ዓይናችን “ጤናማ” ሆኖ በመንግሥቱ ሥራ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ማድረግ
ላይቤሪያን ወይም በአሜሪካን አገር የሚገኘውን ተነሲ የተባለውን ክፍለ ሀገር የሚያክለው ጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ (ጂ ዲ አር) ወይም ምሥራቅ ጀርመን በመባል ይታወቅ የነበረው አገር ጥቅምት 3, 1990 ምዕራብ ጀርመን ተብሎ ይጠራ ከነበረው አገር ጋር ተቀላቀለ።
የሁለቱ ጀርመኖች መዋሀድ ብዙ ለውጦችን አስከትሏል። ሁለቱን አገሮች አለያይቷቸው የነበረው የግንቡ አጥር ብቻ ሳይሆን የርዕዮተ ዓለም ድንበር ጭምር ነበር። ይህ ለውጥ በዚያ አገር የሚኖሩትን ሰዎች አኗኗር እንዴት ነክቷል? በዚያ አገር የሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች ኑሮ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ አስከትሏል?
ለውህደቱ ምክንያት የሆነውና በ1989 የተጀመረው ቬንደ የተባለ አብዮት ለአርባ ዓመታት የቆየውን የሶሺያሊዝም አገዛዝ ተከትሎ የመጣ ነበር። በእነዚህ አርባ ዓመታት የይሖዋ ምስክሮች ሥራ ታግዶ ነበር። በጣም የተፋፋመ ስደት ይደርስባቸው የነበረበት ጊዜ ነበር።a በምሥራቅ ጀርመን ነፃነት በተገኘ ጊዜ ሕዝቡ በታላቅ የደስታ ስሜት ተዋጠ። አፍላ የነበረው የደስታ ስሜት እየሰከነ ሲሄድ ግን ብዙዎቹ ያሰቡትን ሳያገኙ በመቅረታቸው ተበሳጩ፤ እንዲሁም ግራ ተጋቡ። ሁለቱን ጀርመኖች በማኅበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ለማዋሃድ የተደረገው ጥረት በጣም አዳጋች ሆነ።
በዴር ሽፒጋል መጽሔት ላይ በወጣው ልዩ ሪፖርት መሠረት “162 ታገ ዶቼ ገሽክተ” (የ162 ቀኖች የጀርመን ታሪክ) የተባለ ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው ከውህደቱ በኋላ የሥራ አጥነት፣ የገንዘብ ዋጋ ማጣትና የቤት ኪራይ ዋጋ በጣም እንሚጨምር ተፈርቶ ነበር። በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ ሰዎች “በቂ የጡረታ ገንዘብ እናገኝ ይሆንን?” የሚል ስጋት አድሮባቸዋል። የመኖሪያ ቤቶችስ ሁኔታ? “በምሥራቅ ጀርመን በየትኛውም ሥፍራ የሚገኙ አሮጌ ሕንጻዎች እየበሰበሱ በመውደቅ ላይ ሲሆኑ መንገዶቹም ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።” የአካባቢ መቆሸሽ አሳዛኝ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን የሚገኙት የይሖዋ ምስክሮች እንደዚህ ያለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ነውጥ ሲያጋጥማቸው ሁኔታውን እንዴት ተቋቋሙት?።
ዓይን በተገቢ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ
የይሖዋ ምስክሮች ምንም ዓይነት የርዕዮተ ዓለም ድንበር የላቸውም። በምሥራቅም ይሁን በምዕራብ ያላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አንድ ዓይነት እምነት ነው። ከብዙዎቹ ምስክሮች በአካባቢያቸው የሚኖረው ማኅበረሰብ በሽግግር ሂደት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ዓይናቸው በዋነኛ ግባቸው ማለትም ይሖዋን በማገልገል ላይ እንዲያተኩር በማድረግ መንፈሳዊ ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ችለዋል። ሚዛናቸውን መጠበቅ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነበር?
