የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 1/15 ገጽ 24-30
  • አስደሳች ስብሰባዎች መለኮታዊ ትምህርት አስፋፉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አስደሳች ስብሰባዎች መለኮታዊ ትምህርት አስፋፉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጀመሪያው ቀን ከሰዓት በኋላ
  • ሁለተኛው ቀን ጠዋት
  • ሁለተኛው ከሰዓት በኋላ
  • የሦስተኛው ቀን ጠዋት
  • በሦስተኛው ቀን ከሰዓት በኋላ
  • አራተኛው ጠዋት
  • የመጨረሻው ከሰዓት በኋላ
  • የአምላክ ቃል አስተማሪዎች ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ማበረታቻ አግኝተዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • “ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች” ያደረጉት አስደሳች ስብሰባ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
  • ለሰው ሳይሆን ለአምላክ ክብር ስጡ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
  • የአምላክ ቃል አድራጊዎች ደስታ ያገኛሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 1/15 ገጽ 24-30

አስደሳች ስብሰባዎች መለኮታዊ ትምህርት አስፋፉ

ዛሬ ዓለም በዕውቀት ተጥለቅልቃለች። በቴሌቪዥ ን፣ በሬዲዮ፣ በመጽሐፍ ወይም በኮምፒዩተሮች አማካኝነት በማንኛውም ጉዳይ ላይ መጠን የለሽ ዕውቀት ይገኛል ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሰዎች ይታመማሉ፤ እንዲሁም ይሞታሉ። ወንጀል፣ ረሃብና ድህነት በመላው ዓለም ይገኛል። የስሜት መቃወስ ደግሞ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብዙ ሰዎችን እያጠቃ ነው። ይህ ሁሉ ዕውቀት እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል አልቻለም። ለምን? የሰው ልጅ በአምላክ ጥበብ ላይ ጀርባውን ስላዞረ ነው።

እንግዲያው ለዘንድሮው የይሖዋ ምስክሮች የወረዳ ስብሰባ “መለኰታዊ ትምህርት” የሚል መልእክት መመረጡ እንዴት ተስማሚ ነው! ፕሮግራሙ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሁሉ እውነተኛና ሕይወት አድን ጥቅም ያለው ትምህርት የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ብቻ መሆኑን እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል።

የመጀመሪያው የወረዳ ስብሰባ የተጀመረው ሐሙስ ሰኔ 3 ቀን በዩንየንዴል፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነበር። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ፕሮግራሙ በተለያዩ አገሮች በሚገኙ ከተሞች ሲደረግ የቆየ ሲሆን በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ አህጉሮች በሚደረጉት ስብሰባዎች ያበቃል።

የመጀመሪያው ቀን ከሰዓት በኋላ

እያንዳንዱ ቀን በአንድ የመለኰታዊው ትምህርት ዘርፍ ላይ የሚያተኩር የየራሱ መልእክት ነበረው። ለምሳሌ የመጀመሪያው ቀን ፕሮግራም “ከአምላክ የመጣውን ትምህርት ማወቅ” በሚል መልእክት ላይ የተመሠረተ ነበር። (ዮሐንስ 7:17) የቀኑ ፕሮግራም እየቀጠለ ሲሄድ ይህ ሐሳብ በሚገባ ተብራርቷል።

ከመዝሙርና ከጸሎት በኋላ የስብሰባው ሊቀ መንበር “መለኰታዊው ትምህርት አንድ ላይ ያሰባስበናል” የሚል ርዕስ ባለው ንግግር ፕሮግራሙን ከፈተ። የይሖዋ ሕዝቦች የርሱን መንገድ በመማራቸውና በጎዳናውም በመጓዛቸው እርስ በርስ የተባበሩ መሆናቸውን ገለጸ። (ሚክያስ 4:1–5) መለኰታዊው ትምህርት ኅብረታቸውን ያጠናክረዋል። ተሰብሳቢዎቹ ባገኙት ኅብረትና አንድነት እንዲደሰቱ ተበረታተዋል።—መዝሙር 133:1–3

