተኛ ነፃነት አግኝተዋል። ከሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየተደረገ ነው። ከእነዚህም አብዛኞቹ “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ናቸው። አማኞች በሚሆኑበት ጊዜም በመጠመቅ ከአምላክ የሚሰጠው ነፃነት ደጋፊዎች መሆናቸውን የሚያሳይ አቋም ይወስዳሉ። (ሥራ 13:48፤ 18:8) ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ከመጠመቃቸው በፊት ምን እርምጃዎች መውሰድ ይኖርባቸዋል?
13. በእውቀትና በጥምቀት መሃል ምን ዝምድና አለ?
13 አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት የቅዱሳን ጽሑፎችን ትክክለኛ እውቀት ማግኘትና ከተማረው ጋር የሚስማማ ሥራ መሥራት አለበት። (ኤፌሶን 4:13) በመሆኑም ኢየሱስ ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19, 20
14. በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ለመጠመቅ ምንን ማወቅ ያስፈልጋል?
14 በአብ ስም መጠመቅ ማለት ይሖዋ አምላክ፣ ፈጣሪና የአጽናፈ ዓለም ልዑል ገዢ በመሆን ያለውን ቦታ፣ ደረጃና ሥልጣን አምኖ መቀበል ማለት ነው። (ዘፍጥረት 17:1፤ 2 ነገሥት 19:15፤ ራዕይ 4:11) በወልድ ስም መጠመቅ ደግሞ ክርስቶስ ከፍ ከፍ የተደረገ መንፈሳዊ ፍጡር፣ መሲሐዊ ንጉሥና “ተመጣጣኝ ቤዛ” ሆኖ ከአምላክ የተሰጠ በመሆኑ ያለውን ቦታ፣ ደረጃና ሥልጣን መገንዘብ ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6 (አዓት)፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11) በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚጠመቅ አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ ይሖዋ ፍጥረታትን ለመፍጠርና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን ለመምራት፣ እንዲሁም በሌሎች መንገዶች የተገለገለበት የአምላክ ሠራተኛ ኃይል መሆኑን ይገነዘባል። (ዘፍጥረት 1:2፤ 2 ጴጥሮስ 1:21) በእርግጥም ስለአምላክ፣ ስለ ክርስቶስና ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ልንማረው የምንችል ነገር አለ።
15. አንድ ሰው ከመጠመቁ አስቀድሞ እምነት ማሳየት ያለበት ለምንድን ነው?
15 አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እምነት ማሳየት አለበት። “ያለእምነትም [ይሖዋን] ደስ ማሰኘት አይቻልም።” (ዕብራውያን 11:6) በአምላክ፣ በክርስቶስና በመለኮታዊ ዓላማው የሚያምን ሰው ከአምላክ ቃል ጋር ተስማምቶ የሚኖርና የምሥራቹን በመስበኩ ሥራም ተገቢ ተሳትፎ የሚያደርግ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ይፈልጋል። ስለ ይሖዋ ንግሥናና ክብርም ይናገራል።—መዝሙር 145:10-13፤ ማቴዎስ 24:14
16. ንስሐ ምንድን ነው? ከክርስቲያን ጥምቀት ጋር የሚዛመደውስ እንዴት ነው?
