በስፔይን ከመንደር ወደ መንደር እየሄዱ መስበክ
ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ በየከተማውና በየመንደሩ እያስተማረ ያልፍ ነበር።’ (ሉቃስ 13:22) አገልግሎቱን ለማከናወን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ‘በየከተማው’ ብቻ ሳይሆን ‘በየመንደሩ’ ጭምር ሰብከዋል። በከተማዎች ላይ ብቻ ማተኮር ቀላል ሊሆን ቢችልም በገጠር ውስጥ ያሉትን ብዙ መንደሮች ችላ ብለው አላለፏቸውም።a
በስፔይን የሚገኙት የይሖዋ ምስክሮች ኢየሱስን አጋጥሞት የነበረው ዓይነት አስቸጋሪ ሥራ ገጥሟቸዋል። እስከ 1970 መጨረሻ አካባቢ ለመከር የተዘጋጀ በጣም ሰፊ የሆነ ያልተነካ የአገልግሎት ክልል በገጠር ውስጥ ነበራቸው። (ማቴዎስ 9:37, 38) ዝናባማ በሆኑት የሰሜን ተራሮች ላይ የሚገኙት መንደሮች፣ ሞቃታማ በሆነው ማእከላዊ ሜዳማ ቦታዎችና በባሕሩ ጠረፍ ዙሪያ የሚገኙት ሰዎች የመንግሥቱ መልእክት አልደረሳቸውም ነበር።
በስፔይን የሚገኙት የይሖዋ ምስክሮች ምሥራቹን ወደ እነዚህ አካባቢዎች ለማድረስ ትልቅ ጥረት ለማድረግ ቆርጠው ነበር። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩት ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ይህን ያህል ረጅም ጊዜ መጠበቅ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? እንዴትስ ያለ ምላሽ ሰጡ?
ሕጋዊ እውቅና መገኘቱ በገጠር የሚሰጠውን ምስክርነት አፋጠነው
የእርስ በርስ ጦርነቱ ካበቃበት ከ1939 ጀምሮ በስፔይን የይሖዋ ምስክሮች ሥራ እንደታገደ ቆይቶ ነበር። በ1950ዎቹና በ19 60ዎቹ ዓመታት ቀናተኛ ምስክሮች ሥራቸው ብዙም ትኩረት በማይስብባቸው ከተማዎች በጥንቃቄ ሲሰብኩ ቆይተው ነበር። በመጨረሻ ሥራቸው በ1970 ሕጋዊ እውቅና ሲያገኝ በስፔይን ውስጥ ወደ 10,000 የሚጠጉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ። ሁሉም በትልልቅና በትንንሽ ከተማዎች ውስጥ ይኖሩ ነበር። ነገር ግን የስፔይን ገጠሮች የመንግሥቱን መልእክት መስማት አስፈለጋቸው። ታዲያ ይህን አስቸጋሪ ሥራ ማን ይቀበለው ይሆን?
