የብዙ ውኃዎችን መንደር እውነት አጥለቀለቃት
እንዴት ያለ እንግዳ ነገር ነው! በብዙ ውኃዎቿ የታወቀችው ምድር የተጠማች ሆና ተገኘች! ውኃ በደንብ የምታገኘው አካባቢ ደረቅና ውኃ አልባ ሆና ተገኘች! ይህም ጥማት ከአምላክ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ በሚገኝ የእውነት ውኃ ብቻ ሊረካ የሚችል ነው። ይህ ከቤይሩት 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሰሜናዊ ሊባኖስ ክፍል ባሉ ተራሮች ላይ የምትገኘው 2,200 ነዋሪዎች ያሉባት ራህቤ የምትባል ትንሽ መንደር ታሪክ ነው።
ራህቤ የተባለው ስም በአረብኛ “ሰፋ ያለ ቦታ” ማለት ሲሆን “ሰፊ፣ የተንጣለለ” የሚል ትርጉም ካለው ሴማዊ ቃል የመጣ ነው። መንደሯ ከባሕር ወለል በላይ 600 ሜትር ባላቸው በሁለት ትልልቅ ኮረብታዎች ላይ የተንጣለለች ስለሆነች ስሟ ተገቢ ነው። በበረዶና በጸደይ ወራት በምሥራቅ በኩል ባሉት ተራሮች አናት ላይ በረዶ ሊታይ ይችላል። ይህም ታላቅ ውበትን ይጨምርላታል። ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ ራህቤ የብዙ ውኃዎች መንደር ነች። ስንዴ፣ አፕሪኮት፣ ፔርስ፣ ኮክ እና ወይን ለሚያበቅሉት በዙሪያዋ ላሉ ለም ማሳዎች ውድ የሆነውን ውኃ የሚሰጡ 360 የሚያክሉ ትንንሽና ትልልቅ ምንጮች አሏት።
የድሮውና የአሁኑ ታሪክ የሚገናኙባት ራህቤ
በብዙ አቅጣጫዎች በራህቤ ያሉ ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ጀምሮ እንዳሉ ቆይተዋል። በመንደሩ ውስጥ ያሉት ቤቶች በጣም የተጠጋጉ ናቸው። መንገዶቹ ጠባብ፣ ጠመዝማዛ እንዲሁም አህዮችና ላሞች የሚርመሰመሱባቸው ናቸው። አንዳንድ የሞተር ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም እዚህ እንስሳትም በጎዳናዎች ላይ የመጓዝ መብት አላቸው። ብዙውን ጊዜ ባለቤቶቻቸው ከማሳው ላይ ዕቃዎችን ያሸክሟቸውና ራሳቸው ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ ይልኳቸዋል። ቀጭኑን መንገድ እየተከተሉ በተጨናነቁ ቦታዎች እየተሹለከለኩ በመሄድ እቤታቸው ይመለሳሉ። ይህ ሁኔታ ኢሳይያስ “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ” ብሎ ሲናገር በአእምሮው ይዞት ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ይሆን?—ኢሳይያስ 1:3
ራህቤ ልዩነቶችም የሚንጸባረቁባት ከተማ ነች። በአንድ በኩል የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በሌላው በኩል ጭራሽ ከተማ እንኳን ሄደው የማያውቁ ገበሬዎችን በመንደሯ ታገኛላችሁ። ዙሪያውን በአትክልት የተከበቡ ቪላዎችና እንስሳት የሚሯሯጡባቸው ትንንሽ ጎጆዎች አሉ። በየቤቱ ማለት ይቻላል የኤሌክትሪክ እቃዎች አሉ፤ ቢሆንም ኤሌክትሪክ ሁልጊዜ አይገኝም። በዚህ ምክንያት ብዙ ቤቶች የኤሌክትሪክ ጄነሬተሮች አሏቸው። ዋና ዋናዎቹ የመንደሯ ጎዳናዎች አስፋልት ቢሆኑም ወደ ማሳው የሚወስዱት ጥርጊያ መንገዶች ግን ወጣ ገባና ኮረኮንች ናቸው። ስለዚህ በማሳው ላይ የተመረተውን ምርት ለማጓጓዝ ያለው ብቸኛ መንገድ በቤት እንስሳት መጠቀም ነው። በማሳው ላይ ከእርሻ እንስሳት ጋር አብረው ለሚሠሩት የእርሻ መሣሪያዎች ኃይል መስጫ የሚያገለግል የኤሌክትሪክ ጄነሬተር አንድ አህያ ተሸክሞ ሲሄድ ትመለከቱ ይሆናል።
