የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 10/1 ገጽ 22-25
  • ስለ አምላክ ምሕረት ትክክለኛ አመለካከት ይኑርህ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ አምላክ ምሕረት ትክክለኛ አመለካከት ይኑርህ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እንደዚህ ብለን አስበን እናውቅ ይሆንን?
  • ትክክለኛው አመለካከት ምንድን ነው?
  • የኢየሱስ አመለካከት
  • በመጽናት መሠልጠን
  • ሁኔታዎች የማይለውጡት ንጹሕ አቋም
  • ‘አባታችሁ መሐሪ ነው’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • የምናገለግለው አምላክ “ምሕረቱ ብዙ ነው”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2021
  • ‘በክቡር ደም’ ተዋጅተናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • አምላክ ከባድ ኃጢአቶችን ይቅር ይላል?
    ንቁ!—2008
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 10/1 ገጽ 22-25

ስለ አምላክ ምሕረት ትክክለኛ አመለካከት ይኑርህ

ሐኪሙ ደግና በ ጣም አሳቢ ነ በር። በእሱ አ መለካከት ሕመምተኛዋ ሕይወቷን ለማትረፍ በአስቸኳይ የቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልጋታል። ስታመነታና የደምን ጉዳይ ስታነሣ በጣም ተደነቀ። ሃይማኖታዊ በሆነ ምክንያት ደም መውሰድን የሚጠይቅ የቀዶ ሕክምና ለማድረግ እንደማትፈልግ በምታስረዳበት ጊዜ በጣም ደነገጠ። እንዴት አድርጎ ሊረዳት እንደሚችል በማሰብ አእምሮውን ብዙ አስጨነቀው። በመጨረሻም አንድ ጥሩ መፍትሔ ያገኘ መሰለው። “ደም ካልወሰድሽ እንደምትሞቺ ታውቂያለሽ። መሞት ደግሞ አትፈልጊም፣ አይደለም እንዴ?” አላት።

“ልክ ነው፣ መሞት አልፈልግም” አለች ሕመምተኛዋ።

“እንደሚመስለኝ ደም ብትወስጂ የሃይማኖትሽን ሕግ ታፈርሺያለሽ። ይህ ደግሞ ላንቺ ከባድ ነገር ነው። እንግዲያው አንድ ሐሳብ አለኝ። ደም ወስደሽ ለምን ሕይወትሽን አታድኚም። ከዚያም ኃጢአት መሥራትሽን ለአምላክ ትናዘዢና ንስሐ ትገቢያለሽ። በዚህ መንገድ ሃይማኖትሽንም እንደያዝሽ ትቀጥያለሽ።”

በመርዳት ስሜት የተገፋፋው ሐኪም ግሩም የሆነ መልስ እንዳገኘ አድርጎ አስቧል። የእሱ ታካሚ በመሐሪ አምላክ እንደምታምን በደንብ ገብቶታል። እንደ እውነቱ ከሆነ በአምላክ ምሕረት ለመጠቀም ያለው ተገቢ አጋጣሚ ይህ ነበር። ነገር ግን ያቀረበው ሐሳብ ጥሩ መስሎ የሚታየውን ያህል ምክንያታዊ ነበርን?

እንደዚህ ብለን አስበን እናውቅ ይሆንን?

አንዳንድ ጊዜ እኛም ሐኪሙ ባሰበበት በዚያው ዓይነት መንገድ እናስብ ይሆናል። ምናልባት በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ያልታሰበ ተቃውሞ ተነሥቶ በፍርሃት ተውጠን ይሆናል። ሕሊናችንን ቅር የሚያሰኝ አንድ ነገር እንድናደርግ ተጽእኖ ስለተደረገብን ግራ የመጋባት ስሜት ተሰምቶን ይሆናል። ተደናግጠን ስሕተት መሆኑን እያወቅን አንድን ነገር የማድረግና በኋላ ይቅርታ እጠይቃለሁ በሚል ስሜት ከችግሩ በቀላሉ የማምለጥ አዝማሚያ እናሳይ ይሆናል።

