ከቡከንቫልዱ እስር በኋላ እውነትን አገኘሁ
ተወልጄ ያደግሁት በፈረንሳይ አገር በግረኖብል ከተማ በ1930ዎቹ ዓመታት ነበር። የጀርመንኛ ቋንቋ አስተማሪዬ ፈረንሣዊ ቢሆንም አክራሪ ናዚ ነበር። እርሱም ሁል ጊዜ “ጀርመን ጠቃሚ” የምትሆንበት ጊዜ ይመጣል እያለ ይናገር ነበር። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ አስተማሪዎቻችን በአንደኛው የዓለም ጦርነት የዘመቱ ስለ ነበሩ በጀርመን አገር ናዚዝም እየተስፋፋ መምጣቱ በጣም አሳስቦአቸው ነበር። ጦርነት ቅርብ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መምጣቱ እኔንም አሳስቦኝ ነበር።
በ1940፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ በሶም ወንዝ በተደረገው ውጊያ ላይ የምወደውን አጎቴን አጣሁ። በሁኔታው በጣም ተማርሬ ነበር። ሆኖም በጣም ልጅ ስለ ነበርኩ የፈረንሳይ ጦር ሠራዊት አባል ሆኜ ለመመዝገብ አልቻልኩም። ይሁን እንጂ ከሦስት ዓመት በኋላ ፈረንሳይ በጀርመኖች እጅ ስትወድቅ በፈረንሳይ ድብቅ የመከላከያ ድርጅት ውስጥ የንድፍ ሠራተኛ ሆኜ የማገልገል አጋጣሚ ተሰጠኝ። ፊርማዎችን በመቅዳትና የጀርመኖችን ማህተም አስመስሎ በመሥራት የተዋጣልኝ ሆንኩ። በዚህ መንገድ የጠላትን ኃይሎች ለመዋጋት በመቻሌ ትልቅ እርካታ ስላገኘሁ በዚህ ጊዜ ለጓደኞቼ ኮሚንስታዊ አስተሳሰብ ምንም ያህል ዋጋ አልሰጠሁም ነበር።
እስር ቤት መግባት
ኅዳር 11, 1943 የአካባቢው ድብቅ የመከላከያ ኃይል የአንደኛው የዓለም ጦርነት የተኩስ ማቆም ስምምነት የተደረገበትን መታሰቢያ ለማክበር ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቦ ነበር። ነገር ግን ወደ ጦርነቱ መታሰቢያ የሚወስደው ድልድይ በፈረንሳይ ተንቀሳቃሽ የጥበቃ ቡድን ተዘግቶ ነበር። እነርሱም ወደየቤታችን እንድንመለስ መከሩን። ሰልፈኛው ግን በሌላ በኩል አድርጎ ወደ ጦርነቱ መታሰቢያ ሐውልት ለመሄድ ወሰነ። ይሁን እንጂ አንድ የረሳነው ነገር ነበር። ሐውልቱ ከጌስታፖ ጽሕፈት ቤት ምንም ያህል አይርቅም ነበር።
ቡድናችን በድንገት በታጠቁ ወታደሮች ተከበበ። በግንቡ ፊት ለፊት አሰለፉን። ወታደሮቹ እንድንቀሳቀስ ባዘዙን ጊዜ ብዙ ሽጉጦች መሬት ላይ ወድቀው ተገኙ። የሽጉጦቹ ባለቤት እነማን እንደሆኑ ለመናገር የደፈረ አንድም ሰው አልተገኘም። ወታደሮቹም ሴቶችን፣ 16 ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑትን ሰልፈኞች ብቻ ለቀቁ። እኔም የ18 ዓመት ልጅ ስለነበርኩ ከሌሎች 450 ሰዎች ጋር ታሰርኩ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በሰሜናዊ ፈረንሳይ በካምፕየኝ ከተማ አጠገብ ወደሚገኘው የማረፊያ ካምፕ ተወሰድን።
ወደ ጀርመን ተወሰድን