16 ሌላው ለመጠመቅ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ደግሞ ንስሐ መግባት ነው። ንስሐ መግባት ማለት “ባለፈው ጊዜ በተደረገ (ወይም ሊደረግ በታሰበ) ድርጊት፣ ወይም ጠባይ በመጸጸት ወይም ባለመደሰት ምክንያት ሐሳብን መለወጥ፤ ወይም “አንድ ሰው ባደረገው ወይም ሳያደርግ በቀረው ነገር መጸጸት፣ ወይም መቆጨት ወይም ማዘን” ማለት ነው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዶች በኢየሱስ ላይ ስላደረጉት ነገር ንስሐ መግባት አስፈልጓቸዋል። (ሥራ 3:11-26) በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ አማኞች ከምንዝር፣ ከጣኦት አምልኮ፣ ከዝሙት፣ ከሰዶማዊነት፣ ከሥርቆት፣ ከስስት፣ ከስካር፣ ከተሳዳቢነትና ከቀማኛነት ንስሐ ገብተዋል። በዚህም ምክንያት በኢየሱስ ደም “ታጥበውና” ለይሖዋ አገልግሎት የተለዩ ሆነው ተቀድሰዋል። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላክ መንፈስ ‘ጸድቀዋል’ ወይም ‘ጻድቃን ናችሁ’ ተብለዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) እንግዲያውስ ንስሐ መግባት በሠራነው ኃጢአት ምክንያት በጥፋተኛነት ስሜት ከመሰቃየት ነፃ ወደመሆን፣ ወደ ንጹሕ ሕሊናና ከአምላክ ወደሚሰጠው ነፃነት የሚያደርስ እርምጃ ነው።—1 ጴጥሮስ 3:21
17. መለወጥ ምን ማለት ነው? መጠመቅ የሚፈልግ ሰው ምን ማድረግ ያስፈልገዋል?
17 አንድ ሰው የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ከመጠመቁ በፊት መለወጥ አለበት። ንስሐ የገባው ግለሰብ ተለወጠ የሚባለው የተሳሳተ ተግባሩን ትቶ ትክክል የሆነውን ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ሲያደርግ ነው። ከመለወጥ ጋር የሚዛመዱ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ግሦች “ወደኋላ መመለስ፣ መዞር ወይም መመለስ” የሚል ትርጉም አላቸው። ጥሩ በሆነ መንፈሳዊ ስሜት ሲሠራበት ከተሳሳተ መንገድ ወደ አምላክ መመለስን የሚያመለክት ግሥ ነው። (1 ነገሥት 8:33, 34) መለወጥ ‘ለንስሐ የሚገባ ሥራ መሥራትን’፣ አምላክ የሚያዘውን ማድረግን፣ የሐሰት ሃይማኖትን መተውንና ይሖዋን ብቻ ለማገልገል ልባችንን ያለማመንታት ወደ እርሱ ማዞርን ይጠይቃል። (ሥራ 26:20፤ ዘዳግም 30:2, 8, 10፤ 1 ሳሙኤል 7:3) በሕይወት ውስጥ የአስተሳሰብ፣ የጠባይና የዓላማ ለውጥ ማድረግ፣ “አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ” መያዝ ያስፈልጋል ማለት ነው። (ሕዝቅኤል 18:31) ከዚህ የሚገኘው አዲስ ባሕርይም አምላካዊ ያልሆኑ ጠባዮችን አምላካዊ በሆኑ ጠባዮች ይተካል።(ቆላስይስ 3:5-14) አዎን፣ እውነተኛ ንስሐ በእርግጥም አንድን ሰው ‘እንዲመለስ’ ያነሳሳዋል።—ሥራ 3:19
18. በጸሎት ራስን ለአምላክ መወሰን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ይህስ እርምጃ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
18 ከጥምቀት በፊት ራስን በጸሎት ለአምላክ መወሰን ያስፈልጋል። (ከሉቃስ 3:21, 22 ጋር አወዳድር) ራስን መወሰን ማለት ራስን ለቅዱስ ዓላማ መለየት ማለት ነው። ይህ እርምጃ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደርን መሆናችንና እርሱን ብቻ ለማገልገል መወሰናችንን በጸሎት መግለጽ ይኖርብናል። (ዘዳግም 5:8, 9፤ 1 ዜና መዋዕል 29:10-13) እርግጥ ራሳችንን የምንወስነው ለአንድ ሥራ ሳይሆን ለአምላክ ለራሱ ነው። ይህ ቁም ነገር የመጠበቂያ ግንብ ማህበር የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት በነበረው በቻርልስ ቴዝ ራስል የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ግልጽ ተደርጎአል። በዚህ ጊዜ ማለትም በ1916 የማህበሩ ገንዘብ ያዥና ጸሐፊ የነበረው ደብልዩ ኢ ቫን አምበርግ “ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ ሥራ የአንድ ሰው ሥራ አይደለም። በጣም ታላቅ ሥራ በመሆኑ የአንድ ሰው ሥራ ሊሆን አይችልም። የአምላክ ሥራ ስለሆነ የአንድ ሰው ድርሻ መጉደሉ ምንም ዓይነት ለውጥ ሊያስከትል አይችልም። አምላክ ከአሁን በፊት በብዙ አገልጋዮች ተጠቅሟል፤ ወደፊትም በብዙዎች እንደሚገለገል አያጠራጥርም። ራሳችንን የወሰንነው ለአንድ ሰው ወይም ለአንድ ሰው ሥራ ሳይሆን አምላክ በቃሉና በመለኮታዊ አመራሩ የሚገልጽልንን ፈቃዱን ለመፈጸም ነው። አሁንም ሥራችንን የሚመራው አምላክ ነው” ብሎ ነበር። ይሁንና ራስን ለአምላክ በመወሰን ረገድ መደረግ ያለበት ሌላ ነገር ምንድን ነው?
