በ“ገነት” ውስጥ እውነተኛ ደስታ እያገኙ ነው
ገነት! ብዙውን ጊዜ ሰዎች ስለ ሀዋይ ደሴት ሲያስቡ ይህ ቃል ወደ አእምሮአቸው ይመጣል። ለዚህም በቂ ምክንያት አላቸው። በዚህች ደሴት ላይ ብዙ ሰዎች የገነት ገጽታ የሚሰጥ ነፋሻማ የአየር ጠባይ፣ ሰማያዊ መልክ ያለው ሰማይ፣ የተንዠረገጉ የተምር ዛፎች፣ ሰውነትን የሚያድስ ንፋስና አሸዋማ የባሕር ዳርቻዎች ይገኛሉ።
እነዚህ ሁኔታዎች ብዙ ሰዎችን ከሩቅና ከቅርብ ስበዋል። ሰዎች ከእስያ፣ ከፓሲፊክ፣ ከአሜሪካዎችና እንደ ካሪቢያን ደሴቶችና አውሮፓ ከመሳሰሉት ሥፍራዎችም እንኳን ሳይቀር መጥተዋል። በዚህች ደሴት ላይ ዓመቱን በሙሉ ለስለስ ያለ የአየር ጠባይ ስላለ ብዙ ሰዎች ወደ እዚህች ደሴት ሄደው መኖር ጀምረዋል። ሌሎች ደግሞ አስተማማኝ ኑሮና ደስታ ለማግኘት ሲሉ ወደዚህች ደሴት ሄደዋል። በዚህም ምክንያት ደሴቲቱ የተለያዩ ባሕሎችና ሃይማኖታዊ ሐሳቦች የተቀላቀሉባት የተለያየ ዜግነትና ጎሣ ያላቸው ሕዝቦች መሰባሰቢያ ሆናለች።
ይሁን እንጂ ሁኔታው ሌላም ገጽታ አለው። በምድር ላይ እንዳሉት ብዙ የተዋቡ ቦታዎች ሀዋይም በወንጀል፣ በዕፅ፣ በብልግና፣ በአካባቢ ብከላና በየትኛውም ቦታ ሰብአዊውን ቤተሰብ እያዋከቡት ባሉ ሌሎች ችግሮች ተወርራለች። የሀዋይ ደሴቶች በሰው ቸልተኝነትና ራስ ወዳድነት ምክንያት ቀስ በቀስ የተፈጥሮ ውበታቸውን እያጡ ነው። ሰዎች ገነት ይፈልጋሉ፣ ግን እነዚህ ደሴቶች ገነት እንዲሆኑ ወይም ሌላው ቢቀር ያላቸውን የገነት መልክ ይዘው እንዲቆዩ ለማድረግ ደንታ ያላቸው ሁሉም ነዋሪዎች አይደሉም። ገነትን ለማስገኘት ውብ ከሆነ አካባቢና ከተስማሚ የአየር ጠባይ የበለጠ ነገር ያስፈልጋል።
ይሁን እንጂ በዚህ ገነታዊ ቦታ እውነተኛ ደስታ እያገኙ ያሉ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሕዝቦች አሉ። እነርሱም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበሉና “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁና የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም” ብሎ የተናገረውን የአምላክን አስደናቂ ተስፋ ያስተዋሉ ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” የሚሉትን የሐዋርያው ጴጥሮስን ቃላት በማስታወስ የወደፊቱን ጊዜ ደስ እያላቸው በናፍቆት ይጠባበቃሉ። (ኢሳይያስ 65:17፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) እነዚህ ሕዝቦች እነማን ናቸው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀረበውን አስደናቂ ተስፋ ሊያውቁ የቻሉትስ እንዴት ነው? በሕይወታቸውስ ምን ዓይነት ለውጦችን አድርገዋል?