“የዚች ዓለም መልክ” ተለዋዋጭ ስለሆነ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:31) አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንደተናገረው ከቬንደ በፊት በእገዳ ሥር ሆኖ መስበክ ድፍረትን ይጠይቅ ነበር፤ ምስክሮቹ በይሖዋ እንዲመኩና በመጽሐፍ ቅዱስ በጥሩ ሁኔታ እንዲጠቀሙ አሰልጥኖአቸዋል። አሁን ግን “በፍቅረ ንዋይና ስለ ኑሮ በመጨነቅ እንዳንወሰድ ይበልጥ መጠንቀቅ አስፈልጎናል” ብሏል።
ብዙዉን ጊዜ ነፃነትና እድገት የሚመዘኑት በቁሳዊ ነገሮች ነው። በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከዚህ በፊት ማግኘት ያልቻሏቸውን አንዳንድ ነገሮች ለማድረግና ያልሞከሩአቸውን የተድላ ዓይነቶች ለመሞከር ይሯሯጣሉ። በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍሎች ማለትም በቱርንጊያና በሳክሶኒ ከተማዎችና መንደሮች በሚገኙት ኮረኮንች መንገዶች ላይ በመኪና የሚያልፍ ማንኛውም ሰው ይህን ማስተዋል ይችላል። መንገዶቹ ያረጁና ጥገና የሚያስፈልጋቸው የሰዎቹም ኑሮ ዝቅተኛ ቢሆንም በሳተላይት የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ለመከታተል የሚያስችሉ የሰሀን ቅርጽ አንቴናዎች በብዛት ይታያሉ። ማንም ሰው ዓይኑ ያየውን ሁሉ ካገኘ ደስታና አስተማማኝ ኑሮ ለማግኘት እንደሚችል በማሰብ ሊታለል ይችላል። ይህ ደግሞ እንዴት ያለ አደገኛ ወጥመድ ነው!
ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ለቁሳዊ ነገሮች የማያስፈልግ ትኩረት መስጠትና ስለ ኑሮ መጨነቅ የሚያስከትለውን አደጋ ተናግሯል። “ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ [ሀብት] አትሰብስቡ” በማለት ካስጠነቀቀ በኋላ “የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ [ቀላል አዓት] ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ ብሩኅ ይሆናል” ብሏል። (ማቴዎስ 6:19, 22) ኢየሱስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ቀላል ዓይን በአንድ ነገር ላይ የሚያተኩርና ወደ አእምሮም ቁልጭ ያሉ ምስሎችን የሚያስተላልፍ ነው። በትክክል የሚያይ ወይም ቀላል መንፈሳዊ ዓይን ደግሞ የአምላክን መንግሥት ምስል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን በአምላክ መንግሥት ላይ ትኩረት አድርጎና የኑሮ ጭንቀቶችን ችላ ብሎ ዓይኑ በትክክል እንዲያይ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ቢያደርግ በመንፈሳዊ ሚዛኑን ለመጠበቅ ይችላል።
በቬንደ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፍላጎት ያሳዩ በሳክሶኒ ውስጥ በሰቪካው የሚኖሩ ባልና ሚስት ያጋጠማቸው ሁኔታ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። የግል ሥራቸው ብዙ ጊዜ የሚፈልግባቸው ቢሆንም መንፈሳዊውን ነገር በማስቀደም በሁሉም የክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። “ከሥራችን ጠባይ አንጻር ሲታይ ምንም ጊዜ የለንም። ነገር ግን ለመንፈሳዊ ነገር ጊዜ ማግኘት ያስፈልገናል” በማለት ተናግረዋል። እንዴት ያለ ጥበብ የሞላበት ውሳኔ ነው!