ከትንሽ ጊዜ በኋላ በዚያው ከሰዓት በኋላ ትንሽ ቆይቶ “ስለ ይሖዋ መንገዶች የሚያስተምሩን ስብሰባዎች” የሚል ርዕስ ባላቸው ተከታታይ ንግግሮች መደበኛዎቹን የጉባኤ ስብሰባዎች የሚመለከት ማብራሪያ ተሰጠ። የመጀመሪያው ተናጋሪ አንድ ላይ በምንሰበሰብበት ጊዜ ይሖዋን እንደምናስከብርና በዚህም ምክንያት በረከቱን እንደምናገኝ ተሰብሳቢዎቹን አስታወሳቸው። የሚቀጥለው ተናጋሪ በስብሰባ ፕሮግራሞች መካፈል አስፈላጊ መሆኑን አጥብቆ ገለጸ። በስብሰባ ፕሮግራሞች ስንካፈል ይሖዋን በሕዝብ ፊት እናወድሰዋለን፣ እምነታችንን እናሳያለን እንዲሁም የሌሎችን እምነት እናጠነክራለን። የተከታታይ ንግግሮቹ ሦስተኛ ተናጋሪ በስብሰባዎች ላይ የተማርናቸውን ነገሮች በሥራ ላይ የማዋልን አስፈላጊነት አመለከተ። ‘ሰሚዎች ብቻ ሳንሆን ቃሉን የምናደርግ’ መሆን አለብን።—ያዕቆብ 1:22

ቀጥሎ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙሮች ስለመዘመር ጥሩ ማብራሪያ ተሰጠ። ከልብ የመነጨ መዝሙር መዘመር የአምልኳችን ዋና ክፍል ነው። ከዚህ ንግግር ቀጥሎ “መለኰታዊ ትምህርት ያሸንፋል” የሚል የስብሰባውን መልእክት የሚገልጽ ንግግር ተደረገ። እንዴት ያለ ግሩም ርዕስ ነበር! “ከይሖዋ የሚመጣልንን ትምህርት የሚወዳደር ከሌላ ምንጭ የሚገኝ ምንም ዓይነት ትምህርት የለም” አለ ተናጋሪው። ከዚያም ስለ ሰው አእምሮ ተዓምራዊነት አጠር ያለ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ እንዲህ አለ፦ “በመጀመሪያ ደረጃ አእምሮአችንን የምንጠቀምበት መለኰታዊ ትምህርት ለመቀበል መሆን ይኖርበታል። እውነተኛ ጥበብ የሚያስገኝልን ይህ መለኰታዊ ትምህርት ብቻ ነው።” እውነተኛ አባባል ነው!

ሁለተኛው ቀን ጠዋት

የስብሰባው ሁለተኛ ቀን መልእክት “አዳኛችን የሆነውን የአምላክን ትምህርት ማስከበራችሁን ቀጥሉ” የሚል ነበር። (ቲቶ 2:10 የ1980 ትርጉም) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት “መለኰታዊ ትምህርትና የአጋንንት ትምህርት” በሚለው ንግግር ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። አዎን፣ አጋንንትም የራሳቸው ትምህርት አላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ተናጋሪው እንዳስረዳው መለኰታዊ ትምህርት የሐሰት ትምህርቶችንና የዲያብሎስን ሽንገላዎች በማጋለጥ የሰይጣንን “ጥበብ” ድል ይነሳል። በዚህም ምክንያት 4,500,000 የሚያክሉ ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች በሰይጣን ጨለማ ውስጥ ካለው ባርነት ነፃ ወጥተዋል።—ዮሐንስ 8:32

ቢሆንም ሰይጣንን መቃወማችንን ማቆም አይገባንም። ይህም “የዓለም መንፈስ እንዳይጋባባችሁ እየተቋቋማችሁት ነውን?” በሚለው ንግግር ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። የዚህ ዓለም መንፈስ ሕይወት ያሳጣል። ወራዳ ሥነ ምግባርን፣ በሥልጣን ላይ ማመፅን፣ ለቁሳዊ ነገሮች መጎምጀትን ያበረታታል። ክርስቲያን የሆነ ሰው ዘወትር ራሱን መመርመር አለበት። ስለሚያያቸው፣ ስለሚሰማቸውና ስለሚያነባቸው ነገሮች የነበረውን ከፍተኛ የአቋም ደረጃ እንደጠበቀ ነውን? ተናጋሪው በሚያበረታታ መንገድ እንዲህ አለ፦ “እናንተ ወንድሞች፣ እህቶችና ወጣቶች በዚህ ረገድ እስካሁን ላደረጋችሁት ብርቱ ጥረት እናመሰግናችኋለን።”—1 ዮሐንስ 2:15–17

