የአንባብያን ጥያቄዎች
በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የተጠቀሰው በእንግሊዝኛ ዩኒኮርን የሚባለው አንድ ቀንድ፣ የፈረስ ጭንቅላት፣ የድብ እግር እና የአንበሳ ጭራ ያለው እንስሳ መኖሩን መጽሐፍ ቅዱስ ይደግፋልን?
ይህ ዩኒኮርን የተባለ እንስሳ በኪንግ ጀምስ፣ በዱዌይ እና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ተጠቅሶአል። የዕብራይስጡን ቃል በትክክል የተረጎሙ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ግን ይህን እንስሳ አይጠቅሱም።—መዝሙር 22:21፤ 29:6፤ 92:10 (21:22፤ 28:6፤ 91:11, የድዌይ ትርጉም)
ባለፉት መቶ ዘመናት የፈረስ ጭንቅላት፣ የድብ እግርና የአንበሳ ጭራ ስላለው እንስሳ ብዙ አፈ ታሪኮች ተነግረዋል። ይህ አፈ ታሪክ የፈጠረው እንስሳ በይበልጥ የሚታወቀው በግንባሩ ላይ ባለው ጠመም ያለ ቀንድ ነው።a
“የዩኒኮርን ቀንድ መርዝ የሚያረክስ መድኃኒት አለው ተብሎ ይታመን ስለነበረ በመካከለኛው ዘመን ከዩኒኮርን ቀንድ የተቀመመ ነው የሚባል ዱቄት በጣም ውድ በሆነ ዋጋ ይሸጥ ነበር። ብዙ ምሁራን የዩኒኮርን ምስል የተገኘው አውሮፓውያን ስለ አውራሪስ በወሬ ብቻ ከሰሙት መግለጫ ሳይሆን አይቀርም ብለው ያምናሉ።” (ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ) በአንዳንድ የአሶራውያንና የባቢሎናውያን ሐውልቶች ላይ ባለ አንድ ቀንድ እንስሶች ይታያሉ። እነዚህ ሐውልቶች በአሁኑ ጊዜ አንዱን ጎን ብቻ የሚያሳዩ የአጋዘን፣ የድኩላ፣ የላም ወይም የወይፈን ቅርጾች እንደሆኑ ታውቆአል። ሁለቱም ቀንዶች የማይታዩባቸው ቅርጾች ናቸው።
ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ቅዱሳን ጽሑፎች ዘጠኝ ጊዜ ያህል በዕብራይስጥ ሬኤም ስለተባለ እንስሳ ይጠቅሳሉ። (ዘኁልቁ 23:22፤ 24:8፤ ዘዳግም 33:17፤ ኢዮብ 39:9, 10፤ መዝሙር 22:21፤ 29:6፤ 92:10፤ ኢሳይያስ 34:7) ተርጓሚዎች ለብዙ ዘመናት ይህ ቃል የትኛውን እንስሳ እንደሚያመለክት እርግጠኞች አልነበሩም። የግሪክኛው ሰፕቱዋጅንት ሬኤም ለሚለው የዕብራይስጥ ቃል አንድ ቀንድ ያለው አውሬ ወይም ዩኒኮርን የሚል ትርጉም ሰጥቶታል። የላቲን ቩልጌት ብዙ ጊዜ አውራሪስ የሚል ትርጉም ሰጥቶታል። ሌሎች ትርጉሞች ‘የዱር በሬ’፣ ‘የዱር አራዊት’ ወይም ‘ጎሽ’ የሚል ፍቺ ሰጥተውታል። ሮርበት ያንግ የዕብራይስጡን ቃል እንዳለ በማስቀመጥ “ሪም” ስላሉ የቃሉን ትርጉም ሸፍነዋል።
ዘመናዊ ምሁራን ግን ሪኤም በሚለው ቃል ረገድ የሚነሱትን ብዙ ግራ የሚያጋቡ ሁኔታዎች አስወግደዋል። የቃላት ትርጉም ሊቃውንት የሆኑት ሉትቪግ ከለር እና ቫልተር ባውምጌርትነር ሪኤም ቦስ ፕሪሚጂንየስ በሚል ሳይንሳዊ ስያሜ የሚታወቀው “የዱር በሬ” እንደሆነ አመልክተዋል። ይህም አውሬ “የቀንድ እና የእግር ኮቴ ካላቸው ዝርያዎች የሚመደብ ነው።”ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ ሲያብራራ እንዲህ ይላል፦
