የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 10/15 ገጽ 20-23
  • ሽማግሌዎች ኃላፊነታችሁን ለሌሎችም አካፍሉ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሽማግሌዎች ኃላፊነታችሁን ለሌሎችም አካፍሉ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሌሎችን የማሰልጠኑ ጥቅም
  • ኃላፊነትን ለሌሎች ማካፈል ሲባል ምን ማለት ነው?
  • ኃላፊነቶችን ለሌሎች ማካፈል እንዴት እንደሚቻል
  • ለሌሎች ኃላፊነት የምንሰጠው ለምንድን ነው? እንዴትስ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ልካቸውን የሚያውቁ ወንዶች አሠልጥነው ኃላፊነት ይሰጣሉ
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2020
  • ሽማግሌዎች—ኃላፊነት እንዲሸከሙ ሌሎችን አሠልጥኑ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • እነዚህን ነገሮች “ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 10/15 ገጽ 20-23

ሽማግሌዎች ኃላፊነታችሁን ለሌሎችም አካፍሉ!

ትዕግሥተኛ፣ ትሑት የሆነና ከሕይወቱ ባገኘው ተሞክሮ ትክክለኛ ፍርድ የመፍረድ ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር። ስለዚህ ከሦስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ምክር ለማግኘት ይመኩበት ነበር እርሱም እንደጠበቁት ሆኖ ለመገኘት ይጥር ነበር። ከጠዋት አንስቶ እስከ ማታ ድረስ ችግራቸውን ሲሰማና የአምላክ ሕግ በእነሱ ሁኔታ ላይ እንዴት እንደሚሠራ እንዲመለከቱት በትዕግሥት ሲረዳቸው ይውላል። አዎን ከ3,500 ዓመታት በፊት ለተወሰነ ጊዜ ያህል 12ቱ የእስራኤል ነገዶች ሲዳኙ የነበረው በአንድ ግለሰብ ይኸውም በሙሴ አማካኝነት ነበር።

የሙሴ አማት ዮቶር ግን ነገሩ አሳሰበው። ሙሴ በዚህ መንገድ ለረጅም ጊዜ ለመቀጠል እንዴት ተስፋ ሊያደርግ ይችላል? ስለዚህ ዮቶር “አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም” በማለት ገለጸለት። (ዘጸአት 18:17, 18) መፍትሔው ምን ሆኖ ተገኘ? ሙሴ ከኃላፊነቶቹ አንዳንዶቹን ለሌሎች እንዲያካፍል ዮቶር መከረው። (ዘጸአት 18:19-23) ጥሩ ምክር ነበር!

ዛሬም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ልክ እንደ ሙሴ ብቻቸውን ሊፈጽሙ ከሚችሉት በላይ ሊሠሩ የሚሞክሩ ብዙ ሽማግሌዎች አሉ። ስብሰባዎችን ያዘጋጃሉ፤ እንዲሁም በፕሮግራሙ ውስጥ ክፍል ወስደው በመዘጋጀት ሥርዓታማና ውጤታማ በሆነ መንገድ ያቀርባሉ። (1 ቆሮንቶስ 14:26, 33, 40፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:13) በተጨማሪም ሽማግሌዎች የጉባኤው አባሎች በግለሰብ ደረጃ የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ ይሰጧቸዋል። (ገላትያ 6:1፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14፤ ያዕቆብ 5:14) በሁሉም መንገድ አስፈላጊ በሆነው የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ የመሪነቱን ቦታ ይይዛሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 13:7) በተጨማሪም ጉባኤው ለሕዝብ የሚያሰራጫቸውን ጽሑፎች እንዲያገኝ የጽሑፍ አቅርቦት እንዲኖር ያደርጋሉ።