በ1970ዎቹ ዓመታት የልሳነ ምድሩን አካባቢዎች በጠቅላላ በምሥራቹ ለማዳረስ ልዩ ዘመቻ ተጀመረ። ከ1973 እስከ 1979 ድረስ በየወሩ የመንግሥት አገልግሎታችን በሚባለው የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎች ወርኃዊ የአገልግሎት ጽሑፍ ላይ አገልጋይ ስለሚያስፈልጋቸው የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ልዩ ማስታወቂያዎች ይወጡ ነበር። ፈቃደኛ የሆኑና አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ ብዙ ቤተሰቦች ጥሪውን ተቀብለው የምሥራቹ አገልጋይ ይበልጥ ወዳስፈለገባቸው ቦታዎች ሄደው ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃዳቸው አቀረቡ።
ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆኑን ሮሴንዶና ሚስቱ ሉሲ ናቸው። ልዩ አቅኚዎች (የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች) ሆነው በሰሜናዊው ምዕራብ በሚገኘው የዓሣ አጥማጆች መንደር ተመድበው በመሥራት ላይ እንዳሉ ልጅ ወለዱ። በአካባቢው ኑሮአቸውን ለመመሥረትና እዚያው ለመቆየት ወሰኑ። “በጣም አስቸጋሪ ወቅት እንዳሳለፍን ማመን አለብኝ” በማለት ሮሴንዶ ምንም ሳይሸሽግ ተናግሯል። “ዓለማዊ ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር። ነገር ግን በይሖዋ እርዳታ ስለተማመንን አንድም ቀን የምንበላው አጥተን ወይም ሜዳ ላይ አድረን አናውቅም። ብዙ የተጠቀምንበት ወቅት ነበር።” ባለፉት ዓመታት በዚህ የስፔይን ግዛት ውስጥ አራት ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ ረድተዋል።
‘የሚገባው ማን መሆኑን ፈልጋችሁ አግኙ’
ኢየሱስ በእያንዳንዱ ከተማ ወይም መንደር ውስጥ የሚገባው ማን እንደሆነ ‘ፈልገው እንዲያገኙ’ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:11) በስፔይን ገጠሮች ፍለጋው ትጋትና በራስ አነሣሽነት መገፋፋትን ይጠይቅ እንደነበረ በአልኮይ ከሚኖረው ወንድም አንክል ለመረዳት ይቻላል። ማሴያስ በተባለው መንደር ያሉትን ጥቂት ቤቶች አንኳኩቶ ሲጨርስ ዶሮ ሲጮኽ ሰማ። “ዶሮ ካለ፣ በዚህ አካባቢ ሳናንኳኳ ያለፍነው ቤት መኖር አለበት ማለት ነው” ብሎ አሰበ። አካባቢውን ከመረመረ በኋላ አንክል ወደ ጋራው ጥግ የሚወስድ የእግር መንገድ ምልክት አየና ያንን ተከትሎ ሲሄድ ለብቻው የተገለለ አንድ ቤት አገኘ።
የእርሻ ቦታ ጥግ ላይ በተሠራ በዚህ ቤት ውስጥ የሚኖሩት ኮሳ እና ዶሎራስ የተባሉ ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው በሥጋ ወንድምና እኅት የሆኑ ናቸው። መልእክቱን በጥሞና አዳመጡና የቀረበላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዝግጅት ተቀበሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ትሑት ግለሰቦች ጋር ማጥናቱ ቀላል አልነበረም፤ ምክንያቱም ማንበብና መጻፍ አይችሉም፤ እንዲሁም በስፓንኛ ቋንቋ የሚነገራቸው ሁሉም ነገር ወደ ቫለንቺያ መተርጎም ነበረበት። የሚያውቁት ይኽንን ቋንቋ ብቻ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከጎረቤቶቻቸው ከባድ ተቃውሞ ደረሰባቸው። እነዚህ ሁሉ እንቅፋቶች እያሉባቸውና ጉባኤ ለመሰብሰብም ተራሮች አቋርጠው ረጅም መንገድ መጓዝ ቢኖርባቸውም ኮሳ እና ዶሎራስ እውነትን በሥራ ላይ በማዋል እድገት አሳዩ። ከጊዜ በኋላም ተጠመቁና ሁለቱም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጠሉ።
