ይሖዋ የሚያምኑትን ለማዳን የተጠቀመበት “ሞኝነት”
“በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።”—1 ቆሮንቶስ 1:21
1. ይሖዋ “በሞኝነት” የሚጠቀመው በምን መንገድ ነው? ዓለም በጥበቡ አምላክን እንዳላወቀ እንዴት እናውቃለን?
ምን? ይሖዋ በሞኝነት ይጠቀማል? አይጠቀምም! ይሁን እንጂ ለዓለም ሞኝነት መስሎ በሚታይ ነገር ሊጠቀም ይችላል፣ ይጠቀማልም። ይህንንም የሚያደርገው እርሱን የሚያውቁትንና የሚወዱትን ሰዎች ለማዳን ሲል ነው። ዓለም በጥበብዋ አማካኝነት አምላክን ልታውቅ አትችልም። ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎቱ ላይ “ጻድቅ አባት ሆይ፣ ዓለም አላወቀህም” በማለት ይህን ግልጽ አድርጎአል።—ዮሐንስ 17:25
2. የይሖዋ መንገድና የዓለም መንገድ ጎን ለጎን የሚሄዱ የሚመስለው እንዴት ነው? ሐቁ ግን ምንድን ነው?
2 የይሖዋ መንገዶች ከዓለም መንገዶች እንደሚለዩ የኢየሱስ ቃላት ያመለክታሉ። ላይ ላዩን ሲታዩ የአምላክና የዚህ ዓለም ዓላማዎች ጎን ለጎን የሚሄዱ ሊመስል ይችላል። የዚህ ዓለም ዓላማዎች የአምላክ በረከት ወይም ድጋፍ ያላቸው ሊመስል ይችላል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በምድር ላይ ላሉት የሰው ልጆች ሰላም፣ ደስታና ብልጽግና የሠፈነበት ሕይወት የምታመጣ ጻድቅ መንግሥት እንደሚያቋቁም ይናገራል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ማቴዎስ 6:10) ዓለምም በተመሳሳይ አዲስ የዓለም ሥርዓት ብሎ በሚጠራው መንገድ ለሕዝቦች ሰላም፣ ብልጽግናና ጥሩ መስተዳድር እንደሚሰጥ ያስተጋባል። ይሁን እንጂ የአምላክ ዓላማና የዓለም ዓላማ አንድ ዓይነት አይደሉም። የይሖዋ ዓላማ እርሱ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። ይህንንም የሚያደርገው ምድራዊ መስተዳድሮችን በሙሉ በምትደመስስ ሰማያዊት መስተዳድር አማካኝነት ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 4:11፤ 12:10) ስለዚህ አምላክ ከዚህ ዓለም ጋር የሚገናኝ የጋራ የሆነ ምንም ዓይነት ዓላማ የለውም። (ዮሐንስ 18:36፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለት ዓይነት ጥበቦች ማለትም ስለ “እግዚአብሔር ጥበብ” እና ስለ “ዓለም ጥበብ” የሚናገረውም ለዚህ ነው።—1 ቆሮንቶስ 1:20, 21
የዓለማዊ ጥበብ መሠረታዊ ጉድለት
3. የዓለም ጥበብ አስደናቂ ቢመስልም ሰው አመጣለሁ የሚለው አዲስ ዓለም ፈጽሞ የማያረካ የሚሆነው ለምንድን ነው?
3 የዓለም ጥበብ በአምላክ ጥበብ ለማይመሩ ሰዎች በጣም አስደናቂ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። በጣም ከፍተኛ መስለው የሚታዩ አእምሮን የሚማርኩ ዓለማዊ ፍልስፍናዎች አሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብዙ ሰዎች ታላላቅ ጠቢባን ናቸው የሚሉአቸው ሰዎች ያመነጩአቸውን ዕውቀቶች ያስተላልፋሉ። በጣም ሠፊ የሆኑ ቤተ መጻሕፍቶች የሰው ልጆች በመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ባሳለፋቸው ተሞክሮዎች አማካኝነት በተካበቱ ዕውቀቶች ተሞልተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ቢኖርም ዓለማዊ መሪዎች የሚያልሙት አዲስ የዓለም ሥርዓት ፍጽምና በሌላቸው በኃጢአት በጎደፉ ሟች ሰዎች የሚመራ ከመሆን አያልፍም። ስለዚህ ያ የሚያልሙት ሥርዓትም ፍጽምና የጎደለው፣ ያለፉትን ብዙ ታላላቅ ስህተቶች የሚደግምና የሰው ልጆችን ፍላጎቶች በሙሉ ሊያሟላ የማይችል ይሆናል።—ሮሜ 3:10-12፤ 5:12
4. ሰዎች እናመጣለን የሚሉት አዲስ የዓለም ሥርዓት ለምን ዓይነት ድክመት የተጋለጠ ይሆናል? ውጤቱስ ምን ይሆናል?
