ረዓብ በእምነት በሠራችው ሥራ ጻድቅ ሆና ተቆጠረች
አንዲት ዝሙት አዳሪ ሴት በአምላክ ዘንድ ጻድቅ ሆና ስትቆጠር ምን ይባላል? አንዳንዶች “በጭራሽ ሊሆን አይችልም!” ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ በጥንቷ የከነዓናውያን ከተማ በኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ጋለሞታይቱ ረዓብ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟታል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ እንዲህ አለ:- “ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ [ከመንፈስ አዓት] የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።” (ያዕቆብ 2:24–26) ረዓብ ጻድቅ ሆና የተቆጠረችው ለምን ነበር? እንደዚህ የመሰለውን ትልቅ መብት በአምላክ ዘንድ ለማግኘት የበቃችው ምን ስላደረገች ነው?
እስራኤላውያን ደረሱ!
ወደ 1473 ከዘአበ መለስ እንበልና ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችን እንመልከት። ኢያሪኮ በጠንካራ ግንብ የታጠረች ከተማ ነበረች። በከተማይቱ ግንብ አናት ላይ የጋለሞታይቱ ረዓብ ቤት ከፍ ብሎ ይታያል። ከዚህ አመቺ ቦታ ላይ ሆና እስከ አፉ ድረስ የሞላውን የዮርዳኖስን ወንዝ በስተ ምሥራቅ ለማየት ትችላለች። (ኢያሱ 3:15) በዮርዳኖስ ምሥራቃዊ ዳርቻ ላይ 600,000 እግረኛ ጦር የሠፈረበትን የእስራኤላውያንን ሰፈር ተመልክታ ይሆናል። ሠፈራቸው ከኢያሪኮ የሚርቀው በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ብቻ ነው።
ረዓብ እስራኤላውያን በጦርነት ስላገኟቸው ድሎች ሰምታለች። በተጨማሪም ይሖዋ ቀይ ባሕርን ከፍሎ እስራኤላውያንን በማሳለፍ አስደናቂ የሆነውን ኃይሉን እንዴት እንዳሳየ ሰምታለች። ስለዚህ እጅግ ሞልቶ የነበረው የዮርዳኖስ ወንዝ ሊያግዳቸው እንደማይችል ታውቃለች። ረዓብ በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ምን ታደርግ ይሆን?
ረዓብ ቁርጥ አቋም ወሰደች
ብዙም ሳይቆይ ረዓብ ያልጠበቀቻቸውን እንግዶች ማለትም ከእስራኤላውያን ሰፈር የመጡ ሰላዮች ተቀበለች። ማደሪያ ቦታ ይፈልጉ ነበርና በቤቷ ተቀብላ አሳደረቻቸው። ነገር ግን የመምጣታቸው ወሬ ለኢያሪኮ ንጉሥ ደረሰ። ወዲያውኑ እንዲይዙአቸውና በቁጥጥር ሥር እንዲያውሏቸው ሕግ አስፈጻሚ የሆኑ ባለ ሥልጣኖቹን ላከ። — ኢያሱ 2:1, 2
የንጉሡ መልእክተኞች ሲደርሱ ረዓብ አቋሟን ከይሖዋ ጎን አድርጋ ነበር። የንጉሡ መልእክተኞች “ወደ ቤትሽ የገቡትን ሰዎች አውጪ” አሏት። ረዓብ እንዲደርቅ በቤቷ ጣራ ላይ አስጥታው በነበረው የተልባ እግር ክምር ውስጥ ሰላዮቹን ሸሽጋቸው ነበር። እንዲህም አለቻቸው:- “አዎን፣ ሰዎቹ ወደ እኔ መጡ፣ ከወዴት እንደሆኑ ግን አላወቅሁም፤ በሩም [የከተማው በር] ሲዘጋ ሲጨልምም ሰዎቹ ወጡ፤ ወዴት እንደ ሄዱ አላውቅም፤ ፈጥናችሁ አሳድዱአቸው፣ ታገኙአቸውማላችሁ አለች።” (ኢያሱ 2:3–5) የንጉሡ መልእክተኞች በከንቱ ደከሙ እንጂ ፈልገው አላገኙአቸውም።