19. (ሀ) ግለሰቦች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለሕዝብ የሚያሳዩት እንዴት ነው? (ለ) የውሃ ጥምቀት የምን ምሳሌ ነው?
19 አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ መወሰኑን በሕዝብ ፊት የሚያሳየው ሲጠመቅ ነው። ጥምቀት ተጠማቂው ሰው ራሱን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለይሖዋ አምላክ ያለገደብ መወሰኑን የሚያመለክት ምሳሌ ነው። (ከማቴዎስ 16:24 ጋር አወዳድር) አንድ የጥምቀት ዕጩ ውሃ ውስጥ ሰጥሞ ወይም ተቀብሮ በሚወጣበት ጊዜ በምሳሌያዊ ሁኔታ ለቀደመው አኗኗሩ ሞቶ ያለምንም ማወላወል የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸምና ለአዲስ ሕይወት ተነሳ ማለት ነው። (ከሮሜ 6:4-6 ጋር አወዳድር) ኢየሱስ ሲጠመቅ ያላንዳች ገደብ ራሱን ለሰማያዊ አባቱ ሙሉ በሙሉ አቅርቧል። (ማቴዎስ 3:13-17) ለመጠመቅ ብቁ የሆኑ አማኞች ሁሉ መጠመቅ እንደሚገባቸው ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ያሳያሉ። (ሥራ 8:13፤ 16:27-34፤ 18:8) ስለዚህ በዛሬው ጊዜ አንድ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ለመሆን ከፈለገ እውነተኛ አማኝ መሆንና መጠመቅ አለበት።—ከሥራ 8:26-39 ጋር አወዳድር
ጸንታችሁ ቁሙ!
20. የተጠመቅን የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን አምላክ ከሚሰጠው ነፃነት ጐን ብንሰለፍ እንደምንባረክ የሚያረጋግጡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?
20 የተጠመቅህ የይሖዋ ምሥክር በመሆን ከአምላክ ለተሰጠው ነፃነት ጽኑ አቋም ወስደህ ከሆነ አምላክ ባለፉት ዘመናት አገልጋዮቹን እንደባረከ ሁሉ አንተንም ይባርክሃል። ለምሳሌ ያህል በዕድሜ ለሸመገሉት ለአብርሃምና ለሣራ ፈሪሃ አምላክ ያለውን ልጅ ይሥሐቅን በመስጠት ባርኮአቸዋል። ነቢዩ ሙሴ “ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ [እንደ ክርስቶስ (አዓት)] [የክርስቶስ ወይም የአምላክ ቅቡእ ጥንታዊ አምሳያ በመሆን] መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን አስቧልና።” ከአምላክ ሕዝብ ጋር መነቀፍን የመረጠው በእምነት ነበር። (ዕብራውያን 11:24-26) ይህን በማድረጉም እሥራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት መርቶ ለማውጣት የይሖዋ መሣሪያ የመሆንን መብት አግኝቷል። ከዚህም በላይ አምላክን በታማኝነት ስላገለገለ ትንሣኤ አግኝቶ በታላቁ ሙሴ በኢየሱስ ክርስቶስ በምትተዳደረው በምድር ላይ መሣፍንት” ከሚሆኑት ሰዎች አንዱ ሆኖ ያገለግላል።—መዝሙር 45:16 (አዓት)፤ ዘዳግም 18:17-19
21. የጥንት ዘመን አምላካዊ ሴቶችን በሚመለከት ምን አበረታች ምሳሌዎች ተሰጥተዋል?