4 የሰው ልጅ ለማምጣት ያቀደው አዲስ የዓለም ሥርዓት ለሰው ድካምና ስህተት የተጋለጠ ከመሆኑም በላይ ከክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን—አዎ፣ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ቁጥጥር ሊያመልጥ የማይችል ነው። ሰይጣን “የክርስቶስን የክብር ወንጌል” እንዳያምኑ የሰዎችን ሐሳብ አሳውሮአል። (2 ቆሮንቶስ 4:3, 4፤ ኤፌሶን 6:12) በዚህም ምክንያት ዓለም ተደራራቢ ውጥንቅጦች እየደረሱበት ነው። ዓለም ያለ አምላክ እርዳታና ለመለኮታዊው ፈቃድ ምንም ደንታ ሳይሰጥ ራሱን ለመግዛት በሚያደርገው ሙከራ ራሱን እያቆሰለ ያደማል። (ኤርምያስ 10:23፤ ያዕቆብ 3:15, 16) በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው “ዓለም በጥበብዋ እግዚአብሔርን አላወቀችም።”—1 ቆሮንቶስ 1:21
5. የዚህ ዓለም ጥበብ መሠረታዊ ጉድለት ምንድን ነው?
5 ታዲያ የዚህ ዓለም ጥበብ፣ አዲስ የዓለም ሥርዓት ለማምጣት ያወጣው እቅድ ጭምር መሠረታዊ ጉድለቱ ምንድን ነው? መሠረታዊ ጉድለቱ ችላ ሊባል የማይቻለውን የይሖዋ አምላክን የበላይ ገዥነት ወይም ሉዓላዊነት ችላ ማለቱ ነው። ዓለም በዕብሪት ለመለኮታዊው ሉዓላዊነት እውቅና ለመስጠት አሻፈረኝ ብሏል። ሆን ብሎም ይሖዋን ከዕቅዶቹ በሙሉ በማስወጣት በራሱ ችሎታና ብልሃት ይመካል። (ከዳንኤል 4:31-34ና ከዮሐንስ 18:37 ጋር አወዳድር።) መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት” እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 9:10፤ መዝሙር 111:10) ሆኖም ዓለም ይህን ዋና የጥበብ መሥፈርት እንኳን አላወቀም። እንግዲያውስ ያለ መለኮታዊ እርዳታ እንዴት ሊሳካለት ይችላል?—መዝሙር 127:1
የመንግሥቱ ስብከት ሞኝነት ነው ወይስ ተግባራዊ ጥቅም አለው?
6, 7. (ሀ) በአምላክ ጥበብ የሚመሩ ሰዎች ምን እየሰበኩ ነው? ዓለም ግን እንዴት ይመለከታቸዋል? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የሚሰብኩት በማን ጥበብ መሠረት ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?
