ይህ እራት ለአንተ ትርጉም ሊኖረው ይችላልን?
ደብዘዝ ያለ የሙሉ ጨረቃ ብርሃን በምድሪቱ ላይ ያበራል። የብዙ ዘመናት ዕድሜ ባላት የኢየሩሳሌም ከተማ 12 ሰዎች በአንድ መኖሪያ ቤት የላይኛው ፎቅ ውስጥ በአንድ ገበታ ዙሪያ ተሰብስበዋል። አሥራ አንዱ ሰዎች አስተማሪያቸው ትልቅ ትርጉም ያለውን በዓል ሲያስተዋውቃቸውና ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ቃላት ሲነግራቸው በተመስጦ ያዳምጣሉ። ስለዚህ ጊዜ የሚገልጽ አንድ ታሪክ እንዲህ ይላል:-
“ኢየሱስ [ክርስቶስ] እንጀራን አንስቶ ባረከ፣ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሉ፣ ይህ ሥጋዬ [ማለት አዓት ] ነው አለ። ጽዋንም አንስቶ አመስግኖም ሰጣቸው፣ እንዲህም አለ:- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፣ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ነገር ግን እላችኋለሁ፣ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።” — ማቴዎስ 26:26–30
ይህ የሆነው እንደ ዘመናችን አቆጣጠር በ33 ኒሳን በተባለው የአይሁዳውያን ወር 14ኛ ቀን ጀምበር ከጠለቀች በኋላ ነው። ኢየሱስና ሐዋርያቱ እስራኤላውያን በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት ከግብጽ ባርነት ነፃ ለመውጣታቸው የመታሰቢያ በዓል የሆነውን የማለፍ በዓል አክብረው መጨረሳቸው ነበር። ክርስቶስ አሳልፎ ሊሰጠው የተዘጋጀውን ይሁዳ አስቆረቱን አስወጥቶት ነበር። በዚህም ምክንያት በዚህ ጊዜ በቦታው የነበሩት ኢየሱስና አስራ አንዱ ታማኝ ሐዋርያት ብቻ ነበሩ።
ይህ እራት የአይሁዳውያን የማለፍ በዓል ቅጥያ አልነበረም። የጌታ እራት ተብሎ መጠራት የጀመረ አዲስ ዓይነት እራት ነበር። ኢየሱስ ስለዚህ በዓል ተከታዮቹን “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት አዝዞአል። (ሉቃስ 22:19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:24–26) ይህን የተናገረው ለምንድን ነው? ይህ ከብዙ ዘመናት በፊት የተፈጸመ ነገር ለአንተ ትርጉም ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?