አሁንም በሳክሶኒ ውስጥ በሚገኝ ፕላውን በተባለ ቦታ የሚገኘውን አንድ ቤተሰብ እንመልከት። ባልየው የራሱ ድርጅት ያለው ጎበዝ ሰዓት ሠሪ ነው። ከቬንደ በኋላ የሱቁ ኪራይ በጣም ጨመረ። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? “የቤቱን ኪራይ ለመክፈል ብዙ ገንዘብ የሚያስፈልግ ሆነ። በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ መስጠት የሚገባኝ ለእውነት እንደሆነ ተምሬአለሁ።” ስለዚህ አመቺ ባይሆንም ኪራዩ ዝቅ ወደሚልበት አካባቢ ተዛወረ። አዎን፣ ሰዓት ሠሪው ቀላል ዓይን እንዲኖረው ማድረግ እንደሚኖርበት ተገነዘበ።
አንዳንዶች ግን ይህን ቶሎ ብለው ሳይረዱ ቀርተዋል። አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ አዲስ የመጣው የነፃ ገበያ ሥርዓት ጥሩ ተስፋ ያለው መስሎት የራሱን ንግድ ጀመረ። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ንግዱ የሚያመጣበት የሥራ ግዴታ ለመንፈሳዊ ነገሮች ጊዜ እንዲያጣ ሊያደርገው እንደሚችል አሳስቦት ነበር። ውሎ አድሮ ይኸው ያስጠነቀቀው ሁኔታ ደረሰበት። ከጥቂት ወራት በኋላ ሽምግልናውን በራሱ ጥያቄ ተወ። ቆየት ብሎ እንደጻፈው “ከራሴ ተሞክሮ እንዳየሁት የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ የሚጣጣር ወንድም የራሱን ሥራ ባይጀምር ጥሩ ነው ብዬ እመክራለሁ” ብሏል። ይህ ማለት ግን አንድ ክርስቲያን የራሱን ሥራ ቢሠራ ስሕተት ነው ማለት አይደለም። የራሳችን ሥራ ኖረንም አልኖረን ለኢኮኖሚ ጉዳዮች ከልክ ያለፈ ትኩረት ብንሰጥ ሳንፈልግ የሀብት ባሪያዎች ልንሆን እንችላለን። ኢየሱስ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል” በማለት ውጤቱን ገልጿል። (ማቴዎስ 6:24) ገተ የተባለው ጀርመናዊ ባለቅኔ “በውሸት ነፃ ነን ብለው ከሚያስቡ ሰዎች የበለጠ ተስፋ ቢስ በሆነ መንገድ ባሪያ የሆነ የለም” ብሏል።
ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ከፊታችን ቢመጣ የምንሄድበትን አቅጣጫ አጥርተን ለማየት ስንል ዓይናችንን በከፊል እንጨፍናለን ወይም በእጃችን እንከልላለን። በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ወይም በማኅበራዊ ነውጦች ስንከበብ ደግሞ መንፈሳዊ ግባችንን በትክክል ለማየት እንድንችል በትኩረት መመልከት ያስፈልገናል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በመንግሥቱ ሥራ በትክክል የሚያይ ወይም ቀላል ዓይን እንዲኖራቸው ምን እያደረጉ ነው?
በመንግሥቱ ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ከፍ ማድረግ
በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን የይሖዋ ምስክሮች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በስብከቱ ሥራ የሚያሳልፉትን ጊዜ ጨምረዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በመስክ አገልግሎት ላይ የዋለው የሰዓት መጠን በአማካይ 21 በመቶ ከፍ ብሏል። በዚህም ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር ከፍተኛ እድገት በማሳየት 34 በመቶ ጨምሯል። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ያለው የዘወትር አቅኚዎች ቁጥር ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲወዳደር በአራት እጥፍ ከፍ ብሏል። ሌሎች ሲጨነቁና ሲያጉረመርሙ በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን የሚኖሩት ከ23,000 በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ግን ዓይናቸው ቀላል ወይም በትክክል የሚያይ እንዲሆን በማድረግ ሁኔታውን እየተቋቋሙት ነው። ይህ አቋማቸው በመንግሥቱ እንቅስቃሴ ላይ ለተገኘው አስገራሚ እድገት አስተዋጽኦ አድርጓል። — ከኢያሱ 6:15 ጋር አወዳድር።