ቀደም ብለን የጠቀስናቸው ሮሴንዶና ሉሲ በሰሜን ምዕራብ ስፔይን በምትገኘው ሞአንያ ከተማ አጠገብ በሚገኝ ገለልተኛ ቤት ውስጥ ትኖር የነበረች ሽባ የሆነች ግለሰብ እንዴት እውነትን እንደተቀበለች ትዝ ይላቸዋል። ስሟ ማሪያ ይባላል። በመጀመሪያ ከምስክሮቹ ጋር በተነጋገረችበት ወቅት ማንበብና መጻፍ አትችልም ነበር። ፖሊዮ በተባለ የሽባነት በሽታ ምክንያት ከልጅነቷ ጀምራ ለብዙ ዓመታት የአልጋ ቁራኛ የሆነች ናት። ቤቷ በቅርቧ ካለ መንገድ ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ውስጥ ገባ ይላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት በጣም ትጓጓ ነበርና ይሖዋን ለማገልገል ያላት ፍላጎት በግልጽ ይታይ ነበር። ማሪያ ማንበብና መጻፍ ተማረችና ጉባኤው ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ምክንያት በስብሰባዎች መገኘት ጀመረች። ወንድሞች ከቤቷ 200 ሜትር ያህል ታቅፈው ኮረኮንቹን መንገድ ያወጧትና ቀስ ብለው መኪና ውስጥ ያስገቧታል። መጀመሪያ አካባቢ ከቤተሰቧ ተቃውሞ ቢገጥማትም ለመጠመቅ እስክትበቃ ድረስ በእውነት ማደጓን ቀጠለች። መንፈሳዊ እድገቷ ካሳደረባት ልበ ሙሉነት የተነሣ በአሁኑ ጊዜ ለእሷ ሁኔታ የሚስማማ ልዩ ተሽከርካሪ ለመንዳትና መሠረታዊ የሆነ ትምህርት የሚሰጥ አንድ ኮርስ ለመጨረስ ችላለች። “እንደ ማሪያ ያሉ ሰዎችን ለመርዳት መቻል የሚከፈለውን ማንኛውም መሥዋዕትነት የተከበረ ያደርገዋል” በማለት ሮሴንዶ ያስረዳል።
የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ወዲያውኑ አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ
በ1970ዎቹ በስፔይን ውስጥ ሕዝቡ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት እንዲችል ተፈቀደለት። ብዙ የስፔይን ነዋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ገዝተው ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብ ጀመሩ። በማቴና ቴል ካምፖ (ቫላዶሊድ) የምትኖረው ፔላር የይሖዋ ምስክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በ1973 ወደ ከተማዋ ሲመጡ እርሷ ቀደም ብላ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀምራ ነበር። ካቶሊክ ስለሆነች ከምስክሮቹ ጽሑፍ ለመቀበል ባትፈልግም መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ግን ፍላጎት ነበራት። ከዚህም የተነሣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቿን ሊመልስላት የሚችል ውይይት በሳምንት አንድ ጊዜ ለማድረግ ተስማማች።
በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚታተሙትን ጽሑፎች በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም ፔላርን ታነጋግራት የነበረችው አቅኚ ለብዙዎቹ ጥያቄዎቿ መልስ ልትሰጣት ችላለች። በተማረችው ነገር ልቧ ስለተነካ ፔላር ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። እውነት የተባለውን መጽሐፍ አጥንታ ከመጨረስዋ በፊት ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብባ ጨረሰች፤ እንዲሁም እውነትን እንዳገኘች እርግጠኛ ሆነች። በአሁኑ ጊዜ ግሩም የመንግሥት አዳራሽና 63 አስፋፊዎች ላሉበት በማቴና ቴል ካምፖ ውስጥ ለሚገኘው ጉባኤ የመጀመሪያዋ ምስክር ሆነች።
