‘እንደ አስፈላጊነቱ የሚለዋወጥ እምነት’ ያለው ሃይማኖት
“ሞርሞኒዝም ነፃ አመለካከት ባላቸው ዲሞክራሲያዊ መንግሥታትም ሆነ በአምባገነን ጨቋኝ ማህበረሰቦች ሥር ለመስደድ መቻሉ በጣም ያስደንቃል።” ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ይህን የተናገረው የሀንጋሪ መንግሥት ለኋለኛው ዘመን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ እውቅና በሰጠበት ጊዜ ነበር። ቤተክርስቲያኗ ለዚህ የበቃችው እንዴት ነው? ጆርናሉ እንደገለጸው “ቤተ ክርስቲያንዋ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የቻለችበት ቁልፍ ምክንያት ሞርሞኖች በብዛት ተዋልደው ቁጥራቸው ስለበዛ ወይም ወንጌላውያን በትጋት ስለሚያስፋፉ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እምነቱ እንደ አስፈላጊነቱ የመለዋወጥ ባሕርይ ስላለው ነው” ብሏል። እንዴት?
ጆርናሉ በምሥራቅ አውሮፓ በቅርቡ ፖለቲካዊ ለውጥ ከመደረጉ በፊት ስለነበረው ጊዜ ሲናገር “ሞርሞኖች በብሪግሀም ያንግ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቀኞችና የባሕላዊ ዘፋኞች ቡድን በመጠቀም በአብዛኞቹ ኮሚኒስት አገሮች ሚስዮናውያን የሚያጋጥማቸውን ጭቆናና የትብብር እጦት በአቋራጭ ለማለፍ ችለዋል” ይላል። የሙዚቀኛና የዘፋኝ ጓዶቻቸው ወደ ሮማኒያ፣ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ሀንጋሪ፣ ፖላንድና ቻይና እንዲሁም ወደ ሳኡዲ አረቢያ፣ ሊቢያ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ሶማሊያና እስራኤል ሄደዋል። በተጨማሪም “የሞርሞን ቤተክርስቲያን ሀብት ወደ ማርክሲስትና የሦስተኛ ዓለም አገሮች በመግባት ለመደለያነት አገልግሏል።” በሞርሞን የገንዘብ ዕርዳታ ከሚደገፉት ፕሮጄክቶች መካከል የግድብ ግንባታና የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ይገኙበታል።
በዛሬው ተድላ ወዳድና የገንዘብ ረሐብተኛ በሆነው ዓለም ውስጥ እንዲህ የመሰሉት የዘፈንና የጭፈራ እንዲሁም የገንዘብ ተራድኦ ብልሀቶች ኃይለኛ የመሳብ ኃይል ቢኖራቸው አያስደንቅም። (2 ጢሞቴዎስ 3:2, 4) ነገር ግን እውነተኛ በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን የሚስባቸው የመልካሙ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ድምጽ ነው። (ዮሐንስ 10:27) ኢየሱስ ተከታዮቹን “ከአሕዛብ ሁሉ ደቀመዛሙርት እንዲያደርጉ” ሲልካቸው ‘እሱ ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ በማስተማር’ እንጂ በማንኛውም ዘዴ ወይም በማንኛውም ክፍያ ደቀመዛሙርት እንዲያደርጉ ያልተናገረው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህን ተልእኮ በሚፈጽሙበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥነ-ሥርዓት ገሸሽ ማድረግ የለባቸውም።