ረዓብ የእስራኤልን ጠላቶች አታለለች። ወዲያውኑ በይሖዋ ላይ ያላትን እምነት በሥራ ያሳየችበትን ተጨማሪ እርምጃ ወሰደች። ወደ ቤቱ ጣራ ወጥታ ለሰላዮቹ ‘ይሖዋ ምድሪቱን እንደ ሰጣችሁ አወቅሁ’ አለቻቸው። ከ40 ዓመት በፊት አምላክ በእስራኤላውያን ፊት ‘የቀይ ባሕርን እንዳደረቀ’ በመስማታቸው በምድሪቱ የሚኖሩት ሁሉ በፍርሃት እንደተዋጡ ረዓብ በግልጽ ነገረቻቸው። በተጨማሪም ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት እስራኤላውያን እንዴት እንዳጠፏቸው ያውቃሉ። ረዓብም “ይህንም ነገር ሰምተን ልባችን ቀለጠ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና ከእናንተ የተነሣ ከዚያ ወዲያ ለማንም ነፍስ አልቀረለትም” በማለት ተናገረች። — ኢያሱ 2:8–11
ረዓብ ቀጥላ እንዲህ ብላ ተማጸነች:- “አሁንም፣ እባካችሁ፣ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፣ በእውነትም ምልክት ስጡኝ፣ እኔ ለእናንተ ቸርነት እንደ ሠራሁ እናንተ ደግሞ ለአባቴ ቤት ቸርነት እንድትሠሩ፣ አባቴንና እናቴንም፣ ወንድሞቼንና እኅቶቼንም ያላቸውንም ሁሉ እንድታድኑ፣ ሰውነታችንንም ከሞት እንድታድኑ።” — ኢያሱ 2:12, 13
ሰዎቹም በተናገረችው ነገር ተስማሙና ምን ማድረግ እንዳለባት ነገሯት። ከቤቷ መስኮት ማለትም ሰላዮቹን ከኢያሪኮ ግንብ ውጭ ወደ መሬት ባወረደችበት ቦታ ላይ ቀይ ፈትል እንድታንጠለጥል ነገሯት። ቤተሰቦቿን ሁሉ ወደ ቤቷ መሰብሰብ እንዳለባትና ከሚመጣውም ጥፋት እንዲድኑ ከዚያ መውጣት እንደሌለባቸው ነገሯት። ረዓብ ለተለዩአት ሰላዮች አሳዳጆቻቸው እንዳያገኙአቸው ስለ ምድሪቱ አቀማመጥና ቦታ ጠቃሚ መረጃ ሰጠቻቸው። ሰላዮቹም ከአሳዳጆቻቸው አመለጡ። ረዓብ ቀዩን ፈትል ካንጠለጠለችና የቤቷን ሰዎች ሁሉ ከሰበሰበች በኋላ ቀጥሎ የሚከናወኑትን ነገሮች መጠባበቅ ጀመረች። — ኢያሱ 2:14–24
ረዓብ ያደረገችው ትልቅ ነገር ምን ነበር? ሁሉን ማድረግ በሚችለው አምላክ በይሖዋ ላይ እንደምትታመን አሳይታለች። ሕጎቹን ጠብቃ ለመኖር ተስማምታለች። አዎን፣ በዚህ መንገድ በእምነት በሠራችው ሥራ ጻድቅ ሆና ተቆጥራለች።
ግንቦቹ ፈራረሱ
ጥቂት ሳምንታት አለፉ። እስራኤላውያን የጦር ሰዎች ቀንደ መለከት በሚነፉና የተቀደሰውን የቃል ኪዳን ታቦት በተሸከሙ ካህናት ታጅበው ኢያሪኮን መክበብ ጀመሩ። በቀን አንድ ጊዜ እየዞሩ ለስድስት ቀናት ዞሩ። በዚህ በሰባተኛው ቀን ግን ከተማዋን ስድስት ጊዜ ዞረዋል። አሁንም ጉዞአቸውን አላቆሙም።