ወይም ግለሰቦች በራሳቸው የተሳሳተ ዝንባሌ ሊፈተኑ ይችሉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት የብልግና ድርጊት ለመፈጸም እንዲፈተን በሚያደርገው ሁኔታ ውስጥ ሊወድቅ ይችል ይሆናል። የተሳሳተውን ምኞት ታግሎ ከማሸነፍ ይልቅ በኋላ ከአምላክ ጋር እታረቃለሁ ብሎ በማሰብ በፈተናው ሊወድቅ ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች ከክርስቲያን ጉባኤ ሊያስወግዳቸው እንደሚችል እያወቁ ከባድ ኃጢአት እስከ መሥራት ደርሰዋል። ‘ትንሽ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ እቆይና በኋላ ንስሐ ገብቼ ውገዳው እንዲነሣልኝ አደርጋለሁ’ ብለው እስከማሰብ ደርሰዋል።

እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ሁለት ነገሮችን በጋራ ይዘዋል። በመጀመሪያ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ከመታገል ይልቅ ግለሰቦች በቀላሉ ይሸነፋሉ። በሁለተኛ ደረጃ ስሕተት ከሠሩ በኋላ ይቅርታ ከጠየቁ አምላክ ወዲያውኑ ምሕረት እንደሚያደርግላቸው ሆኖ ይሰማቸዋል።

ትክክለኛው አመለካከት ምንድን ነው?

እንዲህ የመሰለው አመለካከት ለአምላክ ምሕረት ተገቢ አድናቆት ያለን መሆኑን ያሳያልን? እስቲ ስለ አምላክ የምሕረት ዝግጅት ለጥቂት ጊዜ አስብ። ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ብሏል። (ዮሐንስ 3:​16) ይህ ምሕረት እንዴት እንደሚሠራ ሐዋርያው ዮሐንስ ሲያስረዳ “ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 2:​1) እንግዲያው ከአለፍጽምና የተነሣ በኃጢአት ብንወድቅ፣ በጸሎት ወደ አምላክ ልንቀርብና በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅርታ እንዲደረግልን ልንለምን እንችላለን።

ታዲያ ይህ ማለት በኋላ ይቅርታ እስከጠየቅን ድረስ ኃጢአት ብንሠራም ባንሠራም ምንም አይደለም ማለት ነውን? እንደዚያ ማለት አይደለም። የጥቅሱን የመጀመሪያ ቃላት ልብ በላቸው:- “ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ።” በዚህ ጥቅስ ውስጥ ያሉት ቀጥለው የተጠቀሱት የዮሐንስ ቃላት አለፍጽምናችንን በተመለከተ እኛን ለመርዳት ይሖዋ ያዘጋጀውን የፍቅር ዝግጅት ያሳያሉ። ይሁንና የምንችለውን ያህል ጥረት አድርገን ከኃጢአት መሸሽ አለብን። አለበለዚያ ግን ለአምላክ ፍቅር አሳዛኝ የሆነ ንቀት በማሳየት በይሁዳ ላይ እንደተጠቀሱት የአምላክን የማይገባ ደግነት ለሴሰኝነት ማሳበቢያ አድርገው እንደተጠቀሙበት ሰዎች እንሆናለን። — ይሁዳ 4

የአምላክ ምሕረት ከጉዳት ሊጠብቅ እንደሚችል መረብ አድርገን የምንመለከተው ከሆነ የአምላክን ምሕረት አቃልለን የምንመለከትና ኃጢአት መጥፎ ነገር እንዳልሆነ አድርጎ ወደማየት ሊያደርሰን ይችላል። ይህ ከእውነት በጣም የራቀ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ እንደሚከተለው ብሎታል:- “እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ የሚያድንበትን ጸጋውን ገልጦአል፤ ይህም ጸጋ ኃጢአተኛነትንና ሥጋዊ ምኞትን እንድንክድና ራስን በመቆጣጠር፣ በቅንነት፣ በመንፈሳዊነት በዚህ ዓለም እንድንኖር ያስተምረናል።” — ቲቶ 2:​11, 12 የ1980 ትርጉም

ጳውሎስ ለአምላክ ምሕረት አድናቆት እንዳለው ከራሱ አለፍጽምና ጋር በታገለበት መንገድ አሳይቷል። እርሱም “ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 9:​27) ጳውሎስ አልፎ አልፎ ኃጢአት መሥራቴ አይቀርም በማለት ነገሩን አቅልሎ አልተመለከተውም። ታዲያ እኛስ አቅልለን ልንመለከተው ይገባልን?