የዓለምን መንፈስ መቋቋም አስቸጋሪ እንዲሆንብን የሚያደርግ አንድ ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድን ነው? ሁላችንም ፍጽምና ጎድሎናል። እውነት ነው፤ ኢየሱስ ለኃጢአታችን ቢሞትም የኃጢአት ዝንባሌዎቻችንን ዘወትር መታገል አለብን። ይህ ጉዳይ “ውዳቂው ሥጋችን በኃጢአት መዳፍ ውስጥ እንዳይወድቅ መታገል” በሚለው ንግግር ተብራርቷል። ተናጋሪው ከተናገራቸው ነጥቦች መሃል አዲሱን ሰውነት ብንለብስና ለኃጢአተኛ ዝንባሌዎች እንድንገዛ ከሚያደርገን ከማንኛውም ነገር ብንርቅ ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ትግል አሸናፊዎች ልንሆን እንችላለን የሚል ይገኝበታል።

ቀጥሎ የቀረበው ንግግር ርዕስ “ጤናማውን ትምህርት የሕይወት መንገዳችሁ አድርጉት” የሚል ነበር። አንዳንዶች ስለ ጤንነታቸው ከሚገባው በላይ ይጨነቃሉ። ሆኖም ይበልጥ ሊታሰብበት የሚገባው መንፈሳዊ ጤንነታችን ነው። ተናጋሪው በዚህ ረገድ ያሉብንን ኃላፊነቶች አክብደን መመልከት የሚያስፈልገን መሆኑን አጥብቆ ገለጸ። በተጨማሪም በተለይ ክርስቲያን ሴቶችን የሚያበረታታ አንድ መልእክት ነበረው። “ሚዛናቸውን ጠብቀው በአገልግሎታቸው ቅንዓት የሚያሳዩትንና የግል ኃላፊነቶቻቸውን የሚወጡትን በዕድሜ የገፉም ሆኑ ወጣት እህቶች በጣም እናደንቃቸዋለን።” አዎን፣ ይሖዋ ከዓለም የሚለየንን ጤናማ ትምህርት ስለሰጠን ሁላችንም እናመሰግነዋለን።

የጠዋቱ ፕሮግራም የተደመደመው “መለኰታዊ ትምህርት የሕይወትን ዓላማ ይገልጣል” በሚል ንግግር ነበር። ተናጋሪው እንዲህ አለ፦ “ይዋል ይደር እንጂ ማንኛውም ሰው ‘የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?’ ብሎ መጠየቁ አይቀርም።” ለጥያቄው መልስ ሊሰጠን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መሆኑን ጠንካራ ምክንያቶች ዓላማ እንዲኖረው እንደሚያደርጉልን ገለጸ። ብዙዎቹ አድማጮች ‘በአገልግሎት ክልሌ ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ይህ ዓይነቱ ትምህርት ነው’ ብለው ሳያስቡ አይቀሩም። የአስተዳደር አካሉም በዚህ ይስማማል። በንግግሩ መደምደሚያ ላይ የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? የሚል ርዕስ ያለው አዲስ ብሮሹር እንደወጣ ተገለጸ። በስብሰባው ላይ የተገኘ ሁሉ በጣም ተደስቶ ነበር! የምሳ ሰዓቱ ዕረፍት አዲሱን ጽሑፍ ለማየት የሚያስችል አጋጣሚ አስገኝቷል።