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሽማግሌዎች በክልል ስብሰባና በወረዳ ስብሰባ ፕሮግራሞች ላይ የተመደቡባቸው ክፍሎች አሉ። ትልልቅ ስብሰባዎችን ያደራጃሉ፤ እንዲሁም በሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ውስጥ ያገለግላሉ። አንዳንዶች በመንግሥት አዳራሽ የግንባታ ሥራዎች ይረዳሉ። እንግዲህ ይህ ሁሉ ከቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸው በተጨማሪ ሲሆን ራሳቸውን በመንፈሳዊ መመገብም ያስፈልጋቸዋል። (ከኢያሱ 1:8፤ መዝሙር 110:3 አዓት፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5፤ 4:15, 16 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ያሉት ክርስቲያን ወንዶች ይህን ሁሉ ሊሠሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ልክ እንደ ሙሴ እርዳታ ሊያገኙ ይገባቸዋል። ኃላፊነቶቻቸውን ለሌሎች ማካፈልን መማር አለባቸው። በእርግጥም ኃላፊነቱን ለሌሎች የማያካፍል ሰው ነገሮችን በማደራጀት በኩል ድክመት አለበት ማለት ነው።

ሌሎችን የማሰልጠኑ ጥቅም

ኃላፊነትን ለሌሎች ለማካፈል የሚያስገድዱን ተጨማሪ ምክንያቶችም አሉ። ስለ መክሊቱ በሚናገረው የኢየሱስ ምሳሌ ላይ ጌታው ወደ ረጅሙ ጉዞው ከመሄዱ በፊት ባሮቹን ጠራቸውና በተለያየ ደረጃ ኃላፊነቶችን በውክልና ሰጣቸው። (ማቴዎስ 25:14, 15) ጌታው እንዲህ በማድረጉ የተለያዩ ግቦችን ማሳካት ችሏል። በመጀመሪያ ደረጃ ሄዶ በነበረበት ወቅት ባሮቹ በሱ ቦታ ሆነው በመሥራታቸው አስፈላጊው ሥራ እየተዳከመ ሄዶ በመጨረሻው እንዳይቆም ረድቷል። ሁለተኛ ደግሞ ከቃላት ይልቅ የተግባር ድምፅ የጎላ ስለሆነ ጌታው የባሮቹን ችሎታዎችና ታማኝነታቸውን ለማየት አስችሎታል። ሦስተኛ ጌታው ባሮቹ በጣም የሚያስፈልጋቸውን ልምድ እንዲያዳብሩ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል።

ዛሬ ይህ ምሳሌ ለእኛም ትርጉም አለው። ኢየሱስ ምድርን ለቆ ሲሄድ ለቅቡዓን ደቀ መዛሙርቱ ኃላፊነት ሰጥቷቸው ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ቀሪዎቹ አሁንም ቢሆን ለዓለም አቀፉ የመንግሥቱ ጉዳዮች ኃላፊዎች ናቸው። (ሉቃስ 12:42) በዘመናዊው የቅቡዓኑ የመጋቢነት ሥራ ወቅት በድርጅቱ ላይ የይሖዋ በረከት እንዳለ ግልጽ ሆኗል። ከዚህም የተነሣ በአስደናቂ ሁኔታ እየፋፋ ሄዷል። ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከአንድ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ አዲሶች ራሳቸውን መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል! ይህም በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ጉባኤዎችንና በመቶ የሚቆጠሩ አዳዲስ ክልሎችን አስገኝቷል።

ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ “ለታማኝና ልባም ባሪያ” ኃላፊነቶችን በውክልና እንደሰጠ ሁሉ እነሱም በተራቸው የጉባኤ ኃላፊነቶችን “ከሌሎች በጎች” ውስጥ ለሆኑት ሽማግሌዎችና ዲያቆናት አካፍለዋል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ዮሐንስ 10:16) ያም ሆኖ የተገኘውን ከፍተኛ ዕድገት ለማራመድ ራሳቸውን የወሰኑ ተጨማሪ ወንዶች ያስፈልጋሉ። ከየት ይመጡ ይሆን? ሽማግሌዎች ሊያሰለጥኗቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች ተስፋ ለሚጣልባቸው ግለሰቦች ኃላፊነቶችን ካላካፈሉ እንዲህ ያሉትን ወንዶች እንዴት ሊያሰለጥኑ ይችላሉ? እንዲህ ካላደረጉ በቀር ሽማግሌዎች የወጣት ወንዶችን ችሎታዎችና ታማኝነት ለማየት የሚችሉበት አጋጣሚ እንዴት ሊያገኙ ይችላሉ?