እንቅስቃሴው በመስፋፋቱ ምክንያት አብዛኛዎቹ ምስክሮች በሚኖሩበት በደቡባዊው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙት ክልሎች በሚገባ ሊሸፈኑ ችለዋል። ብዙዎቹ የቦታ ስሞች ታሪካዊ ዝና ያላቸው ናቸው። የሸክላ ዕቃዎች የምትወድ ከሆነ በዓለም ላይ ወደር የሌላቸው በጣም የተዋቡ የሸክላ ዕቃዎች ምንጭ የሆነችውን በድረስደን አቅራቢያ የምትገኘውን የማይሰንን ከተማ ሳታውቃት አትቀርም። ማይሰን በአሁኑ ወቅት 130 የመንግሥቱ አስፋፊዎች የሚገኙባት ከተማ ነች። ወይም ደግሞ “የጥንቷ ጀርመን ዋና ከተማ” የነበረችውን ቫይማርን ተመልከት። የገተና የሺለር መታሰቢያ በከተማይቱ እምብርት መገኘቱ ቫይማር ከሁለቱ ደራስያን ጋር ዝምድና ያላት መሆኗን ይመሰክራል። በዚህም ብዙዎቹ እንደሚኮሩ መረዳት ይቻላል። ዛሬ ቫይማር ከ150 የሚበልጡ የምሥራች አስፋፊዎች በማግኘቷ ልትኮራ ትችላለች።
በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ግን ሁኔታው ለየት ያለ ነው። ያሉት አስፋፊዎች በጣም ጥቂት ሲሆኑ ጉባኤዎቹም የተራራቁ ናቸው። በተለይ ሰብአዊ ሥራ ለማግኘት ያስቸግራል። ሥራ ያላቸውም ቢሆኑ ሥራቸውን ላለማጣት ሲሉ ትርፍ ሰዓት ለመሥራት ይገደዳሉ። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆኖ የሚያገለግል አንድ ወንድም “በእገዳው ጊዜ እያንዳንዱ ወንድም በመስክ አገልግሎት ሲሰማራ የይሖዋ ጥበቃ የሚያስፈልገው ቢሆንም ሥራ የማግኘት ችግር ግን አልነበረም። አሁን ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል። ለመስበክ ነፃነት አለን፤ ሥራ ለማግኘት ግን የይሖዋ አመራር አስፈልጎናል። እንደዚህ ያለውን ለውጥ ለመልመድ ጊዜ ይጠይቃል።”
አስፋፊዎች ይበልጥ ለመስበክ በመቻላቸው ተደስተዋልን? ቮልፍጋንግ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “ለአንድ አስፋፊ በአንድ ክልል ውስጥ ደጋግሞ ቢሠራ የተሻለ ይሆናል። ሰዎች ስለሚያምኑት ከእርሱ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ይሆናሉ።” ከዚህም በተጨማሪ የቤት ባለቤቶች “በአጠገባቸው የሚያልፍ ሰው እየሰማቸው እንኳ ቢሆን ስለ ሃይማኖት መነጋገር አያሳፍራቸውም። ሃይማኖት የተከለከለ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ ቀርቷል።” ራልፍና ማርቲና በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። “በክልላችን ውስጥ ቶሎ ቶሎ ደጋግመን መሥራታችንን ወደነዋል። ሰዎችን በግል ለማወቅ አስችሎናል፤ በተጨማሪም በርካታ ዓይነት ያላቸው ጽሑፎች በማግኘታችን በጣም ተደስተናል።”
ለጽሑፎቻችን የታየው አድናቆት
ራልፍና ማርቲና በተለይ ሕይወት እንዴት ተገኘ በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለውን መጽሐፍ በጣም አድንቀውታል። ይህ መጽሐፍ በቀድሞዋ ምሥራቅ ጀርመን አምላክ የለም የሚል እምነት ለነበራቸው ለብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት የሚረዳ በጣም ጥሩ መሣሪያ ሆኗል። በተጨማሪም ከዚህ አጠር ያለ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጽሑፍ ለማግኘትም ይመኙ ነበር። “በ1992 በድረስደን በተደረገው ‘ብርሃን አብሪዎች’ የወረዳ ስብሰባ ላይ አምላክ ስለ እኛ በእርግጥ ያስባልን? የተባለውን ብሮሹር ስናገኝ በጣም ደስ አለን። የጸሎታችን መልስ ነበር።”
የይሖዋ ምስክሮች ያልሆኑ ብዙ ሰዎች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ጽሑፎች ማድነቅ ጀምረዋል። በሐምሌ 1992 የኅብረተሰብ ትምህርት አስተማሪ የሆነች ሴት የምታስተምረውን ነገር ለማዘጋጀት ለረዷት ለእነዚህ ጽሑፎች “ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና” እንዳላት ጽፋለች። በጥር 1992 በሮስቶክ የምትኖር አንዲት ሴት ቤቷን አንኳኩተው ካነጋገሯት እኅቶች በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ተቀበለች። በጀርመን ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ የሚከተለውን ጽፋለች:- “የሉተራን ቤተ ክርስቲያን አባል ነኝ። የይሖዋ ምስክሮች ለሚያደርጉት የሥራ እንቅስቃሴ ትልቅ አድናቆት አለኝ። የይሖዋ ምስክሮች ሰው ያለ አምላክ መመሪያ ሊኖር እንደማይችል አጥብቀው ይናገራሉ።”
የሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያኖች ለአባሎቻቸው ምን ያህል መንፈሳዊ መመሪያ ሰጥተዋል? በጣም የታወቀው ዲ ሳይት የተባለው ጋዜጣ በታኅሣሥ 1991 እትሙ ላይ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን “ለትንሽ ጊዜ ሰላማዊውን አብዮት ያስገኘች እናት ተብላ የተሞገሰች ብትሆንም ተወዳጅነቷን በማጣት ላይ ትገኛለች” ብሏል። እንዲያውም አንድ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ተጠሪ “ሰዎች በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ መኖር በገነት ውስጥ መኖር ይመስላቸው ነበር” በማለት ምሬቱን ገልጿል። በማግደበርግ የሚኖር አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ስለ አንዳንድ ነገሮች ለማወቅ ፈልጎ ደብዳቤ ጻፈ። ለምን ጻፈ? “ባለማመን ለብዙ ዓመታት ሳሾፍ ቆይቼ አሁን ግን ይህ ዓለም መጨረሻ ቀኖቹ ላይ እንዳለና በቅርቡም ታላቅ መከራ እንደሚገጥመን አረጋግጫለሁ” ብሏል። — 2 ጢሞቴዎስ 3:1–5
ለሥራው መስፋፋት ሕንፃዎችን መሥራት
ከቬንደ በፊት በምሥራቅ ጀርመን ውስጥ የመንግሥት አዳራሾችን መሥራት ክልክል ነበር። አሁን ግን በአስቸኳይ ስለሚያስፈልጉ የመንግሥት አዳራሾቹን መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ሆኗል። አስገራሚ ለውጥ የታየበት ሌላው የእውነተኛ አምልኮ ገጽታ ይህ ነበር። ይህ ለውጥ ምን ያህል ፈጣን እንደሆነ የአንድ ወንድም ተሞክሮ ያስረዳል።
በመጋቢት ወር 1990 የይሖዋ ምስክሮች በምሥራቅ ጀርመን ሕጋዊ እውቅና ካገኙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይህ ወንድም በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በድምፅ ማጉያ ተጠቅሞ በወንድሞች ፊት ንግግር እንዲያደርግ ተጋበዘ። ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ የሚሰበሰብበት ጉባኤ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ አስመረቀ። በ1992 ማለቂያ ላይ ለ16 ጉባኤዎች ሰባት የመንግሥት አዳራሾች ተሠርተዋል። ከ30 በላይ የሚሆኑ የመንግሥት አዳራሾችና አንድ ውብ የክልል ስብሰባ አዳራሽ ሊሠሩ በእቅድ ላይ ይገኛሉ።
በአምላክ መንግሥት ላይ ያተኮሩ ዓይኖች
አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “ቬንደ እንደመጣ ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት አይቀበሉም ነበር። የተሻለ ሁኔታ ሊያመጣላቸው ቃል የገባላቸውን አዲስ መንግሥት ተስፋ አድርገው ነበር” ብሏል። ታዲያ እንዳሰቡት ሆነላቸውን? “በሁለት ዓመት ውስጥ አሳባቸውን ለወጡ። ብዙ ሰዎች ከእኛ ጋር በመስማማት ሰብአዊ መንግሥታት ሰላምና ጽድቅ እንደማያመጡ ይናገራሉ።”
በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በምሥራቅ ጀርመን የነበረው ግትር ሶሺያሊዝም አብቅቶ የደስታና የብልጽግና ዘመን ያመጣልናል ብለው ያሰቡት የምዕራቡ ዓለም ርዕዮተ ዓለም በመተካቱ በጣም ተደስተው ነበር። ዳሩ ግን ተስፋ ያደረጉትን ነገር አላገኙም። የይሖዋ ምስክሮች በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምንም ዓይነት ቢሆን ዓይናቸውን ቀላል በማድረግ በሰማይ ላይ እንደሚያበራ ኮከብ የሆነውን የአምላክ መንግሥት በትኩረት ይመለከታሉ። እንደዚህ ያለው ተስፋ ሳይፈጸም ቀርቶ ኀዘንን አያስከትልም። — ሮሜ 5:5
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በሚያዝያ 15, በግንቦት 1 እና በግንቦት 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጣውን “በዕገዳ ሥር በነበርንባቸው ዓመታት ይሖዋ እንክብካቤ አድርጎልናል” የሚለውን በሦስት ተከታታይ ክፍሎች የቀረበውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጀርመን የሚገኙ ምስክሮች ያገኙትን ነፃነት በመንግሥቱ ሥራ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመጨመር እየተጠቀሙበት ነው