ሰባተኛው ጉዞ አበቃ፤ ከቀንደ መለከቶቹ ውስጥ የሚወጣው የማያቋርጥ ጩኸት አየሩን ሞላው። እስራኤላውያኑም ወዲያው ታላቅ ጩኸት ጮኹ። በዚያን ጊዜ ይሖዋ ኢያሪኮን ለመከላከል የተገነቡት ግንቦች እንደ ነጎድጓድ በመጮኽ ተንኮታኩተው እንዲወድቁ አደረገ። እንደቆመ የቀረው የረዓብን ቤት ደግፎ ያቆመው ግንብ ክፍል ብቻ ነበር። የቀረው የከተማይቱ ክፍልና ነዋሪዎቿ ተደመሰሱ። ንስሐ የገባችው ጋለሞታ እምነቷ በሥራ ስለተረጋገጠ ከቤተሰቦቿ ጋር ከጥፋቱ ተርፋ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መኖር ጀመረች። — ኢያሱ 6:1–25
የረዓብን ባሕርዮች ጠለቅ ብሎ መመልከት
ረዓብ ሰነፍ ሴት አልነበረችም፤ ምክንያቱም በቤቷ ጣራ ላይ በፀሐይ እንዲደርቅ ያሰጣችው የተልባ እግር ነበር። የተልባ እግር ደግሞ የሐር ፈትል ለመሥራት ያገለግላል። በተጨማሪም በረዓብ ቤት ውስጥ ቀይ ፈትል ተገኝቷል። (ኢያሱ 2:6, 18) ስለዚህ ሐር የምትሠራና ቀለም የማቅለም ችሎታ የነበራት ሴት ሳትሆን አትቀርም። አዎን፣ ረዓብ ታታሪ ሴት ነበረች። ከሁሉም በላይ ይሖዋን በቅድስና የምትፈራ ሴት ነበረች። — ከምሳሌ 31:13, 19, 21, 22, 30 ጋር አወዳድር።
ስለ ሌላው የረዓብ ሥራስ ምን ለማለት ይቻላል? የመኝታ ቤት ብቻ የምታከራይ ሴት አልነበረችም። ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ሥራዋ ሲናገሩ የተጠቀሙበት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃል ዝሙት አዳሪ የሆነችን ሴት የሚያመለክቱ ናቸው። ለምሳሌ ዞህናህ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ሁልጊዜ ከሕግ ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነት ያመለክታል። በከነዓናውያን ዘንድ ዝሙት አዳሪነት እንደ መጥፎ ወይም ወራዳ እንደሆነ ሥራ የሚታይ አልነበረም።
ይሖዋ በጋለሞታ ወይም ዝሙት አዳሪ በሆነች ሴት መጠቀሙ የምሕረቱን ታላቅነት ያሳያል። ውጫዊውን ሁኔታ ብቻ በመመልከት ልንሳሳት እንችላለን። አምላክ ግን “ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) ስለዚህ ንስሐ የገቡ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ጋለሞታዎች የይሖዋ አምላክን ይቅርታ ሊያገኙ ይችላሉ። (ከማቴዎስ 21:23, 31, 32 ጋር አወዳድር።) ረዓብ ራስዋ ከኃጢአትዋ ተመልሳ የጽድቅ መንገድ ስለተከተለች መለኮታዊ ተቀባይነት አግኝታለች።
እስራኤላውያኑ ሰላዮች በአምላክ ሕግ የሚመሩ ሰዎች ስለነበሩ ለማደር ወደ ረዓብ ቤት የገቡት የብልግና ድርጊት ለመፈጸም አልነበረም። ጋለሞታ ቤት ማደራቸው የሰዎችን ጥርጣሬ ሊቀንሰው ይችላል የሚል ግምት ኖሯቸው ሊሆን ይችላል። ቤትዋ በከተማው ግንብ ላይ የሚገኝ መሆኑም በቀላሉ ለማምለጥ ያስችላቸው ነበር። ለእስራኤላውያን የተደረጉትን መለኮታዊ ክንዋኔዎች በመስማቷ ልቧ ወደ ተነካውና ወደ ተለወጠችው ኃጢአተኛ ቤት እንዲያመሩ ያደረጋቸው ይሖዋ እንደሆነ ግልጽ ነው። አምላክ ከነዓናውያንን በብልግናቸው ምክንያት እንዲያጠፉአቸው እስራኤላውያንን ማዘዙና ረዓብን ባርኮ በኢያሪኮ ላይ ድል እንዲገኝ ማድረጉ ሰላዮቹ የብልግና ድርጊት አለመፈጸማቸውን ያረጋግጣሉ። — ዘሌዋውያን 18:24–30