ጥር 17, 1944 ለመጀመሪያ ጊዜ ከጀርመን ወታደሮች ጋር ተገናኘሁ። የሚያሳዝነው ግን ይህ የመጨረሻው ግንኙነት አለመሆኑ ነው። ወታደሮቹ በቀኝ በኩል በስዋስቲካ ያጌጠ፣ በግራ በኩል ደግሞ ሹትስእሽታፊል የሚለውን ቃል የመጀመሪያ ፊደሎች የያዘ SS በሚል ምልክት ያጌጠ የብረት ባርኔጣ አድርገዋል። ወታደሮቹ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ እስረኞችን ሰብስበዋል። እኛም በኮምፕየኝ ወደሚገኘው ጣቢያ የደረስነው በእግር ጉዞ ነበር። ለመቆሚያ ብቻ የሚሆን ቦታ ባላቸው ሳጥን መሰል የባቡር ፉርጎዎች ውስጥ ተወረወርን። እኔ ባለሁበት ፉርጎ ብቻ 125 እስረኞች ነበርን። ለሦስት ቀንና ለሁለት ሌሊት ያህል ምንም የሚበላ ወይም የሚጠጣ ነገር አላገኘንም። ደክመው የነበሩት እስረኞች ከጥቂት ሰዓቶች በኋላ ተዝለፍልፈው ወደቁና ተረጋገጡ። ከሁለት ቀን በኋላ በማዕከላዊ የጀርመን ግዛት በቫይማር አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቡከንቫልድ ደረስን።
በሽታ እንዳላስተላልፍ መድኃኒት ከተደረገልኝ በኋላ ፀጉሬን ተላጭቼ “ኮሚኒስት ሽብር ፈጣሪ” በሚል ምድብ ውስጥ 41,101 የመዝገብ ቁጥር ተሰጥቶኝ ገባሁ። በሽታ እንዳናስተላልፍ ተገልለን በቆየንበት በዚህ ወቅት የዶሚኒካን ተወላጅ ከሆነው ሚሸል ሪኬ ከተባለ ቄስ ጋር ተገናኘሁ። ይህ ቄስ ከጦርነቱ በኋላ በፓሪስ ካቴድራል በኖትርዳም ባደረጋቸው ስብከቶች ከፍተኛ ዝና አትርፎአል። እንደኔው ወጣቶች ከሆኑት እስረኞች ጋር ሆኜ አምላክ ይህን ሁሉ ሥቃይ ለምን እንደፈቀደ ጠየቅሁት። እርሱም “ወደ ሰማይ ለመሄድ ብዙ መከራ ማሳለፍ ይኖርብሃል” ብሎ መለሰልኝ።
የእስር ቤት ኑሮ
በስድሳ አንዱም የእሥር ቤት ሕንጻዎች ውስጥ የምንገኘው እስረኞች በሙሉ ከሌሊቱ በ10:30 አካባቢ ከእንቅልፋችን እንቀሰቀስ ነበር። ከወገባችን በላይ ራቁታችንን ሆነን ውኃው የተጋገረውን በረዶ እየሰባበርን ገላችንን እንታጠባለን። ጤነኛም ሆነ በሽተኛ እንዲህ ባለው ቀዝቃዛ ውኃ መታጠብ ይኖርበታል። ከዚያም ዳቦ የማደሉ ሥራ ይቀጥላል። በየቀኑ ምንም ጣዕም የሌለው ከ200-300 ግራም የሚመዝን የማርጋሪን ጠብታና ማርማላት የሚመስል ነገር የተደረገበት ዳቦ ይሰጠናል። በ11:30 ላይ ሁላችንም ስማችንን ለመጠራት እንሰበሰባለን። ሌሊት ሞተው ያደሩትን ሰዎች አስከሬን በጀርባችን እየተሸከምን ማውጣት ምን ያህል የሚያሰቅቅ ሥራ ነበር! አስከሬኖቹ ሲቃጠሉ የሚመጣው አፍንጫ የሚሰረስር ሽታ የሞቱብንን ጓደኞቻችንን ያስታውሰን ነበር። እኛም አንድ ቀን እንዲህ ዓይነት ዕድል እንደሚያጋጥመን ስለምናውቅ የጥላቻ፣ የመሰቀቅ፣ ተስፋ የመቁረጥና የቂመኛነት ስሜት ይሰማን ነበር።