ኃላፊነትን ለሌሎች ማካፈል ሲባል ምን ማለት ነው?

ለአንዳንዶች “ኃላፊነትን ለሌሎች ማካፈል” ማለት የኃላፊነቶቻቸውን ሸክም ማራገፍ፣ ከነገሩ መሸሽ፣ ቸል ማለት ወይም ከኃላፊነቶቻቸው መውረድ ማለት ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ በትክክል ከተሠራበት “ኃላፊነትን ለሌሎች ማካፈል ወይም መወከል” ማለት ኃላፊነቶችን ለመፈጸም የሚረዳ መንገድ ነው። “ቱ ዴሊጌት” የሚለው የእንግሊዝኛ ግሥ “ለሌላው በአደራ መስጠት፣ ወኪል አድርጎ መሾም፣ ኃላፊነት ወይም ሥልጣን ሰጥቶ ማሠራት” ማለት ነው። ያም ሆኖ ለሚፈጸመው ነገር የመጨረሻው ተጠያቂ ያ ኃላፊነቱን የሚያካፍለው ሰው እንደሆነ ይቆያል።

አንዳንዶች ኃላፊነታቸውን ከማካፈል የሚቆጠቡት የተቆጣጣሪነት ቦታቸውን የሚያጡ እየመሰላቸው ስለሚፈሩ ነው። ሆኖም ኃላፊነትን ለሌላው ማካፈል ማለት የተቆጣጣሪነትን ቦታ ማጣት ማለት አይደለም። ክርስቶስ ኢየሱስ በዓይን የማይታይና ሰማይ ላይ ሆኖ የሚገዛ ቢሆንም የክርስቲያን ጉባኤ በጣም በቁጥጥሩ ሥር ነው። እሱም በተራው ጉባኤውን የመምራቱን ሥራ ልምድ ላላቸው ሰዎች በአደራ ሰጥቶታል።—ኤፌሶን 5:23-27፤ ቆላስይስ 1:13

ሌሎች ደግሞ ኃላፊነታቸውን ለሌሎች ለማካፈል የማያዘነብሉበት ምክንያት ሥራውን ራሳቸው ቢሠሩት በፍጥነት ሊያደርጉት እንደሚችሉ ስለሚሰማቸው ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሌሎችን የማሰልጠኑን ጠቃሚነት ተመልክቷል። በምድር ላይ ከኢየሱስ የበለጠ ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ያስተማረ ማንም የለም። (ዮሐንስ 7:46) ሆኖም ለ70 ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ከሰጣቸው በኋላ ወደ ስብከቱ ሥራ ልኳቸዋል። እነርሱም በማስተማር ችሎታቸው ከኢየሱስ ጋር ሊተካከሉ ባይችሉም እንኳ ስለተሳካላቸው በጣም እየተደሰቱ ተመልሰዋል። ኢየሱስም ከእነሱ ጋር በመደሰት እሱ ከሄደ በኋላ ለረጅም ጊዜ ሥራውን እንደሚቀጥሉበትና በመጨረሻም እሱ ብቻውን ሊሠራ ከሚችለው በላይ እንደሚሠሩ ስለሚያውቅ አመሰገናቸው።—ሉቃስ 10:1-24፤ ዮሐንስ 14:12

በተጨማሪም ኃላፊነትን ለሌሎች ማካፈል ማለት አስፈላጊ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማከናወን ረዳት ማግኘት ማለት ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ አንድ ቀን በፊት ጴጥሮስና ዮሐንስ ለመጨረሻው የማለፍ በዓል ራት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ መድቧቸው ነበር። (ሉቃስ 22:7-13) ኢየሱስ ጠቦት፣ ወይን ጠጅ፣ ያልቦካ ቂጣና መራራ ቅጠል ስለ መግዛት ወይም ደግሞ መመገቢያ ዕቃዎችን፣ ማገዶና የመሳሰሉትን ስለማሰባሰብ መጨነቅ አላስፈለገውም። እነዚህን ዝርዝር ጉዳዮች ጴጥሮስና ዮሐንስ ለማከናወን ችለዋል።

