ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች በጥሞና አንብበሃልን? አንብበህ ከነበረ የሚከተሉትን ነጥቦች ለማስታወስ ትችላለህ:-
▫ ይሖዋ የኢየሱስን ፈለግ ለሚከተሉ ሰዎች የሚያደርግላቸው ‘የጥሩነት ምልክት’ ምንድን ነው? (መዝሙር 86:17)
የጥንት ክርስቲያኖች ስደትን እንዲቋቋሙ ያስቻላቸው “የመንፈስ ቅዱስ ደስታ” ነበር። (1 ተሰሎንቄ 1:6) ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። “የበጎ ስጦታ ሁሉ” ምንጭ የሆነው ይሖዋ መንፈስ ቅዱስን ለሚጠይቁት ሁሉ በደስታ ይሰጣል። (ያዕቆብ 1:17፤ ሉቃስ 11:13) ስለዚህ ለኢየሱስ ተከታዮች ‘የጥሩነት ምልክት’ የሚሆንላቸው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው። — 12/15 ገጽ 18–19
▫ አምላክ ስለ ውሸት ያለውን አመለካከት መቀበላችን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
መዝሙር 5:6 “ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ” ይላል። ራእይ 21:8ም በተጨማሪ የሐሰተኞች ሁሉ የመጨረሻ ዕጣ “የሞት ባሕር” እንደሆነ ይናገራል። ስለዚህ አምላክ ስለ መዋሸት ያለውን አመለካከት መቀበላችን እውነቱን እንድንናገርና እርሱ የሚሰጠንን የሕይወት ስጦታ እንድንቀበል የሚገፋፋ ጠንካራ ምክንያት ይሆንልናል። — 12/15, ገጽ 23
▫ የሣምራውያን አምልኮ በምን ላይ የተመሠረተ ነበር? (ዮሐንስ 4:20)
ሣምራውያን ያቀርቡ በነበረው ቅይጥ አምልኮ እንደ ቅዱሳን መጻሕፍት አድርገው የሚቀበሉት አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ነበር። ከዘአበ በአራተኛው መቶ ዘመን ገደማ ላይ በገሪዛን ተራራ ላይ በኢየሩሳሌም ለሚገኘው የአምላክ ቤተ መቅደስ ምትክ የሚሆን ቤተ መቅደስ ሠሩ። የሣምራውያን ቤተ መቅደስ ፈርሶ የጠፋ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ በገሪዛን ተራራ ላይ በየዓመቱ የማለፍን በዓል ያከብራሉ። 1/1 ገጽ 25
▫ ክርስቲያኖች ብክለትን ለመከላከል ወይም የምድርን አካባቢ ለማጽዳት የሚደረገውን ጥረት እንዲያስፋፉ ይፈለግባቸዋልን?
ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በዘመኑ የነበሩትን ማኅበራዊ ችግሮች በሙሉ ለማስወገድ አልሞከረም። ይሖዋ በመሲሐዊ መንግሥቱ አማካኝነት የጽድቅ ሥርዓቶቹን በመላው ምድር ላይ በሚያሰፍንበት ጊዜ የአካባቢ መበከል ችግሮች ዘለቄታ ባለው መንገድ ይወገዳሉ። ስለዚህ የይሖዋ ምስክሮች ሚዛናዊ አመለካከት አላቸው። ለጎረቤቶቻቸው ያላቸው ፍቅር ለሌሎች ንብረት አክብሮት እንዲያሳዩ ቢገፋፋቸውም የመጀመሪያ ደረጃ የሚሰጡት ለአምላክ መንግሥት ስብከት ሥራ ነው። (ማቴዎስ 6:33) — 1/1 ገጽ 31
▫ ኢየሱስ ብርሃን አብሪ ሆኖ ያገለገለው በምን መንገዶች ነው? (ዮሐንስ 8:12)
ኢየሱስ ራሱን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ሥራ ወስኖአል። (ሉቃስ 4:43፤ ዮሐንስ 18:37) በተጨማሪም ሃይማኖታዊ ውሸቶችን በማጋለጥ በሃይማኖት እስራት ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት አስገኝቶአል። (ማቴዎስ 15:3–9) ፍፁም የሆነውን ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የዓለም ብርሃን መሆኑን በከፍተኛ መንገድ አረጋግጦአል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) — 1/15 ገጽ 10–11
▫ ለይሖዋ ከምንገዛባቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ነው። በዚህም ምክንያት ልንገዛለት ይገባል። በተጨማሪም ይሖዋ ሁሉን ማድረግ የሚችል አምላክ በመሆኑ ማንም እርሱን ለመቃወም አይችልም። ስለዚህ ለእርሱ መገዛታችንን ችላ ለማለት አንችልም። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረቶች በሙሉ የተፈጠሩት የፈጣሪያቸውን ዓላማ ለማከናወን ነው። ይህም እነዚህ ፍጥረታት በሙሉ ለአምላክ እንዲገዙ የሚያደርግ ግዳጅ ይጥልባቸዋል። — 2/1 ገጽ 10–11
▫ ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት ጋር ዝሙት እንዳይፈጽም የረዳው ነገር ምንድን ነው?
ዮሴፍ ጠንካራ የሆነ አእምሮውን የሚያንቀሳቅስ ኃይል ነበረው። ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ዘወትር ይጠብቅ ስለነበረ ዝሙት መፈጸም በጶጢፋር ላይ ብቻ ሳይሆን በአምላክ ላይ ጭምር ኃጢአት መሥራት እንደሆነ ተገንዝቦአል። — 2/15 ገጽ 21
▫ ኢየሱስ “እኔ እውነት ነኝ” ሲል ምን ማለቱ ነበር? (ዮሐንስ 14:6)
ኢየሱስ እውነትን በመናገርና በማስተማር ብቻ አልተወሰነም። እውነትን በመላ ሕይወቱ አሳይቶአል፤ ኖሮበታልም። ስለዚህ ክርስትና የሐሳብ ጉዳይ ሳይሆን የሕይወት መንገድ ነው። — 3/1 ገጽ 15
▫ በመዝሙር 51 ላይ ምን የሚያጽናና ትምህርት እናገኛለን?
ይህ መዝሙር ተደናቅፈን ኃጢአት ብንሠራና ከልብ ንሥሐ ብንገባ አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን ምህረት እንዲያደርግልን የምናቀርበውን ጩኸት ሰምቶ ተስፋ ከመቁረጥ እንደሚያድነን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ይሁን እንጂ በቅድሚያ ሊያሳስበን የሚገባው በይሖዋ ስም ላይ ሊደርስ የሚችለው ነቀፌታ መሆን ይገባዋል። 3/15 ገጽ 18
▫ በውኃ መጠመቅ የምን ምሳሌ ነው?
ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ አምላክ መወሰኑን የሚያሳይ ውጪያዊ ምሳሌ ነው። የሚጠመቁ ሰዎች ውኃ ውስጥ መጥለቃቸው በራሳቸው ላይ ላተኮረው ሕይወታቸው የሞቱ መሆናቸውን ያመለክታል። ከውኃው ውስጥ መውጣታቸው ደግሞ አሁን የአምላክን ፈቃድ በሕይወታቸው ውስጥ የመጀመሪያ ቦታ ሰጥተው ለአምላክ ፈቃድ ሕያዋን መሆናቸውን ያመለክታል። (ማቴዎስ 16:24) — 4/1 ገጽ 5–6