ሁለተኛው ከሰዓት በኋላ

ከሰዓት በኋላ የቀረበው የመጀመሪያ ንግግር “የሚያሳስባችሁን ነገር ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣሉ” የሚል የሚያጽናና መልእክት ነበረው። ጭንቀት የሚያስከትሉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሆኖም የአምላክ ቃል የሚያስጨንቁንን ነገሮች ሁሉ በእርሱ ላይ እንድንጥል ይነግረናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) አንዳንድ ችግሮች ሊወገዱ የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ረገድ ተናጋሪው እንዲህ በማለት አጥብቆ መክሯል፦ ‘ትዕግሥተኞች ሁኑ። ይሖዋን ጠብቁ። መጽሐፍ ቅዱስን መከተል ሁልጊዜ ከሁሉ የተሻለ መንገድ መሆኑን አጥብቃችሁ እመኑ። ልባችንን ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ ካደረግን አእምሮን ሁሉ በሚያልፈው ‘የአምላክ ሰላም’ እንደሰታለን።’—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ቀጥሎ የቀረቡት አራት ንግግሮች መለኰታዊ ትምህርት ለቤተሰብም ሕይወት የሚጠቅም መሆኑን የሚያሳዩ ነበሩ። “ጋብቻን ዘላቂ ኅብረት ማድረግ” የተባለው የመጀመሪያው ንግግር በዓለም ያሉ ብዙ ሰዎች ጋብቻን ሲያረጅ ሊቀየር እንደሚችል ነገር አድርገው ቢመለከቱትም ይሖዋ ግን እንደዚያ ያለ አመለካከት እንደሌለው አስታወሳቸው። ይሁን እንጂ ጋብቻ የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ የይሖዋን መመሪያ መከተል አለብን። የፈጠረን እርሱ ነው። ስለዚህ ለጋብቻ የሚጠቅም ከሁሉ የተሻለ ምክር የምናገኘው በመንፈስ ከተጻፈው ቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው።

“ለቤተሰባችሁ መዳን ጠንክራችሁ ሥሩ” የተባለው ንግግር ደግሞ በዚህ አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ቤተሰብን ማስተዳደር ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ አብራራ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ወላጆች ለልጆቻቸው ስለንጽሕና፣ ስለጥሩ ጠባይ፣ ስለአንዳንድ ሥራዎች አሠራርና ለሌሎች እንዴት ደግና አሳቢ መሆን እንደሚችሉ ያስተምሯቸዋል። ከሁሉ በላይ ግን ልጆቻቸው ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደሩ የአምላክ አገልጋዩች ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድ ሊያስተምሯቸው ይገባል።—ምሳሌ 22:6

ከዚያ ቀጥሎ “ወላጆች ሆይ፣ ልጆቻችሁ ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል” በሚለው ንግግር ተናጋሪው የልጆችን ድክመት አይተው እንዳላዩ ማለፍ ባይገባቸውም ልጆቹን ማመስገን አስፈላጊ እንደሆነ ተሰብሳቢዎቹን አሳሰባቸው። ወላጆች ልጆቻቸው በተለይ የማጭበርበር፣ ቁሳዊ ነገሮችን የማፍቀር ወይም የስግብግብነት ዝንባሌ እንዳለባቸው በንቃት መከታተል ያስፈልጋቸዋል።

በተለይ ወጣት ተሰብሳቢዎች በጥሞና ያዳመጡት “ወጣቶች ሆይ፣ የምትከተሉት የማንን ትምህርት ነው?” የሚለውን ንግግር ነበር። ዛሬ ያሉት ሁኔታዎች ለወጣት ክርስቲያኖች የሚያስቸግሩ ናቸው። ከዓለም ጋር ተስማምቶ መጓዝ ቀላል ነው፤ ግን ወደ ሞት ይመራል። መለኰታዊውን ትምህርት የሙጥኝ ብሎ መኖርን መምረጥ ለአንድ ወጣት ድፍረት የሚጠይቅበት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ታላላቅ በረከቶችን ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያመጣለታል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8

ሁለተኛው ቀን “ፈጣሪያቸውን አሁኑኑ የሚያስታውሱ ወጣቶች” በተሰኘ አስደሳች ድራማ ተደመደመ። የድራማው መሪ በመግቢያው ላይ በአምላክ ድርጅት ውስጥ ያሉትን ወጣቶች ‘ለይሖዋ አምላክና በእርሱ የተሾመ ሰማያዊ ንጉሥ ለሆነው ለክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ የተወሰነ አገልግሎት የሚሰጥ ቲኦክራሲያዊ ሠራዊት’ ሲል ጠርቷቸዋል። አክሎም “በእርግጥም ወጣቶቻችን ጥሩ ነገር እያከናወኑ ናቸው!” አለ። ድራማው ወላጆች ልጃቸውን በደንብ ካሰለጠኑት ልጁ አድጎና ራሱን ችሎ ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችል ጥሩ አቋም እንደሚኖረው በጉልህ አሳይቷል።