የኢየሱስ አመለካከት

ኢየሱስ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ መወላወልና ከችግር ለመሸሽ ሲባል ቀላሉን መንገድ መከተልን በተመለከተ ያለውን አመለካከት የገለጸበት አንድ ወቅት ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ ስለመጪው መሥዋዕታዊ ሞቱ ሊነግራቸው በጀመረበት ጊዜ ጴጥሮስ ሊገሥጸው ጀመረና “አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም” አለው። ኢየሱስ እንዴት ብሎ መለሰለት? “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።” — ማቴዎስ 16:​22, 23

ኢየሱስ ለጴጥሮስ የተናገረው ጠንካራ ወቀሳ ከአምላክ ፈቃድ ጋር እንዲጋጭ የሚያደርግ ቀላል መንገድ ለመከተል እንደማይፈልግ ያሳያል። የተመዘገበው ቃል እንደሚያሳየው ኢየሱስ በሰይጣን እጅ የማያቋርጥ ጥቃት ቢደርስበትም ትክክለኛውን መንገድ ምንም ሳያወላውል ተከትሏል። በመጨረሻም ተዘብቶበታል፣ በጭካኔ ተደብድቧል፣ እንዲሁም የሥቃይ ሞት ደርሶበታል። እንዲህም ሆኖ ከአቋሙ ፍንክች አላለም፣ በዚህም ምክንያት ሕይወቱን ለእኛ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ችሏል። ኢየሱስ ይህንን ሁሉ መከራ የተቋቋመው፣ ችግሮችና ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ‘አይሁንብኝ’ እያልን ለመኖር እንድንችል ብሎ አይደለም።

ስለ ኢየሱስ “ጽድቅን ወደድህ ዓመፅንም ጠላህ” ተብሎ ተጽፎአል። (ዕብራውያን 1:​9) ከችግር ለመሸሽ መሞከር ብዙ ጊዜ ዓመፃ ወደ መሥራት ያደርሳል። ስለዚህ እንደ ኢየሱስ ይህንን የምንጠላ ከሆነ ከአቋማችን ፍንክች የማንል እንሆናለን። በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ይሖዋ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” ብሎ ተናግሯል። (ምሳሌ 27:​11) የኢየሱስ ሚዛኑን የጠበቀና የማያወላውል የጽድቅ አቋም ለይሖዋ ልብ ታላቅ ደስታ አምጥቶለታል። የኢየሱስን የንጹሕ አቋም ምሳሌ የምንከተል ከሆነ እኛም ለይሖዋ ተመሳሳይ ደስታ ልናመጣለት እንችላለን። — 1 ጴጥሮስ 2:​23

በመጽናት መሠልጠን

ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደዚህ በማለት ጽፏል:- “በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፣ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፣ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።” (1 ጴጥሮስ 1:​6, 7) ፍጹማን ስላልሆንንና በሰይጣን ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ያለማቋረጥ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። ጴጥሮስ እንዳመለከተው እነዚህ ፈተናዎች ለጥሩ ዓላማ ሊያገለግሉ ይችላሉ። እምነታችንን በመፈተን ደካማ ወይም ጠንካራ መሆኑን ያሳያሉ።

እነዚህ ፈተናዎች እኛንም ለማሠልጠን ያገለግላሉ። ኢየሱስ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ።” (ዕብራውያን 5:​8) እኛም ጭምር በፈተናዎች ከጸናን መታዘዝንና በይሖዋ መታመንን ልንማር እንችላለን። ጴጥሮስ “አምላክ . . . ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል” ብሎ በተናገረው መሠረት ይህ የመማር ሂደት የተሟላ እስኪሆን ድረስ ይቀጥላል። — 1 ጴጥሮስ 5:⁠10

በፈተና ወቅት ብንወላውል ፈሪዎች ወይም ደካሞች፣ ለይሖዋና ለጽድቅ ጠንካራ ፍቅር የሌለን ወይም ራስን የመግዛት ባሕርይ የጎደለን መሆናችንን እናሳያለን። እንደዚህ ያለው ድክመት ከአምላክ ጋር የገባነውን ዝምድና አደጋ ላይ ይጥለዋል። በዚህ ጊዜ “የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና” በማለት ጳውሎስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ በእኛ ጉዳይ እውነትነት ያለው ይሆናል። (ዕብራውያን 10:​26) ለድክመት ከመሸነፍና በሕይወት የመኖርን አስደሳች ተስፋ ከማጣት ከቶውንም ኃጢአት አለመሥራቱ ምንኛ የተሻለ ነው!