6 በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን የሚያውቁ ሰዎች የአምላክ ጥበብ እንዳላቸው ያሳያሉ፣ በእርሱም ለመመራት ይመርጣሉ። ኢየሱስ በትንቢት እንደተናገረው “ይህን የመንግሥት ወንጌል . . . በዓለም ሁሉ” እየሰበኩ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ምድራችን በጦርነት፣ በአካባቢ መቆሸሽ፣ በድህነትና በሰው ልጆች ሥቃይ በተሞላችበት በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ስብከት ተግባራዊ ጥቅም አለውን? ለዓለማዊ ጥበበኞች ስለ አምላክ መንግሥት የሚደረገው ይህ ስብከት ፍጹም ሞኝነትና ተግባራዊነት የጎደለው ሊመስላቸው ይችላል። የአምላክን መንግሥት ሰባኪዎች የሚመለከቷቸው ለመንግሥት እንቅስቃሴ መሰናክል እንደሆኑና ተስማሚ ፖለቲካዊ መስተዳድር ለማምጣት የሚደረገውን ዕድገት የሚጎትቱ መዥገሮች እንደሆኑ አድርገው ነው። ለዚህ አመለካከታቸውም ከዓለም ጥበብ ጋር በመስማማት የሚሰብኩትንና ስለ አምላክ አዲስ ሥርዓትና ስለ መንግሥታዊ መስተዳድሩ መታወቅ የሚያስፈልገውን ነገር ለሰዎች የማይነግሩት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ድጋፍ አላቸው። የክርስቶስ ዋነኛ ትምህርት ግን የአምላክ ንጉሣዊ መስተዳድር እንደነበረ ሊታወስ ይገባል።—ማቴዎስ 4:17፤ ማርቆስ 1:14, 15
7 ታሪክ ጸሐፊው ኤች ጂ ዌልስ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ሳይፈጽሙ የቀሩትን ይህን ግዴታ አስታውሰዋል። እንዲህ በማለት ጻፉ፦ “ኢየሱስ መንግሥተ ሰማይ ብሎ ለጠራው ትምህርት ከፍተኛ ቦታ መስጠቱና በአንጻሩ ግን በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ትምህርት ውስጥ መንግሥተ ሰማይ ከቁምነገር አለመግባቱ የሚያስደንቅ ነገር ነው።” ስለዚህም የዚህ ትውልድ ሕዝቦች ሕይወት እንዲያገኙ ከፈለጉ በመጀመሪያ ስለተቋቋመችው የአምላክ መንግሥት መስማት ያለባቸው ሲሆን መስማት እንዲችሉ ደግሞ ስለ መንግሥቲቱ ምሥራች ሊሰበክላቸው ይገባል።—ሮሜ 10:14, 15
8. የአምላክን የምሥራች መስበክ በአሁኑ ጊዜ ሊደረግ የሚገባው ከሁሉ የበለጠ ተግባራዊ ጥቅም ያለው ሥራ የሆነው ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ ዘላቂ ጥቅም የማይኖረው ምን ማድረግ ነው?
8 እንግዲያውስ የአምላክን የምሥራች መስበክ በዛሬው ጊዜ ሊደረግ የሚገባው ከሁሉ የበለጠ ተግባራዊ ጥቅም ያለው ሥራ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የመንግሥቱ መልእክት በዚህ ‘ለመኖር አስቸጋሪ በሆነ አስጨናቂ ዘመን’ የሰዎችን ልብ በደስታ የሚሞላ እውነተኛ ተስፋ ስለሚሰጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ሮሜ 12:12፤ ቲቶ 2:13) የዚህ ዓለም ኑሮ ምንም እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት፣ የማያስተማምንና በጣም አጭር ሲሆን በአምላክ አዲስ ዓለም የሚኖረው ሕይወት ግን ደስታ፣ ጥጋብና ሰላም የሠፈነበት በዚህችው ምድር ላይ የሚገኝ ዘላለማዊ ሕይወት ነው። (መዝሙር 37:3, 4, 11) ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው “ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?” አንድ ሰው በአምላክ አዲስ ዓለም የመኖር መብት ካጣ ይህ የሚያልፍ ዓለም ምን ይጠቅመዋል? እንዲህ ዓይነቱ ግለሰብ በአሁኑ ጊዜ ከሥጋዊ ነገሮች የሚያገኘው ደስታ ፍሬ ቢስ፣ ከንቱና ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ነው።—ማቴዎስ 16:26፤ መክብብ 1:14፤ ማርቆስ 10:29, 30
9. (ሀ) የኢየሱስ ተከታይ እንዲሆን የተጋበዘ አንድ ሰው ተከታዩ የሚሆንበት ጊዜ እንዲተላለፍለት በጠየቀ ጊዜ ኢየሱስ ምን እንዲያደርግ መከረው? (ለ) የኢየሱስ መልስ እኛን እንዴት ሊነካን ይገባል?