የዛሬዎቹ ሽማግሌዎችም የኢየሱስን ምሳሌ ቢከተሉ ተመሳሳይ ጥቅሞችን በማግኘታቸው ሊደሰቱ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የጽሑፍ ጉዳይ የሚመለከተው ወንድም ወደፊት ለሚደረግ ጽሑፍ የማበርከት ዘመቻ የሚያስፈልጉ ጽሑፎችን እንዲያዝ ይጠየቅ ይሆናል። ባለፉት ዘመቻዎች ላይ ተመሳሳይ ጽሑፎች እንዴት እንደተንቀሳቀሱ ለማወቅ ይቻል ዘንድ መዝገቦቹን እንዲመረምር ሊነገረው ይችላል። በተጨማሪም ተገቢውን የማዘዣ ቅጽ ከማዘጋጀቱ በፊት የጉባኤውን ክልል ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበት ይሆናል። ከዚያም ቅጹን እንዲመረምረው ለጉባኤው ጸሐፊ ያቀርባል። የጽሑፍ አገልጋዩ አንድ ጊዜ ሥራውን ካወቀና በማዘዣው ላይ የተጠየቁት ጽሑፎች ብዛት ምክንያታዊ ከሆነ ጸሐፊው ያለፉትን መዝገቦች ሁሉ እንደገና መመርመር አያስፈልገውም። በግልጽ እንደሚታየው ይህ ቀላል የሆነ ኃላፊነትን ለሌሎች የማካፈል ሁኔታ የጽሑፍ ማዘዣ ማዘጋጀቱን ያልተወሳሰበ በማድረግ ለሚመለከታቸው ሁሉ ቀላል ያደርግላቸዋል።

እንዲህ ካሉት ጥቅሞች አንፃር ሲታይ አንድ ሰው ውጤታማ በሆነ መንገድ ኃላፊነቶቹን ለሌሎች ማካፈል የሚችለው እንዴት ነው?

ኃላፊነቶችን ለሌሎች ማካፈል እንዴት እንደሚቻል

ሥራው ምን እንደሆነ ግልጽ አድርገው። በመጀመሪያ ደረጃ እንዲገኝ የሚፈለገው ውጤት ምን እንደሆነ ግልጽ አድርገው። በኢየሱስ የምናን ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው “መኰንን” ለአስር ባሪያዎቹ “እስክመጣ ድረስ ነግዱ” ብሎ ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 19:12, 13) እያንዳንዱ ባሪያ ትርፍ በሚያስገኝ መንገድ በምናኑ እንዲነግድና ጌታው በሚመለስበት ጊዜ ያተረፈውን ሪፖርት እንዲያደርግ ጌታው ይጠብቅ ነበር። ባሮቹ ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ያውቁ ነበር። በዘመናችን ባለው የመንግሥት አዳራሽ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት እንዴት በሥራ ላይ ሊውል ይችላል? ለምሳሌ አንድ ጣሪያውን እንዲያድስ የተመደበ ወንድም በምን ነገሮች መጠቀም እንዳለበት፣ እነዚያንም የት ሊያገኛቸው እንደሚችልና መቼ ሥራውን እንደሚጀምር፣ ለሥራው የሚስማማው የአየር ጠባይ የቱ እንደሆነ እንደሚነግረው የታወቀ ነው። እንዲህ ያሉ ግልጽ መምሪያዎች ጥሩ አደረጃጀትን ያስገኛሉ።

የሥራውን ይዘት ብቻ ሳይሆን ግለሰቡ ምን ውሳኔዎችን ሊያደርግ እንደተፈቀደለትና ምን ነገሮች ደግሞ ለሌላ ማስተላለፍ እንደሚገባው መግለጽም አስፈላጊ ነው። ሙሴ የሾማቸው ሰዎች ትንንሽ ጉዳዮችን እነሱው እንዲፈርዱ ከባድ ጉዳዮችን ግን ወደ እርሱ እንዲያመጡ ነግሯቸው ነበር።—ዘጸአት 18:22