በባው 2 ኮማንዶ የግንባታ ሠራተኞች ጓድ ውስጥ የተሰጠኝ ሥራ ለምንም ዓላማ የማይውሉ ጉድጓዶችን መቆፈር ነበር። ሁለት ሜት ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ከቆፈርን በኋላ ወዲያውኑ በጥንቃቄ እንድንሞላው እንታዘዝ ነበር። ሥራው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እኩለ ቀን ላይ ለግማሽ ሰዓት ብቻ ካረፍን በኋላ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ድረስ ይቆይ ነበር። በማታ የሚደረገው የስም ጥሪም በቶሎ የሚያልቅ አልነበረም። በሩሲያ የጦር ግንባር ብዙ ጉዳት ከደረሰባቸው ስም ጥሪው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ይቆያል።
ልዩ የሆኑ እስረኞች
ከመካከላችን ከእስር ቤቱ ለማምለጥ የሚሞክር ማንም ቢኖር በቀላሉ ይታወቃል። ምክንያቱም ፀጉራችን ልዩ በሆነ ሁኔታ ይቆረጥ ስለነበር ነው። መሐል ለመሐል ወይም ከዳርና ከዳር ይላጫል ወይም በአጭሩ ይቆረጣል። ሆኖም የአንዳንድ እስረኞች ፀጉር እንደኛ ዓይነት አቆራረጥ አልነበረውም። እነዚህ ፀጉራቸው ልዩ በሆነ ሁኔታ ያልተቆረጡ ሰዎች እነማን ነበሩ? የክፍላችን ኃላፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆናቸውን ነገረኝ። “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ደግሞ እዚህ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ምን ያደርጋሉ?” ብዬ ተገረምኩ። “ይሖዋን በማምለካቸው ምክንያት የታሰሩ መሆናቸው” ተነገረኝ። ይሖዋ! የአምላክን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት ያኔ ነበር።
ውሎ አድሮ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትንሽ ተጨማሪ እውቀት አገኘሁ። አብዛኞቹ ጀርመናውያን ናቸው። ከእነርሱ መካከል አንዳንዶች ሂትለርን አንታዘዝም በማለታቸው ከ1930ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ጀምሮ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ቆይተዋል። ነፃ መውጣት ይችሉ ነበር። ነገር ግን እጃቸውን ለመስጠት ወይም ከሂትለር ጋር ለመስማማት አልፈለጉም። የኤስ ኤስ ወታደሮች ፀጉር አስተካካዮቻቸው አድርገዋቸው ነበር። እንዲሁም እንደ አስተዳደር በመሳሰሉት እምነት በሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ይመደቡ ነበር። በተለይም የተረጋጉ መሆናቸው፣ የጥላቻ ወይም የተቃውሞ ወይም የመበቀል ስሜት የሌላቸው መሆናቸው ስለ እነርሱ የማወቅ ስሜታችንን ቀስቅሶት ነበር። ለምን እንደዚህ ሊሆኑ እንደቻሉ ለመረዳት አልቻልኩም። በዚያ ጊዜ በቂ የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታ ስላልነበረኝ ከእነርሱ ጋር ለመነጋገር አልቻልኩም።
የሞት ባቡር