9 ኢየሱስ ተከታዩ እንዲሆን ጋብዞት የነበረ አንድ ሰው “አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ” ብሎ ነበር። ታዲያ ኢየሱስ ምን እንዲያደርግ መከረው? ሰውየው ወላጆቹ ቀሪ ዕድሜያቸውን ጨርሰው እስኪሞቱ ድረስ ሲጠብቅ በጣም ጠቃሚ የሆነውን ሥራ እንደሚያስተጓጉል ስላወቀ ኢየሱስ “ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው። (ሉቃስ 9:59, 60) ክርስቶስን በመታዘዝ ጥበብ የሚያሳዩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተግባር ከመፈጸም ዘወር ሊሉ አይችሉም። መለኮታዊ ጥበብ ይህ ዓለምና መሪዎቹ ሞት የተፈረደባቸው መሆናቸውን አስገንዝቧቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:6፤ 1 ዮሐንስ 2:17) የአምላክን ሉዓላዊ ገዢነት ደጋፊዎች የሰው ልጅ ተስፋ የሚፈጸመው በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነትና አገዛዝ ብቻ እንደሆነ ያውቃሉ። (ዘካርያስ 9:10) ስለዚህ የዚህ ዓለም ጥበብ ያላቸው ሰዎች በአምላክ መንግሥት የማያምኑና ይህችን ሰማያዊት መንግሥት የማይፈልጉ ሲሆኑ በመለኮታዊ ጥበብ የሚመሩ ሰዎች ግን ሌሎች ሰዎችን ይሖዋ ቃል በገባላቸው አዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ በማዘጋጀት እውነተኛ ጥቅም የሚያመጣላቸውን ነገር ያደርጋሉ።—ዮሐንስ 3:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
“ለሚጠፉት ሞኝነት ነው”
10. (ሀ) የጠርሴሱ ሳውል ወደ ክርስትና በተለወጠ ጊዜ ምን ሥራ ጀመረ? (ለ) የጥንቶቹ ግሪኮች በምን ነገር ይታወቁ ነበር? አምላክ ግን ጥበባቸውን እንዴት ተመለከተው?
10 የጠርሴሱ ሳውል በኋላ ጳውሎስ የተባለው የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ይህን ሕይወት አድን የሆነ ሥራ ይሠራ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ሳውልን ወደ ክርስትና ሲለውጠው በሞኝነት ተግባር ሊያሰማራው ፈልጎ ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? ጳውሎስ እንዲህ አላሰበም። (ፊልጵስዩስ 2:16) በወቅቱ የግሪክ ሰዎች ከዓለም በሙሉ የበለጡ ጥበበኞችና ምሁራን እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። በታላላቅ ፈላስፎቻቸውና በጥበበኞቻቸው ይኩራሩ ነበር። ጳውሎስ ግሪክኛ ይናገር የነበረ ቢሆንም የግሪካውያንን ፍልስፍናና ትምህርት አልተከተለም። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ የዓለም ጥበብ በአምላክ ዘንድ ሞኝነት ስለሆነ ነው።a ጳውሎስ የፈለገው የምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ለመስበክ የገፋፋውን መለኮታዊ ጥበብ ነበር። በማንኛውም ዘመን ከነበሩት ሰባኪዎች ሁሉ የበለጠ ሰባኪ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ አርአያ ሆኖታል። ይህንንም ሥራ እንዲሠራ አዝዞታል።—ሉቃስ 4:43፤ ሥራ 20:20, 21፤ 26:15-20፤ 1 ቆሮንቶስ 9:16
11. ጳውሎስ ስለ ስብከት ተልእኮውና ስለ ዓለም ጥበብ ምን እንደተናገረ ሊቆጠር ይችላል?