የሞት ፍራት ተወገደ
ኢዛቤልና ባሏ ጆርጅ የፊሊፒኖ ተወላጆች ናቸው። ኢዛቤል በልጅነቷ መጽሐፍ ቅዱስ አንብባ ባታውቅም የወላጆቿን የካቶሊክ ሃይማኖት እንድትከተል ተኮትኩታ ያደገች ናት። የሰው ነፍስ እንደማትሞት ተምራ ነበር። ታዲያ ይህን የሐሰት መሠረተ ትምህርት ስትሰማ እንዴት ተቀበለችው? ነፍሷ ከሳጥኑ መውጣት ያቅታታል ብላ ታስብ ስለነበረ እስከነሕይወቷ በሬሳ ሣጥን ውስጥ ለዘላለም ተቀብራ እንደምትቀር እያሰበች ሞትን በጣም ትፈራ ነበር። ይሁን እንጂ ኢዛቤል በ1973 መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ጀመረች። የሰው ነፍስ የማትሞት አለመሆኗንና አምላክም በትንሣኤ አማካኝነት ሞትን እንደሚሽር በተማረች ጊዜ በጣም ተደሰተች፣ ከመጠን ያለፈ እፎይታም ተሰማት። (ሕዝቅኤል 18:4, 20፤ ዮሐንስ 5:28, 29) የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በጣም ስላስገረማት ፈጣን መሻሻል አደረገች።
ጆርጅስ? እርሱም ምስክሮቹ ስህተተኞች መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሲል ብቻ በመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቱ ላይ ተገኘ። ይሁን እንጂ ሚስቱና እርሱ በሚማሩት ነገር ላይ ምንም ስህተት ሊያገኝ አልቻለም። እንዲያውም ማጥናት ከጀመሩ ከአጭር ጊዜ በኋላ የደም ጉዳይ ተነስቶ ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከደም የተዘጋጁ ምግቦችን መብላት ይወድ ነበር። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ደም መብላትን በግልጽ እንደሚያወግዝ ባየ ጊዜ ከደም የተዘጋጀ ምግብ መብላቱን አቆመ። (ዘፍጥረት 9:3, 4፤ ዘሌዋውያን 17:10-12፤ ሥራ 15:28, 29) በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ መሳተፉን ቀጠለበትና በመጨረሻም እውነትን በማግኘቱ በጣም ተደሰተ። ዛሬ ኢዛቤል፣ ጆርጅና አራት ልጆቻቸው በአምላክ ሥርዓቶች መሠረት በመኖር እውነተኛ ደስታ እያገኙ ነው።
በእውነተኛው ክርስትና ተሳቡ
ጆርጅ የተባለ ትውልዱ ጃፓናዊ የሆነ አንድ ሰውና ሊሊያን የምትባል ፖርቱጋላዊት ሚስቱ በስድሳዎቹ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ሁለቱም ተወልደው ያደጉት በሀዋይ ነው። ጆርጅ ከወላጆቹ ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ትምህርት ያልተሰጠው ስለነበር ሃይማኖትን ከቁም ነገር የማይቆጥር ነበር። ሆኖም ምንጊዜም በአምላክ ያምን ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ሊሊያንን ወላጆቿ በሮማ ካቶሊክነት ሃይማኖታቸው አሳድገዋት ነበር።
ምንም እንኳን ጆርጅ መጽሐፍ ቅዱስ የማንበብ ጥማት የነበረው ባይሆንም ለ30 ዓመታት ያህል መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን ያነብ ነበር። ይህም በመሆኑ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ አውቆ ነበር። ይሁን እንጂ በጣም ከባድ ጠጪና አጫሽ ስለነበረ በሕይወቱ ለውጥ ለማድረግ በጣም ዘግይቶ ነበር። ዓመታት እያለፉ በሄዱ መጠን ጆርጅ መጽሔቶቹን ማንበቡን ቀጠለና በመንግሥት አዳራሹ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አልፎ አልፎ መገኘት ጀመረ። ለምን? ራሱ እንደተናገረው “ሌሎቹ ሃይማኖቶች በጣም ግብዞች በመሆናቸው” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተወገዙ ብዙ ነገሮችን ችላ ስለሚሉ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ግን የተለዩ እንደሆኑ ሊያይ ችሎ ነበር።