የሦስተኛው ቀን ጠዋት

የሦስተኛው ቀን መልእክት “አሕዛብን ሁሉ ማስተማራችሁን ቀጥሉ” የሚል ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) ተሰብሳቢዎቹ ስለስብከቱ ሥራ ወቅታዊ የሆነ ምክር የሚሰጥበት ፕሮግራም ይሆናል ብለው እንደጠበቁ አያጠራጥርም፤ እንደጠበቁትም ሆኗል። “የመስበክና የማስተማር ተልዕኳችንን በደስታ መፈጸም” የሚል ርዕስ ያለው ተከታታይ ንግግር በምስክርነቱ ሥራ ላይ ለመካፈል ያላቸውን ቁርጥ ውሳኔ አጠንክሮላቸዋል። የመክፈቻው ንግግር ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሚደረጉ ጉብኝቶች፣ ሁለተኛው ስለ ተመላልሶ መጠየቆች፣ ሦስተኛው ደግሞ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የሚያብራሩ ነበሩ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሚስዮናውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የወረዳ ስብሰባ እንዲካፈሉ ተጋብዘው ነበር። በአንዳንድ አካባቢዎች ከሚስዮናውያኑ አንዳንዶቹ በዚህ ፕሮግራም ላይ ተሳትፈው ነበር። በተመደቡባቸው ቦታዎች እየተሳካላቸው እንዳለ ማወቅ የሚያስደስት ነበር። ቀጥሎ የቀረበው “የምሥራቹን ለሁሉም ሰው ማዳረስ” የተባለ ንግግር መደበኛ ያልሆነ ምስክርነት ያለውን ኃይል የሚያሳይ ነበር።

የጠዋቱ ፕሮግራም በይሖዋ ምስክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ሁሉ በከፍተኛ ጉጉት በሚጠበቀው የጥምቀት ንግግር ተደመደመ። ራሳቸውን የወሰኑ በጣም ብዙ አዳዲስ ሰዎች በየወረዳ ስብሰባዎቹ በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ቆመው የቀረቡላቸውን ሁለት ጥያቄዎች በእርግጠኛነት አዎን በማለት መለሱ። ከዚያ በኋላ በሕዝብ ፊት ተጠመቁ። መለኰታዊ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኝ ለመሆኑ እንዴት ያለ ጉልህ ማረጋገጫ ነው!

በሦስተኛው ቀን ከሰዓት በኋላ

የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም ጥልቅ በሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማብራሪያዎች ተጀመረ። የይሖዋ ምስክሮች በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ ያሉትን ቃላት በደንብ ያውቋቸዋል። አንዳንዶች ስለነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች ምንም አዲስ ነገር ሊነገር አይችልም ብለው ያስቡ ይሆን? በጣም ተሳስተዋል! ‘የመገኘትህ ምልክት ምን ይሆናል?’ እንዲሁም “ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች መቼ ይሆናሉ?” የሚሉት ንግግሮች ለተሰብሳቢዎቹ በሁለቱ ምዕራፎች ላይ አስደናቂ የሆነ ማብራሪያና በአንዳንዶቹ ቁጥሮች ላይ አዳዲስ መግለጫ ሰጥተዋል። ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ ነጥቦቹን ተረድተዋቸው እንደሆነ ለማረጋገጥ ከያዟቸው ማስታወሻዎች ጋር እያመሳከሩ ሞቅ ያለ ውይይት አደረጉ። ትምህርቱ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ሲወጣ ብዙ ጥያቄዎች እንደሚመለሱ አያጠራጥርም።

“ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቻችሁ የተሰጡ ትምህርት ሰጪ መልሶች” በተባለው ንግግር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚደረገው ጥናት ቀጠለ። ከዚያ በኋላ ፕሮግራሙ ወደሌላ አቅጣጫ አመራ። 1993 የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 50ኛ ዓመቱን ያከበረበት ዓመት ነበር። “ጊልያድ ለሃምሳ ዓመታት ያከናወነው የሚስዮናውያን ሥልጠናና እንቅስቃሴዎቹ” የተባለው ንግግር በዚህ ጊዜ ውስጥ የተከናወነውን ሥራ ለተሰብሳቢዎቹ ገለጸ። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሚስዮናውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር አብረው የወረዳ ስብሰባ እንዲካፈሉ ተጋብዘው ነበር። “በዓለም አቀፉ መስክ በወንጌላዊነቱ ሥራ የተከናወኑት ነገሮች” የሚለው ንግግር በሚቀርብበት ጊዜ ሚስዮናውያን ካሉ አንዳንድ ተሞክሮዎቻቸውን ለአድማጮች እንዲናገሩ ተጋብዘው ነበር። የሚስዮናውያኑን ታሪክ መስማት እንዴት መንፈስን የሚያነቃቃ ነበር!

“የይሖዋ ምስክሮች ነቅተው የሚጠባበቁት ለምንድን ነው?” የሚለው ቀጥሎ የቀረበው ንግግር በታሪክ ላይ የተመሠረተ ነበር። ክርስቲያኖች ከመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ አንስቶ እስካሁን ድረስ ነቅተው እየተጠባበቁ እንዳሉ ገለጸ። ከዚህ ቀጥሎ አስደሳች ነገር ተፈጸመ። ቀጥሎ በተሰጠው “የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በመላዋ ምድር ላይ በትጋት እየሠሩ ናቸው” የሚል ርዕስ ባለው ንግግር መጀመሪያ ላይ ተናጋሪው አንድ ትልቅ መጽሐፍ ከፍ አድርጎ በመያዝ (በቋንቋው ተዘጋጅቶ ከሆነ) እንዲህ አለ፦ “የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምስክሮች የተባለ መጽሐፍ የወጣ መሆኑን ስናሳውቅ በጣም ደስ ይለናል” አለ። መጽሐፉ የይሖዋ ምስክሮችን ዘመናዊ ታሪክ በዝርዝር ይተርካል። ስለጽናታቸው፣ ስለቆራጥነታቸውና ስለሥራቸው መሳካት የሚገልጽ አስደሳች ታሪክ ይዟል። የይሖዋ መንፈስ በአገልጋዮቹ ላይ ምን ያህል እየሠራ እንዳለ ያረጋግጣል።

አራተኛው ጠዋት

የስብሰባው የመጨረሻ ቀን ደረሰ። “ከመለኰታዊ ትምህርት ጥቅም ማግኘት” የሚለው የዕለቱ መልእክት ስብሰባው በጣም ጥሩ አጨራረስ እንደሚኖረው ተስፋ የሚሰጥ ነበር። (ኢሳይያስ 48:17) በጠዋቱ ፕሮግራም የአድማጮችን ትኩረት ስቦ የነበረው ሦስት ኃይለኛ ንግግሮችን የያዘው ተከታታይ ንግግር ነበር። “በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የኤርምያስ የማስጠንቀቂያ መልእክት—ለቀድሞውና ለአሁኑ ዘመን” የሚል ርዕስ ያላቸው ተከታታይ ንግግሮች ኤርምያስ ምዕራፍ 23, 24 እና 25ን ቁጥር በቁጥር የሚያብራሩ ነበሩ። እነዚህ ምዕራፎች የያዙት መልእክት እንዴት ኃይለኛ ነው! እነዚህ ግልጽ የሆኑ መለኰታዊ ማስጠንቀቂያዎች በኤርምያስ ዘመን የነበሩትን እምነት አጉዳይ እስራኤላውያን አስደንግጠዋቸው መሆን አለበት። እነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ፍጻሜያቸውን ባገኙ ጊዜ ደግሞ መላው ዓለም ከዚያ ይበልጥ ደንግጦ ነበር። ዛሬስ ያለው ሁኔታ የተለየ ነውን? በጭራሽ። የይሖዋ ምስክሮች የአምላክን የፍርድ መልእክት በድፍረት እየሰበኩ ናቸው። ይህ የነገሮች ሥርዓት የአምላክን የፍርድ እርምጃዎች ለመጋፈጥ የሚገደድበት ጊዜ ይመጣል። ይህ ደግሞ በሰይጣን ዓለም ላይ ጥፋት ያመጣል።