11 ጳውሎስ ስለተሰጠው የስብከት ተልእኮ ሲናገር የሚከተለውን ብሏል፦ “ክርስቶስ የላከኝ የምሥራቹን ቃል እንዳበሥር ነው . . . ክርስቶስ በመስቀል [በመከራ እንጨት አዓት] ላይ ተሰቅሎ መሞቱ [ቤዛዊ መሥዋዕትነቱ] ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር የምሥራቹን ቃል የማበሥረው ከሰው ጥበብ በተገኘ ንግግር አይደለም። ክርስቶስ በመስቀል [በመከራ እንጨት አዓት] ላይ ተሰቅሎ ሞተ የሚለው ቃል ለሚጠፉት ሰዎች እንደ ሞኝነት ይቆጠራል፤ ለምንድን ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው። ምክንያቱም “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የሊቃውንትንም ዕውቀት አስወግዳለሁ” ተብሎ ተጽፎአል። ታዲያ ጥበበኛ የት አለ? ሊቅስ የት አለ? ተመራማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ሞኝነት አድርጎት የለምን? የዚህ ዓለም ሰዎች በገዛ ጥበባቸው እግዚአብሔርን ማወቅ እንዳይችሉ እግዚአብሔር በጥበቡ ዘጋባቸው፤ ነገር ግን ለዓለም እንደ ሞኝነት በሚቆጠረው የወንጌል መልእክታችን የሚያምኑትን ለማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖአል።”—1 ቆሮንቶስ 1:17-21 የ1980 ትርጉም
12. ይሖዋ “በስብከት ሞኝነት” አማካኝነት ምን እያከናወነ ነው? “ላይኛይቱን ጥበብ” የሚሹ ግን እንዴት ምላሽ ይሰጣሉ?
12 የማይታመን ነገር ቢመስልም ይሖዋ ሰባኪዎቹ አድርጎ የሚጠቀመው ዓለም ሞኞች ናቸው በሚላቸው ሰዎች ነው። አዎ፣ አምላክ በእነዚህ ሰባኪዎች የአገልግሎት ሞኝነት አማካኝነት የሚያምኑትን ያድናል። ይሖዋ የዚህ “ሞኝነት” ሰባኪዎች ራሳቸውን እንዳያከብሩ፣ በእነርሱ አማካኝነት የምሥራቹን የሰሙ ሰዎችም የነገሩአቸውን ሰዎች እንዳያከብሩ አድርጎአል። ይህም የሆነው “ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ” ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:28-31፤ 3:6, 7) እውነት ነው፣ ሰባኪው በጣም አስፈላጊ የሆነ የሥራ ድርሻ አለው። ይሁን እንጂ የሚሰበክለት ሰው የሰማውን መልእክት ካመነ መዳን የሚያስገኝለት ሰባኪው ሳይሆን ሰባኪው እንዲሰብክ የተሰጠው መልእክት ነው። “የላይኛይቱን ጥበብ” የሚፈልጉ ሰዎች ሰባኪው ሞኝና የተናቀ መስሎ ስለታያቸው፣ ስደት ስለደረሰበትና ከቤት ወደ ቤት ስለሚሄድ የሚነግራቸውን መልእክት አይንቁም። በዚህ ፈንታ ትሑት የሆኑ ሰዎች ሰባኪውን በይሖዋ እንደተላከና በአምላክ ስም እንደመጣ ሰባኪ አድርገው ያከብሩታል። ሰባኪው በአፍ በሚነገር ቃልም ይሁን በጽሑፍ ለሚያመጣላቸው መልእክት ከፍተኛ ቦታ ይሰጣሉ።—ያዕቆብ 3:17፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13
13. (ሀ) አይሁዶችና ግሪኮች ስለተሰቀለው ክርስቶስ የሚገልጸውን ስብከት እንዴት ተመለከቱት? (ለ) የኢየሱስ ተከታዮች እንዲሆኑ ያልተጠሩት ምን ዓይነት ሰዎች ነበሩ? ለምንስ?