የጆርጅ ሚስት ሊሊያን የወላጆቿን ሃይማኖት የምታጠብቅ ብትሆንም ወደ አምላክ ቃል እውነት የሳባት ነገር ምን ነበር? ሥጋዊ እህቷ በመንግሥት አዳራሹ ወደሚደረገው ስብሰባ ጋበዘቻት። “ደስተኛ ቤተሰባዊ ሁኔታና ወዳጃዊ የፈገግታ አቀባበል አገኘሁ” በማለት ሊሊያን ታስታውሳለች። በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያየችው እውነተኛ ፍቅር እውነት ይህ መሆኑን አሳመናት። (ዮሐንስ 13:34, 35) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ተስማማችና ባሏ ከተጠመቀ ከጥቂት ወራት በኋላ ተጠመቀች።
ጆርጅ ማጨስና መስከሩን አቁሞአል። ሊሊያንም ሃይማኖታዊ ጣዖቶቿን በሙሉ ጥላለች። ፍቅር በተሞላበት ልብ ያወቁትን ለ25 የልጅ ልጆቻቸውና ለ4 ለልጅ ልጆቻቸው ልጆች እያካፈሉ ነው። ፊታቸውን ብቻ በመመልከት ጆርጅና ሊሊያን ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ልታዩ ትችላላችሁ።
ሰላምና ደስታ አገኙ
ፓትሪክ የሚባል በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ የአየርላንድ ተወላጅ ሰውና ኒና የተባለች አይሁዳዊት ሚስቱ ከደቡብ ምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሀዋይ ተዛወሩ። ከዚህ ቀደም ዕፅ ይወስዱ፣ የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶችንና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር። በአጠቃላይ ነፃ አኗኗር በሚባለው ሕይወት የተጠመዱ ነበሩ። በተጨማሪም በዕፅ፣ በመመሰጥ በግል አስተማሪያቸው አማካኝነት ወደ ከፍተኛ ንቃተ ሕሊና ለመድረስ በመጣጣር የአንድ አምልኮ ቡድን አባላት ሆነው ብዙ ዓመታት አሳልፈዋል። ከጊዜ በኋላ ፓትሪክ ‘ከፍተኛ ንቃተ ሕሊና ደረጃ ላይ’ ደርሰናል በሚሉ የአምልኮቱ አባሎች መካከል በነበረው መቀናናት፣ ጭቅጭቅና የማያቋርጥ ጠብ ሰለቸው። የአምልኮ ቡድኑን ተወና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት በማሰብ ከዚህ በፊት ይኖርበት ወደነበረው ወደ ሀዋይ ተመለሰ። ከዚያ በኋላ ፓትሪክ የሴት ወዳጁ የነበረችውን ኒና እንድትመጣና እንድትጠይቀው አግባባት። በመጨረሻም ተጋቡና በሀዋይ ተቀመጡ።
ፓትሪክና ኒና ሰላምና ደስታ ለማግኘት የሚያደርጉት ፍለጋ ባልጠበቁት መንገድ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ማጥናት አደረሳቸው። ሕይወቷን ሙሉ አምላክ የለሽ የነበረችው ኒና ክፋት ለምን ሊኖር እንደቻለ፣ ጥሩ ሰዎች መጥፎ ነገር ለምን እንደሚደርስባቸውና ለመሳሰሉት ጥያቄዎቿ አጥጋቢ የመጽሐፍ ቅዱስ መልሶችን ማግኘት ጀመረች። በተመሳሳይም ፓትሪክ እውነትን ለማግኘት ያደረገው የአሥር ዓመት ፍለጋ ጥሩ ፍጻሜ አገኘ። ወዲያውኑም እርሱና ኒና ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚማሩት ነገር ሥነ ምግባራዊ አመለካከታቸውን ይለውጠው ጀመረ። ከረዥምና ከጠንካራ ትግል በኋላ ፓትሪክ ሥር የሰደደ ኃይለኛ የትንባሆ ሱሱን ለማሸነፍ ቻለ። አሁን ይኸውና አሥር ዓመት ለሚሆን ጊዜ እርሱና ሚስቱ ከአምላክ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ንጹሕ በሆነ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ኖረዋል። አሁን ይፈልጉት በነበረው ሰላም በንጹሕ ልብና በጥሩ ሕሊና እየተደሰቱበት ነው።
መሥዋዕቶችና ሽልማቶች
“በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፣ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም።” (ሉቃስ 13:24) እነዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት አምላክን ማገልገልና በቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓቶች መሠረት መኖር ቀላል አለመሆኑን በግልጽ ያመለክታሉ። ይህን ለማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ የሆኑትን መሥዋዕቶችም ማድረግ አለበት። በዚህ ታሪክ በተጠቀሱት ግለሰቦች ረገድም መሥዋዕት ማድረግ አስፈልጎ እንደነበረ የተረጋገጠ ነገር ነው። ግን ምንኛ በሚያስደንቅ መንገድ ተባረኩ!