21 በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ያሉት ለአምላክ የተወሰኑ ክርስቲያኖች እውነተኛ ነፃነት ያገኙትንና ደስተኛ የነበሩትን ሴቶች በማሰብ ሊበረታቱ ይችላሉ። ከእነዚህ ሴቶች መሃል ቅስም ሰባሪ የሆነው መበለትነት የደረሰባትና ከዚያም በኋላ ከሐሰት ሃይማኖት ነፃ ከመውጣት የሚገኘውን ደስታ ያገኘችው ሩት ትገኝበታለች። ሩት ሕዝቧንና አማልክቷን በመተው መበለት የነበረችውን አማቷን ናኦሚ የሙጥኝ አለች። “ወደምትሄጂበት እሄዳለሁና፣ በምታድሪበትም አድራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” አለች። (ሩት 1:16) ሩት የቦኤዝ ሚስት በመሆን የዳዊት ቅድመ አያት የነበረው የኢዮቤድ እናት ሆናለች። (ሩት 4:13-17) አዎ፤ ይሖዋ እሥራኤላዊት ያልነበረችው ይህች ትሑት ሴት የመሲሑ የኢየሱስ ቅድመ አያት እንድትሆን በመፍቀድ “ፍጹም ደመወዝ” ሰጥቷታል። (ሩት 2:12) ሩት ትንሣኤ በምታገኝበት ጊዜ ይህን መብት አግኝታ እንደነበረ ስታውቅ ምን ያህል ትደሰት ይሆን! በትንሣኤ ከሚነሡት ሰዎች መሃል ከብልግና ኑሮና ከሐሰት አምልኮ ነፃ የወጣችው የጥንቷ ረአብና ጥፋት ሠርታ ንስሐ የገባችው ቤርሳቤህ ይሖዋ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያቶች እንዲሆኑ እንደፈቀደላቸው ሲያውቁ የሩትን የመሰለ ደስታ ያገኛሉ።—ማቴዎስ 1:1-6, 16
22. በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ ውይይት የሚደረግበት ምንድን ነው?
22 ከአምላክ የሚሰጠው ነፃነት ተጠቃሚዎች የሆኑ ብዙ ሰዎችን መዘርዘር ይችላል። ለምሳሌ ያህል በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የተዘረዘሩት የእምነት ሰዎች ከእነዚህ መሃል የሚቆጠሩ ናቸው። ብዙ መከራና ነቀፋ ታግሠዋል፤ “ዓለም አልተገባቸውም።” በእነዚህ ላይ ደግሞ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮችና ዛሬ ምሥክሮቹ በመሆን የሚያገለግሉትን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መጨመር ይቻላል። በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን ላይ እንደምንመለከተው እንደነዚህ ሰዎች አምላክ ከሚሰጠው ነፃነት ጐን ተሰልፈህ ከሆነ የምትደሰትበት ብዙ ምክንያት አለህ።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ከአምላክ የተሰጠው ነፃነት በታጣ ጊዜ አምላክ ምን ተስፋ ሰጠ?
◻ ክርስቶስ ተከታዮቹን ነፃ ያወጣቸው ከምን “የባርነት ቀንበር” ነው?
◻ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ከመጠመቅ በፊት መቅደም ያለባቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
◻ ከአምላክ ለሚሰጠው ነፃነት አቋም በመውሰዳችን እንደምንባረክ የሚያረጋግጡ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉ?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ ሆኖ ከመጠመቅ በፊት መቅደም ያለባቸው ምን እርምጃዎች እንደሆኑ ታውቃለህ?