13 ጳውሎስ ስለ አምላክ መንገዶች መናገሩን በመቀጠል እንደሚከተለው ይላል፦ “መቼም አይሁዳውያን ምልክትን [ተአምር ማየትን] ይፈልጋሉ፤ ግሪካውያን ደግሞ ጥበብን ይሻሉ። እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው። ለተጠሩት ግን፣ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፣ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው። ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባልና፣ የእግዚአብሔርም ድካም [የእግዚአብሔር ደካማነት ነው ተብሎ የሚታሰበው ነገር የ1980 ትርጉም] ከሰው ይልቅ ይበረታልና። ወንድሞች ሆይ፣ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ኃያላን የሆኑ ብዙዎች፣ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ።”—1 ቆሮንቶስ 1:22-27፤ ከኢሳይያስ 55:8, 9 ጋር አወዳድሩት።
14. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ የተላኩ ስለመሆናቸው መረጃ እንዲሰጡ ቢጠየቁ ምን ያሳያሉ? (ለ) ጳውሎስ የዓለምን ጥበብ በማሳየት ግሪካውያንን ለማስደሰት ያልፈለገው ለምን ነበር?
14 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ አይሁድ ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠይቀውት ነበር። (ማቴዎስ 12:38, 39፤ 16:1) ኢየሱስ ግን አልሰጣቸውም። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ የተላኩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያሳዩት ምልክት የላቸውም። ከዚህ ይልቅ በኢሳይያስ 61:1, 2፤ ማርቆስ 13:10፤ ራእይ 22:17 እና በመሳሰሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አማካኝነት ምሥራቹን የመስበክ ተልእኮ የተሰጣቸው መሆኑን ያሳያሉ። የጥንቶቹ ግሪኮች ጥበብን፣ ማለትም በዚህ ዓለም ነገሮች ከፍተኛ ትምህርት ማግኘትን ይሹ ነበር። ጳውሎስም የዚህን ዓለም ጥበብ የተማረ ሰው ቢሆንም ግሪካውያን ጥበቡን እንዲያዩለት በማድረግ ሊያስደስታቸው አልፈለገም። (ሥራ 22:3) በተራቀቀው የግሪክኛ ሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ከመጻፍና ከመናገር ይልቅ የተራው ሕዝብ መነጋገሪያ በነበረው ቋንቋ ይናገርና ይጽፍ ነበር። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንደሚከተለው በማለት ነግሯቸዋል፦ “እኔም፣ ወንድሞች ሆይ፣ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። . . . እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፣ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።”—1 ቆሮንቶስ 2:1-5
15. ጴጥሮስ በምሥራቹ ላይ የሚያሾፉ ሰዎችን ስለ ምን ነገር አሳስቦአቸዋል? የአሁኑ ጊዜ ሁኔታ ከኖኅ ዘመን ጋር ተመሳሳይ የሆነው እንዴት ነው?
15 ሐዋርያው ጴጥሮስ በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ስለ መጪው የአምላክ አዲስ ዓለምና እየቀረበ ስላለው የዓለም ፍጻሜ በሚገልጸው የምሥራች ላይ የሚዘብቱትን ሰዎች በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለምም “በውኃ ሰጥሞ እንደጠፋ” ሐዋርያው ጴጥሮስ አሳስቦአቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:3-7) ኖኅ ያ መቅሰፍታዊ ፍጻሜ በተደቀነበት ጊዜ ምን አደረገ? ብዙ ሰዎች ስለ ኖኅ የሚያስቡት መርከብ ሠሪ እንደነበረ ብቻ ነው። ጴጥሮስ ግን አምላክ በጥንቱ ዓለም ላይ የውኃ መጥለቅለቅን ሲያመጣ “ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አዳነው” በማለት ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 2:5) ከጥፋት ውኃ በፊት ይኖሩ የነበሩ አምላካዊ ያልሆኑ ሰዎች በዓለማዊ ጥበባቸው በመታመን በኖኅ ስብከት እያሾፉ ሞኝ፣ ያልተጨበጠና ተግባራዊ ጥቅም የሌለው ነገር እንደሚናገር ሰው ቆጥረውት እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ይህን ያለንበትን ትውልድ ከኖኅ ትውልድ ጋር ስላመሳሰለው ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች ከኖኅ ዘመን ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ እያጋጠማቸው ነው። ይሁን እንጂ አሿፊዎች ቢኖሩም የመንግሥቱ ምሥራች ስብከት ተራ ወሬ አይደለም። የዛሬውም ስብከት እንደ ኖኅ ስብከት ለሰባኪውም ሆነ ለሚያዳምጡት ሰዎች ደህንነት የሚያመጣ ነው!—ማቴዎስ 24:37-39፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16
‘ጥበበኛ ለመሆን ሞኝ መሆን’
16. የዚህ ዓለም ጥበብ በአርማጌዶን ምን ይደርስበታል? በሕይወት ተርፈው ወደ አምላክ አዲስ ሥርዓት የሚገቡትስ እነማን ናቸው?