የተባባሪዎቹ መንግሥታት ጦር እያየለ በሄደ መጠን እስረኞች ሩቅ ወደሆኑት የአገሪቱ ማጎሪያ ካምፖች ይላኩ ነበር። ይሁን እንጂ ካምፖቹ በጣም በሚዘገንን ሁኔታ ተጨናንቀው ነበር። ሚያዝያ 6, 1945 ጠዋት ላይ የኤስ ኤስ ወታደሮች 5,000 የምንሆን እስረኞችን ወደ ቫይማር በሚወስደው መንገድ ላይ 9 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ያለው መንገድ በእግር እንድንጓዝ አስገደዱን። ከእኛ ጋር እኩል መራመድ ያልቻሉት እስረኞች በጭካኔ ይረሸኑ ነበር። በመጨረሻም ወደ ቫይማር ጣቢያ ስንደርስ የዕቃ መጫኛ በሆኑ ክፍት የባቡር ፉርጎዎች ላይ እንድንሳፈር ተደረገ። ለ20 ቀናት ያህል በጀርመንና በቺኮዝሎቫኪያ መስመሮች ከአንዱ የባቡር ጣቢያ ወደ ሌላው የባቡር ጣቢያ ተንከራተትን።
አንድ ቀን ጠዋት እኛ ያለንበት የባቡር ክፍል ከሐዲዱ ወጥቶ ቆመ። ወታደሮች ጠመንጃቸውን አቀባብለው መጡና የፉርጎውን በር ከፍተው ውስጥ የነበሩትን የሩስያ እስረኞች በሙሉ ጨረሱአቸው። ምክንያቱ ምን ይሆን? አሥራ ሁለት የሚያክሉ እሥረኞች በሌሊት ዘበኛውን ገድለው በማምለጣቸው ነበር። ከፉርጎው ወለል ወደ መንገዱ የፈሰሰው ደም እስከ ዛሬ ድረስ ይታየኛል።
በመጨረሻም ባቡሩ ዳካው ከምትባለው የጀርመን ከተማ ደረሰ። ከሁለት ቀን በኋላም የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ነፃ አወጣን። ለ20 ቀናት ያህል ሕይወታችንን ጠብቆ ያቆየልን ጥቂት ውኃ እና ጥሬ ድንች ብቻ ነበር። ጉዞውን ስንጀምር ከነበርነው 5,000 ሰዎች መካከል የቀረነው 800 ብቻ ነበርን። ብዙዎቹ ደግሞ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሞተዋል። እኔም አብዛኛውን ጉዞ ያሳለፍኩት በአስከሬኖች ላይ ተቀምጬ ነበር።
አዲስ እርምጃ ወሰድሁ
ከእስር ቤት ከወጣሁ በኋላ የፈረንሳይ ኮሚኒስት ፓርቲ ደጋፊ ከመሆን የበለጠ ነገር እንደሌለ ተሰማኝ። በእስር ቤት ሳለሁ ከአብዛኛዎቹ የኮሚኒስት አባሎች ጋር፣ ከግንባር ቀደም መሪዎች ጋር ሳይቀር ወዳጅ ሆኜ ነበር። በግሬኖብል ለሚገኘው ሕዋስ ረዳት ጸሐፊ ሆንኩ። እንዲያውም በፓሪስ በሚሰጠው የአስተዳዳሪነት ኮርስ እንድካፈል ተጠይቄ ነበር።
ይሁን እንጂ ወዲያው ቅር የሚያሰኝ ነገር አጋጠመኝ። ኅዳር 11 ቀን 1945 በፓሪስ ከተማ በሚደረግ ሰልፍ እንድንካፈል ተጋብዘን ነበር። የእኛን ቡድን ይመራ የነበረው ጓድ ለሚያስፈልጉን ነገሮች የሚውል ገንዘብ ተቀብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ገንዘቡን ሊያካፍለን ፈቃደኛ አልሆነም። ሁላችንንም ሊያስተባብሩን የሚገቡትን የሐቀኝነትና የወዳጅነት ሥርዓት ማክበር እንዳለበት ማስታወስ ነበረብን። በተጨማሪም እንቅስቃሴውን በግንባር ቀደምትነት ይመሩ ከነበሩት ሰዎች ብዙዎቹ ለዓለም ችግሮች ምንም ዓይነት መፍትሄ እንደሌላቸው ለመገንዘብ ቻልኩ። ከዚህም በላይ አብዛኛውን ጊዜ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ሲሆኑ እኔ ግን በአምላክ አምን ነበር።