ኃላፊነቶችን ስትሰጡ ለሁለት ሰዎች አንድ ዓይነት ሥራዎችን እንዳትሰጡ ተጠንቀቁ። በአንድ ሥራ ላይ ከአንድ በላይ ሰዎች ሲመደቡ ውጤቱ መዘበራረቅ ይሆናል። በይሖዋ ምስክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ የጽዳት ክፍሉም የምግብ አገልግሎት ክፍሉም የምግብ ማስቀመጫዎቹን እንዲያጸዱ ቢመደቡ ወይም የአስተናጋጆች ክፍሉና የጥምቀት ክፍሉ ሁለቱም በጥምቀት ጊዜ ተመልካቾችን እየመሩ እንዲወስዱ ቢመደቡ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ገምቱት።

ችሎታ ያላቸውን ወንዶች ምረጡ። ዮቶር ሙሴን “አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን (ችሎታ ያላቸውን ኒው ኢንግሊሽ ባይብል)፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፤ ከእነርሱም . . . ሹምላቸው” ብሎት ነበር። (ዘጸአት 18:21) ሰውየው በመጀመሪያ መንፈሳዊ ብቃቶችን ማሟላት እንደሚገባው ግልጽ ነው። አንድ ሰው የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን ይችል እንደሆነ ለመገምገም የሰውየው ባሕርይ፣ ልምድ፣ ሥልጠና እና የተፈጥሮ ችሎታ ሊታይ ይገባዋል። ስለዚህ በተለይ ተወዳጅ፣ ደስተኛ፣ ለመርዳት ዝግጁ የሆነ ባሕርይ ያለው አንድ ክርስቲያን የመጽሔት አገልጋይ ወይም አስተናጋጅ ሆኖ የተሻለ ሥራ ሊሠራ ይችላል። በተመሳሳይም የጉባኤውን ጸሐፊ የሚረዳ ወንድም በሚመረጥበት ጊዜ ያ ወንድም ምን ያህል ሥርዓታማ መሆኑን በግምት ውስጥ ማስገባቱ ምክንያታዊ ነው። ለዝርዝር ሁኔታዎች ትኩረት ይሰጣልን? እምነት የሚጣልበትና ምስጢር የሚጠብቅ ነውን? (ሉቃስ 16:10) አስፈላጊ ከሆኑት መንፈሳዊ ብቃቶች በተጨማሪ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ማሰብ ለሥራው የሚስማማ ትክክለኛ ሰው ለመምረጥ ይረዳል።

በቂ መሣሪያዎችን ወይም መገልገያዎችን መድቡላቸው። የሚያገለግለው ሰው የተመደበበትን ሥራ ሙሉ በሙሉ ለማከናወን ይችል ዘንድ የተወሰኑ የመገልገያ መሣሪያዎችን በፈለገው ጊዜ ማግኘት ያስፈልገዋል። ምናልባት መሣሪያዎች፣ የገንዘብ ወይም የጉልበት እርዳታ ያስፈልገው ይሆናል። በቂ መገልገያዎችን መድቡለት። ለምሳሌ ያህል አንድ ወንድም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ አንዳንድ አስፈላጊ እድሳቶችን እንዲያደርግ ይጠየቅ ይሆናል። መሠራት የሚያስፈልገው ምን እንደሆነ እንደሚነገረው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ለአንዳንድ ትንንሽ ነገሮች መግዣ የተመደበ ገንዘብም ያስፈልገው ይሆናል። ምናልባት እርዳታ ያስፈልገው ይሆናል። ስለዚህ ሽማግሌዎች ሌሎች እንዲያግዙት ሊጠይቁ ወይም ‘ወንድም እገሌ በአዳራሹ ውስጥ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ሥራ ስለሚሠራ አንዳንዶቻችሁን እንድትረዱት ሊጠይቃችሁ ይችላል’ ብለው በጉባኤው ውስጥ ማስታወቂያ መንገርም ይችላሉ። በጉባኤው ውስጥ እንዲህ ያለው አስቀድሞ የተደረገ አሳቢነት አንድን ሰው በቂ መገልገያዎች ሳይሰጥ ሥራ እንዳይመድብ ያግደዋል። አንድ የአስተዳደር ሥራ አማካሪ እንደገለጹት “ኃላፊነታችሁን ለሌሎች በግማሽ ብቻ አታካፍሉ” ብለዋል።