16 ይሖዋ አምላክ በቅርቡ በአርማጌዶን ላይ “የጥበበኞችን ጥበብ” ያጠፋል። አዲስ ዓለማቸው እንዴት አድርጎ ለሰው ልጆች የተሻሉ ሁኔታዎችን እንደሚያመጣ ትንቢት ይናገሩ የነበሩትን “አስተዋዮች ጥበብ” አሽቀንጥሮ ይጥላል። “ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን የሚሆነው ጦርነት” የዚህን ዓለም አታላይ ፍልስፍናና ጥበብ ፈጽሞ ያጠፋል። (1 ቆሮንቶስ 1:19፤ ራእይ 16:14-16) ከዚያ ጦርነት ድነው በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ይህ ዓለም ሞኝነት ብሎ የሚጠራውን፣ የይሖዋ ክብራማ የመንግሥት ምሥራች የሚታዘዙ ሰዎች ብቻ ናቸው።
17. የይሖዋ ምሥክሮች ‘ሞኞች’ የሆኑት እንዴት ነው? የአምላክ የምሥራች ሰባኪዎች ምን ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል?
17 በአምላክ መንፈስ የሚመሩት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም ሞኝነት ብሎ የሚጠራውን መልእክት መስበክ አያሳፍራቸውም። ዓለማዊ ጥበብ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ‘ሞኞች’ ሆነዋል። እንዴት? ጳውሎስ “ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን” በማለት እንደጻፈው እነርሱም ጥበበኞች ይሆኑ ዘንድ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ይሠራሉ። (1 ቆሮንቶስ 3:18-20) የይሖዋ ምሥራች ሰባኪዎች የሚሰብኩት መልእክት ሕይወት አድን መሆኑን ያውቃሉ። ስለዚህም ይህ ዓለምና ጥበቡ በአርማጌዶን ጦርነት ፈጽሞ እስኪጠፋ ድረስ ያለማቋረጥ ይሰብካሉ። በቅርቡ ይሖዋ አምላክ ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ከማረጋገጡም በላይ “በስብከት ሞኝነት” አምነው እርምጃ ለሚወስዱ ሰዎች ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ምንም እንኳ የጥንታዊቷ ግሪክ ጥበበኞች ብዙ ፍልስፍና ነክ ክርክርና ምርምር ቢያደርጉም ለእውነተኛ ተስፋ ምክንያት የሚሆናቸው ምንም ነገር እንዳላገኙ ጽሑፎቻቸው ያሳያሉ። ጄ አር ኤስ ስቴረትና ሳሙኤል አንገስ የተባሉት ፕሮፌሰሮች “ከግሪካውያን ሥነ ጽሑፎች የበለጠ የሕይወትን አሳዛኝነት፣ የፍቅርን ዘላቂ አለመሆን፣ የተስፋን አታላይነትና የሞትን ጭካኔ የሚመለከቱ አሳዛኝ ምሬቶች የተገለጸበት ሥነ ጽሑፍ የለም” በማለት ያስገነዝባሉ።—የፈንክና የዋግናልስ አዲስ “መደበኛ” የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ 1936፣ ገጽ 313
ምን ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ምን ሁለት ዓይነት ጥበቦች አሉ?
◻ የዓለም ጥበብ መሠረታዊ ጉድለቱ ምንድን ነው?
◻ የምሥራቹን መስበክ ከሁሉ የበለጠ ተግባራዊ ጥቅም ያለው ለምንድን ነው?
◻ በቅርቡ የዓለም ጥበብ በሙሉ ምን ይደርስበታል?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም ሞኝነት ብሎ የሚጠራውን መልእክት መስበክ የማያሳፍራቸው ለምንድን ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ግሪኮች ዓለማዊ ጥበብን ይሹ ስለነበር የጳውሎስን ስብከት እንደ ሞኝነት ቆጥረው ነበር