ከዚያም በፈረንሳይ ደቡባዊ ምሥራቅ ወደምትገኘው ወደ ሊዮንስ ተዛውሬ የንድፍ ሥራ መሥራቴን ቀጠልኩ። በ1954 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጉብኝት አደረጉልኝና ለንቁ! መጽሔት ኮንትራት ገባሁ። ከሁለት ቀን በኋላ አንድ ሰው በሬን አንኳኩታ ከነበረችው ሴት ጋር ሊጠይቀኝ መጣ። ባለቤቴ እና እኔ ሁለታችንም ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት ያደረብን መሆኑን ወዲያው ተገነዘብኩ።
ከዚያ ቀጥሎ ባደረግነው ውይይት በቡከንቫልድ የነበሩትን ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አስታወስኩ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር የይሖዋ ምሥክሮች እና እነዚያ በእስር ቤት ከእኔ ጋር የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አንድ መሆናቸውን ያወቅሁት። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ቀጠልንና ባለቤቴና እኔ አቋማችንን አስተካክለን ሚያዝያ 1955 ተጠመቅን።
ሁሉም ነገር ልክ ትናንት እንደተደረገ ያህል ይታወሰኛል። ባሳለፍኳቸው የመከራ ጊዜያት አልቆጭም። ያሳለፍኳቸው የመከራ ጊዜያት የዚህ ዓለም መንግሥታት ለሰው ልጆች ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር በጣም ጥቂት መሆኑን እንድገነዘብ ረድተውኛል። የግል ተሞክሮዎች ለሌሎች ሊሰጡ የሚችሉት እርዳታ መጠነኛ ቢሆንም የእኔም ተሞክሮ ዛሬ ያላችሁትን ወጣቶች የዚህን ዓለም ወራዳነት ሊያሳያችሁ ከቻለና መልካሙን እንድትሹ፣ ክርስቶስ ላስተማረው የክርስትና ሕይወትም ከፍተኛ ዋጋ እንድትሰጡ በትንሹም ቢሆን ከረዳችሁ በጣም ደስ ይለኛል።
ዛሬ፣ ስቃይና የፍትህ መጓደል የዕለት ተለት ኑሮ ክፍሎች ሆነዋል። በማጎሪያ ካምፕ እንደ ነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እኔም ከአመጽና አጥባቂ ከሆነው የሐሳባዊነት ፍልስፍና ይልቅ የወንድማማች ፍቅርና ፍትህ የሚሰፍንበትን ጊዜ እጠባበቃለሁ። እስከዚያው ጊዜ ድረስ በምችለው ሁሉ አምላክንና ክርስቶስን የጉባኤ ሽማግሌ ሆኜ ከባለቤቴ፣ ከልጆቼ እና ከልጅ ልጆቼ ጋር ሆኜ አገለግላለሁ። (መዝሙር 112:7, 8)—ሬኒ ሲግላ እንደተናገረው
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከላይ በኩል፦ የስም ጥሪ ሲደረግ
በስተግራ በኩል፦ የቡከንቫልድ መግቢያ በር። ጽሑፉ “ለእያንዳንዱ እንደሚገባው”የሚል ነው
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከላይ በኩል፦ በቡከንቫልድ የሚገኘው የሬሳ ማቃጠያ
በስተግራ በኩል፦ አስራስድስት እስረኞች በአንድ ላይ ታስረው