በስፔይን የሚገኙ ምስክሮች “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ” እና የአምላክን ፈቃድ ለመረዳት በመጣር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎች እያገኙ ነው። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) በሱማያ አካባቢ (ሰሜናዊ ስፔይን) የቀድሞዋ ካቶሊክና ሃይማኖታዊ ትምህርትን በጥያቄና መልስ ታስተምር የነበረችው ፔፒ የደብሩን ቄስ ያገኘችው በአቅራቢያዋ ባለው መንደር ስታገለግል ነበር።
ቄሱ “ፔፒ፣ ጊዜሽን የምታባክኚው በከንቱ ነው። በዚህ እዚያር በተባለው መንደር ውስጥ መንፈሳዊ ዝንባሌ ያላቸው ባልና ሚስት የሆኑ ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት እንዲሁ ልማድ ስለሆነባቸው ብቻ ነው” በማለት ነገራት።
“ጥሩ ነው፤ መንፈሳዊ ዝንባሌ ያላቸው ሁለት ሰዎች ብቻ ካሉ ወደፊት የይሖዋ ምስክሮች ይሆናሉ” በማለት ፔፒ መለሰችለት።
ፔፒ ከሌሎች ምስክሮች ጋር ሆና መንደሩን በሙሉ አዳርሰው እስኪጨርሱ ድረስ ከቤት ወደ ቤት እየሄደች የምታደርገውን የስብከት ሥራዋን ቀጠለች። ገለልተኛ በሆነ አንድ ቤት ውስጥ ቄሱ የጠቀሳቸውን ባልና ሚስት በዚያ የሚያገለግሉ ወንድሞች አገኟቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ያነቡ ነበር፤ ግን አልገባቸውም ነበር። የቀረበላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በጉጉት ተቀበሉ፤ ፈጣን እድገት አደረጉና ሚያዝያ 1991 ተጠመቁ።
አንዳንድ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን ሊያውቁ የቻሉት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተሙትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በግላቸው በማንበባቸው ነው። ለምሳሌ በአልማደን (ሱዳድ ሪል) የሚገኙ ወንድሞች ሴሩዌላስ (ባዳጆዝ) በተባለች ትንሽ ከተማ ሲሰብኩ መልእክታቸውን በአንክሮ ያዳመጠች አንዲት ሴት አገኙ። በግልጽ ይነበብ ከነበረው ፍላጎቷ በመነሣት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድትጀምር ጠየቋት። እርሷ ግን አንድ በዕድሜ ሸምገል ያለ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እየሰጣት መሆኑን በመናገር አልፈልግም አለች። በዚያ አካባቢ የሚገኙ ሦስትና አራት ሰዎችም ተመሳሳይ ነገር ተናገሩ። ወንድሞች ስለ ሁኔታው ለማወቅ ጓጉና ሸምገል ያለው ሰው የት እንዳለ ጠየቋቸው። የሚኖርበትን አድራሻ አገኙና ሊጠይቁት ሄዱ።
በጣም ያስገረማቸው ይህ ፋሌፓ የተባለ ሰው ማድሪድ እያለ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ አግኝቶ ነበር። ከዳር እስከ ዳር ካነበበው በኋላ ምሥራቹን ለጎረቤቶቹ የማካፈል ኃላፊነት እንዳለበት ተረዳ። ስለዚህ በመጽሐፉ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይሰጣቸው ጀመር። ወንድሞች ከእርሱ ጋር ለማጥናት ዝግጅት አደረጉ። ከእርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ስታጠና የነበረችው ሴትም እንዲሁ ለማጥናት ተስማማች። ፋሌፓ ዕድሜው 80 ዓመት የሆነውና ጥሩ ጤንነት የሌለው ቢሆንም በእውነት ውስጥ ጥሩ እድገት እያሳየ ነው።
መሠረተቢስ ጥላቻን ማሸነፍ
የገጠር ክልሎች የራሳቸው የሆኑ አንዳንድ ችግሮች አሉባቸው። እንደዚህ ባሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ወጎችና አጉል እምነቶች ጠፍረው የያዟቸው በመሆናቸው በገጠር የሚኖሩ ብዙ ሰዎች “አዲስ ሃይማኖት” ስለመያዝ ኃይለኛ ጥርጣሬ አለባቸው። አንዳንድ የመንደሩ ነዋሪዎች ሃይማኖታቸውን የቀየሩ እንደሆነ ጎረቤቶቻቸው ወይም ዘመዶቻችው ምን እንደሚሏቸው በጣም ያስባሉ። ይህ ሁኔታ በስፔይን ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ካንጋስ ዲ ሞራሶ በተባለች የዓሣ አጥማጆች መንደር ላይ ደርሷል።