በተመሳሳይም በመንደሯ ውስጥ ያለው ኑሮም እምብዛም አልተቀየረም። በመንደሩ ውስጥ ብታድሩ ከሌሊቱ በስምንት ወይም በዘጠኝ ሰዓት ላይ በአውራ ዶሮ ጩኸት ትቀሰቀሳላችሁ። የተለመደው የዕለቱ ሂደት የሚጀመረው በማለዳ ነው። ስለዚህ ገና ጨለማ እያለ እንስሶቻቸውን ለሥራ እያዘጋጁ ጮክ ብለው የሚያወሩ የሰዎችን ድምጽ ብትሰሙ አትደነቁ። ገና ጎህ ሲቀድ ብዙ መንደርተኞች ዕቃ ከተሸከሙት እንስሶቻቸው ጋር ወደ ማሳዎች ወይም ዕቃዎቻቸውን ለመሸጥ ወደ ገበያ ሲሄዱ ታያላችሁ።
ፀሐይዋ ሞቅ እያለች ስትሄድ ትንንሽ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በመንገዶቹና በአደባባዮቹ ላይ ሊጫወቱ ይወጣሉ። ልክ ነቢዩ ዘካርያስ “የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ” በማለት እንደገለጸው በኢየሩሳሌም የነበረውን በሚመስል ሁኔታ ጩኸታቸውና ሳቃቸው አየሩን ይሞላዋል። (ዘካርያስ 8:5) መንደርተኞቹን ሰው ወዳዶችና ጥያቄዎችን የሚያበዙ ሆነው ታገኟቸዋላችሁ። ማን እንደሆናችሁ፣ ከየት እንደመጣችሁ፣ ለምን እዚያ እንደመጣችሁና ወዴት እንደምትሄዱ ሳይቀር ማወቅ ስለሚፈልጉ ላገኛችሁት ለእያንዳንዱ መንደርተኛ ሰላምታ እንድትሰጡ ይጠበቅባችኋል። ሰዎቹ እርስ በርሳቸው በደንብ ይተዋወቃሉ።
የእውነት ውኃ ራህቤ ደረሰ
እንዲህ በተቀራረበ ማኅበረሰብ ውስጥ ወሬ በፍጥነት ይዛመታል። አሳድያውኒስ በ1923 ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ራህቤ በተመለሰ ጊዜም የደረሰው ነገር ይኸው ነው። አሳድ በአሜሪካ ውስጥ ሀብታም ሆኖ ይሆናል በማለት አስቦ ጓደኛው አብደላ ብላል ሊጠይቀው መጣ። አሳድ ግን ስለ ገንዘብ በማውራት ፈንታ ዘ ሀርፕ ኦፍ ጎድ (የአምላክ በገና) የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ሰጠውና “እውነተኛ ሀብት ይኸውልህ” አለው። በፊት ፕሮቴስታንት የነበረው አብደላ ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ አነበበና ስሜቱ በጣም ተነካ። ምንም እንኳ አሳድ ብዙ ማብራሪያ ባይሰጠውም አብደላ በተማረው ነገር በጣም ተደስቶ እውነትን እንዳገኘ በግልጽ ይናገር ጀመር።
ጥቂት ቆይቶ አብደላ በሰሜናዊ ሊባኖስ ወዳለችው ትልቅ ከተማ ወደ ትሪፖሊ ሄደ። እዚያም በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሚለው ስም ይጠሩ የነበሩትን በርካታ የይሖዋ ምስክሮችን ለማግኘት ቻለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱም ተጨማሪ ዕድገቶችን አደረገ። ቆይቶም የተማረውን የምሥራች ለማሰራጨት ወደ ራህቤ ተመለሰ። መንደርተኞቹን እንደ ስላሴ፣ ሰው ዘላለማዊ ነፍስ አለው ወይስ የለውም፣ እንደ ሲኦል፣ ቅስና፣ ቅዳሴ እንዲሁም ስዕልን ለአምልኮ እንደመጠቀም ባሉ ውይይቶች ላይ እንዲሳተፉ እያደረገ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ ምን እንደሚያስተምር በመንገር ያካፍላቸዋል።
አንዳንድ መንደርተኞች ፍላጎት አሳዩ። ከእነርሱ መካከል ሦስት ወይም አራት የሚሆኑት በስብከቱ ሥራ አብደላን ተባበሩት። ከዚያም እሁድ እሁድ መሰብሰብ ጀመሩ። ይህም በሸክላ ላይ የተቀዱ ንግግሮች መስማትን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን ከዚያም በሰሙት ነገር ላይ መወያየትን ይጨምራል። ቆይቶም የአምላክ በገና፣ ሀብት እና “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የሚሉትን መጽሐፎች ጨምሮ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን መጠቀም ጀመሩ። ተሰብሳቢዎቹ ከአስር ሰዎች የማይበልጡ ሲሆኑ ከነሱም አብዛኞቹ ፍላጎት ከማሳየት ይልቅ ሁኔታውን ለማየት ጉጉት የነበራቸው ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ የሚመጡበት ዋናው ምክንያት ከእያንዳንዱ ስብሰባ መጨረሻ ላይ የሚዘጋጀውን ምግብ ለመብላት ነበር።