ሁኔታዎች የማይለውጡት ንጹሕ አቋም

በነቢዩ ዳንኤል ዘመን ሦስት ዕብራውያን ጣዖት ካላመለካችሁ በእሳት ተቃጥላችሁ ትገደላላችሁ የሚል ማስፈራሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። የሰጡት መልስ ምን የሚል ነበር? “የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፣ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፣ ንጉሥ ሆይ፣ እርሱ ባያድነን፣ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።” — ዳንኤል 3:​17, 18

ይህን አቋም የወሰዱት ትክክለኛ የሆነውን ለማድረግ ስለፈለጉ ነበር። የሚያስገድላቸው ከሆነም ሞትን ለመቀበል ዝግጁዎች ነበሩ። በልበ ሙሉነት ተስፋ ያደርጉት በትንሣኤ ነበር። አምላክ ደግሞ በዚያ ወቅት ከሞት ካዳናቸው ደስ ይላቸዋል። ጽኑ አቋማቸው ግን ሁኔታዎች የማይለውጡት ነበር። የሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ሁኔታ እንደዚሁ መሆን ይገባዋል።

በዘመናችን ለመወላወል ፈቃደኞች ያልሆኑ አንዳንዶች ታስረዋል፣ ሥቃይ ደርሶባቸዋል፣ እንዲያውም ተገድለዋል። ሌሎች ደግሞ ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሠውተው ሀብታም ከመሆን ይልቅ ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት አድርገው በድህነት ለመኖር መርጠዋል። በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰችው ክርስቲያን ሴት ምን አጋጠማት? ምንም እንኳ ሐኪሙ የተሳሳተ አስተሳሰብ ቢኖረውም ደግነት ስላሳያት አደነቀችው፣ በእምነቷ ግን አልወላወለችም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ ሕግ ያላት አክብሮት የቀዶ ሕክምናውን አልቀበልም እንድትል አስችሏታል። ያም ሆነ ይህ ደስ የሚያሰኘው ተሽሏት ይሖዋን ማገልገሏን መቀጠሏ ነው። ይሁን እንጂ ያን ጥብቅ አቋም በወሰደችበት ወቅት ወደፊት ምን ሊያጋጥማት እንደሚችል አላወቀችም፤ ሁኔታውን ግን በጠቅላላ በይሖዋ እጅ ላይ ተወችው።

እንደዚህ ያለ ተጽእኖ ሲደርስባት ጸንታ እንድትቆም የረዳት ምንድን ነው? በራሷ ኃይል ለመቋቋም አልሞከረችም፣ የአምላክ አገልጋይ የሆነ ማንኛውም ሰውም እንዲሁ በራሱ ብርታት መመካት አይገባውም። “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው” የሚለውን አስታውስ። (መዝሙር 46:​1) ኃጢአት ሠርተን ምሕረት ለማግኘት ወደ እርሱ ዘወር ከማለት ይልቅ መከራ በሚደርስብን ጊዜ እንዲረዳን አምላክን ለምን አንለምንም!

አዎን፣ የአምላክን ምሕረት ፈጽመን አቅልለን አንመልከት። ከዚህ ይልቅ አስቸጋሪ ሁኔታም ቢገጥመን ትክክለኛ የሆነውን ለማድረግ እውነተኛ ፍላጎት ይኑረን። ይህም ከይሖዋ ጋር የገባነውን ዝምድና ያጠነክርልናል፣ ለዘላለም ሕይወት የሚያስፈልገንን ማሠልጠኛ ይሰጠናል፣ እንዲሁም ለአምላክ ምሕረት ተገቢ አክብሮት እንዳለን እናሳያለን። እንደዚህ የመሰለው ጥበብ የሞላበት አኗኗር ለሰማያዊ አባታችን የልብ ደስታ ያመጣለታል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትንሣኤ ላይ የነበራቸው እምነት ሦስቱን ዕብራውያን ንጹሕ አቋማቸውን እንዲጠብቁ ረድቷቸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