የእሁድ ጠዋቱ ፕሮግራም “አትሳቱ፣ ወይም በአምላክ ላይ አትዘብቱ” በሚል ሁለተኛ ድራማ ተደመደመ። ድራማው መለኰታዊ ትምህርት ወራዳ ቪድዮዎችና ሙዚቃዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብን እንዲሁም በክርስቲያን ወንድሞቻችን መካከል ጠብ የሚያነሳሳ ዝንባሌ ከመዝራት እንዴት ሊጠብቀን እንደሚችል በግልጽ ያሳያል። በድራማው መጨረሻ ላይ ሊቀመንበሩ አንዱ ገጸ ባሕርይ የተናገረውን አእምሮን የሚያመራምር አነጋገር በመጥቀስ እንዲህ አለ፦ “በዓለም ተጽእኖ መነካታችን እንደማይቀር ግልጽ ነው። ይህን ዓለም ካልተቃወምነው ስውር በሆነ ዘዴው አስተሳሰባችንን ሊያበላሽብን ይችላል። ታማኝ ሆነን መኖራችንና አለመኖራችን . . . በምንዘራው ነገር ላይ የተመካ ነው።” ትክክለኛ አባባል ነው!

የመጨረሻው ከሰዓት በኋላ

የስብሰባው ማለቂያ እየተቃረበ መጣ። ተናጋሪው “አስጨናቂ ለሆነው ዘመናችን የሚጠቅም ትምህርት” የሚል ርዕስ ያለውን የሕዝብ ንግግር ሊሰጥ ወደ መድረኩ ወጣ። ግልጽና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ዛሬ እኛን የሚነኩንን ዋና ዋና ችግሮች ጠቀሰና መለኰታዊ ትምህርት የተሻለ ሕይወት አግኝተን እንድንደሰት ሊረዳን የሚችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጠቆመ። በአሁኑ ጊዜ የቅዱስ ጽሑፎችን ትምህርት በመከተል ላይ ከሆንን በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥም እስከዘላለም ልንከተለው እንደምንችል ተናገረ።

ሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በአጭሩ ከተከለሰ በኋላ የመጨረሻው ንግግር የሚቀርብበት ጊዜ ደረሰ። ተናጋሪው በአራቱ ቀናት ፕሮግራም የቀረቡትን ዋና ዋና ነጥቦች ከከለሰ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ አዳዲሶቹን ጽሑፎች እንዳይዘነጓቸው ነገራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ—የሐቀኛ ታሪኮችና የትንቢቶች መጽሐፍ በሚል ርዕስ በተከታታይ ከሚወጡት የቪድዮ ካሴቶች ሁለተኛው በቅርቡ እንደሚወጣ ተናገረ። እንዲያውም አሁን “መጽሐፍ ቅዱስ—ዘመናዊ የሆነው የሰው ልጅ የጥንት መጽሐፍ” የተባለውን ቪድዮ ካሴት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማግኘት ይቻላል። ከባድ ችግሮች ካሉባቸው እንደ ቦስንያና ሄርዜጎቪና ከመሳሰሉ ቦታዎች የመጡ ስሜት የሚነኩ ሪፖርቶች ተነበቡ። ሲደመድምም ተናጋሪው በመክብብ 12:13 ላይ ያሉትን እንዲህ የሚሉትን ቃላት አነበበ፦ “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ ትእዛዙንም ጠብቅ።”

እንዴት ያለ ጥሩ ማሳሰቢያ ነው! መላው የሰው ዘር ሁሉ ታላቁን አስተማሪያችንን ይሖዋን በሚያወድስበትና የሱን መለኰታዊ ትምህርት ሰምቶ በሚከተልበት ዘመን ለመኖር የምንበቃ እንሁን።

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሞስኮና በኪየቭ የተደረጉት “መለኰታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባዎች ከፍተኛ ደስታ አምጥተዋል

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

1. ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በመጠመቅ አሳይተዋል

2. በስብሰባው ላይ የተገኙ የ100 ዓመት አዛውንት አዲስ ጽሑፍ በማግኘታቸው ተደስተዋል

3, 4. አእምሮን የሚያመራምሩት ድራማዎች በጣም ተደንቀዋል

5. በስብሰባው ላይ ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ሚስዮናውያን የመለኰታዊውን ትምህርት ጥቅሞች አጉልተው ገልጸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