በ1940ዎቹ አብደላ ብላል በራህቤ ያለውን ቡድን የመምራት ኃላፊነት ተሰጠው። እሱም ለሌሎች መልካም ምሳሌ እያሳየ ቀናተኛና ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ እንደሆነ አረጋግጧል። ከእነዚህም አንዱ ወንድም ማታር ሲሆን ለምስክርነት ሥራቸው እንዴት ይወጡ እንደነበር ሲናገር እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “በዚያ ጊዜ መኪና ስላልነበረ ወንድም ብላልና እኔ በቅርብ ላሉ መንደሮች ለመመስከር በእግራችን እንሄድ ነበር። እኔ የሸክላ ማጫወቻውን ስይዝ ወንድም ብላል ደግሞ ተናጋሪ ሆኖ ያገለግል ነበር። ብዙውን ጊዜ ወደ ቤታችን ሳንመለስ ለሁለት ወይም ለሦስት ቀናት እንቆይ ነበር።” ወንድም ብላል በ98 ዓመቱ በ1979 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል።
ዕድገት ተቃውሞን አመጣ
ሥራው እያደገ ሲሄድ ወንድሞች ተቃውሞ ያጋጥማቸው ጀመር። በ1950 በመንደሩ ቄስ ገፋፊነት በራህቤ ባሉ ወንድሞች ላይ የስደት ዘመቻ ተጀመረ። ቄሱ ወንድሞች ቤተ ክርስቲያንንና ቅዱስ ነገሮችን እንዳረከሱ አድርጎ ከሰሳቸው። አንዳንድ መንደርተኞች በጣም ከመናደዳቸው የተነሳ ወንድሞችን በድንጋይ መቱአቸው፤ አንዳንድ ወንድሞችም ታሰሩ። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ የተደረጉ ምርመራዎች ክሱ ሐሰት መሆኑን አረጋገጡ። ያም ሆኖ ግን ወንድሞች በርከት ላሉ ቀናት እስር ቤት ቆዩ።
ሌላው ተቃዋሚ ደግሞ መንደርተኞቹን፣ በደንብ ማንበብ የማይችሉትን አንዳንዶችን ጭምር፣ ወንድሞች አሁንም አሁንም እቤታቸው እየሄዱ ሰዎቹን እንደሚረብሹ የሚናገረውንም ጨምሮ ብዙ ክስ በሰፈረበት ወረቀት ላይ እንዲፈርሙ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ወረቀቱ ላይ የሰፈረውን ፊርማ ለማብዛት ሲል አንድ ሠራተኛ ወደ መንደሩ እንዲዛወር የቀረበ አቤቱታ መሆኑን ለሰዎቹ ነገራቸው። ሰዎቹ ነገሩ በምስክሮቹ ላይ የተደረገ ክስ መሆኑን ሲያውቁ ፊርማቸውን ሰረዙ። እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች በአካባቢው ላሉ ብዙ ባለ ሥልጣኖች ጥሩ ምስክርነት ለመስጠት ረድተዋል።
እንዲህ ካሉት ግልጽ ተቃውሞዎች በተጨማሪ ወንድሞች ሌላ ዓይነት እንቅፋት ገጥሟቸዋል። ሁሉም ሰው እያንዳንዱን ሰው በሚያውቅበት እንዲህ ባለው ትንሽ መንደር ውስጥ ምሳሌ 29:25 እንደሚያመለክተው “ሰውን መፍራት ወጥመድ ያመጣል።” ያለማቋረጥ ለሚነቅፏቸውና ለሚያሾፉባቸው ጎረቤቶች፣ ወዳጆችና ዘመዶች ለመስበክ ወንድሞች ድፍረት አስፈልጓቸዋል። እንግዲያው በማቴዎስ 10:36 ላይ “ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት እውነተኛ ትርጉም አላቸው። ሆኖም ምሳሌው በመቀጠል እንደሚገልጸው “በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል።” የወንድሞች እምነትና ጽናት ተወዳዳሪ የሌላቸው ውጤቶችን አስገኝተዋል።
ራህቤን እውነት አጥለቀለቃት