ለምሳሌ ያህል ከላይ የተጠቀሱትን ፓትሪክንና ኒናን እንውሰድ። በጣም ከፍተኛ ገቢ ያገኙበት ከነበረው አኗኗር አስገራሚ ለውጥ በማድረግ በትርፍ ጊዜ በሚሠራ ሥጋዊ ሥራ ወደሚደገፍ የሙሉ ጊዜ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ኑሮ ቀየሩት። ሆኖም ካደረጉት ከማንኛውም ቁሳዊ መሥዋዕት በሙሉ መንፈሳዊው ትርፍ በጣም እንደሚያመዝን እርግጠኞች ናቸው፤ ስለዚህም በእርግጥ ደስተኞች ናቸው።
በዕድሜያቸው ምክንያት በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ማድረግ ለጆርጅና ለኒና ቀላል አልነበረም። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በአገልግሎት መካፈል ጊዜ፣ ትኩረትና፣ የጉልበት ጥረት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ጤንነታቸው በመሻሻሉ፣ አሁን የሚመሩት ሕይወት ንቁ፣ የተሟላና ደስተኛ ሕይወት በመሆኑ ተደስተዋል።
ጆርጅና ኢዛቤልን በተመለከተ ትልቁ ችግር የሆነባቸው ልጆቻቸውን ማሠልጠንና ወደ ሕይወት በሚመራው መንገድ ላይ እንዲሄዱ መርዳት ነው። አራት ወጣት ልጆችን ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ማዘጋጀት ወይም በክርስቲያናዊ አገልግሎት አብረዋቸው እንዲሄዱ ለማድረግ ብዙ ጊዜና ጥረት ያስፈልጋል። በአንድ ወቅት ጆርጅና ኢዛቤል የደረሰባቸው የማያቋርጥ ጭንቀት የወላጅነት ኃላፊነታቸውን ችላ እንዲሉ አድርጓቸው ነበር። ነገር ግን “ራስን መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ ማደስ” የተሰኘ ርዕስ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለአራቱ ልጆቻቸው ‘በይሖዋ ምክርና በተግሣጽ ለማሳደግ’ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ዓይነት ትኩረትና ማሠልጠኛ ለመስጠት እጥፍ ድርብ ጥረት እንዲያደርጉ ገፋፋቸው። በእርግጥም እንዲህ ያለው ጥረት በጣም ተባርኮአል።—ኤፌሶን 6:4
ለእነዚህ ግለሰቦችና ለሌሎችም ብዙ ሰዎች እውነተኛ ደስታ ያመጣላቸው የሚያምረው የተፈጥሮ አካባቢ፣ ተስማሚ የአየር ጠባይ ወይም የተዝናናው የኑሮ እንቅስቃሴ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ደስታ ያገኙት ሕይወታቸውን ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መጠቀማቸውና ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው እንደሚኖሩ ማወቃቸው ነው። (መክብብ 12:13) ከዚህም በላይ ምድራዊ ገነት በምድር ዙሪያ የምትመለስበትን አስደሳች ጊዜ ሲያሰላስሉ እውነተኛ ደስታ ከልባቸው ውስጥ ይፈልቃል።—ሉቃስ 23:43
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆርጅ፣ ኢዛቤልና ልጆቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ደስታ አስገኝቶላቸዋል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆርጅና ሊሊያን በክርስቲያናዊ አገልግሎታቸው ደስታ አግኝተዋል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፓትሪክና ኒና በይሖዋ አገልግሎት እውነተኛ ሰላም እያገኙ ነው