የዚህ መንደር ተወላጅ የሆነ ሮቤርቶ የተባለ ሰው እንደፈለገው ለመሆን ስላሰበ በ14 ዓመቱ መርከበኛ ሆነ። የመርከበኞቹ ቅጥር ክፍል ኃላፊ ሆኖ መሥራቱ በባሕር ላይ የሚያሳልፏቸውን የብቸኝነት ሰዓቶች ብዙ በመጠጣትና ዕፅ በመውሰድ ከሚያሳልፉ ሌሎች ወጣቶች ጋር እንዲወዳጅ አደረገው። ብዙም ሳይቆይ ሮቤርቶም ኃይለኛ ጠጪና የዕፅ ሱሰኛ ሆነ።
ከጊዜ በኋላ ሮቤርቶ ወደቤቱ ቢመለስም መጥፎ ልማዶቹን ለመተው ችሎታውም ፍላጎቱም የሌለው ሰው ሆነ። የዕፅ ሱሱን ለማርካት ሲል ሌባ ሆነና በተለያዩ ጊዜያት ስድስት ጊዜ ታሰረ። 18 ዓመት ሲሆነው ሊገድለው የሚችል የወይንና የአደንዛዥ መድኃኒት ድብልቅ ጠጣ። ሐኪሞች ሕይወቱን ቢያተርፉለትም እጅና እግሩ የማይሠራ ሆነ። እጅ እግሩ ሽባ ሆኖም ከሆስፒታል ወጣ። በተሽከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀስ ቢሆንም ከዕፅ ልማዱ ሊላቀቅ አልቻለም ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ የይሖዋ ምስክሮች እስካነጋገሩት ድረስ ስለ ሃይማኖት ግድ የሌለውና ሕይወትን ጣዕም ያለው የሚያደርገው ዕፅ መውሰድ ነው የሚል አስተሳሰብ ነበረው።
ፍጻሜያቸውን ስላገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መማሩ ሮቤርቶ የነበረውን ጥርጣሬ እንዲያሸንፍ ረዳው። በመንግሥት አዳራሹ ያጋጠመው ሞቅ ያለ አቀባበል እውነተኛ ሃይማኖት የአባላቱን ሕይወት ትርጉም ያለው ያደርገዋል የሚል እምነት አሳደረበት። በዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ ሮቤርቶ የዕፅ ሱሱን አሸንፎ ተጠመቀ። ካለበት የአካል ችግር ጋር ላለፉት ስምንት ዓመታት አቅኚ ሆኖ አገልግሏል። ከሁለት ዓመት ወዲህ ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። ፍራንቼስኮ የተባለ ከቀድሞ ጓደኞቹ አንዱ ሮቤርቶ በሕይወቱ ውስጥ ባደረገው ለውጥ በጣም በመነካት እሱም ምስክር ሆነና አሁን የጉባኤ ዲያቆን ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ሊፋቅ የማይችል በሚመስለው የዕፅ ሱስ ተይዞ የነበረው ሰው ያደረገው ለውጥ በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች የይሖዋ ምስክሮች ሥራ በተሻለ መንገድ እንዲገባቸው ረድቷል። አንዲት ሴትም የዕፅ ሱሰኛ የሆነውን ልጅዋን ምስክሮቹ ይፈውሱላት እንደሆነ ለማየት ወደ መንግሥት አዳራሽ ይዛው መጥታ ነበር።
እውነቱን ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ
አብዛኛውን ጊዜ በገጠር የሚኖሩ ሰዎች ለእውነት ልዩ አድናቆት አላቸው። ይህ አድናቆታቸው ብዙ ጊዜ የዓለምን ጠቢባን የሚያሳፍር ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:26, 27) አደሊና የተባለች በመካከለኛ የዕድሜ ክልል ላይ የምትገኝ ዓይናፋር ሴት ከእነዚህ አድናቂ ሰዎች መካከል አንዷ ናት። የካቶሊክ እምነቷን አጥብቃ የያዘች ሴት ነበረች። በየዕለቱ ጠዋት ምንም ሳታዛንፍ ተንበርክካ ሦስት አራት ጊዜ እየደጋገመች አባታችን ሆይ እና እመቤቴ ማሪያም ሆይ የተባሉትን ጸሎቶች ትጸልያለች። ቢያንስ አንደኛው እንኳ እንዲሰማላት በሳምንቱ መካከል ባሉት ቀናት ለተለያዩ “ቅዱሳን” ጸሎቷን ታደርሳለች።