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ መንደርተኞቹ የይሖዋ ምስክሮችን መልካም ጠባይ ለማድነቅ ቻሉ፤ ብዙዎችም እውነትን ተቀበሉ። በ1969 ሁለተኛው ጉባኤ በራህቤ ሲቋቋም ወንድሞች በጣም ተደሰቱ። ጠንክረው መሥራታቸውንም ቀጠሉ። ብዙዎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ጀመሩ። እንዲያውም አንዳንዶች ወደ ቤይሩትና ወደ ሌሎችም የአገልግሎት ክልሎች ተዛውረው ማገልገል ጀመሩ። ይሖዋም ብርቱ ሥራቸውን ባረከላቸውና በ1983 በራህቤ ውስጥ ሦስተኛው ጉባኤ ተቋቋመ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙ ወንድሞች ለመኖር ወደ ከተሞች ሄዱ። ጭማሪው አሁንም ቀጠለና በ1989 አራተኛው፣ በመቀጠል ደግሞ በ1990 አምስተኛው ጉባኤ ተቋቋመ።
በዚህ ጊዜ በመንደሩ ውስጥ ያለ ሁሉም ቤተሰብ ለማለት ይቻላል ምስክር የሆነ ዘመድ ወይም ጓደኛ ሊኖረው ችሏል። በአንድ ወቅት ላይ የነበረውም ጥላቻ በረደ። ሰዎች ከምስክሮቹ ጋር በተሻለ ሁኔታ ተዋወቁ። እንዲያውም “ሽማግሌ”፣ “አቅኚ”፣ “የክልል የበላይ ተመልካች”፣ “ስብሰባ” እና “አርማጌዶን” የሚሉት ቃላት የመንደርተኞቹ መነጋገሪያ ቃላት ክፍል ሆነዋል። እንደ ክልል የበላይ ተመልካች ጉብኝት ወይም የመታሰቢያው በዓል ባሉ ልዩ አጋጣሚዎች ላይ መንገዶቹ ባዶ ይሆኑና የመንግሥት አዳራሾቹ በሕዝብ ይጠቀጠቃሉ። እንዲያውም አንዳንድ ጉባኤዎች ለጎረቤቶቹ ምቹ እንዲሆንላቸው በማሰብ ድምጽ ማጉያዎችን በሰገነቱ ላይ ያስቀምጣሉ።
አሁን በራህቤ ውስጥ ከ250 በላይ የመንግሥት አስፋፊዎች አሉ። ይህም ማለት በመንደሩ ውስጥ ካሉት 8 ሰዎች አንዱ ምስክር ነው ማለት ነው! 51 አስፋፊዎች ያሉት አንድ ጉባኤ 76 ቤቶች ያሉበት የአገልግሎት ክልል ሲኖረው በየሳምንቱ ይሸፍኑታል። ባለፈው ዓመት ከ250 አስፋፊዎች ውስጥ 98ቱ የረዳት አቅኚዎች 13ቱ ደግሞ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው በነበሩበት በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት በራህቤ ውስጥ ምን ተፈጽሞ እንደነበር ገምቱት። የአገልግሎት ክልሉ በያንዳንዱ ሳምንት ብዙ ጊዜ ይሸፈን ነበር። አንድ ቤት በዚያው ቀን ወይም በዚያው ሰዓት እንኳን ሁለት ወይም ሦስት ጥንድ አስፋፊዎች መንኳኳቱ ያልተለመደ ነገር አልነበረም። አብዛኞቹ መንደርተኞች ከዚህ ጉብኝት ጋር ተለማምደዋል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው በማማረር በተናገረ ጊዜ አንድ አስፋፊ፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያጠኑ የምናቀርብልዎትን ግብዣ ቢቀበሉ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እንመጣ ነበር” በማለት መልሷል። በመስክ ላገኙት ሰው ሁሉ ማለትም ለሚያርሰው፣ ለሚዘራው፣ ውኃ ለሚያጠጣው ወይም በአህያ ላይ ለሚጋልብ ሰው ሁሉ ይናገራሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የብዙ ውኃዎች መንደር የሆነችውን ራህቤን አጥለቅልቋታል። ይህ ብቻ አይደለም ራህቤ በአካባቢው ላሉ ብዙ መንደሮች የፈሳሽ ውኃ ምንጭ እንደሆነች ሁሉ ሕይወት ሰጪ የሆነውንም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አቅርባላቸዋለች። በራህቤ ያሉ አስፋፊዎች በአካባቢው ያሉትን መንደሮች በእግር በመሄድ ይጎበኟቸዋል። እንዲሁም ለአንድ ቀን ጉዞ በመኪና የሚሄዱ ቡድኖችን ያደራጁና በርቀት ወዳሉ መንደሮች በመሄድ ይሰብካሉ። አንዳንድ አስፋፊዎች ለማገልገል ሲሉ ወደ ሌሎች ከተሞች ተዛውረው ሄደዋል። በይሖዋ በረከት ለሰማያዊ አባታችን ለይሖዋ አምላክ ገና ብዙ ውዳሴዎችን የሚያመጡ ተጨማሪ ዕድገቶች ይኖራሉ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በራህቤ የሚገኝ የአንድ መንገድ ሁኔታ