ሰላዮቹን ይከታተሉ የነበሩትን ሰዎች ለማሳሳት ረዓብ የተጠቀመችባቸው የማታለያ ቃላትስ እንዴት ይታያሉ? አምላክ ያደረገችውን ተቀብሎታል። (ከሮሜ 14:4 ጋር አወዳድር።) የአምላክን አገልጋዮች ከሞት ለማዳን የራሷን ሕይወት አደጋ ላይ ጥላለች። ሌሎችን ለመጉዳት ታስቦ የሚነገር ውሸት በይሖዋ ዓይን መጥፎ ቢሆንም ማንም ሰው ለማይመለከታቸው ሰዎች እውነተኛ መረጃዎችን የመንገር ግዴታ የለበትም። ኢየሱስ ክርስቶስም ቢሆን የማያስፈልግ ጉዳት እንዳይደርስበት ዝርዝር ነገሮችን ወይም ቀጥተኛ መልስ ያልተናገረበት ጊዜ አለ። (ማቴዎስ 7:6፤ 15:1–6፤ 21:23–27፤ ዮሐንስ 7:3–10) ረዓብም ጠላት የሆኑትን ባለ ሥልጣኖች ማሳሳቷ በዚሁ ዓይን ሊታይ እንደሚችል ግልጽ ነው።
ረዓብ ያገኘችው ሽልማት
ረዓብ እምነት በማሳየቷ ምን ሽልማት አገኘች? በኢያሪኮ ላይ ከደረሰው ጥፋት መትረፏ ከይሖዋ ያገኘችው በረከት መሆኑ እርግጠኛ ነገር ነው። በኋላም ከይሁዳ ነገድ የሆነውንና የምድረበዳ አለቃ የነበረውን የነአሶንን ልጅ ሳልሞንን (ሳልማን) አገባች። ሳልሞንና ረዓብ አምላካዊ ሰው የነበረውን ቦኤዝን ወለዱና ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዳዊት የሚያደርስ የዘር መስመር አስገኙ። (1 ዜና መዋዕል 2:3–15፤ ሩት 4:20–22) ከዚህ የበለጠ ግምት የሚሰጠው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ በሚናገረው የማቴዎስ ጽሑፍ ላይ በስም ከተጠቀሱት አራት ሴቶች መካከል አንዷ የቀድሞዋ ጋለሞታ ረዓብ መሆኗ ነው። (ማቴዎስ 1:5, 6) ከይሖዋ እንዴት ያለ ታላቅ ብድራት አግኝታለች!
ረዓብ እስራኤላዊ ያልሆነችና ጋለሞታ የነበረች ሴት ብትሆንም አንኳ በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ያላት መሆኗን በሥራዋ ያሳየች እጅግ በጣም ግሩም ምሳሌ የሆነች ሴት ነች። (ዕብራውያን 11:30, 31) የግልሙትናን ኑሮ እንደተዉት እንደ አንዳንዶቹ ሴቶች ትንሣኤ በማግኘት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ሌላ ሽልማት ታገኛለች። (ሉቃስ 23:43) ረዓብ በሥራ በተደገፈው እምነትዋ ምክንያት በአፍቃሪውና በመሐሪው ሰማያዊ አባታችን ዘንድ ተቀባይነት አግኝታለች። (መዝሙር 130:3, 4) የእርስዋ መልካም ምሳሌ የጽድቅ አፍቃሪዎች የሆኑ ሁሉ ይሖዋ አምላክ የዘላለም ሕይወት ይሰጠናል ብለው ተስፋ እንዲያደርጉ ማበረታቻ እንደሚሰጥ የተረጋገጠ ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ረዓብ ጻድቅ ሆና የተቆጠረችው እምነቷን በሥራ ስላስመሰከረች ነው
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የከርሰ ምድር አጥኚዎች የጥንቷን የኢያሪኮ ከተማ ፍርስራሽ ከመጀመሪያ ግንቦቿ ውስጥ ጥቂቱን ክፍል አግኝተዋል
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.