አደሊና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስትጀምርም ይህንኑ ሃይማኖታዊ ቅንዓቷን አዲስ ባገኘችው እምነቷ ላይ ተጠቀመችበት። ምንም እንኳ እሷና በሏ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መንግሥት አዳራሹ ሲመጡ ደፍረው ለመግባት አሥር ደቂቃ ያህል ቢፈጅባቸውም ዓይናፋርነቷ ወደ ስብሰባው ከመግባት አላገዳትም። አንዴ ውስጥ ከገቡ በኋላ ግን በአንክሮ ታዳምጥ ነበር። አንድ ጊዜ ስለ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ተማረች። ይህ ርዕሰ ጉዳይ በጣም ስላስደሰታት ቤቷ ስትመለስ ከመጽሐፍ ቅዱሷ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ ለማንበብ ፈለገች። እሷም ሆነ ባሏ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ እንደተጠቀሰ ቢያውቁም ትምህርቱን የት ሊያገኙት እንደሚችሉ አላወቁም ነበር። ስለዚህ አደሊና ማታውኑ የራእይን መጽሐፍ ጀምራ ሊነጋጋ ሲል ምዕራፍ 20 ላይ እስክትደርስ ድረስ ማንበቧን ቀጠለች።
በሌላ ጊዜ ደግሞ አደሊና አንድ ባል ሚስቱን ወክሎ መጸለዩ ተገቢ እንደሆነ ተማረች። ባሏ ለመጸለይ ፈቃደኛ ቢሆንም በጸሎቱ ውስጥ ምን ብሎ እንደሚናገር አላወቀም ነበር። በዚያው ሌሊት አደሊና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ዓይነት መመሪያ ፈልጋ ለማግኘት ወሰነች። ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ሲሆን ባሏን ቀሰቀሰችውና ማቴዎስ ምዕራፍ 6 ላይ ስለ ጸሎት ጉዳይ በዝርዝር የሚናገር ቦታ እንዳገኘች ነገረችው። የኢየሱስን መመሪያዎች ካነበቡ በኋላ ለሁለቱም ባሏ ጸሎት አደረገ። አሁን አደሊና እና ባሏ ሁለቱም የይሖዋ ምስክሮች ናቸው።
መልካም መከር
ቀናተኛ በሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች አማካኝነት ላለፉት 25 ዓመታት ገደማ የገጠር ምስክርነት ከተሰጠ በኋላ ሁሉም የስፔይን ግዛት ምሥራቹን ሰምቷል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረችው ታናሽቱ እስያ ‘የይሖዋ ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ’ ተብሎ ሊነገር ይችላል። (ሥራ 13:49) ከዚህም የተነሣ በሺህ የሚቆጠሩ የገጠር መንደር ነዋሪዎች ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ ሰጥተዋል።
በስፔይንና በሌሎች ቦታዎች በገጠር የአገልግሎት ክልሎች አጣርቶ መስበክ ትዕግሥትና የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ነገር ግን የይሖዋ ፈቃድ ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ’ ስለሆነ የይሖዋ ምስክሮች አድናቆት ያላቸውን ሰዎች ፈልገው ለማግኘት ደስ ብሏቸው ይሠራሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ከላይ የተመለከትናቸው ተሞክሮዎች እንዳሳዩት በስፔይን ውስጥ ከመንደር ወደ መንደር እየሄዱ ለመስበክ የተደረገውን ጥረት ይሖዋ በእጅጉ ባርኮታል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ጆሴፈስ በገሊላ አውራጃ ብቻ 240 “ከተማዎችና መንደሮች” እንደነበሩ አሰላና አካባቢውን “በጣም ብዙ መንደሮች” ያሉበት ነው በማለት ገልጾት ነበር።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ፈረንሳይ
ፖርቱጋል
ስፔይን
ባሌአሪክ ደሴቶች
ካናሪ ደሴቶች
[ምንጭ]
Vilac, Lérida
[ምንጭ]
Puebla de Sanabria, Zamora
[ምንጭ]
Casarabonela, Málaga
[ምንጭ]
Sinués, Huesca
[ምንጭ]
Lekeitio, Vizcaya