የሥራ ኃላፊነት በምትሰጡበት ጊዜ ያ ሰው በአንተ ፈንታ ሆኖ እንደሚሠራ ለሌሎች አስታውቅ። በአንተ ቦታ ሆኖ የመሥራት ሥልጣን መቀበሉ ራሱ አንዱ መሣሪያ ነው። ኢያሱ አዲሱ የእስራኤል መሪ ሆኖ የተወከለው “በማኅበሩ ሁሉ ፊት” ነበር። ሙሴም “ከክብርህ አኑርበት” ተብሎ መመሪያ ተሰጥቶታል። (ዘኁልቁ 27:18-23) በጉባኤው ውስጥም የተመደቡ ሥራዎች ያሏቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በማስታወቂያ መለጠፊያው ሰሌዳ ላይ በመለጠፍ ይህን ለመፈጸም ይቻላል።

ውሳኔያቸውን ደግፉላቸው። አሁን የተመደበው ሰው በፊት ያለውን ሥራ መጀመር ይችላል። የሚያደርጋቸውን ጥሩ ውሳኔዎች የምትደግፉለት ከሆነ የማበረታቻ ምንጭ ልትሆኑለት እንደምትችሉም አስታውሱ። ለምሳሌ ያህል እንደ ሽማግሌነትህ መጠን የድምጽ ማጉያዎቹንና በመንግሥት አዳራሹ መድረክ ላይ የሚቀመጡትን ዕቃዎች እንዴት እንደሚቀመጡ በሚመለከት ምናልባት የተመደበው ወንድም ከሚያደርገው ትንሽ ለየት ያለ የራስህ ምርጫ ይኖርህ ይሆናል። ይሁን እንጂ መድረኩን እንዲያበጅ የተመደበው ወንድም በሥራው ላይ አንዳንድ የምርጫ ነፃነቶች እንዲኖሩት ቢፈቀድለት በራሱ መተማመንና ልምድ ሊያገኝ ይችላል። ከዚህም ሌላ ነገሮችን እንኳ ሊያሻሽል ይችላል። አንድ የንግድ ሥራ አማካሪ እንደገለጹት፦ “ኃላፊነታችሁን ለሌሎች ስታካፍሉ እንዴት እንደሚሠራ ሳይሆን ሥራውን ብቻ አካፍሉ። . . . አብዛኛውን ጊዜ የፈጠራ ችሎታው ራሱ ይመነጫል።”

ከዚህም በተጨማሪ በሥራው ላይ ያለው ወንድም አንዳንድ ነገሮችን ቀረብ ብሎ ስለሚመለከታቸው ከሥራው ጋር የተያያዙትን ችግሮች በተሻለ ሁኔታ ሊረዳቸው ይችላል። ለችግሮቹ ተግባራዊ የሆኑ መፍትሔዎችንም ሊያገኝላቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ለተመልካቾች ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችን እያከናወነ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ልምድ ስላለው አንድ ረዳቱ ሲናገር፦ “በዚህ አፈር ውስጥ አንዳንድ ድንጋዮች አሉ ቢለኝ ላምነው ይገባኛል” ብሏል።

አዎን፣ ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ያሏቸው በጣም ጠቃሚ ሀብቶች በማንኛውም አቅጣጫ ለመርዳት ፈቃደኞች የሆኑ ችሎታ ያላቸው ራሳቸውን የወሰኑ ወንዶችና ሴቶች ናቸው። ሽማግሌዎች፣ በዚህ ውድ የእርዳታ ምንጭ ተጠቀሙ! ኃላፊነትን ማካፈል አቅምን የማወቅ ምልክት ሲሆን ውጥረትንና ብስጭትን ይቀንሳል። የበለጠ ሥራ ለማከናወን ከመቻልህም በላይ ሌሎችም አስፈላጊውን ልምድ እንዲያገኙ አጋጣሚ ትሰጣቸዋለህ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