“አንዳንድ የብሉይ ኪዳን የግጥም ምንባቦች ሪኤም ስለሚባል ጠንካራ የሆነና አስደናቂ ቀንድ ያለው እንስሳ ይጠቅሳሉ። ይህ ቃል በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ዩኒኮርን ወይም አውራሪስ ተብሎ ተተርጉሞአል። ብዙ ዘመናዊ ተርጓሚዎች ግን ሪኤም የሚለውን የእብራይስጥ ቃል የዱር በሬ ብለው ለመተርጎም መርጠዋል። የዕብራይስጡ ቃል ትክክለኛ ትርጉምም ይህ ነው።”
በዘመናዊው ቋንቋ በሬ የሚለው ቃል የተቀጠቀጠ እንስሳ ስለሚያመለክት የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ሪኤም የሚለውን ቃል “የዱር ወይፈን” በማለት ተርጉሞአል። የዱሩ በሬ ወይም የዱሩ ወይፈን በመካከለኛው ዘመን የጠፋ ቢመስልም ይህ እንስሳ በአፈታሪክ ከሚነገርለት ከዩኑኮርን ፈፅሞ የተለየ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ተረድተዋል። የጥንቱ የዱር ወይፈን 1.8 ሜትር ከፍታ እና 3 ሜትር ቁመት ሲኖረው 900 ኪ.ግ. ክብደትና ከ75 ሴ.ሜ. በላይ ርዝመት ያላቸው ቀንዶች ነበሩት።
ይህ አውሬ በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው ሪኤም ወይም የዱር ወይፈን ጋር ይመሳሰላል። በጥንካሬውና ሊገራ በማይችል ፀባዩ እንዲሁም በፈጣንነቱ የታወቀ አውሬ ነው። (ኢዮብ 39:10, 11፤ ዘኁልቁ 23:22፤ 24:8) በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ዩኒኮርን አንድ ቀንድ ሳይሆን ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውሬ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሙሴ ከዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች የሚወጡት ሁለት ነገዶች የሚኖራቸውን ኃያልነት ለመግለጽ የዱር ወይፈንን ቀንዶች ጠቅሶአል።—ዘዳግም 33:17
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በአፈ ታሪክ የሚታወቀው ዩኒኮርን የተባለ ባለ አንድ ቀንድ እንስሳ መኖሩን አይደግፍም። መጽሐፍ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጀምሮ እስከ ጥቂት ዘመናት በፊት ድረስ ይኖር የነበረውን ግዙፍና አስደናቂ የሆነ የዱር ወይፈን ገፅታ በዝርዝር ባይሆንም በትክክል ገልጾልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፕሮፌሰር ፓውል ሃውፕት ሲያብራሩ ‘በመካከለኛው ዘመን የተሰበሰቡ የአውራሪስ ቀንዶችና ሻርክ የሚመስሉ ዓሶች ጥርሶች (ዩኒኮርን ዓሳ ወይም ዩኒኮርን አሳነባሪ ተብለው ይጠራሉ) የዩኒኮርን ቀንዶች እንደሆኑ ተደርጎ ይቆጠር ነበር’ ብለዋል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል ምንጭ]
አስደናቂ የሆኑና በአፈታሪክ የታወቁ ፍጥረታት ግምጃ ቤት፦ ከታሪካዊ ምንጮች የተገኙ 1,087 ሥዕሎች በሪቻርድ ሂዩበር አሳታሚዎች